ሊገዳደሉ ከአንድ ጦር አውድማ የተገኙ ወንድማማቾች

(BBC – Amharic)

በኢትዮጵያና ኤርትራ መሃከል የተደረገው ጦርነት በወንድማማቾች መካከል የተደረገ ጦርነት ስለመሆኑ ብዙዎች ጽፈዋል። የአቶ ታፈረ ቤተሰብ እውነታ የዚህ አሳዛኝ እውነታ ምስክር ነው።

1990ዎቹ መጀመርያ ወርሀ ግንቦት ነው። የሁለቱ ሃገራት የለት ተለት ህይወታቸው እንደ ሁሌው ቢመስላቸውም ወታደሮችን የጫኑ ተሽከርካሪዎች ወደ ተለያዩ አካባቢዎች ሲንቀሳቀሱ መመልከት አንድ ልክ ያልሆነ ነገር መኖሩን ልብ እንዲሉ ግድ አለ።

የሃዘን ጥግን ያየችው የአቦይ ታፈረ ጎጆ

አቦይ ታፈረ ተክለ በትግራይ እገላ በሚባል ልዩ ቦታ ከባለቤታቸው አደይ ሓጉሽ ገረማርያም አምስት ልጆች ወልደው ያሳደጉ አባት ናቸው።

ለገሰ ታፈረ እና ጆርጆ ታፈረ ታላቅ እና ታናሽ ወንድማማቾች ናቸው። እነዚህ ከአንዲት እናት አብራክ የተገኙ ወንድማሞች ትግራይ ተወልደው ኤርትራ ያደጉት ሲሆን በ1970ቹ ከደርግ ጋር ይደረግ በነበረው ፍልምያ በሁለት የትጥቅ ሀይሎች ስር ተሰልፈው ተዋግተዋል።

ታላቅየው ለገሰ ታፈረ ቀድሞ ህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይን ሲቀላቀል ከጥቂት ዓመታት በኋላ ደግሞ ታናሹ ጆርጆ ታፈረ የሻዕብያ ታጋዮች አጋር ሆኖ በየፊናቸው ትግሉን ተያያዙት።

ለገሰ ታፈረ ለኤርትራ ነጻነት ለሚታገለው ታናሽ ወንድሙ ጆርጆ ታፈረ ህወሓት ተመልሶ አብረው እንዲታገሉ ተደጋጋሚ ደብዳቤ ቢጽፍለትም ጆርጅዮ “የምናካሂደው ትግል የደርግን ስርዓት ለመገርሰስ እስከሆነ ለኔ ሁሉም ያው ነው እዚሁ ተመችቶኛል” በማለት ጥያቄውን ሳይቀበል ይቀራል።

ወንድማማቾቹ በ1983 ዓ.ም ወርሀ ግንቦት በየፊናቸው ሲታገሉለት የነበረው ዓላማ ተሳክቶ ታላቅ አዲስ አበባ ታናሽ ጆርጆ ደግሞ አስመራ ገብተው የትግላቸውን ፍሬ ከህዝባቸው ጋር ለማጣጣም በቁ።

Photo - Legese Tafere and Georgo Tafere
Photo – Legese Tafere and Georgo Tafere

ሰላም አልባዋ “ሰላሞ ግንባር

የሁለቱም ሃገራት መንግስታት በሚቆጣጠሯቸው የሚድያ አውታሮች ባወጁት የጦርነት ክተት አዋጅ እና ሀገርህን አድን ጥሪ የሁለቱም ሀገራት ወጣቶች ወደ ግንባር ዘመቱ፣ ጦርነቱም በአሰቃቂ ሁኔታ ተካሄደ።

ከመጀመሪያው አንድ አላማ ያነገበ ነገር ግን በተለያየ መስመር ከተደረገው ትግላቸው ድል በኋላ በየፊናቸው የሄዱት እነዚያ የአንድ እናት ልጆች እርስ በርስ ሊታኮሱና ሊገዳደሉ አፈሙዛቸው ጠራርገው በአንድ የጦር አውድማ ተገኙ።

በኢትዮጵያ በኩል የተሰለፈው ኮለኔል ለገሰ ታፈረ የመካናይዝድ አዛዥ፣ በኤርትራ በኩል የተሰለፈው ጆርጆ ታፈረ ደግሞ በ161ኛ ኮር የአንዲት ክፍለ ጦር አዛዥ ሆኖ በሰላሞ ግንባር ተገናኙ።

ከጦርነት የሚገኝ ትርፍ የለም፣ መጨረሻው የሰው ህይወትና የንብረት ጥፋት ነው።

በሁለት ወንድማማቾች የተደገሰው ጦርነት ተካሄደ በኤርትራ በኩል ተሰልፎ የነበረው ጆርጆ ታፈረም በወንድሙ ወገን በተተኮሰ ጥይት ለአንዴ እና ለመጨረሻ ላይመለስ በዚያች ሰላማዊ ባልሆነችውን ሰላሞ ህይወቱ አለፈ።

እንደታናሽ ባይከፋም ታላቅ ለገሰም ከክፉ እጣ አላመለጠም።በሰላሞ ግንባር ከወንድሙ ወገን በተተኮሰ ጥይት ተመትቶ አጣ።

ኢትዮጵያ እና ኤርትራ ተመልሰው ወደ ጦርነት መግባታቸው አጅግ እንደሚያሳዝነው የሚገልፀው ኮሎኔል ለገሰ ታፈረ “በተለይም እህት እና ወንድም የሆነው የትግራይ እና የኤርትራ ህዝብ በውጭ ሃይሎች ተንኮል በሁለት ሀገራት ተከፍሎ ሲያበቃ ዳግመኛ ደም መቃባቱ በጣም ያሳዝነኛል” ይላል።

“የታችኛው እና ላይኛው ሰላሞ የኔ ተልእኮ ነበር፣ እሱ( ታናሽ ወንድሙ ጆርጆ ታፈረ) ደግሞ በ161ኛ ኮር የአንዲት ክፍለጦር አዛዥ ሆኖ እኔ ወደ ተሰጠኝ ተልእኮ እንደመጣ መረጃ ነበረኝ እና የእኔ እና የእሱ ክፍለ ጦሮች ናቸው የተዋጉት” በማለት ትውስታውን ለቢቢሲ አካፍሏል።

“እሱ እዛው ግንባር ተሰዋ እኔም የመቁሰል አደጋ ገጥሞኝ ጦርነቱ በሰራዊታችን አሸናፊነት ተጠናቀቀ። ሆኖም ግን እርስ በእርሳችን ስለነበር ሙሉ ድል አይደለም”በማለት ድሉ እንዴት ሙሉ እንዳልነበር ይናገራል።

የታንኮችን ዒላማ እንዳታሳስት?

ጦርነቱ ሊጀመር አከባቢ የኢትዮጵያ ሰራዊት አዛዦች ኮሎኔል ለገሰ ታፈረ በተሰጠው ተልእኮ የሰላሞ ግንባር የኤርትራን ሰራዊት መርቶ የገባው ታናሽ ወንድሙ ጆርጆ መሆኑን መረጃ ስለነበራቸው ለኮሎኔሉ ” ከወንድምህ ጋር ግንባር ለግንባር ከምትዋጋ ለምን አንቀይርህም” ብለዉት እንበነበር ያስታውሳል

አንዳንድ ጓዶቹ “የታንከኛ አዛዥም ስለነበርኩ ወንድምህን ላለመምታት የታንኮችን ተተኳሾች ዒላማ እንዳታሳስታቸው” እያሉ ይቀልዱበት እንደነበርም ያስታውሳል።

መልሱ” ዓላማ ዓላማ ነው ግድ የላችሁም ታንኮቹ ዒላማቸውን አይስቱም”የሚል ነበር።

ወላጅ አባታቸው አቦይ ታፈረ ተክለ በትጥቅ ትግል ወቅት ህይወታቸው እንዳለፈ የሚናገረው ልጃቸው ኮሎኔል ለገሰ በቅርብ በሞት እስከተለዩበት ጊዜ ድረስ ለእናተቸው የልጃቸው ጆርጆ አሟሟት እንዳልተነገራቸው ኮሎኔል ለገሰ ይናገራል ።

በትግራይም ይሁን በኤርትራ ያሉ የቤተሰባቸው አባላት በተፈጠረው ሁኔታ እጅግ እንደሚያዝኑ ይገልፃል ኮሎኔሉ።

በሌላ በኩል በአሁኑ ወቅት እሱና ሟች ወንድሙ ተወልደው ያደጉባት እገላ ወጣቶች ሳውዲ ለመግባት የመርሃና የባህር ሲሳይ ሆነው ባጭር ሲቀጩ ማየት ልቡን እንደሚሰብረው ይናገራል።

*******

Content gathered and compiled from online and offline media by Hornaffairs staff based on relevance and interest to the Horn of Africa.

more recommended stories