የምግብ ዋስትና ፖለቲካ እና የኢትዮጵያ ሁኔታ

በብዙ ጉዳዮች የተቃዋሚው ጎራና የኢትዮጵያ ምሁራን ኋላ እንደሚቀሩ በግሌ ስገምት ነበር:: አንዱ ምክንያቴ የመንግስትና ህዝብ አስተዳደር ጉዳዮች በተለይም ህዝብ ከሚፈልጋቸው ፕሮግራሞችና ፅንሰ ሀሳቦች ጋር በቀጥታ ያለመገናኘታቸው ነው:: ሌላኛው ምክንያት የተቃዋሚው ጎራ እራሱን ከአዳዲስና አማራጭ የፖሊሲ ሀሳቦች ጋር ከማስተዋወቅ ይልቅ እንትን ይወድቅልኛል ብሎ የሚከተል አይነት በመሆኑ ነው::

ሀገር በብቃት ለመምራት የሀገሪቱን የተሳኩና ያልተሳኩ ትልሞችን፣ የፖሊሲና የህግ ማዕቀፎችን፣ ገዢ አስተሳሰቦችን ብቻ ሳይሆን በክልል፣ በክፍለ አህጉርና በአህጉር አቀፍ እንደዚሁም በአለም አቀፍ ጉዳዮች ላይ የጠራና ከጊዜው ጋር የሚሄድ አስተሳሰብ ያስፈልጋል:: በተለይ በነዚህ ተቋማትና በይነ መንግስታት አስተሳሰቦች፣ ማዕቀፎች፣ ዲፕሎማሲያዊና ፖለሲያዊ ቋንቋዎች መነጋገር ያስፈልጋል::

ኢህአዴግና መሪዎቹ ይህ ዕድል እነሱ ፈልገውት ሳይሆን ፈልጎአቸው ወደነሱ እየቀረበ ነው:: በዚያው መጠን ተቃዋሚዎች ስለፖሊሲና ስትራቴጂዎች ስለማይጨንቁ ከኢትዮጵያ የአመራር፣ ፍላጎት፣ ክህሎት፣ ደረጃና ብቃት እንደዚሁም ከህዝቡ ችግሮች እጅግ እየተራራቁ መሆናቸውን ማየት ይቻላል::

ለዚህም ነው አንዳንድ አስተሳሰቦች ግር ሲላቸው የሚታየው:: በቅርበት ካለመስራት ከህዝቡ ችግሮች የልማት ተግዳሮቶችና እነዚህን ለመፍታት ካሉት አማራጭ ሳይንሳዊ የሁለትዮሽና የሦስትዮሽ ትብብር ሀሳቦች ጋር በቅርበት ያለመተዋወቅ ችግር በብዙዎቹ የተቃዋሚዎች መሪዎችና አክቲቪስቶች ዘንድ በስፋት ይነበባል::

ይህን የክህሎትና የአመለካከት ገደል ለመሙላት በአቅም ግንባታ ብቻ የሚሽፈን አይሆንም:: ሀላፊነት የሚሰማው ተቃዋሚ የፖሊሲ ግምገማ ስልጠናዎችንና ታላላቅ አለም አቀፍ ስብሰባዎችን በመሳተፍና ለአባላቱ የውስጥ ስልጠናና ግንዛቤ ማስጨበጫ ዝግጅቶችን በማዘጋጀት እንደዚሁም አሳሽና ጉዳይ ተኮር ጥልቅ ጥናቶችን በማካሄድ ለአባላቱ ለካድሬዎችና ለአክቲቪስቶቹ ማስተዋወቅና ማንቃት ያስፈልጋል:: እንዲሁ ምርጫ ሲመጣ በርበሬ ቀንጥሱ ወይም ጩኸቴን ቀሙኝ ከሚሆን መታገያ መንገዶችንና ስስ ብልቶችን እየለዩ፣እያሰሱ መቆየት ተገቢ ነው::

ከነዚህ የፖሊሲና የስትራቴጂ ጉዳዮች አንዱ የምግብ ዋስትና ፖሊሲና ስትራቴጂ ነው:: እውነቱን ለመናገር ተቃዋሚዎችም ለአክቲቪስቶቻቸውም በቂ ግንዛቤ ስለሌላቸው ይህን በመሰለ ጉዳይ ላይ በጨበጣ ሲነቁሩና ያለበቂ ግንዛቤ ሲዳክሩ ማየት ይሸክካል::የጨበጣ ውጊያው በዚህ ጉዳይ ብቻ አያበቃም የፖሊሲ ጥያቄ ባለባቸው ጉዳዮች ሁሉ ሲምታታባቸው ማየት የዕለት ተዕለት ጉዳይ ነው:: ይሁንና ለዛሬ በምግብ ዋስትና ጉዳይ ለማተኮር እሻለሁ::

የምግብ ዋስትና ደርዝ

የምግብ ዋስትና ጉዳይ ከ1970ዎቹ ጀምሮ የተያዘ ሰፊ ጽንሰ ሀሳብ ነው:: በ1990ዎቹ መጨረሻ ግን ከሚሊየንየሙ ግቦች የመጀመሪያው ከሆነው ረሀብን የማጥፋት ዘመቻ ጋር እንዲያያዝ ተደርጎ በመታሰቡ ብዙ ሀገሮች የፖሊሲዎቻቸው አካል ካደረጉት ቆዩ:: ኢትዮጵያን በተደጋጋሚ ከሚያጠቃት ረሀብ አንጻር ይህ ዘግይቶ የተፈጸመ ቢሆንም በጣም አስቸኳዩና ቅድሚያ የሚሰጠው ጉዳይ ነው::

በአለም የምግብና እርሻ ድርጅት መረጃ መሰረት የምግብ ዋስትና ያልተረጋገጠላቸው ህዝቦች የ2013 አሃዝ መሠረት 842ሚሊዮን ይደርሳል:: ከአለም ህዝብ 12%ቱ የምግብ ዋስትና አልተረጋገጠለትም:: ይህ አሀዝ በአፍሪካ አህጉር በጠቅላላው 21% ሲሆን ከሰሃራ በታች ባሉ ሀገሮች ብቻ ደግሞ ከህዝቡ 25%ቱ አካባቢ የምግብ ዋስትና ያልተረጋገጠለት ነው:: በኢትዮጵያ በምግብ ጥናት ተቋም መረጃ መሰረት ባለፈው በኢትዮጵያ የምግብ ዋስትናው ያልተረጋገጠለት ከ10 ሰው አንዱ ነው::

በስታንፎርድ ዩንቨርሲቲ መረጃ መሰረት በያዝነው ዓመት መጀመሪያ ላይ ወደ ኢትዮጵያ የመጡት 23 የአሜሪካው የህግ መወሰኛ ምክርቤት ኮንግረስ አባላት ይህ የኢትዮጵያ ለየት ያለ ለውጥ አስደንቋቸዋል:: ባለፈው ዓመት ዘኢኮኖሚስት መጽሔት ባወጣው ጥቅል የምግብ ዋስትና ኢንደክስ መሰረትም ኢትዮጵያ አስደናቂ ለውጥ ማሳየቷ ተመስክሯል:: የቀድሞው የአሜሪካ የእርሻ ሚኒስትር ዳን ግሊክማን የኢትዮጵያ የምግብ ዋስትና መንገድ /አያያዝ/ ሲል አሞካሽቶታል::
የፖሊሲ መሳሪያዎች

የዓለም የምግብና እርሻ ድርጅት /FAO/ እንዲህ አይነት ለውጦች የሚመጡት ሶስት ዋና ዋና ጉዳዮች አብረው መከናወናቸውን ያሳየናል ይላል::
1. ሀገሮች የምግብ ምርትና ምርታማነትን መጨመር የሚያስችሉ ፖሊሲዎችና ማዕቀፎች ሲኖራቸው::በተለይም አነስተኛ አምራቾችን ማዕከል ያደረገና የሚያበረታታ ሲሆን
2. በቅርቡ የአለም አቀፍ እርዳታን በሶስት እጥፍ እያስከነዳ ያለው ከውጭ የሚገባው ሪሚታንስ መጠን መጨመር
3. ለረዥም ጊዜ የቆየ እና ቀጣይነቱ የተረጋገጠ ጠንካራ የምግብ ዋስትና የተመጣጠነ ምግብ ፖሊሲ ፖለቲካዊ ኮሚትመንት ሲኖር ነው ይለናል::

የምግብ ጥናት ተቋሙ/IFPRI/ና የአስፒን/Aspin/ ተቋም የምግብ ዋስትና ስትራቴጂ ቡድን በዚህ ይስማማሉ:: በኢትዮጵያ ባለፉት አመታት 60,000 የልማት ሰራተኞች መሰልጠናቸውንና ለገበሬው እርዳታ ሲያደርጉ መቆየታቸውን በቅድሚያ ያወሳሉ:: የምግብ ጥናት ተቋሙ የጥራጥሬ ምርት እመርታ በአማካይ የዓመት እድገት መጠን እስከ 12% ደርሷል ብሏል:: የዋና ዋና ጥራጥሬዎች ይልድ/ምርት/ በሄክታር ባለፉት 23 ዓመታት ከ30-40% ዕድገት ማሰየቱን ጠቅሰው ለዚያ የእርሻ ምርምር ተቋማት ላይ ከፍተኛ ትኩረትና የመዋዕለ ነዋይ ፍሰት ትክክለኛ እርምጃ አድርገው ይመለከቱታል::

የምግብ ዋስትና ደረጃዎች

የምግብ ዋስትና ሦስት ደረጃዎች አሉት:: ሦስቱም ደረጃዎች ካልተሳኩ የምግብ ዋስትና ሙሉ በሙሉ ተረጋግጧል ማለት አይቻልም:: ነገር ግን በየደረጃው የምግብ ዋስትና አረጋግጠናል የሚል ግቦችን ማስቀመጥ ይቻላል:: በዚህ መሰረት

1. በሀገር/ክፍለ ሀገር/ክልል ደረጃ ያለ የምግብ ዋስትና

በሀገር ደረጃ የምግብ ዋስትና ተረጋግጧል ማለት ሁሉም ኢትዮጵያዊ የምግብ ፍላጎቱን ሊያሟላ የሚያስችለው በቂ ምግብ በሀገር ውስጥ ተመርቷል ማለት ብቻ ነው:: ነገር ግን ይህ ዋስትና የተመረተው ምግብ ተፈላጊነት፣ የምግቡ ተመራጭነትን እና አቅርቦቱ በሁሉም ቦታ ይደርሳል የሚለውን አያካትትም:: በሀገር ደረጃ ማለት እንደ ኢትዮጵያ ነው:: ሌላው ቀርቶ የትኛውም ክልል የሚበቃውን ምግብ በአይነት በአይነቱ አምርቷል ማለት አይደለም:: የእያንዳንዱን ሰው በየሳምንቱ ስጋ የመብላት አቅም አለው ማለትም አይደለም::

የምግብ ምጣኔ እና የመለኪያው ግርድፍነት

በተቃራኒው ይህ መለኪያ ስጋን ወይም ስጋ የሚሰጠውን ጥቅም ሊወክሉ የሚችሉትን የምግብ አይነቶች ሁሉ በካሎሪያቸው ስለሚመዝን በካሎሪያቸው ምጣኔ በኩል እኩል አድርጎ ነው የሚያቸው:: 1ኪሎ ስጋ ከ1ኪሎ ሽሮ ጋር እኩል ካሎሪ ካላቸው አንድም የእንሰሳ ተዋጽኦ በሳምንቱ የምግብ ቅርጫትህ ሳይቀላቀልም ከስጋ የሚገኘውን ጥቅም ሁሉ እንዳገኘህ ተደርገህ ልትቆጠር ትችላለህ:: ይህ የመለኪያው ድክመት ነው::

የምግብ ዋስትና አረጋግጠናል ሲባል ሁሉም ህዝብ በሳምንት አንድ ቀን አሳ መብላት ይችላል ማለት አይደለም:: የምግቡን ስብጥር ፣የምግብ ዝግጅት ባህልና ልምድን፣ ምርጫን፣ በተወሰነ ደረጃም አብዛኛው ህብረተሰብ በእሴት ደረጃ ከፍ አድርጎ የሚወስደውን የምግብ አይነትን፣ የማግኘትና የመጠቀምን አቅም አይወክልም::

የምግብ ዋጋና የጣዕም ምርጫ

የምግብ ዋጋ እንደማንኛውም መሰረታዊ ተፈላጊ ዕቃ በገበያ ይመራል:: ዋጋ ከዕቃው የምታገኘውን እሴት/value/ ብቻ ሳይሆን ስምምነትንና ማህበረሰቡ ለዕቃው ያለውን አጠቃላይ አመለካከትም ያንጸባርቃል ተብሎ ይታሰባል::ለምሳሌ አሳ በማህበረሰባችን ዘግይቶ የተዋወቀ ምግብ ነው:: የኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን አባቶች አስረግጠው ዓሳን አትብሉ! ጾም ነው! ለማለት ተቸግረው እንደነበር በኔ ዕድሜ አስታውሳለሁ::

በ1980ቹ ሁለተኛ አጋማሽ አካባቢ አርባምንጭ ብትሄድ ከጉልት በ2ብር እስከ 3ኪሎ አሳ ወይም ከእርሻ ልማት 4ኪሎ ሙዝ ትገዛ ነበር:: በዚያው ጊዜ ግን አንድ ኪሎ የበሬ ስጋ ከ6-10 ብር ነበር:: አሳው ከበሬ ስጋ በጥቅም አንሶ አይደለም እንዲያውም ይበልጣል:: አንድ በብዛት ስለሚገኝ/ስለሚመረት/ ነው:: ሁለትም ለአሳ የምግብ ጥቅም ያለው አመለካከት ዝቅተኛ ነው:: ስለዚህ ይህን አይነት የማህበረሰቡ አመለካከት በዋጋውም ላይ ተጽዕኖ ነበረው:: ከአካባቢው ውጭ ያለው የምግብ ግንኙነትም ዝቅተኛ ነው:: ዘግይቶ እነዚህ ጉዳዮች ተቀይረዋል::

የቀን አማካይ ካሎሪና የምግብ ምጣኔ ኦፕቲማይዜሽን

ስለዚህ ጥያቄው መሆን ያለበት የተመረተው ምግብ ለመኖር የሚያስፈልገውን በቀን 2,200 ኪካሎሪ ለእያንዳንዱ ግለሰብ በተለመደው የምግብ ዓይነት የመስጠት አቅም አለው ወይ? ነው:: ይህ ኪካሎሪ እንደግለሰቡ ጾታና የስራ ጠባይ ሊለያይ ይችላል:: እዚህ ላይ የተቀመጠው አማካይ ካሎሪ ብቻ ነው::

እንደምርጫህ እና ከሽሮ በላይ የመብላት አቅምህን የሚለካው ግን የገቢህ መጠን ነው:: ያንን ለመገበያየት የሚያስችል የሚመነዘር እሴት ፈጥረሀል ወይ ነው? የእያንዳንዱ ሰው የግል ቴስትም ውሳኔም ይጨመርበታል:: አሳ የማይወደው ሰው ሽምብራ አሳ የሚወክልውን ካሎሪ ያገኛል:: አለያ ከምንቸት የሚገኘውን ካሎሪ ትክን ካለች ሽሮ ለማግኘት ትሞክራለህ::

ምርት፣ የሰብል ምርጫና ምርታማነት

ሌላው ጉዳይ በቂ ምግብ ሀገር ውስጥ ተመርቷል ማለት የምንፈልገው የምግብ ዓይነት ሁሉ ሀገር ውስጥ ተመርቷል ማለት አይደለም:: እንደምታውቀው አንዳንድ ጥራጥሬዎች በብዛት ሊመረቱ ይችላሉ:: አንዳንዴም ሀገር ውስጥ ልንጠቀም ከምንችለው በላይ ሊሆን ይችላል:: ለምሳሌ ባለፈው ዓመት 400,000ኩንታል በቆሎ ከኢትዮጵያ ገበያ ለሌሎች ሀገሮች ልከናል:: በበቆሎና በስንዴ ምርት በአፍሪካ ሁለተኛ ነን::

ይሁንና የስንዴ ፍላጎታችንን ማሟላት አልቻልንም:: ጤፍም እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ተፈላጊነቱም በሄክታር የሚሰጠውም ከሌሎች ሰብሎች አንጻር ዝቅተኛ ነው:: አንድ ገበሬ 1ኩንታል ስንዴ በማምረት የሚያገኘው የስንዴ ዋጋ ከሁለት ኩንታል በቆሎ የሚያገኘው ከሆነና ከአንድ ሄክታር መሬት የሚያገኘው በቆሎ ከሁለት ሄክታር መሬት ከሚያገኘው ስንዴ የሚበልጥ ከሆነ ወይም ወጪውን የሚቀንስለት ከሆነ በቆሎን መምረጡ አይቀርም::

በ2008 በIFPRI በተዘጋጀ ጥናት መሰረት በቆሎን ኢትዮጵያ ውስጥ ማምረት ከጠቅላላው ድሃ ሀገሮች yield ይልቅ የተሻለ ምርታማነት አለው:: ለምሳሌ ሌላ ያላደገ ሀገር ከማምረት ኢትዮጵያ ውስጥ ማምረት በሄክታር 168% ምርት እንዲጨምር ምክንያት ይሆናል:: ከምስራቅ አፍሪካ ጋር ያወዳደርን እንደሆን ደግሞ የኢትዮጵያ አንድ ሄክታር በቆሎ ምርት የምስራቅ አፍሪካውን አማካይ 141% ይሆናል::

በዚህ ሁኔታ በቆሎ ከስንዴ ይልቅ ብዙ ሊመረት ይችላል:: ሰሊጥ ብዙ ይመረታል:: ሌሎች ሀገሮች ደግሞ ከኛ ይልቅ ሩዝ ብዙ ይመረታል:: በወጪም ደረጃ ተወዳዳሪ በሀገር ውስጥ ከማምረት ይልቅ ከነሱ መግዛት ያዋጣ ይሆናል:: ስለዚህ ቀለል ባለ ወጪ የሚመረተውን ሰሊጥ ልከን ሩዝ እንገዛለን:: ወይም በቆሎ ለኢንዱስትሪያቸው ሰጥተን በስንዴ እንለውጣለን:: ሁሉም ሀገር ሀገሩ ማምረት የማይችለውን ከውጭ ያስገባል:: ሙሉ በሙሉ ፍላጎቱን በሀገር ውስጥ የምግብ ምርት የሚያሳካ ሀገር የለም::

የምግብ ንግድ ሚዛን

የተዘጋ ኢኮኖሚ ሞዴል የምንለውና ሁሉንም የምግብ ፍላጎቱን በሀገር ውስጥ ምርት የመሸፈን ስትራቴጂ በዚህ ዘመን አይሰራም:: ሌላው ቀርቶ የአውሮፓ ህብረትና የዩስ አሜሪካ ለገበሬዎቻቸው የሚሰጡት ከፍተኛ የእርሻ ድጎማ ይህንን አላስቻላቸውም:: አንድም ከነጻ የኢኮኖሚ መርህ አንጻር አለምዓቀፍ ቅዋሜ አስነስቷል:: በ2013 ከኢትዮጵያ ለአውሮፓ ከተላከው የውጭ ንግድ ገቢ ውስጥ 50% የተገኘው ከምግብ ኤክስፖርት ነው:: ከአውሮፓ ህብረት ካስገባነው የንግድ ሸቀጥና አገልግሎት ውስጥ ደግሞ 3.9% ብቻ ነው ምግብን የሚመለከተው:: በዚያው ዓመት ከውጭ ያስገባነው ስንዴ ከአጠቃላይ የገቢ ንግዳችን ዋጋ 4.2% ብቻ ነው::

ሌላው በመጠኑ ገርበብ አርገው በከፍቷቸው በሮች የላቲንና የሌሎች ሀገሮች ምርቶች አውሮፓ ድረስ ሄደውና ከነድጎማቸው የአውሮፓውያንን ገበሬዎች ምርት ተወዳዳሪነትና ዋጋ እየጣሉባቸው ነው:: ይህን ፖሊሲ አውሮፓውያኑ በቅርቡ ተገደው ማንሳታቸው አይቀርም::ይህ የዓለም የንግድ ድርጅት ክርክሮች ዋነኛ አካልና የሰሜን ደቡብ የንግድ ንትርክ ትልቁ ክፍል ነው :: ለዚህም ነው አብዛኛው ሄጅ ፈንዶች ወደ አፍሪካ ኤዥያና ደቡብ አሜሪካ በመሄድ መሬት እየተቀራመቱ ያሉት::

ዩስ አሜሪካና የምግብ ንግድ ሚዛኗ

ዩስ አሜሪካ ከጠቅላላው አለም ጋር ያላት ንግድ ሚዛን በ17% አካባቢ ጉድለት አለው::የሀገሪቱ ኤክስፖርት የምታስገባውን አይሸፍንም:: የአሜሪካውያን የምግብና ምግብ ነክ ግብይት በ2013 ደግም ይህን ይመስላል:: በተጠቀሰው ዓመት አሜሪካ ለውጭ ገበያ ያቀረበችው ምግብና ምግብ ነክ የኤክስፖርት ጠቅላላ ዋጋ/እሴት/ 136ቢሊዮን ዶላር ወይም የጠቅላላ የወጪ ንግዷን 6% አካባቢ ሲሆን ወደ ሀገር ውስጥ ያስገባችው የምግብ ኢምፖርት ደግሞ 115ቢሊዮን ዶላር ዋጋ ያለውና 4.2% የጠቅላላ ገቢ ንግዷን ወይም ኢምፖርቷን እሴት ይዟል::

የምግብ ዋስትና እና የምግብ ገቢ ንግድ

ከላይ ያቀረብኳቸው መረጃዎች የሚያሳዩት የምግብ ገቢ ንግድ ማለት የምግብ ዋስትና ወይም እጥረትን በግድ ያሳያል ማለት እንዳልሆነ ነው:: ሽሪምፕ ወይም ሎብስተር አምሮህ ወደ ሬስቶራንት ብቅ ያልክ እንደሆን በኢትዮጵያ ሁኔታ የገቢ ንግዱን ፍላጎት ከፍ አደረግህ ማለት ነው:: እነዚህ ባአብዛኛው ከባህርና ውቅያኖሶች የሚገኙ ስለሆነ በኢትዮጵያ አምራች የላቸውም:: የውጭ ፓስታ ወይም ሩዝ ተዋጽኦዎችም ይህንን አይነት ሚና ይጫወታሉ::

በነገራችን ላይ ያደጉት ሀገሮች በሀገር ደረጃ 2% የሚሆን ህዝባቸው የምግብ ዋስትናው እንዳልተረጋገጠ የአለም ምግብና እርሻ ድርጅት የ2013 መረጃ ያሳያል::በተመሳሳይ አመት በኢትዮጵያ የምግብ ርዳታ የሚሹትና በዚህ ላይ የሚመረኮዙት ሰዎች ወደ 10% አካባቢ እንደነበር የተጠቀሰ ሲሆን ዘንድሮ ወደ 7% ወርዷል የሚሉ መረጃዎች ወጥተዋል::

2. በቤተሰብ ደረጃ ያለ የምግብ ዋስትና

የቤተሰብ ደረጃ የምግብ ዋስትና እንኳን ኢትዮጵያ ያደጉት ሀገሮችም ሙሉ በሙሉ ያሳኩ አልመሰለኝም::ለምሳሌ ፊዲንግ አሜሪካ የተባለ ፕሮጀክት እንደገለጸው ከ6 ሰዎች አንዱ አሜሪካ ውስጥ ይራባል ወይም የምግብ ዋስትና የላቸውም:: በ2012 49 ሚሊዮን ህዝቧ የምግብ ዋስትና ችግር በተደቀነበት ቤተሰብ ኖረዋል ሲል ዘግቧል::

ከነዚህ ውስጥ 1/3ኛው ህጻናት ሲሆኑ አንድ ሚሊዮን የሚሆኑት የመጨረሻው ደረጃ ሴፍቲ ኔት አካል የሆነው የፉድ ስታምፕ እንኳን አይደርሳቸውም ሲል ኤም ኤስኤንቢሲ ባለፈው ወር ዘግቧል:: ኢትዮጵያ ውስጥ በገጠሩ አካባቢ ከ10 ሰዎች አንዱ በሴፍቲ ኔት ፕሮግራም ታቅፈው ብታገኝ በሀገር ደረጃ የምግብ ዋስትና አልተረጋገጠም ማለት አያስችልም:: የሴፍቲ ኔቱ ፕሮግራም በራሱ የምግብ ዋስትናው አካል ነው ማለት ነው::

3. በግለሰብ ደረጃ ያለ የምግብ ዋስትና

ይህን የምግብ ዋስትና የሚያሟሉ በዓለም ላይ ጥቂት የሰሜን አውሮፓ ሀገሮች ናቸው ተብሎ ይገመታል:: ይሁንና ከላይ እንደተጠቀሰው በነዚሁ ሀገራት ይህ የማይሆንበት ሁኔታ ብዙ ምክንያቶች አሉ:: ለምሳሌ ኖርዌይ ውስጥ የሚኖር ዕውቅና ያልተሰጠው ስደተኛ ይህ ባይጠበቅለት አይገርምም:: ነገር ግን እነዚህ መንግስታት አንድን ሰው ሊያኖረው የሚችል ዝቅተኛ ገንዘብ በየወሩ ይሰጡታል:: በዚህም የተነሳ በነዚህ ሀገሮች በሱስና መሰል የግለሰቡ ውሳኔ ችግሮች ካልሆነ የምግብ እጥረት ችግር አያጋጥመውም ተብሎ ይጠበቃል:: ይህ ዝቅተኛ የመኖሪያ ገቢ በማይሰጥባቸው ወይም በቂ ባልሆነበት ሀገሮች ግን ችግሩ አለ::

የምግብ ዋስትና ላይ ያጠናቀርኩትን እዚህ ላይ አበቃሁ:: ቸር ሰንብቱልኝ::
**********

Reagan Solomon

more recommended stories