ግልጽ ደብዳቤ ለጠ/ሚ ኃይለማርያም ደሳለኝ እና ለፕ/ት ገዱ አንዳርጋቸው

ይድረስ ለክቡር የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ እና ለተከበሩ የአማራ ብሄራዊ ክልል ፕሬዚደንት አቶ ገዱ አንዳርጋቸው

በወልድያ እና በቆቦ በፀጥታ ሃይሎች እርምጃም ይሁን በዘረኛ መንጋዎች ጥቃት ለደረሰባቸው ሁሉም ዜጎች የተሰማኝን ጥልቅ ሃዘን በቅድሚያ እየገለፅኩ ለቤተሰቦቻቸዉና ለሁላችንም መፅናናትን እመኛለሁ። አስፈላጊ ማጣራትና ምርመራ ተደርጎ ከሁሉም ወገን መጠየቅ ያለበት አጥፊ መጠየቅ አለበት እላለሁ፡፡ ያንዱ ጥቃት የሁሉም ስጋት ነው ብየ የማምን ሰላማዊት፣ የበለፀገች፣ ዴሞክራስያዊት ኢትዮጵያ እና ምክንያታዊና የሞራል ስብእና የተላበሰ ህዝብ ያላት ሀገር እንድትገነባ የምሻ ዜጋ ነኝ። የከዚህ በፊት ተሳትፎየም መነሻና መድረሻው ይህ መሆኑ እሙን ነው።

በዓለም አቀፍ የዘር ማጥፋት ወንጀል ህግ እና በተባበሩት መንግስታት የሽብር ወንጀል መረዳት መሰረት ዘር ተኮር የሂወትና የንብረት ጥቃት እንዲሁም የዘር ማጥፋትና (Genocide) የዘር ማፅዳት (Ethnic Cleansing) ወንጀሎች በምንም ዓይነት አመክንዩ ተቀባይነት ሊኖራቸው እንደማይችል ይደነግጋል። Justifiable ድርጊት አይደለም። ኢትዮጵያም እነዚህን ህጎች አፅድቃ የህጓዋን አካል ያደረገች ሀገር መሆንዋ ይታወቃል።

በተጨማሪም ከ አስራ ሰባት ዓመት የእርስ በርስ ጦርነት በኃላ ትፈርሳለች፣ አብቅቶላታል፣ እንደ ሶቭየት ህብረት ትበተናለች የተባለችዉኢትዮጵያ የሁሉም ብሄር ቤት ትሆን ዘንዳ ብዝሃነትን መሰረት ያደረገ ፌዴራላዊ ስርዓት በማቆም ህዝቦች በማንነታቸው ጥቃት እንዳይደርስባቸው የሚደነግግ ሕገ-መንግስት በዝቅተኛ ደረጃም ቢሆን ተግባራዊ ማድረግ የጀመረች ሀገር ናት ኢትዮጵያ።

አሁን በወልድያና በቆቦ እየተደረገ ያለው ነገር ሀ-እና-ለ የሌለው ዘር ተኮር ጥቃት በዓለም አቀፍ የዘር ማጥፋት ወንጀልም፣ በሕገ መንግስታችንም ከፍተኛ ደረጃ የሚይዝ የህግና የፖለቲካ ወንጀል ብቻ ሳይሆን የሞራል ዝቅጠትም ማሳያ ነው። ይህ ድርጊት በምንም ዓይነት መንገድ አመክንዮ (Justification) የሚቀርብለት ጉዳይ አይደለም። እምንበታተነው ብሄራዊ ማንነት የኩራት ሳይሆን የጥቃት ምንጭ የሆነ እለት ነው።

የክልሉ መንግስት ምን እያለ ነው?

አቶ ገዱ አንዳርጋቸው የችግሩ መንስኤ የብአዴን ችግር እንደሆነና ከመልካም አስተዳደር እና ከተመሳሳይ ነገሮች የሚመነጭ እንደሆነ እንደተናገሩ ሰምተናል። ልክ ነው ወልድያም፣ ጎንደርም፣ መቐለም፣ ቆቦም፣ ወለንጪቲም ብቻ አብዛኛው የኢትዮጵያ አካባቢዎች የአስተዳደር ችግር አለ። ይህ ማለት ግን በንፁሃን ዜጎች ላይ፣ ለዛዉም ክልሉን በማስተዳደር ምንም ተሳትፎ በሌላቸው ዜጎች ላይ እርምጃ ለመዉሰድ ምክንያት ይሆናል ማለት አይደለም። የወልድያን ወጣት ያስለቀሰው የከተማው የብአዴን አመራር እንጂ አብረሀት የተባለች ጉሊት ቸርቻሪ አይደለችም።

አቶ ገዱ ይህን ትግራዋይ ላይ በብሄራዊ ማንነቱ ምክንያት እየደረሰበት ያለዉን የዘር ጭፍጨፋ ድርጊቱን በሚመጥን ቃል ሊኮንኑት ይገባል። ዘር ተኮር ጥቃት ዓለም አቀፍ የዘር ማጥፋት ወንጀል እንደሆነና የፌዴራል ስርዓታችን የመጨረሻው ቀይ መስመር መሆኑ ተገንዝበው ድርጊቱን በምንም ምክንያት እና አመክንዩ ተቀባይነት ሊኖረው የማይደረግ መሆኑ ተገንዝበው በማያሻማ አገላለፅ ሊኮኑኑት ይገባል። ይህ ማለት ለክልላቸው ህዝብና መንግስት ተመሳሳይ ድርጊት እንዲታገሉም አቅምና ስልጣን መስጠት ማለት ነው።

የክልሉ መንግስት መኮነን ብቻ ሳይሆን ይህን የወንጀሎች ሁሉ ቁንጮ ወንጀል የሆነዉን የዘር ማጥፋት ወንጀል ለመከላከል ምን እንደሰራ፣ ምን ዉጤት እንዳስገኘ፣ ምንስ እያደረገ እንደሆነና፣ በሌሎች የክልሉ አካባቢዎች እንደማይፈጠር ምን ቅድመ ዝግጅት እያደረገ መሆኑ በይፋ ለህዝቡ ማሳወቅ አለበት። የክልሉ መንግስት “አይ እየተፈፀመ ያለ ጥቃት ዘር ተኮር አይደለም” እሚል ከሆነም በግላጭ አቛሙን ያሳዉቅ። አብሮ የሚያኖረንን የብዝሃነት መስመር እየተጣሰ አንድ ሃገር ብሎ ነገር የመኖር እድሉ የኮሰመነ መሆኑ የዘርፉ ሳይንስም ዓለማዊ ሃቁም ይነግረናል።

የተከበሩ ጠቅላይ ሚኒስቴር

የፌዴራል መንግስትም ፌዴራላዊ ስርዓቱንና ሕገመንግስቱን የመጠበቅ፣ የህዝቦች የግልና የቡድን መብቶችን የመከላከል ሃገሪትዋን ከመፍረስ የማዳን ግዴታ እንዳለበት ተገንዝቦ እየተፈጠረ ስላለው ሁኔታ ያለዉን መረዳት (Understanding of the problem) ፣ ያደረገው ተግባራዊ እንቅስቃሴ ፣ እንዲሁም የወደፊት እቅዱን በይፋ ለህዝቡ ማሳወቅ አለበት። መንግስት በቦታው እንዳለ ማሳወቅ አለበት፣ ዜጎች በሃገራቸው የመኖር መብታቸው በቦታው እንዳለና የመኖር ዋስትና እንዳላቸው እርግጠኛ መሆን ይሻሉ።

ስለዚህም የዘር ማጥፋት ወንጀል በዓለም አቀፍ ህግም ይሁን አብሮ ያኖረናል ብለን ባፀደቅነው ሕገ መንግስታችን መሰረት በአመክንዮ ሊስተባበል የሚችል ወንጀል እንዳልሆነ ተገንዝበው የአማራ ክልል መንግስት እና የፌዴራል መንግስት ድርጊቱን በስሙ ጠርተው በፅኑ እንዲኮንኑና፣ ይህን ወንጀል ለመከላከል የሄዱበት ርቀት ገልፀው፣ ድርጊቱ ዳግም እንዳይደገም እየሰሩት ያለን ስራ ለህዝቡ በይፋ በመግለፅ መንግስታዊ ኃላፊነታቸው ሊወጡ በሚችሉበት የአመራር ቁመና እንዳሉ በማሳየት ህዝቦች አሁንም ኢትዮጵያ እምትባል ተማምነው የሚንቀሳቀሱባት ሀገር እንዳለቻቸው ማሳየት ይገባቸዋል።

በሰው ሂወት ክቡርነት የሚያምን ሁሉ ሼር እንዲያደርገው እጠይቃለሁ።

*******

more recommended stories