Sendek | ኢህአዴግ – ከአብዮታዊ ዲሞክራሲ እስከ መለስ ራዕይ

(በዘሪሁን ሙሊጌታ)

አቶ መለስ በሞት ከተለዩን ከሁለት ወራት በላይ ሆናቸው። ኢህአዴግ አቶ መለስን በአቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ ተክቶ ጉዞውን ከጀመረ ከአንድ ወር በላይ ተቆጠረ። ኢህአዴግ አቶ መለስን በአቶ ኃይለማርያም ቢተካም የእሳቸው ራዕይ ግን እንደሚቀጥል አስታውቋል። ስለሆነም በእያንዳንዱ የድርጅቱና ሀገራዊ እንቅስቃሴዎች ውስጥ የአቶ መለስ መንፈስና ራዕይ ዋነኛው የፖለቲካ ማጠንጠኛ ሆኗል።፡

ወ/ሮ አዜብ መስፍን የቀድሞ የጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ባለቤት እንዳሉትም የአቶ መለስ ራዕይ ሳይበረዝና ሳይከለስ እንዲቀጥል የተወሰነ ይመስላል። ድርጅቱም ባልተለመደ መልኩ የፖለቲካ አቅጣጫው «ከአብዮታዊ ዲሞክራሲ» የመለስ ራዕይን ወደማሳካት የተቀየረ ይመስላል።

ኢህአዴግ ድንገትና ባልተጠበቀ ሁኔታ ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩትን አቶ መለስ ዜናዊን ሀዘን ወደ ልማትና የጋራ ተነሳሽነት መለወጥ በሚል የታችኛውን፣ መካለኛውና ከፍተኛውን አመራር በማሰልጠን ሥራ ላይ ተጠምዷል። ከሰሞኑም በርካታ ሰብሰባዎች በሀገሪቱ የተለያዩ ከተሞች እየተከናወኑ ይገኛሉ።

እነዚህና ከነዚህ ጉዳዮች ጋር በተያያዘ አቶ መለስ ካለፉ በኋላ የኢህአዴግ ባህሪና የመለስን ራዕይ በማሰቀጠል ዙሪያ ስላሉ ሁኔታዎች የተለያዩ የፖለቲካ ምሁራንን አነጋግረናል። ከአንድነት ፓርቲ የፓርቲውን የጽ/ቤት ሃላፊ አቶ አስራት ጣሴ፣ ከአረና አቶ ብርሃኑ በርኧና የሰማያዊ ፓርቲ ፕሬዝዳንት ኢንጂነር ይልቃል ጌትነትን እንዲሁም በግል በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የታሪክ ትምህርት ክፍል መምህር የሆኑትን አቶ አበባው አያሌውን ጋብዘናል።

የአንድነት ፓርቲ የጽህፈት ቤት ኃላፊ የሆኑትና እና ለረጅም ጊዜ በተቃዋሚ ፓርቲ አመራርነት የቆዩት፣ በትምህርት አስተዳደር ጋር በተያያዘ በትምህርት ሚኒስቴር ውስጥ ሰፊ የሥራልምድ ያላቸው አቶ አስራት ጣሴ ከአቶ መለስ በኋላ የኢህአዴግ የፖለቲካ ባህሪ በአንድ ማጠንጠኛ ላይ ትኩረት ማድረጉን ገልፀዋል።

«አቶ መለስ ካለፉ በኋላ ኢህአዴግ ሙሉ በሙሉ የአቶ መለስን ራዕይ እናስቀጥላለን በሚል አስተሳሰብ ውስጥ ገብቷል። ይሄ መርህ ደግሞ ኢህአዴግ ከሀዘኑ በኋላ በወጣው መግለጫ» «ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ የሰነቁትን ራዕይ ይዘን እናስፈፅማለን»ብሏል። መግለጫው አብረን የሰነቅነውን ራዕይ የሚል ነገር እንኳ የለውም» ያሉት አቶ አስራት ይህ አካሄድ ለእርሱ ለኢህአዴግም ሆነ ለሀገር የሚበጅ አይደለም ይላሉ።
አልበርት አነስታይን «ችግሩን በፈጠረው አስተሳሰብ ችግሩን መፍታት አይቻልም» ማለቱን የጠቀሱት አቶ አስራት አቶ መለስም የአብዮታዊ ዲሞክራሲ ብቸኛ ደራሲ መሆናቸውን በማስታወስ አሁን ያሉት የኢህአዴግ አመራሮች እነሱ ያልተሳተፉበትን ድርሰት እናስፈፅማለን እያሉ ነው ብለዋል። ስለሆነም አሁንም ከአቶ መለስ ራዕይ በሻገር የቡድን ራዕይ፣ የሀገር ራዕይ ነው የሚያስፈልገው ብለዋል።

የሰማያዊ ፓርቲ ፕሬዚዳንት የሆኑት ኢንጂነር ይልቃል ጌትነት በበኩላቸው ከአቶ መለስ ህልፈት በኋላ የኢህአዴግ የፖለቲካ ባህሪ ድርጅቱ መዳከሙን የሚያሳይ እንደሆነ ነው የሚገልፁት ። እንደ ኢንጅነር ይልቃል እምነት ኢህአዴግ ከአቶ መለስ ህልፈት በኋላሁሉንም ነገር በአቶ መለስ ላይ የመንጠልጠል አዝማሚያ ማሳየቱም የመዳከሙ አንዱማሳያ ነው።

ኢህአዴግ የመለስን ራዕይ በማስፈፀም ዙሪያ ለመመሸግ የተገደደው በአቶ መለስ ድንገተኛ ሞት በመደናገጡ ነው የሚሉት ኢንጅነር ይልቃል፤ ኢህአዴግ ከ1993 የህወሃት መከፋፈል በኋላ አቶ መለስ ገንብተውት የነበረውን የግል አምልኮ በማጉላት ድርጅቱ ያለበትን ውስጣዊ አለመረጋጋትን በመሸፋፈን፣ በውስጡ ያሉ ክፍተቶችን ለመሙላትና ጊዜ ለመግዛት ያደረገው ጊዜአዊ የፖለቲካ መፍትሄ መሆኑን ነው የገለፁት።

«ኢህአዴግ የጋራ አመራር ወይም የግለሰብ አመራር መፍጠር ያልቻለበት፣ ግልፅ የፖለቲካ ስልጣን ከእነማን እጅ መሆኑ በውል ያልታየበት ሁኔታ ተፈጥሯል»ያሉት ኢንጅነር ይልቃል ኢህአዴግ በግልፅ ወደ መጠባበቅ ፖለቲካ የገባበትና የወደፊት ሁኔታው ያለየበት ታሪካዊ አጋጣሚ መፈጠሩን ነው ያመለከቱት።

ይህ የመጠባበቅ ፖለቲካ በአጠቃላይ በሀገሪቱ የፖለቲካ አየር ላይ የራሱ ተፅዕኖ ሊያሳድር እንደሚችል የገለፁት ኢንጂነር ይልቃል፤ በሀገሪቱ ስራን የማስፈፀም አቅም ይዳከማል፣ ምናልባትም በኢህአዴግ አባል እና አጋር ድርጅቶች ውስጥ ያልተጠበቁ ቅሬታዎች ተፈጥረው ምስጢር የማውጣትና ያለመተማመን ስሜቶች በሂደት ተፈጥሮ ኢህአዴግ ይበልጥ ሊዳከም እንደሚችል ገልፀዋል። የኢህአዴግን መዳከምን ተከትሎ ሙስናና ብልሹ አሰራር፣ የሀገር ደህንነት አደጋ ላይ የመውደቅ ሁኔታ ተፈጥሮ በሀገሪቱ ላይ መዳከምን ሊፈጥር ይችላል ሲሉ ገምተዋል። በልምድ በአንዳንድ ሀገራት ወታደሩ በራሱ የፖለቲካ ሃይል ሆኖ የሚወጣባቸው አጋጣሚዎች ቢኖርም በእኛ ሀገር ግን ወታደራዊ ሃይሉ በፖለቲካ የበላይ ከሆነው አካል ጋር ሲቆም ነው የሚታየው ብለዋል።

«በእርግጠኝነት ለመናገር የሚቻለው አቶ ሃይለማርያም እስካሁን ድረስ የትኛውንም አይነት ኃይል እንደሌላቸው መናገር ይቻላል። በፓርላማ ቀርበው ካደረጉት ንግግርና አቀራረብ ተነስተን ብንመዝናቸው። የሌላቸውን ስልጣን እንዳላቸው ለማስመሰል (Posturing) አይነት ነው»ያሉት ኢንጅነር ይልቃል አቶ ኃይለማርያም በአንዳንድ ጉዳዮች እርግጠኛ ያለመሆን እና የሀሳብ መቆራረጥ አሳይተዋል። አቶ መለስን ለመሆን ከፍተኛ ጥረት ሲያደርጉም ተስተውለዋል ብለዋል።

ኢህአዴግ አሁን ያለበት ተጨባጭ ሁኔታዎች ሲደማመሩ የኢህአዴግን መዳከም ያሳያሉ የሚሉት ኢንጂነር ይልቃል፤ ኢህአዴግ በቀጣይ በሚፈጠርበት የማስፈፀም አቅም መጓደልን ተከትሎ፣ የአመራር መክዳትን ጨምሮ ምስጢር አፈትልኮ የመውጣት እድል ሊኖር እንደሚችልም አመልክተዋል።

ኢህአዴግ በተበታተነ ሃይል የሚጠለፍ ከሆነ ድርጅቱ ሄዶ ሄዶ ይቆማል ያሉት ኢንጅነር ይልቃል ኢህአዴግ «የመለስ ራዕይ እናስፈፅማለን» በማለት 21 ዓመት በስልጣን ላይ ቢቆይም ካድሬዎቹን መልሶ እንደ አዲስ ለማነቃቃት የሚያደርገው ጥረት ሲታይ ድርጅቱ ወደ መዳከም እያመራ መሆኑን የሚያመለክት ነው ብለዋል።

አቶ ብርሃኑ ብርኧ ለረጅም ጊዜ የህወሀት አባል የነበሩና በአግአዚ ኦፕሬሽን ከመቀሌ እስር ቤት ከወጡ ታጋዮች አንዱ ነበሩ። በኋላም የድርጅቱን አካሄድ በመቃወም ከአረና መስራቾች በፊት የወጡ ታጋይ ናቸው። ከሲቪል ሰርቪስና ከህንድ ዩኒቨርስቲ በህግ የመጀመሪያና የማስተርስ ዲግሪ አላቸው። አረና የድርጅቱ ሊቀመንበር ከሁለት የምርጫ ጊዜያት በላይ መመረጥ የለበትም የሚል ደንብ ያለው በመሆኑ ዘንድሮ የአቶ ገብሩ አስራት የስልጣን ጊዜ ስለሚጠናቀቅ ጠበቃው አቶ ብርሃኑም ይተኳቸዋል ተብሎ ይጠበቃል።

ያም ሆኖ አቶ ብርሃኑ እምብዛም ከፊት አመራር ላይ የማይታዩ ቢሆንም ከጠንካራ የአረና አመራሮች አንዱ ናቸው። እሳቸውም ከአቶ መለስ ህልፈት በኋላ የኢህአዴግ ፖለቲካዊ ባህሪ በተመለከተ ሲናገሩ ኢህአዴግ ከ1983 እስከ 1993 ዓ.ም ድረስ ኮሚቴአዊ ወይም የጋራ አመራር መርህን ይከተል እንደነበር አስታውሰዋል። ይሁን እንጂ ድርጅቱ ይመራበት የነበረው «አብዮታዊ ዲሞክራሲ»በመሆኑ ለዲሞክራሲ ተፃራሪ የሆኑ መርሆዎችን እንደ ግለሰብም እንደ ቡድንም ይከተል እንደነበር ጠቅሰዋል።

ከ1993 ዓ.ም ወዲህ ያለው የኢህአዴግ ባህሪ ድርጅቱ በአንድ ሰው ፈላጭ ቆራጭነት የፖለቲካ ሁኔታ ውስጥ መውደቁ ነው ያሉት አቶ ብርሃኑ አሁን ከአቶ መለስ ህልፈት በኋላ ሁሉም የኢህአዴግ ሰራዎችን የአቶ መለስ የማድረግ አካሄድ ነው ብለዋል። በሌላ አነጋገር (ኢህአዴግ = መለስ ወይም መለስ = ኢህአዴግ) መርህን እየተከሰተሉ መሆኑን በመጥቀስ የአብዮታዊ ዲሞክራሲ መርህንም እንደማይለቁ በመግለፅ ማወጃቸውንም አስታውሰዋል።

በመሆኑም እንደ አቶ ብርሃኑ አገላለፅ ኢህአዴጎች ያላቸው አማራጭ ሁለት መሆኑን አውስተዋል። የመጀመሪያው አብዮታዊ ዲሞክራሲን ትተው ወደ ዲሞክራሲ መግባት ወይም አብዮታዊ ዲሞክራሲውን በመያዝ የአምባገነን ስርዓቱን ማስቀጠል ነው ብለዋል። ያም ሆኖ ኢህአዴግ በቀላሉ ወደ ዲሞክራሲ ይመጣል ተብሎ የማይታሰብ በመሆኑ የያዙት መንገድ ይዘው ቀጥለዋል ብለዋል።

ይሁን እንጂ አቶ መለስ የድርጅቱ ቁልፍ ሰው ስለነበሩ እሳቸውን ማጣት በኢህአዴግ ውስጥ ቅጥ ያጣ መደናገጥ መፍጠሩን አቶ ብርሃኑ ሳይገልፁ አላለፉም። የተደናገጠ አካል ደግሞ እንግዳ የሆኑ ባህሪዎችን ማሳየቱ አይቀርም ብለዋል።

«ኢህአዴግ የተረጋጋ ህልውናው እንዳለ መቀጠሉን ማረጋገጥ ስለሚፈልግ ከነበረው ጸረ ዲሞክራሲያዊ አሰራርና ተግባር በባሰ ሁኔታ ሊመጣ ይችላል። ይህም የተለያዩ የፕሬስ ውጤቶችን ማፈን፣ በትግራይም ህወሃት የአቶመለስ ዜናዊ የቀብር ሥነ- ሥርዓት ከመፈፀሙ በፊት በአዋጅ ወደተራ ስድብ መውረዱና ከዚህም አለፍ ሲል ተቃዋሚዎችን የሚያሸብር ፕሮፓጋንዳ ተከትሏል» ሲሉ አቶ ብርሃኑ ይናገራሉ።

በአሁኑ ወቅት ኢህአዴግ መሸበሩን የሚያመለክተው አመራሩና ተመሪው በስብሰባ መጠመዱ ነው ያሉት አቶ ብርሃኑ በትግራይ የመንግስት ስራመቆሙንና በመንግስት ገንዘብና ጊዜ «የመለስን ራዕይ እናስቀጥላለን» እያሉ አቶ መለስ እንደነበሩ ጊዜ እንደሚሆነው መንግስትና ፓርቲ አደባልቀው ከፖለቲካ ስልጣን ባለፈ የኢኮኖሚ ስልጣኑን በመያዝ፣ በሙስና ሀብት በማጋበስ ላይ ጠንክረው እየሰሩ ነው ብለዋል። ይሄም አልበቃ ብሎ የተጨነቀው የህወሃት /ኢህአዴግ አመራር አስጨናቂ የአስተዳደር ገፅታ ውስጥ መግባቱን ነው ያብራሩት።

አቶ አስራት ጣሴ በበኩላቸው የአቶ መለስ ራዕይ መፈተሸ አለበት ይላሉ። ኢትዮጵያ እንደሀገር ለመቀጠል ብዙ የሚያሳስቡ ችግሮች አሉባት። የኢህአዴግ መንግስት በኢትዮጵያ ህዝብ ተቀባይነቱና አክብሮቱ የላላ መሆኑ፣ የተወሰኑ ሰዎች በአንድ ሌሊት ሚሊየነር ሆነው የምድርን ገነት የሚቀጩበት፣ አብዛኛው ህዝብ በድህነት እየማቀቀና በቀን ሶስት ጊዜ ቀርቶ አንዴ እንኳ ለመብላት የሚፈተንበት ጊዜ ነው ።የዋጋ ግሽበት ህዝቡን እያመሰ ነው፣ ሰብዓዊ እና ዲሞክራሲያዊ መብቶች በፊት በር በኩል ተሰጥተው በጓሮ በር የተነጠቁበትና የይስሙላ የኢኮኖሚ እድገት ነው። በጥቅሉ በአብዮታዊ ዲሞክራሲ መርህ ይህች አገር ችግር ስለማይፈታ የአቶመለስ ራዕይ መፈተሸ እንዳበት ነው አቶ አስራት የጠቀሱት።

ሌላው ከአቶ መለስ ህልፈት በኋላ ኢህአዴግ ተዳክሟል ለማለት በቂ ማስረጃ እንደሚያስፈልግ የጠቀሱት አቶ አስራት የሆኖ ሆኖ መዳከሙን የሚጠቁሙ ምልክቶች ግን መኖራቸውን አልሸሸጉም። ይህም የኢህአዴግ ራዕይ የአንድ ሰው ብቻ መሆኑ፣ ያም ሰው አቶ መለስ መሆናቸውና እሳቸው ካለፉ በኋላ የታዩ ግርግሮች የሚጠቀሱ ምልክቶች ናቸው። በተጨባጭም አሁን ያለው የኢህአዴግ አመራር የተሳሳተውን የአቶ መለስን ራዕይ የማስፈፀም አቅም እንኳ እንደሌለው የታየበት አጋጣሚ ነው ብለዋል። ለዚህም አንዱ ማሳያ አቶ መለስ በህይወት እያሉ ያልተዘጉ ጋዜጦች ከሞቱ በኋላ መዘጋታቸው ነው ብለዋል።

ለኢህአዴግ መዳከም ሌላው ምልክት አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ በፓርላማው ያደረጉት ንግግር መሆኑን አቶ አስራት ሳይጠቅሱ አላለፉም። ከቋንቋ አጠቃቀም አንስቶ ሰዎችንና ድርጅቶችን የገለፁባቸው መንገዶች ጨዋነት የጎደለው እንደነበር ገልፀዋል።

«አቶ ኃይለማርያም ለፖሊሲ ለውጥ ባይዘጋጁ እንኳ ጨዋነትን ሊያሳዩ ይገባል።ከጳጳሱ ቄሱ እንዲሉ ከአቶ መለስም በልጠው ኃይለኛና አስፈራሪ ሆነው ለመታየት ሞክረዋል» ያሉት አቶ አስራት ይሄ ደግሞ ተገቢ አለመሆኑን ተናግረዋል። በተጨማሪም የአንድነት ፓርቲ ልሳን ስለሆነው «ፍኖተ ነፃነት» ጋዜጣ ማተሚያ ቤት ማጣትን በመተለከተ በፓርላማው የሰጡት መልስ እጅግ የወረደ እንደነበርም አቶ አስራት ሳይገልፁ አላለፉም። እንደአቶ አስራት እምነት የፍኖተ ነፃነት ጉዳይ የህገ መንግስቱ አንቀፅ 29 (የመናገርና የመፃፍ መብት) የመጣስና ያለመጣስ ጉዳይ እንደሆነም አስረድተዋል።

ኢህአዴግ ወይ ተዳክሟል አልያ ደግሞ በመዳከም ላይ መሆኑን ደጋግመው የሚገልፁት ኢንጅነር ይልቃል ጌትነት በበኩላቸው ኢህአዴግ የፈሪ ዱላ (Panic reaction) ሊወሰድ እንደሚችልም ነው የሚያስረዱት።ይህ ደግሞ እንደ አጠቃላይ ለሀገሪቱ ፖለቲካዊ ከባቢ አየር ወይ ጥሩ እድል ነው አልያም መጥፎ እድል ሊሆን እንደሚችል ነው ያስገነዘቡት። እንደ ጥሩ ዕድል ሊቆጠር የሚችለው ተቃዋሚዎች በህዝብ ድጋፍ፣ በድርጅት ጥንካሬና በገንዘብ ጉልበት ኢህአዴግን ወደ ድርድር ማምጣት የሚችሉበት አጋጣሚ ሊፈጠር እንደሚችል ነው የገለፁት።

የአረናው ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ብርሃኑ አዲሱ ጠቅላይሚኒስትር አቶ ኃይለማርያ ደሳለኝ ከተሾሙ በኋላ ስልጣን ከሰሜን ወደ ደቡብ መሄዱን፣ የህወሃት የበላይነት አበቃለት መባሉን፣ እንዲሁም ህወሃት ከኋላ ሆኖ ስልጣን እየተቆጣጠር ነው የሚሉ ነገሮች እንደሚወሩ አስታውሰው በእሳቸው እምነት ግን ህወሃት እንደፓርቲ የበላይነት የነበረው እስከ 1993 ዓ.ም የነበረ ሲሆን ከዚያ በኋላ ስልጣን የነበረው በአቶ መለስ የግል ስልጣንና ከብአዴን አመራሮች ጋር ከነበራቸው ቅርበት የሚመነጭ እንጂ አቶ መለስ የህወሃት ሊቀመንበር ቢሆንም በዙሪያቸው ጠንካራ ሰው ባለመኖሩ የህወሃት የበላይነት አለመኖሩን ይገልፃሉ።

የስልጣን ሸግግሩም በዘመነ መሳፍንት እንደነበረው «የአልጋ ወራሽነት»ሂደት መሆኑን በመጥቀስ የአመራር ሽግግሩን ያጣጣሉት አቶ ብርሃኑ ሽግግሩ ሰላማዊ ፣ ዲሞክራሲያዊ ሊባል አይችልም ብለዋል። ኢህአዴግ አቶ መለስን ካጣ በኋላ በተቀናቃኝ ፓርቲዎች የሚፈጥረው መልካም እድል እንደሌለና ከበፊቱ የባሰ የፖለቲካ ሁኔታ ይፈጠራል ብለዋል። ቀደም ሲል ተቃዋሚው ለኢህአዴግ ስልጣን አደጋ እስካልሆነ ይቀጥል በሚል በቁጥጥር ስር የነበረ ትግል መሆኑን በኋላም የተሸራረፈ ነፃነት በመስጠት እንዲንቀሳቀስ መደረጉን በመግለፅ በቀጣይም ጫናው ይበረታል ብለዋል።

አቶ አስራት ጣሴም የአቶ ብርሃኑን ሀሳብ በመጋራት መጪው ጊዜ የከፋ ሊሆን እንደሚችል ነው ያስረዱት። አቶ መለስ በህይወት በነበሩበት ወቅት ያልተዘጉ ጋዜጦች እንኳ እሳቸው ካለፉ በኋላ መዘጋታቸው የኢህአዴግን ባህሪ በግልፅ ያሳየ አጋጣሚ መሆኑን ነው የጠቀሱት።

በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የታሪክና የስነ-ጥበብ መምህር የሆኑት አቶ አበባው በበኩላቸው ኢህአዴግ እስከ 1993 ዓ.ም በቡድናዊ አመራር መመራቱን ያስታውሳሉ። ከ1993 ዓ.ም በኋላ «በቦናፓርቲዝም» በሚለው መከራከሪያ የፓርቲው አጠቃላይ አካሄድ የተመነጠረበትና የአቶ መለስ ሁለአቀፍነት የገነነበት አጋጣሚ እንደነበር አስታውሰዋል።

አሁን ከአቶ መለስ ህልፈት በኋላ በአራቱ ድርጅቶች አመራሮች ሙሉ በሙሉ ለአቶ መለስ ድጋፍ ሲሰጡና በእሳቸው አመራር ስር ሲጓዙ መቆየታቸው አሁን ላይ ተፅኖ መፍጠሩ የተጠበቀ እንደሆነ ገልጸዋል። ተፅኖውን ለመቋቋም ቀደም ሲል ከነበረው የአንድ ሰው አመራር የፓርቲ አመራር ለመጀመር እየሞከሩ ይመስላል ሲሉ አቶ አበባው ይገልፃሉ።

«የመለስን ራዕይ እናስቀጥላለን» የሚለው የራዕይ ፖለቲካ በተመለከተ አቶ አበባው ሲያስረዱ ኢህአዴግ እንደ ኢህአዴግ ብዙ ግቦች አስቀምጦ ሲንቀሳቀስ እንደነበር በመጥቀስ ከድርጅት ራዕይ ወደ ግለሰብ ራዕይ የመውረዱ ሁኔታ አጠያያቂ ነው። የተቀመጡት ራዕዮችም በአብዛኛው ግባቸውን ያልመቱ መሆኑን በማስታወስ እንደምሳሌም ኢትዮጵያውያንን በቀን ሶስቴ መመገብ የሚለው ራዕይ አለመሳካቱን አስታውሰዋል።

የአምስት ዓመቱ የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ በራሱ የረጅም ጊዜ እቅድ መሆኑን የጠቀሱት አቶ አበባው የአቶ መለስ ራዕይ በአጫጭር ግቦች ላይ ያልተመሰረና በቀላሉም ይሳካል ተብሎ እንደማይገመት ነው የሚያስረዱት። የኢህአዴግ አመራሮች በአሁኑ ወቅት በመለስ ራዕይ ዙሪያ ብቻ ለመሰባሰብ የተገደዱት ከመጀመሪያው ስብስቡ ውስጥ ከመለስ በስተቀር ባለ ራዕይ ባለመኖሩ እንደሆነም አቶ አበባው ያስረዳሉ። አቶ መለስ በነበሩበት ወቅት አቶ መለስን የሚተች ኃይል ያልተገነባ በድርጅቱም ውስጥ የፖለቲካ ሂስ የሌለ በመሆኑ የመጨረሻው አማራጭ የአቶ መለስን መንፈስ መከተል ግድ ብሏል። ይሄንንም ይበልጥ ሲያብራሩ፡-

«የኢህአዴግ ስብስብ በአጠቃላይ ሲመራ የነበረ ስብስብ ነው። አዲስ አጀንዳም ሆነ። አዲስ ግብ የለውም። ስለዚህ ኢህአዴግ የነበረውን ማስጠበቅ ላይ ትኩረት አድርገዋል። ምንም አይነት ሽኩቻ ሳይፈጠር ይዞ ማቆየት የመጀመሪያው ተግባራቸው ነው። ከዚህ ባለፈ ሌላ ራዕይ የላቸውም» ብለዋል።

የመለስ ራዕይ እያሉ ማቀንቀን ከውስጥ ባዶ መሆን የሚያመለክት እንደሆነ የጠቀሱት አቶ አበባው የኢህአዴግ አመራሮች ሌላ የፖለቲካ አጀንዳ ይዘው ለመምጣት ጊዜ ያስፈልጋቸዋል ብለዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ በተመለከተ አዲስ እንደመሆናቸው ህዝቡ ብዙ አዲስ ነገር መጠበቁ የተለመደ መሆኑን የሚያስታውሱት አቶ አበባው ነገር ግን የጠቅላይ ሚኒስትሩ የፓርላማ ንግግር አዲስ አጀንዳ የሌለው፣ አብረን እንሰራለን የሚል የጋባዥነት መንፈስ የሌለበትና ንግግሩም በፓርቲ ተወስኖ የተሰጠ የሚመስል ነው ካሉ በኋላ አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር በፓርቲው ቁጥጥር ስር ያሉ ይመስላል ብለዋል። አቶ ኃይለማርያም በፓርቲው ውስጥ ረጅም ጊዜ ካለመቆየታቸው ጋር በተያያዘ በፓርቲው መደገፋቸው ሊያስወቅሳቸው አይገባም። ሆኖም ህዝብ በጉጉት እንደጠበቀው አልሆኑም ብለዋል።

የኢህአዴግ «ባለበት ይቀጥል» አስተሳሰብ ድርጅቱን ቆሞ ቀር እንዳያደርገው ስለሚለው ስጋት አቶ አበባ የሚሉት አላቸው። አንድ ፓርቲ ሁል ጊዜ ጠንካራ አመራር እንደሚያስፈልገውና በጋራ መወሰንም ያለና የሚጠበቅ ቢሆንም አንድ ጠንካራ የሆነ፣ ተቀባይነት ያለው አሳማኝ መሪ ያስፈልጋል ብለዋል። በኢህአዴግ ውስጥ እስካሁን ጎልቶ የወጣ፣ የሚያሳምን፣ ጠንካራና በራሱ የሚተማን ሰው አልታየኝም ብለዋል።

ኢህአዴግ የተበታተነ ኃይል ሆኗል የሚለው አገላለፅ ብዙም አያሳምንም ያሉት አቶ አበባው እንደውም ድርጅቱ ያሉበትን ወቅታዊና ነባር ችግሮችንም ቢሆን ይዞ ቡድናዊ አመራርን እየተለማመደ መሆኑን የሚያሳዩ ምልክቶች መኖራቸውን ጠቁመዋል። በመሆኑም ስልጣን ያለው በድርጅቱ ማዕከላዊ አመራር መሆኑ ግልፅ ነው ሲሉ ተናግረዋል። ይህ ማዕከላዊ አመራር ግን ባልተጠበቁ ፈተናዎች ላይ መውደቁ አይቀርም ብለዋል። ፈተናዎቹን በፍጥነት ለመፍታት ባለው ማዕከላዊና ቡድናዊ አመራር ቶሎ ውሳኔ ለመስጠት ከመቸገሩም በላይ ያልተገመተ አለመግባባትም ሊፈጥር ይችላል ሲሉም አስረድተዋል።

የኢህአዴግ ወቅታዊ ባህሪ ከኢህአዴግ ውጪ ለሆኑ አካላት ከባድ ተፅኖ እንደሚኖር አቶ አበባው ይገምታሉ። በተግባርም ፕሬሶችን የማፈን የተቃዋሚዎችን የማዳከም በህገ -መንግስቱ መሰረት ያለመንቀሳቀስ ሁኔታዎች በሰፊው የሚጠበቅ እንደሆነ ገልፀዋል። ከዚህ በተጨማሪ በውጪው ተፅኖዎች ማለትም ከአባይ ጋር በተያያዘ፣ ከአክራሪነት ጋር በተያያዘ እና በኤርትራና በሶማሊያ ያሉ ተግዳሮቶች ከኢህአዴግ ውስጣዊ ሁኔታ ጋር ተዳምሮ በሀገር ውስጥ ያለውን ተቃውሞ በቁጥጥር ስር ማስገባት ቀዳሚ አጀንዳ ሊሆን እንደሚችል አቶ አበባው ገምተዋል።

ሆኖም ኢህአዴግ የሀገር ውስጡን ተቃውሞ ማፈን የበለጠ ችግር ሊያመጣ እንደሚችል ሳይገልፁ አላለፉም በተለይም ከኑሮ ውድነቱና ከስራ አጥነት ችግር ጋር በተያያዘ ያልተጠበቀ ህዝባዊ ተቃውሞ ሊያስከትል ይችላል ብለዋል። ኢህአዴግ የውስጥ መረጋጋቱን በሰከነ መንፈስ ለመፍታት ከኑሮ ውድነቱ ጋር የተከማቹ ችግሮችን በቶሎ መፍታት አለበት። የመለስ ራዕይ የተባሉት ግዙፍ የመሰረተ ልማት ግንባታዎች በሀብታም መንግስትና ህዝብ የሚተገበሩ ቢሆኑም በተጨባጭ ግን ከእለት ወደ እለት መኖር ያቃተው ደሃ ህዝብ ባለበት ሀገር ሁኔታዎች ሁሉ አስቸጋሪ መልክ እንደሚይዙ ስጋታቸውን ገልፀዋል። ኢህአዴግ በኑሮ ውድነት ህዝቡ እየተጎዳ በተመሳሳይ የህዝቡን ሰብዓዊና ዲሞክራሲያዊ መብት እየነጠቀ ለመቀጠል ይቸገራል ብለዋል።
****************
*Originally published on the Amharic weekly, Sendek, on Oct. 24, 2012. Republished here with the permission to do so, without implying endorsements.

Check the drop down menu for posts on related topics.

Content gathered and compiled from online and offline media by Hornaffairs staff based on relevance and interest to the Horn of Africa.

more recommended stories