የሲቪል ሰርቪሱ የተሃድሶ መድረኮች የላቀ ሚና አላቸው!

የሲቪል ሰርቪሱ የተሃድሶ መድረኮች ለልማት መፋጠንና ለዴሞክራሲ መጎልበት የላቀ ሚና አላቸው!
በመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት የተዘጋጀ
ሳምንታዊ አቋም መግለጫ
ጥር 05 ቀን 2009 ዓ.ም

አገራችን ባለፉት 14 ዓመታት ላስመዘገበቻቸው አስተማማኝና ዘላቂ ሰላም ፣ ፈጣንና ቀጣይነት ያለው የኢኮኖሚ ዕድገት እንዲሁም የዴሞክራሲ ስርዓት ባህል ግንባታ መስፈን ሲቪል ሰርቪሱ የማይተካ ሚና አበርክቷል፤ እያበረከተም ይገኛል። ኢትዮጵያ በየዘርፉ እያስመዘገበቻቸው ካለችው  ስኬቶች መላው ህዝብ በየደረጃው ተጠቃሚ የሚሆንበት ስርዓት ተዘርግቷል፤ ሲቪል ሰርቫንቱም የዚህ ተጠቃሚ ነው። በቀጣይም እነዚህን ስኬቶች የበለጠ ለማጠናከርና የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት ወደ ተሻለ ደረጃ ለማሳደግ ሲቪል ሰርቫንቱ በተሰማራበት የስራ መስኮች ኃላፊነቱን  በአግባቡ ሊወጣ ይገባል።

መንግስት፣  የመልካም  አስተዳደር ችግሮችን ለመቅረፍ፣ ለህዝብ የገባውን ቃል ለመፈጸም እንዲያስችለው የተለያዩ  ተግባራትን በማከናወን ላይ  ላይ ይገኛል።  ከእነዚህ ተግባራት መካከል አንዱ ሰሞኑን በተለያዩ ክልሎችና ፌዴራል  ተቋማት የሚገኙ  ሲቪል ሰርቫንቶች የአገልግሎት አሰጣጥ ሂደታቸውን የሚገመግሙበት የተሃድሶ መድረኮች መዘጋጀታቸው ተጠቃሽ ነው። እነዚህ መድረኮች በአንድ በኩል ሲቪል ሰርቫንቱ  መንግስት የጀመረውን የጥልቅ ተሃድሶ ሂደት እንድያግዝና አሉ በሚላቸው አጠቃላይ የመንግስት ችግሮች ዙሪያ  ሃሳቡን በነጻነት በማውጣት፣  በሰፊ ተሳትፎ የተጀመረውን የመታደስ ጉዞ  የሚያጎለብቱ  ሃሳቦች እንዲያቀርብ እንዲሁም መግባባት እንዲፈጥር ያስችሉታል። በሌላ በኩል ሂደቱ  ሲቪል ሰርቪሱ ጠንካራና ደካማ ጎኖቹን  የሚለይበት፣ ሰራተኛው እርስ በርስ የሚማማርባቸው በመሆናቸው ጠቀሜታቸው የጎላ ነው።

መልካም አስተዳደርን ለማስፈን  መንግስት ከሚወስዳቸው አጠቃላይ እርምጃዎች በተጨማሪ ሲቪል ሰርቪሱ ለህዝብ  የሚሰጠውን አገልግሎት ማሻሻል  አንዱና ዋነኛው ተግባር ነው። የመንግሥትን ፖሊሲዎች፣ ፕሮግራሞች እና ዕቅድች የሚያስፈጽመውና የሚፈጽመው ሰቪል ሰርቫንቱ በመሆኑ፣ የአገልግሎት አሰጣጥን ለማሻሻል   የዚህን አካል ሙያዊ ብቃት በማሻሻል ላይ ብቻ ማተኮር የሚፈለገውን ለውጥ ማምጣት አይቻልም። በመሆኑም ሲቪል ሰርቫንቱ ህዝባዊ ሃላፊነቱን በተሻለ ብቃት እንዲወጣ  የተስተካከለ ልማታዊና ዴሞክራሲያዊ  አስተሳሰብ ሊያሲዘው በሚችል  ጥልቅ ተሃድሶ  ማለፍ ይኖርበታል።

ሲቪል ሰርቪሱ በጥልቅ ተሃድሶ ውስጥ ያልፋል ሲባል በተሰማራበት  ስራ ላይ  የመንግስትን ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች ጠንቅቆ አውቆ የተሰጠውን ህዝባዊ ሃላፊነት ለህዝብ ጥቅም ብቻ እንዲያውል ለማድረግ የሚያስችለው አመለካከት ባለቤት እንዲሆን መድረኮቹ ግንዛቤ ይፈጥሩለታል ማለት  ነው። የመንግስት አሰራር ግልጽነትና ተጠያቂነት የነገሰበት እንዲሆን ሕገ መንግስቱ ይደነግጋል።  በአሁኑ ወቅት በተለያዩ ተቋማት  እየተካሄዱ ያሉት  የተሃድሶ  መድረኮች  ሲቪል ሰርቫንቱ ህዝብን ለማገልገል የገባውን ቃል ለመፈጸም የሚያስችለውን አቅም የሚፈጥርባቸው ናቸው።

Photo - Ethiopia Federal Government Communication Office
Photo – Ethiopia Federal Government Communication Office

ከዚህ በተጨማሪም  የህዝብ አገልጋዩ አካል የሲቪል ሰርቪስ ማሻሻያ ሪፎርም ስራዎችን በመተግበር የተገልጋዩን ህብረተሰብ እርካታ ማረጋገጥ ይኖርበታል።  ስራን ቆጥሮ የመስጠትና መቀበል ባህል  በሲቪል ሰርቪሱ ውስጥ  ሊጎለብት ይገባል።  ይህ ሲሆንም ህብረተሰቡ ከመንግስት የሚፈልገው ቀልጣፋ የአገልግሎት አሰጣጥ ውጤታማ ይሆናል። ስለሆነም ሲቪል ሰርቫንቱ ለሕዝብና ለአገር ያለውን ወገንተኝነት ለማረጋገጥ  በተሰማራበት መስክ መስክ ስራውን በቅንነት፣ በታማኝነትና በቁርጠኝነት እንዲሁም የአገልጋይነት መንፈስን በመላበስ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን በዘላቂነት ለመቅረፍ መረባረብ ይኖርበታል።

የሲቪል ሰርቫንቱ ህዝባዊ መንፈስን መላበስ ለመንግስት አገልግሎት አሰጣጥ ወሳኝ ነው።  በመሆኑም ለአገራችን ዕድገት፣ ለህዝቦች አብሮነትና መቻቻል ጠንቅ የሆኑት የኪራይ ሰብሳቢነት፣ የትምክህት፣ የጥበትና የሃይማኖት አክራሪነትን የመሳሰሉ እኩይ ተግባሮችን  አጥብቆ ሊዋጋቸው ይገባል። ሲቪል ሰርቫንቱ ይህን ዓላማ በማንገብ ህዝባዊ ተልዕኮዎችን በታማኝነት  መወጣት ከቻለ፤  የመልካም አስተዳደር ችግሮች እልባት ያገኛሉ። የአገራችንም የዴሞክራሲ ስርዓት ይጎለብታል። የተጀመሩ የልማት ስራዎችም ይፋጠናሉ። ይህ ሲሆንም  ሲቪል ሰርቫንቱ በየደረጃው ተጠቃሚ ሆኖ ህይወቱም በዘላቂነት አብሮ ይቀየራል። በመሆኑም በመካሄድ ላይ ባሉት የተሃድሶ መድረኮች ሲቪል ሰርቫንቱ  በንቃት በመሳተፍ  ለመልካም አስተዳደር  መጎልበት የበኩሉን ሚና መወጣት ይኖርበታል።

***********

Content gathered and compiled from online and offline media by Hornaffairs staff based on relevance and interest to the Horn of Africa.

more recommended stories