መኢአድ – ቦርዱ የሰጠኝን የቤት ስራ የጨረስኩ በመሆኔ የምጠራው ጉባኤ የለም

(ጥላሁን ካሳ)

በአቶ ማሙሸት አማረ የሚመራው የመላው ኢትዮዽያ አንድነት ድርጅት/መኢአድ/ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ የሰጠኝን የቤት ሰራ ቀደም ሲል አጠናቅቂያለሁ ከዚህ በኋላ የምጠራው ጠቅላላ ጉባኤ የለም አለ ዛሬ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ።

የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ በመጪው ማክሰኞ ጥር 19 ከአመራር ምርጫ ጋር ያሉበትን ችግሮች ፈቶ ሪፖርት እንዲደረግለት ነበር ከሁለት ሳምንታት በፊት አስገንዝቦ የነበረው።

የቦርዱ ጥቅል መልዕክት ፓርቲው ላወጣው ህግ ይገዛ የሚል ይዘት ያለው ነው።

ፕሬዝዳንትና ተቀዳሚ ምክትል ፕሬዝዳነት ሆነው በጽህፈት ቤት የቀረውን ፓርቲ የሚመሩት አቶ ማሙሸት አማረ እና ዶክተር ታዴዎስ ቦጋለ ከፓርቲው የተባረሩ እና በፓርቲው ደንብ መሰረት መዋጮ ያልከፈሉ መሆናቸውን በቀዳሚነት ተጣሰ ለተባለው ህግ ምክንያት ናቸው በማለት ጠቅሷል። Logo - AEUP (All Ethiopia Unity Party)

ምክትል ተቀዳሚ ፕሬዝዳንት ናቸው የሚባሉት ዶክተር ታዴዎስ ቦጋለ የማዕከላዊ ምክር ቤት አባል ያልነበሩ በመሆናቸው ራሱ ፓርቲው እገዛበታለሁ ብሎ ለቦርዱ ካሳወቀው አንቀጽ 7 ነጥብ 4 እና 4 ነጥብ 2 ውጪ መሆናቸውንም ቦርዱ ቀደም ሲል በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ አስታውቆ እንደነበር ይታወሳል።

ፓርቲው በጠራው አስቸኳይ ጠቅላላ ጉባኤ ሌላ ደንብ መጣሱንም የብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ፕሮፌሰር መርጋ በቃና በጋዜጣዊ መግለጫቸው ማስታወቃቸው አይዘነጋም።

ፕሮፌሰሩ ፓርቲው ቀደም ሲል የጣሳቸውን ደንቦች አስተካክሎ ለየብቻ የተከፋፈሉ ክንፎች አንድ ላይ ሆነው እንደገና ጠቅላላ ጉባኤ ጠርተው የውስጥ ችግሮቻቸውን እንዲፈቱ ተጨማሪ ጊዜ መሰጠቱንም በድጋሚ አብራርተዋል።

በተሰጣቸው የሁለት ሳምንታት ጊዜ የመኢአድ ሁለቱም ክንፎች አንድ ላይ ሆነው የውስጥ ችግሮቻቸውን በመፍታት፥ እንደገና ጠቅላላ ጉባኤ በመጥራትና ውጤቱን ሪፖርት በማድረግ ምርጫውን ይቀላቀላሉ የሚል ነበር የቦርዱ ማሳሰቢያ።

ቦርዱ የትኛውም ፓርቲ ለተሻሻለው የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዘገባ አዋጅ ካልተገዛ በየደረጃው የተቀመጠው እርምጃ ይወሰድበታል በማለት በተደጋጋሚ መግለጹም አይዘነጋም።

ይሁን እንጂ በአቶ ማሙሸት አማረ የሚመራው ቡድን ዛሬ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ በ60 ቀናት ወስጥ ሁለት ጊዜ ጠቅላላ ጉባኤ ጠርተን የቤት ስራችንን ሰርተናል የሚቀረን ተግባር የለም ነው ያለው።

መሃል ቁጭ ብለው ከግራና ቀኝ አመራሮቻቸውን አስቀምጠው መግለጫውን ሲመሩ የነበሩት ተቀዳሚ ፕሬዝዳንቱ ዶክተር ታዴዎስ ቦጋለም ከዚህ በኋላ የሚካሄድ ጠቅላላ ጉባኤ እንደሌለ ነው ያስታወቁት።

የሌላኛው ቡድን ፕሬዝዳንት ነኝ የሚሉት አቶ አበባ መሃሪ ለጣቢያችን እንዳሉት ህጋዊው የመኢአድ ፕሬዝዳንት እኔ ነኝ የምርጫ ቦርድ ውሳኔን እጠብቃለው ይላሉ።

የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ፓርቲው በውስጡ አለመግባባት ፈትቶ እና ጠቅላላ ጉባኤ አካሂዶ አመራር መርጦ እንዲያሳውቅ የሰጠው የጊዜ ገደብ የፊታችን ማክሰኞ ይጠናቀቃል።

***********

ምንጭ፡- ፋና፣ ጥር 12-2007

 

Content gathered and compiled from online and offline media by Hornaffairs staff based on relevance and interest to the Horn of Africa.

more recommended stories