ሕዝብ በእንጀራ ብቻ አይኖርም – በርዕዮተ ዓለም ጭምር እንጂ

አብዮታዊው ኢህአዴግ – ኢትዮጲያን በልል ፌዴራሊዝም (loose federalism) መንፈስ በተቀመረ ህገመንግስት አዲስ ስርአት የመሰረተ እና የመራ፤ ጠንካራ እና የጠራ ርዕዮተ ዓለም እና አባላት የነበረው፤ በዘረጋው ያልተማከለ የፌዴራል ስርአት የተነሳ አገር ሊበታትን እንደሆነ ይታማ የነበረ እና በብሄረተኞችና በግራ ዘመም የብዝኀነት (diversity) ኀይሎች የሚታመን ነበር፡፡

ድኅረ 97 ኢህአዴግ – በይደር ያቆያቸውን ህገመንግስታዊ ድንጋጌዎችን በቅድሚያ ሳይመልስ የመናገሻ ከተማ ፕላን ለማስፈፀም ታጥቆ ተነስቶ ጣጣ ውስጥ ሲገባ አይተናል፡፡ በፌዴራል ሀገር ውስጥ የኢኮኖሚ ሳይንስ ፅንሰ ሀሳብን ብቻ ታሳቢ ባደረገ ያልተመጣጠነ ትኩረት አዲስ አበባ ላይ የተከማቸ የሀብት አና የእድገት ጎዳና ሲከተል ታዝበናል፡፡ ጉድ አለና አገር አትልቀቅ ነው መቼም፡፡ ያለፉት አስር አመታት ኢህአዴግ እና ኢትዮጲያ በኢኮኖሚ እለት ተእለት እያደጉ በአብዮታዊነት እና የፖለቲካ መስመር ጥራት እለት ተእለት እየደከሙ የሄዱበት ነበር፡፡ ይህም ግንባሩ ሊታገለው የተነሳው እና የወደቀው የትምክህት አስተሳሰብ መልሶ እንዲያገግም በማድረጉ፤ ተራማጅነትን ገፍቶ አሁን በአንዳንድ ቦታዎች የታየው አይነት ወደ ኋላ የመመለስ ችግር እንዲፈጠር አስችሏል፡፡ በዚህ አመት በኦሮሚያ የታየው ነውጥም ቢሆን፤ ግንባሩ ቀድሞ ሁሉም ይተማመንበት የነበሩት ፌዴራላዊ አቋሞቹ ላይ እንኳን በሕዝብ ያለው መታመን እንደወረደ ያሳየ ነበር፡፡

ብዙዎች ደጋፊዎቹ እና አንዳንድ ተቃዋሚ ታዛቢዎች ጭምር ግንባሩ በሚልየን የሚቆጠሩ ጥቅም እና ዋስትና ፈላጊ አባላትን መሰብሰቡ አደጋ እንደሆነ ሲያስጠነቅቁ ኖረዋል፡፡ ግንባሩ የቅንጅት አባላትና አመራሮችን በጅምላ በመሰብሰቡ ራሱን ለወደፊት የርዕዮተ ዓለም ቀውስ እያመቻቸ እንደሆነ፤ አዳዲሶቹ አባላት የግንባሩን ግራ ዘመምነት የሚቀይሩ ብሎም ወደ መሀከለኛ እና ከፍተኛ አመራር በሚደርሱበት ግዜ የግንባሩን የብዝሀነት (diversity) አብዮት ስኬቶች የሚሸረሽሩ እንደሚሆኑ ብዙዎቻችንስጋታችንን  ከዩኒቨርሲቲ ጀምሮ ስንገልፅ ነበር፡፡

ሌሎች ደግሞ የርዕዮተ ዓለም ቀውሱ ስጋት ከአዲሶቹ ስብስቦች ብቻ ሳይሆን የመናገሻ ስልጣን የሚፈጥረው ተፈጥሮአዊ የጠቅላይነት(state dominance) ቀኝ ዘመምነት ጭምር እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡ ለዚህም ከአባላት ጥራት ባለፈ ክልሎችን ማጠናከር እና የክልል ፓርቲዎችን ከዲሞክራሲያዊ-ማአከላዊነት ነፃ ማድረግ እንደሚገባም ሲመክሩ ተሰምቷል፡፡

ይሁንና ስጋቶቹንም ምክሮቹንም አየር ወሰዳቸው፡፡ ለሌሎች አማራጭ የርዕዮተ ዓለም ሀይሎች ቦታ ለማሳጣት እና አውራ dominant ግንባር ለመመስረት ሲባል ግንባሩ የሁሉም አይነት ፖለቲካዊ አመለካከቶች መሰባሰቢያ ትልቅ ድንኳን እንዲሆን ተተወ፡፡ ዘፈኑ ሁሉ እድገት እድገት ብቻ ሆነና የግንባሩ ፖለቲካዊ ጤንነት (internal health) ጨርሶ ተዘነጋ፡፡ ግንባሩም በሂደት የአዛዥ ታዛዥ መድረክ እና ኢንቨስትመንት እና ኢንቨስተር ብቻ የሚያስጨንቃቸው ቢሮክራቶች መናኸሪያ ሆነ፡፡

ዛሬስ?

ከአስር አመታት የፖለቲካ መንሸራተት በኋላም የርዕዮተ ዓለም ወ ጥራቱ የተዳከመ ግንባር፣ በፋይናንስና በፖለቲካ አመራር አቅም ደካማ የሆኑ የክልል መንግስታት፣ እጅግ ጠንካራ የፌዴራል መንግስት እና ስርአቱን የመከላከል አቅማቸው አስተማማኝ ያልሆነ ተቋማት ያሉበት ሁኔታ ላይ ደርሰናል፡፡

አሁንም አልረፈደም፡፡ የግንባሩን የርዕዮተ ዓለም መስመር እና አመራር ለማጥራት ይቻላል፡፡ ደካማ አባላት እና አመራርን በጅምላ መሸኘት፤ የግንባሩን የርዕዮተ ዓለም መስመር በግልፅ በማቀመጥና በማስረጽ ሙሉ በሙሉ የሚያምኑበትን አባላት እና አመራር ብቻ ማስቀጠል፤ ትርጉም ያለው የሀገራዊ ተቋማትን እና የግንባሩን አባል ፓርቲዎች ድርጅታዊ ጤንነት ለማስጠበቅ የሚችሉ የውስጥ እና የውጭ የcheck & balance አሰራሮች ከልብ በመዘርጋት፤ የግንባሩ አባል ፓርቲዎች በሚመሯቸው ክልሎች ውስጥ ያለ ተቀናቃኝ እና ፉክክር የሚገዙበትን ሁኔታ ለመቀየር መጣር፤ ጤነኛ ሚዲያን የሚያበረታታ እና በሽተኞቹን የሚያከስም የሚድያ ምህዳር እንዲፈጠር መስራት፤ የግንባሩ አጋር ፓርቲዎችን ወደ ግንባሩ አካል በማካተት የሀገሪቱ እና የግንባሩን የመንፈስ ጉልበት (dynamism) ማደስ፤ ከዴሞክራሲያዊ-ማዕከላዊነት ተላቆ የሀሳብ ብዝሀነትን፣ ነፃነትንና የፓርቲ ዲሲፕሊንን ያጣጣመ አሰራር መቀየስ…ወዘተ ከምር ሊወሰዱ የሚገባቸው የተሀድሶ እርምጃዎች ይመስሉኛል፡፡

ይህ ከሆነ ግንባሩ አብዮታዊነቱን ሊመልስ፣ ራሱ ከቀየሰው ህገመንግስታዊ ስርዓት ጋር የገጠመውን ትግል ሊፈታ፣ እየተጫነው ካለው ወግ አጥባቂነት conservative stagnation /ተቸካይነት/ ተላቆ የግንባሩ ትግል ውጤት ከሆነውና እያደገ ከሚሄደው ብሄረተኝነት ጋር የማያቃርነውን የቀድሞ ተራማጅነት (progressivism) መልሶ ሊያገኝ ይችላል፡፡ በዚያውም አውራ ገዢ ፓርቲ ሆኖ ሊቀጥል ይችላል፡፡

ወይም ረፍዷል፡፡ ስለ ተሀድሶው እስካሁን የሰማነው ከላይ ለተጠቀሱት ችግሮች ትኩረት ያልተሰጠ ነው የሚመስለው፡፡ ተሀድሶው በመልካም አስተዳደር፣ ሙስና እና የስልጣን መባለግን በመሰሉ የበሽታው ምልክቶች ላይ እንጂ ምንጭ በሆነው የግንባሩ የርዕዮተ ዓለም መስመር ችግር ላይ ያተኮረ አይመስልም፡፡ በፌዴራል ስርአቱ አተገባበር ላይ ካሉ ህፀፆች በተለይ በህገመንግስቱ ፌዴራላዊ መንፈስ አረዳድ ላይ የሚታየውን መላላት ትኩረት ተነፍጎት በስራ ፈጠራ እና ሌሎች ኢኮኖሚያዊ ማስተካከያዎች ላይ የሚያጠነጥን ይመስላል፡፡ እንደ ኢኮኖሚስት የችግሮችን ምንጭ እና መፍትሄ የህዝቦች እና የግለሰቦች የኢኮኖሚ ሁኔታ እንደሆነ የማሰብ ዝንባሌ ቢኖረኝም ሰው/ህብረተሰብ በእንጀራ ብቻ እንደማይኖር እና የሚሄድበትን እና መድረሻውን ማወቅ የሚፈልግ (ርዕዮተ ዓለም ያለው) እንደሆነ እገነዘባለሁ፡፡

ሰው/ህብረተሰብ የሚኖርለት ግብ እና ሂደቱን የሚለካበት መለኪያዎች እንዳሉት የተረዳው ህገመንግስትም መድረሻችን የሆነውን  ራሳቸውን (በሚገባ) በቻሉ አባል መንግስታት የተዋቀረ የፌዴራል ሪፐብሊክ ንድፍ አስቀምጦልናል፡፡ ይህንን ንድፍ ይዞ ላደገው (በተለይ ለአዲሱ ትውልድ) ወጣት ከዚህ ንድፍ እየራቅን መሄድ እና ጥለነው ወደመጣነው አሀዳዊ ስርአት የማፈግፈግ ሁኔታ ተቀባይነት የሚኖረው አይሆንም፡፡ የትኛውም አይነት የኢኮኖሚ እድገት እና የኑሮ መሻሻል ይህንን የሀገራዊ እና የገዢው ፓርቲው የመስመር ጥራት መጥፋት የሚያስረሳ አይሆንም፡፡ ከድህነት መውጣት ትልቅ ሀገራዊ መድረሻ ግብ (vision) አይሆንም፤ ወደ መድረሻ ግባችን ለመድረስ ስንል የምናሳካው አንድ ግብ እንጂ፡፡ የኑሮ/ኢኮኖሚ መሻሻልን ብቻ እንደ ግብ የያዘ ህዝብ ህይወቱ አላማ/ትርጉም-አልባ በላተኛ (consumerist) የሆነና ቁርኝትም ሆነ ቁርጠኝነት የሚያንሰው ነው የሚሆነው፡፡ እንደዚህ አይነት ማህበረሰብ/ሀገር ደግሞ እንኳን ታላቅ ሊሆን ለቅርምት እና ግጭት ተጋላጭ የመሆን እድል አለው፡፡ ከኮሚኒዝኒም መውደቅ በኋላ ሩሲያ ያለችበትን ማህበረሰባዊ እና ሀገራዊ ድቀት ልብ ይሏል፡፡ እናም ለዚህም ነው ምን እይነት ሕዝቦች እና ሀገር መሆን እንደምንፈልግ የሚያሳይ ራዕይ፣ ለዚያም የምንጓዝበትን መንገድ የሚያሳይ አገራዊ ንድፍ (ህገመንግስት) እና የምንመራበት ርዕዮተ ዓለማዊ መስመር የግድ አስፈላጊ የሚሆነው፡፡

በተሀድሶው እና በጠቅላይ ሚኒስትሩ የተነሱት አገራዊ ሀገራዊ የፖለቲካ ምህዳሩን የማስፋት ሀሳቦች ለሀገሪቷ ጠቃሚ በመሆኑ አንድ የተሀድሶው መልካም ውጤት ሊሆን ይችላል፡፡ የምህዳሩ መስፋት በግንባሩ ላይ የፉክክር ጫናን የሚጨምር ብሎም ግንባሩ የርዕዮተ ዓለም መስመሩን እንዲያጠራ ተጨማሪ ግፊት የሚሆን ውጫዊ ሁኔታን የሚፈጥር ነው፡፡ በመሆኑም ግንባሩ በተሀድሶው ሂደት ለመስመር ጥራትን ቀጥተኛ ትኩረት ሳያሰጥ ቢቀር እንኳን ወደዚያ ተገዶ የሚመጣበት ሁኔታ የመኖር ተስፋ አለ፡፡ ያ ባይሆን እንኳን ኢትዮጲያውያን የርዕዮተ አለም አማራጭ እንዲኖራቸው እድል የሚፈጥር በመሆኑ የግንባሩ የመስመር ጥራት ሁላችንንም የማያሳሳብ የግንባሩ የራሱ ጉዳይ ያደርገዋልና መልካም የሚባል ነው፡፡

ከኢህአዴግ ጋር ከሁለቱ ወደ የትኛው አቅጣጫ እንሄዳለን የሚለውን የተሀድሶው ጥልቀት እና ትኩረት አይተን በሂደት የምንገምተው ካላረካን ደግሞ በጨረታው አንገደድም እና ከሌላ ተራማጅ ድርጅት ጋር የምንጓዝበት ይሆናል፡፡ ቸር እንሰንብት፡፡

*******

Fetsum Berhane is an Ethiopian resident, economist researcher and a blogger on HornAffairs.

more recommended stories