አፋን ኦሮሞ ሁለተኛው የፌዴራል የሥራ ቋንቋ እንዳይሆን ምን ያግደዋል?

(ቶለዋቅ ዋሪ)

ከ25 ዓመታት በላይ እንደ ፈንጂ ሲፈራ የነበረው የኦሮሚያ ክልል ከፊንፊኔ ማግኘት ያለበት ህገ መንግስታዊ የልዩ ጥቅም ጉዳይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ፀሃይ የሞቀው አገር ያወቀው ጉዳይ ሆኖ አነጋጋሪና አወያይ  በመሆን ቀጥሏል መልካም ነው::

ጉዳዩ እንዲህ ግልጥልጥ ብሎ  ለሰፊው ሕዝብ መቅረብ ሲችል ለአመታት ተደፋፍኖ ለፀረ ሰላምና ፀረ ሕዝብ ኃይሎች የተቃውሞ አጀንዳ ሆኖ መቆየት አልነበረበትም፤ይሁንና አሁን ሁሉም ነገር ትክክለኛውን መስመር በመያዝ ላይ ስለሚገኝ ቢዘገይም ለበጎ ነው ማለት ይቻላል::

በቅርቡ በኢፌዴሪ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ፀድቆ  ወደ ተወካዮች ምክር ቤት የተመራው የልዩ ጥቅም ረቂቅ አዋጅ በተወካዮች ምክር ቤት አባላትም ውይይት ተካሂዶበት ጉዳዩ ወደ ሚመለከተው ቋሚ ኮሚቴ ተመርቶ በይደር እንዲቆይ መወሰኑ ይታወቃል::

“የእነ ቶሎ ቶሎ ቤት ግድግዳው ሰንበሌጥ” እንዲሉ ይህ ረቂቅ አዋጅ ውጤት አልባ እንዳይሆንና ሁሉንም የሚያነጋግር በመሆኑ በውይይት እንዲብላላና የኦሮሞ ሕዝብ ፍላጎት ተሳክቶ የሌሎች ወገኖች መብትም ሳይነካ አዋጁ ብሰለት እንዲኖረው እንወያይበት መባሉ ትክክለኛና በአመራሮቻችን ብስለት የመጣ አመርቂ ውሳኔ እንደሆነ መረዳት አያዳግትም::

በረቂቅ አዋጁ ውስጥ በተጠቀሱት ልዩ ጥቅም በተባሉ ጉዳዮች ላይ በሌላ ፅሁፌ እይታዬን የማንፀባርቅ መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ በዚህ ፅሁፍ በረቂቅ አዋጁ ላይ ስለተጠቀሰው የአፋን ኦሮሞ በፊንፊኔ የስራ ቋንቋ መሆን ፍላጎትን መሰረት በማድረግ እንዲህ ቢሆንስ የሚል ሌላውን እይታዬን ላንፀባርቅ::

የኦሮምኛ ቋንቋ አፋን ኦሮሞ የቀድሞዎቹ ጨቋኝ ስርዓቶች በሰፊው የኦሮሞ ሕዝብና በሌሎች ብሄር ብሄራሰቦችና ሕዝቦች ላይ ባደረጉት ገደብ የለሽ ተፅዕኖ ምክንያት የስነ ፅሁፍና የስራ ቋንቋ የመሆን ዕድል ባለማግኘቱ፤እንዳውም ሆን ተብሎ የቋንቋው ተናጋሪዎች የሚያፍሩበትና የሚሸማቀቁበት እንዲሆን በመደረጉ ምክንያት የሚፈለገውን ያህል ዕድገት ሳያመጣ ቆይቷል::

ይህም ሆኖ ቋንቋው እንዳይረሳና እንዳይጠፋ በፅኑ የኦሮሞ ታጋዮችና ተቆርቋሪ ግለሰብ ምሁራኖች እንዲሁም ሰፊው የኦሮሞ ሕዝብ ለማንነቱ ባደረገው የዘመናት ተጋድሎ አፋን ኦሮሞ ዕድሜው ረዝሞ መቆየት ችሎ በጨቋኝ ገዢዎች በተፅዕኖ ከተቀበረበት ጉድጓድ በመውጣት ከ1983 ዓ.ም ወዲህ በይፋ ከሽግግር መንግስት ጊዜ ጀምሮ በኦሮሚያ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት የስራና የትምህርት ቋንቋ ሆኖ በማገልገል ላይ ይገኛል፤ይህ ለሰፊው የኦሮሞ ሕዝብ ታላቅ ድል ሆኖ በታሪክ ተመዝግቧል::

Image - Afaan Oromo alphabet
Image – Afaan Oromo alphabet

አፋን ኦሮሞ አሁን በምን ደረጃ ላይ ይገኛል?

የኦሮምኛ ቋንቋ አፋን ኦሮሞ የክልሉ መንግስት የስራና የትምህርት ቋንቋ ከሆነ ወዲህ በቀላሉ ሊታመን የማይችል ለውጥ ታይቷል፤በቋንቋው ለመናገርና ለመጠቀም ለዘመናት ሲጓጓ የቆየው የኦሮሞ ሕዝብ ከመንግስት ጎን ሆኖ ባደረገው ከፍተኛ ርብርብ እስከ ታችኛው ደረጃ ድረስ ትምህርት ቤቶች ተስፋፍተዋል፤በእነዚህ ትምህርት ቤቶች በሚሊየን የሚቆጠሩ ወድ የኦሮሞ ልጆች ተምረው ወደ ከፍተኛ ትምህርትም በመሸጋገር ተመርቀዋል በሚሊየን የሚቆጠሩ ደግሞ በመማር ላይ ይገኛሉ::

በአሁኑ ወቅት አፋን ኦሮሞ በከፍተኛ የትምህርት ተቋማትም የምርምር ቋንቋ ሆኖ በማገልገል ላይ ይገኛል፤ቋንቋው የዕድገት ግስጋሴውን በማጠናከር በተለያዩ ዩኒቨርስቲዎች በመጀመሪያ በሁለተኛና በሶስተኛ ድግሪ ጭምር በሺዎች የሚቆጠሩ ብቁ ዜጎችን በማፍራት ላይ እንደሚገኝ በገሃድ ይታወቃል::

ከዚህም በተጨማሪ በተለያዩ የህትመትና የብሮድካስት ሚዲያዎች እንዲሁም በአዲሱ ሚዲያ በቋንቋው በመሰራት ላይ እንደሚገኝ ይታወቃል፤በአፋን ኦሮሞ ተዘጋጅተው ለተደራሲያን የቀረቡ በርካታ መፅሓፍትም ታትመው ተሰራጭተዋል::

ባለፉት አመታት ታትመው ለተደራሲያን የቀረቡ በአፋን ኦሮሞ የተዘጋጁ መፅሃፍቶች ይዘታቸው ምንም ይሁን ምን ለቋንቋው እድገት የማይናቅ አስተዋፅኦ አበርክተዋል፤አሁንም በማበርከት ላይ ይገኛሉ ማለት ይቻላል::

ከላይ እንደጠቀስኩት አፋን ኦሮሞ ከዘመኑ ቴክኖሎጂ ጋርም የተዋደደና ያለምንም ችግር በማገልገል ላይ ይገኛል፤በተለይ የቁቤ አፋን ኦሮሞን አነባበብና ስርዓት ጠብቆ ለሚፅፍ የዘመኑ ቴክኖሎጂ እጅግ በጣም ምቹ ስለመሆኑ ጥርጥር የለውም::

እነዚህን ሁሉ ተጨባጭ ምቹ ሁኔታዎች ያሉት የኦሮሚኛ ቋንቋ አፋን ኦሮሞ የኢፌድሪ ፌዴራል መንግስት የስራ ቋንቋ መሆን የማይችልበት ምክንያት ምንድነው? ምን የሚያግደው ነገርስ አለ? እንደ አንዳንድ ወገኖች አመለካከት አፋን ኦሮሞም ሆነ ሌላ ቋንቋ ወደ አማርኛ ቋንቋ  ድርሽ እንዳይል ይፈለጋል ይህ ሊያዋጣ የሚችል አካሄድ እንዳልሆነ ጉዳዩን በማቀንቀን ላይ የሚገኙ ወገኖች ሊገነዘቡት ይገባል፤ጉዳዩን ከተለያየ አቅጣጫና ከአለማዊ ሁኔታ አንፃር በቅንነት ማየትም ይጠበቅባቸዋል::

አማርኛ በታሪክ አጋጣሚና የቀድሞ ገዢ መደቦች በፈጠሩት ምቹ ሁኔታ እንዲሁም በርካታ ቅን ምሁራን ባከናወኑት በጎ ስራ እድገቱ ቀጥሎ በአሁኑ ስርዓታችንም የፌዴራል የስራ ቋንቋ መሆን ችሏል መልካም ነው፤የዚህ ፅሁፍ አቅራቢም እየተጠቀመበት ነው፤ሌላውም ወገን ቅንነትና ፍላጎት ካለው አፋን ኦሮሞን ሁለት ሳምንት ባልበለጠ ጊዜ ቁቤ አፋን ኦሮሞን በመማር መጠቀም ይችላል::

ለህዳሴ ጉዞአችን ስኬት የአፋን ኦሮሞ ቋንቋ ትኩረት አግኝቶ የፌዴራል መንግስት የስራ ቋንቋ ሊሆን ይገባል!

አፋን ኦሮሞ በኢትዮጵያ አይደለም በአፍሪካ አህጉር የስራ ቋንቋ መሆን ይችላል፤ይህ ማለት ምቹ ሁኔታዎች ከተፈጠሩ የቋንቋው ተናጋሪዎች እጅግ በርካታ በመሆናቸው ቋንቋው የአገር የስራ ቋንቋ ሆኖ ከማገልገል የሚያግደው ምንም ነገር የለም፤ስለዚህ ያለፈው አልፏል፤ከአሁን በኋላ ባለው ሂደት አፋን ኦሮሞ የፌዴራል መንግስታችን የስራ ቋንቋ ሆኖ እንዲያገለግል ጉዳዩ በሚመለከታቸው አከላት መሰራት አለበት::

ይህ መሆን ያለበት ባለው ነባራዊ ሁኔታ ላይ በመመስረት ነው እንጂ በጫናና የሌሎችን መብት በመጋፋት አይደለም፤መሆን የለበትም።የተያያዝነው የህዳሴ ጉዞ ከሰፊው የኦሮሞ ሕዝብ የተሟላ ተሳትፎ ውጭ ከግቡ ሊደርስ አይችልም፤በህዳሴው ጉዞ ውስጥ በሚከናወኑ ስራዎች ውስጥ ሁሉም ኦሮሞዎች አምነውና ፈቅደው በሚችሉት ቋንቋ በየትኛውም የፌዴራል መንግስት ተቋማት ውስጥ መስራት እንዲችሉ መደረግ አለበት::

ይህን የታላቅ ሕዝብ ፍላጎት ወደ ጎን በመተውና በምን አገባኝ አካሄድ በቸልታ ማለፍ በህዳሴው ጉዞ ላይ እንቅፋት እንዲፈጠር መፍቀድ እንደሆነ መገንዘብ ተገቢ ነው፤ቋንቋው ሁለተኛ የፌዴራል የስራ ቋንቋ ከሆነ በሚሊየን የሚቆጠሩና በዚህ ስርዓት ጊዜ ውስጥ  የተወለዱ የኦሮሞ ልጆች በተለያዩ የፌዴራል መንግስትና በቋንቋው በሚሰሩ መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት ውስጥም የስራ እድል ማግኘት ይችላሉ::

በዚህ ስርዓት የመማር እድል አግኝተው የተማሩ የኦሮሞ ልጆች በተለያዩ ሙያዎች ከሰለጠኑ በኋላ በጥቃቅንና አነስተኛ ስራዎች ላይ ብቻ ተሰማርተው ኑሮአቸውን እንዲገፉ ማድረግ ተገቢ አይሆንም፤የተማሩ የኦሮሞ ወጣቶች በግብርና ስራዎች ላይ መሰማራት ብቸኛ አማራጭና ዕጣ ፍንታቸው ሊሆን አይገባም::

በየትኛውም የኦሮሚያ ክልል ዞን ውስጥ የሚገኝና የተማረ የኦሮሞ ወጣት ልክ ከሌላው ክልል በፌዴራል የስራ ቋንቋ በሆነው አማርኛ በተለያዩ የመንግስት ተቋማት የስራ ዕድል ማግኘት እንደሚችለው ሁሉ በአስተማማኝ ሁኔታ አማራጭ የስራ ዕድል ማግኘት እንዲችል ምቹ ሁኔታ መፍጠር ያሻል፤ለእኩል ተሳትፎና ተጠቃሚነት በዚህ ረገድም መታሰብ አለበት::

የኦሮሚያ ክልል ከአዲስ አበባ ፊንፊኔ ማግኘት ስለሚገበው ልዩ ጥቅም ረቂቅ አዋጅ ላይ እንደተጠቀሰው አፋን ኦሮሞ በአዲስ አበባ መስተዳድር መስሪያ ቤቶች የስራ ቋንቋ ሆኖ ያገለግላል፤ልምን ይህ ብቻ? ይህ እንዳለ ሆኖ አፋን ኦሮሞ በአዲስ አበባ መዋቅር ብቻ አይደለም በፌዴራል የመንግስት መዋቅሮች ውስጥም ከላይ በዘረዘርኳቸው ነባራዊና ተጨባጭ ሁኔታዎች ምክንያት የስራ ቋንቋ መሆን ይገባዋል::

ከልዩ መብትና ጥቅም ጋር ተያይዞ ሰሞኑን በተለያዩ መገናኛ ብዙሃኖች ተቃውሞአቸውን በማሰማት ላይ ለሚገኙ ኃይሎች ይህ እውነታ ተቃባይነት እንደሌለው ይታወቃል፤ግን ደግሞ በተቃውሞ በጩኸት፤ጉዳዩን ዝቅ አድርጎ በማበሻቀጥና በመንጫጫት የሚሆን ነገር የለምና በዚህ ሁኔታ በመንቀሳቀስ ላይ የሚገኙ ወገኖች ወደ ልቦናቸው ተመልሰው ጉዳዩን በሰከነ መንፈስ ሊመለከቱት ይገባል::

የሌላውም ድጋፍ አስፈላጊና ተገቢ ቢሆንም በራሱ ጉዳይ ላይ ወስኖና ድምፅ ሰጥቶ ተግባራዊ በማድረግ ተጠቃሚ መሆን የሚችለው ሰፊው የኦሮሞ ሕዝብ ነው፤ለዚህ ደግሞ የኦሮሚያ ሕዝብ ፍላጎቱም አቅሙም እንዳለው በመረዳት ሁሉም ወገን የአብሮነት ኑሮ እንዲቀጥል የበኩሉን እገዛ ማድረግ ይጠበቅበታል “ጨው ለራስህ ስትል ጣፍጥ…..”ይላል ያገሬ ሰው፤ያለበለዚያ በህገ መንግስቱ አንቀፅ 39 ላይ ያለውን ተግባራዊ ማድረግ የመጨረሻ አማራጭ ሊሆን ይችላል::

*********

Guest Author

more recommended stories