“ሰው እየሳቀ መሞት እንደሚችል አሳያችኋለሁ ነበር ያልኳቸው” አቶ አንዳርጋቸው ፅጌ

(BBC Amharic)

በሽብርተኝነት የተፈረጀው የግንቦት ሰባት ንቅናቄ ዋና ፀሃፊ አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ በልዩ ይቅርታ እንደሚፈቱ ጠቅላይ አቃቤ ህግ ቅዳሜ እለት መግለፁን ተከትሎ ከትንናት ሰኞ ጀምሮ ቤተሰቦቻቸውና ወዳጆቻቸው መፈታታቸውን ሲጠብቁ ቆይተው ዛሬ (ማክሰኞ) አመሻሽ ላይ ተለቀዋል።

በቤተሰባቸው ቤት ከቅዳሜ ጀምረው ሲጠባበቁ ለነበሩት ወዳጆቻቸው ባደረጉት ንግግር አቶ አንዳርጋቸው ”እኔ ተፈትቻለሁ ኢትዮጵያ ግን ያልተፈቱ ብዙ ችግሮች አሉባት” ብለዋል።

ከእስር ተፈተው ቤታቸው ሲደርሱ የተመለከቱት ነገር ያልጠበቁት እንደሆነ የተናገሩት አቶ አንዳርጋቸው። “ምንም መረጃ ባይኖረኝም ኢትዮጵያዊያን እኔን ለማስፈታት ጥረት እንደሚያደርጉ ይሰማኝ ነበር” ብለዋል።

ለዚህ ቀን መምጣት ለደከሙ ለሁሉም ሰዎች ከፍተኛ ምስጋና ያቀረቡ ሲሆን፤ “የኢትዮጵያ ሕዝብ ገብቶበት ካለው አስቸጋሪ ሁኔታ አንፃር፤ እንዲህ አይነት ሃገር ከማየት ፍርድ ቤታችሁ የወሰነውን የሞት ቅጣት ተግባራዊ አድርጉ” በማለት ለመርማሪዎች መናገራቸውን ገልፀዋል።

ከዚህ በፊት በቴሌቪዥን ተቆራርጦ ነው የቀረበው ያሉትን ምስል እንዳዩት የተናገሩት አቶ አንዳርጋቸው “ሰው እየሳቀ መሞት እንደሚችል አሳያችኋለሁ ነበር ያልኳቸው፤ ነገር ግን ቆራርጠው ነው ያቀረቡት።”

ጨምረውም “ፍቱኝ ብዬ አልጠይቃችሁም አብሬያችሁ የሰራሁበትን ጊዜ እንደውለታ ቆጥራችሁ የሞት ፍርዱን ተግባራዊ አድርጉ ብዬ ጠይቄያቸዋለሁ” ሲሉ ተናግረዋል።

Photo - Andargachew Tsige after release from prison
Photo – Andargachew Tsige after release from prison

ትናንት ጠዋት የእንግሊዝ ኤምባሲ መኪኖች በማረሚያ ቤት አካባቢ ተገኝተው ነበር፤ የአቶ አንዳርጋቸው እህት በስፍራው ከኤምባሲ ሰዎች ጋር የነበረች ሲሆን ለቤተሰቦቿ ደውላ ማለዳ እንዳገኘችውና ወደቤት እንደሚመጣ ነግራቸው ነበር።

ሆኖም እስከማምሻው ድረስ ወደ ቤተሰቦቻቸው ቤት እንዳልመጡ ለማወቅ ተችሏል።

በትናንትናው እለት አዲስ አበባ ቦሌ አካባቢ የሚገኘው የቤተሰቦቹ ቤትና አካባቢው በመፈታቱ የተሰማቸውን ደስታ በሚገልጡ መልዕክቶችና በፎቶዎቹ አሸብርቆ ውሏል።

የአንዳርጋቸው ደጋፊዎች የእርሱን ምስል የታተመበት ቲሸርት ለብሰው በአካባቢው ተገኝተው ሲጨፍሩ እና ደስታቸውን ሲገልጡ እንደነበር ተመልክተናል።

በለንደን የምትኖረው የአቶ አንዳርጋቸው ጽጌ የህይወት አጋር ወ/ሮ የምስራች ኃይለማርያም (የሚ) በባለቤቷ ሊፈታ በመሆኑ እጅግ መደሰቷን እና እስካሁንም የተፈጠረውን እንዳላመነች ለቢቢሲ ተናግራለች።

”ከአንድ ሰው ህይወት 4 አመት የሚሆነውን በእስር ማሳለፍ ምን አይነት ተጽዕኖ ሊፈጥር እንደሚችል መገመት ይከብዳል። ነገር ግን ባለቤቴ ከዚህ በኋላ ወደ ፀሃፊነት ያዘነብላል ብዬ አስባለሁ” ትላለች ወ/ሮ የሚ።

ለልጆቼ ዜናውን ስትነግራቸው በደስታ አልቅሰው ነበር የምትለው የሚ፤ እስካሁን አንዳርጋቸውን ለማነጋገር እየጠበቁ እንደሆነ ገልጻለች።

ባለቤቷ በሽብርተኝነት በተፈረጀው ግንቦት ሰባት ድርጅት ስለነበረው ኃላፊነት እና ስለቤተሰቡ ሁኔታ የተጠየቀችው የሚ፤ እንደዚህ አይነት እንቅስቃሴ ውስጥ ያሉ ሰዎች ከመንግሥት ጋር የሚኖራቸው ግንኙነት ይታወቃል፤ ስለዚህ ሁሌም ቢሆን የሆነ ነገር ሊፈጠር እንደሚችል እገምት ነበር ብላለች።

አቶ አንዳርጋቸው ፅጌ በቁጥጥር ስር ከዋሉበት ቀን ጀምሮ እንዲለቀቁ ሲወተውት የነበረው ሪፕራይቭ የተሰኘ መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት ዋና ኮሚሽን የሆኑት አዳም ስሚዝ እስካሁን ድረስ አለመለቀቃቸውን ገልጾ ዛሬ ብሔራዊ በዓል ስለሆነ ላይለቀቁ ይችላሉ ሲሉ ስጋታቸውን አስቀምጠዋል።

አክለውም የእንግሊዝ ኤምባሲ አስቸኳይ የጉዞ ሰነዶችን ሊያዘጋጅ ይገባል፤ አንዳርጋቸውም አባቱን ማየት ሊፈልግ ይችላል ብለዋል።

የእንግሊዝ ዜግነት ያላቸው ትውልደ ኢትዮጵያዊው አቶ አንዳርጋቸው፣ በሽብር ወንጀል ሁለት ጊዜ ክስ ተመሥርቶባቸው በዕድሜ ልክና በሞት እንዲቀጡ እንደተፈረደባቸው ይታወሳል።

**********

Content gathered and compiled from online and offline media by Hornaffairs staff based on relevance and interest to the Horn of Africa.

more recommended stories