የኢህአዴግ አባል ድርጅቶች መደበኛ ጉባኤያቸውን ዛሬም ቀጥለው አካሂደዋል

(በዛይድ ተስፋዬ፣ ዳዊት መስፍን፣ ጥላሁን ካሳ እና መቆያ ሃይለማርያም)

የኢህአዴግ አባል ድርጅቶች መደበኛ ጉባኤ ዛሬም ቀጥሎ በመካሄድ ላይ ይገኛል። 

የህዝባዊ ወያኔ ሃርነት ትግራይ /ህወሓት/ 12ኛ ድርጅታዊ ጉባኤ ዛሬም ቀጥሎ ተካሂዷል።

የጉባኤው  ተሳታፊዎች  በክልሉ  ባለፉት ዓመታት በግብርና ፣በትምህርትና ጤና ለተመዘገቡ ውጤቶችና ስኬቶች እውቅና ሰጥተዋል።

የጉባኤው ተሳታፊዎች በማእከላዊ ኮሚቴው ሪፖርት ላይ ግልፅ ባልሆኑና ተጨማሪ ማብራሪያ በሚያስፈልጋቸው ጉዳዮች በርካታ ጥያቄ አንስተው ተዋይተውበታል።Photo - SEPDM Congress, Hawassa, Ethiopia

የጉባኤው ተሳታፊዎች ሪፖርቱ ላይ በድክመት የተነሱ ጉዳዮችን ትኩረት በመስጠት ሰፊ ውይይት እያካሄደ መሆኑን የገለፁት የጉባኤው ቃል አቀባይ አቶ አባይ ፀሀዬ የተነሱ ጉዳዮችን በዝርዝር ለማየት በሪፖርቱ የሚደረገው ውይይት እስከ ነገ እንደሚቀጥል ተናግረዋል።

የህወሓት 12ኛ ድርጅታዊ ጉባኤ የድርጅቱ ህገ ደንብ በሚፈቅደውና ዴሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ ዝግጅት ተደርጎበት እየተካሄደ ያለ ጉባኤ መሆኑን አዘጋጅ ኮሚቴ በማረጋገጥ የተጀመረ መሆኑን አቶ አባይ ፀሀዬ ገልፀዋል።

በጉባኤው ከአንድ ሺህ 500 የሚበልጡ በድምፅና ያለድምፅ የሚሳተፉ አባላት በመሳተፍ ላይ መሆናቸውን ተናግረዋል።

የብሄረ አማራ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ /ብአዴን/ የድርጅቱ 11ኛ ጠቅላላ ጉባኤ በዛሬው ውሎው በውስጠ ድርጅት ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና መልካም አስተዳደር ዘርፎች አፈጻጸም ላይ ተወያይቷል።

የጠቅላላ ጉባኤው የፕሪዚዲየም አባል አቶ ብናልፍ አንዱአለም፤ ጉባኤው በክልሉ የታየውን የኢኮኖሚ እድገት በእቅድ ደረጃ ከተቀመጠው ጋር ተቀራራቢ ሆኖ እንደተፈጸመ መገምገሙን ተናግረዋል።

በግብርናና ገጠር ልማት በ10ኛው ድርጅታዊ ጉባኤ ላይ የተላለፉ ውሳኔዎች በስኬት መፈጸማቸውን ያነሱት አቶ ብናልፍ፤ መልካም አስተዳደርን ከማስፈን አንጻር ግን ህዝቡ በሚፈልገው ደረጃ ምላሽ መስጠት እንዳልተቻለ መገምገሙንም ነው የተናገሩት።

ባለፉት አምስት አመታት በገጠርና በከተማ ለ2 ሚሊየን ዜጎች የስራ እድል ቢፈጠርም፤ በክልሉ ካለው የስራ አጥ ቁጥር አንጻር በቂ አይደለም ተብሎም ነው የተገመገመው።

በክልሉ ባለሁለት አሃዝ የኢኮኖሚ እድገት ማስመዘገብ የተቻለ ሲሆን፤ በክልል ደረጃ የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ መቻሉ ለተመዘገበው የግብርና እድገት ማሳያ ነው ተብሎ በጉባኤው ተገምግሟል።

ጉባኤው በነገው እለት የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት ምርጫ በማካሄድ እና ውሳኔዎችን በማስተላለፍ ይጠናቀቃል ተብሎ ይጠበቃል።

የኦሮሞ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት /ኦህዴድ/ በተያያዘ የኦሮሞ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት /ኦህዴድ/ ያለፉትን 7ኛ ዙር ጉባኤ ውሳኔዎች፣ የ1ኛው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ አፈፃም እና ክፍተቶች እንዲሁም በሁለተኛው ዙር እቅድ ዘመን የሚተገበሩ ዋና ዋና አቅጣጫዎች ላይ ተወያይቷል።

የጉባኤው ተሳታፊዎች በቡድን ሆነው በተናጠል ባደረጉት ውይይት፤ የ7ኛው ዙር ውሳኔዎች በህብረተሰቡ ላይ ለውጥ ያስመዘገቡ፣ የጋራ ተጠቃሚነትን ያረጋገጡ እና በየደረጃው ያሉ ምክር ቤቶችን አቅም ያጠናከሩ መሆናቸውን በጋራ መድረኩ አንስተዋል።

1ኛው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ዘመን በሁሉም የልማት ዘርፎች ለውጥ የታየበት እንደነበርም ነው ያነሱት፤ የትምህርት፣ የጤናና የመንገድ ተደራሽነት የተመዘገቡ ለውጦችን በመጥቀስ።

ዝናብ አጠር በሆኑ አካባቢዎች የተጀመረው የመስኖ ልማት ተጠናክሮ እንዲቀጥል፣ የገበያ ስርአቱን ፈር ማስያዝ፣ በከተሞች ከመሬት አስተዳደር ጋር ያለውን ብልሹ አሰራር ማስተካከልና በአገልግሎት አሰጣጡ ላይ ያሉ ክፍተቶች መስተካከል ይገባቸዋል ሲሉም ነው የተናገሩት።

የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሙክታር ከድር፤ በመጀመሪያው የእቅድ ዘመን ለተመዘገበው ሃገራዊ እድገት የክልሉ አስተዋጽኦ ከፍተኛ እንደነበር ጠቅሰው፤ ልማቱ ፍትሃዊና የህዝቡን ተጠቃሚነት ያረጋገጠ መሆኑን ገልጸዋል።

በቀጣይ በግብርናው ዘርፍ በትኩረት ይሰራል ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ በዘርፉ የታሰበውን ያክል ምርት ማምረት እንዳልተቻለ አንስተው በቀጣይ የውጭ ምንዛሬን የሚያስገኙ ምርቶችን በስፋት ማምረት ይገባልም ነው ያሉት።

በኢንዱስትሪና በመልካም አስተዳደር ላይ ስር ነቀል ለውጥ ለማምጣት የሚደረገው ርብርብ ከቀጣይ የድርጅቱ የትኩረት አቅጣጫዎች መካከል ዋነኛው ነው ብለዋል።

የደቡብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ /ደኢህዴን/ በሌላ በኩል የደቡብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ድርጅት /ደኢህዴን/ እያካሄደ ባለው ጉባኤ፤ ያለፈውን አምስት ዓመት የእድገት እና ትራንስፎርሜሽን እቅድ የገመገመ ሲሆን፥ በግብርና በተለይም ዜጎች በምግብ እህል ራሳችውን እንዲችሉ ማስቻል ላይ አበረታች ውጤት መመዝገቡን አንስቷል።

በእቅድ ዘመኑ ዋነኛ የእድገት ምንጭ ሆኖ የተቀመጠው የግብርናውን ዘርፍ በማስፋት ስትራቴጅ አማካኝነት ከፍተኛ ዋጋ የሚያስገኙ ምርቶችን በማምረት በክልሉ ዘርፉ የ9 ነጥብ 4 በመቶ አመታዊ አማካይ እድገት እንዲያስመዘግብ ጥረት ሲደረግ ቆይቷል።

በዚህም መሰረት በ2002 ዓ.ም 23 ነጥብ 27 ሚሊየን ኩንታል የነበረው የሰብል ምርት በ2007 ዓ.ም 34 ነጥብ 3 ሚሊየን ኩንታል ደርሷል፤ በክልሉ በስፋት በአርሶ አደሩ የሚመረቱት የእንሰትና ስራስር ሰብሎች አመታዊ ምርትም ከ35 ወደ 74 ነጥብ 2 ሚሊየን ኩንታል ከፍ ብሏል።

የግብርናው ዘርፍ በክልሉ የ8 ነጥብ 7 በመቶ ዕድገት ያሳየ ሲሆን፥ በአርሶ አደሮች መካከል ያለው የምርታማነት ልዩነት ለማጥበብ ተጨማሪ ስራዎች እንዲሰሩ ጉባኤው አቅጣጫ አስቀምጧል።

የኢንዱስትሪ ዘርፍን የገመገመው ጉባኤው፥ በጥቃቅንና አነስተኛ ኢንዱስትሪ ዘርፍ አማካኝነት 1 ነጥብ 06 ሚሊየን ለሚሆኑ የክልሉ ነዋሪዎች የስራ እድል የተፈጠሩ ሲሆን፤ የስራ እድሎቹ ቋሚና ዘላቂ እንዲሆኑ በማድረግ በከተማ ግብርና የተሰማሩ ወጣቶች በአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፍ እንዲሰማሩ በመደገፍ የማምረቻ ኢንዱስትሪው በቀጣይ እንዲጠናከር አቅጣጫ አስቀምጧል።

*********

Source: Fanabc, Aug. 24, 2015

Content gathered and compiled from online and offline media by Hornaffairs staff based on relevance and interest to the Horn of Africa.

more recommended stories