ከሴራሊዮን የመጣ ግለሰብ በኢቦላ ተጠርጥሮ ምርመራ ቢደረግለትም ከቫይረሱ ነፃ መሆኑ ተረጋገጠ

*የደም ናሙናው ለተጨማሪ ማረጋገጫ ወደ አሜሪካ በዛሬው ዕለት ተልኳል፡፡

በትናንትናው ዕለት አንድ ከሴራሊዮን የመጣ ግለሰብ በኢቦላ ሕመም ተጠርጥሮ ምርመራ ቢደረግለትም ከቫይረሱ ነፃ መሆኑን የጤና ጥበቃ ሚኒስትር ዶክተር ከሰተብርሃን አድማሱ አስታወቁ፡፡ Photo - IFRC Kenema Ebola treatment centre - October 2014

ታማሚው በሴራሊዮን በአንድ የአለም አቀፍ የበጎ አድራጎት ድርጀት በኩል ተቀጥሮ የአካባቢ ቁጥጥር ባለሙያ በመሆን  ይሠራ የነበረ  ሲሆን፥ ከሴራሊዮን ከተመለሰ በ15ኛ ቀኑ በትኩሣት ራሱን በመሳቱ በተደረገለት የደም ምርመራ ፋልሲፓረም የተባለ የወባ በሽታ የተገኘበት በመሆኑ ለዚሁ አገልግሎት ባዘጋጀችው ላብራቶሪ ለኢባላ የደም ምርመራ ተደርጎለት ውጤቱ ከበሽታው ነፃ እንደሆነ ታውቋል፡፡

በላብራቶሪ ውጤቱ ሙሉ በሙሉ እርግጠኛ ብንሆንም ታካሚው ሴራሊዮን ደርሶ ከመመለሱ አንፃር የደም ናሙናው ለተጨማሪ ማረጋገጫ ወደ አሜሪካ በዛሬው ዕለት መላኩንና ከ48 እስከ 72 ሰዓታት ውስጥ ውጤቱ እንደሚታወቅ ነው የተመለከተው።

በውጤቱ ላይ ለውጥ የሚኖር ከሆነ በቀጣይ ሚኒስቴሩ እንደሚያሳውቅ ዶክተር ከሰተብርሃን ገልጸዋል፡፡

ታካሚው በሕክምና ሲረዳ ቆይቶ በዛሬው ዕለት ረፋድ ላይ ሕይወቱ ማለፉንም ነው ያስታወቁት፡፡

የተላከው ናሙና ውጤት እስከሚመጣ ድረስ ከተጠርጣሪው ጋር ቀጥታ ግንኙነት የነበራቸው ጓደኞቹና ቤተሰቦቹ ላይ የባለሙያ ክትትል በመደረግ ላይ መሆኑም ተገልጿል፡፡

ኢትዮጵያ ኢቦላን ለመከላከል የምታደርገው ጥረት ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ዶክተር ከሰተብርሃን አድማሱ አረጋግጠዋል፡፡

********

ምንጭ፡- ፋና – ጥር 6፣ 2007

Content gathered and compiled from online and offline media by Hornaffairs staff based on relevance and interest to the Horn of Africa.

more recommended stories