ኳታር እና ኢትዩጵያ በሶማልያ ጉዳይ ለምን ተጣሉ?

ይህን ፅሑፍ የጻፍኩት የዛሬ አመት ሲሆን ለመፃፍ ያስገደደኝ አንደኛዉ ሙያየ ስለሆነ፣ ሁለተኛዉ ማንም ሊያዉቀዉ የሚገባ ያገር ጉዳይ ስለሆነ ነዉ፡፡ በቅርቡ የኳታር ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት ልዑክ ከኢትዮጵያ አቻው ጋር በብሔራዊ ቤተ መንግሥት ውይይት ማካሄዱ ሰምተናል፡፡

የኢትዮጵያ መንግሥት በወቅቱ ግንኙነቱን ለማቋረጥ የወሰነው ኳታር የሶማሊያ አሸባሪዎችን በመርዳት፣ የአፍሪካ ቀንድን የመረበሽና በኢትዮጵያ ብሔራዊ ደኅንነት ላይ ጉዳት የማድረስ እንቅስቃሴ በማድረግ ላይ ነች በማለት ወቀሳውን ከሰነዘረ በኋላ ነው፡፡ ይሄ እንደተጠበቀ ሁኖ መንግስት ጉዳዩን ሙያ በልብ በሚል መንፈስ ጉዳዩን ግንኙነት ከማቋረት ዉጭ የተነፈሰዉ ጉዳይ አልነበረም፡፡

የኳታር መንግሥት የኢትዮጵያን ወቀሳ መሠረተ ቢስ ውንጀላ ነው በማለት ቢያስተባብልም፤ የዚህ ፅሑፍ ዋና አላማ የኢትዮጵያን መንግስት ወቀሳ በመረጃ እና ማስረጃ ለማስደገፍ ነዉ፡፡

ሁለተኛዉ አላማ ደግሞ በሶማልያ ጉዳይ የኳታር መንግሥት የፓለቲካ ባህሪ ለዉጥ በግዴታ እንጂ በዉዴታ እንዳልመጣ ማስረዳት ነዉ፡፡ በሶማሊያ የተገኘውን አንፃራዊ ሰላም ለማጐልበትና አገሪቱን በድጋሚ ለመገንባት የኳታር መንግሥት ለዚህ ልዩ ድጋፍ ለመስጠት የተስማማዉ ተገዶ እንጂ ፈልጎ እንዳልሆነ ለማስረዳት ጭምርም ነዉ፡፡ ለዚህ ፅሑፍ ለማዘጋጀት ከታሪካዊ መፃህፍቶች እስከ የዊኪሊክስ መረጃዎችን ተጠቅሚያለዉ፡፡ መልካም ንባብ፡፡

የፀብ መጀመርያ

የፀብ መነሻ እ.ኤ.አ በ2006 ዓ.ም የእስላማዊ ፍርድ ቤት ህብረት ተብሎ የሚጠራዉ፣ የሶማልያን ቦታዎች ሙሉ በሙሉ በመቆጣጠር፣ አለም አቀፍ እዉቅና የተሰጠዉ ግን ደካማ የነበረዉ የባይድዋ መንግስት ተብሎ የሚጠራና የአሁኑ የሶማልያ መንግስት መሰረት የሆነዉን ለማጥቃት እና ለማጥፋት በተንቀሳቀሰበት ወቅት ነበር፡፡ ከዚህ ባለፈ በተመሳሳይ ኢትዪጵያ ላይ “የሃይማኖት ጦርነት” ያወጀበት ወቅት ጭምር ነበር፡፡

የእስላማዊ ፍርድ ቤት ህብረት የአክራሪ እስልምና አጀንዳ ይዞ የሚንቀሳቀስ እና በአንዳንድ የዉጭ አገራት እየተደገፈ መንግስት ለማቋቋም ዳር ደርሶ የነበረ ሃይል ነበር፡፡ ከእስላማዊ ፍርድ ቤት ህብረት የኢኮኖሚና የዲፕሎማሲያዊ ድጋፉ በስተጀርባ የነበሩት የዉጭ መንግስታት በቀዳሚነት የሚጠቀሱት ኳታር እና ኢራን ነበሩ፤ የተለያየ የፓለቲካዊ እስልምና ፍልስፍና የሚያራምዱ ቢሆንም፡፡

የእስላማዊ ፍርድ ቤት ህብረት ሶማልያን ሙሉ በሙሉ ሊባል በሚችል የተቆጣጠረበት ወቅት፣ የተባበሩት መንግስታት በሶማልያ ለሁለት አስርት አመታት ጥሎት የነበረዉ የጦር መሳርያ ማዕቀብ በሰፊዉ እየተጣሰ የነበረበት ጊዜ ነበር፡፡ እ.ኤ.አ በግንቦት 2006 ዓ.ም የተባበሩት መንግስታት ቋሚና እና ጊዚያዊ የፀጥታዉ ምክር ቤት አባላት ለምሳሌ ቻይና፣ጃፓን፣ ግሪክ፣ ሩስያ፣ኮንጎ እና ጋና የጦር መሳርያ ማዕቀብ መጣሱ የተቋወሙ ሲሆኑ፣ ጠበቅ ያለ ቁጥጥር እና ክትትል እንዲደረግ አጥብቀዉ ጠይቀዋል፡፡

Photo - Doha, Qatar
Photo – Doha, Qatar

በዚያን ወቅት የሶማልያ የጦር መሳርያ ማዕቀብ ተቆጣጣሪ ኮሚቴ ሊቀመንበር ኳታር ነበረች፡፡ የኳታር መንግስት እንደ ሊቀመንበርነቱ አዎንወታዊ ሚና መጫወት ትቶ፣ ፀረ ኢትዪጵያ የሆኑ አቋሞች ባገኘችዉ አጋጣሚ መጠቀም ስራየ ብሎ ተያያዘዉ፡፡ ኳታር የሶማልያ የጦር መሳርያ ማዕቀብ ተቆጣጣሪ ኮሚቴ ስራ ለማቀላጠፍ ቃል ገብታ የነበረች ብትሆንም፣ የጦር መሳርያ ማዕቀብ ጥሰት አይታ እናዳላየች፣ ሰማታ እንዳልሰማች በዝምታ የሚገለፅ አፍራሽ የሆነ ግዳጅ ይዛ ስትንቀሳቀስ የነበረችዉ፡፡

እ.ኤ.አ በግንቦት 2006 ዓ.ም የእስላማዊ ፍርድ ቤት ህብረት ሶማልያን ሙሉ በሙሉ ለመቆጣጠር እየተንቀሳቀ የነበረበት እንዲሁም የሚያካሂደዉ ዘመቻ ያጠናከረበት በነበረበት ወቅት ፣ ኳታር የባይድዋን መንግስት ከልብ ሳትቀበለዉ ግን የእርስ በእርስ ጦርነት አቁሞ ሁሉም ወገኖች ወደ ድርድር እንዲገቡ ከሌሎች የፀጥታዉ ምክር ቤት አባላት ጥሪ አቅርባ ነበር፤ ከልብ የመነጨ ባይሆንም፡፡ የዚህ ሁሉ ድራማ መቋጫ ያገኘዉ በኢትዪጵያ መከላከያ ሰራዊት ጣልቃ ገብነት እንደነበረ የቅርብ አመት ትዉስታ ነዉ፡፡

ከዛ በኃላ የባይድዋን መንግስት በአብዱላሂ የሱፍ መንግስት አመራር እና በኢትዪጵያ መንግስት ድጋፍ እየተጠናከረ የሄደበት ሂደት መጣ፡፡ በዚህ ወቅት ኳታር የተባበሩት መንግስታት ጊዝያዊ የፀጥታ ምክር ቤት አባል በነበረችበት ወቅት (እ.ኤ.አ 2006-2007 ዓ.ም) የሶማልያ ጉዳይ በተነሳ ወቅት የኢትዩጵያ ሰራዊት ያለ ቅድመ ሁኔታ ከሶማልያ መዉጣት አለበት ብላ ሽንጧን ገትራ ስትከራከር የነበረች አገር ነች፡፡

ከአንድ አመት ብኃላ እ.ኤ.አ ግንቦት በ2007 ዓ.ም የባይድዋን መንግስት የፓርላማ አባላት የነበሩ ወደ 42 የሚጠጉ ተወካዮች በአብዱላሂ የሱፍ የሚመራዉን መንግስት በመቃወም፣ “የሶማልያ ነፃ ፓርላማ” ራሱን በማለት ከሶማልያ ዉጭ ወጥተዉ ለብቻቸዉ የሚንቀሳቀሱበት ጊዜ ነበር፡፡ “የሶማልያ ነፃ ፓርላማ” ከአስመራ እና ኳታር መንግስታት ጠበቅ ያለ ግንኙነት የመሰረተበት ወቅት ጭምር ነበር፡፡

“የሶማልያ ነፃ ፓርላማ” መቀመጫዉ አስመራ አድርጎ በቀድሞ የፓርላማ አፈ-ጉባኤ ሻሪፍ ሃሰን ሼኽ አዳን የሚመራ ቡዱን ነበር፡፡ “የሶማልያ ነፃ ፓርላማ” የፓለቲካ ግብ በወቅቱ የሶማልያ ጠቅላይ ሚኒስትር የነበሩት ጌዲ በለዘብተኛ የእስላማዊ ፍርድ ቤት ህብረትአባል ተተክቶ፣ ለሃዊይ ጎሳ አባል የጠቅላይ ሚኒስተርነሩ ቦታ እንዲሰጠዉ ነበር፡፡ “የነፃ ፓርላማ” ቡዱን የመጨረሻዉ ግብ ግን በአብዱላሂ የሱፍ የሚመራዉን መንግስት ማስወገድ እንደነበረ ለማንም ግልፅ ነበር፡፡

በዚህ ወቅት የኳታር መንግስት ሌላ ጥፋት ሰራ፡፡ በአብዱላሂ የሱፋ የሚመራዉን መንግስት ወደ ጎን በመተዉ ፣ ሻሪፍ ሃሰን ሼኽ አዳን እና የእስላማዊ ፍርድ ቤት ህብረት ለዘብተኛ የነበሩ ኃላም የሶማልያን ፕሬዝደንት የሆኑት ሼኽ ሸሪፍ ሼኽ አህመድ በኳታር ዶሃ ለማደራደር ጥረት አድርጋለች፡፡

ኳታር ሻሪፋ ሃሰን ሼኽ አዳን እና ሼኽ ሸሪፋ ሼኽ አህመድ ለማደራደር እንደ ምክንያትነት የተጠቀመችበት ፣ ሁለቱም ወገኖች “የኢትዩጵያ ሰራዊት ያለ ቅድመ ሁኔታ ከሶማልያ መዉጣት አለበት” የሚል ግዜያዊ የፓለቲካ አቋም ነበር፡፡ ድርድሩ ግን ዉጤት አልባ ነበር፡፡

ምክንያቱም ለዘብተኛ የሆኑት የእስላማዊ ፍርድ ቤት ህብረት አባለት የሚኒስትርነት ቦታ ይዘዉ በአብዱላሂ የሱፋ የሚመራዉ መንግስት ለመቀላቀል አማራጭ ሃሳብ ያቀረቡት ሻሪፍ ሃሰን ሼኽ አዳን ኳታር ደስተኛ ባለመሆና ነበር፡፡

እ.ኤ.አ 2007 ዓ.ም ፀረ-ኢትዩጵያ የሚያራምዱ የነበሩት “የነፃ ፓርላማ” ብዱን እና የእስላማዊ ፍርድ ቤት ህብረት ሊቀ መንበር የነበሩት ሼኽ ሸሪፍ ሼኽ አህመድ እንዲሁም የፌደራል የሽግግር መንግስት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስተር የነበሩት ሁሴን መሃመድ ፍራ አይዲድ በኤርትራ መንግስት ጋበዥነት አስመራ ላይ እንዲገናኙ ኳታር ከኤርትራ መንግስት በስተጀርባ ሁና ስትንቀሳቀስ ነበር፡፡

የኤርትራ መንግስት ምኞት የሞቃድሾን መንግስት ሊቀናቀን የሚችል ሌላ መንግስት እንዲቋቋም ነዉ፡፡ ለዚህ ተግባር እንዲደርስ የኢትዮ-ኤርትራ የድንበር ዉሳኔ አፈፃፀም ላይ ቅሬታ በማሳደሩ ነዉ፡፡ የኤርትራ መንግስት የኢትዮ-ኤርትራ የድንበር ዉሳኔ ያለ ቅድመ ሁኔታ እንዲፈፀም ፋላጎቱ ነዉ፡፡

የኢትዮ-ኤርትራ የድንበር ዉሳኔ ተፈፃሚነት ዋስ የሆኑት የአሜሪካ እና የአልጀርያ መንግስታት ኢትዩጵያን ማስገደድ ባለ መቻላቸዉ የኤርትራ መንግስት ቅሬታ እንዳደረበት የምስራቅ አፍሪካ ተንታኞች ይገልፃሉ፡፡ ኤርትራም የፀረ ኢትዩጵያ ሃይሎች ማደራጀት የዚህ ቅሬታ ዉጤት ነዉ፡፡በኢትዮ-ኤርትራ የድንበር ዉሳኔ በተመለከተ የኳታር መንግስት በኤርትራ መንግስት የነበረዉ አቋም ተመሳሳይ ነበር፡፡

የኳታር መንግስት በኢትዩጵያ የዉስጥ ጉዳይ ጭምር ገብቷል፡፡ የቀድሞ የእስላማዊ ፍርድ ቤት ህብረት አባል የነበሩት እና የኢትዩጵያ የሽብርተኝነት ዝርዝር ዉስጥ የገቡት አዳን ሃሺ ኤይሮ ያደረገችዉ ቀጥታዊ ያልሆነ ድጋፋ ነዉ፡፡ አዳን ሃሺ ኤይሮ በኢትዪጵያ ሶማልያ የሚንቀሳቀስ ራሱ ኦብነግ ብሎ የሚጠራዉ ኃይል ጋር በመመሳጠር ፀረ ሰላም የሆኑ እንቅስቃሴ ሲያደርጉ ነበር፡፡

እ.ኤ.አ ሐምሌ 2007 ዓ.ም ሶማልያ በታሪካ ትልቅ የሚባል ታሪካዊ ሂደት አስተናግዳለች፡፡ እሱም የሶማልያ ሙሉ ጎሳዎች ሊባል በሚችል የተካፈሉበት የእርቅ እና የሰላም ኮንፈረንስ ነበር፡፡ የሶማልያ የእርስ በርስ ጦርነት ምክንያት እስከ የንብረት እና ሀብት ክፍፍል የሚመለከት ለ45 ቀናት የቆየ ኮንፈረንስ ነበር፡፡ እ.ኤ.አ 1991 ዓ.ም የሶማልያ የእርስ በርስ ጦርነት ለመጀመር ምክንያት የነበሩ የሃዊይ ጎሳዎች ተሳትፈዉ ነበር፡፡ የሃዊይ ጎሳዎች ንኡስ ጎሳዎች እንደ ኡጋስ ሃዋድል፣ ኡጋስ ዲር፣ ሱልጣን ሱሉዕማን፣ ሱልጣን ሙርሳድ በኮንፈረንሱ ተሳታፊዎች ነበሩ፡፡

በኮንፈረንሱ ላይ ያልተሳተፉት የሃዊይ ንኡስ ጎሳ ኡጋስ አይር ነበሩ፡፡ በአሜሪካ የሽብርተኝነት ዝርዝር ዉስጥ የገቡት ሃሰን ዳሂር አወይስ የሃዊይ ንኡስ ጎሳ ኡጋስ አይር በእርቀ ሰላሙ እንዳይሳተፉ ከፍተኛ ጫና በማሳደሩ እንደ ነበረ በምክንያትነት ይጠቀሳል፡፡ የእርቀ ሰላሙ የሃዊይ ንኡስ ጎሳ ኡጋስ አይር ባለ ማሳተፉ ግን ሙሉ በሙሉ ዉጤታማ ነበር ማለት አይቻልም፡፡ ሃሰን ዳሂር አወይስ በስተጀርባ ደግሞ የኤርትራ እና የኳታር መንግስታት ነበሩ፡፡

የሱዑዲ አረብያ ንጉስ አብደላሂ በአስመራ የሚገኝዉ የነበረ ቡዱን ወደ ሽግግር መንግስት እንዲገብ እንዲሁም ለዘብተኛ ተብለዉ የሚጠሩ የእስላማዊ ፍርድ ቤት ህብረት አባለት የኳታር መንግስት እንዲያግባባ ለቀረበላት ጥያቄ ፋቃደኛ አልነበረም፡፡ ሌሎች የኳታር ወዳጅ አገሮች በተደረገ የማግባባት ጥረትም ስኬታማ አልነበረም፡፡

ለምሳሌ የፈረንሳይ ከኳታር መንግስት ጥሩ ግንኙነት ካላቸዉ የአዉሮፓ አገራት አንዷ ነች፡፡ የኳታር ኢሚር ልጅ በፈረንሳይ የጦር ኮሌጅ እንደሚማር እንዲሁም የሴት ጓደኛዉ የፕሬዝዳንት ነበር ሳርኮዚ እህት መሆና ኳታር ላይ ተፅእኖ ማሳደር ሞክራ ነበር፡፡ዉጤት አልባ ሆነ እንጂ፡፡

አሜሪካ ሌላዋ የኳታር ወዳጅ አገር ነች፡፡ግን አሜሪካ እና ኳታር በሶማልያ የነበራቸዉ አቋም የተለያየ ነበር፡፡አሜሪካ በሶማልያ ያላት አቋም ከሁለት አመክንየቶች ይመነጫል፡፡ መጀመርያዉ የፀረ-ሽብርተኝነት ትግል ሲሆን ሁለተኛዉ ደግሞ የነዳጅ ሕግ ጋር የተያያዘ ነዉ፡፡ የአሜሪካ የፀረ-ሽብርተኝነት ትግሉ እንደተጠበቀ ሁኖ እ.ኤ.አ ከ 1991 ዓ.ም በፊት በሶማልያ ነዳጅ ፋለጋ የተሰማሩ የአሜሪካ ታላላቅ ኩባንያዎች ዉል እንዲቀጥል ትልቅ ፋላጎት አላት፡፡

አሜሪካ የአብዱላሂ የሱፋ እንዲሁም ሼኽ ሸሪፋ ሼኽ አህመድ መንግስት ድጋፍዋ የሰጠችዉ እ.ኤ.አ ከ1991 ግ.ም በፊት የነዳጅ ፍለጋ ዉሎች እንደሚያከብሩ ቃል ስለ ገቡ ጭምር ነዉ፡፡ እ.ኤ.አ 1991 ዓ.ም በፊት በሶማልያ የነዳጅ ፍለጋ ዉሎች ዋና ተጠቃሚዎች የአሜሪካ ኩባንያዎች ናቸዉ፡፡

የኤርትራ መንግስት በሶማልያ የዉስጥ ጉዳይ ጣልቃ መግባት ትርጉም እንዲኖረዉ ምክንያት የነበረችዉ ኳታር ነበረች፡፡ ምክንያቱም የኤርትራ መንግስት ለሶማልያ አሸባሪ ቡዱኖች የሚያደርገዉ ድጋፍ የኤርትራ መንግስት ኢኮኖሚ የመሸከም አቅም የለዉም፡፡

ከዚህ በተጨማሪ ፀረ-ኢትዮጵያ አቋም ያላቸዉ ሃይሎች ድጋፍ ለማድረግ የኤርትራ መንግስት ኢኮኖሚ የመሸከም አቅም የለዉም፡፡ የኤርትራ መንግስት ከሱዳን ጀምሮ እስከ መካከለኛዉ ምስራቅ ጣልቃ ገብነት የኤርትራ መንግስት ኢኮኖሚ የመሸከም አቅም የለዉም፡፡ ለዚህም ኳታር በተዘዋዋሪ ተጠያቂ ነች፡፡

እ.ኤ.አ መስከረም 2007 ዓ.ም ኳታር በሚስጥር ራሱን “የሶማልያ ዳግም ነፃ አዉጪ ህብረት” ብሎ የሚጠራዉ የአብዱላሂ የሱፍ መንግስት መተካት አላማ አድርጎ የተንቀሳቀሰዉ ቡዱን የቅድመ ድርድር ያካሄደዉ በኳታር ዋና ከተማ ዱኃ ላይ ነበር፡፡ “የሶማልያ ዳግም ነፃ አዉጪ ህብረት” የኳታር መንግስት ፋላጎት የሚወክል እንደነበረ ግልፅ ነበር፡፡ ግን “የሶማልያ ዳግም ነፃ አዉጪ ህብረት” በአንድ ድምፅ አቋም ይዘዉ እንዲሄዱ የኳታር እና የኤርትራ መንግስት ያደረጉት ጥረት የተሳካ አልነበረም፡፡ ምክንያቱም “የሶማልያ ዳግም ነፃ አዉጪ ህብረት” ስብስብ ጤናማ አልነበረም፡፡

ሌላ አግራሞት የፈጠረዉ ሂደት ግን ኳታር ሃሰን ዳሂር አወይስ ከአሜሪካ የሽብርተኝነት ዝርዝር እንዲሰረዝ በዉጭ ጉዳይ ሚኒስተር አህመድ አል ማሁሙድ በኩል ያደረገችዉ ዉጤት አልባ ሙከራ ነበር፡፡ ኳታር ሃሰን ዳሂር አወይስ ከአሜሪካ የሽብርተኝነት ዝርዝር ተሰርዞ የሶማልያ መንግስት አካል እንዲሆን ትልቅ ፋላጎት ነበራት፡፡ ሃሰን ዳሂር አወይስ በተመለከተ የኳታር መንግስት ከኤርትራ መንግስት በጋራ ለመስራት ፋላጎት እንደነበራት መረጃዋች ያሳያሉ፡፡

በስተመጨረሻም እ.ኤ.አ መጋቢት 2009 ዓ.ም የአረብ ሊግ አመታዊ ስብሰባ በኳታር ዋና ርእሰ ከተማ ዶኃ ላይ ነበር የተካሄደዉ፡፡ ለስብሰባዉ ከተያዙት የመወያያ አጀንዳዋች አንዱ የሶማልያ መልሶ ለማቃቃም የአረብ ሊግ ሊያደርገዉ የሚገባ የገንዘብ ድጋፍ ነበር፡፡

ለዚህ ጉዳይ በሶማልያዉ ፕሬዝደንት ሼኽ ሸሪፍ ሼኽ አህመድ ያደረጉት ጥረት ፋሬ እንዳያፈራ እና የአረብ ሊግ አባል አገራት እንደ ህብረት ድጋፍ እንዳያደርጉ ዉስጥ ለዉስጥ ከፍተኛ የዲፕሎማሲያዊ ጨዋታ አድርጋለች፡፡ ለዚሁም ኳታር ተሳክቶላታል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ኳታር የአፍሪካ ህብረት ጥበቃ ድጋፍ ተልእኮ በሶማልያ (AMISOM) ድጋፍ ለማድረግም ፍላጎት አልነበራትም፡፡

ስለሆነም ከአቅሙ በላይ የሆነበት የኢትዮጵያ መንግስት ያለዉ ቅሬታ ለኳታር መንግስት በተደጋጋሚ በተለያዩ አለም አቀፍ መድረኮች ያመለከተ ቢሆንም፣ የኳታር መንግስት ግን ከድሪጊቱ ሊቆጠብ አልቻለም ነበር፡፡ ስለሆነም በኢትዮጵያ እና በኳታር መንግስታት የዲፕሎማሲ ግንኝነት መቋረጥ ነበረበት፡፡ ስለሆነም ግንኝነቱ ተቋረጠ፡፡

ታድያ የአሁኑ የኢትዮጵያ እና የኳታር መንግስታት የዲፕሎማሲ ግንኙነት መሻሻል ለብቻዋ የተነጠለችዉን ኤርትራ ላይ ያለዉ ትርጉም ምንድን ነዉ ብሎ መፈተሽ ያስፈልጋል፡፡ እርግጥ ነዉ የኳታር እና የኤርትራ መንግስታት በሶማልያ ያላቸዉ አቋም አሁን ተለያይቷል፡፡ ለዚህም ይመስላል የኤርትራ መንግስት በኳታር በኩል በአሁኑ በሃሰን ሼክ መሃሐድ የሚመራዉ መንግስት መታረቅ የፈለገዉ፡፡ ዉጤቱ በተቃራኒዉ ቢሆንም፡፡

ይሄ ሲባል ግን በሶማልያ ዉጭ ሁለቱም አገራት የሚያስተሳስራቸዉ የጋራ አጀንዳዎች ግን የሉም ማለት አይደለም ፡፡ ለምሳሌ የኤርትራ ወደቦች አስተዳደር፣ የዳህላክ ደሴቶች እንቨስትመንት፣ የአፍሪካ ቀንድ የፀጥታ እና ሰላም ጉዳዮች ኳታር እና ኤርትራን በጋራ የሚያስተሳስራቸዉ አጀንዳዎች ናቸዉ፡፡ የኳታር መንግስት በአፍሪካ ቀንድ እንዲሁም በምስራቅ አፍሪካ ለሚኖረዉ ተፅእኖ የኤርትራ ድጋፋ ይፈልጋል፡፡

ኳታር ከኢትዮጵያ ጋር በብዙ ሁኔታዋች የጋራ አቋም መዉሰዱ ብቻ ኳታር በምስራቅ አፋሪካ ጉዳዮች የበላይ ሊያደርጋት አይችልም፡፡ አደራዳሪ የጠፋበት የኢትዮ-ኤርትራ የድንበር ዉሳኔም ለኳታር በቀንድ አፋሪካ የመጫወቻ ካርድ ሊሆን ይችላል፡፡በሶማልያ ያጣችዉ የዲፕሎማሲ ድል በየኢትዮ-ኤርትራ የድንበር አተገባበር ዉሳኔዉ በማስፈፀም ልታካክሰዉ ትችላለች፡፡

ማጠቃለያ

የኳታር እና የኢትዪጵያ የሁለትዮሽ ግንኝነት መበላሸት የጀመረዉ የኳታር መንግስት በሶማልያ ጉዳይ ሲያራምደዉ በነበረዉ አቋም ምክንያት ነበር፡፡ የኳታር መንግስት የሶማልያ ጉዳይ በተመለከተ የሚያራምደዉ አቋም ከጅምሩ የተሳሳተ ነበር፡፡ የኳታር መንግስት የሶማልያ ጉዳይ የአፍሪካ አገሮች እና የአፍሪካ ህብረት አጀንዳ መሆኑ ቀርቶ የአረብ ሊግ ጉዳይ እንዲሆን ተደጋጋሚ ዉጤት አልባ ሙከራዎች አድርጓል፡፡

እ.ኤ.አ 2006 እስከ 2008 ዓ.ም ሶማልያን ሲያስተዳድር የነበረዉ የሽግግር ፌደራላዊ መንግስት እዉቅና እንዳያገኝ በፊት አዉራሪነት ዘመቻዉ መርታለች፡፡ ኳታር የአብዱላሂ የሱፍ መንግስት የአረብ ሊግ አገሮች እዉቅና እናዳያገኝ ሌት ተቀን ሰለቸኝ ደከመኝ ሳትል ሰርታለች፡፡ የአረብ ሊግ ተፅእኖ ፈጣሪ አገሮች እንደ ሳዉዲ አረብያ የአብዱላሂ የሱፍ መንግስት እዉቅና እንዳይሰጠዉ የኳታር ጠቅላይ ሚኒስተር ሃሚድ በግል ሳእዉዲ አረብያ ንጉስ አብደላህ ለማግባባት ሞክሮ ሳይሳካለት ቀርቷል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ የግብፅ መንግስት በሶማልያ የነበረዉ አቋም ከኳታር መንግስት የሚመሳሰል የነበረ ቢሆንም በስተመጨረሻ ግን የአብዱላሂ የሱፍ መንግስት እንደደገፈ ለማዎቅ ተችላል፡፡ስለዚህም የኳታር መንግስት የግብፅ መንግስት ለማግባባት ያደረገዉ ጥረት አልተሳካለትም፡፡ ስለሆነም የኳታር መንግስት በሶማልያ ያራምድ የነበረ አቋም የተሳሳተ እንደነበር ብዙ ተከታዪች አለማፍራቱ አንድ መገለጫ ነዉ፡፡

የኳታር መንግስት የሶማልያ ጉዳይ እሱ በሚፈልገዉ መንገድ ሳይሄድ ሲቀር የሞቃድሾዉ እና የአስመራዉ ቡዱን ለማግባባት በመሞከር ዶሃ ሌላ መደራደርያ ፎረም እንዲሆን ጥረት አድርጓል፡፡ የሶማልያ ጉዳይ የኢጋድ እና የአፍሪካን ህብረት አጀንዳ እንዳይሆን ብዙ ዉጤት አልባ ሙከራዎች አድርጋለች፡፡

የሶማልያ የቂም በቀል ጉዳይ አደብ ገዝቶ እርቀ ሰላም እንዲወርድ በሙሉ የሶማልያ ጎሳዋች የተሳተፉበት የ2007 እ.ኤ.አ በሞቃድሾ የተደረገዉ የሰላም ኮንፈረስ እዉቅና በመንፈግ የአስመራ ቡዱን ተብሎ የሚጠራ የፀረ-ኢትዩጵያ አቋም የሚያራምዱ የእስላማዊ ፍርድ ቤት ህብረት እዉቅና ሰጥታት ነበር፡፡ ከዚህ ባለፈ የኳታር መንግስት በኢትዩጵያ ዉስጣዊ ጉዳይ ከመግባትም አልቦዘነም፡፡ ፀረ-ኢትዩጵያ አቋም ያለዉ ራሱን “የኦጋዴን ነፃ አዉጭ ግንባር” ብሎ የሚጠራ አሸባሪ ቡዱን በኤርትራ በኩል ግንኝነት በመመስረት ኢትዩጵያ ላይ የእጅ አዙር ጦርነት ከፋታ ነበር፡፡

የአሸባሪዉ ”የኦጋዴን ነፃ አዉጭ ግንባር” ፕሮፓጋንዳ የአለም አቀፍ አጀንዳ እና እዉቅና እንዲሰጠዉ በማሰብ ኳታር በዋናነት የምታንቀሳቅሰዉ የአልጀዚራን ቴሌቪዥን በመሳሪያነት በመጠቀም ስፊ ሽፍን እንዲሰጠዉ በማድረግ ኢትዩጵያ ላይ የስም ማጥፋት ጦርነት ከፋታ ነበር፡፡

የአሜሪካ መንግስት የኳታር መንግስት ፀረ-ኢትዩጵያ አቋም እያወቀ ተፅእኖ ለማድረግ አለመሞከሩ ወይም አለመፈለጉ እንቆቅልሽ ነበር፡፡ ከኳታር መንግስት ቀረቤታ የነበራቸዉ አገራት እንደ ፈረንሳይ እና ጣልያን የኳታር የአፍሪካ ቀንድ አፋራሽ አካሄድ ለማስቆምም ፍላጎታቸዉ ከትንሽ ጥረቶች በስተቀር እምብዛም አልነበረም፡፡

የኳታር በተባበሩት መንግስታት የሶማልያ የመሳርያ ማዕቀብ ተቆጣጣሪ ኮሚቴ ሊቀ መንበር በነበረችበት ወቅት ባገኘችዉ አጋጣሚ የፀረ-ኢትዩጵያ ሃይሎች የጦር መሳርያ ማዕቀብ ሲጣስ እንደ ሊቀ መንበርነቷ አዎንታዊ ሚና ለመጫወት ፈቃደኛ አልነበረችም፡፡

ኳታር የተባበሩት መንግስታት ጊዝያዊ የፀጥታ ምክር ቤት አባል በነበረችበት ጊዜ የሶማልያ ጉዳይ በተነሳ ወቅት የኢትዩጵያ ሰራዊት ያለ ቅድመ ሁኔታ ከሶማልያ መዉጣት አለበት ብላ ሽንጧን ገትራ ስትከራከር የነበረች አገር ነች፡፡

ታድያ የምስራቅ እና አፍሪካ ቀንድ አገራት የሶማልያ ጉዳይ በዋናነት የሚመለከታቸዉ እያሉ እንዴት ተብሎ ነዉ ሶማልያ የአረብ ሊግ እና የኳታር አጀንዳ የምትሆነዉ? እዉነትም ቅዥት ነበር፡፡የኳታር መንግስት ከዚህ ቅዥት ነቅቶ ከኢትዪጵያ መንግስት አቋም መቀላቀሉ የሚያስመሰግነዉ ነዉ፡፡ የዘገየ ዉሳኔ ቢሆንም፡፡

ኢትዪጵያ ወዳጆች ያብዛላት! አሜን!

*******

* ጸሐፊው አቶ አብይ ጨልቀባ በአምቦ ዩኒቨርስቲ መምህር ናቸዉ፡፡ በኢሜይል አድራሻቸዉ [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

Abiy Chelkeba Worku is a blogger in this blog. He is a lecturer at collge of law and governance of Mekelle University and can be reached at [email protected]

more recommended stories