የኮንሶ ህዝብ ራስን በራስ የማስተዳደር ጥያቄ

የኮንሶ ጥናታዊ ጉዞየን እንድሰርዝ ያስገደድኝኝ ግጭት ምንነት ለማወቅ ያካባቢው ሰዎችን አነጋግሬ ያገኘሁት መረጃ ለማካፈልና አሳሳቢነቱን ስለማሳወቅ ስል ይህንን ፅፍያለሁ።ሁኔታው ካሁኑ ካልተገታ ወደ እማያባራ ግጭትና መተራረድ ሊያመራ ስለሚችል የክስተቱ አጣዳፊነት ለማስገንዘብ ስል ጭምርም ነው ይህንን የፃፍኩት።

የኮንሶ ህዝብ በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች ክልላዊ መንግስት ተደራጅቶ ያለ ብሔረሰብ ሲሆን ከ2004 መጋቢት ወር በፊት በልዩ ወረዳ መዋቅር ራሱን በራሱ በማስተዳደር ቆይቶአል፡፡ ከመጋቢት 2004 ጀምሮ ብሄረሰቡን ጨምሮ የቡርጂ፣ የአማሮ፣ የአሌ እንዲሁም የደራሼ ህዝቦችን በመጨመር የሰገን አከባቢ ዞን እንድመሰርቱ ተደርጎአል፡፡ በተዋቀረው ዞን ውስጥ የኮንሶ ብሄረሰብ በህዝብም ሆነ መልክዓ ምድሩ ስፋት ከሌሎች አንጻር አብላጫው ድርሻ ይወስዳል፡፡ የሰገን ዞን ምስረታ በባህሪው ራስ ገዝ አስተዳደር የሆኑ ልዩ ወረዳዎችን በማሰባሰብ የተፈጠረ ሲሆን ህዝቦች መክረውበት እና ፈቅደው የተዋሔዱበት ሳይሆን የክልሉ አመራሮች ባቀዱት መሠረት ብቻ እንደሆነ ይነገራል፡፡

Map - Konso, Ethiopia
Map – Konso, Ethiopia

በልዩ ሁኔታ የኮንሶ ህዝብ ቅር መሰኘቱንም በተለየዩ ስብሰባዎች እና አጋጣሚዎች ገልጾአል፡፡ በጋራ መግባባት ላይ የተመሰረተ አሰራርን ተከትሎ በህዝቦች በመፈቃቀድ ላይ ብቻ የተመሰረተ የፖለቲካ ማህበረሰብን መገንባት መርህን ያልተከተለ ስህተትም ተሰርቷል፡፡ በዞኑ ምስረታ ወቅትም በክልሉ አመራር የልዩ ወረዳ መዋቅር ፈርሶ በክልሉ የሚገኙ ልዩ ወረዳዎች ወደ ሚቀርባቸው ዞኖች እንደሚቀላቀሉም ቃል ተገብቶ ነበር ግን ሌሎች ልዩ ወረዳዎች ላይ ተመሳሳይ አሰራር የተከተለ አካሄድ የለም፡፡

መጋቢት 2004 ሰገን ዞን ሲቋቋም የዞኑ ማዕከል ላይም ቢሆን የህዝቦች ምክክር ሳይደረግ የክልሉ አመራር በሰሜን ምስራቃዊ አቅጣጫ በኮንሶ ብሔር ክልል ውስጥ ሰገን ከተማ በሚትባል ቦታ እንዲቀመጥ አድርገዋል፡፡ በሰኔ 2004 የኮንሶ ህዝብ ሳይወስንና ሳይፈቅድ የዞኑ አመራር ባሳለፈው ውሳኔ ከኮንሶ ህዝብ ሶስት ቀበሌያት ማለትም በቾ፣ አዲስ ገበሬ እንዲሁም ሰገን ከተማ ወደ ከተማ ክልል እንድገቡ ውሳኔ አስተላልፈዋል፡፡ ይህም ሉዓላዊ የኮንሶ ህዝብ ምክር ቤት ሳይወስን የተደረገ ስህተት ነው ማለት ነው።፡፡ ይህ በዚህ ሳይበቃ ከ2004 የዞኑ ምስረታ ጀምሮ የዞኑ ማዕከል ህጋዊ ድጋፍ እና ውሳኔ ከኮንሶ ምክር ቤት በኩል አለማግኘቱ እና እስከ አሁንም ድረስ ውሳኔ አለማግኘቱ ሌላው የዞኑና የክልሉ አመራር ህጋዊነት ያልተከተለ ስህተት ነው፡፡

የኮንሶ ህዝብ አብላጫ ከመሆኑ የተነሳ የማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ጥቅሞቼን ተነፍግያለሁ በማለት ጥያቄ እያነሳ ቢሆንም ምላሽ ሰጪ አካል በማጣት ከዞኑ ምስረታ ማግስት ጀምሮ ባለው መዋቅር ደስተኛ አይደለም፡፡ ለአብነትም ያህል:

➢ ፍትሀዊ የበጀት፣ የጤና፣ የትምህርት፣ የግብርና እንድሁም ማህበራዊ ጥቅሞች መጓደል

➢ ብሄርን መሰረት በማድረግ ጥቃቶችን ማድረስ (ከኮንሶ አርባምንጭ በሚወስደው መንገድ የዞን አመራር አርሶ አደርን ያለምንም ምክንያት መግደል እና ተመጣጣኝ ቅጣት አለመቀጣት)፣

➢ ከዞኑ መንግስት መስሪያቤቶች የኮንሶን ብሄር ተወላጅ ማግለል

➢ ነባር አርሶ አደሮችን ከጎረበት ህዝቦች ጋር ማጋጨት ከመረት ማፈናቀልና ከሰው ክልል ውጡ በማለት በህዝቦች መካከል ቅራኔ ማባባስ (በኮልሜ፣ በቡርጂ እና በኦሮሚያ ባሉ አዋሳኞች)::

የኮንሶ ህዝብ ራስን በራስ የማስተዳደር ጥያቄ በዋናነት የተነሳው ከዚህ በላይ በተጠቀሱ እና ሌሎች ችግሮች ምክንያት ቢሆንም በ2004 ህጋዊ ውሳኔ ያላገኘ የከተማ መዋቅር፣ በኮንሶ ወረዳ ውስጥ ያሉ ቀበሌያት ወደ ከተማ ያለ ህዝብ ፈቃድ መከለል፣ ህዝቡ ቀድሞ በልዩ ወረዳነት ራስ-ገዝ በሆነ መዋቅር መተዳደር የተለማመደው የተሻለ፣ አንጻራዊ ልማት፣ እና በህዝቡ ላይ የደረሱ በደሎች ተደማምረው ለጥያቄው መንስኤ ሆኗል፡፡

በሐምሌ 2007 የዞኑ አመራር በኩል የከተማ መዋቅር ቀድሞ ውሳኔ ያገኘ በማስመሰል ተግባራዊ ለማድረግ እንቅስቃሴ ማድረግ የአመራሩ የህግ ጥሰትን አጉልቶ በማውጣት ከፍተኛ የህዝብ ንቅናቄ ፈጥሯል፡፡ በመሆኑም:

➢ ተቃውሞው በሰፋፊ ህዝባዊ ሰልፎች በተለያዩ ጊዜያት ተደርጓል፡፡ በተለይም በአንድ ጊዜ ከ40000 ህዝብ በላይ እየተሰበሰበ ታላላቅ ትዕይንቶች ከአራት ጊዜ በላይ ተደርገዋል፡፡

➢ ለፈደራል እና ለክልል ፈደረሽን ምክር ቤቶች እንድሁም ለሚመለከታቸው አስተዳደር አካላት በተደጋጋሚ ጥያቄው ቀርቦአል፡፡ ተገቢ ምላሽም አልተገኘም፡፡ የፈደራሉ እና የክልሉ ህገመንግስትን መሰረት ያደረገ ምላሽ ባለመሰጠቱ ህዝቡ አልረካም ምላሹንም እየተጠባበቀ ይገኛል፡፡ በተለይም የክልሉ መንግስት ህጋዊ ምላሽ የመስጠት ሃላፊነት ያለበት በመሆኑ ህዝቡ በትዕግስት ይጠባበቃል፡፡

➢ ህዝቡ አላምንባቸውም ያላቸውን የተወካዮች ምክር ቤት (አንድ ሰው) እንድሁም የክልል ምክር ቤት ተወካይ (አንድ ሰው) ይውረድልኝ በማለት ከ50000 በላይ ፊርማ በህዳር ወር 2008 ዓ.ም በማሰባሰብ ለፈደራል እና ክልል ምርጫ ቦርድ ጽ/ቤቶች ገቢ አደርጎ እስካሁን አድርጎ ምላሽ አልተሰጠውም፡፡

➢ የኮንሶ ወረዳ ምክር ቤት በሙሉ ድምጽ የራስ በራስ የማስተዳደር እና በዞን የመዋቀርን ጥያቄ ማቅረብን እንድሁም ያለ ምክር ቤቱ እውቅና ከወረዳው ላይ የተቆረጡ ቀበሌያት ሙሉ በሙሉ እንድመለሱ፣ ህዝብ ያላመነባቸው አመራር አካላት ከህዝብ ሰልጣን እንድወርዱ ውሳኔ አስተላልፏል፡፡

ይህ ሂደት ፍጹም ሰላማዊ እና ህገ መንግስታዊ ስርዓትን ተከትሎ እየሄደ ያለ ቢሆንም አንዳንድ የዞን እና የክልል አመራር አካላት:

➢ ከህዳር ወር 2008 ጀምሮ የክልሉን ልዩ ሀይል ወደ ወረዳው በማሰማራት ድብደባ፣ ዘረፋ፣ እስራት እና የህዝብ ተቋማትን በመውረር ሰላማዊ አከባቢን ከማወክ በተጨማሪ ደበና በሚባል ቀበሌ ሁለት አርሶ አደሮችን በቀን 4/07/2008 በጥይት በመደብደብ ግድያ ፈጽመዋል፤

➢ ለሁሉም ወታደራዊ ጫና የኮንሶ ህዝብ የሰጠው ትዕግስት የተሞላበት አካሄድ እና ሰላማዊ ሂደትን የተከተለ በመሆኑ የክልሉ አመራር የበሰለ አመራር መስጠት አለመቻላቸው፤

➢ የህዝብ ጉዳይ እንድያስፈጽሙ የተመረጡትን 12 ግለሰቦች በማስፈራራት በህዳር ወር 2008 አርባ ምንጭ፣ በጊዶሌ ከወረዳቸው ውጪ በማሰር ማንገላታት፣ የተለያዩ የውሸት ወሬዎችን ማሰራጨት

➢ የኮንሶ ህዝብ ባህሉን አክብሮና ከመንግስት ጋር ላለፉት ጊዜያት በከፍተኛ ደረጃ በመግባባት ለልማት ጉልህ አስተዋጽኦ ያበረከተ ቢሆንም ለህዝቡ ጥያቄ ከተወከሉት ውስጥ ከባህል መሪዎች መካተታቸውን ለመከላከል ሲባል ብቻ ባህልን ማንቋሸሽ አልፎም ከ9ኙ የኮንሶ ጎሳ መሪዎች አንዱን በአርባ ምንጭ ማረሚያ ያለ ምክንያት ማሰርና መፍታት፣ የባህል ንብረቶችን ከጎሳ መሪ መግፈፍ ከፍተኛ ቁጣን ቀስቅሶአል፤

➢ የህዝቡን ጥያቄ የግንቦት ሰባት፣ የጥቂት ሽፍቶች፣ የሰማያዊ ፓርቲ፣ የኦነግ፣ የተቃዋሚ ፓርቲ በማለት የህዝብን ህሊና መጉዳት (በተጨባጭ በአከባቢ ኤፍ ኤም ሬዲዮ ማሰተላለፍ)፤

➢ የጥያቄው ህጋዊነት ላይ ታምኖ የፈደራል መንግስት ህዝቡ የወከላቸው 12 አባላት ከክልሉ መንግስት ጋር በመሆን የህዝቡ ጥያቄ በአግባቡ እንድፈታ አቅጣጫ የተቀመጠ ቢሆንም ክልሉ ጥያቄው እንድነሳ ፈጽሞ አለመፈለጉ ጉዳዩ እልባት እንዳያገኝ አድርጓል፤

➢ የህዝቡ ንቃተ ሂሊና እና የአላማ ጽናት ከዞኑ እና ከክልሉ አመራር በላይ በመሆኑ ለሚወሰዱ የሀይል እርምጃዎች ትዕግስት የተሞላበትና ሰላም የሰፈነበት ትግል ብቸኛና ትክክለኛ መስመር መከተል ህዝብን የሚያስመሰግን ነው፤

➢ ሕዝቡ የጠየቀውን ጥያቄ ምላሽ በጽሁፍ ከነምክንያት እንድገለጽለት የፈለገ ቢሆንም ምንም ዓይነት ምላሽ እስከ ሚያዝያ አጋማሽ ድረስ አለመሰጠት፤

➢ ከራስ በራስ የማስተዳደር ጥያቄ ጋር ብቻ በተያያዘ ከ250 በላይ ሰዎች ታስረው ያለምንም ምክንያት መለቀቅ በህዝቡ ዘንድ ቅራኔ ፈጥሯል፡፡ እስከ 17/8/2008 ድረስ አራት የኮንሶ ብሄር ተወላጆች ከወረዳው ውጪ በአጎራባች ወረዳ ከአራት ወራት በላይ እስራት ላይ ይገኛሉ::

የተጠየቀው ጥያቄ ህጋዊነቱን እና ህገመንግስታዊ አካሄዱን የጠበቀ እስከሆነ ድረስ ህጋዊ ምላሽ ከመስጠት ይልቅ ይህ ጥያቄ ለምን ተጠየቀ ተብሎ የሀይል እርምጃ መውሰድ ዘላቂና ተገቢ መፍትሄ ፈጽሞ አይሆንም፡፡ የኣካባቢው አመራሮች እየፈፀሙት ያለው ወንጀል ልክ የለዉም። በሰሞኑ ግርግርም ወደ ሶስት መንደር እሚሆኑ የሳር ጎጆዎች መቃጠላቸዉና ነብሳቸው ለማዳን ሲሉም በርከት ያሉ ኮንሶዎች ለመሰደድ መገደዳቸው ለመረዳት ችያለሁ።

ፌዴራላዊና ሕገ መንግስታዊ ስርዓቱን ወደላቀ ደረጃ ሊያደርሱ እሚችሉ ዴሞክራስያዊ የህዝቦች ተሳትፎ ተገቢ ምላሽ እንጂ ዱላና ጠብ-መንጃ አይገባቸዉም። የክልሉና የፌዴራል መንግስትም ሁኔታው እጅግ አሳሳቢ መሆኑ ተገንዝበው አፋጣኝ ምላሽ እንዲሰጡ እማፀናለሁ።

ግልባጭ

➢ ለ ክቡር አቶ ሃይለማርያም ደሳለኝ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስቴር
➢ ለ ኢፌዴሪ ፌዴሬሽን ምክር ቤት
➢ ለፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስቴር
➢ ለኢፌዴሪ ህዝብ ተወካዮች ምክርቤት
➢ ለደቡብ ክልል መንግስት
➢ ለሁሉም የግል እና የመንግስት ሚድያዎች

ከሰላምታ ጋር

***********

Avatar

Death for Neftegna ! Tegaru First and Forever !!!

more recommended stories