የኦባማ ቅልስልስ አስተዳደር ከኢራን ጋር ያደረገው ስምምነት የብዙ አረብ አገራትን ቀልብ የገፈፈ ነበር። በዚህም የተነሳ ረስተውት የቆዩትን ጦራቸውን ማጠናከር እና በጓደኛ ብዛት መፎካከሩን ተያይዘውታል።

ብዙዎቹ (ሚጢጢዎቹ) ሀገራት ሳይቀሩ ጦራቸውን አፍሪካ ላይ ማስፈር አሜሪካ አሜሪካ መጫወት ጀምረዋል። ለዚህ ደግሞ ዋናው የትርኢቱ መድረክ ለመካከለኛው ምስራቅ ስትራቴጂካዊ ትርጉም ያለው ምስራቅ አፍሪካ ነው።

ጅቡቲ

ከፈረንሳይ ነፃ ወጥታ የማታውቀው ጅቡቲ አሁን ጦር ያለውን አገር ሁሉ ታስተናግዳለች። አገሪቷ ዋና የኢኮኖሚ መሰረቷ ኢትዮጲያ የሆነች የተለየ የአይዲዮሎጂ ዝንባሌ የሌላት ሰላም ፈላጊ ጥገኛ ነች። በዚያ ላይ አሜሪካም ቻይናም ሁሉም አሉባትና የተለየ ስጋት አታጭርም።

ኤርትራ

ኤርትራ ያው ኤርትራ ነች። እሺ ካሏት ለእኛ ጥፋት የማትሆነው የለም። እዛ የሰፈረው የቃጣር እና ሳውዲ ጦር ለግዜው ዋና ትኩረቱ የመን ላይ ነው። አሜሪካን ከመጠበቅ እራሳቸው ወደ መደብደብ ያደጉት ሀገራት በአረብ ሆነ በምዕራብ ሀገራት አንድ ሰልፍ ሳይወጣባቸው የየመንን ህዝብ እየፈጁት ነው። ሲጨርሱ ኤርትራን ለቀው ወደ ቀጠናቸው ይመለሱልናል ወይስ እዚሁ ተወዝፈው ስራ ይሰጡናል የሚለውን በሂደት የምናየው ይሆናል።

ኢትዮጲያ ወደፊት ኤርትራ ላይ ልትወስደው በምትችለው ወታደራዊ እርምጃ ላይ እንቅፋት የመሆናቸው እድልም ቀላል አይደለም። 

ሱዳን

ሱዳን ላይ የሰፈረ ጦር አለ ከተባለ ያው የእኛው ነው። ወደ 6000 የሚሆኑ የኢትዮጵያ ወታደሮች በሱዳን በሰላም ማስከበር ላይ ይገኛሉ። ያው የሄዱት ጠበንጃና ወኔያቸውን ይዘው ነውና የግራ ጎናችንን በሚገባ ሸፍነውልናል።

ሱዳን ከግብፅ ጋር ያላት ግንኙነት ከእኛ ቢብስ እንጂ አይሻልም። የግብፅ በምስራቅ አፍሪካ እግር ማብዛት ጨርሶ ደብሯታል። እናም ግራ ጎናችን በዚህ ረገድ ሴፍ የሚባል ነው።

ነገር ግን ከግብፅ ጋር ያላት ፀብ ወደ ሳውዲ እየገፋት ይመስላል። ይህ የተጠናከረው ወዳጅነት የሳውዲን ጦር ወደ ማስፈር እንዳያመራ መስራት ያስፈልጋል። ካስፈለገ የወታደራዊ ስምምነት ልንፈራረምና ሱዳን ከግብፅ በሚመጣባት ነገር ብቻዋን እንደማትሆን ልናሳምናት ይገባል።

ሀገራቸው ላይ ጦር ማስፈር የማይወዱት ሱዳናውያን ያመኑት ጦራችንን እንዲተማመኑበት ማድረግ ጠቃሚ ይመስለኛል።

ደቡብ ሱዳን

ደቡብ ሱዳን አዲሷ ጆከር ነች። ትርምስምሷ የወጣው ሀገር የማንም መፈንጫ ለመሆን የምትመች ሆናለች። ለዚህም ነው ግብፅ እንደ ውሀ ቀጂ የምትመላለሰው። ይሄ ወጣ ገባ ሱዳንንም ኢትዮጲያንም ያሳሰበ ሆኗል። የኪር መንግስት አይዲዮሎጂካል ወይም የጠላትነት አጀንዳ የሌለው ስልጣኑን ለማስቀጠል ማንንም የሚያስተናግድ ጥቅም ተኮር ነው።

አያያዙ ካላማረ ኢትዮጲያ በጥቅሙ (ስልጣኑ) ልትመጣበት የምትችልባቸው ብዙ መንገዶች አሏት። ቀይ መስመሩ ከታለፈ ሀገሪቷን ወደለየለት ቀውስ መክተት እንደምንችል ለኪርም ለሚያሳስባቸው የቀጠናውና የአለም ሃገራት ግልፅ ማድረግ ይበጃል።

ሶማልያ

የሶማልያ መንግስት ህልውና የተመሰረተው ኢትዮጲያ ባሰፈረችው ጦር ላይ እንደሆነ በተደጋጋሚ ታይቷል። የሶማልያን መንግስት ለመጣል እንደው ከተፈለገ የኢትዮጵያን ጦር ከካምፑ እንዳይወጣ ማዘዝ ይበቃል። ይህ ማለት ኢትዮጵያ ሶማልያ ላይ ትልቅ leverage አላት ማለት ነው።

ለዚህ ነው አዲስ የተመሰረተው መንግስትም የኢትዮጵያ ወዳጅ ከመሆን ሌላ አማራጭ የማይኖረው። የቀደመው ፕሬዘዳንት ከግብፅ የቀረበለትን የጦር ማስፈር ጥያቄ ውድቅ ማድረጉ ለዛም በምርጫው የኢትዮጵያን ድጋፍ ማግኘቱ ይታወሳል። አዲሱ አሜሪካዊው የሶማልያ ፕሬዘዳንትም ከኢትዮጵያ ጋር ጋር ያለውን ወዳጅነት መጠበቅ ግድ ይለዋል። አለዚያ አልሸባብ ወደ ቡፋሎ (buffalo) ይመልሰዋል። ይህንን እንዳይረሳው ማስታወስ አይጎዳም።

ሶማሊላንድ

ሶማሊላንድ ሀገር አይደለችም። ከእኛ ውጪ ለኢኮኖሚያዊ ትዳር የሚያስባትም የለም። የሶማሊላንድ ገዢ ፓርቲ ግን ያን የዘነጋ ይመስላል የሶማሊላንድ ነፃነትን የምትቃወመዋን አረብ ኢሚሬት ጦር ለማስፈር ተስማምቷል።

ነገ አረብ ኢሚሬትስ ከሞቃዲሾ መንግስት ጋር ተዋውላ አልለቅም ብትል የሚያስለቅቅበት የህግ መሰረት የሌለው እውቅና አልባ መንግስት በሶማሊላንድ ነፃነት ላይ ትልቁን ቁማር ተጫውቷል። ጠበቆቻቸውን ሳያማክሩ በምርቃና የወሰኑት ይመስላል።

ምንአልባትም አይዟችሁ ያላቸው ሌላ ሀገር ይኖራል። ኢትዮጲያ ይህንን ስምምነት ለማሰረዝ ከበቂ በላይ አቅም አላት። ከሶማሊላንድ ጋር ያላትን የኢኮኖሚ ትብብር ለማቆም ማስጠንቀቂያ መስጠት ብቻውን የዛን መንግስት ምርቃና ይሰብራል። ካላደረግን ምክንያቱ እንቅልፍ ብቻ ነው ሊሆን የሚችለው።

ኬንያ

ኬንያ እናቷ – ካሰፈረችም የእኛን ስደተኞች ነው የምታሰፍረው። ከእሷ የሚመጣ ስጋት ኖሮም አያውቅም ወደፊትም እንደማይኖር መገመት ይቻላል።

ማጠቃለያ

ለግዜው ተከበናል ማለት ይከብዳል። በሁለቱ ጎረቤቶች (Eritrea & Somaliland) የአረብ ሀገራት ጦር ለመስፈር እድል ቢያገኝም በሁለቱ (Sudan & Somalia) ደግሞ የእኛ ጦር ሰፍሯል። የደቡብ ሱዳን ገና አልለየም። ቀሪዎቹ ሁለቱ (Djibouti & Kenya) ሴፍ ናቸው። 

በንፅፅር ግን እንግዳ ሀይሎች በቀጠናችን የሚያደርጉት እንቅስቃሴ ጨምሯል። በተለይ የግብፅ መቍነጥነጥ ትኩረት ሊሰጠው እና የውጭ ጉዳይ እርምጃዎቻችን ክስተቶችን የሚቀድሙ (preemptive) ሆነው መቃኘት ይኖርባቸዋል። ሰርፕራይዝ የሚያምረው ለቫለንታይን ብቻ ነው።

********

Fetsum Berhane is an Ethiopian resident, economist researcher and a blogger on HornAffairs.

more recommended stories