የምርጫ ክርክር – ካለፈው በመማር ሊታረም የሚገባው

ነብሱን ይማረውና ነውጠኛው ቅንጅት በ1997ዓ.ም የማይናቅ የህዝብ ድምጽና ድጋፍ ያገኘው ከኢህአዴግ የተሻለ ብቃት ስለነበረው ወይም ያቀረበው የፖሊሲ አማራጭ ሳቢ ስለነበረ እንዳልሆነ ሁላችንም እናውቀዋለን፡፡ ወይም የህዝባችን ኑሮ ሊቀይር የሚችል የመነጠቀ ሐሳብ በማቅረብ አልነበረም፡፡ ጅብ በቀደደው ውሻ ይገባል እንደሚባለው የኢህአዴግ ንዝህላልነትና ቸልነትነት እንጂ! ይህን ያልኩት ያለምክንያት አይደለም፡፡

ኢህአዴግ ከቅንጅት ቡድን ጋር ለክርክር ሲቀርብ ማሰብ እና ማድረግ የነበረበት ብዙ ስትራተጂዎች ነበሩ፡፡ እንደምናስታውሰው ቅንጅቶች በነበረባቸው የብልጣ ብልጥነት (ተራ የአራዳነት) ስብእና በከፍተኛና በሚያስገርም ጥበብ የኢሀአዴግን ደካማ ጎን ተጠቅመውበታል፡፡ የኢህአዴግ ቸልተኝነት፣ በክርክር ታክቲክ በልጦ አለመገኘት እንዲሁም እዚህም እዛም ይታዩ የነበሩ የመልካም አስተዳደር እጦት ፣ የአፈጻጸም ግድፈቶች እና የልማት እጥረቶችን በሚሊዮን ግዜ በማጋነን ፣ ልብ የሚነኩ ቃላቶች በመደርደር የተወሰነ ህብረተሰብን በማሳመን ረገድ ቅንጅቶች ከፍተኛ ብልጫ አሳይተዋል፡፡ በኔ ግምት ይህን ሊያደርጉ የቻሉበት ዋናው ምክንያት 1ኛ የኢህአዴግ ጠንከር ላለ ፖለቲካዊ ክርክር በቂ ዝግጅት አለማድረግ እና የሰራውን ስራ በሚማርክ ቃለት እና በሚመጥን መልኩ መግለጽ አለመቻሉም ጭምር ነው፡፡ 2ኛ ደግሞ መቶ በመቶ በሚያስብል መልኩ አጀንዳው በኢህአዴግ የፖለቲካ መስመር ፣ ርእዮት ዓለምና ኢህአዴግ በሚመራው የመንግስት የፖሊሲ አፈጻጸም ዙርያ መሆኑ ነው፡፡

ታድያ ብልጣ ብልጦች የቅንጅት ተከራካሪዎች እነሱ ገምጋሚዎች ኢህአዴግዬ ደግሞ ተገምጋሚ ሆና መቅረብዋ ምን ያህል ለነሱ አመቺ ሜዳ እንደነበረ ማንም ሰው ሊስተው አይችልም፡፡ ቅንጅቶች ይህን ክፍተት በመጠቀም ኢህአዴግ የሰራውንና ያልሰራውን ስራ አፈር ድሜ አበሉት፡፡ ኢህአዴግ በትምህረት ፣ በልማት ፣ በጤና ፣ በድህነት ቅነሳ ፣ ጸጠታ በማስፈን ረገድ ፣ በተለይም የብሄር ፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ጥያቄ መልስ መስጠቱ ፣ በአጠቃላይ ሀገሪትዋ ወደ ተሻለ ደረጃ እያሸጋገራት መሆኑ እና ብሄራዊ ጥቅም ማስከበሩ የአደባባይ እውነታ እንዲሁም በሌሎች ዘርፎች መሰረታዊ እና የሚያኮራ ስራ የሰራ ቢሆንም ቅንጅቶች በአሉታዊ መነጽር ጠምዝዞ በማቅረብ ኢህአዴግን ድባቅ መትቶታል፡፡ እንዲህ ነው አንድ ሰው በሰራው በጎ ስራ ሲመታ!! ለዚህ ነው ኢህአዴግ በሰራው አኩሪ ስራ ጭምር ኩፍኛ ተመትተዋል ያልኩኝ፡፡ እንዲህ ነው ዋሽቶ ማሳመን ማለት ብዬ ከላይ የገለጽኩት፡፡ አንባቤ ልብ ሊለው የሚገባ ነጥብ ግን ኢህአዴግ ለፖለቲካ ሲል ዋሽቶ ማሳመን ነበረበት እያልኩኝ እንዳል ሆነ ሊሰመርበት ይገባል፡፡ ቢያንስ ኢህአዴግ የሰራው ስራ ግን አኩሪ መሆኑ በበቂ ቃለት ማሳመን ነበረበት ማለቴ ነው፡፡Photo - Ethiopia Election debate 2015

ሌላኛው ዋና ለቅንጅቶች ሀሪፍ ክፍተት የሆነላቸው ግን የራሳቸውና አለን የሚሉት አማራጭ ሐሳብ ፣ የመንግስታቸው አወቃቀር (ሲያሸንፉ የሚከተሉት)፣የውጭ ፖሊሲ እቅዳቸው ፣ የገጠርና የከተማ ፖሊሲያቸው ፣ እንዲሁም ኢትዮጵያን በምን አቅጣጫ ሊመርዋት እንዳሰቡ የሚጠይቃቸው ማጣታቸው ነው፡፡ ኢህአዴግ ነቅቶ አጀንዳ አሲይዞ የኔ ፖሊሲ ሰምታችዋልንም ሂስ አድርጋችዋልም ፣ ስለዚህ እኔ በተራዬ የናንተ አማራጭ ፖሊሲ እንድገመግም ፣ እንድተችም እድል ይሰጠኝ ብሎ ቢል ኖሮ፣ እንዲሁም ህዝቡ የተሻለ አማራጭ እንዲኖረው እና አመዛዝኖ የተሻለ የፖለቲካ ፓርቲ ሊመርጥ ይመቸው ዘንድ በናንተ ርእዮት ዓለምም እንከራከር ብሎ ሐሳብ ቢያቀርብ ኖሮ….በእርገጥኝነት ለመናገር አጀንዳ አልባ የነበሩ ቅንጅቶች የሚዩዙት የሚጨብጡት ያጡ ነበረ፡፡

ህዝቡም ቅንጅቶች ምን ዓይነት መንግስት ለመመስረት እንደፈለጉ ፣ ሀገራችን በምን ስትራተጂ ሊያስተዳድርዋት እንደአቀዱ ፣ እንዲሁም የብሄረ ፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ውስብስብ ጥያቄዎች በምን መልኩ (ከኢህአዴግ በተለየ መልኩ) እንደሚመልሱዋቸው ፣ የገጠርና የከተማ ህዝባችን እንዴት እንደሚያስተዳድሩት ለማሳወቅ ይገደዱ ነበረ፡፡ ቢያንሰ ቢያንስ ጸረ-ብሄር ፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች መርህ እንደነበራቸው ህዝቡ ፊት ማጋለጥ ይቻል ነበረ፣ ምክንያቱም ብሄር ብሎ ነገር አናውቅም የሚል ፕሮፖጋንዳ ሲነዙ ነበረና፡፡ ኢህአዴግም ይህን እድል ተጠቅሞ የቅንጅት ፖሊሲ እንዴት በሀገራችን ተጨባጭ ሁኔታ መተግበር እንደሚቻል እንዲሁም ያቀረቡት ፖሊሲ ለህዝብ እንደማይጠቅምና የራሱ ፖሊሲ ይበልጥ እንደሚጠቅም ፣ በተግባር የታዩ ተጨባጭ ምሳሌዎች በመጥቀስ እርቃናቸው ያወጣተቸው ነበር፡፡ የቅንጅት መስመር የትም እንደማይደርስና ምን ያህል ህዝብ የተዋደቀለት የብሄር፣ብሄረሰቦችና ህዝቦች ጥያቄዎች ለመደፍጠጥ እንደተዘጋጁ ኢትዮጵያውን ማሰመን ይችል ነበር. ነበር ነው እንግዲህ፡፡

ከንግግሮቻቸው መገንዘብ ይቻል እንደነበረው የኒዮ-ሊበራል ርእዮት-ዓለም አራማጆች እንደነበሩ ነው፡፡ በመሆኑም ለምሳሌ መሬት ይሸጥ ይለወጥ የሚል አጀንዳቸው ብናይ እንኳን ለገጠሩና ለድሀው ህዝብ ምን ማለት እንደሆነ ይህን ፖሊሲ የተከተሉ የአፍሪካ ሀገራት ኢኮኖሚያቸው እንዴት እንደደቀቀና እንዴት ድሀው ህዝብ በጥቂት ከበርቴው እንደተገፋ ከሀገራችን ተጨባጭ (ነባራዊ) ሁኔታ አስተሳስሮ ማስረዳት ይቻል ነበረ፡፡ ቢያንስ ህዝቡ መጠነኛ እውቀት መጨበጥ ይችል ነበረ፡፡ ህዝቡ የትኛው ፓርቲ ፖሊሲ እንደሚጠቅመውም አመዛዝኖ ወደ ምርጫ ይገባ ነበረ ብሎ ማሰብ ይቻላል፡፡ የሆነው ግን የተገላቢጦሽ ነው ፡፡ አብዛኛው ህዝብ የቅንጅት አማራጭ ፖሊሲ ሳያውቅ ፣ በቅንጅት ትችት መጠነኛ ምት የደረሰበትን የኢህአደግ ፖሊሲ ብቻ ፈትሾ ነው ካርዱ ለመስጠት የገባው፡፡

ያኔ ቅንጅቶች ባልሰሩበትና ባልደከሙበት ይባስ ብሎም ውጤት በማምጣት ላይ የነበረ ፖሊሲ በማንኳሰስና በማዋረድ ነው የወቅቱ የፖለቲካ ክርክሩ የተጠናቀቀው፡፡ በሌላ አነጋገር ቅንጅቶች የኢህአዴግን የስራ አፈጻጸም ገምጋሚዎች ኢህአዴግዬ ተገምጋሚ ነበር የሆኑት፤ ለዛውም ሚዛነዊ ባልሆኑ ገምጋሚዎች፡፡ ቅንጅቶች የመንግስት አፈጻጸም የሚከታተለው የህዝብ ተወካዮች ምክርቤት (ፓርላማ) ስልጣን በመተካት ጉዳዩ ከህዝብና ከሀገር ጥቅም በመጠምዘዝ ለራሳቸውና ለቅስቀሳ በሚመቻቸው ሁኔታ አዋሉት፡፡ ይህ ያልኩበት ዋናው ምክንያት ሀገርና ህዝብ የሚጠቅሙ ስራዎችና ፖሊሲዎች አጥፊ ነው ብሎ ነገርየው በተለያዩ ቃላት በማጨቅ የኢህአዴግ በመሆኑ ብቻ እና በየትም ፍጪው ዱቄት አምጪው ፈሊጥ አፈር ድሜ አበሉት፡፡

ህዝቡም ለሀገር የሚጠቅምና የማይጠቅም ለይቶ እንዳያውቅ በስሜት ቀሽቃሽ ቃላት ውዥንብር ውስጥ ከቶታል፡፡ ከጅምሩ ኢህአዴግ ማድረግ የነበረበት ከላይ የተጠቀሱ ዋና ዋና ሐሳቦች ማካተት ሲገባው ይባስ ብሎም ህገ- መንግስቱ ከመሰረቱ የሚኒድና የሚጥስ ፕሮፖጋንዳና ፣ ብሄር ከብሄር የሚያጋጭ ፣ የሚያንኳስስ ፣ ህገ-መንግስቱ በጠራራ ጸሐይ ህገ አራዊት ነው ብሎ እስከሚያጣጥሉት ድረስ ፣ መሰረት የሌለው ወሬ እየፈጠሩ ኢህአዴግን ሰይጣን አድርጎ በህዝብ ልብ እስኪስሉት ድረስ ዝም ብሎ ግዜ ሰጣቸው፡፡ ትርፉም በትርምስና ምስቅልቅል ያለ ምርጫ ሆኖ አለፈ፡፡ ከኋላ ኋላ ቅንጅቶች የደርግና ያለፉት ስርዓቶች (በወንጀል የሚጠረጠሩ ዓይነት ወሬ አሰማን) ዋና እና ቁልፍ ሰዎች መኖራቸው ኢህአዴግ ነገረ፡፡ አረ፣ ዶ/ር ብርሀኑ ነጋ የውጭ ዜግነት እንዳለውም በወሬ ወሬ ሰማን፡፡ ምን ዋጋ አለው ጅብ ከሄደ ውሻ ይጩሀል እንደሚባለው ነገርየው በጣም ከመቆየቱ የተነሳ እምብዛም ትኩረት አልሳበም ፣ ምንም እንኳ አባባሉ እውነታ ቢኖሮውም፡፡ እንድያውም ቅንጅቶች ኢንዲህ ከሆኑ ለምን ህግ ጥሶ ህጋዊ ፓርቲ እንዲሆኑ ፈቀዳላቸውም ተብለዋል-ኢህአዴግ፡፡ ዞሮ ዞሮ የተደፋ ወተት አይታፈስምና ክስተቱ ጠባሳ ትቶ አልፈዋል፡፡

ከታሪክና ከስህተት መማር ግን ትልቅነትና አዋቂነት ነው፡፡

አሁን ቢሆንም ግን ኢህአዴግ ከስህተቱ የተማረ አይመስለኝም፡፡ ምክንያቱም በ2007 ዓ.ም ለሚካሄደው ሀገራዊ ምርጫ በማስመልከት የፖለቲካ ፓርቲዎች ክርክር በኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን የምንከታተለው ያለ ጉዳይ ነው፡፡ አሁንም ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች የራሳቸው አጀንዳ ማለትም አለን የሚሉት የፖሊቲካ ፣ የልማት ፖሊሲ ፣ የማህበራዊና ዴሞክረሲያዊ መርሆች ለህዝብ ማሳወቅና በነሱ ዙርያም በጥልቀት መከራከር ሲገባቸው በኢህአዴግ ግድፈቶች ላይ እየተንጠለጠሉ ያሉበት ሁኔታ ነው ያለው፡፡

የተቀዋሚ ፓርቲዎች አለን የሚሉት አማራጭ ፖሊሲ በጥልቀት ለማየትና ለማማዛዘን ህዝቡ ያሻል ፣ መብቱ ነውና! ማሳወቅ አለባቸውም፡፡ ለምንና እንዴት የኢህአዴግ ፖሊሲ ለሀገራችን እንደማይበጅና የኛ የሚሉትም እንዴት የተሸለና ለህዝባችን እንደሚረባ በክርክሩ መድረክ በአጀንዳነት ተይዞ ክርክር ይደረግበት ዘንድ እጠይቃለሁኝ፡፡ ይህ በጣም ጠቃሚና መሰረታዊ ጉዳይ ነው፡፡

1ኛ/ ከኢህአዴግ በምን መሰረታዊ መርሆች እንደሚለዩና እንዴት ለሀገራችን ጠቃሚ መሆናቸው እንድናውቅ ይረደናል፡፡

2ኛ/ ኢህአዴግ ሁሌን ተቃዋሚዎች አማራጭ ፖሊሲ የላቸውም ብሎ ለሚከሳቸው ተወዳዳሪ ፓርቲዎችም ይጠቅማችዋል፡፡

3ኛ/ ተፎካካሪ ፓርቲዎች በኢህአዴግ ፖሊሲና አፈጻጸማቸው ተንጠልጥሎ ከሚነታረኩ፤ ምን ያህል ለምርጫው ዝግጅት ማድረጋቸው በቂ ምርመራ ለማድረግ ይጠቅመናል፡፡

የመድረክ ፣ሰማያዊ ፣ አንድነትና ሌሎች ፓርቲዎች አማራጭ ፖሊሲያቸው ምንድ ነው እንዴትስ ከሀገራችን ተጨባጭ ሁኔታ ይሄዳል ብለን እንድንጠይቃቸውና ከኢህአዴግ የሚለዩበት ግልጽ የሆነ ነጥብ ለማወቅም ያግዘናል፡፡

የአብዘኞቹ ተወዳዳሪ ፓርቲዎች የፖለቲካ ርእዮተ-ዓለም በግርድፉ ሶሻል ዴሞክራቲክ ፣ ሊበራል ነኝ ከሚሉት ውጭ ዘርዘር ያለ ማብራርያ ይስጡን፡፡ እንደገና ተፎካካሪ ፓርቲዎች ምርጫ በመጣ ቁጥር ፕሮግራም ፣ ፖሊሲ አለን ይሄው ብሎ ይዘቱ የማይታወቅ ጽሁፍ ከሚያሳዩን በጥልቀት አንብቦ ፣ አጀንዳ ተይዞለት አንቀጽ በአንቀጽ ወይም ነጥብ በነጥብ ተከራካሪ ፓርቲዎች ቢወያዩበት ከለይስሙላህ ክርክር ባሻገር በጣም ለህዝብም ለሀገርም ይጠቅም ነበረ ባይ ነኝ፡፡

ሳጠቃልል ኢህአዴግ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ልክ እንደ ፓርላማ መንግስት የሰራውን ገምጋሚዎች ኢህዴግም ተገምጋሚ ሁሌን ከመሆን ያድናል፡፡ ኢህአዴግም በነሱ አጀንዳም እንዲከራከር እድል ይሰጠኝ ማለት አለበት፡፡ ካልሆነ በስተቀር ልክ እንደ 1997 ዓ.ም ቅንጅት ገምጋሚ ኢህአዴግ ተገምጋሚ የሆነበት እና የቅንጅት ውስጣዊ ስብእና ሳናውቅ ወደ ምርጫ የገባንበት አጋጣሚ እንዳይደገም ስል አሳስባለሁ፡፡

ቸረ ያሰማን፣ ሰለማዊና ዴሞክራሲያዊ ምርጫ ይሆንልን ዘንድ እመኛለሁ፡፡

ዘርአይ ኃ/ማርያም አበበ

The writer is a blogger at hornaffairs.com and can be reached at [email protected]

*************

Zeray hailemariam Abebe is a scholar of International Relations and is researcher in the horn of Africa’s conflict, inter-state relations and cooperation. He blogs at HornAffairs and can be reached at [email protected]

more recommended stories