የመኢአድ ፓርቲ ውዝግብ| ምርጫ ቦርድ ለነአበባው መሐሪ ቡድን የፈረደበት ሙሉ ቃል

ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የተሰጠ መግለጫ

መላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት /መኢአድ/ በተመለከተ

መግቢያ

በቦርዱ ዕዉቅና ያገኘዉና በስራ ላይ ያለዉ የፓርቲው መተዳደሪያ ደንብ የ2001 ዓ.ም ስለመሆኑ፣ ደንቡ የፓርቲዉ አመራሮችም ሆነ አባላት መብትና ግዴታቸዉን አዉቀዉ በእንቅስቀሴዉ ዉስጥ ተሳታፊ እንዲሆኑ ለማስቻል እንደሆነ፣ በአመራሩ/በበታች አካሎችና አባሎች መካከል ዴሞክራሲያዊ የሆነ መከባበር ላይ የተመሰረተ አሰራር ለመፍጠር እንደሆነ በግልጽ ሰፍሮ ይገኛል፡፡ መኢአድ በአሁኑ ጊዜ በሁለት ቡድን በመከፈሉ የፓርቲዉ የስራ እንቅስቃሴ ተገቷል በሚባል ደረጃ ያለ ስለመሆኑ እንረዳለን፡፡

አሁን ተመርጠናል በሚሉት በእነ አቶ ማሙሸት አማረ ቡድን የተፈጸሙ የህግ ጥሰቶችን እንደሚከተለዉ ማንሳት ይቻላል፡፡

1ኛ. የፓርቲዉ ፕሬዚደንትን ከጠቅላላ ጉባኤ አባላት መካከል መመረጥ እንዳለበት፣ የፓርቲዉ ተ/ምክትል ፕሬዚደንት ደግሞ የጠቅላላ ጉባኤ አባል መካከል ከመሆኑ ባሻገር የማዕከላዊ ምክር ቤት አባል መሆን እንዳለበት የፓርቲዉ ደንብ በአንቀጽ 7.4 እና 4.2.2 ስር ተደንግጎ ይገኛል፡፡ ይሁንና አሁን የተመረጡት ግለሰቦች በ2003 ዓ.ም ከፓርቲዉ አባልነት የተሰረዙ ከመሆኑም በላይ ለሶስት ተከታታይ ወራት የአባልነት መዋጮ ያልከፈለ አባልነቱ ቀሪ እንደሚሆን ስለሚደነግግ ለዚህ ኃላፊነት መስፈርቱን የማያሟሉ ሰዎች በመመረጣቸዉ የህግ ጥሰት ተፈጽሟል፡፡Photo-Election-board-chairs-top-and-AEUP-faction-leaders-Mamushet-Amare-and-Abebaw-Mehari.jpg

2ኛ. ፓርቲዉ አካሂጃለሁ የሚለዉን የጠቅላላ ጉባኤ ዉጤት ሪፖርት፣ የምርጫ መወዳደሪያ ምልክት ጥቆማ ሲያደርግ እና ሌሎች የፓርቲዉን ወሳኝ ክንዉኖችን ሲያሳዉቅ በፓርቲዉ ማህተም የተረጋገጠ ሰነድ ማቅረብ እንዳለበት የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባ አዋጅ ቁጥር 573/2000 አንቀጽ 20/1/ በግልጽ ያስቀምጣል፡፡ ይሁንና ፓርቲዉ በዚህ አግባብ አረጋግጦ ሊያቀርብ አልቻለም፣ ይባስ ብሎ ህጋዊ ማህተም በሌሎች የፓርቲዉ ቡድን እጅ መኖሩ እየታወቀ ተመሳሳይ ማህተም በማስቀረጽ የህግ ጥሰት ፈጽሟል፡፡

3ኛ. የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባ አዋጅ ቁጥር 572/2000 አንቀጽ 19/2/ለ// ስር የፓርቲዉ ጠቅላላ ጉባኤ ሲካሄድ ወይም ሌሎች ወሳኝ ክንዉኖች ሲኖሩ የቦርዱ ተወካይ መገኘት እንዳለበት ከመደንገጉም በላይ የተለመደ አሰራር መሆኑ ይታወቃል፡፡ የቦርዱ ተወካይ በተገለፀው ቀን በመገኘት ለመታዘብ የሞከሩ ሲሆን አብዛኛው ጊዜ በንትርክና ጭቅጭቅ የታጀበ እንደነበር፣ ስብሰባው በአግባቡ ሊመራ ባለመቻሉ የፓርቲው ኃላፊዎች ምርጫ ለቦርዱ ባልተገለፀበት ቀጣይ ቀን ስለነበር የአካሄድ ችግር ነበረበት፡፡

4ኛ. የፓርቲዉ መተዳደሪያ ደንብ አንቀጽ 10.2.2 የፓርቲዉ መደበኛ፣ ልዩ እና አስቸኳይ ጠቅላላ ጉባኤ መጠራት ያለበት በፓርቲዉ ማዕከላዊ ምክር ቤት መሆኑን ይደነግጋል፡፡ ሆኖም ግን ፓርቲዉ የጠራቸዉን ጠቅላላ ጉባኤዎችና ከቦርዱ ጋር የተደረጉትን የደብዳቤዎች ልዉዉጥ ስንመለከት የፓርቲዉ አመራር ማን እንደሆነ ማወቅ እስኪያስቸግር ድረስ አቶ አበባዉ መሐሪ፣ ኢ/ር ኃይሉ ሻውል እና አቶ ማሙሸት አማረ ያለቦርዱ ዕዉቅና ሲፈራረቁበት ተመልክተናል፡፡ ይሄም የህግ ጥሰት ነዉ፡፡

በሌላ በኩል

በእነ አቶ አበባው መሐሪ ቡድን በኩል ያለዉን እንቅስቃሴ ስንመለከት የሚከተሉትን ነጥቦችን ማንሳት ይቻላል፡፡

በ2005 ዓ.ም በተደረገ ጠቅላላ ጉባኤ የተመረጡ ስለመሆኑ፣ የፓርቲዉ ጠቅላላ ጉባኤ አባልነታቸዉ ላይ የተነሳ ክርክር የሌለ ስለመሆኑ፣ በወቅቱ የጠቅላላ ጉባኤዉን ሪፖርት ለቦርድ በትክክለኛዉ የፓርቲዉ ማህተም አስደግፈዉ ያቀረቡ ስለመሆኑ፣ ቦርዱ እንዲሟላ የጠየቀዉ የጠቅላላ ጉባኤ ብዛት እንደነበርና ይሄንን የተሰጠዉን የቦርዱን አመራር ተከትሎ 600 አባላት እንዲሆን በሚል በማስወሰን ያሳወቁ ስለመሆኑ፣ በወቅቱ የቦርዱን ህጋዊ አመራር ለመተግበር የተንቀሳቀሰ ቡድን ስለመሆኑ መረዳት እንደሚቻል፣ በስብሰባው ላይ የተገኙት የጠቅላላ ጉባኤ አባላት በወቅቱ ሲታይ 285 ስለነበር እንዲያስተካክሉ በቦርዱ እንደተገለጸ፣ እነ አቶ አበባዉ መሐሪም ይሄንን ተከትሎ የተረሱ ተሳታፊዎች ናቸዉ በሚል የ41 ሰዎች ስም ዝርዝር እንዳቀረቡና በወቅቱ ቀደም ሲል አንድ ላይ ተጠቃሎ ባለመቅረቡ ተቀባይነት እንዳላገኘ ተገልጾ እንደነበር እናስታዉሳለን፡፡

አሁን ጉዳዩን በጥልቀትና በስፋት ስንመረምር በኋላ የመጣዉ የጠቅላላ ጉባኤ ተሳታፊዎች ዝርዝር የጠቅላላ ጉባኤ አባላት በመሆናቸዉ፣ አንዳንዶቹ አባላት ብቻ ሳይሆኑ ኢ/ር ኃይሉ ሻወልን ጨምሮ በአመራር ላይ የነበሩ ሰዎች ስለመሆናቸዉ በመረጋገጡ እና አሁንም ቢሆን ህጋዊ የፓርቲዉን ማህተም በመጠቀም ከቦርዱ ጋር ግንኙነት እያደረገ ያለ በመሆኑ ሰነዱ ተቀባይነት እንዲያገኝ ከስምምነት ተደርሷል፡፡ ከዚህ ተነስተን ጉዳዩን ስንመረምር ከ600 የጠቅላላ ጉባኤ አባላት መካከል 326 መገኘታቸዉን ለመገንዘብ ችለናል፡፡ በመሆኑም አቶ አበባዉ መሐሪ የተመረጡበት የ2005 ዓ.ም ጠቅላላ ጉባኤ ዉጤት ዕዉቅና እንዲያገኝ ተወስኗል፡፡

በአጠቃላይ ከላይ እንደተመለከተዉ ፓርቲዉ በሁለት ቡድን የተከፈለ ስለመሆኑ፣ ከእነዚህ ቡድኖች ዉስጥ ደግሞ የእነ ማሙሸት አማረ ቡድን ከላይ በዝርዝር እንደተገለጸዉ ራሳቸዉም ለመመረጥ በዉስጠ ደንባቸዉ መሠረት መስፈርቱን የማያሟሉ ከመሆኑም በላይ የጠቅላላ ጉባኤዉ ሂደት በአጠቃላይ እና የአመራር ምርጫ ሂደቱ በተለይ በርካታ የፓርቲዉን ደንብ እና የምርጫ ህጉን ድንጋጌዎች የጣሱ በመሆኑ ዕዉቅና ሊሰጣቸዉ እንደማይገባ ቦርዱ ወስኗል፡፡

በሌላ በኩል አቶ አበባ መሐሪ የተመረጠበት አግባብ የፓርቲዉን ደንብ ባከበረ መልኩ በመሆኑ የእርሳቸዉን የምርጫ ሂደትም ሆነ የተመረጡበትን የጠቅላላ ጉባኤ ዉጤት ሪፖርት በቦርዱ ዕዉቅና ተሰጥቶታል፡፡

የሁለቱም ፓርቲዎች ጉዳይ ሲጠቃለል ቦርድ ጥር 21 ቀን 2007 ዓ.ም ባካሄደው በ005/2007 አስቸኳይ ስብሰባ አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትሕ ፓርቲ /አንድነት/ እነ አቶ ትግስቱ አወሉ እና የመላ ኢትዮጵያዊያን አንድነት ድርጅት /መኢአድ/ በተመለከተ ደግሞ የእነ አቶ አበባዉ መሐሪ ፓርቲዉን በመምራት ወደ ምርጫዉ እንዲገቡ በአንድ ድምፅ ወስኗል፡፡

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ

ጥር 21 ቀን 2ዐዐ7 ዓ.ም.

አዲስ አበባ

*********

[አንድነትየሚመለከተውን የመግለጫውን ክፍል እዚህ ጋር ያንብቡ፡፡]

Content gathered and compiled from online and offline media by Hornaffairs staff based on relevance and interest to the Horn of Africa.

more recommended stories