ከቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የተፈናቀሉ ዜጎችን ሁኔታ የሚያጣራ ቡድን ወደ ባህርዳር ተልኳል

(በላይ ተስፋዬፋና)

ከቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የተፈናቀሉ ዜጎችን ሁኔታ የሚመረምር ቡድን ወደ ባህርዳር መላኩን የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ገለፀ።

የኮሚሽኑ ኮሚሽነር ዶክተር አዲሱ ገብረእግዚያብሄር እንደገለፁት፥ የተላኩት የኮሚሽኑ መርማሪ ባለሙያዎች የተፈናቀሉ ዜጎችን ጨምሮ የሚመለከታቸውን አካላት በማነጋገር የሰብዓዊ መብት ጥሰት መፈፀም አለመፈፀሙን ያጣራሉ።

የተገኙ መረጃዎችን በማጠናከርም የምርመራ ውጤቱ ሪፖርት ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ይቀርባል ብለዋል።

በምርመራ ውጤቱ የሰብዓዊ መብት ጥሰት መፈፀሙን የሚያመላክት ከሆነም በድርጊቱ የተሳተፉ ግለሰቦችን ተጠያቂ በማድረግ የእርምት እርምጃ እንዲወሰድ ኮሚሽኑ ለምክር ቤቱ ምክረ ሃሳብ አያይዞ እንደሚያቀርብም ተናግረዋል።

በተያያዘም ባለፈው ሳምንት በሰብዓዊ መብት ላይ የተፈጸመን ጥሰት ሲመረምር በነበረ የኮሚሽኑ የሶማሌ ክልል ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኮሚሽነር አቶ ጀማል መሃመድ ላይ የተፈጸመውን ጥቃት ኮሚሽነሩ አውግዝዋል።

በጉዳዩ ላይ አስፈላጊ ማጣራት ተካሂዶ ሪፖርቱን ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ማቅረባቸውንም ኮሚሽነሩ አስረድተዋል።
አቶ ጀማል ላይ ጥቃት ፈጽመዋል የተባሉት የመንግስት አካላትም ተጠያቂ እንዲሆኑ ኮሚሽኑ እንደሚሰራ ገልጸዋል።

******

Content gathered and compiled from online and offline media by Hornaffairs staff based on relevance and interest to the Horn of Africa.

more recommended stories