(ህዳሴ ኢትዮጵያ)

መነሻ ሃሳብ

እንደ ኣውሮፓውያን ኣቆጣጠር (እ.ኣ.ኣ) በ1960ዎች ኣብዛኛው የአፍሪካ ኣገራት ከቅኝ ኣገዛዝ ነፃ ሲወጡ፣ ቅኝ ገዢዎች የተዉላቸው መሰረተ ልማቶችና ኢንዱስትሪዎች የአፍሪካ መንግስታት ለአገር እድገታቸው እንደ መነሻ ሃብት ሲጠቀሙበት፤ በዛን ጊዜ አገራችን ይቅርና መነሻ ሃብት ሊኖረን ህዝባችን በድህነት ኣሮንቋና በረሃብ የሚያልቅበት ጊዜ ነበር፡፡ እ.ኣ.ኣ. በ1970ዎች መጀመሪያ የህዝቦች ቁጣ ጫፍ ደርሶ በመላው የኢትዮጵያ ህዝቦች ዓመፅ ዘውዳዊ ስርኣት ተንኮታኩቶ ሲገረሰስ በምትኩ የደርግ ወታደራዊ ስርኣት ሲተካ፣ የነበረውን ጭቆና በከፋ መልኩ ቀጥሎበት በመጨረሻም ደርግ በህዝቦች ትግል ተንኮታኩቶ ወድቋል፡፡

በዚህ ጊዜ ኢህአዴግ ኢትዮጵያን ሲቆጣጠር፣ አገራችን የድሆች ድሃ፣ ያለ ምፅዋት እንደ አገር መቆም የማትችልበት ደረጃ ደርሳ የሶማሊያ እጣፈንታ ይደርሳታል ትበታተናለች ሲባል የነበረው፡፡ አገራችን የአኩሪ ታሪክና ስልጣኔ ባለቤት እንዳልነበረች እንዲሁም የጀግኖች ህዝቦች ባለቤት እንዳልሆነች፣ ከዘመናት የኋልዮሽ ጉዞ ወደ መበታተን ኣፋፍ ልትደርስ የዳረጋት ዋናው ምክንያት ህዝባዊ ወገንተኝነት ያለው መስመር፣ ኣመራርና የህዝቦች ትግል መሪ ድርጅት ማጣት ነው፡፡ በስተመጨረሻ እንደ መታደል ሆኖ አገራችን፣ ህዝባዊ ወገንተኝነት ያለው፣ የህዝብን ጥቅም የሚያስቀድም ኣብዮታዊ ዴሞክራሲ መስመርና ዓላማ፣ ስለ አገርና ንጉስ/መሪ ሳይሆን ስለ ህዝብና አገር መስዋእት የሚከፍል ግንባር ቀደም ኣመራርና፣ ምልኣተ ጭቁን ህዝብ ማሰለፍ የሚችል መሪ ድርጅት በማግኘትዋ የኋልዮሽ ጉዞዋና የመበታተን አደጋው ተቀልብሶ በአሁኑ ደረጃ እነሆ ከአለማችን በፈጣን፣ ቀጣይነት ያለውና ፍትሃዊ የኢኮኖሚ ዕድገት ከሚያስመዘግቡ አገራት በቀደምትነት የምትገለፅ ለመሆን በቅታለች፡፡

በአፍሪካ በመሰረተ ልማትና በኢንዳስትሪ ደረጃ የመጨረሻዎቹ መጨረሻ የነበረች አገር አሁን ከአፍሪካ ከፍተኛ ኢኮኖሚ ባለቤቶች ከሚባሉት ውስጥ አንዷ ለመሆን የበቃችው ዋናው ሚስጥር የኢትዮጵያ ህዝብ ለዘመናት ሲመኘው የነበረ ህዝባዊ ወገንተኝነት ያለው ኣብዮታዊ ዴሞክራሲ ወይም ልማታዊ ዴሞክራሲ መስመርና በዚህ መስመር የተካኑ ኣመራርና ድርጅት በማግኘቱ ነው፡፡

ስለዚህ ኢህአዴግ የኣብዮታዊ ዴሞክራሲ ባህሪዉን ሳይለውጥ እስከሄደ ድረስ የአገራችን ዳግመ-ትንሳኤ ይቀጥላል፡፡ ኣብዮታዊ ዴሞክራሲ ባህሪው መሸራረፍ ሲጀምር ውጤቱም ያው እየተሸራረፈ ብሎብሎ ወደ ቀደምት ስርዓት ባህሪ መግባቱ የማይቀርና አገራችን ወደ ድህነት ጎዳና መግባቷ ኣይቀሬ ነው፡፡ ስለዚ የገዢ ፓርቲ ኣብዮታዊ ዴሞክራሲ ባህሪውን የማስቀጠልና ያለማስቀጠል ጉዳይ አገራችን ወደፊት የመራመድና ያለመራመድ ጉዳይ መሆኑ መታወቅ ኣለበት፡፡

ይህን እንደ መነሻነት በመውሰድ የኣብዮታዊ ዴሞክራሲ መስመር እና አሁን በመታየት ላይ ያለውን የለውጥ ጉዞ ትኩረት መሰጠት ያለበትን ጉዳይ ለውይይት አስተዋፅኦ ለማድረግ ያህል የሻዕብያ ትንኮሳና ኣብዮታዊ ዴሞክራሲ በሚል ርእስ ይህ ፅሁፍ ቀርቧል፡፡ በዚህ ርእስ ማቅረብ የፈለኩት ኣጀንዳ በሻዕብያ ትንኮሳና የኢትዮጵያ ፖሊሲ ዙርያ ሆኖ ከታሪካዊ ኣመጣጡ (ከትጥቅ ትግል) ጀምሮ እስከ ኣሁን ያለውን ሁኔታና የፖሊሲ ውጤት ቀጣይ ምን መሆን ኣለበት የሚለውን በኣብዮታዊ ዴሞክራሲ ኣመለካከት ለመዳሰስ ተሞክረዋል፡፡

መግቢያ

ሻዕብያ የኢትዮጵያ ሰላምና መረጋጋት፣ የኢትዮጵያ ልማትና ዴሞክራሲ የማይዋጥላቸውና ባላቸው ዓቅም ስርዓታችን ለማፍረስ ከሚሰሩት ሃይሎች ውስጥ ኣንዱና ዋነኛው ነው፡፡ ሻዕብያ ዓቅም ካገኘ ኢትዮጵያን ለማፈራረስ የማይፈንቅለው ድንጋይ የለም፡፡ ስለዚ በተቻለ መጠን ለእንደዚ ዓይነቱ ልክፍት መንግስት ሃይል ኑሮት አገራችን ለማበጣበጥ ዕድል መሰጠት እንደሌለበት ሁሉም አገር ወዳድ ዜጋ ይስማማበታል፡፡ ሻዕብያ ለምን በኢትዮጵያ እንዲህ ዓይነት ኣቋም ያዘ? የሻዕብያ ባህሪ በትጥቅ ትግሉና አሁን ምን ይመስላል? ሻዕብያ የለኮሰው ጦርነት ምክንያትና የኢትዮጵያ ምላሽ፣ ከጦርነቱ ቦሃላ ኢህኣዴግ የተከተለው ፖሊሲ ምን ይመስላል? ውጤቱስ እንዴት ይመዘናል? ግን ሻዕብያ አሁን በርግጥ ኢትዮጵያን የማተራመስና የማፈራረስ ዓቅሙና ብቃቱ ኣለውን? ኣሁን የምንከተለው ፖሊሲ በኣብዮታዊ ዴሞክራሲ ኣመለካከት መከለስ ያስፈልገዋል ወይስ ኣያስፈልገውም? የሚለውን ነገሮች ዘርዘር ባለ መልኩ ለማየት እንደሚከተለው ቀርቧል፡፡

1/ የሻዕብያና የኢትዮጵያ ህዝቦች ትግል ግንኙነት

ሻዕብያ የኤርትራ ህዝብ ጥያቄ ይዞ በመነሳትና ህዝቡን ከጎኑ በማሰለፍ ለድል የበቃ ድርጅት መሆኑ የሚካድ ኣይደለም፡፡ ሻዕብያ ኣንዱንና ኣንገብጋቢው የኤርትራ ህዝብ የነፃነት ጥያቄ ይዞ በመውጣቱና ህዝብን ከጎኑ ኣሰልፎ ለድል መብቃቱ ካልሆነ በስተቀር ሌላው ባህሪውና ተግባሩ ፀረ ህዝብና ፀረ ዴሞክራሲ መሆኑ ኣሁን በዓለም ኣደባባይ ጎልቶ የሚታይና ኣብዛኛው የሚስማማበት ጉዳይ ነው፡፡ ይህ ባህሪው ኣሁን የመጣ ሳይሆን ገና ትጥቅ ትግል ሲጀምር ጀምሮ ከድርጅቱ የተዋሃደና እዚህ ደረጃ የደረሰ ነው፡፡ በትጥቅ ትግል ጊዜ ሻዕብያ የሚያሳያቸው የነበሩ ፀረ ህዝብና ፀረ ዴሞክራሲ ተግባራት፣ እንደ ጊዝያዊና ትግሉ የሚጠይቀው ኣፈፃፀም እንከኖች እንጂ ከሻዕብያ መሰረታዊ የፀረ ዴሞክራሲና የፀረ ህዝብ ባህሪ የሚመነጭ ነው ብሎ የሚያምን በጣም ጥቂት ብልሆች ብቻ ነበሩ፡፡

በሌላ ኣነጋገር ሻዕብያ በትጥቅ ትግል ኣመታት ውስጥ ይፈፅማቸው የነበሩ በርካታ የፀረ ህዝብና የፀረ ዴሞክራሲ ተግባራት ለሁሉም ግልፅ የነበረ ቢሆንም፣ የህዝብ ጥያቄ ይዞ ህዝብን ከጎኑ ኣሰልፎ የተነሳ ድርጅት፣ ስለ ህዝብ ጥያቄ እስከ ሂይወት መስዋእትነት የሚከፍል ሃይል በትግሉ ወቅት የሚፈፅማቸው ፀረ ህዝብና ፀረ ዴሞክራሲ ተግባራት እንደ የኣፈፃፀም ችግር እንጂ ከባህሪው የመነጨ ችግር ኣይደለም የሚል ኣብዛኛው የሚስማማበት ጉዳይ ነው የነበረው፡፡ በዚህ ጊዜ ሻዕብያ ከሚፈፅማቸው ተግባራትና የሚከተላቸው መርሆዎች በመነሳት ሻዕብያ ፀረ ዴሞክራሲና ፀረ ህዝብ ነው ማለት እንደ እብደት የሚቆጠርበት ጊዜ ነበር፡፡

ማንኛውም ፖለቲካዊ ድርጅት የቆመለትን ዓላማ ለማሳካት ውስጣዊና ውጪያዊ ፖለቲካዊ ሁኔታዎችን በዝርዝርና ሳይንሳዊ በሆነ መልኩ በመገምገም በውስጡ ያለውን ጥንካሬና ድክመት፣ በውጪያዊ ሁኔታ ያለውን መልካም ኣጋጣሚና ስጋቶች በዝርዝር ለይቶ በማስቀመጥ ውስጣዊ ጥንካሬውና ውጭያዊ መልካም ኣጋጣሚ በበለጠ እንዲጠቀምበት የሚያስችል እንዲሁም ውስጣዊ ድክመቱና ውጪያዊ ስጋቶች በተቻለ መጠን ለማስወገድ ወይም ለመቋቋም ስትራቴጂና ታክቲክ መቀየስ የግድ ነው፡፡ ይህ የማያደርግ ፖለቲካዊ ድርጅት ለውድቀት ሁኔታው ያመቻቸ ብቻ ነው፡፡ ይህ ሳይንሳዊ ትንታኔ ኣንዴ ተደርጎ የሚቀመጥ ሳይሆን ቀጣይና ካለው ውስጣዊና ውጫዊ ለውጦች በየጊዜው እያጣጣሙ መሄድ ይጠይቃል፡፡

በዚህ መሰረት ህወሓት የቆመለትን የኣብዮታዊ ዴሞክራሲ ዓላማ ከማሳካት ኣኳያና ለትግሉ ካለው ፋይዳ የቅርብ ውጪያዊ ሁኔታ (በትግራይና ኢትዮጵያ) እንዲሁም የሩቅ ውጪያዊ ሁኔታ (በኣፍሪካ፣ በኤሽያና በዓለም ደረጃ) ያለውን ፖለቲካዊ ሁኔታ ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ በመተንተን ያሉትን ፖለቲካዊ ሃይሎች ካላቸው ህዝባዊና ዴሞክራሲያዊ ባህሪ በመነሳት ስትራቴጂክ ወዳጅና ጠላት ተንትኖ በሚለይበት ጊዜ ከትንታኔው ውጤት አንዱ ሻዕብያ ነበርና ሻዕብያም ስትራቴጂያዊ ጠላት ሆኖ ተገኘ፡፡

ትንታኔውንም እንደሚከተለው ማስቀመጥ ይቻላል፡፡

ኤርትራ ከዘመነ ኣፄ ሚኒሊክ በፊት በኢትዮጵያ ነገስታት ትተዳደር እንደነበረች፣ ከኣፄ ሚኒሊክ ጊዜ ጀምሮ ለ50 ዓመታት በጣሊያን ስር፣ ቀጥሎ ለ10 ዓመታት በኢንግሊዝ ስር በቅኝ ግዛት ስትተዳደር የቆየች ስትሆን በሃ/ስላሴ ዘመን በፌደሬሽን መልክ በኤርትራ ህዝብ ፍላጎት ወደኢትዮጵያ የገባች እንደሆነች፤ ሆኖም ግን ዘውዳዊ ስርዓቱ ካለው የፀረ ህዝብ ባህሪ የተነሳ ፌደሬሽኑ በማፍረስ የኢትዮጵያ 14ኛ ክፍለ-ሃገር እንድትሆን በመደረጉ ከዚህ ጊዜ ጀምሮ የኤርትራ ህዝብ ጥያቄ እንዳነሳና ጥያቄውን ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ የሚያስተናግደው ስርዓት ሲያጣ ወደ ትጥቅ ትግል መግባቱ፣ በዚህም ምክንያት የኤርትራ ህዝብ በተለያዩ ድርጅቶች ስር ሆኖ መታገል መጀመሩ፣ በመጨረሻም ኣብዛኞቹ ድርጅቶች በሂደት ሲከስሙ ሻዕብያ ግን እንደ ዋነኛው የኤርትራ ተቃዋሚ ሃይል ሆኖ መገኘቱ፡፡

የኤርትራ ህዝብ ጥያቄ በሰላማዊ መንገድ የሚያስተናግደው በማጣት ዴሞክራሲያዊ መብቱ ለማረጋገጥ የተነሳ የህዝብ ጥያቄ በመሆኑ ትክክለኛ እንደሆነ፣ ኣብዮታዊ ዴሞክራሲ የህዝብ ጥያቄ ያለ ምንም ማቅማማት የሚያከብርና የሚደግፍ በመሆኑ የኤርትራ ህዝብ ጥያቄና ትግልም እንደ ኣብዮታዊ ዴሞክራሲ የምንደግፈውና የምናከብረው እንደሆነ፣ ነገር ግን ሻዕብያ ካለው ባህሪ አኳያ ሲታይ ፀረህዝብና ፀረ ዴሞክራሲ እንደሆነ፣ ከኤርትራ ህዝብ የሚያስተሳስረው ነገር ቢኖር በአንድ አጀንዳ ብቻ እንደሆነ፣ እሱም የኤርትራ ነፃነት እውን የማድረግ ዓላማ ብቻ እንደሆነ፣ የኤርትራ የነፃነት ጥያቄ ፍትሃዊ የህዝብ ጥያቄ በመሆኑ ዙሮ ዝሮ የህዝብ ጥያቄ ያነገበ የጊዜ ጉዳይ ካልሆነ በስተቀር ለድል መብቃቱ ኣይቀሬ እንደሆነ፣ ግን ደግሞ ከድል ቦሃላ ሻዕብያ ካለው የፀረ ህዝብና የፀረ ዴሞክራሲ ባህሪ የተነሳ ለድርጅታችን ብቻ ሳይሆን ለኤርትራ ህዝብም ስትራቴጂያዊ ጠላት እንደሆነ ሳይንሳዊ በሆነ ትንታኔ ተደመደመ፡፡

ይህ ድምዳሜ ከተደረሰ ቦሃላ በህወሓት ማእከላይ ኮሚቴው አንድ መሰረታዊ ጥያቄ ተነሳ፡፡ ጥያቄውም፡- ይህ ድርጅት በትንታኔያችን በደረስንበት ድምዳሜ መሰረት ፀረ ህዝብና ፀረ ዴሞክራሲ ከሆነ እንዴት ኣብረን መስራት እንችላለን፣ ከፀረ ህዝብ ድርጅት አብሮ መስራት ራስን የፀረ ህዝብ ተግባራት መፈፀም ወይም መደገፍ ኣይሆንም ወይ? ሰፊ ክርክርና ዓመታት የፈጀ ውይይት ከተደረገ ቦሃላ ለጥያቄዎቹ ምላሽ አገኙ፡፡

እነሱም ፡- ለመጀመሪያው ጥያቄ ሻዕብያ ምንም እንኳ ፀረ ህዝብና ፀረ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት ቢሆንም ቢያንስ ኣንድን የህዝብ ጥያቄ አንግቦ የኤርትራ ህዝብን ከጎኑ ያሰለፈ ድርጅት በመሆኑ በዛች የህዝብ ጥያቄ የሚያገናኘን ነገር አለ፡፡ እሱም የጋራ ጠላታችን የሆነው የሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ የትግል በሮች ጥርቅም አድርጎ የዘጋው ሰው በላው የደርግ ስርዓት በጋራ ለማንበርከክ ወይም ለመደምሰስ አብረን የምንሰራበት ዕድል ኣለ፡፡ ስለዚህ በምናምንበት ኣብረን እየሰራን በማናምንበት ደግሞ ልዩነታችንን ይዘን በጋራ መታገል እንችላለን፡፡ ስለዚህ ሻዕብያ ፀረህዝብና ፀረዴሞክራሲያዊ ድርጅት በመሆኑ ከሱ ጋር ሊኖረን የሚችል ግንኙነት ታክቲካዊ (የጋራ ጠላት በመታገል) እንጂ ስትራቴጂካዊ ሊሆን አይችልም፡፡

ቀጥሎ ሌላ ጥያቄ ምናልባትም የህወሓት አመራር ሊከፋፍል የሚችል ቁልፍ ጥያቄ ተነሳ፡፡ ሁለተኛው ጥያቄ፡- ይህን ትንታኔያችን ትክክለኛና ሳይንሳዊ ቢሆንም፣ አሁን ባለንበት ደረጃ አቋማችን ወዳጅና ጠላት እንዲያውቀው ለህዝብ ይፋ ይደረግ አይደረግ የሚሉ ነበሩ፡፡ ይህም ከብዙ ክርክርና ውይይት ቦሃላ አንድን ህዝባዊና ዴሞክራሲያዊ ድርጅት ህዝባዊና ዴሞክራሲያዊ ነው የሚባለው ያለውን ዓላማና ፕሮግራም ምንም ሳይደብቅ ለህዝብ ግልፅ ማድረግና ህዝቡ የራሱ ዓላማ ያነገበ ድርጅት መሆኑ ተረድቶ በትግሉ እንዲሳተፍ ሲያደርግ ነው፡፡ ያለህን ዓላማና ፕሮግራም ደብቀህ መጓዝ በራሱ ፀረ ህዝብነት ነው፡፡ የአንድን ድርጅት ለድል የሚያበቃ ዋናው ነገር ከውስጥ ይዘትና ጥንካሬ እንጂ የውጭ ድጋፍ ማግኘት ወይም ማጣት አይደለም፡፡ ስለዚ በዚህ ህዝባዊ አቋማችን የሚከፋው ቢኖር ፀረ ህዝብ የሆነ ብቻ ነው ስለዚ አቋማችን ይፋ ይደረግ፣ አቋማችንን ኣይቶ ከኛ በጋራ በምንስማማባቸው ነገሮች ኣብሮ መስራት የሚፈልግ በራችን ክፍት ነው ተባለ፡፡

ይህ አቋም ይፋ ከተደረገ ቦሃላ እንደተፈራው ሻዕብያ ካለው የፀረህዝብና የፀረ ዴሞክራሲ ባህሪው በመነሳት በንቀት መንፈስ እናንተ የት የነበራቹ ናችሁ እኛን የምትፈርጁ፡፡ አቅማቹና ልካቹ የማታውቁ ዓቅመ ቢሶች፡፡ ከእንግዲህ ከናንተ ጋር የሚኖረን ግንኝነት በቃ አከተመ ሲሉ፡፡ አብረን የምንሰራበት ጉዳዮች ኣሉ፣ ቢያንስ የጋራ ጠላት ከሆነውን ደርግ በመደምሰስ በጋራ መስራት እንችላለን ስለዚ አትቆጡ ሲባሉ በትምክህትና በንቀት ጠቅላላ በራቸው ዘጉብን፡፡ በዚህ ጊዜ ነበር የትግራይ ህዝብ በ1977 ዓ.ም. ለኣስከፊ ድርቅና ረሃብ ተጋልጦ ሂይወቱን ለማትረፍ ወደ ሱዳን በሚያደርገው ጉዞ፣ በሰማይ የደርግ የጦር ጄቶችና ሄሊኮፕተሮች የቦንብ ናዳ ሲያወርዱበት በመሬት ደግሞ የሻዕብያ ሰራዊት መንገድ ላይ መሽጎ ወደ ሱዳን እንዳይገባ በመከልከል በረሃብና ውሃ ጥም እንዲያልቅ ኣደረገ፡፡

በትንታኔ የተደረሰው የሻዕብያን ፀረ ህዝብነት ባህሪ በ1977 ዓ.ም. ነበር በተግባር ባህሪው ምን ያህል ፀረ ህዝብ እንደሆነ በትግራይ ህዝብ በፈፀመው ኣሳፋሪ ተግባር የታየው፡፡ ይኸውም በብዙ ሺ የሚቆጠረውን በረሃብ የተሰቃየ በብዙ መቶዎች ኪሎሜትር ያለ በቂ ምግብና ውሃ ተጉዞ ድንበር ላይ የደረሰ ህዝብ በነፃ መሬቴ ኣታልፍም በማለት ሻዕብያ በትግራይ ህዝብ ላይ ጥቁር ጠባሳ ጣለ፡፡ በዛን ጊዜ ከከፍተኛ ኣመራር እስከ ተራ ታጋይ ደሙ ያልፈላ የህወሓት ኣባል ኣልነበረም፡፡ ነገር ግን ህወሓት እንደ ድርጅት በሳልና የሰከነ ኣመራር በመስጠት ችግሩ ታለፈ፡፡ በዛን ጊዜ በስሜት ታውሮ በቀጥታ ሻዕብያን እንዳመጣጡ በትዕቢት ለመመለስ ቢሞከር ኑሮ በተራበው ህዝብና በታጋዮች ኣላስፈላጊ ከባድ መስዋእትነት ከመክፈልና የደርግን ዕድሜ ከማራዘም ሌላ ፋይዳ ባልነበረው ነበር፡፡

ሻዕብያ በትግራይ ህዝብ ላይ የፈፀመውን ፀረ ህዝብ ተግባር ከህወሓት ጋር በገባው አተካራ ተነስቶ የፈፀመው የእልህ የአጋጣሚ ክስተት ሳይሆን ከፀረ ህዝብና ፀረ ዴሞክራሲ ባህሪው በመነሳት የፈፀመው ተግባር ነው፡፡ እንደዚህ ኣይነት ፀረ ህዝብና ፀረ ዴሞክራሲ ባህሪ ያለው ድርጅት ደግሞ እወክለዋለሁ በሚለው ህዝቡም ቢሆን ባህሪውን ማሳየቱ ኣይቀርም፣ የኣፈፃፀም መርሆው ይህ ባህሪው ነው ና እነሆ የኤርትራ ህዝብ ነፃነት ኣይሉት ባርነት እየተሰቃየ ይገኛል፡፡

ሻዕብያ ይህን ያህል ኣሳፋሪ ድርጊት በትግራይ ህዝብ ላይ ኣድርሶ ሲያበቃ ከ3 ዓመታት ቦሃላ የህወሓትን ጥንካሬና ግስጋሴ በማየት ራሱ ሻዕብያ ጥርቅም ኣድርጎ የዘጋው በር በራሱ ከፍቶ እንደገና በጋራ እንስራ የሚል ጥያቄ ኣቀረበ፣ ህወሓት በቂም በቀል ሳይሆን በትክክለኛና ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ ተተንትኖ በተቀመጡት መርሆዎች የሚመራ ድርጅት በመሆኑ ቅድም በተቀመጠው መሰረት ሻዕብያ ስትራቴጂክ ወዳጅ እንዳልሆነ በትንታኔ ብቻ ሳይሆን በተግባር የተረጋገጠ ቢሆንም ስልታዊ ግንኙነት በመፍጠር የድህነትና ኋላ-ቀርነት ዘበኛና ቀንደኛ የህዝብ ጠላት የሆነውን ደርግ ዕድሜውን ማሳጠር ይቻላል የሚል ድምዳሜ ስለነበር ግንኝነቱ ተፈጥሮ መጀመሪያ ህወሓትና ሻዕብያ ከዛም ኢህኣዴግ ከተቋቋመ በሃላም ግንኝነቱ ኢህኣዴግና ሻዕብያ ሆኖ ቀጠለ፡፡

ህወሓት ደርግን ለመደምሰስ ቁልፍ ሚና ያላቸው መጠነ ሰፋፊ የማጥቃት ዕቅዶች ነድፎ በዚህ ላይ የሻዕብያ ሚናም ምን መሆን እንዳለበት መግባባት ላይ ለመድረስ ከሻዕብያ ጋር ውይይት ሲደረግ በሻዕብያ በኩል ተስፋ ኣስቆራጭና ትግሉ በነበረበት ኣካሄድ (በሽምቅ ውግያ) እንደሚቀጥል ነበር የገለፀው፡፡ የቀድሞ የኢትዮጵያ ኢታማጆር ሹም ሌ/ጀነራል ፃድቃን ገ/ትንሳኤ ኣንድ ወቅት ለሆርን ኣፌርስ በሰጡት ቃለ መጠይቅ እንዳረጋገጡት በዛን ጊዜ ሻዕብያ የሰጣቸው መልስ “ሞኞች ናችሁ እንዴ፣ በየጊዜው ከ12 ክፍለሃገር የሰው ሃይል በግፍ እየመለመለ የሚመጣው ደርግ እንዴት በኣጭር ጊዜ 2 ክፍለሃገር ለ12 ክፍለ ሃገር እናሸንፋለን ብላቹ ታስባላቹ” ነበር ያለው፡፡

የሻዕብያ መልስ ተስፋ ኣስቆራጭ ቢሆንም ህወሓት ከዛም ኢህኣዴግ ቀድሞ በተቀመጠ ስልታዊ ግንኝነት ተጠናክሮ እንዲቀጥል በማድረግ በስተመጨረሻ ደርግን ለመደምሰስ በቅተዋል፡፡ ኢህኣዴግ በጥር ወር 1983 ዓ.ም. ባደረገው ኮንፈረንስ ደርግ ክረምት ከመግባቱ በፊት በመደምሰስ ኣርሶ ኣደር ታጋይና ምልሻ ወደ ግብርናው መመለስ ኣለበት በማለት የደርግን ውድቀት ኣስቀድሞ ባቀደው መሰረት ግንቦት 20፣ 1983 ዓ.ም. ከህዝቡ ጋር ድሉን ሲቋደስ ሻዕብያ ደርግ ከመውደቁ 2 ዓመት በፊት በጨለማ ሆኖ የድል ጭላንጭል የሚባል ነገር ኣይታየኝም ሲል የነበረው ከ2 ዓመት ቦሃላ የደርግን ውድቀት እውን ሲሆን ሻዕብያ ያላሰበው ነገር ቶሎ በማግኘቱ እነሆ እስከ ዛሬ ድረስ ከእንቅልፉ ሳይቧንን ነፃነትን በህልሙ እያጣጣመ ይገኛል፡፡

2/ የኤርትራና የኢትዮጵያ ግንኙነት ከደርግ ውድቀት በኋላ

ከደርግ ውድቀት ቦሃላ ኣገራችን የነበረውን የደርግ የኣፈና መዋቅሮች በሙሉ በማፈራረስ በምትኩ የኣብዮታዊ ዴሞክራሲ መዋቅሮች እንዲተኩ በማድረግ፣ ለዘመናት ዴሞክራሲያዊና ሰብኣዊ መብቶች ታፍነው የኖርባት ኣገር ሰብኣዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ተከብረውባት የታጠቁና የተደራጁ ሃይሎች በሰላም ገብተው ሰላማዊ ትግል እንዲያደርጉ፣ በሚቋቋም የሽግግር መንግስት እንዲሳተፉ ጥሪ ቀርቦ ሁሉም /ከደርግና ኢህኣፓ/ ውጭ ኦነግን ጨምሮ ኣብዛኞቹ በሽግግሩ ጊዜ ተሳታፊ ሆኖዋል፡፡ ሻዕብያ በታዛቢነት የተሳተፈበት በዚህ ስብሰባ የሽግግሩ ጊዜ ቻርተር በማፅደቅ ከሁሉም ተቋዋሚ ድርጅቶች የተውጣጣበት የሽግግር መንግስትና ተቋቋመ፡፡

ሻዕብያ ኤርትራን በሃይል ነፃ ብያወጣም፣ በስተመጨረሻ የኤርትራ ዕጣ ፈንታ በኤርትራ ህዝብ መወሰን ኣለበት በሚል የኤርትራ ህዝብ ድምፅ የሚሰጥበት (ሪፈረንደም) ዕድል ተሰጥቶት 99.8% ነፃነትን በመምረጥ ኤርትራ ራሷን የቻለች ነፃ መንግስት መስርታ በዓልም ደረጃ ዕውቅና ተሰጥቷት 53ኛ የኣፍሪካ አገር ለመሆን በቅታለች፡፡ ኤርትራና ኢትዮጵያ የተለያዩ ሁለት መንግስታት ቢሆኑም ሰፊ መሰረት ያለው በማሕበረ ኤኮኖሚያዊና መስኮች ትብብር ተደርጓል፡፡ ከተደረጉ ትብብሮች መካከል ሁለቱም ኣገራት “ብር” በጋራ እንዲጠቀሙ፣ በሁለቱም ኣገራት የሚደረገው የኢኮኖሚ ግብይት በብር እንዲለዋወጡ፣ ኢትዮጵያ ሁሉም የኤርትራ ወደቦች እንድትጠቀምና የአገልግሎት ክፍያ በብር እንዲከፈል፣ እንዲሁም የጋራ የመከላከያ ትብብር ስምምነቶች የሚጠቀሱ ናቸው፡፡

ሻዕብያ ላይ ለመጥቀስ እንደተሞከረው በቅርብ ርቀት የድል ጭላንጭል የሚባል ነገር ፈፅሞ ኣይታየኝም ሲል እንደነበር እና ግን ደግሞ በኢትዮጵያ ህዝቦች ትግል ቁልፍ ሚና የደርግን ዕድሜ እንዲያጥር በመደረጉ ሻዕብያ ባላሰበው ጊዜ ድል በማግኘቱ እራሱን ከዓቅሙ በላይ ኣግዝፎ ማየት ጀመረ፡፡

ሻዕብያ ገና ከአመሰራረቱ ጀምሮ ባህሪው ፀረ ህዝብና ፀረ ዴሞክራሲ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ፣ ከግማሽ ሚልዮን በላይ ሰራዊት ያለውና በሁለመናው ትጥቁ በአፍሪካ ወደር የሌለው የሚባለው የደርግ ሰራዊት በኢትዮጵያ ህዝቦች የተባበረ ትግል ቁልፍ ሚና በመደምሰሱ ለሻዕብያ ልዩ ስሜት ፈጠረለት፡፡ ከአፍሪካ ተወዳዳሪ የሌለው ሰራዊት ማሸነፍ ማለት በሻዕብያ አስተሳሰብ ለ12 ክፍለሃገር 2 ክፍለሃገር እንዳሸነፉ በሌላ ኣነጋገር ሻዕብያ ለኢትዮጵያ ህዝብ እንዳሸነፈ ኣድርጎ ወሰደው፡፡ ይህ ማለት ደግሞ እራሱ በአፍሪካ ልዩ ቦታ በማስቀመጥ የአፍሪካ ልዩ ሃይል (ሞኒተር)፣ ፈላጭ ቆራጭ አድርጎ ወሰደ፡፡ ይህ በኣስተሳሰብ ደረጃ ብቻ ሳይሆን በተግባርም ማሳየት ጀመረ፡፡ ይኸውም ለአጎራባች ኣገሮች ሁሉም እንደ ዕብድ ውሻ እየዞረ መላከፍ ጀመረ፡፡ በስተመጨረሻም “ውርደቷን የተቃረበ አይጥ የድመት አፍንጫ ታሸታለች” እንዲሉ የኢትዮጵያ ድንበር ደፈረ፣ የሻዕብያ ገናናነት ዓስር ዓመት ሳይሞላው በ7 ዓመት አከተመለት፣ ኤርትራ በሻዕብያ ኣገዛዝ ምክንያት ዜጎችዋ የሚፀየፍዋት አገር ሆና ቀረች፡፡

3/ የኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት መነሻ

ሻዕብያ ከፀረ ህዝብና ፀረ ዴሞክራሲ ባህሪው የተነሳ በኣቋራጭ የአጎረባች ኣገሮች የሰውና የተፈጥሮ ሃብትን በመጠቀም ኤርትራን ሲንጋፖር የማድረግ ህልሙን እውን ለማድረግ ህጋዊና ህገወጥ ተግባራትን በአንድ ላይ ኣጣምሮ መተግበር ጀመረ፡፡ በተለይ በውጭ ምንዛሪ ግብይት ላይ በጥቁር ገበያ ገብቶ ማሻሻጭ ተያያዘው፤ የኮንትሮባንድ ተግባራት በሁሉም ኣጎራባች ኣገሮች በስፋት መግባት ጀመረ፡፡ በአንድ ወቅት በኮንትሮባንድ ኤርትራ የታወቀች የቡና ላኪ አገር እስከመሆን ደርሳ ነበር፡፡ የሻዕብያ መንግስት ካለው ፀረ ህዝብና ኣጭበርባሪነት ባህሪ የተነሳ የአንድ ቀን ጥቅም ኣለው ከተባለ የፈለገውን መስዋእት በመክፈል ለማግኘት የሚጥር ሃይል ሆነ፡፡

በሌላው በኩል ደግሞ በኢትዮጵያ ወገን በህግና በህገመንግስት የሚመራ መንግስት እንደመሆኑ መጠን፣ ካለው ህዝባዊና ዴሞክራሲያዊ ባህሪያት የተነሳ ኤርትራን ጨምሮ ከአጎራባች ኣገሮች የሚያጋጥሙ ችግሮች በመቻቻልና በጋራ ጥቅምን በማረጋገጥ መንገድ እንዲፈቱ፣ የረጅም ጊዜ ጥቅምን በማየት ትናንሽና ጥቃቅን ችግሮችን በቸልታ በማለፍ በግንኝነቱ ላይ ችግር እንዳያጋጥም ቢሞከርም፣ የሻዕብያ ኣጭበርባሪ ተግባራት ሊቀንሱ ቀርቶ በስፋት እየተጧጧፈ መጣ፡፡

የሻዕብያ ኣጭበርባሪነት ተግባር መልኩን ቀይሮ ለመቀጠል በተለይ በገንዘብ ኣጠቃቀም ላይ ኣዲስ ተንኮል ፈጥሮ ብቅ ኣለ፡፡ እሱም፡- ኤርትራ እንደ ማንኛውም ነፃ አገርና መንግስት የራስዋ ናቅፋ የሚባል ገንዘብ እንዲኖራት እንደምትፈልግ፤ ግን ደግሞ የተንኮሉ ማጠንጠኛ በኢትዮጵያና በኤርትራ ያለውን ግንኝነት እንዳይሻክር የነበረውን የኢኮኖሚ ትስስር የበለጠ ተጠናክሮ እንዲቀጥል በኤርትራና በኢትዮጵያ ሁለቱም ገንዘቦች ማለትን ብር እና ናቅፋ ያለምንም ገደብ አንድ ለአንድ እየተቀያየሩ በነፃነት እንዲሰሩ የሚል ሃሳብ አመጣ፡፡

ሃላፊነት በማይሰማው፣ በህግ በማይመራው፣ በኮንትሮባንድና በጥቁር ገበያ የሚሳተፍ መንግስት የሚያትመው ገንዘብ እንደልቡ በአገራችን ገብቶ ይገበያይበት ማልት የአገርን ሃብት ለአጭበርባሪው ሻዕብያ ኣሳልፎ መስጠት ማለት ነው፡፡ ሃላፊነት የሚሰማውና በህግ የሚመራ መንግስት በአገሪቱ ውስጥ ኢኮኖሚውን ማንቀሳቀስ የሚችለውን ትክክለኛውን የገንዘብ መጠን በማወቅ በዛ ልክ እያተመ ኢኮኖሚውንና የዋጋ ንረትን (ኢንፍሌሽንን) በመቆጣጠር ጤነኛ ኢኮኖሚ እንዲኖር ያደርጋል፡፡ ኢኮኖሚውን መሸከም ከሚችለው በላይ ሃላፊነት በጎደለው መንገድ የገንዘብ ኖቶችን ካባዛ ግን የዋጋ ንረቱ ኣሻቅቦ የኢኮኖሚ ቀውስ መፈጠሩ ግልፅ ነው፡፡

የሻዕብያ ተንኮል አንድ ናቅፋ በአንድ ብር እንዲለዋወጡ የመጠየቁ ሚስጥር፤ ለአጭር ጊዜም ቢሆን በኤርትራ (የ5 ሚልዮን ህዝብ አገር) ኢኮኖሚው ከሚሸከመው በላይ የናቅፋ ኖቶችን ሃላፊነት በጎደለው እንደ ሎተሪ ወረቀት በማባዛት በኢትዮጵያ (የ80 ሚልዮን ህዝብ አገር) አንድ ናቅፋ ለአንድ ብር በሚል ስምምነት አምጥቶ በማፍሰስ ከመጠን በላይ በታተመው ገንዘብ ምክንያት የሚፈጠረውን የዋጋንረትና የኢኮኖሚ ቀውስ ኢትዮጵያ እንድትሸከመውና በዛው የኢትዮጵያን ሃብት ለመዝረፍ ነበር፡፡ ሻዕብያ ብርን በጋራ በመጠቀም ላይ የጀመረውን የኮንትሮባንድና የጥቁር ገበያ የማጭበርበር ስራ ኣልበቃ ብሎት (ብሩ በኢትዮጵያ መንግስት ስለሚታተም)፣ የራሱ ገንዘብ (ናቅፋ) እሱ በሚፈልገው መጠን በማተም በኢትዮጵያ እያራገፈ ዝርፍያውን አጠናክሮ ለመቀጠል ነበር ዋናው ሴራ፡፡

በኢትዮጵያ በኩል የተሰጠው ምላሽ ኤርትራ እንደ ነፃ አገር የራስዋ ገንዘብ እንዲኖራት በመርህ ደረጃ ትክክልና የምትቀበለው እንደሆነ፣ ባላደጉ አገራት የተለያዩ የኢኮኖሚ ፖሊሲዎች እያላቸው በጋራ አንድ ገንዘብ (ብር) መጠቀም ኣስቸጋሪ እንደሆነ፣ ገንዘብ ዋነኛ የሞኒታሪ ፖሊሲ መሳርያ እንደሆነና ይህ ማለትም አንድን አገረ መንቀሳቀስ የሚገባውን የገንዘብ መጠን የሚወስንበት እንደሆነ፣ ስለዚ የኤርትራ መንግስትም ይህን የሞኒታሪ ፖሊሲ ለመተግበር የራሱ ገንዘብ መኖሩ ትክክል እንደሆነ ድጋፋችን ስንሰጥ፣ የገንዘብ አጠቃቀም ላይ ግን አንድ ለ አንድ የሚለው ትክክል እንዳልሆነ፣ የኢትዮጵያ ፖሊሲ በገንዘብ ልውውጥ እንደ ማንኛውም የአፍሪካ አገር በውጭ ምንዛሪ መሆን እንዳለበት ተቃውሞ አቀረበ፡፡

በዚህ የኢትዮጵያ ውሳኔ የተከፋ ሻዕብያ ሌላ ሰንካላ የዘረፋ ሃሳብ አቀረበ፡፡ እሱም በኤርትራ ያለው ብር በናቅፋ ስለምንቀይረው የተቀየረውን ብር ሰብስበን ኢትዮጵያ ከተስማማች የተሰበሰበውን ብር በውጭ ምንዛሪ ቀይራ እንድትሰጠን (Plan A) ካልተስማማች ደግሞ በኤርትራ ውስጥ የተሰበሰበው ገንዘብ በመዋቅራችን በኩል ኢትዮጵያ ውስጥ እንዲበተንና ሃብት እንዲዘርፉበት (Plan B) በድብቅ በማቀድ፣ የብሩ ምትክ የውጭ ምንዛሬ ጥያቄ አቀረበ፡፡

በአንድ አገር የሚዘዋወረው ገንዘብ የሚወክለው የአገሪቱ ሃብትና ኢኮኖሚ ነው፣ ኤርትራ ውስጥ ያለውን ብር የሚወክለው ኤርትራ ውስጥ ያለውን ሃብት ነው ስለዚህ በምን ስሌት ነው መንዝረን የምንሰጣቹ? በብር የነበረውን የሃብት ውክልና በናቅፋ ሆነ ስለዚህ እንዴት ለወረቀት ዶላርን ቀይረን እንሰጣቹሃለን? ተባሉ፡፡ ኢትዮጵያም ከሻዕብያ ኣጭበርባሪነት ባህሪ በመነሳት (Plan B) እንደሚኖር ኣስቀድማ በመገምገም ሻዕብያ ሳያውቀው በሚስጥር የብር ለውጥ ለማድረግ ዝግጅት ጀመረች፡፡ ሻዕብያ ብርን በናቅፋ ለመቀየር ማስተናገድ ሲጀምር ኢትዮጵያም የብር ኖት የቀለም ለውጥ ስለሚደረግና ህዝቡ ያለውን የብር ኖት ወደ ባንኮች ሄዶ እንዲለወጥ አሳሰበች፡፡

ሻዕብያ ይህን ሲሰማ መሰብሰብ የጀመረውን የኢትዮጵያ ብር በጆንያ ሞልቶ በመዋቅሩ በኩል ወደ ኢትዮጵያ በማስገባት ልክ እንደ የግለሰብ ብር ኣድርጎ በኢትዮጵያ ባንኮች ለማስቀየር ሊያስገባ ሲሞክር በህዝብና በፀጥታ ሃይሎች ንቁ ተሳትፎ ሊከሽፍ ችለዋል፡፡ በዚህ ጊዜ ሻዕብያ ሁሉንም የዝርፍያና የማጭበርበሪያ መንገዶች ሲዘጋበት በጣም ተበሳጨና ኢትዮጵያን በሃይል ኣስፈራርቶ ሁሉንም የማጭበርበርና የዝርፍያ በሮችን ለማስከፈት በድንበር ሰበብ ኢትዮጵያን ወረረ፣ የኤርትራ ሰራዊት መጀመሪያ ባድመ ሲይዝ ቀጥሎ ሁሉም የድንበር ቦታዎች ዘልቀው የኢትዮጵያ ቦታዎች ወረው ያዙ፡፡ በዚህ ጊዜ ነበር በትዕቢት ተወጥረው ከባድመ ወጣን ማለት ፀሃይ የተፈጥሮ ዑደትዋን አቆመች ማለት ነው ብለው ጠቅላላ የሰላም መንገዶችን ሁሉ ዘጉ፡፡

በመጨረሻ የኢትዮጵያ መንግስት የሻዕብያን ወረራ ኣስመልክቶ ለፓርላማ በማቅረብ ሻዕብያ በማን አለብኝነትና ሃላፊነት በጎደለው የኢትዮጵያ ሉኣላዊ መሬት በሃይል እንደወረረ በማሳወቁ፣ ፓርላማውም፣ ይህ ወረራ የድንበር ጉዳይ ኣይደለም፣ የድንበር ጉዳይ የሚፈታው በጦርነት ኣይደለም፣ የድንበር ጉዳይ የሚፈታው በድርድር ካልሆነም በኣለም ኣቀፍ ፍርድ ቤት ነው፡፡ ስለዚህ ኣሁን ኢትዮጵያ እየጠየቀች ያለው ባድመ የኔ ነው ወይም የድንበር ጥያቄ ኣይደለም፤ ኢትዮጵያ እየጠየቀች ያለው ክብሬን ተደፈረ፣ ሉኣላዊነቴን ተደፈረ፣ ስለዚህ ከሰላም ድርድሩ በፊት ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ወረራው እንዲቀለበስ (Status co ante) ማለትም ሻዕብያ ከወረረው ቦታ ባፋጣኝ እንዲወጣ፣ የሚጠይቀው የድንበር ጥያቄ ካለም ህጋዊና ሰላማዊ በሆነ መንገድ በድርድር እንዲፈታ፣ ካልሆነ ግን የኢትዮጵያ መንግስት ሉኣላዊነቱን በሃይል እንደሚያረጋግጥ በማሳወቅ ለኢትዮጵያ ህዝብም ዳርድንበሩን ለማስከበር ጥሪ ኣቀረበ፡፡

ሻዕብያ ግን በደርግ ያገኘውን ድል ትዕቢት ፈጥሮለት ጠቅላላ ኣፍሪካን በሙሉ ኣሳንሶ በማየት እሱ ራሱ የአፍሪካ ልዩ ሃይል፣ የአፍሪካ እስራኤል፣ ኤርትራዊ ማለት ልዩ ተፈጥሮና መለኮታዊ ሃይል እንዳለው ኣድርጎ በመቁጠር ለሰላም ድርድር ሊጠይቁት የሄዱ የኣፍሪካ መንግስታት መሪዎች እየሰደበና እያዋረደ ነበር የሚሰዳቸው፡፡ ደርግን ማሸነፍ ማለት የኢትዮጵያ ህዝብን ማሸነፍ ኣድርጎ ነበር የወሰደው ምክንያቱም በሻዕብያ ኣስተሳሰብ የደርግ ውድቀት ማለት 2 ክፍለ ሃገር ለ12 ክፍለ ሃገር የተደረገ የህዝቦች ጦርነት ነው ብሎ የሚያስብ በመሆኑ፡፡

የኢትዮጵያ ህዝብ ከጫፍ እስከ ጫፍ ሻዕቢያ ባልገመተው ደረጃ ህዝቡ በቁጣ ተነሳ፡፡ በስተመጨረሻም ሻዕብያ ሁሉም የሰላም መንገዶች በመዝጋቱ የኢትዮጵያ ሰራዊት ሻዕብያ በቆፈረው ጉድጋድ ቀብሮ ዳርድንበሩ ኣከበረ፣ የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ኤርትራ ውስጥ በመዝለቅ ለሻዕብያ ኣይቀጡ ቅጣት ቀጥቶ ሻዕብያ በ1974 ዓ.ም. እንዳደረገው ዳግም ስልታዊ ማፈግፈግ በሚል ጓዙን ጠቅልሎ ወደ ናቅፋ በረሃ እንደሚሄድ በሚድያው ሳይቀር ገልፆ ነበር፡፡ የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ሻዕብያ ታክሞ የማይድን ቁስለኛ መሆኑን ካረጋገጠ ቦሃላ እዛው መሬቱ ላይ ትቶት መጣ፡፡ ሻዕብያ ተገዶ ወደ ሰላም ድርድር መጣ ከባድመና ከሌሎች የኢትዮጵያ ቦታዎች ኣልወጣም ሲል የነበረው ሻዕብያ በጠቅላላ ከድንበሩ 25 ኪ.ሜ. እንዲርቅና ይህ 25 ኪ.ሜ. ደግሞ የፀጥታ ቀጣና ሆኑ የተባበሩት መንግስታት እንዲረከቡት ተስማማ፣ የኢትዮጵያ ሰራዊት ቦታው ለተባበሩት መንግስታት ሰላም ኣስከባሪ ኣስረክቦ ወደ ቦታው በሰላም ተመለሰ፡፡

4/ ግን የድንበር ችግር አለ ወይስ የለም?

የኣፍሪካ ኣገራት በባዕዳውያን ቅኝ ገዢዎች ስር ሲተዳደሩ ገዢዎች ለነሱ ኣገዛዝ በሚመች መንገድ ድንበሩን ሲያካልሉት ኣንድ ህዝብ በሁለት ሶስት ወይም ከዛ በላይ ኣገራት በመከፋፈል፤ ኣንድን እምነት፣ ኣንድን ባህል ያለው ህዝብ በሁለት ሶስት ቦታ በመከፋፈል፣ ለኣተረጓጎም ክፍተት የሚሰጡ ውሎች በመዋዋል፣ ለአንድን ቦታ የተለያየ ስም በመስጠት፣ ኣንድን ስም ለተለያዩ ቦታዎች በመስጠት ወዘተ የድንበር ኣካለል ችግር ያልተውለት የአፍሪካ ኣገር የለም ቢባል ማጋነን ኣይሆንም፡፡ እኛ ኢትዮጵያውያን በቅኝ ኣገዛዝ ኣልተገዛንም በማለት የምንኮራበት ታሪካችን ቢሆንም በድንበር ኣካለል ግን የቅኝ ገዢዎች ጦስ ኣልደረሰንም ማለት ኣይደለም፡፡ ከኣጎራባች ኣገራት ጋር ያለንን የድንበር ወሰን ኣካለለ ከቅኝ ገዢዎቻቸው ጋር የተደረጉ ስምምነቶች ከመሆናቸው ጋር ተያይዞ እላይ የተጠቀሱትን የድንበር ኣካለል ችግሮች እኛም ይነኩናል፡፡ ስለዚ የቅኝ ገዢዎች ያካለሉት ድንበር ችግር የሌለበት የለም ማለት ይቻላል፡፡

የኛ የድንበር ጉዳይ ከተነሳ ከሁሉም ኣጎራባች ኣገሮች በሁለታችን ኣገራት ስምምነት የተደረሰበት በትክክል የተከለለ ድንበር የለንም፡፡ ኣሁን በተጨባጭ ያለን የድንበር ወሰን/ክልል ስምምነት ጎሮቤቶቻችን ነፃ ከመውጣታቸው በፊት ከቅኝ ገዢዎቻቸው የተደረገ ስምምነት ነው፡፡ ኣሁን ለመጀመሪያ ጊዜ በኣለም ኣቀፍ ፍርድ ቤት የተወሰነ ድንበር ያለን ከኤርትራ ብቻ ነው፡፡ ያለን የድንበር ወሰን ከቅኝ ገዢዎች የተደረገ ስምምነት ቢሆንም ግን ብዙ አከራካሪ የድንበር ጥያቄዎች በሁሉም ወገኖች ኣሉ፡፡

የኣፍሪካ ኣገራት ከረጅምና መራራ ትግል ቦኋላ ከቅኝ ገዢዎቻቸው ነፃ ቢወጡም፣ ቅኝ ገዢዎች ኣፍሪካውያን እርስ በራሳችን የማያስማማ ብሎም ወደ ግጭት የሚያስገባ የድንበር ስምምነቶች መርዝ ትተውልን የሄዱ በመሆኑ ትልቅ ስጋት ነበር፡፡ ይህ የቅኝ ገዢዎች የድንበር ስምምነትና ውል ኣንድን ብሄር፣ ሃይማኖት፣ ጎሳ፣ ቤተሰብም ሳይቀር በሁለት ሶስት ኣገር ከፋፍለው ነው ያቆዩን፡፡ ይህ ትተውልን የሄዱት የድንበር ስምምነቶች እርስ በርሱ የሚምታታ፣ ፍትሃዊነት የጎደለው፣ በሁሉም ወገን ቋንቋ የተለያዩ ትርጉም የሚሰጥ በመሆኑ በብልህነትና በኣስተዋይነት ካልተያዘ በጣም ኣደገኛ እንደሆነ በኣፍሪካ ሃገራት መግባባት ተደርሷል፡፡ የድንበርን ግጭቶችን በመፍታት ኣኳያ ልንከተለው የሚገባ መርሆ ኣስመልክቶ በኣፍሪካ ኣንድነት ድርጅት ኣስተባባሪነት የተደረሰው ስምምነት በ1902 እና በ1908 እአአ የተደረጉ ስምምነቶችን መሰረት በማድረግ ሰላማዊ በሆነ መንገድ ብቻ በመፍታት ዋናው ትኩረታችን ግን ድህነትን ማጥፋት ላይ እንዲሆን የሚል መግባባት ተደርሷል፡፡

በዚህ መሰረት እኛም ከሁሉም ኣጎረባች ኣገሮች (በኛና በሱዳን፣ በኛና በኬንያ፣ በኛና በሱማሊያ፣ በኛና በጁቡቲ) የድንበር ውዝግብ ሊያስነሱ የሚችሉ ችግሮች ቢኖረንም ግን እንደ ኣፍሪካ ዋነኛ ችግራችን የድንበር ችግር ስላልሆነ፣ በያለንበት የያዝነው ይዘን ቆይተን ኣስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ በሁለታችን ወገኖች ስምምነት ተደርጎ ሰላማዊ በሆነ መንገድ በድርድር ወይም ደግሞ በኣለምኣቀፍ ፍርድቤት እናካልላለን በሚል ስምምነት ነው ያለነው፡፡

ታዲያ ሻዕብያ ይህን ስምምነት ሲደረግ ስላልነበረ ነው ወይስ ስላላወቀ ወይስ ስለማያምንበት ነው የወረረን፤ የሻዕብያ ጥያቄ የባድመ ጥያቄ ወይም የዘላንበሳ ጥያቄ ወይም የድንበር ጥያቄ ሳይሆን ኢህአዴግ ወይም የኢትዮጵያ መንግስት የዘጋቸውን የዝርፍያና የማጭበርበሪያ በሮች ለማስከፈትና የኢትዮጵያ ሃብትና ንብረት ለመዝረፍ ነው፡፡ ድንበር ሽፋን ነው፡፡ ዋናው ምክንያቱ ሻዕብያ እንደሚለው በትግርኛ “ኤርትራ ናይ ቤንትና ኢትዮጵያ ናይ ኩላትና“ በኣማርኛ ሲተረጎም “ኤርትራ የብቻችን ኢትዮጵያ የጋራችን“ ይህ ማለት ደግሞ በሩን ክፈቱ እንደፈለግን እንዋኝበት ማለት ነው፡፡ ስለዚህ ጦርነቱ የኢትዮጵያን ሃብት ኣዘርፉኝ ኣናዘርፍም በሚል ክርክር ነው ወደ ጦርነት የተገባው፡፡

እነዚህ ፍላጎቶች (የኢትዮጵያ ህዝብ ሃብት ለመዝረፍ መፈለግና፣ የዝርፍያ በሮችን መዝጋት) የማይታረቁ ፍላጎቶች ናቸው፡፡ ስለዚ እነዚህ ፍላጎቶች እስካሉ ድረስ በሁለቱም ኣገሮች ግጭቶች መነሳታቸው የማይቀር ጉዳይ ነው፡፡ ለዚህ ነው ኣሁን ያሉ ስርዓቶች (የሻዕብያ ወይም የኢህኣዴግ) ባህሪ ካልተቀየረ በቀር በኢትዮ-ኤርትራ ጉዳይ በድርድር ሰላም ሊመጣ ኣይችልም የሚባለው፡፡ ሻዕብያ የዝርፍያው ድብቅ ዓላማ ትቶ በራሱ ሃብት በራሱ የሰው ሃይል በመተማመን መሰረት ያደረገ ኣገር ግንባታ ካሰበ፣ ከኣጎራባች ኣገራት በጋራ የመጠቃቀም መርህ ስምምነት ከፈለገ፣ የኢትዮጵያ በር እንኳንስ ለኤርትራ የኢትዮጵያ ኣካል የነበረች ለባዕድ ቅኝ ገዢዎች የነበሩም በጋራ ለመስራት በሯ ክፍት ነው፡፡

ስለዚህ ኣንዱ የሰላም ኣማራጭ የሻዕብያ ባህሪ መሰረታዊ ለውጥ እንዲያመጣ ማድረግ ነው፡፡ ሌላው በኢትዮ-ኤርትራ የሰላም ኣማራጭ ደግሞ የኢህኣዴግ ባህሪ መቀየር ነው፡፡ እሱም ሻዕብያ በኢትዮጵያ ገብቶ እንደፈለገው ህጋዊውና ህገወጡን ባንድላይ እያተራመሰ የኢትዮጵያን ሃብት እንዲዘርፍ በሩን መክፈት ነው፡፡ በሌላ ኣነጋገር ኢህኣዴግ የህዝብን ኣደራ፣ የሰማእታት ኣደራ፣ የአብዮታዊ ዴሞክራሲ መስመር በራሱ እግር ረግጦ ክህደትን እንዲፈፅም መጠበቅ ማለት ነው፡፡

5/ የኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት የለ ሰላም የለ No war! No Peace ሁኔታ የኢትዮጵያ ፖሊሲና ውጤቱ

የኢትዮጵያ መንግስትና ህዝብ ገና ከጅምሩ ወደ ጦርነት መግባት ኣልፈለገም ነበር፡፡ በመሆኑም ኣሜሪካና ሩዋንዳ፣ የኣፍሪካ ህብረት፣ የተባበሩት መንግስታት እንዲሁም ሌሎች ያቀረቡትን የሰላም ድርድር በመቀበል ችግሩ በጠረጴዛ ዙርያ ውይይት ለመፍታት ዝግጁ እንደሆነ ነገር ግን ድርድሩ ከመጀመሩ በፊት ሻዕብያ ወደነበረበት እንዲመለስና ወደ ድርድሩ እንዲገባ ተጠየቀ፡፡ የኢትዮጵያ መንግስት ሻዕብያና የኤርትራ ህዝብ ለያይቶ በማየት የኤርትራ ህዝብ የኢትዮጵያን የሰላም ጥረት እንዲደግፍና ለሰላም እንዲቆም ጥሪ አቀረበ፤ በተቻለ መጠን ጦርነቱ ለማስቀረት ሰፊ ውትወታ ኣደረገ፡፡ ግን በአንድ እጅ ማጨብጨብ ኣይቻልምና የሰላም መንገዱ ሳይሳካ ቀረ ጦሩነቱ በኢትዮጵያውያን ድል ሲጠናቀቅ የድንበሩ ጉዳይ ወደ ኣለም ኣቀፍ ፍርድ ቤት ተመራ ፍርድ ተሰጠበት፡፡

የኣለም ኣቀፍ ፍርድ ቤት ውሳኔ በመሬት ላይ ወርዶ ተፈፃሚ እንዲሆን ውሳኔውን ተቀብለን ወደ ቀድመው ሁኔታ እንድንመለስ፣

* የህዝብ ለህዝብ ግንኝነቱ በሁሉም መስክ (በማህበረ ኢኮኖሚ መስኮች) እንዲጠናከር ዘለቄታ ያለው ሰላምና መረጋጋት በኣከባቢው እንዲሰፍን የሁሉም ወገኖች ትብብር እንዲኖር፣

* ኣንዱን በሌላው በውስጥ ጉዳይ ጣልቃ መግባት እንዳይኖር፣ በሁሉም ወገን የሰራዊቱን መጠን እንዲቀንስ፣

* የፍርድ ውሳኔ ለመተግበር የሚያስቸግሩ ቦታዎች በሰጥቶ መቀበል መርህ በድርድር እንዲፈቱ፣

የሚሉ የሰላም ድርድር ነጥቦችን ኣቀረበ፡፡ ሻዕብያ ይህን የሰላም ጥያቄ ሊቀበለው ኣልቻለም በመሆኑም በሁለቱም ኣገራት ድንበር ኣከባቢ ያለ ጦርነት (ጦርነት የለ ሰላም የለ) ውጥረት ሰፍኖበት እስከ ኣሁን ድረስ ኣለ፡፡

ኢህአዴግ በዚህ የኢትዮ-ኤርትራ ጉዳይ የተከተለው ኣቅጣጫ ሻዕብያ ባህሪዉን ቀይሮ የሰላም ድርድሩ ከተቀበለ እሰዮ በጋራ እንሰራለን (Plan A)፤ ካልተቀበለ ተገዶ የሰላም መንገዱን እንዲቀበል የማዳከም ስራ እንሰራለን (Plan B) የሚል ነው፡፡ በዚህ መሰረት ላለፉት 16 ዓመታት Plan B ነበር በመተግበር ላይ ያለነው፡፡ የዚህ (Plan B) ምንነትና ውጤቱ ምን ይመስላል የሚል ከዚህ በታች በዝርዝር ቀርቧል፡፡

6/ በኢትዮ-ኤርትራ ጉዳይ ኢትዮጵያ እየተከተለችው ያለውን (Plan B)

ያቀረብናቸው የሰላም ነጥቦች ሻዕብያ ካልተቀበለም እስኪቀበለው ድረስ ድንበራችንን ዳግም ላለማስደፈር እየጠበቅን ልማታችንን እናፋጥናለን፡፡ ከሻዕብያ ለሚመጣ ማንኛውም ትንኮሳ ተመጣጣኝ የኣፀፋ መልስ እንሰጣለን፡፡ ምናልባት ሻዕብያ እንደልማዱ ልማታችንን ለማደናቀፍ መጠነ ሰፊ ወረራ ጦርነት ከሰነዘረ ደግሞ ዳግም ላይነሳ ላንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ኣይቀጡ ቅጣት እንቀጣለን፣ ሻዕብያ ካለው ባህሪ ተነስቶ ዓቅም ካገኘ መውረሩ ስለማይቀር ኣቅም እንዳይኖረው በዲፕሎማሲ ከፍተኛ ርብርብ በማድረግ ከኣለም ህብረተሰብ እንዲነጠልና እንዲወገዝ እናደርጋለን፤ የኤርትራ ህዝብ ወንድም ህዝብ እንደሆነና የሻዕብያ ፀረህዝብና ፀረ ዴሞክራሲ ተግባራት ሰለባ ወይም ተጎጂ እንደሆነ፣ ፀባችን ከሻዕብያ እንጂ ከኤርትራ ህዝብ እንዳልሆነ የማስረዳት ስራ መስራት እንዳለብን፣ የተፈጠረው ጠባሳ ለመደምሰስ የህዝቦች ግንኝነት እንዲኖር ኣጠንክሮ መስራት፣ የሻዕብያን ስርዓት ኣማሮት የሚመጣ ኤርትራዊ በወንድማማችነት መንፈስ ተቀብሎ ማስተናገድ፣ በተቻለ ዓቅም ድጋፍ መስጠት የሚል ፖሊሲ እየተከተልን እነሆ 16 ዓመታት ኣስቆጠረ፡፡

የሻዕብያ ስርዓት ገና በትጥቅ ትግል ላይ እያለ የገነባው የፀረ ህዝብና ፀረ ዴሞክራሲ ባህሪው የተነሳ ሁሉንም ፍላጎቱ በውስጥም በውጭም በሃይል ለማስፈፀም የሚፈልግና ሁልንም ነገር ካለው የሃይል ሚዛኑ በመነሳት እንዳበደ ውሻ መናከስ የማይቀር እንደሆነ በተግባር የታየ በመሆኑ ሻዕብያ እስካለ ድረስ ሁሌም በስጋት መኖሩ የማይቀር ጉዳይ ነው፡፡ የኤርትራ ህዝብና ኣጎራባች ኣገራት ዘለቄታዊ ሰላምና መረጋጋት እንዲያገኙ ከተፈለገ ሻዕብያ መሰረታዊ የባህሪ ለውጥ ማምጣት ወይም ደግሞ ስርዓቱ ተወግዶ በህዝባዊና ዴሞክራሲያዊ ስርዓት መተካት ነው መፍትሄው የሚል የኢትዮጵያ እምነት ነው፡፡ ይህ በእንዲህ እያለ እንዴት የሻዕብያ ባህሪ መቀየር ይቻላል? ካልሆነ እንዴት ስርዓቱ ማስወገድ ይቻላል? የሚል ጥያቄ ቀርቦ ኣካራካሪ መልስ ወይም ኣማራጭ መፍትሄ ሊመጣ ይችላል፡፡ እዚህ ላይ የልማታዊ ዴሞክራሲያዊ መንግስታችን ኣቋም ግልፅና ግልፅ ነው፡፡

የሻዕቢያ ባህሪ የመቀየር ይሁን ስርዓቱ የማስወገድ ጉዳይ የኤርትራ ህዝብ ጉዳይ ብቻ መሆን ኣለበት የሚል ፅኑ ኣቋም ኣለ፡፡ የአንድን አገር ስርዓት ወይም ባህሪ ለኔ ኣላማረኝም ለአገሩ ህዝብም ኣይጠቅምም ስለዚህ መወገድ ኣለበት ብሎ ስርዓቱ ለማስወገድ መፈለግ የአንድን ሉኣላዊ አገር የውስጥ ጉዳይ ገብቶ መፈትፈትና ሉኣላዊነትን መድፈር በመሆኑ ፀረ ህዝብና ፀረ ዴሞክራሲ፣ እኔ ኣውቅልህ ኣለሁ ባይነት ነው፡፡ ይህ ደግሞ ከህዝባዊ ወገንተኝነት ያለውና ዴሞክራሲያዊ ስርዓት እየገነባሁ ነው ከሚል አገር/ስርዓት የማይጠበቅ ተግባር ነው፡፡ ግን ደግሞ ይህ ፀረ ህዝብና ፀረ ዴሞክራሲ ስርዓት ድንበሩ ተሻግሮ ኣንድን ልኡላዊ አገር የማተራመስ ተግባሩ ቆመን እንጠብቅ ማለት ኣይደለም፣ ከሆነ ይህም ቂልነት ነው፡፡

የሻዕብያ መንግስት ኢትዮጵያን የማተራመስ ፍላጎቱ መቼም ቢሆን የማይተወው እንደሆነ፣ ኣቅም ካገኘ ይህን ፍላጎቱ ለማሟላት እንደሚሰራ በግልፅ የሚታወቅና የማያከራክር ጉዳይ ነው፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ የኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት በኢትዮጵያ የበላይነትና ኣሸናፊነት ቢጠናቀቅም፣ ኣሁን ያለው የኢትዮጵያ ትውልድ እንደ ኣባቶቹ የኢትዮጵያ ሉኣላዊነቷ የደፈረውን ወራሪው የሻዕብያ ስርዓት ውርደቱን ተከናንቦ የሰላም ድርድሩ እንዲቀበል ብናደርግም፣ በተገኘው ኣኩሪ ድል የልብ ልብ ቢሰማንም ይህ ድል ብዙ ውድ የኢትዮጵያ ምርጥ ልጆች ተከፍሎበት፣ ከባድ ሃብት ፈሶበት የመጣ ነው፡፡

በሁለቱም እህት አገራት በተደረገው ኣስከፊ ጦርነት ከሁሉም ወገን ከፍተኛ መስዋእትነት የተከፈለበት ጦርነት ነው፡፡ በዚህ ጦርነት ኣሸናፊና ተሸናፊ እንዳለ ሆኖ በተደራቢ በሁለቱም ህዝቦች ላይ ትቶት የሄደው ጠባሳ በተለይ በኤርትራ በያንዳንዱ ቤት የገባ በመሆኑ ጠባሳው በቀላሉ የማይሽር ሁሌም በታሪክ በኣሉታ ጎኑ እየታወሰ የሚኖርና በሁለቱም ህዝቦች ከፍተኛ መጠራጠርን የፈጠረ መደገም የማይገባው ጉዳይ ነው ብሎ ኣብዮታዊ ዴሞክራሲ ያምናል፡፡

ስለዚህ የኢትዮጵያ መንግስት ኣቋም ሻዕብያን እስኪወረን ድረስ ቆመን መጠበቅ ሳይሆን የሻዕብያን ዓቅም በዲፕሎማሲ፣ በወታደራዊ፣ በኢኮኖሚያዊና በማህበራዊ በሁሉም እንዲዳከምና ሻዕብያ ዓቅም ኣግኝቶ ወደ ወረራ እንዳይገባ በስፋት መስራት ኣለብን የሚል መንገድ ነው የተከተልነው፡፡ መንግስታችን የተከተለው ፖሊሲ ያለ ደም መፋሰስ፣ ያለ የመሳሪያዎች ጋጋታ ፀረ ህዝብና ፀረ ዴሞክራሲ የሆነውን የሻዕብያ መንግስት በማዳከም ሽባ ማድረግ የሚል ነው፡፡

ሻዕብያ ፀረ ህዝብና ፀረ ዴሞክራሲ ስርዓት በመሆኑ ከህዝቡ ኣልፎ በኣጎራባች ኣገሮች ከፍተኛ ትንኮሳ ሲያደርግና በሉኣላዊ አገራት የውስጥ ጉዳይ እየገባ የሚፈተፍት በመሆኑ፣ ይህን ፀረ ህዝብና ፀረ ዴሞክራሲ ዓላማውን ለማሳካት ከኣሸባሪ ድርጅቶች (ከነኣልሸባብ) ኣብሮ እንደሚሰራ፣ እንደሚያሰለጥን፣ እንደሚደግፍ፣ የኤርትራ ህዝብ ሃብት ለሽብር ተግባር እንደሚያውል፣ በተጨባጭ ማስረጃ ተደግፎ በዓለም ኣቀፍ ማሕበረሰብ ፊት በማጋለጥ ሻዕብያን የሚያዳክም ማዕቀብ እንዲደረግለት መጣር ኣንዱ የPlan B ተግባር ነው፡፡ ይህ ተግባር በመፈፀም የኢትዮጵያ መንግስት ከፍተኛ ድል ኣስመዝግበዋል፡፡

7/ Plan B ያስገኘው ውጤት

ኢትዮጵያ የሻዕብያን ሰራዊት ኣይቀጡ ቅጣት በመቅጣት ከሁሉም ድንበሮች ካባረረች ቦኋላ ሻዕብያን በማንበርከክ ወደ ሰላም ድርድር እንዲገባና የሰላም ድርድሩ እንዲፈርም ካደረገች ቦሃላ ኢትዮጵያ የተከተለችው ፖሊሲ የሻዕብያን ስርዓት የሚያዳክምና በቁሙ ሽባ የሚያደርግ በኣንፃሩ የኢትዮጵያን ኣቅም በሁለመናው የሚያሳድግ ነበር፡፡ ውጤቱም ኢህአዴግ ባለፉት 15 ዓመታት በኢትዮጵያ በዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታና በልማት ዙርያ ካስመዘገባቸው ኣመርቂ ውጤቶች ባልተናነሰና በጣም ውጤታማ በሚባል ሁኔታ ተመዝግቧል፡፡ ለዚህ ማስረጅ የሚሆን ኢትዮጵያና ኤርትራ በንፅፅር እንመልከት፡-

7.1/ የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት

የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ወታደራዊ ብቃቱና ሞራሉ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተገነባ ኣሁን በከፍተኛ ደረጃ የደረሰ የደረስንበትን የዕድገት ደረጃ የሚመጥን ዘመናዊ ቴክኖሎጂ የታጠቀ ቴክኒካዊ አቅሙና ህዝባዊ ወገንተኝነቱ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ የመጣ፣ በአገር ውስጥ ይሁን በኣጎራባች ሃገራት ባደረጋቸው ወታደራዊ ኦፐሬሽኖች ድል በድል እየተጎናፀፈ ያለ፣ በዓለም ኣቀፍ የሰላም አስከባሪነት በብቃቱ ተመራጭ እየሆነ የመጣ የምንመካበት አለምአቀፍ ተቋም ሆኖዋል፡፡

የሰራዊታችን ብዛትና የብሄር ስብጥር በምናይበት ጊዜ በሁሉም መለኪያ 90 ሚልዮን ህዝብና የዚህን ህዝብ ኤኮኖሚና ህገመንግስት ለመጠበቅ የሚመጥን ቁጥር ያለው፣ ለአስቸጋሪ ሁኔታ አስተማማኝ ተጠባባቂ ሃይል ያለው፣ በብሄራዊ ተዋፅኦ የተመጣጠነና ትክክለኛ የኢትዮጵያ ገፅታ የሚያሳይ ሰራዊትና ተቋም ለመሆን የደረሰ ነው፡፡ በመሆኑም ከአሁን በፊት የማይታሰቡ የነበሩ ብሄራዊ ጥቅማችን የማስከበርና የመደራደር አቅማችን ከፍያደረገ፣ በአለምአቀፍ ተሰሚነታችን ወደላቀ ደረጃ ካደረሱን ተቋሞቻችን አንዱ ለመሆን በቅቷል፡፡ ይህ የልማታዊ ዴሞክራሲያዊ መንግስታችን ፖሊሲ ውጤት ነው

የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት የሰራዊቱ ግንባታ ኣቅጣጫ ብዛት ያለው ሰራዊት መያዝ ሳይሆን ጥራትን መሰረት ያደረገ፣ ወታደራዊና ፖለቲካዊ ኣቅሙ ብቁ የሆነ፣ ወታደራዊ ትጥቁ ዘመኑ የሚጠይቀውና የአገራችን ኢኮኖሚ የሚፈቅደው ቴክኖሎጂ ማስታጠቅ፣ ቴክኖሎጂውን በተቻለ ፍጥነት መቅዳትና ኣገርውስጥ እንዲሰራ ማድረግ፣ የሰራዊቱ ፊሲካላዊ ኣቅም ሁሌም ዝግጁ እንዲሆን “ላብ ደምን ያድናል“ በሚል መርህ ሁሌም የኣካል ብቃት ስልጠናና ልምምድ እንዲወስድ ማድረግ፣ ዋናው እምነቱ ህዝባዊ ወገንተኝነት እንደመሆኑ መጠን ህዝብን በልማት ወይም በተለያዩ ማህበረ-ኢኮኖሚ ጉዳዮች ማገዝ፣ የሚሉ ነው፡፡

ለዚህም የሚያግዘው ብቁ ባጀት የሚመደብለትና የኣገሪቱን ዕድገት ባደገ ቁጥር የመከላከያ ባጀትም በዛው መጠን ልማቱን በማይጎዳና ልማቱንና ህዝብን መጠበቅ በሚያስችል እያደገ እንደሚሄድ ነው፡፡ ኣሁን በተጨባጭ የኢትዮጵያ የመከላከያ ባጀት በመደበኛ ሁኔታ (የጦርነት ስጋት ወይም ዝግጅት በሌለበት ጊዜ) ከጠቕላላ ባጀታችን 1.5% ባልበለጠ ነው የሚመደበው፡፡ ይህ ደግሞ ማንኛውም ልማታዊ መንግስት የሚባል አገር የሚያደርገው ነው፡፡ ቢበዛ ከ2% የሚበልጥ ኣይሆንም፡፡

ኣሁን ኤርትራ ማለት መንግስት ስላላት ብቻ ምናልባት ከሶማሊያ የተሻለች የአለማችን ጭራ አገር ናት፡፡ ኤርትራ ማለት መሰረታዊ ሸቀጦች ለህዝቧ እንደ ወታደር በራሽን የምታከፋፍል ኣገር ናት፡፡ የኛ የመከላከያ የአንድ ዓመት ባጀታችን የኤርትራ የኣመታት የአገር ባጀትን የሚሸፍን ባጀት ይሆናል፡፡ ሻዕብያ ኣንድን ጦርነት የሚመዝነው በሰራዊት ብዛትና በመሳርያ ዘመናዊነትና ጋጋታ ነው፣ ስለዚ ሻዕብያ በኣሁኑ ጊዜ የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ኣቋም በራሱ ጥናት ሲያየው እዛው እንዳለ የተሸነፈ ስርዓት ነው፡፡ ይህ የልማታችን ውጤት ነው፡፡

የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት የኣገራችን ሉኣላዊነትና ሕገመንግስታችን ከመጠበቅ ጎን ለጎን የኣገራችን ልማት በማፋጠንም ቁልፍ ሚና እየተጫወተ ያለ የምንኮራበት ሃይል ሆኖዋል፡፡ የአገራችን ልማት ፍጥነቱን ጠብቆ ለመሄድ የኢንዱስትሪ ሴክተር ልማት በኢኮኖሚያችን ቁልፍ ሚና እንዲኖረው በብረታብረት ኢንጂኔሪንግ ኮርፖሬሽን በኩል ከፍተኛ ኣስተዋፅኦ እያደረገ ይገኛል፡፡ ይህ ኮርፖሬሽን የአገራችን የውጭ ምንዛሪ እጥረትን ለመቅረፍ የውጭ ምርት በመተካት፣ የአገራችን የሃይል ፍላጎት ለማሟላት በህዳሴ ግድብ ግንባታ፣ ተሰራዊቱ የሚያስፈልጉ መሰረታዊ የቀላልና ከባድ መሳርያ ፍላጎት በኣገር ውስጥ እንዲመረቱ በማድረግ ከፍተኛ ኣስተዋፅኦ የሚያደርግና በኣጭር ጊዜ ውስጥ ከፍተኛ ደረጃ የደረሰ ተቋማችን ነው፡፡ ይህም የልማታዊ ዴሞክራሲ መንግስታችን ውጤት ነው፡፡

7.2/ የኤርትራ መከላከያ ሰራዊት

የሻዕብያ ውድቀት ማረጋገጫ ኣንዱ በየቀኑ በብዙ መቶዎች የሚቆጠር ወጣቱ ሃይል ወደ ኢትዮጵያና ሱዳን መጉረፉ ነው፡፡ በዓለማችን ስደት የማይሰደድባት አገር የሌለችና ስደት እንደ የተሻለ ኑሮ ፍለጋ የሚደረግ ተፈጥሯዊ ክስተት ቢሆንም መጠኑ ሲበዛ ግን አነጋጋሪ ይሆናል፡፡ ስደት በጭራሽ ልንከላከለው ወይም ልናቆመው የማንችል የተፈጥሯዊ ክስተት ነው፡፡ በዓለማችን ከታላቕዋ ልዕለ ሃያል መንግስት አሜሪካ ጀምሮ እስከ የመጨረሻዋ ያልተረጋጋችው አገር የምትባለው ሶማሊያ ያሉ ኣገሮች ዜጎች የተሻለ ኑሮ ፍለጋ ይሰደዳሉ፡፡ ልዩነቱ የስደቱ መጠን /ስደት ፐር ፖፑሌሽን/ ነው፡፡

መረጃዎች እንደሚያመላክቱት ከስደተኞቹ ውስጥ ከ40% በላይ የሚሆኑት ሻዕብያን እስከ ኣሁን ድረስ ጠብቀው ያቆዩት ኣገልጋዮቹ ወይም የሻዕብያ ሰራዊት እንደሆነ ነው የሚያሳየው፡፡ በዓለማችን በኣሁኑ ወቅት ከሶርያ ቀጥሎ፣ በኣፍሪካ ደግሞ ሶማሊያን ቀድማ ቁጥር አንድ ስደተኞችን የምትልክ አገር ኤርትራ ናት፡፡ በጦርነቱ ያጋጠማትን ሽንፈትና ይህ የወለደው ስደት ምክንያት በኣሁኑ ወቅት ኤርትራ የወጣት ሃይል ከፍተኛ እጥረት እንዳጋጠማት በተለያዩ ሚድያዎች ሲነገር ይሰማል፡፡

አሁን የሻዕብያ ቁመና በምናይበት ጊዜ፣ ወታደራዊ ብቃቱና ሞራሉ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየወረደ ያለ፣ ከኤርትራ ወጣት ባልተናነሰ መጠን ስርዓቱን እርግፍ አድርጎ በመተው በመሰደድ ላይ ያለ፣ /በየወሩ ከሚሰደዱ ኤርትራውያን 40% ወታደር እንደሆነ/ በመሆኑም የመዋጋት ሞራሉ የሌለው፣ በግዴታ ያለ ፍላጎቱ የተቀላቀለ፣ ባገኘበት አጋጣሚ ለመሸሽ ዝግጁ የሆነ ሰራዊት እንደሆነ፣ በወታደራዊ ትጥቁ በሚታይበት ጊዜ ከ5 የማይ በልጡ ዘመናዊ የጦር አውሮፕላን ቢኖሩትም የተገነባ ተቋም ባለመኖሩ ብዙ ውጤታማ የማያደርግ እንደሆነ፣ በሌላ በኩል ኣብዛኛው ወታደራዊ ትጥቁ ጊዜ ያለፈበት የደርግ ስርዓት ይጠቀምበት የነበረ እንደሆነ፣ ከኤርትራ ነፃነት ቦኋላ ያደረጋቸው ወታደራዊ ኦፐሬሽኖች በሙሉ የከሸፉበትና ጠቕላላ ወታደራዊ ዓቕሙ የላሸቀ፣ ህዝባዊ ወገንተኝነት የሌለው ቀንደኛ የኣፈና መሳሪያ የሆነ ወታደራዊ አቅም ነው፡፡

በመሆኑም ሻዕብያ ለአገራችን በሁሉም መለኪያዎች ፈፅሞ ስጋት ሊሆን በማይችልበት ደረጃ እንዳለ፣ ኢትዮጵያን ለማፈራረስ ፍላጎት እንጂ የማድረግ አቅም የሌለው ሽባ ስርዓት ለመባል ደርሷል፡፡ በኣጠቃላይ የሻዕብያ ስርዓት በውስጡ ከህዝቡ የተገለለና የመጨረሻ ጠርዙ የደረሰ፣ በኣለምአቀፍ ደረጃ የተገለለና ጠቅላላ የተረሳ፣ ዲፕሎማሲያዊ አቅሙ እዚህ ግባ የማይባል ስርዓት ነው፡፡

የሻዕብያ ውድቀት ሌላው ማረጋገጫ ዓምና በሞላ አስገዶም የሚመራው የዴምህት ቡዱን ከፀረ-ህዝብና ፀረ-ዴሞክራሲ ኣፍራሽ ተግባሩን በመፀፀት ይቅርታ ጠይቆ በመጣበት ወቅት በኣስረጅ የነገረን ሓቅ ቢኖር ይህንኑ የሻዕብያ ውድቀት ነው፡፡ ሌላ ቀርቶ ሻዕብያ የሚመካበት የስለላ መረቡ በመበጣጠስ የኢትዮጵያ የደህንነትና የመረጃ ሃይሎች፣ የሻዕብያን ጓዳ እንደፈለጉት ከዓንድ ዓመት በላይ እንዳመሱት ስንሰማ እውነትም ሻዕብያ በውድቀት ጎዳና ላይ እንዳለ ማሳያ ነው፡፡

የሻዕብያ ውድቀትና የኢትዮጵያ Plan B ስኬት ሌላው ማረጋገጫ በዲፕሎማሲ በኩል የተገኘው የኤርትራ ውድቀትና የኢትዮጵያ ስኬት ነው፡፡ ኤርትራ በኣሁን ወቅት ከኣለማችን የተገለሉ ከሚባሉ ሁለት ኣገሮች ኣንዷ ናት፡፡ ኢትዮጵያ ከአጋሮቿ ጋር በመሆን የተቀናጀ አታካች እልህ አስጨራሽ የዲፕሎማሲ ስራ በመስራት ሻዕብያ መጀመሪያ ከኢጋድና ከአፍሪካ ሕብረት እንዲነጠል ቀጥሎ ከኣለም አቀፍ ሕብረተሰብ እንዲነጠል እና ተደራራቢ ማዕቀቦች እንዲደረጉለት ፖሊሲያችን ኣስተዋፅኦ ኣድርገዋል፡፡

ሻዕብያም በኣሁኑ ሰዓት ምላስ ያለው ሊናገር የሚችል ቢሆንም ሌላው ኣካላቱ ግን ምንም ነገር የማይሰራ በሞት አፋፍ ላይ ያለ የተገለለ ስርአት ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ ኣሁን በኤርትራ የኤርትራው መሪ የኢሳያስ አፈወርቂን ጨምሮ ዋና ዋናዎቹ የሻዕብያ መሪዎች ከኣለም አቀፍ መድረኮች ተገልለው እንደ እስረኛ ሆስፒታል ፍለጋ ወደ አረብ አገሮች ብቻ ሲወጡና ሲገቡ እናያለን፡፡ ኤርትራ ከኣንዳንድ (እንደ እስረኛ ጠያቂ ዘመድ) አገራት ከሚጎበኙዋት በስተቀር፣ ሌላ ዓለም ሁሉ ያገለላት አገር ሆናለች፡፡ በእውነት እንነጋገር ከተባለ ሻዕብያ ለ15 ዓመት በጣረ-ሞት ላይ ሆኖ በመሰቃየት ላይ ያለ ስርዓት ነው ቢባል ማጋነን ኣይሆንም፡፡

ስለዚ ሰላምም ጦርነትም የለም No war No Peace ሲባል የመሳርያ ጋጋታ ስለሌለ እንጂ የኢትዮጵያ መንግስት ይህን ፖሊሲ ከመተግበር ኣኳያ ከጦርነቱ ባልተናነሰ በጣም አታካችና እልህ አስጨራሽ የማጥቃት ስራ ሲሰራ ነው የነበረው፡፡

ሌላው የPlan B ስኬትና የሻዕብያ ውድቀትን የሚያረጋግጠው፣ ሻዕብያ ከኤርትራ ህዝብ መነጠሉ ነው፡፡ ሻዕብያ ገና ከመጀመሪያው ጀምሮ የወረሰውን የፀረ ህዝብና ፀረ ዴሞክራሲ ባህሪ ብዙዎች በደንብ ያልተገነዘቡት የነበረና ኣብዛኛው የኤርትራ ህዝብን በስሩ ማሰለፍ የቻለ ድርጅት እንደነበር የቅርብ ጊዜ ትውስታ ነው፡፡ ሆኖም ግን የኤርትራ ነፃነት እውን ከሆነ ቦኋላ የኤርትራ ህዝብ ከሻዕብያን ይጠብቀው የነበረውን ነገር ማግኘት ኣልቻለም፡፡

የኤርትራ ህዝብ ከሻዕብያ ይጠብቀው የነበረ መሰረታዊ ነገር ኣንዱ ከኢትዮጵያ ህዝብ በፊት (በፌደረሽኑ ሽግግር ጊዜ) ማጣጣም ጀምሮት የነበረ የዴሞክራሲ መብቶች፣ የፕረስ ነፃነቶች፣ የነፃ ምርጫ ሂደቶች በኣዲስቷ ነፃ ሄገር ኤርትራ ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ ተግባራዊ ማድረግ ነበር፡፡ ይህ ግን የህልም እንጀራ ሆኖ ቀረ፡፡ ይባስ ብሎ ተቋዋሚ ፓርቲዎች ማዋከብ፣ ነፃ ሚድያው ማፈን ጀመረ፡፡ በዚህ ጊዜ የኤርትራ ህዝብም የሻዕብያን ፀረ ህዝብና ፀረ ዴሞክራሲያዊ ባህሪ መረዳት ሲጀምርና ከስርዓቱ መነጠል ሲጀምር ነበር የኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት የተከፈተው፡፡ ሻዕብያ ራሱ የጀመረው ጦርነት እንደተወረረ ኣድርጎ በማቅረቡ መነጠል ጀምሮ የነበረውን ህዝብ የውስጡን ብሶት ወደ ጎን በመተው ከሻዕብያ ጋር የተሰለፈው ቀላል ኣልነበረም፡፡

ከዚህ ሁኔታ በመነሳት ነበር ኢትዮጵያ የጦርነቱ ኣጀማመር ትክክለኛውን ገፅታ ለኤርትራ ህዝብና ለኣለም ህብረተሰብ ለማሳወቅ ኣታካችና እልህ ኣስጨራሽ የPlan B ስራ በመስራት ትክክለኛውን ግንዛቤ ማስጨበጥ የተቻለው፡፡ በመሆኑም የጦርነቱ ጀማሪ ወይም ወራሪው የኤርትራ መንግስት እንደ ሆነ፣ በኤርትራ ወደቦች የነበሩ የኢትዮጵያ ንብረት እንደዘረፈ፣ የዓለም ኣቀፍ ፍርድቤት በማረጋገጡ ኤርትራ ለኢትዮጵያ ካሳ እንድትከፍል ፍርዱን ኣስቀመጠ፡፡

የተሸነፈው የሻዕብያ ስርዓት የፀረ ህዝብና የፀረ ዴሞክራሲ ተግባራቱ ከጦርነቱ ቦኋላ በባሰ በኤርትራ ህዝብ መፈፀም በመጀመሩ፣ በጦርነቱ ምክንያት መቀራረብ ጀምሮ የነበረውን ህዝብ እየራቀ እየተገለለ ብሎም እስከ ስርዓቱን ጥሎ መሸሽ ጀመረ፡፡ በጦርነቱ ጊዜ በሻዕብያ የሚነዛ ፕሮፖጋንዳ የወያኔ ስርዓት ጭራቅና ከዛም የከፋ ሰው በላ ስርዓት እንደ ሆነ በስፋት ሲሰራበት እንደነበር፣ በዚህም የሚደናገር ኣካልም እንደነበር የሚታወቅ ነው፡፡ ከሁሉም የሚገርመው ግን የወያኔ ስርዓት ጭራቅ ነው ብለው የሚያስቡ ሳይቀር ድንበርን ኣቋርጠው ከኛ (የሻዕብያ ስርዓት) ጭራቅ የሚብስ የለም በማለት ወደኢትዮጵያ ሲገቡ ይታያል፡፡

የኢትዮጵያ መንግስት ካለው ህዝባዊ ወገንተኝነት የተነሳ የሻዕብያ ስርዓትና የኤርትራ ህዝብ ለያይቶ በማየት ለህዝቡ ያለው ወገንተኝነት በማሳየቱ ባለው ኣቅም በመደገፉ፣ ኤርትራዊያን ስደተኞች በፈለጉት የኢትዮጵያ ከተማ እንዲኖሩ በመፍቀዱ፣ ስደተኞቹ ኣቅም በፈቀደ በኢትዮጵያ ዩኒቨርሲቲዎች ገብተው እስከ 2ኛ ዲግሪ በነፃ እንዲማሩ በመፍቀዱ፣ ወዘተ በማድረጉ ምንያክል ህዝባዊ ወገንተኝነት እንዳለው በተግባር በማሳየቱ የሻዕብያን ጠባጫሪነት እንዲረዳ፣ የኢትዮጵያ ህዝብና መንግስት ለኤርትራ ህዝብና መንግስት ያለው ቀና ኣመለካከት በደንብ እንዲገነዙ ኣድርጓል፡፡ በመሆኑም በኣሁኑ ጊዜ በየ ቀኑ በመቶዎች የሚቆጠሩ ኤርትራውያን ድንበራቸውን ኣቋርጠው ወደ ኢትዮጵያ ሲጎርፉ ይታያል፡፡ ይህ ሁሉ የሚያሳየው የኤርትራ መንግስት ውድቀት መሆኑ ነው፡፡

ከዚህ ማጠቃለል የሚቻለው ልማታዊ ዴሞክራሲያዊ መንግስታችን የተከተለው የውጭ ጉዳይ ፖሊሲና በተለይ ደግሞ በኤርትራ ላይ የተከተለው ልዩ ፖሊሲ ማለትም፡-

* የሻዕብያ ስርዓት ከኣለም ህብረተሰብ ማግለል፣ ስርዓቱን የሚያዳክሙ ማእቀቦችን እንዲጣሉ ማድረግ

* የሻዕብያን ስርዓት በሁሉም (በኢኮኖሚ፣ በማህበራዊ፣ በፖለቲካዊ፣ በዲፕሎማሲ) መስክ ማዳከም፣

* የሻዕብያ ስርዓት ካለው የፀረ ህዝብና የፀረ ዴሞክራሲ ተግባራት በመነሳት ከዓለም ህብረተሰብ ብቻ ሳይሆን ከኤርትራ ህዝብ መነጠል፣

* የኢትዮጵያ ህዝብና መንግስት የኤርትራ ህዝብን ሰላም፣ ልማት፣ ዴሞክራሲ ፈላጊ እንጂ ጠላት እንዳልሆነ በተግባር ማሳየት፣ የኤርትራ ህዝብም ይህ እንዲገነዘብ ማድረግ፣

* እንዲሁም በሻዕብያ የሚደረጉ ትንኮሳዎች የአፀፋና ተመጣጣኝ /ኣስተማሪ/ እርምጃ በመውሰድ ሰራዊቱን ማዳከም፣

የሚሉትን ተግባራዊ በመፈፀም ኣኳያ ባለፉት 15 ዓመታት በጣም ውጤታማ እንደነበሩና ከፍተኛ ድል እንደተጎናፀፍን መታወቅ ኣለበት፡፡ እኔ በበኩሌ ይህ ውጤታማ ፖሊሲ ተጠናክሮ ሳይበረዝ ከቀጠለ የሻዕብያ ዕድሜ ያጥራል የኢትዮጵያ ግስጋሴ ፍጥነቱን ሳይቀንስ ይሄዳል የሚል እምነት ኣለኝ፡፡

8/ ሻዕብያን በሃይል በማስወገድ የሚገኝ ትርፍ ይኖራል?

የኢሳያስ ኣፈወርቂ ወይም ደግሞ የሻዕብያ ስርዓት መወገድ የኢትዮጵያ ሰላምና መረጋጋት ይረጋገጣል ወይ? ብሎ መወያየት በጣም ኣስፈላጊ ነው፡፡ ከኢህኣዴግ ስኬት የተማርነው ኣንድ ቁልፍ ነገር የውስጥ ችግሮቻችን መፍታት ከቻልን የአገራችን ሰላም፣ መረጋጋትና ልማት ማረጋገጥ እንችላለን፡፡ የውስጥ ችግሮቻችን ከፈታን የውጭ ጠላቶቻችን መግብያ ስለሚያጡ ሊረብሹን ኣይችሉም፡፡ የውስጥ ችግሮቻችን ካልፈታን ወይም በኣግባቡ ካላስተናገድናቸው የውጭ ጠላቶቻችን እዛው ላይ በማንዣበብ ሊያውኩንና በቀላሉ ሊያፈርሱን ይችላሉ፡፡ ስለዚህ የውጭ ችግሮቻችን የውስጡን ማባባስ ካልሆነ በስተቀር በራሱ ወሳኝ ሃይል ሆኖ ሊያተራምሰን፣ ሊያበጣብጠን፣ ሊያፈርሰን ኣይችልም፡፡ የውስጥ ችግሮች ካሉ ህዝብና መንግስት ሆድና ጀርባ ይሆናሉ የውጭ ጠላቶች ይህን ክፍተት ተጠቅመው እርስ በርሳችን ግጭት ውስጥ እንድንገባና ድህነትና ድንቁርና እንዲባባስ ሊያደርጉ ይችላሉ፡፡

የኢትዮጵያ ዋናው ችግር ድህነትና ኋላ ቀርነት ነው፡፡ የዚህ ችግር ዋናው መንስኤ ደግሞ ገዢዎቻችን የተከተሉት የተሳሳተ ፖሊሲዎችና ተግባራት ናቸው፡፡ እነዚህ ችግሮችና መንስኤዎች የኢሳያስ ኣፈወርቂ ወይም የሻዕብያ ስርዓት የፈጠሩት ሳይሆን የአገራችን የነፍጠኛው ወይም የትምክህት ስርዓት የፈጠሩት ጦስ ነው፡፡ የኢሳያስ ኣፈወርቂ ወይም የሻዕብያ ስርዓት እነዚህ ችግሮች እንዲባባሱና እንዳይፈቱ ይፈልጋሉ እንጂ እንዲባባሱና እንዳይፈቱ ግን ማድረግ ኣይችሉም ሲባል በቲኦሪ ደረጃ ሳይሆን በተግባር ስላየነው ነው፡፡

ኢትዮጵያ ከኤርትራ ጦርነት በኋላ ያስመዘገበችው ፈጣን፣ ፍትሃዊና ቀጣይነት ያለው ልማት በሻዕብያ ሲደናቀፍ ኣላየንም፡፡ ለዚህ ነው የኢሳያስ ኣፈወርቂ ወይም የሻዕብያ ስርዓት መወገድ የኢትዮጵያን ችግር ይፈታል የሚል ዕምነት ዋስትና የለውም፡፡ የኢትዮጵያ ችግር የሚወገደው የውስጥ ችግር ሲፈታ ብቻ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ችግር በዘላቂነት የሚፈታው ድህነት ሲጠፋና ፈጣን ኢኮኖሚያዊ ዕድገት እያስመዘገብን ስንሄድ ነው፡፡

በኢኮኖሚ እያደግን በሄድን ቁጥር የመደራደር ዓቅማችን በዛው መጠን እያደገ ይሄዳል፣ ተሰሚነታችን በዛው መጠን እየገነነ ይሄዳል፣ የማንም ጎረምሳ መቀለጃ ኣንሆንም፡፡ ኣባይን ለመገደብ የበቃነው ብብድርና ዕርዳታ ሳይሆን በራሳችን ገንዘብ ነው፣ ይህም ስላደግን ነው፡፡ ግብፅን ወደ ድርድር ማምጣት የማይታሰብ ይባል የነበረው እነሆ በማደጋችን የመደራደር ኣቅማንም በዛው መጠን በመጨመሩ ሱዳንና ግብፅ ወደ ጠረጴዛ ዙርያ እንዲመጡ ኣደረግን፡፡

ስሜታችን መቆጣጠር ኣቅቶን በአንዳንድ ጥቃቅን የሻዕብያ ትንኮሳዎች እየተገደድን ከመንገዳችን ወጥተን ለማስተናገድ መሞከር ልማት ከማደናቀፍ ውጭ ሌላ ፋይዳ የለውም፡፡ “የኢትዮጵያ መንግስት ኤርትራ ውስጥ ገብቶ ሻዕብያን አፈራርሰን …….” የሚባል ነገር ፈፅሞ መታሰብ የሌለበት ቀይ መስመር መሆን ኣለበት፡፡ ማንኛውም ህዝብ ጣልቃ ገብነት ኣያስተናግድም፡፡ የፈለገው የውስጥ ችግር ቢኖርም ራሱ በውስጡ እንዲፈታ የሚያስተባብረውና የሚያታግለው ነው የሚፈልግ እንጂ ማንም የውጭ ሃይል እንዲገባበት ኣይፈልግም፡፡ ይህ ሉኣላዊነቱ መንካትና መዳፈር ኣድርጎ ይወስዳል፡፡ ማንኛውም ህዝብ ባዕድ ባዕድ ነው ብሎ ያምናል፡፡ ይህም ትክክለኛ እምነት ነው፡፡ የራሳችን ታሪክ በምናይበት ጊዜ ይህንኑ ያረጋግጥልናል፡፡ የውስጥ ችግሮቻችን በጣም የባሱ እያሉ፣ ገዢዎቻችን ጡት ቆራጮች፣ እጅና እግር ቆራጮች፣ ህዝብ ጨፍጫፊዎች እያሉ፣ ተደፍረሃል፣ ተወረሃል ብለው የክተት ጥሪ ሲያሰሙት ቆፎው እንደተነካ ንብ ነበር ወጥተው ወራሪውን የሚመክቱት የነበረው፡፡ ስለዚ ይህ ጉዳይ ፈፅሞ መታሰብ የለበትም፡፡ ማንኛውም የህዝብ ወገንተኝነት ያለው ሃይል በአንድ አገር ውስጥ ገብቶ ስርዓትን ለማስወገድ ኣይጥርም፤ እምነቱ ካልተሸረሸረ በቀር ኣይሞክረውም፡፡

ማንኛውም የህዝብ ወገንተኝነት ያለው ሃይል የህዝብን ሰቆቃ ያመዋል፣ ይሰማዋል፣ ከሰቆቃው ለማላቀቅ ይፈልጋል፣ ይሞክራል፡፡ ግን እንዴት? እኔ ኣውቅልህኣለሁ፣ እኔ ላንተ መስዋዕት ልክፈልልህ፣ እኔ ኣንተን ወኪየ ኣደርገዋሎ በሚል መንገድ ሳይሆን ህዝባዊ በሆነ መንገድ፤ ህዝብን አደራጅቶና ንቅናቄ ፈጥሮ፣ ኣስታጥቆ ነው፡፡ ይህ ሲባል ግን ሻዕብያ ፀረ ህዝብና ፀረ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት በመሆኑ፣ ለኤርትራ ህዝብ ኣስታጥቀን፣ ኣደራጅተን፣ ንቅናቄ ፈጥረን እናስወግድ ማለት ኣይደለም፣ ይህ ተግባርም የኤርትራዊ ዜጋ ተግባር ነው፡፡

ይህ ለማድረግ ጊዜ የለንም፣ ጊዜ የማይሰጥ ህዝባችን በማሰቃየት ላይ ያለ ትልቅ ጠላት (ድህነትን) በመዋጋት ተጠምደናል፡፡ የራሳችን ችግር፣ የህዝባችን ጠላት እጓያችን ኣላላውስ ኣላንቀሳቅስ ብሎን እያለ የጎረቤት ህዝብ ጠላት ለማስወገድ ጦርነት ኣናውጅም፡፡ ስለዚ ስለ የሻዕብያ ስርዓት መወገድ የኢትዮጵያውያን ጉዳይ ሳይሆን የኤርትራዊያን ጉዳይ ነው፡፡ ድጋፍ ከጠየቁ እንደፈለጉት መጠን ባይሆንም የምንችለው ከህዝባዊ ወገንተኝነት የሚነሳ ድጋፍ ብናደርግ ችግር የለውም፡፡ ችግር የሚኖረው የኤርትራዊ ዜጋ ሚና ተክቶ መንቀሳቀስ ብቻ ነው፡፡

በኢህአዴግ የመበስበስ አደጋ ጊዜ ትልቁ የአንጃና የተሃድሶው ሃይል ላይ የነበረው ልዩነት እዚህ ላይ ነበር፡፡ ለዚህ ነው አንጃው የኤርትራ ህዝብን ተክቶ ሻዕብያን ባለማስወገዳችን የአገር ክህደት እያለ የሚያራግበው፡፡ ወይ ጉድ ለሻዕብያ መወገድ ብሎ ኤትዮጵያዊ ዜጋ መስዋዕት ባለመክፈሉ የአገር ክህደት ተባለ? ለሻዕብያ መወገድና ለኤርትራ ተቋዋሚ ድርጅቶችን ወደ ስልጣን ለማምጣት ተብሎ የድሃዋ ኢትዮጵያ ሃብትና ንብረት በኤርትራ ውስጥ በሚደረገው ጦርነት ማባከን የአገር ክህደት ተባለ?

የአገር ክህደት ማለት በተገላቢጦሹ የሚደረገው ጥረት ነው፡፡ የአገር ክህደት ማለት የአገርና የህዝብን ስልጣንና ሃላፊነት ተሸክሞ በሰከነ ኣእምሮና በህዝባዊ ወገንተኝነት ለችግሮች መፍትሄ ከማምጣት ይልቅ በስሜታዊነትና በጀብደኝነት እየተመራ የአንድን አገር ስርዓት ያለ ህዝቡ ፍቃድ ወይም ይሁንታ ለማስወገድ መፈለግ፣ መስዋእት መክፈል፣ ሃብትና ንብረት ማባከን ነው ከሃዲነትን የሚያስብለው፡፡

የኢሳያስ አፈወርቂ መወገድ የኢትዮጵያን ችግር ይፈታል የሚል እምነት ቢኖር ተልእኮው (ምሽኑ) በኢትዮጵያ የመከላከያ ሰራዊት ጠንካራ ዝግጅት፣ ሰፊ የፕሮፖጋንዳ ስራ መስራት ወዘተርፈ ጋጋታዎች ሳያስፈልግ በቀላሉ በመረጃና ደህንነት ሃይላችን በኣንድ ለሊት ይፈፀም ነበር፡፡ ምክንያቱ ዓምና በመገናኛ ብዙኋን እንደሰማነው እንዳየነው፣ የመረጃና ደህንነት መዋቅራችን የኢሳያስ ቤተመንግስት ለኣንድ ኣመት ሙሉ ሲያተራምሰው ተገንዝበናል፡፡

በሌላ በኩል ኣሁን በጣረ-ሞት ያለውን ስርዓት በመንፈራገጥ ምክንያት (ጥቃቅን ትንኮሳዎች፣ የአገራችን ኣሸባሪዎችን ኣሸልኮ ማስገባት፣ ከጠላቶቻችን ኣብሮ በመተጋገዝ ምክንያት) እኛ ከፈጣኑ የልማት ጉዟችን ወጥተን በሞት አፋፍ ላይ ያደረስነውን ስርዓት መውጋት ወይም መውረር ማለት ትርፉ ኪሳራ ነው፡፡ ምናልባት ስሜታችንን ማርካት እንችል ይሆናል ነገር ግን መዳን ጀምሮ የነበረውን የሁለቱም ህዝቦች ጠባሳ ዳግም እንዲያገረሽና ከህዝቡ ተነጥሎ የቆየውን ስርዓት ዳግም ሂይወት እንዲዘራና ድጋፍ እንዲያገኝ ካልሆነ በስተቀር የሻዕብያ ግብኣተ ሞት ኣያፋጥንም፡፡ ሻዕብያ በራሱ ህዝብ ሲቀየር ብቻ ነው ኢትዮጵያ ከኤርትራ ዘለቄታ ሰላምና መረጋጋት መፍጠር የምትችለው፡፡

ማንም ህዝብ የውስጥ ጉዳዩን የሚፈታለት ሌላ አገር/መንግስት አይፈልግም፡፡ ማንኛውም ዴሞክራሲያዊና ህዝባዊ እምነት ኣለኝ የሚል ስርዓትም የሌላ ስርዓት ለመቀየር ፈፅሞ ኣይንቀሳቀስም፡፡ ከተንቀሳቀሰ በፀረ ህዝብነትና በፀረ ዴሞክራሲያዊነት ከመፈረጅ ኣይድንም፡፡ አሁን በርግጠኝነት መናገር የሚቻለው የኢትዮጵያ መንግስት ሻዕብያን ማስወገድ ይችላል ቀላሉ ስራም ይህ ነው፤ እንኳን ኣሁን ልዩነታችን ሰማይና ምድር ሆኖ፣ ኢትዮጵያ የዘጠና ሚልዮን ህዝብ ኣገር ላለፉት 15 ዓመታት የኢኮኖሚ ዕድገቷ በድርብ አሃዝ በማደግ ላይ የነበረች፣ በተቃራኒ ኤርትራ የ6 ሚልዮን ህዝብ ኣገር ወደታች እየወደቀች ያለች ይቅርና ከ16 ዓመት በፊት ከድህነትና ድንቁርና ለመውጣታችን እርግጠኛ ባልሆንበት ጊዜም፣ ሁለታችን ኣገሮች በተመሳሳይ የዕድገት ደረጃ እያለን ሻዕብያ ማዝመት የሚችለዉን ሁሉ አዘምቶ እያለም ሻዕብያ ተሸንፏል፡፡

ግን ሻዕብያን ማሸነፍና ማስወገድ እርግጠኛ ብንሆንም፣ ሻዕብያን የሚተካ ሃይል ግን ሌላ ሻዕብያ ላለመሆን ምንም ማረጋገጫ የለም፡፡ ግን ደግሞ አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ሓይል እንደማይመጣ በርግጠኝነት መናገር ይቻላል ምክንያቱ ኣብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት በአንድ ጀንበር የሚፈጠር ሳይሆን የራሱ ሂደት ስላለው፡፡ ስለዚ ከመስመራችን አልፈን ሻዕብያን እናስወግድ ብለን ጦርነት ብንከፍት ትርፉ በጦርነቱ ምክንያት የሚጠፋ የሰው ሂይወትና የአገር ሃብት ማጣት እንጂ ሌላ ጥቅም የለዉም ምክንያቱ ሻዕብያ ኣስወግዶ ሌላ ስም ያለዉ ሻዕብያ ላለመምጣቱ ምንም ዋስትና የለምና፡፡

በመርህ ደረጃ የአንድን አገር ስርዓት ስላልወደድነው ለማስወገድ መፈለግ በ21ኛው ክፍለዘመን ተቀባይነት የለውም፡፡ እንደዚህ ዓይነት ፖሊሲ ይዞ መጓዝ በራሱ ጦረኝነት እንጂ ልማታዊ ሊሆን ኣይችልም፡፡ አሁን የተፈጠረ ሻዕብያ ትተን ግብፅ በታሪካችን ስናያት የኢትዮጵያ ልማት፣ ኣንድነት፣ ሰላም፣ መረጋጋት፣ እንዳይኖር ስትሰራ የነበረችና ኣሁንም በመስራት ላይ ያለች አገር ናት፡፡ ይሁንና እስከ ቅርብ ጊዜ ግብፅ በስራዋ ድል በድል እየተጎናፀፈች የመጣችና የተሳካ ፖሊሲ ነበራት፡፡ ምክንያቱም ከአሁኑ ስርዓት በፊት የነበሩ ገዢዎች ፀረ ህዝብና ፀረ ዴሞክራሲ ከመሆናቸው የተነሳ የኢትዮጵያን ችግር የህዝቡን ችግር በትክክል ማንበብ ስላልቻሉ/ስላልፈለጉ ግብፅ ወደ ኣዘጋጀችው ወጥመድ በመግባት “የሁሉንም ችግሮቻችን ማጠንጠያው በጠላት ጎረቤቶች በመከበባችን ነው” ስለዚህ ታርጌታችን የውጭ ጠላቶችን ማንበርከክ ነው በሚል እሳቤ የውስጥ ችግሮቻችን ሳይፈታ፣ ድህነት እንደፈለገው ሲፈነጭብን በመቆየቱ የመበታተን ኣደጋ ኣንዣብቦብን ነበር፡፡ በጎረቤቶቻችንም በዓይነ ቁራኛ እየተያየን ነበር ዘመናትን ያሳለፍነው፡፡

በዚህ ፖሊሲ መሰረት ኢትዮጵያ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየወደቀች፣ እየደሀየች፣ ሄዳ ሄዳ በመጨረሻ ከውፅዋት ውጭ መቆም የማትችል አገር ሆና ቀረች፡፡ ስለዚህ ሻዕብያ በውስጥ ጉዳዮቻችን እየገባ፣ የኢትዮጵያ ኣሸባሪ ተቃዋሚዎች (ከ500 የማይበልጡ) እያስታጠቀና ለሽብር ተግባር እያሾለከ እየላከ ልማታችን ለማደናቀፍ እየሞከረ ነውና ባለፉት 16 ዓመታት የተከተልነው ፖሊሲ በመከለስ ሻዕብያን ለማስታገስ እንንቀሳቀስ ብንል ይህ ፖሊሲ ሻዕብያ ላይ ብቻ የማይቆምና ቀጥሎም ወደ ግብፅ ብሎም ባህር ማዶ መሄዱ ኣይቀርም፡፡ ይህም ጦረኝነት ነው፡፡ ይህ ኣመለካከት ሻዕብያ ተከትሎት በስተመጨረሻ እኛጋ ሲደርስ ለውድቀት ያደረሰው ትዕቢት ነው፡፡ ስለዚ ቆሞ ማሰብ ያስፈልጋል፡፡

9/ ዋናው ችግር ላይ መረባረብ /የውስጥ ችግር/

የኢህአዴግ መንግስት ይህን አካሄድ በመሰረቱ በመቀየር የሁሉም ችግሮቻችን ምንጭ የውስጣችን ችግር ነው፤ የዚህ ችግር ዋናው ማጠንጠኛ ደግሞ ድህነት ነው፡፡ ድህነት ካላስወገድን ማንም የጎረቤት ጎረምሳ እየመጣ ሊደፍረን ነው፡፡ ጠላታችን ድህነት ነው፣ ድህነት ነው እንድንዋረድ ያደረገን በሚል ኣስተሳሰብ አሁን ኢትዮጵያ የምትከተለው ፖሊሲ ከውስጥ ወደ ውጭ ሆኖ ይህም እንደ ጋሪ ፈረስ ቀንደኛ ጠላታችን የሆነውን ድህነት በመዋጋት ማሸነፍ ነው፡፡

በዚህ “ዘመን የማይሽረው ፖሊሲያችን” መሰረት ድህነትን በማጥፋት ስራችን እሚያደናቅፈን ጠላት እስካላገኘን ድረስ ከመስመራችን ሳንወጣ ልማታችንን የምናፋጥን ሲሆን፣ ይህን ስራችን ለማደናቀፍ እጅና እግራችን የሚይዝ ከመጣ ደግሞ በሙሉ ኣቅማችን ተረባርበን መመከት ነው፡፡ ይህ ሲባል ማንኛውም ትንኮሳ ጆሮዳባልበስ ማለት ሳይሆን ተመጣጣኝ እርምጃ መውሰድ ነው፡፡ በመሆኑ፣ እነሆ የኢትዮጵያ ትንሳኤ ገሃድ ሆኖ በህዳሴ ጎዳና እንገኛለን፡፡

በዚህ ልማታዊ ጎዳና መጓዝ ስለጀመርን ካለፉት 50 ዓመታት በአደጋነቱ ከፍተኛ የተባለው ድርቅ ኣጋጥሞን በራሳችን ዓቅም ተወጥተነዋል፡፡ የዚህ ፈተና በድል መወጣት ምሽጥር በዚህ ልማታዊ ጎዳና መጓዝ ከጀመርን ቦኋላ ያገኘናትን ትናንሽ ትርፍ በማስቀመጣችን ይኸው ለክፉ ቀን ሆና በድርቅ የተጎዱት ህዝቦቻችን ሂይወት ለመታደግ ኣበቃን፡፡ ኣሁን ኣንዳንድ ወገኖች እንደሚያስቡት ስለለማን ትንሽ ማጠራቀም ስለጀመርን፣ እንደ የዓጋም እሾህ ከኛ ጋር ተጠግቶ እያደማን ያለውን የሻዕብያ ስርዓት ነቅለን ለምን ኣንጥለውም ሊባል ይቻላል፡፡

ለመውጋት ምክንያት መደርደር ይቻላል ነገር ግን ውጤቱ ኪሳራ ነው፡፡ ጦርነት ሂይወት ይቀጥፋል (የዋናው የልማት ሃይል የሆነው የወጣቱ ሂይወት)፣ የአገር ሃብት ይበላል፣ በህዝቦች መካከል መቃቃር ይፈጥራል፣ የዲፕሎማሲ ጫና ይፈጥራል፣ እነዚህ ሁሉ ተደማምረው ለድህነት የተመቻቸ ሁኔታ ይፈጥራሉ፡፡ ለምሳሌ ባገኘናት ትንሽ ዕድገት ተኮፍሰን ከድርቁ በፊት የሻዕብያ መንግስት ለማስወገድ ብንሞክር ይሳካልን ይሆን ነበር፡፡ ነገር ግን ባለፈው ዓመት ኣጋጥሞን የነበረውን ድርቅ መቋቋም ኣንችልም ነበር፡፡ ምክንያቱ ያጠራቀምናት ብር በጦርነቱ ስለሚቃጠል፡፡ ድርቅን መቋቋም ካልቻልን ደግሞ ከጦርነት በባሰ የወገኖቻችን ሂይወት ይቀጠፍ ነበር፣ በየደጃፍ ያደጉ ኣገራት እግር ስር ወድቀን የዕርዳታ እህል እንለምን ነበር፡፡ ታድያ ውርደት ማለት የቱ ነው?

1/ የሻዕብያ እብሪት፣ የሻዕብያ ትንኮሳ፣ ከ500 የማይበልጡ የሰው ሃይል ያለው የግንቦት 7 እና የኣርበኞች ኣሸባሪዎች በኩል በሚያደርጉት ጠባጫሪነት ምክንያት ስሜታችን ተቆጣጥረን ወደ ጦርነት ኣለመግባት ነው ውርደቱ? ወይስ

2/ ህዝባችን መቀለብ ኣቅቶን እሚበላና እሚላስ ታጥቶ ሂወት ሲቀዘፍ፣ ወይስ ህዝባችን መመገብ ኣቅቶን ሰርተው ባደጉ ኣገሮች እግር ስር ወድቀን የዕርዳታ እህል መለመን?

ተ.ቁ 1 ነው ውርደት የሚል የለም ማለት ኣይቻልም ወይም ደግሞ ቁ. 2 የሚል የለም ማለትም ኣይቻልም፡፡ ሁለቱም ውርደቶች ውርደት ቢሆኑም የመምረጥ ጉዳይ ግን ካለን የህዝብ ወገንተኝነት ኣመለካከት የሚነሳ ይሆናል፡፡ ሁለቱም የሰው ሂይወት የሚቀጥፉ ቢሆንም የምርጫ ጉዳይ ሲሆን ሻዕብያን በመዋጋት ሻዕብያን ማንበርከክ እርግጠኛ ብንሆን በሻዕብያ ምክንያት የሚቀጠፈውን ሂይወት እናድናለን፡፡ በዚህም ጥርጥር የለም እንኳን ኣሁን ድሮም በሌለን ኣሸንፈነዋል፡፡ ሁለተኛው ድርቅን ማሸነፍ ድህነትን በመዋጋት ድህነትን ማንበርከክ እርግጠኛ ከሆንን፣ በድርቅ ምክንያት የሚቀጠፈው ሂይወት እናድናለን፡፡

በዚህም ጥርጥር የለም ምክንያቱም ድህነትን መዋጋት በመቻላችን በ50 ዓመታት በአደጋነቱ ከፍተኛ የተባለው ድርቅ ስለመከትን፡፡ ታድያ የቱ ነው ውጤታማ? በኔ ምርጫ የሻዕብያ አደጋ ከድህነት ወይም ድርቅ ኣደጋ ኣይበልጥም ወይም ጫፉም ኣይደርስም፣ ስለዚህ ለሻዕብያ ትንኮሳ ትኩረት ሳንሰጥ ወደ ድህነት መዋጋት ትኩረት ሰጥተን ብንሄድ የሻዕብያ ጉዳይ በቆየውና ውጤታማነቱ ቅድም በገመገምነው ፖሊሲ ብንከተል ልማታችን እናፋጥናለን፣ ሻዕብያም በራሱ ጊዜ ይጠፋል፡፡

10/ ኣሁን በኤርትራ ጉዳይ መወሰድ ያለበት እርምጃ ታድያ ምን መሆን ኣለበት

ሻዕብያ ራሱ በለኮሰው ጦርነት በኢትዮጵያ ህዝቦች የተባበረ ክንድ ተደቁሶ የተሸነፈ ቢሆንም፣ ከዚህ ጦርነት በባሰ ወደ ሞት ኣፋፍ ያደረሰው ግን ከጦርነቱ ቦኋላ በተደረጉ ጦርነት ኣልባ ጥቃቶች ነው፡፡ ኢትዮጵያ በተከተለችው ፖሊሲ በዝቅተኛ መስዋእትነትና ኪሳራ በጣም ከፍተኛ ድል በሻዕብያ እንድትጎናፀፍ ኣስችሏታል፡፡ ሻዕብያ ከቁስሉ ኣገግሞ ዳግም እንዳይወረን የተሰራው ስራ ሁላችን ኢትዮጵያውያንም ሰላም ወዳድ ኤርትራውያንም ልንኮራበት ይገባል፡፡ የሻዕብያ መወገድ ከኛ ኢትዮጵያውያን በላይ የሚጠቅመው ለኤርትራ ህዝብ ነው፡፡

የኢሳያስ ኣፈወርቂ ወይም የሻዕብያ ስርዓት መወገድ ለኤርትራ ህዝብ ትልቅ ምዕራፍ እንደሚከፍት ምንም ጥርጥር የለውም፡፡ ምክንያቱም በኣሁኑ ሰዓት የኤርትራ ህዝብ በሻዕብያ ኣሰቃቂ ጭቆና የተነሳ ከማታውቀው መልኣክ የምታውቀው ሰይጣን ይሻላል ከሚለው እምነት በመውጣት የማያውቀውን ሰይጣን እስከ መናፈቅ ላይ የደረሰበት ደረጃ ደርሷል፡፡ ስለዚህ ሻዕብያ የማስወገድ ጉዳይ ለኤርትራ ህዝብ መተው ነው፡፡

ማንኛውም ኢትዮጵያዊ የህዝቡ ሲቃይና ሰቆቃ ያመዋል ይሰማዋል፡፡ ስለዚ ለህዝቡ ቀና ከማሰብና በተጨማሪ ወደ ኢትዮጵያ ለሚመጡት ኤርትራዊያን መልካም ኣቀባበልና እንክብካቤ እንዲሁም በሚያደርገው ትግል ቀናውን መንገድ በማማከርና በመደገፍ ብዙ ስራ መሰራት ኣለበት የሚል እምነት ኣለኝ፡፡ እንዲህ ስል ግን እዚህ ላይም መታለፍ የሌለበት ቀይ መስመር ኣለ፡፡ እሱም በማንኛውም ጊዜ የኣንድ ሃገር ጉዳይ መወሰን ያለበት በሃገሪቱ ህዝብ ብቻ መሆን ኣለበት፡፡ የውጭ ጣልቃ ገብነት ነገሮችን ከማወሳሰብና ጥፋትን ከማባባስ ውጭ እርባና የለውም፡፡ ስለዚህ የኣንድን ኣከባቢ ወይንም ሃገር ጉዳይ በራሱ ባከባቢው ውይንም በሃገሪቱ ህዝብ እንቅስቃሴ ብቻ የሚወሰንበት ቀይ መስመር መሰመር ኣለበት፡፡ የኢትዮጵያ ሚና በኣከባቢ ሰላምና መረጋጋት እንቅስቃሴ ከዚህ ቀይ መስመር መለስ መሆን ኣለበት፡፡

በኤርትራ ውስጥ ተጠልለው የሚገኙ ከ500 የማይበልጡ ኣባላት ያሉት የጉንበት 7 እና ኣርበኞች የኣሸባሪ ቡድን በምንም ተኣምር ለ90 ሚልዮን ህዝብ ባለቤት የሆነች ኢትዮጵያ ስጋት ሊሆኑ ኣይችሉም፡፡ ስሜታዊነታችን መቆጣጠር ኣቅቶን ለነዚህ ሃይሎች ከመስመራችንም ወጥተን ቢሆን የእጃቸውን ለመስጠት ካለን ስሜት ካልሆነ በስተቀር ሻዕብያ ይሁን እነዚህ ኣሸባሪዎች ፖሊሲያችንን የማስቀየር ዓቅሙ የላቸውም፡፡ በኛ መደረግ ያለበት ነገር ቢኖር የጦርነት ኣልባው ጥቃታችን ኣጠናክሮ በመቀጠል እኛ እየተጠናከርን የሻዕብያ ሞትን ማፋጠን ነው፡፡

በሌላ በኩል የኤርትራ ህዝብ ትግል መደገፍ በተመለከተ ህዝባዊ ዓላማ ይዞ የሚንቀሳቀስ ድርጅት ካለ ያለምንም ማወላዳት ኣስፈላጊውን ድጋፍ በማድረግ መደገፍ አይናችን ልናሽ /ልናቅማማ/ አይገባም፡፡ አሁን ያሉት የኤርትራ መንግስት ተቋዋሚዎች ሲታዩ ልክ እንደ የኛዎቹ ተቋዋሚዎች ውጭ አገር ሆኖው ያለምንም መስዋዕትነት በሆነ ተዓምር ሻዕብያ እንዲወድቅላቸው የሚፈልጉና ሰተት ብለው ስልጣን ለመያዝ የሚፈልጉና እርስ በርሳቸው የማይስማሙ ናቸው፡፡ ፀሎታቸውና ምኞታቸው ከተቻለ የኢትዮጵያ መንግስት ሻዕብያን በመደምሰስ ስልጣን እንዲይዙ፣ ካልሆነም በማዕቀብና በሃያላን መንግስታት ጫና ሻዕብያ ከስልጣን በማውረድ ለመተካት የሚፈልጉ ናቸው፡፡

ስለዚህ አሁን በኤርትራ ያሉ ሃይሎች በሙሉ የስም ልዩነት ካልሆነ በስተቀር የዓይነት ልዩነት ያላቸው ኣይመስሉም፡፡ የኤርትራ ህዝዝብ ከማንም ጊዜ በላይ ለትግል የሚያደራጀው ትክክለኛ ኣብዮታዊ ዴሞክራሲ ሓይል ያስፈልገዋል፡፡ በዝርዝር ለማየት እንደተሞከረው፣ በሻዕብያ ፀረ ህዝብና ፀረ ዴሞክራሲ ተግባራት ከማንም በላይ የተጎዳው የኤርትራ ህዝብ ነው፡፡ ይህ የተከፋ ህዝብ በሻዕብያ ላይ ጫናውን ለማሳረፍ መደራጀት፣ መሰባሰብ፣ መነጋገር፣ መመካከር ያስፈልገዋል፡፡ ይህን ለማድረግም የተመቻቸ ሁኔታ መፍጠት ተገቢ ነው ፡፡ .

11/ ታድያ ዘላቂ ሰላምና መረጋጋትና በአገራችን እንዴት ማስፈን ይቻላል?

እላይ ለመጥቀስ እንደተሞከረው ኢትዮጵያ የብዙ ብሄር ብሄረሰቦች አገር ከመሆንዋ ጋር ተያይዞ የተለያዩ ባህል፣ ቋንቋ፣ የኣኗኗር ዘይቤ፣ እምነቶች፣ ሃይማኖቶች፣ ወዘተ ያላት አገር ናት፡፡ ከዚህ ልዩነቶችን የሚነሱ የተለያዩ ፍላጎቶችና ልዩነቶችን መኖራቸው የማይካድ ሃቅ ነው፡፡ እነዚህ ልዩኖቶችና ፍላጎቶችን ኣጣጥሞ የመምራት ጉዳይ ኣንገብጋቢ ጉዳይ ሆኖ ቆይቷል፡፡ ሆኖም ግን ባለፉት ዘመናት እነዚህን ልዩነቶች ኣቻችሎና ኣጣጥሞ ከመምራት ይልቅ ኣንዱን ወገን ከሌላው ወገን በማጋጨት ለመፍታት ይሞከር ስለነበር ባለፉት ጥቂት መቶ ኣመታት የጠባብነትና የትምክህተኝነት ኣፍራሽ ኣመለካከቶች በህዝቡ ዘንድ ስር እየሰደዱ በመምጣታቸው፣ ኣሁን ለደረስንበት ድህነትና ኋላ ቀርነት ትልቅ ኣስተዋፅኦ ኣድርጓል፡፡

ከረጅም ዓመታት የተበታተነ የህዝቦች ትግል እና ከ17 ዓመት መራራ የተደራጀ የህዝቦች ትግል ቦኋላ በህዝቦች ጫንቃ ተጭኖ ለዘመናት ይኖር የነበረውን የትምክህት ስርዓት ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ፣ እንደ ስርዓት ላይመለስ ተንኮታኩቶ ተሰባብረዋል፡፡ ሆኖም ግን ይህን ስርዓት የረጨው የትምክህት ኣስተሳሰብ መርዝና የዚህ ስርዓት ኣስከፊ ጭቆና የወለደው የጠባብነት መርዝ በህዝቡ ውስጥ ተረጭቶ ገና ብዙ የማፅዳት ስራ የሚፈልግ ጉዳይ ሆኖ ይገኛል፡፡ ይህን ኋላቀርና ኣፍራሽ አመለካከት (ትምክህትና ጥበት) በህዝቡና ኣመራሩ ዘንድ ስር ሰዶ በመቆየቱ ኣሁን የምናደርገው የልማትና የዴሞክራሲ እንቅስቃሴ መልኩን እየቀያየረ ብቅ ጥልቅ እያለ እንቅፋት በመፍጠር ላይ ይገኛል፡፡

ለኣብዮታዊ ዴሞክራሲ ትልቅ ፈተና የሚሆነው ይህ የትምክህትና የጠባብነት ኣመለካከት ነው፡፡ ከሻዕብያም ከግብፅም በላይ ኣሳሳቢው ፈተና ትምክህትና ጠባብነት በመሆኑ እዚህ ላይ ለልማት ከምናደርገው ርብርብ በላይ ተረባርበን ካልታገልነው ኣመታትን ጥረን ግረን ያፈራነውን ሃብት በአንድ ጀንበር ሊያወድምብን ነው፡፡ ሃብት ማውደም ብቻ ሳይሆን በህዝቦች መካከል መቃቃር ብሎም እርስ በርስ መፋጀት ያመጣል፡፡ በኢትዮጵያ የትምክህትና የጠባብነት ኣስተሳሰብ እስካለ ድረስ የአገራችን ሰላምና መረጋጋት ዋስትና የለውም፡፡ .

ካለፈው ዓመት (2008 ዓ.ም.) ክረምት ጀምሮ በአንዳንድ የኦሮሚያና የኣማራ ኣከባቢዎች ተፈጥሮ የነበረውን ሁውከት ያሳየን ነገር ቢኖር፣ ለኣመታት ያፈራነውን ሃብት በኣስር ሺዎች የሚቆጠር የስራ ዕድል ፈጥረው የነበሩ የልማት ተቋሞች ህዝብን ይጠቀምበት የነበረው የትምህርት፣ የጤና፣ የውሃና ሌሎች ኣገልግሎቶች የሚሰጡ ተቋሞች በሁለት ሶስት ቀናት በነው ሲጠፉና ዜጎች በማንነታቸው ሲገደሉና ሲንገላቱ ተመልክተናል፡፡ ከነዚህ ፀረ ህዝብ ተግባራት በስተጀርባ የሻዕብያና የግብፅ እጅ እንዳለበት የሚታወቅ ቢሆንም ዋናው መንስኤ ግን የጠባብነትና የትምክህት ኣስተሳሰቦች የወለዱዋቸው ችግሮች ናቸው፡፡

እዚህ ላይ የግብፅና የሻዕብያ ሚና ከኣጨብጫቢነት የሚዘል ኣይደለም ስለዚ ዋናው ትኩረታችን የሁሉም ችግሮቻችን ግንድ የሆነውን ለዘመናት ኣብሮን የነበረውን ትምክህትና ጠባብነት ነቀርሳዎች መሆን እንጂ ለቅርንጫፍ ችግሮች መሆን የለበትም፡፡ ስለ ሻዕብያ ህልውና መጨነቅ ያለበት የኤርትራ ህዝብ እንጂ የኢትዮጵያ መንግስት ኣይደለም፡፡ የሻዕብያና የግብፅ መግብያ በሮች የሆኑት የትምክህትና የጠባብነት ኣስተሳሰቦች በኣብዮታዊ ዴሞክራሲ ከዘጋናቸው የኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላምና መረጋጋት ኣስተማማኝ ይሆናል፡፡

ስለዚህ ክቡር መሪያችን ኣቶ መለስ ዜናዊ የቀየሱልን የልማትና የዴሞክራሲ ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች ዘመን ተሻጋሪ እንጂ በኣራትና ኣምስት ኣመታት የሚከለሱ ወይም የሚበረዙ ኣይደሉም፡፡

ኣገራችን በታሪኳ ኣይታው የማታውቅ የህዝቦች እኩልነት የተረጋገጠባት ሰላምና መረጋጋት እንዲሰፍንባት ያደረገ፣ በተከታታይ ለ15 ዓመታት ፈጣን፣ ፍትሃዊና ቀጣይነት ያለው ልማት እያረጋገጠች እንድትመጣ ያደረገ፣ የሻዕብያ ስርዓት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየሟሸሸ እንዲሄድ ያደረገ፣ ግብፅና ሱዳን በኣባይ ጉዳይ ወደ ሰላማዊ ድርድር እንዲገቡ ያደረገ፣ የመከላከያ ሰራዊታችን ብቃትና ተሰሚነት በፍጥነት እያደገ እንዲሄድ ያደረገ በኣብዮታዊ ዴሞክራሲ እምነቶች የተነደፉ የሰላም፣ የልማትና የዴሞክራሲ ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች ስለያዝን ነው፡፡ ከኣብዮታዊ ዴሞክራሲ ወይም ከልማታዊ ዴሞክራሲ ውጭ ያሉ መንገዶች ሁሉ የጥፋት መንገዶች ናቸው፡፡ ስለዚህም ነው የኣብዮታዊ ዴሞክራሲ ህልውና ጉዳይ የኢህኣዴግ ህልውና ብቻ ሳይሆን የአገራችን ህልውና ጉዳይ ነው የምለው፡፡

**********

Guest Author

more recommended stories