ዳኛ ዘርዓይ ወ/ሰንበት ስለወልቃይት የጻፉትን አስመልክቶ ለቀረበ ጥያቄ የሰጡት ምላሽ

በፌዴራል ከፍተኛ ፍ/ቤት 4ኛ የወንጀል ችሎት እየታየ በሚገኘው በነብርሀኑ ሙሉ መዝገብ ላይ ተከሳሾች ከዳኞቹ አንዱ የሆኑት ዳኛ ዘርዓይ ወ/ሰንበት እንዲነሱ ጥያቄ አቅርበው ነበር። 

ችሎቱ ባለፈው ሳምንት አርብ በሰጠው ብይን የዳኛ ይነሳልን ጥያቄውን ውድቅ አድርጎታል። 

ተከሳሾች ዳኛ ዘርዓይ እንዲነሳላቸው ሲጠይቁ ካቀረቡት ምክንያቶች አንደኛው፤ ዳኛ ዘርዓይ ከዚህ ቀደም በHornAffairs – Amharic በታተመው ጽሑፋቸው  ላይ: “አማሮች በሀገራቸው የመላው አማራ ማህበረሰብ ነን ብለው አባልነታቸውን አጥብቀው አያውቁም” ብለው ያሰፈሩትን በመጥቀስ ነበር።

ተከሳሾቹ ያንን በመጥቀስ “[ዳኛ ዘርዓይ] አማራ በማንነቱ የማይኮራ በጎጥ የሚጠራ ህዝብ እንደሆነ አድርገው የዘር ልዩነቱን አጉልተው የጻፉ በመሆናቸው እና እኛ አማራ በመሆናችን በኛ ክስ ላይ ሊዳኙ አይገባም” የሚል አቤቲታ ነበር ያቀረቡት።

ችሎቱ ከውሳኔው በፊት ዳኛ ዘርዓይ ወ/ሰንበት ምላሽ እንዲሰጡ ጋብዞ የነበረ ሲሆን፤ የዘርዓይ የመልስ ጽሑፍ እጅግ ረጅም በመሆኑ አንባቢያንን ይስባል ብለን ያሰብነውን ክፍል ወስደን አቅርበነዋል።

Photo - Lideta Federal High Court
Photo – Lideta Federal High Court

——
ተከሳሾች በጠቀሷቸው ምክንያቶች ላይ የተሰጠ መልስ

1.  ተከሳሾች የተከሰሱበት ጉዳይና የፅሑፉ ጉዳይ የተለያዩ ስለመሆኑ (ወይም በተከሰሱበት ጉዳይ ላይ አስቀድሜ የሰጠሁት ውሳኔም ሆነ አስተያየት ወይም ሐሳብ የሌለ ስለመሆኑ)፡-

ተከሳሾች በማመልከቻቸው ላይ የተከሰስነው ሐምሌ 24 ቀን 2008 ዓም ጎንደር ላይ በተደረገው ሰላማዊ ሰልፍ የወልቃይት ሕዝብ የማንነት ጥያቄ ምላሽ ያግኝ፣ የታሰሩት የወልቃይት ሕዝብ የአማራ ማንነት ጠያቂ ኮሚቴዎች ይፈቱ የሚል እና ሌሎች አስተዳዳራዊ በደሎች እንዲቆም በሚል የተጀመረ ስለሆነ አሁን የተለያየ ስያሜ ቢሰጠውም የክሳችን ዋናው ምንጭ የወልቃይት ሕዝብ አማራ ማንነት ጥያቄ ነው በማለት ጠቅሰዋል፡፡ ይሁንና ተከሳሾች የተከሰሱት በገለፁት ምክንያት አይደለም፡፡ የተከሰሱት የሽብርተኝነት ወንጀል ለመፈፀም አሲረዋል በሚል እንደሆነ የክሱ ማመልከቻ በግልፅ ያሳያል፡፡

ተከሳሾች የተከሰሱበት ጉዳይ (ምክንያት) የሚታወቀው ከቀረበው የወንጀል ክስ ማመልከቻና ከተጠቀሰባቸው የወንጀል ሕግ (የሽብርተኝነት ሕግ) እና አንቀፅ ወይም ቁጥር ነው፡፡ በዚህም መሰረት በተከሳሾ ላይ የፌዴራል ጠቅላይ ዓ/ሕግ በቀን 05/01/2010 ዓ.ም በተፃፈ የወንጀል ክስ ማመልከቻ ያቀረበው የወንጀል ክስ የሚያሳየው ተከሳሾች የተከሰሱት የአርበኞች ግንቦት ሰባት የተሰኘው የሽብርተኛ ድርጅትን የፖለቲካ አላማ ለማራመድ በማሰብ አባል በመሆን የሽርተኝነት ድርጊት ለመፈፀም የማሴር ወንጀል የፈፀሙ በመሆኑ በፀረ ሽርተኝነት አዋጅ ቁጥር 652/2001 አንቀፅ 4 ስር የተከሰሱ መሆኑን ነው፡፡ በመሆኑም ተከሳሾች የተከሰስነው በወልቃይት ሕዝብ የአማራ ማንነት ጥያቄ ነው በማለት ያቀረቡት መከራከሪያ ተገቢነት የለውም፡፡

በሌላ በኩል የፅሑፉ ጉዳይ፡-  

1. የማንነት ጥያቄ ምንነት፣

2. የድንበር አከላለል ለውጥ ጥያቄን ምንነት፣

3. የኢትዩጵያ ሕግስ እንዴት ይጠብቃቸዋል እና

4. የትግራይ ሕዝብ ታሪካዊ አሰፋፈር ናቸው፡፡

በመሆኑም የተከሰሱበት ጉዳይና የፅሑፉ ጉዳይ የተለያዩ ናቸው፡፡ ከዚህም በላይ ፅሑፉ በድህረ ገፅ የታተመው በግንቦት ወር 2008 ዓ.ም ሲሆን ተከሳሶች የሽብርተኝነት ድርጊት ለመፈፀም አሲረዋል የተባለው ፅሑፉ ከታተመ በኃላ ነው፡፡ ስለሆነም የፅሑፉና የተከሰሱበት ጉዳይ አንድ አይደሉም፡፡ በአጠቃላይ ተከሳሾች በተከሰሱበት ጉዳይ  (የሽብተኝነት ድርጊት ለመፈፀም የማሴር ወንጀል ጉዳይ) ላይ አስቀድሜ በፅሑፍ ውስጥ የሰጠሁት ውሳኔም ሆነ አስተያየት ወይም ሃሳብ የለም፡፡

2. ፅሑፉም ሆነ የፅሑሁፉ ተጠቃሹ የመደምደሚያ ክፍል ቃላት አንድ የፌዴራል ፍርድ ቤት ዳኛ ተከሳሾች በተከሰሱበት የወንጀል ጉዳይ ላይ ትክክለኛ ፍትሕ አይሰጡም ወይም ገለልተኛ አይደሉም የሚያሰኝ በቂ ምክንያት ስላለመሆኑ

2.1. ፅሑፉም በአጠቃላይ ሆነ ተጠቃሹ የፅሑፉ የመደምደሚያ ክፍል ቃላት ተከሳሾች የሰጡት ትርጓሜ የሌለው ስለመሆኑ

ተከሳሾች በማመልከቻቸው ላይ ዳኛው ስለብሄር ማንነት በሰፊው ሲዘረዝሩ በተለይ ቀደም ባሉት ዘመናት የአማራ ሕዝብ ለማንነቱ ግድ እንደማይሰጥ የአማራን ሕዝብ የሚያናንቅ ፅሑፍ አቅርበዋል እንዲሁም ሰፋ ያለ የዘረኝነት ሃሳብ ያቀረቡ በተለይም አማራ በማንነቱ የማይኮራ በጎጥ የሚጠራ ሕዝብ እንደሆነ አድርገው የዘር ልዩነትን አጉልተው የፃፉ በመሆናቸውና እኛ አማራዎች በመሆናችን በእኛ ክስ ላይ እውነተኛ ፍትሕ ይሰጣሉ የሚል ግምት የለንም ብለዋል፡፡

ይህን ያሉትም የፅሑፉን የመደምደሚያ ክፍል ተጠቃሹን ቃላት በዓላማ በሚመስል መልኩ በመተርጎም ነው፡፡ይሁንና ተጠቃሹ ቃላት (ዓረፍተ ነገር) ሆነ አጠቃላይ ፅሑፉ ተከሳሾች ይላል በማለት የሰጡዋቸው ትርጓሜዎችን አይልም፡፡ ተከሳሾም ከትርጓሜአቸው ላይ እንዴት ሊደርሱ እንደቻሉ የገለፁት አንዳችም ነገር የለም፡፡ተከሳሾች የጠቀሱትን የፅሑፍ መደምደሚያ ክፍል ቃላት (የቃላት ስብስብ) ሆነ ፅሑፉን በጠቅላላ ለመረዳት የፅሑፉን ዓላማና የፅሑፉን ጉዳይ ማወቅ ያስፈልጋል፡፡ በሌላ አነጋገር አንድን የፅሑፉ ቃል ወይም ቃላት መረዳት የሚገባው ካጠቃላይ የፅሑፉ ይዘት አኳያ ነው፡፡

ማንኛውም ሰው አንድን ፅሑፍ ወይም ቃላት ወይም ቃል ለመተርጎም በሚነሳበት ጊዜ፡-

1. በመጀመሪያ የፅሑፉ ማውጣት ተግባር ዓላማ ምንድነው? ወይም ፅሑፉ ምን ዓላማን ተመርኩዞ ነው የተፃፈው?

2. ሁለተኛ ፅሑፉ የሚናገረው (የሚዳስሰው) ስለምንድነው?

3. ሶስተኛ ፅሑፉ ሊያስተላልፋቸው (ሊያስወግዳቸው) የፈለጋቸው ችግሮች የቶቹ ናቸው?

4. ፅሑፉ እንዲያመጣ የታሰበው ውጤት ወይም ለውጥስ ምንድነው? የሚሉትን ጥያቄዎች መጠየቅና መመርመር ይገባዋል፡፡

ካለበለዚያ አጠቃላይ የፅሑፉን ጉዳይ ወይም የፅሑፉን ቃል በዘፈቀደ ወይም በዓላማ (purposive understanding) ካልሆነ በቀር የፅሑፉን ጉዳይ ፀሐፊው ባሰበው መልኩ ሊረዳው የሚችልበት ሁኔታ የለም፡፡ በጠቅላላው በፅሑፉ ውስጥ ያለ ቃል ወይም ያሉ ቃላት የሚያገለግለው ፅሑፉ ለሚገልፀው ጉዳይ ነው፡፡ በሌላ አነጋገር በፅሑፉ ውስጥ ያለ ቃል ወይም ያሉ ቃላት ትርጓሜአቸውን ማግኘት የሚቻለው ፅሑፉ የሚዳስሰውን እና የፅሑፉ ዓላማ በማወቅ ነው፡፡ ለፅሑፉ ቃል ወይም ቃላት ትርጓሜ መስጠት የሚገባው ከፅሑፉ ቃል ወይም ቃላት ሳንወጣ ጭምር ነው፡፡

ተከሳሾች ማመልከቻቸው እንደሚያሳየው ዳኛው በፅሁፋቸው ላይ ስለብሔር ማንነት በሰፊው ሲዘረዝሩ በተለይ ቀደም ባሉት ዘመናት የአማራ ሕዝብ ለማንነቱ ግድ እንደማይሰጥ የአማራን ሕዝብ የሚያናንቅ ፅሑፍ አቅርበዋል እንዲሁም በፅሑፋቸው ሰፋ ያለ የዘረኝነት ሃሳብ ያቀረቡ በተለይም አማራ በማንነቱ የማይኮራ በጎጥ የሚጠራ ሕዝብ እንደሆነ አድርገው የዘር ልዩነትን አጉልተው ፅፈዋል ብለዋል፡፡ይህንንም ብለዋል ያሉት የፅሑፉ መደምደሚያ ክፍል ላይ፡-

“…እዚህ ላይ ለመጥቀስ ያህል አማሮች በሃገራቸው የመላው አማራ ማህበረሰብ ነን ብለው አባልነታቸውን ከቶ አጥብቀው አያውቁም፡፡ ማንነታቸውን ለመግለፅ በክፍለ ሃገር ደረጃ ጎጃሞች፣ ሸዋዎች፣ በሚል ነው፡፡ በተቃራኒው በትግራይ ሕዝብ መካከል የተለየ ቅርብ ግንኙነት ነበረም፤አለም፡፡ ምንም እንኳን የትግራይ ሕዝብ በአማሮች ነገስታት እንደራሴዎች ሲገዛ ቢኖርም ከአማሮች ጋር የመፎካከር ባህል ቢኖርም ከኢትዩጵያ ብሔራዊ ማህበረሰብ ዓላማ ጋር አንድ አይነት ያላቋረጠ ታማኝነት ጠብቶ ኖሮአል፡፡” የሚሉትን ቁራጭ ቃላት (የተቆረጡ ቃላትን) መሰረት በማድረግ ወይም በመጥቀስ ነው፡፡

ይህም ተጠቃሹ ቃላት ሆነ አጠቃላይ ፅሑፉ የአማራ ሕዝብ ለማንነቱ ግድ አይሰጥም አይልም፡፡ እንዲሁም ተከሳሾች ስለየትኛው አይነት ማንነት እንደጠቀሱ ማመልከቻው አያሳይም፡፡ አንድ ሰው በኢትዩጵያ ውስጥ በአንዴ የተለያዩ ስምንት ማንነቶች (identities) ሊኖሩት ይችላል፡፡ እነዚህም ዜግነታዊ ማንነት፣ ብሔራዊ(የብሄር) ማንነት፣ ሰዋዊ ምንነት፣ ሃይማኖታዊ ማንነት፣ ወንዛዊ(አከባቢያዊ) ማንነት፣  ክፍለ ሃገራዊ ማንነት፣ ጎሳዊ ማንነት፣ ዘራዊ (racial) ማንነት፣ እና ነገዳዊ ማንነት ናቸው፡፡ እናም አንድ ማንነት በጉልህ የሚታየው ወይም የሚገለፀው ከሌላው ጋር ሲነፃፀር እንደመሆኑ መጠን፤ አንድ ሰው ወይም ቡድን ማንነቱን የሚገልፅበት መንገድ እንደሁኔታው ይለያያል፡፡

በነገሩ ሁኔታ (ሁኔታው) ብሄራዊ ማንነትን (ethnic identity) የሚመለከት ከሆነ የብሔር ማንነቱን ይገልፃል፡፡ ሁኔታው ዜግነትን ሲከተል ደግሞ ዜግነታዊ ማንነቱን (ኢትዩጵያዊነቱን) ያንፀባርቃል፡፡ እንዲሁም ሁኔታው ወንዛዊ ማንነትን ሚመለከት ከሆነ ወንዛዊ ማንነቱን ያጎላል፡፡ ጎሳዊ ማንነትም እንዲሁ ነው፡፡ የነገሩ ሁኔታ  ክፍለ ሃገራዊ ማንነትን የሚመለከት ከሆነ ክፍለ ሃገራዊ ማንንነቱን ያንፀባርቃል ወይም ያጎላል፡፡ ውጭ ሃገር የሚኖሩ የተለያዩ ብሄሮች አባላት የሆኑ ኢትዮጵያውያን ኢትዮጵያዊ ማንነታቸውን ያስቀድማሉ፡፡

በሌላ አነጋገር ማንነታቸውን በዜግነት (በኢትዩጵያዊነት) ይገልፃሉ፡፡ ሁኔታው በዋናነት የሚወሰነው በቦታ ነው፡፡ ሰዎች የብሔር ማህበረሰባቸው በሰፈረበት መልክዓ ምድር ውስጥ በሚኖሩበት ጊዜ ማንነታቸውን በጎሳዊ፣ በወንዛዊ፣ ወይም ክፍለ ሃገራዊ ማንነት ይገልፃሉ፡፡ የፅሑፉ መደምደሚያ ተጠቃሹ ቃላትም ትርጓሜው ይህ ስለመሆኑ የፅሑፉን ገፅ ስድስት ያስረዳል፡፡

“በአገራቸው” ሲል የአማራ ሕዝብ በሰፈረበት መልክአ ምድር ውስጥ ሲሆኑ ማለት ነው፡፡ በዚህም መሰረት አማራዎች የአማራ ሕዝብ በሰፈረበት መልክዓ ምድር ውስጥ ብሄርተኝነትን (አማራነትን) ከቶ አጥብቀው አያውቁም ማለት ለብሔራዊ ማንነት (ለአማራዊ ማንነት) ግድ የላቸውም ማለት አይደለም፡፡ እንዲሁም ራሳቸውን በብሄርተኝነት (በአማራነት) ጨርሶ አይገልፁም ማለት አይደለም፡፡ ይልቁኑም ተጠቃሹ የፅሑፉ የመደምደሚያ ክፍል የሚለው አማሮች የአማራ ሕዝብ በሰፈረበት ግዛት ውስጥ በሚኖሩበት ጊዜ ብሄርተኝነትን ከቶ አጥብቀው አያውቁም ነው፡፡

የፅሑፉ ገፅ 10 እና 13 ላይ የአማራ ሕዝብ በሕገመንግስቱ አንቀፅ 47(1) እና 39(5) መሰረት ጥያቄ ማቅረብ ሳያስፈልገው በስም ተጠቅሶ የብርሄርተኝነት (የአማራነት) ዕውቅና አስቀድሞ እንደተሰጠው ይጠቅሳል፡፡ ይህም የሚያሳየው ፅሑፉ የአማራ ሕዝብ ለብሔርተኝነት (ለአማራነት) ግድ አይሰጠውም ብሎ እንደማያስብ (እንደማያምን) ነው፡፡ አንድ ሕዝብ የብሄርተኝነት ወግ አጥባቂ ላይሆን ይችላል፡፡ በመሆኑም አንድ ማህበረሰብ የብሔርተኝነት ወግ አጥባቂ ነው ወይም አይደለም ቢባል እንኳን ማወደስ ወይም ማናናቅ አይደለም፡፡

ከዚህም በላይ ተጠቃሹ የፅሑፉ የመደምደሚያ ክፍል ቃላት የአማራ ሕዝብ በጎጥ የሚጠራ ሕዝብ ነው ጨርሶ አይልም፡፡ ራሱን በክፍለ ሃገራዊ ማንነት መግለፅ ጎጠኝነትም አይደለም፡፡ፅሑፉ አንድም ቦታ የአማራ ሕዝብ በጎጥ የሚጠራ ነው አይልም፡፡ ለምሳሌ አንድ ኦሮሞ ኦሮሞነቱ እንደተጠበቀ ሆኖ በሜጫነቱ፣ በቦረናነቱ፣ በቱልማነቱ፣ በገላንነቱ ራሱን ሊገልፅ ይችላል፡፡ አንድም ሶማሌም የራሱን ብሄር በሰፈረበት ግዛት ውስጥ ሲኖር ራሱን በኦጋዴናዊ፣ በሀውያዊ፣ ወይም በኢሳዊ ማንነቱ ሊገልፅ ይችላል፡፡ አንድም አማራ ራሱን ወለዬ፣ ሸዋ ወይም ጎጃሜ በማለት ሊገልፅ ይችላል፤ ይገልፃልም፡፡ ይህ ምንም ክፋት የለውም፡፡ በየትኛውም አከባቢ ወይም ብሄር ውስጥ ሊኖር የሚችል ነው፡፡

ለማጠቃለል ያህል አንድ አማራ በሃገሩ ውስጥ (በብሄሩ በሰፈረበት ግዛት ወይም ክልል) ውስጥ ራሱን በወለዩነቱ፣ በጎጃሜነቱ ወይም በሸዋዊነቱ ይገልፃል ማለት ወይም አጉልቶ ይገልፃል ማለት በማንነቱ የማይኮራ በጎጥ የሚጠራ ሕዝብ ነው ማለት አይደለም፡፡ ከዚህም በላይ የፅሑፉ ተጠቃሽ ቃላት ከቶ አጥብቆ አያውቅም ይላል እንጂ ከቶ በብሔራዊ ማንነቱ አይኮሩም፤ በጎጥ የሚጠራ ህዝብ ነው ጨርሶ አይልም፡፡

ፅሑፉ አንድም ቦታ የአማራ ሕዝብ በጎጥ የሚጠራ ሕዝብ እንደሆነ ወይም የዘር ልዩነትን አጎልቶ የገለፀበት ሁኔታ የለም፡፡ በነገራችን ላይ እንኳን በአማራ ሕዝብ መካከል ይቅርና በትግራይና በአማራ ሕዝብ መካከል የዘር(race) ልዩነት የለም፡፡ በአማራ ሕዝብ መካከል ሊኖር የሚችለው ልዩነት ክፍለ ሃገር ወይም ወንዛዊ ልዩነት ይሆናል፡፡ በአማራና በትግራይ ሕዝቦች መካከል የሚኖረው ልዩነት የዘር ሳይሆን የብሔር ነው፡፡ ልዩነት(diversity) ፀጋ እንጂ ሌላ ሊሆን አይችልም፡፡ ልዩነት ጎጠኝነት አይደለም፡፡ ልዩነትን እንደጎጠኝነት የምንረዳው ወይም የምናስብ ከሆነ ልዩነትን የማክበር ፍላጎት የለንም ማለት ነው፡፡ ልዩነት ካለ መከበር አለበት፡፡ ከሌለ ደግሞ በግድ ልዩነት መኖር አለበት አይባልም፡፡

የፅሑፉ ዓላማ ስለ አማራ ሕዝብ ብሄርተኝነትና ክፍለ ሃገራዊነት ጉዳይ መፃፍ አይደለም፡፡ ለዚህም ነው ተጠቃሹ የፅሑፍ የመደምደሚያ ክፍል ቃላት “እዚህ ላይ ለመጥቀስ ያህል…” በማለት የጀመረው፡፡ የፅሑፉ ዓላማ በፅሑፉ ገፅ ሦስት ላይ እንደተገለፀው ስለማንነት ጥያቄ ምንነትና ስለ ድንበር አከላለል ለውጥ ጥያቄ ምንነት በማጥናትና በመመራመር ስለአተረጓገማቸው ሃሳብ (አስተያየት) ማቅረብ ነው፡፡ በዚህም መሰረት ፅሑፉ የዳሰሳቸው ጉዳዩች፡- 

1. የማንነት ጥያቄ ምንነት፣

2. የድንበር አከላለል ለውጥ ጥያቄን ምንነት፣

3. የኢትዩጵያ ሕግስ እንዴት ይጠብቃቸዋል እና 

4. የትግራይ ሕዝብ ታሪካዊ አሰፋፈር ናቸው፡፡

በመሆኑም የዘር ልዩነት ወይም ከብርሄርተኝነት በታች ስለሆኑ የማንነት ጉዳዩች ፅሑፉ የመዳሰስ ዓላማ የለውምም፤ አልፃፈምም፡፡

ከዚህ በላይ ተከሳሾች ዳኛው በፅሑፋቸው ላይ ሰፋ ያለ የዘረኝነት ሃሳብ አቅርበዋል ብለዋል፡፡ ፅሑፉ የዘረኝነት ሃሳብ ይዟል ወይስ አልያዘም የሚለውን ከማየታችን በፊት ዘረኝነት ምን ማለት ነው? የሚለውን ማወቅ የግድ ነው፡፡ ዘረኝነት በእንግሊዘኛው Racism ለሚለው ቃል አቻ ትርጉም ሲሆን ዘረኝነት (racism) ብሎ ነገር የሚኖረው የዘር(race) ልዩነት ሲኖር ብቻ ነው፡፡ ይሁንና እንኳን በአማራና በትግራይ ሕዝቦች መካከል ይቅርና በየትኛውም የኢትዩጵያ ሕዝቦች መካከል የዘር ልዩነት የለም፡፡ ስለሆነም ተከሳሾች የዘረኝነት ሐሳብ ያሉት የብሔርተኝነት ሐሳብ ሊሆን ይችላል፡፡

ብሔርተኝነት የሚለው የአማርኛ ቃል በኢንግሊዘኛ Nationalisim ማለት ነው፡፡ ብሔርተኝነት ማለት የብሔር ጥያቄ ማለትም ራስን በራስ የማስተዳደርና ማንነትን የማስጠበቅ ትግል ማለት ነው፡፡ ሕገ መንግስታችን ብሔርተኝነትን ያከብራል፡፡ ሦስት ዐይነት ብሔርተኝነት ያለ ሲሆን ከእነዚህ ውስጥ ሕገ-መንግስታችን የሚያራምደው ዴሞክራሲያዊ ብሔርተኝነትን ነው፡፡ ስለሆነም በሕገ  መንግስቱ ውስጥ የቀመጠውን ዴሞክራሲያዊ ብሔርተኝነትን ሐሳብ በፅሑፉ ውስጥ ማቅረብ የሚነቀፍ አይደለም፡፡ ትግራዋይነትን መግለፅና መከላከል ዴሞክራሲያዊ ብሔርተኝነት እንጂ ዘረኝነት አይደለም፡፡ ዳኛ ብሔር አልባ እንዲሆን መጠበቅም ተገቢ አይደለም፡፡

ፅሑፉ የአማራ ሕዝብ የራሱን ማንነት እውቅና አሰጥቶ ራሱን በራሱ የሚያስተዳድርበት ክልል ከመመስረቱም በላይ በውስጡ ለሚገኙት ብሔሮች ማለትም የኦሮሞ እና የቅማንት ማንነቶችን ያከበረ እንደሆነ ዕውቅና በመስጠት በመልካምነት አንስቷል፡፡ (የፅሑፉን ገፅ 10 እና 16 ይመልከቱ)፡፡

በአጠቃላይ ተከሳሾ ለፅሁም ሆነ ለተጠቃሹ የፅሑፉ የመደምደሚያ ክፍል ቃላት የሰጡት ትርጓሜ ከተጠቃሹ ቃላቱም ሆነ ከአጠቃላይ የፅሑፉ ይዘትና ዓላማ አኳያም መሰረት የለውም፡፡ በመሆኑም ይህን መሰረት የሌለው ትርጓሜን መሰረት በማድረግ ያነሱት የይነሳልኝ ጥያቄ ተቀባይነት ሊኖረው አይችልም፡፡…..

በመሆኑም አንድ ዳኛ ያለ በቂ ምክንያትና ያለበቂ ማስረጃ በተከራካሪ ወገኖች ወይም በአንዱ ተከራካሪ ወገን እንዲነሳ ስለጠየቀ ብቻ መነሳት አይችልም፡፡ በሌላ በኩል ማንኛውም ተከራካሪ ወገን ወይም ተከሳሽም ሆነ ከሳሽ በሕዝብ ተወካዩች ምክር ቤት (በሕዝብ) በተሾመ ዳኛ የመዳኘት ግዴታ አለበት፡፡ ይህም ማለት ሁለቱም ወገኖች ወይም አንዱ ተከራካሪ ወገን ጉዳዩን እገሌ አይዳኘኝም እገሌ ይዳኘኝ ብለው ዳኛ የሚያማርጡበት መብት የላቸውም፡፡ በመሆኑም ተከሳሾች ተቃውሞ ማቅረባችን ወይም በመጠራጠራችን ብቻ ዳኛው ሊነሱ ይገባል በማለት ያቀረቡት መከራከሪያ የአዋጅ ቁጥር 25/88 አንቀፅ 27/1/ሠ እና 30 ያላገናዘበና መሰረት ያላደረገ ነው፡፡ ስለሆነም በአጠቃላይ ከችሎት የመነሳት ጉዳይ ከሕግና ከማስረጃ አኳያ በጣም በጥንቃቄና ዘርዘር ባለ ሁኔታ መታየት አለበት፡፡

በአጠቃላይ የግራ ዳኛ ከሽርተኝነት ጉዳይ ላይ ሊያስነሳ የሚችል በቂ ሕጋዊ ምክንያትና ማረጋገጫ የለም፡፡ በሌላ አገላለፅ የግራ ዳኛው በተከሳሾች ላይ በቀረበው የሽብርተኝነት ጉዳይ ላይ ገለልተኛ ዳኝነት አይሰጥም (ትክክለኛ ፍትሕ አይሰጥም) የሚያሰኝ በቂ ምክንያትና ማረጋገጫ የለም፡፡ በመሆኑም ጥያቄው ተቀባይነት የለውም፡፡

********

Daniel Berhane

more recommended stories