‘የእነአየለ ስሜ አንድነት’ ፕ/ት ትዕግስቱ አወሉ:- "ብቸኛ አማራጭ ምጣዱን መስበር ነበር"

(ፋኑኤል ክንፉ)

ታህሳስ 28 ቀን 2007 ዓ.ም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ባካሄደው አስቸኳይ ስብሳባ አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ የፈጸማቸውን የሕግ ጥሰቶች በመመርመር እስከ ጥር 4 ቀን 2007 ዓ.ም ድረስ በሕጉና እና በፓርቲው መተዳደሪያ ደንብ መሰረት አሟልቶ እንዲያቀርብ በደብዳቤ ማሳወቁ ይታወቃል። ይህን የቦርዱ ጥያቄ ባይሟላ ቦርዱ የመጨረሻ ሕጋዊ እርምጃ በፓርቲው ላይ እንደሚወስድ በደብዳቤ ቁጥር አ/573/ፓ4/ጠ405 በተፃፈ ደብዳቤ መግለጽን ለማወቅ ተችሏል።

የቦርዱን ማሳሰቢያ ከግምት በመውሰድ አንድነት ፓርቲ ጥር 1 ቀን 2007 ዓ.ም በፃፈው ደብዳቤ የሕግ እና የውስጥ ደንብ ሁኔታዎችን የመመርመር ሥልጣን ያለው ጠቅላላ ጉባኤ መሆኑን ጠቅሶ፣ አስቸኳይ ጠቅላላ ጉባኤውን ጥር 3 ቀን 2007 ዓ.ም ቀበና መድሐኒዓለም አጠገብ በሚገኘው ጽ/ቤት ከጠዋቱ በ3፡00 ሰዓት ጀምሮ ለማድረግ መወሰኑን ለምርጫ ቦርድ በደብዳቤ አስታውቋል።

በሌላ መልኩ ምርጫ ቦርድ ግልባጭ እያለ ለሚያሳውቃቸው “የእነአቶ አየለ ስሜነህ” የአመራር ቡድን በበኩላቸው፣ ታህሳስ 30 ቀን 2007 ዓ.ም በፃፉት ደብዳቤ ፓርቲው ጠቅላላ ጉባኤውን ጥር 3 ቀን 2007 ዓ.ም ከጠዋቱ 3፡00 ሰዓት ጀምሮ በሳሬም ሆቴል የመሰብሰቢያ አዳራሽ እንደሚያደርጉ በደብዳቤ ለቦርዱ አስታውቀዋል።

ከላይ የሰፈሩት ሁለቱ አካሎች በተለያየ ቦታዎች ጉባኤ እንደሚያካሂዱ ማሳወቃቸውን አግባብነት የሌለው መሆኑን ገልፃ፣ ምርጫ ቦርድ በሁለቱም ጠቅላላ ጉባኤ ላይ ታዛቢ ሳይልክ ቀርቷል።

ዝግጅት ክፍላችን ከላይ የሰፈረው ውዝግብ እንደተጠበቀ ሆኖ፣ አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ በጠራው አስቸኳይ ጠቅላላ ጉባኤ ላይ በመገኘት ያጠናከረውን ዘገባ እና በእነአየለ ስሜ ጠቅላላ ጉባኤ የተመረጡትን ፕሬዝደነት ቃለ ምልልስ ይዞ ቀርቧል። ዘገባው ሁለቱንም አካሎች በተቻለ መጠን ሽፋን የሰጠ ሲሆን፣ አንብቦ ፍረድ መስጠት ለአንባቢዮቻነን ትተነዋል።Tigistu Awelu's election as President of UDJ Andinet party

አቶ ትዕግስቱ አወሉ ይባላሉ። በትምህርት ምርምርና ዴቬሎፕመንት የማስተርስ ዲግሪ አላቸው። ሃያ አመታት በመምህርነት አገልግለዋል። በአሁኑ ወቅትም በግል ዩኒቨርስቲዎች በመምህርነት እያገለገሉ ይገኛሉ። በአንድነት ፓርቲ ውስጥ የፖለቲካ ጉዳይ ቋሚ ኮሚቴ ም/ኃላፊ ሆነው ሰርተዋል። በእነአየለ ስሜነህ በተጠራው አስቸኳይ ጠቅላላ ጉባኤ የአንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ ፕሬዝደነት ሆነው ተመርጠዋል።

እሳቸው እንደሚሉት “ከመነሻው በተፈጠረው ልዩነት ውስጥ አልነበርኩም። ታህሳስ 3 ቀን 2007 ዓ.ም ከተደረገው ጠቅላላ ጉባኤ በኋላ ግን ከእነአየለ ቡድን ጋር ለመቀላቀል ወስንኩ። “ደንብ ተጥሷል” የሚል ተደጋጋሚ ጥያቄ ለጠቅላላው ጉባኤ ባቀርበም ሰሚ አጣሁ። ባልጸደቀው የ2006 ዓ.ም ደንብ ላይ፣ ሌላ ደንብ ማሻሻል አንችልም፣ ፓርቲው ለአደጋ ይጋልጣል፣ የሚል ተቃውሞ በተደጋጋሚ በጠቅላላው ጉባኤ ላይ አሰምቻለሁ። ሰሚ ግን አጣሁ። በጉባኤው ውስጥ የማይታረሙ ሴረኞች መኖራቸውን ተረዳሁ። በመጨረሻም በፓርቲው ውስጥ የተዘረጋ የፖለቲካ ሴራ መኖሩን በመገንዘቤ፣ ራሴን ከዚህ የሴራ ቡድን ለማራቅ ወስኜ ለቅቂያለሁ” ብለዋል። ዝግጅት ክፍላችንም ካቀረቡት ቅሬታ ጋር በተያያዙ ጉዳዮች እና በዲ-አፍሪክ ሆቴል ባለፈው እሁድ ዕለት ስለተደረገው አስቸኳይ ጠቅላላ ጉባኤ የምርጫ ሂደት መነሻነት ቃለ መጠይቅ አድርጓላቸዋል።

ሰንደቅ፡- አንድነት ፓርቲን ወክላችሁ ጠቅላላ ጉባኤ ለማድረግ ምን ዓይነት ሕጋዊ መሰረት አላችሁ?

አቶ ትዕግስቱ፡- ጠቅላላ ጉባኤ የመጥራት ሕጋዊ መሰረት ያለው አካል ይሄኛው ነው፤ ያኛው ነው ለማለት ነገሮችን በዝርዝር መመልከት ተገቢ ነው። ወደኋላ ብዙ ርቀት ሳንጓዝ፣ ይህ ከደንብ ውጪ ስልጣን የያዘው የእነአቶ በላይ ቡድን በታህሳስ 27 በምርጫ ቦርድ በኩል ከእኛ ጋር ያለውን ልዩነት ለመፍታት በጋራ አስቀምጦን ለውይይት ጋብዞን ነበር። በዚህ የውይይት መድረክ ላይ የእነአቶ በላይ ቡድን ያሳየው ባሕሪ ሁሉንም ነገር ወደ ተስፋ አልባ መስመር መግፋቱን ተረዳን። ምርጫ ቦርድም ቀን ቆርጦ ውይይት አድርጋችሁ ልዩነታችሁን ፈታችሁ ቅረቡ አለ። በተሰጠው ቀነ ገደብም ለመቀራረብ ያደረግነው ጥረት ከንቱ ሆነ። የነበረን የመጨረሻ አማራጭ የራሳችን ጠቅላላ ጉባኤ ጠርተን ፓርቲውን ማዳን ብቻ ነበር። ይህን ለማድረግ ጠቅላላ ጉባኤ ጠራን።

ሰንደቅ፡- ለሁለታችሁም ነው ጠቅላላ ጉባኤ እንድትጠሩ ምርጫ ቦርድ አቅጣጫ የሰጣችሁ?

አቶ ትዕግስቱ፡- በጋራ ጠቅላላ ጉባኤ እንድንጠራ ነው አቅጣጫ የሰጠን። ሆኖም ግን ይህ ሊሳካ አልቻለም።

ሰንደቅከእነሱ በኩል በጠቅላላ ጉባኤ ስብሳባ ላይ እንድትገኙ ጥሪ አልቀረበላችሁም?

አቶ ትዕግስቱ፡- የእነበላይ ቡድን ጠቅላላ ጉባኤ እኛን ሊጠራ አይችልም።

ሰንደቅ፡- እንዴት?

አቶ ትዕግስቱ፡- ምርጫ ቦርድ የሰጠው አቅጣጫ ችግራችሁን በጋራ ፍቱና ጠቅላላ ጉባኤ አድርጋችሁ አሳውቁኝ ነው ያለው። ችግራችን ለመፍታት በተለያዩ ነባር አባላት የተደረገው ሙከራ ውጤት አላመጣም። ስለዚህም በራሳችን ጠቅላላ ጉባኤ ጠርተን የመጨረሻ ውሳኔ ከምርጫ ቦርድ እየጠበቅን ነው።

ሰንደቅ፡- ጠቅላላ ጉባኤውን የጠራችሁት በየትኛው ደንብ መሰረት ነው?

አቶ ትዕግስቱ፡- ጠቅላላ ጉባኤውን የጠራነው በ2004 ዓ.ም ብርሃን ለአንድነትና ለዴሞክራሲ ፓርቲ ከአንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ ጋር ባደረገው ውህደት ወቅት በጸደቀው መተዳደሪያ ደንብ መሰረት ነው። ይሄውም ጥር 30 እና ታህሳስ 1 ቀን 2004 ዓ.ም በዲያ ፍሪክ ሆቴል በተጠራው የአንድነት ጠቅላላ ጉባኤ ላይ የጸደቀው መተዳደሪያ ደንብ ነው። በዚሁ ጠቅላላ ጉባኤ ላይ ዶክተር ነጋሶ ጊዳዳ የፓርቲው ፕሬዝደነት ሆነው መመረጣቸው ይታወሳል። ይህ ደንብ በምርጫ ቦርድ በኩልም በሕጋዊነት ፀድቆ ያለ ደንብ መሆኑም ይታወቃል።

ሰንደቅ፡- በ2004 ዓ.ም መተዳደሪያ ደንባችሁ የጠቅላላ ጉባኤ ኮረም ብዛት ምን ያህል ነው ተብሎ የሰፈረው?

አቶ ትዕግስቱ፡- በ2004 ደንባችን ላይ የሰፈረ የጠቅላላ ጉባኤ አባለት መጠን ብዛት የለም። ደንቡ የሚለው ከየወረዳው በሚወከሉ አባላት ብዛት የጠቅላላው ጉባኤ ተሳታፊ መጠን ይወሰናል። ከዚህ ውጪ ቁርጥ ያለ በመጠን የሰፈረ ነገር የለም።

ሰንደቅጥር 3 ቀን 2007 ዓ.ም በዲያፍሪክ ሆቴል በጠራችሁት አስቸኳይ ጠቅላላ ጉባኤ ላይ፣ ለምን ያህል የጠቅላላ ጉባኤ አባላት ጥሪ አደረጋችሁ?

አቶ ትዕግስቱ፡- ለ122 ጥሪ አድርገን የተገኙት 82 ብቻ ናቸው።

ሰንደቅከጠራችሁት መካከል ምን ያህል አባላት ሲገኙ ነው ኮረም ሞላ የሚባለው?

አቶ ትዕግስቱ፡- ጥሪ ከተደረገላቸው የጠቅላላ ጉባኤ አባላት መካከል ሃምሳ ሲደመር አንድ ከመጡ ኮረም ሞልቷል ይባላል።

ሰንደቅየጠቅላላው ጉባኤውን ስብሳባ ለመታዘብ ምርጫ ቦርድ ተወካይ ልኮ ነበር?

አቶ ትዕግስቱ፡- አልላከም።

ሰንደቅየስብሰባው ሕጋዊነት ላይ ችግር አይፈጥርም?

አቶ ትዕግስቱ፡- የምርጫ ቦርድ ውሳኔን ወደፊት የምናየው ነው የሚሆነው። የህጋዊነት ጥያቄ ከተነሳ የእነበላይ ቡድንም ከምርጫ ቦርድ ተወካይ ሳይቀርብላቸው ነው ስብሰባ ያደረጉት። ስለዚህም ሁለታችንም የምርጫ ቦርድ ውሳኔን መጠበቅ የግድ ነው የሚሆነው።

ሰንደቅበቀበና በተደረገው ጠቅላላ ጉባኤ ላይ፣ የእናንተን ወገን ለሆዳቸው ያደሩ፣ የገዢው ፓርቲ የተጠለፉ እየተባለ በአደባባይ ስትወገዙ ነበር። በዚህ ክስ ላይ ምን አስተያየት አልዎት?

አቶ ትዕግስቱ፡- በተቃዋሚ ጎራ ውስጥ ሆነህ በሃሳብ ከተለየህ የተለመደ መዝሙር አለ። እሱም፣ “ለሆዳቸው ያሩ፣ በገዢው ፓርቲ የተጠለፉ” ይህ የተቋውሞ ጎራው ለበርካታ አመታት ውስጣዊ እውነትና ትግልን ለመሸሽ የሚፈልጉ ኃይሎች ሲያሰሙት የነበረ፣ አሁን ደግሞ በቀበና የአንድነት ጽ/ቤት እየተዘመረ ያለ መዝሙር ነው። በእኛ በኩል ይህ የተለመደ መዝሙር መፍትሄ የሚያመጣ ነው ብለው የሚያምኑ ከሆነ መዝሙሩን አጠናክረው መዘመር ያለባቸው ይመስለኛል።

ሰንደቅ፡- በእናንተ በኩል ፓርቲውን ለመጥለፍ አለመንቀሳቀሳችሁን እንዴት ታስረዳላችሁ?

አቶ ትዕግስቱ፡- እንደዚህ አይነት ጥያቄ ከመሰንዘርህ በፊት የተፈጠረውን ችግር ከመሰረቱ ማወቅ ይጠበቅብሃል። በእኛ ፓርቲ ውስጥ የተፈጠረው የአይጧ እና የምጣዱ ተረት ነው። ይሄውም አይጧ ብድግ ብላ ምጣዱ ላይ ትቀመጣለች። ከምጣዱ እንድትወርድ ብዙ ሙከራዎች ቢደረግም አልወርድም ብላ ቁጭ አለች። ያለው ብቸኛ አማራጭ ምጣዱን መስበር ብቻ ነበር። ይህን አይነት ውሳኔ ለአይጥ ብሎ መወሰን ብስለት ያለው ውሳኔ አይደለም። ያለው አማራጭ የፈጀውን ጊዜ ወስዶ አይጧን ከምጣዱ ላይ ማውረድ ነው። ለዚህም ነው፣ እኛም ፓርቲው ላይ ከሕግ ውጪ ስልጣን የተቆናጠጡትን አካሎች በሕግ አግባብ ለማውረድ የፈጀውን ጊዜ ይፍጅ እንጂ እንዲወርዱ እየሰራ እንገኛለን። ይህ አካሄዳችን ፓርቲውን ለመጥለፍ ተደርጎ ከተወሰደ፣ መሰረት የሌለው ውንጀላ ነው የሚሆነው። ወይም ከምጣዱ አይጧን ማስቀደም ነው የሚሆነው።

ሰንደቅየፕሬዝደነት ምርጫ ያደረጋችሁት በመተዳደሪያው ደንብ መሰረት ነው?

አቶ ትዕግስቱ፡- ደንቡን ተከትለን አስመራጭ ኮሚቴ በጠቅላላ ጉባኤው ተመርጦ ነው፣ ወደምርጫ የገባነው። ሰባት ሰው ተጠቁሞ አምስት አስመራጭ ኮሚቴዎች ተሰየሙ። እነሱም፣ ሰብሳቢ አቶ በሃይሉ ሽመክት፣ ፀሃፊው ገዛሃኝ አዱኛ፣ አባላት አቶ በዕምነት አሰፋ፣ አቶ ተስፋዬ እና አቶ ግርማ ታረቀኝ ናቸው።

ሰንደቅ፡- ለፕሬዝደነት ዕጩነት ምን ያህል ተወዳዳሪዎች ቀርበዋል?

አቶ ትዕግስቱ፡- አራት ናቸው። እነሱም፣ አቶ ትዕግስቱ አወል፣ አቶ አየለ ስሜነህ፣ አቶ የማነአብ አሰፋ እና ወ/ት ኤዶም ሰይፉ ናቸው። ከእነዚህ ተወዳዳሪዎች መካከል ሁለቱ ራሳቸውን ለሚፈልጉት ሰው ድምጽ እንዲሰጥ አስታውቀው ራሳቸውን ከምርጫ አግልለዋል።

ሰንደቅበምን ያህል የጉባኤው ድምጽ ነው ፕሬዝደነት ሆነው የተመረጡት?

አቶ ትዕግስቱ፡- ከጠቅላላው ጉባኤ አባላት ድምጽ 61 አግኝቼ ነው፣ ፕሬዝደነት ሆኜ የተመረጥኩት። ወ/ት ኤዶም ሰይፉ ደግሞ 19 ድምጽ አግኝታለች። 2 ድምጸ ተአቅቦም ነበር።

ሰንደቅበሁለት ጎራ የተከፈለ ቡድን እየታየ ያለው። በአንፃሩ አንድነት ፓርቲን አምነው ብዙ ዋጋ የከፈሉ አባላት መኖራቸው ይታወቃል። አሁን እናንተ የፈጠራችሁት መከፋፈል ለፓርቲው ዋጋ ከከፈሉት አባላት አንፃር ሲያነፃፅሩት ምን ይሰማዎታል?

አቶ ትዕግስቱ፡- በጣም ነው የማዝነው። ለተፈጠረው መከፋፈል ግን ሃላፊነት መውሰድ ያለበት የእነበላይ ቡድን ነው። መታወቅ ያለበት ግን የተከፈለው አንድነት ፓርቲ ሳይሆን፣ ጥቂት ስልጣን ለራሳቸው ጥቅም ለማዋል በፈለጉ ኃይሎች የተፈጠረ የህግ ጥስት ነው። የእኛም ጥያቄ ሕጋዊ አሰራር ይስፈን፣ ሕጋዊ የፓርቲ መሪዎች ይመረጡ ነው። ጥያቄያችን ፓርቲው ከመታደግ አኳያ እንጂ የተከፈለውን ዋጋ መና የሚያስቀር አይደለም።

ሰንደቅበቀበና የተደረገው ምርጫ በሚስጥር ድምጽ የተሰጠ ነበር። እርስዎ ከሚሉት ጋር እንዴት ይታረቃል?

አቶ ትዕግስቱ፡- ለማያውቀው የሚስጠር ድምጽ ይመስላል። አንድነት ውስጥ የፖለቲካ ሴራ እነማን እንደሚሰሩ ለምናውቀው አባላት የምርጫውን ውጤት ሳይሰጥ ውጤቱን እናውቃለን። ለዚህም ነው ግልፅ አሰራር በፓርቲው ውስጥ እንዲሰፍን እየሰራን ያለነው። ኢንጅነር ግዛቸው በነፃ አሰራር ስልጣን አላስረከቡም። እሳቸውንም ያስቸገረው በአንድነት ውስጥ ያለው ፖለቲካዊ ሴራ ነው። በቀበና የተደረገውም ከዚህ ተመሳሳይ ሴራ የሚያመልጥ ምርጫ አይደለም። ፓርቲውን ለማዳን ያለው ምርጫ ችግሮችን በግልፅ አውጥቶ በግልፅ ውይይት መፍትሄ ሰጥቶ መራመድ ብቻ ነው። በቲፎዞና በፖለቲካ ሴራ ፓርቲያችን የተፈለገውን ያህል ርቀት መጓዝ አይችልም። ሁሉም ቆም ብሎ ማሰብ ያለበት ይመስለኛል።

*********

ምንጭ፡- ሰንደቅ፣ ጥቅምት 09-2007 – ‹‹አንድነት፣ በቀበና እና በሆቴል ዲ-አፍሪክ›› በሚል ርዕስ፡፡

Content gathered and compiled from online and offline media by Hornaffairs staff based on relevance and interest to the Horn of Africa.

more recommended stories