"ህወሓት ተተኪ የማፍራት ችግር አለበት" – አቦይ ስብሃት ነጋ

Highlights:

* “አንድ ቋንቋ፣ አንድ ሃይማኖት፣ አንድ ሕዝብ የሚሉ ሁሉ ህወሓትን ይጠሉታል።”

* “ከአሜሪካንና ከእሥራኤል ጋር ያጣላን ፕሮግራማችን ነው።”

* “ተወልደ የህወሓት ምክትል ሊቀመንበር፤ ስዬም የመከላከያ ሚኒስትር እያሉ ኤርትራ ነፃነቷን ስታገኝ የአሰብ ጉዳይ ያለቀለት ጉዳይ ነው። ወንበር ፍለጋ ነው እንጂ የኤርትራ ጉዳይ ሰበብ ሊሆን አይችልም።”

* “ህወሓት…… ለስድስት ወር ያህል ዝብርቅርቅ ያለ ፕሮግራም ተቀምጦ ነበር። ኢትዮጵያዊነትም አለ። ትግራይነትም አለ። ይሄ ጉዳይ በስድስት ወር ውስጥ እንዲጠራ ተደረገ።”

(ጌትነት ምህረቴ)

የመምህርነት ሙያቸውን ትተው ነበር በ1967 ዓ.ም ወደ ትግል የተቀላቀሉት። ከህወሓት ነባር ታጋዮች መካከል አንዱ ናቸው፤ አቦይ ስብሃት ነጋ። ህወሓት የተመሠረተበትን 40ኛ ዓመት ምክንያት በማድረግ ዝግጅት ክፍላችን በህወሓት አመሠራረት፣ ዓላማና የትግል አግባብ ዙሪያ ከአቦይ ስብሃት ነጋ ጋር ያደረግነውን ቃለ- ምልልስ የመጀመሪያ ክፍል ይዘን ቀርበናል።

አዲስ ዘመን፡- የንጉሡ ሥርዓት ተገርስሶ ወታደራዊ ሥርዓት ሲመጣ የነበረው የፖለቲካ አሰላለፍ ምን ይመስላል?

አቦይ ስብሃት፡- የአፄ ኃይለሥላሴን መንግሥት የጣለው ሕዝቡ ነው። የጣለው ደግሞ መውደቅ ስለነበረበት ነው። ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ሁኔታው የከፋ ነበር። በሌላው ሀገር ኢንዱስትሪው ማቆጥቆጥ ጀምሯል። የአፄው ሥርዓት በጣም ያከረረ ፊውዳል ስለነበር በሀገሪቷ ልማት የሚባል ነገር አልነበረም። ትምህርትም ቢሆን እንደ ጠበል የሚንጠባጠብ በጣም የተወሰነ እንጂ የሰፋ አልነበረም። ሕክምናም እንደዚሁ።

ሀገሪቷ ለማንኛውም አደጋ የተጋለጠች ነበረች። ሕዝቡ በረሃብ እየሞተ «ኢትዮጵያ የአፍሪካ የዳቦ ቅርጫት ናት» ይባል ነበር። ሕዝቡ ኑሮው አስከፊ ሆኖ ሳለ በወቅቱ የሚነገረው ግን ኢትዮጵያ ሀገራችን በሳይንስና ቴክኖሎጂ ያደገች ናት የሚል ነው። ይህ ደግሞ ከነባራዊ ሁኔታው ጋር ተቃራኒ ነበር። ማንኛውም ነገር ሲመረቅ በአፍሪካ አንደኛ በዓለም ሁለተኛ ነው ይባል የነበረው። በአፄው ዘመነ መንግሥት ጊዜ የነበረው የከፋ ሁኔታ የኢትዮጵያ ሕዝብ መንስኤውን ይወቀው አይወቀው አገፍግፎት ነው ከተማሪዎች ጀምሮ እስከ ገበሬው ድረስ ሥርዓቱን ለመጣል ትግል የጀመረው። ፖለቲካውም አንድ ቋንቋ፣ አንድ ሕዝብና አንድ ሃይማኖት የሚል ነው። ይህ ደግሞ ሁሉንም የኢትዮጵያ ሕዝቦች የሚገልጽ አይደለም። የመናገር የመፃፍ መብት የለም። እነዚህ ሁኔታዎች የአጼው ሥርዓት እንዲወድቅ ምክንያት ሆነዋል። ሥርዓቱ ከተገረሰሰ በኋላ ደርግ ሥልጣኑን ተቆጣጠረው። ምክንያቱም በወቅቱ የተደራጀ ኃይል የለም፤ ሊደራጅ የሚችል ብቃት ያለው ልምድም አልነበረውም።

በወቅቱ የተለያዩ ተደራጅተው የሚታገሉ የፖለቲካ ፓርቲዎች ነበሩ። አሰላለፋቸውንም በአራት ከፍሎ ማየት ይቻላል።

አንደኛው የነበረውን ንጉሣዊ ሥርዓት ለመመለስ የሚታገል ነው። በሰሜን ሸዋ፣ በትግራይና በላስታ የባላባት ወገኖች ንጉሣዊ ሥርዓቱን ለመመለስ እዚህም እዚያም ትግል ሲያደርጉ ነበር።

ሁለተኛው ቡድን የብሔር ግንባሮች ናቸው። የአፋር ነፃ አውጪ ግንባር፣ የሲዳማ ነፃ አውጪ ግንባር፣ የኦሮሞ ነፃ አውጪ ግንባርና የምዕራብ ሱማሌ ነፃ አውጪ ግንባር የሚባሉት ይገኙበታል። እነዚህ ከዚህ የከፋ የለም ብለው ነው ጥለው የወጡ። እነዚህ ግንባሮች «ከዚህ የከፋ የለም» ማለታቸው ትክክል ነው ግን ምንድንነው መንስኤው፣ መፍትሔውና ተለዋጩ ሥርዓት ምን ሊሆን ይችላል? የሚለውን ማስቀመጥ አልቻሉም።

ሌላው ሦስተኛው ቡድን ግራ አዝማሚያ የሚከተለው ነው። በዚህ አሰላለፍ መኢሶን፣ ኢህአፓ፣ ኢሰፓ አለ። እነዚህ ፖለቲካቸውና ምድባቸው አንድ ነው። በኢትዮጵያ ያለ ቅራኔ በሠራተኛውና በባለሀብቱ መካከል ያለ ቅራኔ ነው ብለው ያምናሉ። ይሁን እንጂ በኢትዮጵያ የነበረውን መሠረታዊ ሥርዓት ሳይነኩ እንዳለ ሥልጣን ላይ መውጣት ነበር ግባቸው። ኢህአፓም ጊዜያዊ ሕዝባዊ መንግሥት መቋቋም አለበት ቢልም ደርግን ለመመከት የተከተለው ስልትና ስትራቴጂ የተዛባ ነው። ፕሮግራሙም ብቻ ሳይሆን አካሄዱም ኢትዮጵያን ያንፀባረቀ አልነበረም። እናም አፄ ኃይለሥላሴ ከሥልጣናቸው ከወረዱ በኋላና ደርግ ሥልጣን ከወጣ ወዲህ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ሁኔታ የተዘበራረቀ ነበር።

ህወሓትን በአራተኛ አሰላለፍ ልናስቀምጠው እንችላለን። ሕዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይን (ህወሓት) ያቋቋሙት በተማሪዎች እንቅስቃሴ የነበሩ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ናቸው።

አዲስ ዘመን፡- የህወሓት አመሠራረት ዓላማና የትግል አግባብ እንዴት ነበር?Photo - Sebhat Nega 2013

አቦይ ስብሃት፡- ህወሓትን የመሠረተው ማህበረ ገስገስ ብሔረ ትግራይ (ማገምት) የሚባለው ቡድን ነው። ማገምት ይህን የፖለቲካ ሁኔታ ካየ በኋላ ኢትዮጵያ የብዙ ብሔሮች ብሔረሰቦች ሀገር ናት። ስለዚህ ዋነኛው ቅራኔ የብሔር ቅራኔ ነው። ይህ ሁኔታ ዴሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ መፈታት አለበት። እናም በእኩልነት ላይ የተመሠረተ አንድነት ነው አማራጩ አለ። ቅራኔው ሀገር እየበታተነ ነው። በእኩልነት ላይ የተመሠረተ አንድነት መመስረት ካልተቻለ ደግሞ መገንጠል ይከተላል። በእኩልነት ላይ አንድነትን ማምጣት ይቻላል ብሎ ተነሳ።

ሁለተኛው ቅራኔ በገበሬውና በከተማ ነዋሪ ያለው ቅራኔ ነው። ሀብታችን መሬት ሆኖ ሳለ በገበሬውና በከተማው ነዋሪ ያለውን ቅሬታ ካልተፈታ ልማት አይመጣም። ሀገሪቷን የማወቅ ሙከራ እንደ መደርደሪያ ይዞ በሂደት እየጠራ የሚሄድ አቅጣጫ ተከተለ። ስልትና ስትራቴጂውም ከገጠር የሚጀምር የተራዘመ የትጥቅ ትግል ማድረግ ነው ።

እና ይህን ፕሮግራም ለማስፈጸም ደግሞ ከማንኛውም በሀገራችን የነበሩ የፖለቲካ ድርጅቶች የጠራ አደረጃጀት ፈጥሮ ነው የተንቀሳቀሰው። ለትግሉ የሚያስፈልገው አደረጃጀትም በኅዳር ወር 1967ዓ.ም ነድፎ ደደቢት የሚገባው ደደቢት ገባ። ኤርትራ የሚሄደው ኤርትራ ለሥልጠና ሄደ። ከተማ የሚሰማራው ከተማ ገባ። ትግሉ የካቲት 11ቀን 1967 በደደቢ በረሃ ተጀመረ ።

አዲስ ዘመን፡- ህወሓት በትግል የመጀመሪያ ምዕራፍ የትግራይን ህዝብ በኋላ ደግሞ ቀሪውን የኢትዮጵያ ህዝብ በማንቀሳቀስ ረገድ ስኬታማ ያደረገው ምስጢር ምንድንነው?

አቦይ ስብሃት፡- ምስጢሩ ፕሮግራሙ ነው። ሕዝባዊነቱ ነው። ለፕሮግራሙ ሲል ህወሓት ረጅምና መራራ ትግል ማድረጉን ማንም ሊክደው አይችልም። ፕሮግራሙ የኢትዮጵያን ተጨባጭ ሁኔታ ስለሚያንፀባርቅ በሕዝቡ ዘንድ ተቀባይነት አገኘ። ያም ሆኖ አንድ ሕዝብ፣ አንድ ሃይማኖትና ሌሎች አንዶችን በውስጡ አስርጾ ለኖረ ሕዝብ ስለ ትግሉ ፕሮግራም በቀላሉ ማስረዳት ይቸግራል። እናም ህወሓት ስኬታማ የመሆኑ ዋናው ምክንያት ፕሮግራሙ ነው። ፕሮግራሙን ለመፈጸም የነበረው አደረጃጀትና አሠራር የጠራ መሆኑ ለስኬቱ አስተዋጽኦ ነበረው።

ፕሮግራሙን ለሕዝብ እያሳወቀ መሄዱ፤ ቀስ በቀስ ደግሞ ይህንን የሚቀበሉ የፖለቲካ ድርጅቶች እኛም እያገኘናቸው እነርሱም እያገኙን መምጣት ፕሮግራሙን ወደ ሕዝቡ ለማስፋፋት ተችሏል። በመጀመሪያ ፕሮግራሙን የትግራይ ሕዝብ ተቀበለው፤ ሌላ አማራጭ እንደሌለ በጥልቀት አመነው። ማንኛውንም ዋጋ ለመክፈል ተዘጋጀ። ከትግራይ ውጪ ያለው የኢትዮጵያ ሕዝብ ደግሞ ይህን እያመነ ሄደ።

በተለይ ደግሞ ህወሓት በትጥቅ ትግሉ የማረካቸውን የደርግ ወታደሮች ስለፕሮግራሙ አስረድቶ ስለሚለቃቸው በሚሄዱበት ቦታ ሁሉ ህወሓትን የመሰለ ድርጅት የለም እያሉ ይመሰክሩ ነበር። ይህም ለድርጅቱ ኃይል እየፈጠረ እየሰፋ እንዲመጣ አድርጓል። ህወሓት ትግራይ ውስጥ 17 ዓመት ትግል አካሂዷል። ወደ አማራ ሕዝብ ስንገባ ደግሞ ትግሉ እያጠረ ሄዷል። ሕዝቡም ህወሓ /ኢህዴግ ከነበረው ሥርዓት የተሻለ መሆኑን እያመነ ሄደ። ቁርጠኛ አመራርና ታጋይ እየተበራከተ መጣ። ታጋይ ስንል ገበሬውና ሐኪሙንም ይጨምራል። ለፕሮግራሙ ቁርጠኛ የሆነ አባልና አደረጃጀት ስለነበረን ውጤታማ መሆን ችለናል።

አዲስ ዘመን፡- ህወሓት ከሌሎች አጋር ድርጅቶች ጋር አብሮ ለመታገል የአቋም ለውጥ አድርጎ ይሆን?

አቦይ ስብሃት፡- የህወሓት ፕሮግራሙ በትክክል የኢትዮጵያን ሁኔታ የሚያፀባርቅ ነው። ይሁን እንጂ ኢዲዩ አይቀበለንም። ኢህአፓም አይቀበለውም። እንዲያውም የብሔር ድርጅቶች አያስፈልጉም የተፈጠሩ ካሉ በኢህአፓ አመራር ውስጥ መግባት አለባቸው ይል ነበር። የኢህዴን/ብአዴን አባሎች ከኢህአፓ የወጡ ናቸው። ኢህአፓ ኢትዮጵያን ለማወቅ ፍቃደኛ አልነበረም። ለመጀመሪያ ጊዜ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት ሆኖ ያገኘነው ኢህዴን/ ብአዴንን ነው። ከእነርሱ ጋርም የፖለቲካ ውይይት አድርገን ምንም ፖለቲካዊ ልዩነት አላገኘንም። ስለዚህ ትግሉን አብረን ቀጠልን። ነገር ግን ህወሓት የለወጠው ምንም ነገር የለም። የህወሓት ፕሮግራም አይለወጥም። ምክንያቱም ትክክለኛውን የኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ የሚፀባርቅ ነውና።

አዲስ ዘመን፡- በህወሓት የትግል የመጀመሪያ ዓመታት ደርግን ለመፋለም የወጡ የፖለቲካ ኃይሎች በህወሓት ላይ ጥቃት ይፈጸሙ እንደነበር ይነገራል። ምክንያቱ ምንድንነው? እነዚህ ድርጅቶች ሲከስሙ ህወሓት እስካሁን መዝለቅ የቻለበት ምክንያትስ ምንድንነው?

አቦይ ስብሃት፡- ከሌሎች የፖለቲካ ድርጅቶች ጋር የተጋጨንበት መንስኤ ፕሮግራሙ ነው። ኢዲዩ በምዕራብ ሀገራት እየተደገፈ የመጣ ነው። ምዕራባውያን ህወሓትን ሀገር የሚበትን ሥርዓት አድርገው ነው የተረዱት። አንድ ቋንቋ፣ አንድ ሃይማኖት፣ አንድ ሕዝብ የሚሉ ሁሉ ህወሓትን ይጠሉታል። ኢህአፓም እንዲሁ ነው። ከደርግም ቅራኔ ውስጥ የከተተን ፕሮግራማችን ነው። ገንጣይ አስገንጣይ ዘረኛ የሚል ስያሜ ነው የሰጡን።

አርነት ትግራይ የሚባል የትግራይ ድርጅት ነበር። በጣም ጠባብ ነው። ከእርሱ ጋርም በፕሮግራም ተጋጨን። ጀብሃም እርሱን ይደግፍ ስለነበር ከጀብሃ ጋርም ተጣላን። የብሔሮቹ ድርጅቶች ደግሞ በእኩልነት የተመሠረተ አንድነት አይቻልም የሚል እምነት ነበራቸው። እና ከሌሎች የፖለቲካ ድርጅቶች ጋር ያጋጨን ፕሮግራማችን ነው። ስኬታማ ያደረገንም ፕሮግራማችን ነው።

እነዚህ ድጅቶች የከሰሙት በፖለቲካ ባህሪያቸው ነው። የኢትዮጵያን ሕዝብ ችግሮች አያንፀባርቁም። የነበራቸውን ፕሮግራም ይዘው ኃይል መፍጠር አልቻሉም። የእኛ የኢትዮጵያን ነባራዊ ሁኔታ ያንፀባረቀ ነው። መንስኤውን አስቀምጦ መፍሔውንም ያሳያል። ለስኬት እንዲበቃ ያደረገው ፕሮግራሙ ነው።

ሁለተኛ ይህንን ፕሮግራም ለመፈጸም የሚያስችል አደረጃጃትና አቅም ፈጥሯል። ምቹ ሁኔታ የማያመልጠው አደጋን መከላከል የሚችል ታጋይ ተፈጥሯል። አመራሩም ሲሄድም ሆነ ሲተኛም ለፕሮግራሙ የሚታገል ነው። በጥቅሉ አደጋ ካለ የሚከላከል ምቹ ሁኔታ ካለ የሚጠቀም ኃይል ስላለው ነው።

አዲስ ዘመን:- በትጥቅ ትግሉ ዘመንም ሆነ ከትግል በኋላ ህወሓትን ያጋጠመው ትልቁ መሰናክል ምንድንነው?

አቦይ ስብሃት፡- አንዱ ያጋጠመን ችግር ከፕሮግራሙ የመነጨ ነው። ከአሜሪካንና ከእሥራኤል ጋር ያጣላን ፕሮግራማችን ነው። ሌላው ጠባብነትና ትምክህት ናቸው። የራሱን ጥቅም ለማራመድ የሚፈልግ ሰው ጠባብነትን በማስፈንና ትምክህትን በማርገብገብ ነው የሚንቀሳቀሰው። በትጥቅ ትግል ጊዜ የነበሩ ችግሮች አሁንም አሉ። ትልቅ አቅም የላቸውም እንጂ ጠባብነትና ትምክህት አሁንም ይታያሉ።

በትግሉ ሂደት ከነበሩ የውስጥ ችግሮች መካከል አንደኛው በ1967 ዓ.ም አንዳንድ የሽፍታ ባህሪ ያላቸው ሰዎች ከእኛ ጋር መቀላቀላቸው ነው። ተማሪዎችም አሉ። ግማሽ የግብርና ግማሽ የሽፍትነት ባህሪ የነበራቸው ሰዎች አንድ አደጋ ለማድረስ ሞክረው ነበር። እንዳሰቡት አልተሳካላቸውም እንጂ ሙከራ ቸው ድርጅቱን የሚጉዳ ይሆን ነበር።

በ1969ዓ.ም ደግሞ የነበረው ችግር ህወሓት ወዳጅ ድርጅት ያልነበረው መሆኑ ነው። ሻዕቢያም ቢሆን ኢህአፓን ካገኘ በኋላ የብሔር ጥያቄን አላውቅም፤ ከእኛ ጋር የሚኖራችሁ ግንኙነት ከኢህአፓ ጋር ጥሩ ከሆነ ብቻ ነው አለን። ኢዲዩ ደግሞ 12ሺ የጦር ሠራዊት ይዞ ያስፈራራል። ያን ጊዜ እኛ የነበረን 450 የሚሆን ኃይል ብቻ ነበር። በሌላ በኩል ደግሞ ሶቭዬት ኅብረት የእኛ ጓደኛችን ነው ስንል ከደርግ ጋር ታርቆ ስለነበር አጋር ማግኘት ከባድ ሆኖብን ነበር።

የኢኮኖሚ ችግራችንም ከፍተኛ ነበር። ይሄን ችግራችንን ለመፍታት ንግድ እንዳንነግድ ሻዕቢያ የትግራይ ሕዝብ ኤርትራ ሂዶ አይነግድም አለን። ዘመን በጨለመበት ጊዜ ከእኛም የጨለመባቸው «ይህ አመራር ብቁ አይደለም» ብለው በአብዛኛው ድርጅቱን ተቆጣጥረውት ነበር። ያን ጊዜ መሬት ቢጨልምም የትግራይ ሕዝብ እንደ ተስፋ አድርጎ የሚቆጥረው ህወሓትን ነበር። እነዚህ ግለሰቦች ግን ድርጅቱን አፍርሰው ወደ ቤታቸው ለመሄድ ፈለጉ። ህወሓትን ከድተው ቢሄዱ ሕዝቡ አይቀበላቸውም፤ ድርጅቱ ፈረሰ ከተባለ ግን የሚወቀሱበት ምክንያት የለም። ስለዚህ ድርጅቱን ለማፍረስ ተንቀሳቀሱ። የእነዚህ ግለሰቦች ሴራ መንስኤ ፍርሃትና ተስፋ መቁረጥ ሆኖ ሳለ አውራጃዊነት አለ ብለው ድርጅቱን ለማፍረስ የአውራጃ መፈክር ይዘው ተን ቀሳቅሰዋል።

«ደቡብ ትግራይ ተገልሏል። የአክሱም፣ አድዋና ሽሬ ሰዎች ናቸው አመራሩን የተቆጣ ጠሩት። እርስ በራሳቸው አይነቃቀፉም ይቻቻላሉ። እኛ ደቡቦቹን ግን አግልለውናል» የሚል ጠባብነት ነው ሲያራግቡ የነበሩት። ይህን ይዘው ነው ድርጅቱን ለማፍረስ የሞከሩት። ብልሹ የሆነ ቡድን ጠባብ የሆነ ሃይማኖትን ወይም ብሔርተኝነትን አልያም ትምክህትን ነው የሚጠቀመው። አሁንም ጠባቦችና ትምክህተኞች አሉ። በወቅቱ ይህ ነበር ትልቁ አደጋ። ኢኮኖሚው በጣም ፈተና ነበር።

የ1977ዓ.ም ድርቅም ሌላው ፈተና ነበር። ከፍተኛ ድርቅ ነው ያጋጠመው። ህወሓት የሰዎችን ሕይወት ለማዳን ርብርብ አድርጓል። በሱዳን ደንበር በተወሰነ ደረጃ የአስቸኳይ እርዳታ ለማድረግ ተሞክሯል። ቤት ለቅቀው ሲሄዱ ቤቱ ባዶ እንዳይሆን የገበሬው እሴት እንዳይጎዳ ድርጅቱ በኃላፊነት ይጠብቃል። ሕዝቡ ቤቱን ትቶ ሲሰደድም ከአስተዳደሩ ጋር ነው እንዲሄድ የተደረገው። ምዕራባውያን ግብረ ሰናይ ድርጅቶች ድርቁ ካለፈ በኋላ «በሱዳን መጠለያ ጣቢያ የነበረው ሕዝብ እዚያው ይቆይ፤ የምትወስዱት ለረሃብና ለጦርነት ነው» እያሉ ቅስቀሳ ቢያደርጉም በፊት ሄደው የነበሩት ሳይቀር ወደ ትውልድ ቦታቸው ተመለሱ። ይሄ የሚረሳ ታሪክ አይደለም።

በ1993ዓ.ም ደግሞ ህወሓት የመከፋፈል አደጋ አጋጥሞት ነበር። ለዚህ ምክንያት የሆኑት በህወሓት/ኢህአዴግ በከፍተኛ የአመራር ቦታ ላይ የነበሩ ግለሰቦች ናቸው። መነሻቸው የኤርትራ ጉዳይ ይሁን እንጂ ዋና ዓላማቸው ሥልጣን መያዝ ነው። የሥልጣን ጥማቱ ታምቆ የቆየ ነው። ሻዕቢያ ኢትዮጵያን የመውረሩን ጉዳይ ያለመከታተላችን የሁላችን ድክመት ነው። ቀደም ብለን ማወቅ ነበረብን የሚል እምነት አለኝ።

ችግሩን ሰላማዊ በሆነ መልኩ ለመፍታት የዲፕሎማሲ ጥረት ማድረግ ያስፈልግ ነበር። ለሰላም አሟጥጠን ዕድል እንስጥ፤ ዕድሉ ካላዋጣ መዋጋት ማን ይከለክለናል የሚሉ የአመራር አባላት ነበሩ። እኛ ከኢሳያስ ተሽለን መገኘት አለብን። የእኛ ሰዎች ግን እንደ ኢሳያስ ሆኑ። ነፋስ በኤርትራ መጣ ከተባለ እንዋጋ ነው የሚሉት ከወላጆቻቸው በምንም አይለዩም። ስንወረር ዝም ብላችሁ አያችሁ የሚለውን እንደ ምክንያት ወስደው ቡድን ፈጠሩ።

አዲስ ዘመን:- ክፍፍሉ ግን ከአሰብ ወደብ ጋር የሚገናኝ ነው የሚሉ ወገኖች አሉ። ይህ ምን ያህል እውነትነት አለው?

አቦይ ስብሃት፡- አሰብ የኤርትራ ግዛት ነው ተብሎ ሪፈረንደም ተደርጎበታል። ድሮም በጣሊያን ጊዜ ያለቀለት ጉዳይ ነው። ተወልደ የህወሓት ምክትል ሊቀመንበር፤ ስዬም የመከላከያ ሚኒስትር እያሉ ኤርትራ ነፃነቷን ስታገኝ የአሰብ ጉዳይ በተባበሩት መንግሥታት ያለቀለት ጉዳይ ነው። ወንበር ፍለጋ ነው እንጂ የኤርትራ ጉዳይ ሰበብ ሊሆን አይችልም።

አዲስ ዘመን:- ህወሓት ተተኪ አመራሮችን የማፍራት እጥረት እንዳለበት አንዳንድ ወገኖች ይናገራሉ? በዚህ ጉዳይ ምን አስተያየት አልዎት?

አቦይ ስብሃት፡-ህወሓት ተተኪ የማፍራት ችግር አለበት። ሌሎችም ድርጅቶች ችግር አለባቸው። ካለፈው ትውልድና የአሁኑ ትውልድ ሲነፃፀር የአሁኑ ትውልድ መብለጥ አለበት። ትውልድ ስል ማህበረሰቡን ማለቴ ነው። ምክንያቱም ድርጅቱም ሆነ መንግሥት የሚመሠረተው ከኅብረተሰቡ ነው። ትውልዱ ከጠባብነትና ከትምክህት የራቀ መሆን አለበት። እነዚህ ለሀገር ከፍተኛ አደጋ የሚያመጡ ናቸው። ስለዚህ ትውልዱን ዓለም ከተፋቸው አመለካ ከቶች ነፃ ማውጣት ይገባል። ህወሓት/ ኢህአዴግ ትውልዱን ከአዕምሮ ስልብነት ነፃ ለማውጣት መሽቀዳደም ይገባዋል። ድርጅቱ እየመለመለ እሳት የላሰ ለበጎ ተግባር የሚቆም ተተኪ ማፍራት ግድ ይላል። በየደረጃው የቡድን (ኮሌክቴቭ ሊደርሽፕ) አመራር መረጋገጥ አለበት።

አዲስ ዘመን:- ህወሓት ሲመሠረት የትግራይ ሕዝብ ጥያቄዎችን ለመመለስ ነው። አሁን ላይ ሆነው ሲያዩት የትግራይ ሕዝብ ጥያቄዎች ተመልሰዋል ብለው ያስባሉ?

አቦይ ስብሃት፡- ህወሓት የተመሠረተው በትግራይ ሕዝብ ግፊት ነው። ይህን የሕዝብ ግፊት መሸከሙ አስቸጋሪ ነበር። ህወሓት በትግራይ ሕዝብ ግፊት ቢመሠረትም ፕሮግራሙ ግን አገራዊ ነው። የትጥቅ ትግሉን ከትግራይ ጀምሮ በመላ ሀገሪቷ እያስፋፋ ለመሄድ ነው ዓላማው። ለስድስት ወር ያህል ዝብርቅርቅ ያለ ፕሮግራም ተቀምጦ ነበር። ኢትዮጵያዊነትም አለ። ትግራይነትም አለ። ይሄ ጉዳይ በስድስት ወር ውስጥ እንዲጠራ ተደረገ። የትግራይ ሕዝብ እንደሌላው የኢትዮጵያ ሕዝብ በአስተማማኝ ጎዳና ላይ አለ።

ፓለቲካዊ ጠባብነትና ትምክህት በየመ ንደራችን አለ። ቢሮክራሲው የፀዳ አይደለም። እንግዲህ ፓርቲውን የሚመራው መንግሥት ነው። ተወዳዳሪና ቀና የሆነ ቢሮክራሲ ገና አልተገነባም። ከላይ እስከ ታች ሕገ መንግሥቱ በትክክል እየተተገበረ ነው ወይ? የሚለው ጎደሎ አለበት። ስለዚህ አፍሪካውያን የሚጎመጁበት የተዋጣለት ጉዳና ቢኖርም በጉዳናው ላይ የሚደረግ ሩጫ ውጣ ውረድ አለበት። የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ እያለም «አንድ እጃችንን ታስረን ነው የምንታገለው» ብሏል። ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝም የመልካም አስተዳደር ችግር እንዳለ ገልጿል። ችግሩን የምንፈታው ሕዝቡን ይዘን ነው።

በአስተማማኙ ጎዳና እየተደረገ ያለው ሩጫ ዘገምተኛና እንከን ያለበት ነው። እንከን ስል ቢሮክራሲው የተሳለጠ ባለመሆኑና የቀናነት ጉድለት ስላለ ሕዝቡ በሚገባ ደረጃ እየተጠቀመ አይደለም። የተዛባ አመለካከትና የተንዛዛ አሠራር ይስተዋላል። ይህ ክፍተት መቀረፍ አለበት። ህወሓት/ ኢህአዴግ ስህተቱን ይፋ የሚያደርግና የሚያርም ድርጅት ነው። ስለዚህ ከሕዝቡ ጋር በመተባበር ችግሮቹ ይፈታሉ የሚል እምነት አለኝ። ህወሓት ሕይወቱ ሁሉ ትግል ነው፤ ትግሉንም አጠናክሮ ይቀጥላል።

አዲስ ዘመን:- በእርስዎ እምነት የኢትዮጵያ የወደፊት ዕጣ ፈንታ ምን ሊሆን ይችላል?

አቦይ ስብሃት፡-የዕድገትና የትራንስፎ ርሜሽን ዕቅዱ ኢኮኖሚውን ስር ነቀል ለውጥ እንዲያመጣ ያደርጋል። ግብርና በይበልጥ ማደግ አለበት። እያደገም መሪነቱን ለኢንዱስትሪ ማስረከብ አለበት። በዚህ ጊዜም ገበሬው ቀስ በቀስ ወደ ላብ አደርነትና ባለሀብትነት እየተቀየረ ይሄዳል። ኢንዱስ ትሪውም መሪነቱን ይረከባል። ይህን ተከትሎም ብዛት ያለው ባለሀብትና ላብአደር ይፈጠራል። እናም በኢኮኖሚው ስር ነቀል ለውጥ ላብአደሩና ባለሀብቱ የመሪነቱን ሚና ሲይዙ የሚፈጠሩ ፓርቲዎች ተፎካካሪ ይሆናሉ። አውራ ፓርቲ የሚባል አይኖርም።

አዲስ ዘመን:- ለሰጡኝ ማብራሪያ እጅግ አድርጌ አመሰግናለሁ።

አቦይ ስብሃት፡- እኔም አመሰግናለሁ።

ምንጭ፡- አዲስ ዘመን – የካቲት 2007

********

Content gathered and compiled from online and offline media by Hornaffairs staff based on relevance and interest to the Horn of Africa.

more recommended stories