Tigray| ምላሽ ለፕ/ር መስፍን ወ/ማርያም – በፕ/ር ገብሩ ታረቀና በአማኑኤል መሓሪ

ስለትግራይ ሕዝብ ጆሮ የሚጠልዙ ንግግሮችን በማሰማት የሚታወቁት መስፍን ወ/ማርያም(የቀድሞ የአ.አ.ዩ. ፕሮፌሰር)፤ ባለፈው ነሐሴ በፍትህ ጋዜጣ ላይ ባቀረቡት ጽሁፍ የራሳቸውን ክብረ-ወሰን አሻሽለዋል፡፡

መስፍን በጽሁፋቸው ካሉት መሀከልም፡-mesfin_woldemariam_1

በኤርትራና በትግራይ ይኖሩ የነበሩ የኤርትራና የትግራይ ዜጐች ተግተው ኢጣልያንን ቢወጉ ኖሮ ከሐረር፣ ከሀድያና፣ ከሲዳሞ፣ ከሸዋ… ወደ ሰሜን መዝመት አያስፈልጋቸውም ነበር፤ ይህ ቢሆን ዛሬ ሌሎች ያልሞቱትን ሞት በመሞታቸው አይወቀሱም ነበር፤

አፄ ምኒልክ ጦራቸውን ሰብስበው በእግርና በበቅሎ ከደቡብ ተነስተው ትግራይ እስቲደርሱ ኤርትራና ትግራይ ምን አድርገው ጠበቁዋቸው? የኢጣልያ ጦር ትግራይን ሰንጥቆ አምባ አላጌ እስቲደርስ ማን ሊያቆመምው ሞከረ? የኢጣሊያ ጦር መቀሌ ገብቶ ሲመሽግ ማን ተከላከለው? ስብሓት እስከዛሬ ሳይገለጥለት ቀርቶ ከሆነ የኢጣልያንን ጦር ከአምባ አላጌ ያስወጣው የምኒልክ ጦር ነው፡፡ ከመቀሌም ምሽግ ያስወጣው የጣይቱ ዘዴና የምኒልክ ጦር ነው፡፡ በኢትዮጵያዊ ይሉኝታ ተሸፋፍኖ የቆየውን እናፍረጥርጠው ከተባለ ለማን አሳፋሪ እንደሚሆን ግልጽ ነው፡፡

ስለአድዋው ጦርነት ምስክርነት የሚሰጠን ገለልተኛ ታዛቢ እስክናገኝ ስለማይጨው ጦርነት የነበረ የዓይን ምክስር አንድ በቅርቡ ያነበብሁት መጽሐፍ ትዝ አለኝ፤ አንድ የቼኮዝላቫኪያ ጎበዝ የጻፈውን የሃበሻ ጀብዱ የሚል መጽሐፍ ተጫነ ጆብሬ መኮንን የተባለ ሰው የተረጎመውን አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አሳትሞታል፤ አቶ ስብሓት ብቻ ሳይሆን ማንበብ የሚችል ሁሉ ሊያነብበው የሚገባ መጽሐፍ ነው፤ እኔ ፈረንጅ ስለኢትዮጵያ የፃፈውን ማንበብ ከተውሁ ብዙ ዓመታት ሆኖኛል፡፡ ይህንን ግን በአንድ ቀን ተኩል ጨረስሁት፤ የኢትዮጵያን ዘማቾች ከኋላ እያጠቁ ስለነበሩት “የትግራይ ሽፍቶች” ማን ይናገር? የነበረ፤ ነውና እንዲህ ይላል፡-

“ የትግራይ ሽፍቶች ለምን ወንድሞቻቸውን ይገድላሉ?… ከመሀል አገር ስድስትና ሰባት ወር ሙሉ ፍዳውን እያየ ሲጓዝ ከርሞ እዚህ የደረሰው ወንድማቸው፣ የነዚህን ምስኪኖች ህይወትና ንብረት ከጠላት ለመከላከል የገዛ ህይወቱን አልጋ ላይ ጥሎ፣ ቤት ንብረቱን በትኖ መከራውን ባየ ለምን ይገድሉታል?”

እነዚህ ሽፍቶች ወንድሙን የገደሉበት አብቹ የሚባል የአስራ ስድስት ዓመት የሰላሌ ዘማች በጣም ተናዶ የራሱን የግል ቡድን አቋቁሞ ያሳድዳቸው ነበር፡፡

ይህን ተከትሎ ገብሩ ታረቀ (ፕሮፌሰር ኤመሪተስ) እና አማኑኤል መሓሪ (ፀሀፊ ተውኔትና ገጣሚ) ጠንከር ያሉ ምላሾችን ሰጥተዋቸዋል፡፡ የመስፍን ወ/ማርያም ጽሁፍ በየዌብሳይቱ የሚገኝ ሲሆን፣ ባንጻሩ ምላሾቹ ተደራሽ ባለመሆናቸው በዚህ ብሎግ ላይ ማተሙ ተገቢ ሆኖ ተገኝቷል፡፡

********************

በነገራችን ላይ፡- በHobart and William Smith Colleges ድረ-ገጽ የሰፈረው የገብሩ ታረቀ ግለ-ታሪክ እንደሚከተለው ይነበባል፡-

Gebru Tareke – Emeritus Professor of History (1978)

Ph.D., Syracuse
M.A.,Wisconsin, Madison
B.A., Addis Ababa

*******************************

ለፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም

ገብሩ ታረቀ (ፕሮፌሰር ኤመሪተስ)

ሰላምታየን ላስቀድምና በፍትሕ ጋዜጣ ነሐሴ 6 ቀን 2ዐዐ3 ዓ.ም. “ንግግራችን ትርፋማ እንዲሆን ከአሉባልታ እንውጣ” በሚል ርዕስ ያቀረቡትን ጽሑፍ በአንክሮ አንብቤ (በጊዜው ባይሆንም) አንድ ሁለት ጥያቄዎችን ለመሰንዘር ፈለግኩ፡፡ እንደመቅድም አድርጌ ግን የማይተኛና የማያስተኛ አዕምሮዎትን ብሎም ኃይለኛ ብዕርዎን ከሚያደንቅልዎት የቀድሞ ተማሪዎችዎ አንዱ መሆኔን እንዲያውቁልኝ እፈልጋለሁ፡፡Professor Gebru Tareke

ከአሉባልታ እንውጣና በቁም ነገር አዘል ጉዳዮች ላይ እንወያይ በማለት የቸሩንን አስተምህሮት በአክብሮት ተቀብየዋለሁ፡፡ የፍትሕ አንባቢያንም እንደሚስማሙበት አልጠራጠርም፡፡ ነገር ግን በጽሑፉ ውስጥ አሳሳቢ ስህተቶችና ክፍተቶች መስለው ስለታዩኝ ነጥቦች ባጭሩ ላብራራ ይፈቀድልኝ፡፡

አንደኛ፣ አቶ ስብሐት ነጋ “የውጫሌ ስምምነት ለምን አስፈለገ;” ብሎ ሲጠይቅ የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊ አይመስለኝም፡፡ ሌሎችም ጠይቀውታል፡፡ እውነትም የውጫሌ ውል ለምን አስፈለገ? ለዓድዋው ጦርነት ዋናው መንስዔ ውሉ ያስከተለው ንትርክና ሙግት ነበርን? እነዚህና የመሳሰሉት ጉዳዮች በግልጽነት በጥልቀትና በሚዛናዊነት እስካልተፈተሹ ድረስ በዚች ሀገር ዕርቅና አስተማማኝ ሰላም ይገኛል ብለው ያምናሉ?

ሁለተኛ፣ የዓድዋን ጦርነት በተመለከተ፣ “የኤርትራና የትግራይ ዜጐች ተግተው ኢጣልያንን ቢወጉ ኑሮ”፣ የመሀል ሀገር ወገኖቻቸው ወደ ሰሜን መዝመት ባላስፈለገ ነበር ይሉናል፡፡ አስደማሚ ትችት ነው፡፡ ኤርትራውያን እኮ የኢጣልያ እስረኞች ከሆኑ ዓመታትን ቆጥረዋል፡፡ ራሳቸውን ነፃ ለማውጣት ለምን አጋጣሚውን አልተጠቀሙበትም እንል እንደሆነ እንጂ፣ ለኢትዮጵያ ለምን አልተዋጋችሁም ለማለት የሞራል ሉዓላዊነት የለንም፡፡ ፕሮፌሰር፣ ኢትዮጵያዊነታቸው ከተነጠቁ እኮ ሰንብተው ቆይተዋል! ለኢትዮጵያ “ተግተው” እንዲዋጉ የሚያስገድዳቸው የዜግነት ግዴታ ነበራቸውን;፡፡ ይህንን ለይቶ ለመረዳት ባለመቻል ሳይሆን ይቀራል አፄ ምኒልክ የእነዚያ 4ዐዐ የሚያህሉ ኤርትራውያን እጅና እግር አስቆርጠው የሕይወት ሽባዎች ያደረጉዋቸው; ከኢትዮጵያ ታሪክም የማይፋቅ አሻራ የተውልን; ከታሪካችን ጋር ለመታረቅ፣ ከድላችን ትረካ ጋር ገመናችንም አብሮ መጠናት የለበትም ይላሉ;

ትግራይን በተመለከተ፣ በዚያን ወቅት ክፍለ ሀገሪቱ የነበረችበት አሳዛኝ ሁኔታንና የኃይሎች አሰላለፍን ከግንዛቤ አለማስገባትዎ አስደምሞኛል፡፡ እውን ትግራይ በብቸኝነት የኢጣልያን ኃይል ልትመክት ትችል ነበር ብለው ከልብዎ ያምናሉ? እጠራጠራለሁ፡፡ ደግሞም ኢትዮጵያዊ ዜግነትን በትግራይ ዜግነት መተካትዎ ምን ቢያስቡ ነው? በዚህ አባባልዎ ብዙዎች ዜጐችን ሳያስከፉ እንዳልቀሩ ሳልጠቅስ ለማለፍ አልፈልግም፡፡

ሶስተኛ፣ እኔ ያላነበብኩትን መጽሐፍ አንብበዋል፡፡ በእርስዎ ትጋት ስደነቅ በራሴ ስንፍና አፈርሁ፡፡ የሆነ ሆኖ የቼኮዝላቫኪያው “ጐበዝ” በማይጨው ጦርነት “የትግራይ ሽፍቶች” በሀገር ወገኖቻቸው ስለፈፀሙት ግፍ የጻፈውን አስነብበውናል፡፡ መልካም፡፡ ይህንን መጥቀስዎ በሽፍቶቹ አሳብበው መላውን ትግራይ ለመፈረጅ ነው የሚል እሳቤ የለኝም፡፡ ምናልባት ወንጀለኞቹ ከራያና አዘቦ ሳይሆኑ አይቀርም የሚል ግምት አለኝ፤ ግምቴ ትክክል ከሆነ ስለድርጊቱ እኮ ብዙ ተጽፏል፤ ለምን አዲስ እንደሆነብዎት አስገርሞኛል፡፡ ለመሆኑ አመፁን ለመፈጸም የገፏፏቸው ታሪካዊና ማህበራዊ ምክንያቶች ይኖሩ ይሆን ብለው ራስዎን ጠይቀዋልን? በትክክል ጠቅሰውት ከሆነ “ጐበዙ”፣ ግን አላዋቂው ፈረንጅ ያልጠየቀው? ይህንን ስል ድርጊቱን የደገፍኩ መስሎ እንደማይታይብኝ እተማመናለሁ፡፡ ለመሆኑ ፈረንጅ የጻፈውን ማንበብ ካቆሙ ዓመታት ከሆነዎት፣ ይኸኛውን ለምን መረጡት? ወደዱትስ? ከኢትዮጵያ ታሪክ የሚያነቡት በመረጣ መሆኑን አስገንዝበውኛል፡፡ የሆነ ሆኖ ስለድርጊቱ እኔም በመጠኑ ጽፍያለሁና፣ ለየት ያለ ግንዛቤ ያገኙበታል ከሚል ግምት የመጀመሪያው መጽሐፌን፣ በተለይም አራተኛውን ምዕራፍ እንዲያነቡልኝ በትህትና እጋብዝዎታለሁ፡፡

“እንነጋገር ማለት እውነትን በማስረጃ አስደግፎ ነው” ሲሉ፣ የታሪክ ባለሙያነቴን ነውና ያስታወሱኝ አመሰግንዎታለሁ፡፡ እንደ ሙያተኛነቴ ደግሞ ታሪክን እየቦጫጨቁ ማንበብ ተገቢ አለመሆኑን ስጠቁም፣ እንደርስዎ የመሰለ ሊህቅና ተመራማሪ የሚስተው አይደለም ብዬ በማመን ነው፡፡ ፕሮፌሰር፣ እኔም እንደ አስገደ ገብረሥላሴ “የወዲያው ማዶ” ልጅ ነኝ፡፡ ግና ይህች ማስታወሻ የቀረበችልዎት ከአንድ የታሪክ ተማሪ እንጂ ከ”ማዶው ዜጋ” ሆና እንዳትታይልኝ አደራ እላለሁ፡፡ ታሪክ-ተኮር ጥያቄዎችንና አስተያየት እንዲህ ቢሆን ኖሮ በሚል ማዕቀፍ በመሰንዘሬ ‘ወተት ቢኖር በእንጀራ አምገህ ትበላ ነበር’ ካለችው ሴትዮ ጋርም እንደማያመሳስሉኝ አምናለሁ፡፡

ለጨዋታ ያህል ደግሞ ዲግሪዬና ፕሮፌሰርነቴ ከአሜሪካ ናቸው፣ በዶላር እንዳልተሸመቱ ሳረጋግጥልዎት በትህትና መሆኑን ይገንዘቡልኝ፡፡ ትንሽ ለማሰብና ለመተንፈስ ስለቆሰቆሱኝና ስለገፋፉኝ በእጅጉ አመሰግንዎታለሁ፡፡

ገብሩ ታረቀ (ፕሮፌሰር ኤመሪተስ)

Email: [email protected]

***********************************

ኤርትራ፣ ሚኒልክ፣ ፕሮፌሰር እና አቦይ ስብሓት

(አማኑኤል መሓሪ – ፀሀፊ ተውኔትና ገጣሚ)

ይህን ፅሁፍ ለፍትህ ጋዜጣ አዘጋጅቼ የላኩት ከሶስት ሳምንት በፊት ነበረ፡፡ ሆኖም ግን ፅሑፉን ያደረስኩበት ቀንና ጋዜጣው የሚወጣበት እለት በጣም ተቀራራቢ ስለነበር ለህትመት ሳይበቃ መቅረቱን ከጋዜጣው ዋና አዘጋጅ ወዳጄ ተመስገን ደሳለኝ ለመረዳት ቻልኩኝ፡፡ እኔም ፅሑፉ ካልወጣ አይቀር የተመስገንን ፅሑፍ መነሻ በማድረግ በተከታታይ የወጡትን የፕ/ር መስፍን እና የአቦይ ስብሓት ህትመቶችን በማንበብ የፀሐፊዎቹን ተከታታይ ሓሳቦች ያካተተ ሃሳብ ለመጨመር እና ለማጠናከር ጊዜ እንዲሰጠኝ ጠይቄ ዛሬ ምልከታዬን ለማስፈር ሞክሬያለሁ፡፡

ርዕሰ ጉዳዩ ከእድሜአችን በላይ ያረጀ ቢሆንም፤ በተለይም በወጣት ፀሐፍት በተደጋጋሚ የሚነሳው “ኤርትራን እንዴት አጣናት” የሚለው ጥያቄ እና ጭፍን ድምዳሜ በአብዛኞቹ ፀሐፊዎች ያለው ተመሳሳይነት የፈጠረብኝ ግረምት ነው ለዚህ ፅሑፍ መነሻ የሆነኝ፡፡ በዚህ ላይ ሰሞኑን አ ቦይ ስብሓት በገደምዳሜ ፕ/ር መስፍን እሳቸውን “እናፍረጥርጠው” በማለት የሰነዘሯቸው ሀሳቦች ሌላው ንሸጣ ነው፡፡

ወጣት ፀሐፍት ማለቴ ሆን ብዬ የመረጥኩት ቃል ነው፡፡ ምክንያቱም ካሁን ቀደም በነበሩ እና አሁንም ባሉ ጋዜጠኞች ላይ በርካታ አምደኞች ወጣት መሆናቸውን ከስማቸው በላይ በሚታየው ፎቶ ግራፍ መገንዘብ ከመቻሌም በላይ ከአንዳንዶቹ ጋር የቀረበ ግንኙነትም ስላለኝ ጭምር ነው፡፡ በእኔ እምነት እነዚህ አምደኞች ኤርትራን ያጣንበት መሰረታዊ ምክንያት ላይ ያላቸው ግንዛቤ ሁሉም ለማለት በሚያስችል ሁኔታ ተመሳሳይ ነው፡፡ የተመሳሳይነት ስህተቱ የሚመነጨው (አውቀው እያጠፉ ካልሆነ) በመሰረቱ ከፀሐፊዎቹ አይደለም፡፡ ስህተቱ ከተቃራኒው ወገን የሚቀርብ ይህ ነው የሚባል ተጨባጭ መልስ በተደራጀ እና በተጠና መልኩ ካለመቅረቡ ላይ ነው፡፡

በጣም የሚገርመው ደግሞ ቴሌቪዥን እና ሬዲዮ ማለትም ትልቁን ሚዲያ ለ20 ዓመታት በእጁ የያዘው አካል እያለ ኤርትራን አስመልክቶ ታሪካዊ ማስረጃዎችን የሚያቀርቡልን ፈፅሞ ከስርዓቱ ጋር ግንኙነት የሌላቸው ታሪክ ፀሐፊዎች እና ተመራማሪዎች መሆናቸው ነው፡፡ ገሚሶቹ የውጭ ዜጐች መሆናቸው ደግሞ የበለጠ ግርምትን ይፈጥራል፡፡

በእርግጥ አንዳንዶቹ በፕ/ር ደረጃ ያሉ ምሁራኖች እውነታውን በደምብ ስለሚያውቁት በዚህ ርዕስ ላይ ደፍረው ከመናገር ይልቅ ዝምታን መምረጣቸው በሰፊው የሚስተዋል ሲሆን ከዚህ የከፋው ደግሞ ወጣቶች አስተያየታቸውን ሲያሰፍሩ ጠላቴን በተሳሳተ መልኩም ቢሆን መውቀስህ ትክክል ነው ብለው ማመናቸው ነው፡፡

የዚህ ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ ለኤርትራ መገንጠል አፄ ሚኒልክ ምንም ሚና የላቸውም ተጠያቂዎቹ አቦይ ስብሓት እና ጓደኞቻቸው ናቸው ማለታቸውን ተከትለው ለወጡት ኤርትራን የተመለከቱ ክርክሮች መነሻ መሆኑ እንዳለ ሆኖ ቢያንስ ቢያንስ ነገርን ከስሩ ከመሰረቱ (Root cause) የማየት ችግር የአብዛኞቹ አምደኞች ችግር መሆኑን በቀላሉ የሚያመለክት ነበር፡፡ የነገርን ምንጭ የማያገናዝብ ፅሑፍ ሳይንስ መሆኑ ቀርቶ እምነት አሊያም አውቆ መተኛት ይሆናል፡፡

የነገርን ምንጭ ማገናዘብ ስንጀምር ኤርትራን የማትጨምር ኢትዮጵያ መቼ ተፈጠረች ብለን ለመጠየቅ እንገደዳለን፡፡ በመሆኑም አንድ መካድ የሌለበት የታሪክ እውነታን መጥቀስ ግድ ይለናል፡፡ ኤርትራን የማትጨምር ኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ የተፈጠረች ው በአፄ ሚኒልክ ዘመነ መንግስት መሆኑን አረረም መረረም የግድ መቀበል ይኖርብናል፡፡ አፄ ቴዎድሮስም ሆኑ አፄ ዮሐንስ ከዚያም በፊት የነበሩት አፄዎች ኤርትራን የማትጨምር ኢትዮጵያን አያውቁም፡፡ ለዚህም ይመስላል በአፄ ሚኒልክ ያጣናትን ኤርትራ ከሃምሳ እና ስልሳ አመት በኋላ በአፄ ኃ/ስላሴ ስትቀላቀል የሚከተለው ውዳሴ ለንጉሱ የቀረበው፡፡

ምነው ቀድሞ ቢሆን ያንተ መወለድ
ምፅዋና አስመራ ጅቡቲ ሳይሄድ

(የሕልም ሩጫ ቢተ- እንዳልካቸው መኮንን 1949)

ጅቡቲ የክርክራቸው ማዕከል ስላልሆነች ቢያንስ ጅቡቲንም በማን እና በምን ምክንያት እንዳጣናት በልባችን እናቆይና ምክንያቱ ምንም ይሁን ምን ኤርትራን ከአፄ ኃ/ስላሴ በፊት በነበሩት ሚኒልክ እንዳጣናት ይህ ለጃንሆይ በውዳሴነት የቀረበው እና በመጽሐፉ የታተመው ግጥም ያስረግጥልናል፡፡ በዛ ላይ ፀሐፊው ቢተ-እንዳልካቸው መኮንን መሆናቸው በጃንሆይ ዘንድም ተቀባይነት ያገኙ ፀሐፊ መሆኑን መዘንጋት የለብንም፡፡

አሁን ሚኒልክ ኤርትራን ሳያስመልሱ ከአድዋ ለምን ተመለሱ የሚለውን የምንጊዜም አነታራኪ ርዕሳቸውን መጀመር እንችላለን፡፡ ይህን ርዕስ ከመጀመሬ በፊት አንዱ ማሳሰቢያ ቢጤ ጣል ማድረግ እንዳለብኝ ተሰምቶኛል፡፡ እንዲህ ያሉ ርዕሶችን ስናነሳ አንዱን መሪ ለማወደስ ወይም ለማዋረድ ለማስጠላት ወይም ለማስወደድ አላማ አድርገን መነሳት ስህተት መሆኑን መግለፅ ይኖርብኛል፡፡ ይልቅስ ሚኒልክን የመሰሉ መሪ እምዬ እስከመባል ያደረሳቸው ታላላቅ ተግባራት በጋራ ልንኮራባቸው፤ የፈፀሟቸው ስህተቶችን በጋራ ልናዝንባቸው ነው የሚገባ፡፡ አለመታደል ሆኖ ይህ ፀሐፊ በታላላቅ ተግባሮቻቸው የሚኮራባቸውን ያህል በኤርትራ ጉዳይ ላይ በወሰዱት አቋም ከሚያዝኑት ወገን ነው፡፡

ፕ/ር መስፍን ባሳተሙት ፅሑፍም ሆነ በዚህ ጋዜጣ ላይ በጻፉት ጽሑፍ በተደጋጋሚ እንደሚገልፁት ሚኒልክ አንድ ሺህ ኪሎ ሜትር ተጉዘው ትግራይን በተለይም አድዋን ነፃ ሲያወጡ የአካባቢው ህዝብ ማለትም የትግራይና የኤርትራ ህዝብ ምን ይሰራ ነበር? ከዚህ በላይ ምን ሊያደርጉ ይችሉ ኖሯል? የሚል መከራከሪያቸውን ከማቅረብ አልፈው በቅርቡ ለህትመት የበቃውን "የሀበሻ ጀብዱ" የተባለ በቺኮዝላቫኪያዊ /እሳቸው ጐበዝ ቼኮዝላቫኪያዊ ነው የሚሉት/ የተፃፈ መጽሐፍ ጠቅሰው እንዲያውም የትግራይ ሽፍቶች ለሚኒልክ ሰራዊት የጐን ውጋት ሆኖውባቸው ነበር የሚል ድምዳሜ ይዘው "በኢትዮጵያዊ ይሉኝታ ተሸፋፍኖ የቆየውን እናፍረጥርጠው ከተባለ ለማን አሳፋሪ እንደሚሆን ግልፅ ነው" ይላሉ፡፡ ለማን አሳፋሪ የሚለው ቃል ከሳቸው ባይጠበቅም፡፡

አቦይ ስብሓት ደግሞ "በአፄ ሚኒልክ ዘመነ መንግስት የነበረውን ብናየው ግን ከኢትዮጵያዊነት ስሜት የራቀ መደረግ ያልነበረበትን ስላደረጉ ነው ኤርትራ የተገነጠለችው” በማለት ተደረገ የሚሉትን ከኢትዮጵያዊነት ስሜት የራቀ ተግባር ሳይገልፁ ያልፉታል፡፡ ስለትግራይ ሽፍቶች እና ስለመሳሰሉት ባለፈው ሳምንት በሰፊው ስለገለፁት መድገሙ አላስፈለገኝም፡፡

ሁለቱን ጠንካራ ፅሑፎች መነሻ በማድረግ ወደ ቀጣዩ አጀንዳ ስገባ አቦይ ስብሓት መደረግ ያልነበረበት በማለት በግርድፉ ምናልባትም “በኢትዮጵያዊ ይሉኝታ” ያለፉትን እና ፕ/ር “ተሸፋፍኖ የቆየውን እናፍረጥርጠው” በማለት የተጠቀሙበትን አገላለፅ ከኢትዮጵያዊ ይሉኝታ በመገለል የማፍረጥረጥ አንድ አካል ወደሆነው ቀጣዩ ሐተታ እዘልቃለሁ፡፡

በዚህ ዓመት ፕ/ሩ ከጠቀሱት “የሀበሻ ጀብዱ” የተሰኘ መጽሐፍ ተመሳሳይ ጊዜ ለህትመት የበቃው እና በሁለት ፖላንዳውያን /ጎበዛዝት/ ተመራማሪዎች የተፃፈው እና በአለማየሁ አበበ “የኢትዮጵያ ታሪክ” በሚል ርዕስ የተተረጐመው መጽሐፍ አቦይ ስብሓት ሊነግሩን ያልደፈሩትን የሚኒልክ ከዓድዋ መመለስ ፖለቲካዊ ምስጢር በዝርዝር ያትታል፡፡ መጽሐፉ ሚኒልክ ከዓድዋ ድል በኋላ ወደ ሸዋ ለመመለሳቸው በተደጋጋሚ ሶስት ምክንያቶች እንደሚጠቀሱ ገልፆ እነሱም የክረምት ወራት መቃረብ፣ የውስጣዊ አመፆች ስጋት እና ድንገት ሳይሳካ ቢቀር የተገኘውን ድል ከንቱ እንዳይሆን ከመፍራት ነው የሚሉ ምክንያቶች ይጠቅስና ፖለቲካዊ አንድምታው ግን የኢትዮጵያ ውስጣዊ ሁኔታ መሆኑን በሰፊው ያብራራል፡፡ (ሶስቱን ምክንያቶች ውድቅ የሚያደርግበትን ምክንያት መጽሐፉ ላይ በሰፊው ስለምታገኙት እዚህ አልጠቅሳቸውም፡፡)

መጽሐፉ እንደሚያስረዳው በዚያን ወቅት በሸዋ እና በትግሬ ጠቅላይ ግዛት /የአሁና ትግራይ የቀድሞ መጠሪያ ነው/ መካከል የበላይነትን የማስከበር ሽኩቻ በተደጋጋሚ ሲካሄድ የቆየ መሆኑን ይጠቅስና እንዲህ እያለ ይቀጥላል

 “በሚኒልክ ዓይን ትግሬ ለሸዋው ስርወ መንግስት የመሪነት ስልጣን እጅግ አደገኛ ተፎካካሪ ነው፡፡ ስለዚህ የትግሬ ተሰሚነት ማደግ ለዚህ ስርወ መንግስት የሚበጅ አይሆንም፡፡ ጣሊያኖችን ከኤርትራ ጨርሶ ማስወጣት የግድ የዚህን ጠቅላይ ግዛት ክብደት ያጠናክረዋል፡፡ ኢትዮጵያ የባህር በሯን መልሳ እጇ ከተደረገ የውጭ ንግድ ስለሚስፋፋ የባህር አዋሳኝ የሆኑ አውራጃዎች ሁሉ ትግሬም ጭምር በኢኮኖሚ እንዲጠነክሩ ያደርጋል፡፡ በአንፃሩ ሸዋ ከባህር ርቆ በደቡብ የሚገኝ እንደ መሆኑ ከባህሩም ጋር የሚያገናኘው ምንም አመች መንገድ ስለሌለው ተጠቃሚነቱ ውስን ነው የሚሆነው፡፡ ስለዚህ በሚኒልክ አስተሳሰብ የትግሬ መዳከም ለሸዋ ጠቃሚነው የሚባል ከሆነ ኤርትራን ለማስመለስ ያልተጨነቀበት ምክንያት ግልፅ ይሆናል”

በማለት በኢትዮጵያዊ ይሉኝታ የተሸፈነውን ታሪክ ይተነትናል፡፡

የወቅቱን ፋሽን ማለትም የላስታ፣ የትግራይ፣ የጐንደር እና የሸዋ የበላይነትን ለማስከበር ይደረጉ የነበሩ ሽኩቻዎችን ላስተዋለ ሚኒልክ ትግረኛ ተናጋሪውን ክፍል ሁለት ቦታ ከፍለው መመለሳቸው የሸዋን የበላይነት ከማስጠበቅ አንፃር የመከራከሪያ ሀሳቡን ከባድ ሚዛን እንዲደፋ ያደርገዋል፡፡

መጽሐፉ ያነሳውን ርዕስ ከማጠቃለሉ በፊት የደረሰበትን ድምዳሜ ሲያስቀምጥ

“ለጠቅላላው ኢትዮጵያ ጐጂ የነበረ ቢሆንም ለሸዋው ዲናስቲ የራሱን የበላይነት ለመጠበቅ እድል የከፈተለት እና ስልጣን ለማጠናከር ዋስትና የሚሰጠው በመሆኑ በትግሬ ኪሳራ የተገኘውን የመረብና የበለሳን ወንዞች የኢትዮጵያ ሰሜናዊ ወሰን አድርጐ ተቀበለ፡፡ የዚህ ስርወ መንግስት የውጭ ፖሊሲ ዋና ትኩረት ያረፈው በደቡብ አቅጣጫ አንጂ በሰሜኑ ላይ አልነበረም፡፡ ስለዚህ ሚኒልክ ኤርትራን ችላ ብሎ ከአድዋ የተመለሰበት መሰረታዊ ምክንያት የሸዋን እና ከዚህ ግዛት የበቀለውን ስርወ መንግስት ጥቅም ከመላዋ ኢትዮጵያ መንግስታዊ ጥቅም በላይ አድርጐ በማየቱ ነው፡፡ ዳግማዊ ሚኒልክ በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ታላቅ ሚና የተጫወቱ መሪ መሆኑ ቢታወቅም እንኳ ይህን እውነታ ሊለውጠው አይቻልም” ይላል፡፡ (ገጽ 353-356)

ፀሐፊዎቹ ዳግማዊ ሚኒልክ በኢትዮጵያ ታሪክ ታላቅ ሚና የተጫወቱ መሪ መሆናቸውን መግለፃቸው እንደሚያስመሰግናቸው ተስማምተን የዛሬው ማጠንጠኛ ወደሆነው የ”እናፍረጥርጠው” ፕሮግራም ስንመለስ አንዱ ተጨማሪ ሀገር በቀል መጽሐፍ ለመጥቀስ እንገደዳለን፡፡ በዘውዴ ረታ የተፃፈው “የኤርትራ ጉዳይ” የተሰኘው መጽሐፍ በኃ/ስላሴ ስርዓት ከ1955 እስከ 1962 የኤርትራ ቺፍ ኤግዚኩቲቭ የነበሩት ቢትወደድ አስፈሐ ወልደሚካኤል እንዲህ ብለው በምሬት መናገራቸውን በደማቅ ይገልፃል “እኛ ኤርትራውያን ንጉስ ሚኒልክ ለጣሊያን ሸጠውን ነው አንጂ ኢትዮጵያውያን ነን” (ገጽ 460)

ይህን ጽሑፍ ከማጠቃለሌ በፊት ሁለት ነገሮችን ማንሳት እፈልጋለሁ፡፡ አንደኛው ለዚያን ያህል አመታት ኤርትራን አግልለን ቅኝ ያልተገዛች ሀገር እያልን ማውራታችን ምን ማለታችን እንደነበረና ከዚያ በኋላ በተከታተሉት ስርዓቶች የተፈጠረው የታሪክ ሂደት መነሻ ምንጩ ምኒልክ ስለመሆናቸው ሲሆን ሁለተኛው ነጥብ ደግሞ የአፄ ሚኒልክን ያህል ባይሆንም ኃ/ስላሴ ኋላ ላይ የተፈጠሩትን ፌደሬሽኑን በአግባቡ አለመያዝ እና እኛን መስላቹ እደሩ የአገዛዝ ስህተቶች ጨምሮ (የኤርትራ ጉዳይን ልብ ይላል) ለኤርትራ ዳግም መነጠል የሻዕቢያ መፈጠርን ጨምሮ የራሳቸውን ድርሻ እንዳላቸው ማስገንዘብ ነው፡፡

በቀጣይ ጽሑፌ ከሻዕቢያ መፈጠር በኋላ ለኤርትራ መገንጠል ከኤርትራ ህዝብ ትግል በተጨማሪ በወቅቱ የነበረው የደርግ አገዛዝ ጉዳዩን የያዘበት መንገድ ፣ ኢህአዴግ ከሻዕቢያ ጋር የፈጠረው ስትራቴጂክ ትብብር እና ያራመደው አይዶሎጂ ፣ ኢህአፓን ጨምሮ በወቅቱ የነበሩ ሀይሎች በኤርትራ ጉዳይ ላይ የነበራቸው የኃይል አሰላለፍ እና ተቃርኖ በዚህም ምክንያት ኤርትራ ዳግም ከእናት ሀገሯ በህጋዊ ማህተም የተለየችበት ሁኔታ ለመዳሰስ እሞክራለሁ፡፡ የነገሩ ምንጭ ሳይዘነጋ፡፡

********************************

ተዛማጅ ጽሁፎች፡-

ወያነ-ትግራይና የሉዓላዊነት አጀንዳ | Woyane-Tigray and the Question of Sovereignty

Text of Wuchale Treaty | 1889 Ethio-Italian Treaty

Daniel Berhane

more recommended stories