History | ያልሰመረው የቤልጅየም ኢትዮጲያን የመግዛት ውጥን

(ወልደብርሃን ስሁል)

የዛሬ መቶ ሰባ ዓመት አካባቢ አንዲት “ሚጢጢየ” አውሮፓዊት ሃገር ማንም ሳይቀድማት ኢትዮጵያን በጉልበት ይዛ ቅኝ ለመግዛት “ክተት ሰራዊት ምታ ነጋሪት ብላ” ቆርጣ ተሰናዳች። በቆዳ ስፋቷ አንድ ትልቅ ወረዳ እምታክል ናት። አፍሪካ ውስጥ ግን የራሷን መቶ እጥፍ የሚያክል ግዛት መቆጣጠር እሚያስችል አቅምና እብሪት ነበራት። ህልሟን ለማሳካት ፕሮጀክት ቀርፃ feasibility study አካሄደች። እቅዷና ጥናቷ ያነጣጠረውም በዘመነመሳፍንቷ ኢትዮጵያ ላይ ነበር። የቀይ ባህር አካባቢ ደከም ባለ አውሮፓዊ ሃይል እንዲያዝ ትሻ የነበረችው ታላቋ ብሪታንያም ይሁንታ ሰጠቻት፤ በወርራ ቅኝ ልትገዛን ቆርጣ ለተነሳችው ቤልጅየም!

ቤልጅየም ለኢትዮጵያ ያሰበችው ፕሮጄክት ብሎንዲል ከሚባል እብሪተኛ ሰው የጀብድ ልክፍት ጋር የተቆራኘ ነበር። ግብፅ በወርኔር ሙዚንጀር፤ ጣልያን በፔትሮ አንቶኖሊ ምን እንዳደረጉን ጠንቅቀን እናውቃለን። ከነሱ በፊት ቀድሞ ስለተሰናዳልን የብሎንዲል Humanitarian Mission ግን ብዙ አናውቅም። ነገሩ ያስገርማል እንጂ አያስቅም። “ገድለ‐ብሎንዲል” በጥቂቱ እንዲህ ነበር፦

የቤልጂግ መንግስት መጀመርያ በ1841 ከፍተኛ በጀት መድቦ ብዛት ያላቸው የስለላ ወኪሎቹን ወደ ግብጽ አሰማራ። ወኪሎቹም “ለሳይንሳዊ ጥናት እና ለሰብአዊ ተልእኮ” በሚሉ ሽፋኖች ካይሮ ላይ ከትመው ስለ ኢትዮጵያ ጥናት ጀመሩ። ማንኛውንም ዓይነት መረጃ በዝርዝር እየቀራረሙ ከሚያቀርቡት ሪፖርት የቤልጂየም ንጉስ ቀዳማዊ ሊዮፖልድ “በውስጧ ሁከት የነገሰባት ኢትዮጵያን” በቀላሉ መውረርና መቆጣጠር እንደሚችል አመነ። ለወረራም ቋመጠናም የሰላዮቹ አስተባባሪ በአካል ወደ ኢትዮጵያ ሂዶ “ሰብዓዊ ተልእኮ” የሚል ስም ያለው ጉብኝት እንዲያካሂድ አዘዘው። ዋናው ተልእኮው ግን ለወረራ ምቹ ሁኔታ እንዲፈጥር እና ባስቸኳይ እሚተገበር የድርጊት መርሃ ግብር እንዲያዘጋጅ ነበር። ይህን ሃላፊነት የተቀበለው የሰላዮቹ አለቃም ካይሮ ተቀማጩ በግብጽ የቤልጂክ መንግስት ዋና ቆንሲላ የነበረው ብሎንዲል ነው።

Map - Belgium
Map – Belgium

ብሎንዲል የፖለቲከኞቿ እርስበርስ ጥልና ፉክክር በመጠቀምና የካቶሊክ እምነት በማስፋፋት ኢትዮጵያን በቀላሉ ቅኝ ማድረግ ይቻላል ብሎ አምኗል። ይህ እምነቱም ጽኑ ስለነበር የተለየ ነገር ሰምቶና አይቶም አልለወጠውም። ብሎንዲል ገና ካይሮ እያለ አዲስ ፓትሪያርክ ሊያመጡ ወደ ግብጽ የሄዱ የኢትዮጵያ ልኡካን አግኝቶ ጉዳዩን “የቤልጅየም መንግስት ለአቢሲኒያውያን የሰብዓዊ እድገትና ስልጣኔ ካለው ተቆርቋሪነት” አንጻር አዋዝቶ እየተነተነ አጫወታቸው።

እነሱም (ከመካከላቸው አንዲት ፀጉር ለብዙ ሰንጥቀው ብዙ እሚሟገቱ ነቄ ካህናት ነበሩ) አዋዝተው መለሱለት፦ ጥንት ጀምሮ የኦርቶዶክስ ክርስትና በተስፋፋባት ሃገራቸው የካቶሊክ እምነት ተቀባይነት እንደማያገኝ፣ እስላሞቹም ሆኑ ክርስቲያኖቹ ኢትዮጵያውያን ተባብረው በጋራ ሃገራቸውን ከጠላት እንደሚጠብቁ፣ የየአካባቢው መሳፍንት በአንድነት የውጭ ወራሪን እንደሚመክቱ በማሳሰብ ብዙ ምሳሌ ጠቁመው ሃሳቡ እንደማይሳካ…በትህትና ነገሩት። አጅሬ ግን ሊያምን አልፈቀደም። በመጨረሻ በ1841 ወደ ኢትዮጵያ መጥቶ በየመሳፍንቶቹ አካባቢዎች እየተዘዋወረ “ለሰብዓዊ ተልእኮው” የሚያመቹ ቆላና ደጋ የአቢሲንያ መሬቶችን እየማተረ ሰነበተ።

ብሎንዲል በቆይታው የትግራዩን ደጃች ውቤ፣ የበጌምድሩን ራስ አሊ እና የጎጃሙን ደጃች ጎሹ ተራ በተራ ጎበኛቸው። ሁሉም ሞቅ አድርገው ተቀብለው አስተናገዱት። ከእያንዳንዳቸው ጋር ስጦታዎች እየተለዋወጠ ስላገሩና ስላገራቸው ጠቅለል ያለ ውይይት እያካሄደ ሁኔታቸውን አጠና። ሁሉም እንደተለመደው ለሚወዱት ታቦት የሚሰጥ የቤተክርስቲያን ደወል፣ ለግላቸው የሚታጠቁት እሚያምር ሽጉጥ ወይም ጠመንጃ…ግፋ ካለም እነዚህን ነገሮች የሚሰራ ጎበዝ የፈረንጅ አንጠረኛ ከቤልጀም ቢመጣላቸው እንደማይጠሉ ነገሩት። በፖለቲካ ቋንቋ ሲመነዘር ከአውሮፓ ወታደራዊና ቴክኒካዊ ድጋፍ ከመጠየቃቸው ውጭ ከመካከላቸው ለቤልጂየም ፍላጎት ተባባሪ ሊሆን የፈቀደ አንድም አልነበረም።

ብሎንዲል ግን ከታዘበው አጠቃላይ ሁኔታ ተነስቶ የራሱ ድምዳሜ ላይ ደረሰና በአፉ ለሚናገረው ሰብዓዊ ነገር ሳይሆን ከልቡ ለያዘው ኢሰብአው ተልእኮ የሚመቹ አጋሮች መረጠ። ደጃች ውቤ ስሜን፣ ትግራይና ባህረ ነጋሽ ባንድ ላይ ያጠቃለለ ስትራቴጂክ ግዛት ስለሚያስተዳድር፣ ግዙፍ ሰራዊት ስለሚመራ እና ከሌሎቹ ተፎካካሪዎቹ በተሻለ ንጉሰ ነገስት ለመሆን ዝግጅት ላይ ስለነበር ለአጋርነት አልታጨም። ውቤ ኢትዮጵያውያንን አሰተባብሮ ጠንካራ ሃይማኖታዊና ወታደራዊ መከላከል አካሂዶ የቤልጅየምን ህልም ሊያጨልም ይችላል ብሎ ስለፈራ የብሎንዲል አይን ራስ አሊ እና ደጃች ጎሹ ላይ አረፈ። በሱ እምነት ራስ አሊ “ከአንጀቱ የኦርቶዶክስ እምነት ተከታይ ስላልሆነ” ከግብፁ መሪ መሃመድ አሊ ጋር በመተባበር የኢትዮጵያ ክርስቲያኖችን እንዲወጋ ማድረግ እንደሚቻል እርግጠኛ ሆኗል። ደጃቸ ጎሹ ደግሞ ቀደም ብሎ ፖርቱጋላውያን የካቶሊክ እምነት በተወሰነ ደረጃ ያስፋፉበትን አካባቢ ስለሚያስተዳድርና “ከሌሎቹ የአቢሲንያ መሪዎች በተለየ የአውሮፓውያን ስልጣኔ ለመቀበል ትልቅ ፍላጎት ያለው ምሁር ሃገረ ገዢ በመሆኑ” ሚሲዮናውያንና የእደጥበብ ባለሙያዎች ቢላኩለት ኢትዮጵያ ውስጥ የካቶሊክ እምነት በማስፋፋት የቤልጅየምን ህልም ለማሳካት እንደሚጠቅም አመነ። ብሎንዴል ወደ ካይሮ ተመልሶ ይህንኑን ድምዳሜ ለቀዳማዊ ሊዮፖልድ በደብዳቤ አሳወቀ። ቀጥሎም ኢትዮጵያን በወታደራዊ ወረራ ለመቆጣጠር የሚያስችል ዝርዝር እቅድ አዘጋጅቶ ረቂቅ ፕሮፖዛሉን በሴፕቴምበር 30፣ 1843 ለቤልጅየም የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቀረበ።

ፕሮፖዛሉ ባጭሩ ሲቀመጥ ቤልጅየም በወረራ ኢትዮጵያን በቀላሉ ተቆጣጥራ እና የውስጥ ዓመጽ አክሽፋ በይዞታዋ ስር ማቆየት ትችላለች ይላል። ለዚህም እንደተጨባጭ የቀረቡት ማሳመኛዎች ደግሞ “ኢትዮጵያ ህዝቦቿ ተራራን መከታ ከማድረግ ውጭ ዘመናዊ ጦር መሳሪያ የማያቁ መሃይማን መሆናቸው፣ በሃገሪቱ ውስጥ የማያባራ የእርስበርስ ብጥብጥ የተለመደ ክስተት መሆኑ፣ ህዝቦቿ በሁሉም ነገር ኋላ ቀር መሆናቸው…” የሚሉ ናቸው።

ከዚህ ጋር አብሮ አንድ አስገራሚ የማሳመኛ ነጥብ ተካትቷል ቀረቦ። ራሱ ብሎንዲል ቀደም ብሎ ኢትዮጵያ ውስጥ አሰራጨሁት ያለው የፈጠራ ትንቢት፦ “ኢትዮጵያ በፈረንጅ ትወረራለች ነጭ ንጉስም ይገዛታል፤ ህዝቦቿም እንደ ፈረንጆች በእውቀት፣ በሃብትና በጽድቅ ይንበሸበሻሉ” የሚል ራሱ ያሰራጨው የፈጠራ ትንቢት በኢትዮጵያውያን ዘንድ ተቀባይነት አግኝቷል በማለት ቤልጅየም ወረራ ስትፈፅም ኢትዮጵያውያን “ትንቢቱ ይፈጸም ዘንድ ግድ ነው” ብለው “ለነጩ ንጉስ እጃቸውን በቀላሉ ይሰጣሉ” የሚል ቂላቂል መሟገቻ ፕሮፖዛሉ ውስጥ አቅርቧል። ብሎንዲል ከፕሮፖዛሉ ጋር አብሮ ያቀረበው ረቂቅ ወታደራዊ እቅድም እጅግ መሳጭ ነው። ቤልጅየም ኢትዮጵያን ለመውረር በምታካሂደው ዘመቻ 230 መድፈኞች፣ 100 ፈረሰኞች፣ 870 እግረኛ ወታደሮች ያሉት ሰራዊት እና 1200 ድጋፍ ጋፍ ሰጭ ባለሙያዎች የጉልበት ሰራተኞች ማክተት ብቻ በቂ እንደሆነ በግልጽ አስቀምጧል። በጁን 19 ቀን 1844 የቤልጂክ መንግስት ይህንን ዝርዝር ወታደራዊ እቅድ አጽድቆ ወረራው እንዲፈጸም ወሰነ፤ ታላቋ ብሪታንያም መልካም ፈቃዷን ሰጠች።

ከዚያ በኋላ “ሚጢጢየዋ” ቤልጅየም “ታላቋ” ኢትዮጵያን በቅኝ ግዛት መዳፏ ስር ልታስገባ ወታደራዊ መሰናዶዋን አጣድፋ አጠናቀቀች። አውሮፓ ውስጥ የብሎንዲል “ሰብዓዊ ተልእኮ” /Humanitarian Mission/ ወዳፈጠጠ “ወታደራዊ ወረራ” /Outright Aggression/ መሆን የሚያስችለው ይፋዊ እውቅና ተሰጥቶት ብራሰልስ ውስጥ ነጋሪት ሲጎሰም ኢትዮጵያውያን ስለጉዳዩ የሚያውቁተ ሃባ ነገር አልነበረም። ሌላው ቀርቶ ብሎንዲን ለስለት የሚሰጡ የስጦታ እቃዎች ወይም እሚያምሩ ትጥቆች አልያም ጎበዝ አንጠረኛ እንዲልክላቸው “አደራ” ያሉት መሳፍንት እንኳ በእርስበርስ ፉክክርና ጦርነት ተወጥረው ስለነበር እሱ ከሄደ በኋላ የሱን ስምና ያገሩን ስም የሚያስታሱበት ጊዜ አልነበራቸውም። ባይሆን “አደራ” ያሉትን ስጦታ ወይም አንጠረኛ ቢልክላቸው ወይም ራሱ ይዞ ቢመጣ ኖሮ የጦረኛ ካባ ኣልብሰውና በቅሎ ከነ ሙሉ ሽልማቷ ጀባ ብለው ወዳገሩ ይሸኙት ነበር፤ የሱና የሃገሩም ስም በኢትዮጵያ ታሪክ ይሰፍር ነበር። እሚገርመው ግን የብሎንዲል ገድልም ኢትዮጵያ ሳይደርስ እዚያው ላይ አበቃ።

ቤልጅየም ለወረራ ቀን ቆርጣ ሽርጉድ ካለች በኋላ ፕሮጄክቷን ድንገት ተወችው። ጓቴማላ ላይ ያቀደችው ተመሳሳይ ፕሮጀክት ስለነበር እሱን ማጠናከር ይሻለኛል ብላ። በዚህም የተነሳ ኢትዮጵያን እንዲህ አቅልሎና አሳንሶ ያየው የብሎንዲል እቅድ “Castle in the air” (ላም አለኝ በሰማይ) ብለው የቅኝ አገዛዘ ዘመን ታሪክ ጸሃፍት ተሳልቀውበታል። መቼም የቤልጂየም ቅኝ አገዛዝ ባለስልጣናት ከጓቴማላ በኋላ ወደ አፍሪካ ሰራዊታቸውን አዝምተው ኮንጎን ወርረው መያዛቸው አልቀረም። ታዲያ ምን ሁነው ነው ከጓቴማላ በኋላ መጀመሪያው ቋምጠው ወደ ተሰናዱበት ወደ አፍሪካ ቀንድ ያልመጡት ብለን ብንጠይቅ ካልተከናወነ ታሪክ የቢሆን ኖሮ መልስ ማግኘት ይከብዳል። ከዚያ በኋላ አፍሪካ ቀንድ ውስጥ ከተፈጸመው ታሪክ ተነስተን ስንገምት ግን በጠንቃቃዎቹ ቤልጂያኖች ልብ “ግብፅንና ጣልያንን ያየ ኢትዮጵያ ጋር አይሳፈጥም” የሚል ብሂል ተቀብሮ ተቀምጦ ሊሆን እንደሚችል እንጠረጥራለን።

አይበለውና እነብሎንዲል እቅዳቸውን በወቅቱ ፈጽመው አሳክተውት ቢሆንስ ኖሮ ውጤቱ ምንይሆን ነበር? በእርግጥም ኢትዮጵያ እንደ ኮንጎ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ የትልቅ ትንሽ ከመሆን አልፋ ለአፍሪካውያን ሰብዓዊ መብት የሚቆረቆሩ ፈረንጆች ፕሮጄክታቸው ሲሳካ ምን አይነት ሃገርና ህዝብ እንደሚፈጥሩ ልክ እንደ ኮንጎዎች ከሰውነት ወደ እንስሳነት ወርደን ለአዓም እንመሰክር ነበር። አሁን በሃያኛው ክፍለዘመን በፈረንጅ ሃገር ስለ “ሰብዓዊ መብት” /Human Rights/ አፋቸውን ሞልተው እየተመጻደቁ የሚለፍፉ ፈረንጅና የፈረንጅ ወኪል “ተቆርቋሪዎች” ትረካዎቻቸው የ19ኛው ክፍለዘመን ሰነዶች ከተከማቹባቸው የአውሮፓ ቤተመዘክሮች ሂደው ከብሎንዲል Humanitarian Mission መሰል ፕሮፖዛሎች ገጽ በገጽ ቃላት ገልብጠው ሲጠቀሙ እናስተውላቸዋለን።

ልክ እንደብሎንዲል ከአፋቸው እሚያማልሉ ጣፋጭና ተቆርቋሪ ቃላት ይወጣሉ፤ በልባቸው የውስጥ ቁርቁሳችን ላይ ያተኩራሉ፤ አንዳንዶቹም አፍሪካውያን እርስ በርሳችንም እንድንጠፋፋ ሌት ተቀን ተግተው ይሰራሉ። ደግነቱ ተግባር ላይ ሲመጣ “ጉዳዩ ሃበሾችን አይመለከትም” የሚል የውስጥ መግባብያ ወይም ያልተጻፈ የተግባር መመርያ የሚጠቀሙ ይመስላል። “ገድለ‐ብሎንዲል” ባጭር የተቀጨው በዚህ መመርያ ይሆን?

**********

Content gathered and compiled from online and offline media by Hornaffairs staff based on relevance and interest to the Horn of Africa.

more recommended stories