ሰማያዊ ሆይ – ለአኩራፊ ምሳው እራቱ ነው!

(አርአያ ጌታቸው
የአዲስ ዘመን ጋዜጣ ም/ዋና አዘጋጅ)

አንደ ተረት አለ፤ እንዲህ የሚል:-

በአንድ ወቅት በአንድ ስፍራ የሚኖር ቤተሰብ ነበር፡፡ በቤተሰቡ ውስጥ አንድ አባወራና ባለቤቱ ከሴት ልጃቸው ጋር ይኖሩ ነበር፡፡ ነገር ግን ሶስቱም መስማት የተሳናቸው ነበሩ፡፡ ከእለታት አንድ ቀን አመሻሽ ላይ አባወራው አህያውን ወደ ወንዝ ወስዶ ውሃ ሊያጠጣው ፈልጎ አህያውን እየነዳ ወደ ወንዝ ወረደ፡፡ ወንዙ አጠገብ እንደደረሰም ሌሎች ብዙ እረኞች ከብቶቻቸውን ውሃ ያጠጡ ነበር፡፡ እነእርሱም “ሰማህ አንተ ሰው? ከብቶቻችን እየጠጡ ነው፡፡ ያንተ ግን አህያ ስለሆነ ከብቶቻችን ቀድመው ይጠጡ፡፡” አሉት፡፡

መስማት የተሳነውም ሰው ‹‹ይቅርታ አህያዬ የሚሸጥ አይደለም›› አላቸው፡፡

እነርሱም ‹‹ሰውየው ምን ነካው?›› ብለው አሰቡ፡፡ እንዲህም አሉት «ያንተ አህያ ቢሸጥ ባይሸጥ ግድ የለንም፡፡ ከከብቶቻችን ቀድሞ እንዳይጠጣ ነው የምንፈልገው፡፡»

ሰውየውም ቀና ብሎ አይቷቸው «የምናገረውን አትሰሙም እንዴ? አህያዬ አይሸጥም አልኳችሁ እኮ፡፡» አላቸው፡፡

እረኞቹም «ሰውየው እብድ ነው?» ብለው አስበው ዝም አሉት፡፡

አህያውም ውሃውን ጠጥቶ ወደ ቤታቸው ተመለሱ፡፡

ሰውየው ወደቤት እንደደረሰም ወደ ኩሽና ሄዶ ሚስቱን እንዲህ አላት «ይገርምሻል! ዛሬ ነጋዴዎችን መንገድ ላይ አግኝቼ ‘አህያህን ካልሼጥክልን’ ብለው ሲያስቸግሩኝ የሚሸጥ አንዳልሆነ ነገርኳቸው››፡፡ ሚስቱም ቀና ብላ አይታው ምንም ሳትሰማው እንዲህ አለችው «እንግዲያውማ ልትፈታኝ ከወሰንክ አንድም ቀን ካንተ ጋር ማደር ስለማልፈልግ ወደ ቤተሰቦቼ እሄዳለሁ›› ብላ ትታውም ልትሄድ እቃዎቿን እየሰበሰበች እያለች ልጃቸው ወደ ቤት ገባች።

ሚስትየው ቀና ብላ አይታት «ይገርምሻል! ከእነዚያ ብዙ የትዳር አመታት በኋላ አባትሽ ሂጂልኝ አለኝ እኮ» አለቻት፡፡ ልጅቷም የሃፍረት ፈገግታ አሳይታ ቀና ብላ ‹‹እንግዲህ እናንተ ወላጆቼ ናችሁ፡፡ ልትድሩኝ ከፈለጋችሁ በሃሳባችሁ እስማማለሁ›› አለቻቸው ይባላል፡፡ /ስሙን ከዘነጋሁት ድረ ገፅ ያገኘሁት ተረት ነው/

አንዳንድ ነገሮችን ልብ ብለን ስናያቸው ልክ እንደተረቱ ይሆኑብናል። በተለይ ደግሞ የአገራችንን የተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲዎች የፖለቲካ አያያዝ ጊዜ ሰጥቶ ላስተዋለው የተረቱ ቤተሰብ ታሪክ ልኩ ሆኖ ያገኘዋል። እንዴት? ቢሉ፣ ብዙዎቹ መስማት በሚፈልጉት ላይ ብቻ ተጠምደው፤ ለእውነታው ብዙም ግድ የሌላቸው ሆነዋል ነው። Logo - Blue Semayawi party Ethiopia

ነገሬ ወዲህ ነው። የአገራችን ተቃዋሚ ፓርቲዎች በቅንፍ ውስጥ ሁሉንም ማለቴ አይደለም፤ ምንጊዜም መስማት የሚፈልጉት መስማት የሚፈልጉትንና እነሱ ዘንድ ያለውን ቢያንስ ለእነሱ እውነት ነው ያሉትን ጉዳይ ብቻ የሆነ ይመስለኛል። ፓርቲዎቹ «መንግስት ሁሉንም ነገር ጠቅልሎ ይዞ እኛን ከጨዋታ ውጭ እያደረገን ነው። የመንግስት መገናኛ ብዙኃንን መጠቀም አልቻልንም። አምስት አመት ጠብቀን የምናገኛት የጋዜጣ አምድና የአየር ሰዓትም ብትሆን ሳንሱር የበዛበት ስለሆነ ህዝቡን በትክክል ማግኘት አልቻልንም፤ ኢህአዴግ በዋና ዋና አገራዊ ጉዳዮች ላይ አሳትፋችኋላሁ የሚለውም ህልም ነው…» የሚል ክስ ሲያቀርቡ መስማት ብዙም እንግዳ ነገር አይደለም።

ቁምነገሩም ያለውም እዚህ ላይ ነው። ይሄ ክስ በትክክልም ልክ እንደ ተረቱ ሁሉ እነሱ መስማት የሚፈልጉት የእነሱ ሀቅ ነው። መሬት ላይ ያለው እውነታ ግን አሁንም እንደተረቱ ሌላ ነው። እስኪ ጉዳዩን አንድ በአንድ ባለቤት እየሰጠን እንመልከተው። ለዛሬ ጉዳዬን ሰማያዊ ፓርቲ ላይ ማድረግ እፈልጋለሁ።

የተነሳሁበትን ነገር ለማስረዳት ብዙም እሩቅ መሄድ አላስፈለገኝም። በቅርብ ጊዜ ሁነቶች ላይ ብቻ አተኩራለሁ።

አሁንለታ ኦባማ የመጡ ሰሞን መንግስት ለፕሬዝዳንቱ የክብር የእራት ግብዣ አድርጎላቸው የተከበረ ምሽት ማሳለፋቸውን እናስታውሳለን። ታዲያ መንግስት በእዚህ የእራት ግብዣ ላይ ሊገኙ የሚገባቸውን ሰዎች በውል ለይቶ ሲያበቃ በእርግጥም የክብር እንግዶች ናቸው ላላቸው ኢትዮጵያዊያን ጥሪ አድርጓል። ከእነዚህ ጥሪ ከተደረገላቸቸውና መንግስትም ክብር ይገባቸዋል ካለቸው አካላት መካከል የሰማያዊው ፓርቲ ሊቀመንበር ኢንጅነነር ይልቃል አንዱ ነበሩ።

እርሳቸው ግን የአገሪቷን የክብር ግብዣ ሳያከብሩ፣ እንደ ተረቱም የእራሳቸውን ብቻ የሚሰሙ ናቸውና በእራት ግብዣው ላይ ሳይገኙ ቀርተዋል። ምነው ሲባሉም የኢትዮጵያ ህዝብ ጠግቦ ሳያድር የእኔ የእራት ግብዣ ይቅርብኝ ሲሉ በፌስቡክና መሰል ድረ ገፆች ላይ ነገሱ። እርግጠኛ ሆኖ መናገር የሚቻለው ኢንጀነሩ ለእራት ግብዣው ባይጠሩ ኖሮ ሊሉት የሚችለው ይሄንን አይሆንም ነበር። እናውቃቸዋለንና!

ኢንጀነሩ መስማት የሚፈልጉት ጥሪ እርሳቸው መስማት የሚፈልጉትን አይነት ብቻ ስለሆነባቸው እንጂ የተጋበዙት እኮ ነጋ ጠባ፣ ከአመት አመትም የኢትዮጵያን መንግስት ያማልዷቸው ዘንድ ደጅ ለሚጠኑባት ታላቅ አገር መሪ የተዘጋጀ የክብር ግብዣ ነበር። እንደአለመታደል ግን ሊቀመንበሩ አጠገባቸው አስተዋይ አማካሪ የላቸውም ወይንም አማካሪዎቻቸውም እንደ እርሳቸው መስማት የሚፈልጉትን ብቻ የሚሰሙና የሚመክሩ ስለሆኑ ታላቁን ጥሪ ሳይጠቀሙበት ቀርተዋል። ይሄ በሳል ፖለቲከኛ ነኝ ከሚል የሚጠበቅ ተግባር አይደለም። ፖለቲካ ማግኘት የሚፈልጉትን ለማግኘት ማድረግ የሚፈልጉትን ብቻ ሳይሆን ማድረግ የማይፈልጉትን ሁሉ የሚያደርጉበት የብልሆች ጨዋታ ነው።

ሌላም አለ። የመንግስት መገናኛ ብዙኃንን መጠቀም አልቻልንም፤ ያለንን ሃሳብም ለህዝቡ ማድረስ አልቻልንም የሚል ወቀሳ። ይሄንን ወቀሳ ከሚሰነዝሩ ፓርቲዎች መካከል ህጻኑ ሰማያዊን ፓርቲ፣ በቅንፍ ውስጥ የምስረታ እድሜውን ብቻ አስልቼ ህጻን ማለቴን ይረዱልኝ፤ የሚያክል የለም። እውነታው ግን ፓርቲው የሚለው አይደለም። ፓርቲውና አመራሮቹ የሚናገሩት እነሱ መስማት የሚፈልጉትን አይነት ብቻ ስለሆነ ለእውነታው ጆሯቸው ዝግ ነው።

የመንግስት መገናኛ ብዙኃን በተለያዩ አገራዊ ጉዳዮች ላይ የተፎካካሪ ፓርቲዎችን ሀሳብ ማስተናገድ ዋነኛው የስራቸው አካል ነው። በዚህም አንድ ወቅታዊ ጉዳይ በተከሰተ ወይንም በአንድ ትልቅ አገራዊ ጉዳይ ላይ ፓርቲዎች አቋማቸውን ለህዝቡ መግለጽ አለባቸው ተብሎ በታመነ ጊዜ የመጀመሪያ ጥሪ የሚያደርጉት ለተቃዋሚ ፓርቲዎች ነው ብል ለመሳሳቴ ማስረጃ ማቅረብ የሚችል አይኖርም። ምክንያቱም ምንም እንኳን ይሄ ፅሁፍ የግል አስተያየቴ ቢሆንም የጋዜጣው አዘጋጅ ነኝና ጉዳዩን በትክክል አውቀዋለሁ።

በግሌ ከእያንዳንዱ ፓርቲ ጀርባ ይብዛም ይነስም ህዝብ አለ የሚል እምነት አለኝ። ያ ህዝብ ደግሞ ግብር ከፋይ የአገሪቷ ዜጋ ነው። ስለሆነም ግብር ከፋዩ በ[አዲስ ዘመን] ጋዜጣ ላይ የመናገር የመጻፍ መብት አለው። በሌላ አነጋገር ጋዜጣው የሁሉም ወገን ነው ማለት ነው። እኔና ባልደረቦቼም ይሄንን የማክበርና የማስከበር ግዴታ አለብን። ይሄንን ግዴታችን ለመወጣትም ሁሌም ወደ ተቃዋሚ ፓርቲዎች መረጃ ፍለጋ እንደውላለን። በእዚህ ወቅት ጥያቄያችንን በአግባቡ ተቀብለው ያመኑበትንና የፓርቲያችን አቋም ነው ያሉትን የሚነግሩን ፓርቲዎች በርካታ ናቸው። ከእዚህ አንጻር መድረክ፣ አንድነት፣ ቅንጅት፣ ኢራፓ፣ ኢፍዴኃግ፣ መኢብን፣ ኢዴፓና ሌሎች ተመስጋኝ ፓርቲዎች መሆናቸውን መጥቀስ እወዳለሁ።

በተቃራኒው መረጃ በጠየቅን ቁጥር ከአፋቸው ስድብ የሚቀድም ፓርቲንና መንግስትን ለይተው ያልተረዱ፣ የተከበረውን የጋዜጠኝነት ሙያ ከፕሮፓጋንዳ ነጥለው ማየት የማይችሉ ፓርቲዎች አሉ። የእዚህ አይነት ችግር ካለባቸው ፓርቲዎች መካከል ሰማያዊን የሚወዳደር የለም። ሰማያዊ በተለይ ሊቀመንበሩ ከእሳቸው እውነታ ውጭ ምንም አይነት ሌላ እውነት የለም ብለው የሚያምኑ እያንዳንዷ የምናቀርባት ጥያቄም ኢህአዴግ የላካት አድርገው የሚመለከቱ የተረቱን አይነት ችግር ያላባቸው ሰው ናቸው። እደግመዋለሁ ይሄ የግል አስተያየቴ ነው።

በቅርቡ የትግራይ ህዘቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄን /ዴምህት/ ወደ አገር መመለስ በተመለከተ ምን አስተያየት አለዎት? ተብለው ሲጠየቁ፤ ወዲያውም የመንግስት መገናኛ ብዙኃንን እንዲጠቀሙ ሲጋበዙ የሰጡት ምላሽ አሳዛኝ ነበር። የኢትዮጵያ ችግር ይሄ አይደለም… በማለት እዚህ ላይ ልፅፋቸው የማልችላቸውን ንግግሮች ሁሉ መልስ ነው በማለት ሰጥተውናል። «አጭበርባሪዎች» ሲሉም እንደመረቁልን አልረሳውም።

እነሆ ዛሬ ደግሞ ሌላ ነገር ከኢንጅነሩ ሰማሁ። መንግስት ሁሉን ነገር ጠቅልሎ ይዟል፤ በአገራዊ ጉዳይ አወያያለሁ የሚለውም ህልም ነው የሚል ፓርቲ በአሁኑ ወቅት የአገሪቷ ቁጥር አንድ አጀንዳ በሆነው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅዱ ላይ እንዲወያዩ የተደረገላቸውነ ጥሪ ውድቅ አድርገውታል። ለመሆኑ የግለሰቡም ሆነ የፓርቲው አልፋና ኦሜጋ ፍላጎት ስልጣን ብቻ ነው እንዴ? ስልጣንም ለመያዝ እኮ መጀመሪያ በተመሳሳይ መድረኮች መገኘትና ብቃትንና አማራጭን ማሳየት የግድ ይላል። ስልጣን እኮ ጸበል ፀዲቅ አይደለም። ለመሆኑ ህዝቡስ ምንና የቱን አማራጭ አይቶ ውክልናውን ይሰጣችሁ ዘንድ ተፈልጋላችሁ?

እንደ ፓርቲ ቆፍጠን ብላችሁ እቅዱንም ብትንትን አድርጋችሁ ገምግማችሁ ስታበቁ ኢህአዴግን በመድረክ ፊት ለፊት ገጥማችሁ ብቃታችሁን ማሳየት ከእናንተ የሚጠበቅ ተግባር ነበር። እናንተ ግን እንደተረቱ አይነት አዙሪት ውስጥ ገብታችሁ «ኑ እራት ተጋበዙ» ስትባሉ፣ ምርጫው ተጭበርብሯል። በአንድ ጉደይ ላይ አስተያየታችሁ ምንድነው? ስትባሉ መገናኛ ብዙኃንን መጠቀም አልቻልንም። ኑ በእቅዱ ላይ ተወያዩ ስትባሉም ለመሰረታዊ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ቅድሚያ ተሰጥቶ ውይይት ይደረግ ስትሉ መልሰ ትሰጣላችሁ። እንደ በሳል ፖለቲከኛና ፓርቲ ከእናንተ መስማት እፈልግ የነበረው እቅዱ ላይ ለመወያየት መጋበዛችን ጥሩ ነው። ነገር ገን ከእቅዱ ስፋት አንጻር የተሰጠን ጊዜ አጭር ነውና ቀኑ ይራዘምልን፤ ወይንም በተለመደው አሉታዊ አባባል ኢህአዴግ እቅዱን በደንብ እንዳንመለከተው ስለፈለገ በአጭር ቀን ውስጠ ኑ ተወያዩ ማለቱ ተገቢ አይደለም የሚል ነበር። ይሄ ግን አልሆነም። ለምን ቢሉ «የሞኝ ዘፈን ሁልጊዜ አበባየ ሆይ» ነው መልሱ።

ይሄ የኩርፊያ ጉዞ የትም አያደርስም። ለአኩራፊ ምሳው እራቱ ነው የሚለውን ብሂልም ልብ ይሏል። ስለሆነም ሰማያዊያን ሆይ ይሄንን የተሰጣችሁን እድል ተጠቀሙበትና አማራጮቻችሁን በትክክለኛው ሜዳ ለትክክለኛው ዳኛ አሳዩ። አገራችን የጋራ ናት፤ የጋራ በሆነችው አገራችን ደግሞ የጋራ የሆነ ነገር ሊኖረን የግድ ነው። አንዱ የጋራ የሚያደርገን ደግሞ የዚህ አይነቱ የልማት እቅድ ነውና በዚህ ላይ ፊትን ማዞር የእናትን ጡት መንከስ ይሆናል። ለመሆኑ ምርጫውን አሸንፋችሁ ስልጣኑን ይዛችሁ ቢሆን ኖሮስ ኢህአዴግን ለተመሳሳይ ውይይት አትጋበዙትም ነበር ማለት ነው? አበቃሁ!

**********

Areaya Getachew (MA) is a public relations expert at a foreign embassy. He studied second degree at Addis Ababa University and was deputy editor in-chief of Addis Zemen newspaper.

more recommended stories