«የኢትዮጵያ ህዝብም ጠመንጃ የታጠቀ ጓደኛ ያገኘው በዚህ ትግል ነው»-ጄኔራል ሳሞራ የኑስ

በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ስር የምትታተመዋ ዘመን መፅሄት የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ኢታማዦር ሹም ጄኔራል ሳሞራ የኑስን እንግዳ አድርጋ ዘርዘር ያሉ መረጃዎችን ይዛ ወጥታለች። ከእነዚህ ነባርና አንጋፋ ታጋዮች መካከልም ጄኔራል ሳሞራ ለመጽሄትዋ ከሰጡት መረጃ የተወሰኑትን በመምረጥ እንዲህ አቅርበነዋል።

ዘመን፡- እናመሰግናለን ጄኔራል ሳሞራ እንደሚታወቀው የህወሀት 40ኛ ዓመት መከበር ጀምሯል። እርስዎ ደግሞ በትግሉ ግንባር ቀደም ተጠቃሽ ነዎትና እንደ ግለሰብ ትግሉን እንዴት ያስታውሱታል፤ ዛሬ ላይ ሆነው ሲያስቡት?

ጀኔራል ሳሞራ፡- አርባ ዓመት ረጅም ጊዜ ነው። የትግሉ ሂደትም አንድ ዓይነት አልነበረም። የመጀመሪያዎቹ አስራ ሰባት ዓመታት ጨቋኙን ፋሽስት የደርግ ስርዓት ለማስወገድ የተደረገ የትግል ጊዜ ነበር። ይሔ ትግል ደግሞ በርካታ መስዋዕትነት የተከፈለበት ነው። ብዙ ወጣት ኢትዮጵያውያን የተሰዉበት የትግል ሂደት ነው። ደርግ ከተሸነፈ በኋላ ደግሞ የሰላም፣ የልማትና የዴሞክራሲ ትግሉ ነው የቀጠለው። እንዳልኩት የመጀመሪያው አስራ ሰባት ዓመት የትግል ዓላማ ጨቋኙን ሥርዓት የማስወገድ ቢሆንም የመጨረሻው ዓላማ ግን ዴሞክራሲን፣ ልማትንና ፍትህን ማረጋገጥ ነበር። እና ትግሉ የመላው ኢትዮጵያ ህዝቦችን ድጋፍ አግኝቶ በተሳካ ሁኔታ ነው የተጠናቀቀው። በትግሉ ውስጥ ትልቁና ወሳኙ ነገር የደርግን ኃይል መደምሰስ ቢሆንም ከዚያ በመቀጠል ለግጭት፣ ለድህነትና ለሰላም እጦት ይዳርገን የነበረው ሁኔታ በ1987 ዓ.ም በፀደቀው ህገ መንግሥታችን መፍትሔ አግኝቷል። በዚህም ያ የተደመሰሰው ሥርዓት ዳግመኛ እንደማይመለስ እርግጠኛ የተሆነበት ሁኔታ ነበር የነበረው፡፡ ለአሁኑ ልማትና ዴሞክራሲያችን መሰረት የሆነውም ይሄው ህገ መንግስታችን ነውና በትግሉ የደርግ ሥርዓትን መደምሰስ አንዱ ጉዳይ ሆኖ ሁለተኛው ደግሞ ህገ መንግስቱ መጽደቁ ነው፡፡ ከዚህ አንፃር ሲታይ ህገ መንግስቱ ለአሁኑ ልማት፣ ሰላምና ዴሞክራሲ መሰረት መሆኑም እሙን ነው። በአጠቃላይ ትግሉን በሁለት ምዕራፍ ነው ከፍለን ማየት ያለብን፡፡

አንዱ የትጥቅ ትግሉ ጊዜና ከዚያ በኋላ ያለው ነው፡፡ በእነዚያ አስራ ሰባት የትግል ዓመታት ውስጥ ደግሞ ሁለት ነገሮችን ማየት እንችላለን። ትግሉ ከትንሽ ወደ ትልቅ ነው ያደገው። በጥቂቱ ተጀምሮ አድጐ ደርግን መደምሰስ የሚችል ኃይል መገንባት ችሏል። ዋናው ነገር ግን ትግሉ በጥቂት ታጋዮች መጀመሩ አይደለም። እነዚህ ታጋዮች የትጥቅ ትግሉን ሲያስኬዱ የነበረው ነባራዊው ሁኔታ የተመቸ መሆኑ ነበር። በዚህ ውስጥ ደግሞ ዋናው ህዝቡ ነው። ትግሉ ህዝቡ የደገፈው ነበር። ህዝቡ ትግሉ ሲጀምር ተቀበለው፣ ብሎም አሳደገው፡፡እና ትግሉ ወደ ድል ሊሸጋገር የቻለው በዋናነት በወቅቱ ሲደረጉ የነበሩት ውጊያዎች የትግሉን የፖለቲካ ዓላማ ያገለግሉ ስለነበር ነው። ማለትም ውጊያዎቹ በሙሉ የትግሉን የፖለቲካ ዓላማ ያገለግሉ ስለነበር ነው ለድል የበቁት። በዚህ ሁኔታ እንግዲህ ትግሉ እያደገ ሄዶ በስኬት ለመጠናቀቅ በቅቷል። እኔ በዚህ የትግል ሂደት ውስጥ የማልረሳውና የማስታውሰው የህዝቡን ተሳትፎ ነው። ህዝቡ ትግሉን ፈጠረው፣ አሳደገው፣ በድልም እንዲጠናቀቅ አደረገው። እና ለትግሉ ድል ወሳኝ የነበረው ህዝቡ ነው። ድሉም የህዝቡ ነው። ስለዚህ ትግሉ በርካታ መስዋዕትነት የተከፈለበት ነው። እና የማልረሳው የህዝቡን ታሪክ ሰሪነትና ወሳኝነት ነው።

ዘመን፡- እርስዎ ዛሬ ላይ ሆነው ሲያዩት የዚያን መራራ ትግል ውጤት እንዴት ይገ ልጹታል?Photo - General samora yenus

ጀኔራል ሳሞራ፡- በትግሉ ወቅት እያንዳንዱ ስራና ዓመት የዕድገት ዓመት ነበር። ይሄ ዕድገት ደግሞ መስዋዕትነት እየተከፈለበት ሲመጣ የነበረ ዕድገት ነበር። ብዙ ውጣ ውረድ የነበረበት ነው። ሆኖም ድርጅቱና ህዝቡ እየተማረ ዕድገት እያሳየበት የመጣበት ሁኔታ ነበር የነበረው፡፡ በመጨረሻም በድል ተጠናቀቀ። በድል መጠናቀቁ የዕድገቱ ውጤት ነው። በድል ከተጠናቀቀም በኋላ እንዳልኩት ሁለት ነገር ሆኗል። አንዱ ጨቋኝ የደርግ ሥርዓት ሙሉ ለሙሉ ተደመሰሰ። ሁለተኛው የኢትዮጵያ ህዝቦችን ለግጭት ይዳርጉ የነበሩ የመልካም አስተዳደር፣ የድህነትና የኋላቀርነት ችግሮችን ለመፍታት መሰረት የሆነው ህገ መንግሥት ፀደቀ። ስለዚህ የመጀመሪያው ወሳኙ ውጤት ይሄ ነው። በዚህም ህዝቡ ህገ መንግሥቱ ያጐናፀፈውን መብት እንዲያጣጥም ያደረገ ነው። ስለዚህ በዚህ ህገ መንግሥት ህዝቡ ዴሞክራሲያዊና ሰብአዊ መብቱ ተረጋግጧል። የእነዚህ መብቶች ባለቤትም ሆኗል። ይሄም ሰፊው ማህበረሰብ በፍላጐቱና በመፈቃቀድ ለአንድ ኢኮኖሚ እንዲሰራ አድርጐታል። እና ዛሬም የእዚህ ውጤት የሆነውን ሰላምና ልማት እያረጋገጥን የሄድንበት ሁኔታ ነው ያለው። ስለሆነም ውጤቱን የምናየው ነው። ያገኘነው ሰላም፣ ልማትና ዴሞክራሲ ነው፡፡ እስካሁን ትግል እያልኩ የጠቀስኩት ጠመንጃውን ሳይሆን ህዝቡን ነው። የህዝቡን የትግል ውጤት ነው።

ዘመን፡- እርስዎ እንደ አንድ ታጋይ በዚያ ወቅት የነበሩ የትግል ጓዶችዎን ፅናት፣ ጀግንነትና ተጋድሎ እንዴት ይገልፁታል?

ጀኔራል ሳሞራ፡- የነበረው ጀግንነትና ፅናት እጅግ የሚደንቅ ነበር። ከፍተኛ የኃይል ሚዛን ልዩነት እያለም በወቅቱ የነበረው ታጋይ ጥቂት ቢሆንም እንደምናሸንፍ እርግጠኛ ነን ብሎ ይታገል ነበር። የኃይል ሚዛኑን ስናይ ያኔ የደርግ ጦር በመቶ ሺዎች የሚቆጠር ነበር። ታጋዩ ግን ሺም አይሞላም። መቶም፣ ስልሳም ሆኖ ሳለ ነገር ግን ሺ ሆኖ እናሸንፋለን የሚል ወኔ ነበረው። ይህን ይልበት የነበረው ምክንያት ግን ልዩ ጀግንነት ስለነበረው አይደለም። ይሔ ትግል የህዝብ ነው ብሎ ስላመነና የማያቋርጥ የህዝብ ድጋፍ እንደነበረው በደንብ ያውቅ ስለነበር ነው። ህዝቡ ከጐኑ እንደተሰለፈም ያውቅ ነበር። ይሔ ህዝብ የትግራይ ህዝብ ብቻ አይደለም። ኢህአዴግ ከተመሰረተ በኋላም በሄደበት ሁሉ ህዝቡ ከታጋዩ ጐን ነበር። እና የታጋዩ ቁጥር ጥቂት ቢሆንም የህዝቡ ድጋፍ ግን ብዙ ነበር። የጀግንነቱና የድሉ ምን ጭም ይሔ ነው የነበረው።

የኢትዮጵያ ህዝብም ጠመንጃ የታጠቀ ጓደኛ ያገኘ ውም በዚህ ትግል ነው። የኢት ዮጵያ ህዝብ ከዚህ ትግል በፊት ጠመንጃ የታጠቀ ጓደኛ አልነ በረውም። ጠመንጃ ይዞ የሚያ ስፈራራውና የሚያንቀጠቅጠው እንጂ እንደ ጓደኛ የሚያየው አልነበረም። የኢትዮጵያ ህዝብ ጠመንጃ የያዘ የሚያከብረው ጓደኛ ያገኘው በዚህ ትግል ነው። እና ትግሉ ከህዝቡ ጋር በጥብቅ የተሳሰረ ነበር። ይሔ አሁንም እንደቀጠለ ነው። ዛሬም ሠራዊቱ ህዝባዊ ባህሪውን እንደቀጠለበት ነው ያለው። የህዝቡን ጥቅምና ፍቅር የሚያስቀድም ሠራዊት ነው ያለን። እና ያኔ ጥቂት ሆኖ ግን ብዙ መሆንን የሚያውቅ ታጋይ ነው የነበረው። ይሔ ደግሞ የጀግንነቱም የድሉም ምንጭ ነው። መስዋዕትነትን ለመክፈል የተዘጋጀና ለዓላማው የተሰለፈ ቁርጠኛም ነበር። በወቅቱ እያንዳንዱ ውጊያና ጦርነት የፖለቲካ ዓላማውን የሚያገለግል ስለነበር እያንዳንዱ ታጋይ ለዓላማውና ለመስዋዕትነት ዝግጁ ነበር። እና የነበረው የዓላማ ፅናት መገለጫ አልነበረውም።

በትግሉ ሂደት በርካታ ችግሮች ያጋጥሙ ነበር። በወቅቱ የነበሩትን ችግሮች ሁሉ አሁን ማስታወስ ባይቻልም ችግር ሲያጋጥም ግን ችግሩን እንወጣዋለን የሚል አመለካከት የሁሉም ነበር። ለማንኛውም ችግር የሚሸነፍ አልነበረም፡፡ እንደ ድርጅትም እንደ ህዝብም እንደ ቡድንም ችግር የሚያሸንፈው አልነበረም። እና በወቅቱ ታጋዩ እነዚህን ባህሪያቶች የተላበሰ ነበር። ህዝባዊ ፅናትና የህዝብ ፍቅር የነበራቸውና ሁሌም የሚማሩ ነበሩ። ሁሉም ለእኔ ጓደኞቼ ናቸው። ሁሉም አብረውኝ የነበሩ ናቸው። ህዝቡም ታጋዩም እንደጓደኛዬ ነበሩ።

ዘመን፡- ሠራዊታችን በሳይንስና ቴክኖ ሎጂም ሆነ በብቃቱና በአቋሙ በጥሩ ደረጃ ላይ እንዳለ ሁሉም የሚመሰክሩለት ሀቅ ነው። በልማቱም ተሳታፊና ጥሩ ስነ ምግባር ያለው መሆኑ ለአገራችን ትልቅ ኩራት ነው። ትልቅ ስምም ያለው ነው። ይሔንን እርስዎ እንዴት ይገልፁታል? ምስጢሩስ ምንድን ነው?

ጄኔራል ሳሞራ፡- ዋናው ነገር ሠራዊቱ እንደእዚህ እንዲሆን ያደረገው አንደኛ የሚገነባበት ዓላማ ላይ ግልፅነት መፍጠር ስለተቻለ ነው። ሠራዊቱ የሚገነባበት የመጀመሪያው ዓላማ ለሰላም ነው። በእኛ አገር ሁኔታ ሠራዊት የሚገነባው የመጀመሪያው አላማ ለሰላም ነው። የኢትዮጵያ ህዝቦች ተስፋ ሰላምና ልማት ነው። ሌላ ተስፋ የላቸውም። ሁለተኛው የሚገነባበት ዓላማ የጦርነት አደጋ ሲያጋጥም ቶሎ ተዋግቶ ማሸነፍ ነው። ሦስተኛው ዓላማ ዴሞክራሲያዊ አመራርን ማረጋገጥ ነው፡፡ ስለዚህ የሚገነባበት ዓላማ ግልፅነት አለው ማለት ነው። ሌላው ይሔ ሠራዊት በትጥቅ ትግሉ ወቅት የነበሩ እሴቶቻችንን የወረሰ ነው። እነኚህም እሴቶች ህዝባዊነት፣ ህዝባዊ ፍቅር፣ ዴሞክራሲያዊነት፣ ከራስ በፊት ህዝብን ማስቀደም እና ማንኛውንም ሥራ በላቀ ውጤት መፈፀም ናቸው። እነኚህን እሴቶች ወርሷል። የራሱም አድርጓቸዋል። አሁንም የራሱ ናቸው፡፡ ህገ መንግሥታዊ ሥርዓቱም ይህን እንዲወርስና እንዲጠብቅም ያደርገዋል።

ህገ መንግሥቱ በመሰረቱ የኢትዮጵያ ሕዝቦች በመፈቃቀድ ይበጀናል ብለው የመሰረቱት ነው። ስለዚህ ህገ መንግሥቱን መጠበቅ ማለት የህዝቡን ጥቅም መጠበቅ ማለት ነው። ህዝቡን ማስቀደም ማለት ነው። ስለዚህ ይሄ ህዝባዊነቱን ጠብቆ እንዲቀጥል ያደርገዋል ማለት ነው። እና እንዳልኩት ዋናው ነገር የሚገነባበት ዓላማ ላይ ግልፅነት ተፈጥሯል። በሌላ በኩል ህገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን መጠበቅ ማለት የህዝባችንን ጥቅምና ሉአላዊነት ማስጠበቅ ማለት ስለሆነ እነኚህን እሴቶች የራሱ አድርጐ እንዲቀጥል ያደርገዋል። ማንኛውም ህዝብ ለእሱ አንድ ነው፤ የዳርፉርም ይሁን የሌላው። ስለሆነም የተሰጠውን ግዳጅ በውጤት ይፈፅመዋል፡፡  (ምንጭ፡- አዲስ ዘመን – የካቲት 2007)

*********

Content gathered and compiled from online and offline media by Hornaffairs staff based on relevance and interest to the Horn of Africa.

more recommended stories