አጀንዳ ኤርትራ | ላለፈው ክረምት ቤት አይሠራም!

በዚህ ፅሑፍ ከህወሓት ተገንጥሎ በወጣው የአመራር ቡድን ሲቀነቀን የነበረውና በገብሩ አስራት መሪነት ጫፍ የደረሰ የሚመስለው በኤርትራ ዙሪያ ከሚያጠነጥነው የታሪክና የሉአላዊነት ጥያቄ ከገዛ ተጋሩ ፓልቶክ ፣  ከዓይጋ ፎረም ድረ ገጽ እንዲሁም ከአሜሪካ ድምፅ ሬድዮ ጋር ባደረጉዋቸው ምልልሶችና በሰጡዋቸው መግለጫዎች በመመስረት የበኩሌን እላለሁ።

ከታሪካዊ ሙግቶች አንፃር በገብሩ አስራት  በኩል እየተራመደ ያለውን ዋንኛ መከራከሪያ አጀንዳ ህወሓት በትጥቅ ትግል ፕሮግራሙ ላይ በማስፈር ሲታገልለት የቆየውን የኤርትራ ጥያቄ መሰረት ቅኝ ግዛት ማድረጉ በበቂ ጥናት ላይ ያልተመሰረተ፣ ከኢትዮጵያ ይልቅ የኤርትራን ጥቅም ያስቀደመ ብሎም በኢትዮጵያ ሉአላዊነትና ዘላቂ ሀገራዊ ጥቅሞች ላይ እጅግ የበዛ ሳንካ የፈጠረ ታሪካዊ ስሕተት እንደሆነ ነው። ለኤርትራ መፈጠር የውጫሌ ስምምነት መሆኑን የተቀበሉ የሚመስሉት ገብሩ አስራት ጣልያን ቃልዋን በማጠፍ በ1928 ዓ/ም ባደረገችው ወረራ ምክንያት ውሎቹ ጥቅም አልባ በመሆናቸው የኤርትራ ግዛትና ድንበር አሁን በምናውቀው መልኩ መካለሉ ተገቢ አለመሆኑን እምነታቸው ነው። አርትራውያን የራሳቸውን እድል በራሳቸው የመወሰን መብታቸው እንደተጠበቀ ሆኖ የፍቺው አፈፃፀም ግን የኢትዮጵያን የወደቦች ጥያቄ የሚመልስ ተደርጎ መወሰን ነበረበት ባይ ናቸው። ምክንያቱም በሳቸው እምነት የውጫሌ ውል መፍረስና የፈደሬሽኑ ውህደት የቅኝ  ግዛት ድንበሮችን እንዳልነበሩ መሆን ለኢትዮጵያ በቂ መተጣጠፊያ ዕድል ፈጥረው ስለነበረ ነው።

ሌላው የሉአላዊነት መደፈር ምክንያት ሆኖ በገብሩ አስራት በኩል የሚቀርበው ጉዳይ በኤርትራ ወራሪነት በቅርቡ ያደረግነውን ጦርነት የሚመለከት ነው። ሻዕቢያ ሊወረን እንደሚችል በተደጋጋሚ ሃሳብ ማቅረባቸውና በመንግስት በኩል በተለይ ደግሞ በወቅቱ ከጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ የሰላ ተቃውም እንደገጠማቸው ውሎ አድሮ ግን የፈሩት ነገር መድረሱን ይነግሩናል። ሲያክሉም የመለስ ዜናዊ ተቃውሞ ተራ የትንታኔ ስሕተት ሳይሆን ለሳቸው(ለገብሩ አስራት) ግልፅ ባልሆነ ሁኔታ ሁሌ ለኤርትራ ያሳዩት ከነበረው “መቆርቆር” የሚመነጭ እንደሆነ ያብራራሉ። በሳቸው እምነት ለድርድር ያጠፋነውን ጊዜ አላስፈላጊ ከመኖሩም በላይ አጨራረሱም የኢትዮጵያን ጥቅም ያላስከበረ እንዲሁም መንግስት ሻዕቢያን ላንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ለመደምሰስ የነበረውን እቅድ ጋር ፈፅሞ እንደማይጣጣም ነው። እነዚህን ሁለት ዋንኛ መከራከሪያዎች በየተራ እንመልከት።Map - Eritrea Ethiopia

ሲጀመር የኤርትራ ችግር የቅኝ ግዛት ወይስ የራስን እድል በራስ የመወሰን መብት የሚሉትን ክርክሮች በመሰረቱ ለጉዳዩ መፍታት የሚያበረክቱት አስተዋፅኦ ኢምንት ቢሆንም ታሪክን በትክክለኛ እይታ መተንተን በራሱ አስፈላጊና ጠቃሚ ነገር ነው። በኔ እምነት የችግሩ ምንጭ ከቅኝ ግዛት የተያያዘ ነው ማለትና ኢትዮጵያ የኤርትራ ቅኝ ገዢ ነበረች ማለት ለየቅል ናቸው። በጉዳዩ የኢትዮጵያን የቅኝ ገዥነት ካባ የሚያጎናፅፉ መገለጫዎችን ፈፅሞ ማግኘት አይቻልም። በፖለቲካው፣ በኢኮኖሚና በማህበራዊ ልኬቶች አንፃር ኤርትራዊና ኢትዮጵያዊ የተለዩበት ክስተት ታሪክ አልዘገበም። በማህበራዊ ግንኙነታቸው ሌሎች አፍሪካውያንን የገጠማቸው  ዓይነት የዘርና ኢኮኖሚያዊ አድልዎ ፈፅሞ አልነካቸውም። ይልቁንስ ኤርትራውያን ከጣልያን ተገዥነታቸው ባገኙት ትሩፋት ሳቢያ በሀገራዊ ኢኮኖሚው ላይ የበላይነት የነበራቸው መሆኑ ነው። እንዲያውም ኢትዮጵያውያን ወንድም እህቶቻቸውን በኋላቀርነት ፈርጀው ቁልቁል የሚመለከቱ የሃገራችንና ህዝቧን  “ኋላቀርነት”  እንደ አንዱ ምክንያት ለሚያቀርበው የነፃነት ትግል መጋቢ እንደነበሩ ያደባባይ ምስጢር ነው። ስለዚህ ኤርትራውያን “ኢትዮጵያ ቅኝ ገዥያችን ነበረች” የሚለውን ተረት ተረት እየታፈሰ ለትግል ይሰለፍ የነበረውን ወጣት አሳምኖ ለውጊያ ከማሰለፍ የዘለለ ውሀ የሚቋጥር ይዘት አልነበረውም፤ ኣይኖረውምም። ከዚህ  ሞልቶ ከፈሰሰው “ኩራታቸው” አንፃር የቅኝ ግዛት ተረት ተረቱን ፈቅደው መቀበላቸው እስካሁን እንደገረመኝ አለ። በመሬት ላይ የነበሩ ሃቆችና ከባቢያዊ  ተፅዕኖዎች እንዳሉ ሆነው የኢትዮጵያ ኤርትራ ጉዳይ ለኔ ከቻይናና ሆንግ ኮንግ ጉዳይ ያለፈ ትርጉም አይሰጠኝም። ስለዚህ የህወሓት አመራር በወቅቱ “ኢትዮጵያ የኤርትራ ቅኝ ገዢ ናት” የሚል አቋም ከነበረው ለችግሩ አፈታት ወሳኝ ጉዳይ ባይሆንም መጠነኛ  የአገማገም ሚዛን ጉድለት ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል።  ነገር ግን ጉዳዩ ዱሮ ለነበሩትና በሂደት ለተፈጠሩት ችግሮች ምንጭ እንደሆነ ለማሳመን መኳተን ከምክንያታዊነቱ ይልቅ በቀልን ያነገበ እይታ እንደሆነ ለመረዳት አይከብድም። ምክንያቱም የኤርትራ ትግል መነሾ የህወሓት አመራር የፖለቲካዊ ትንታኔ ችግር የፈጠረው አይደለም። ይልቁንስ ችግሩ ህወሓት ከመወለዱ ከግማሽ ምዕተ ዓመት በላይ ኖሯል። የኤርትራን ትጥቅ ትግል ከተጀመረ አስራ ሶስት ዓመታት በኋላ የተመሰረተ ድርጅት የሁሉም ሃጥያቶች ተሸካሚ እንደሆነ የሚተነትን እይታ መፅሐፍ ለማሻሻጥ የሚኖረው ፋይዳ ቢገባኝም ለኢትዮጵያ ሀገራዊ ጥቅሞች ከማሰብ እንዳልተነሳ ግን ልቤ ይነግረኛል።

እስከሚገባኝ ድረስ ከታሪክ አንፃር ኤርትራን በሚመለከት የተደበቀ ሚስጢር አለ ብዬ አልወስድም። የኢትዮጵያና የኤርትራ ኮንፈደሬሽን በፈ.አ. 15 መስከረም ቀን 1952 ዓ/ም ሲመሰረት በሁለት ተነፃፃሪ ሉአላዊነት ባላቸው አካላት መካከል የተደረገ ቃልኪዳን መሆኑ ማንም ቢሆን መካድ አይቻለውም። ኤርትራ በዚሁ ጊዜ የራስዋ የሆነ ድንበር፣ ባንዴራ ህገ-መንግስትና የተወካዮች ምክር ቤት ይዛ ነው የተቀላቀለችው። ይህ እየሆነ ያለው እንግዲህ ከ1928 ዓ/ም የጣልያን ወረራ ብዙ ዓመታት በኋላ መሆኑ ነው። እነዚህ ውሎች ገብሩ አስራት እንደሚሉት ጥቅም አልባ ሆነው ከነበሩ ኤርትራ የትኛውን የመሬት አካልና ወሰን ይዛ እንደተቀላቀለች ሊነግሩን ይገባል። ኢትዮጵያ የባህር አስተዳደርን፣ የኮንፈደሬሽኑ ፀጥታና ደህንነት እንዲሁም የወጪና ገቢ ንግድን በበላይነት እንድታስተዳድር ቻርተሩ የሰጣትን ስልጣን ቃልዋን እስካከበርችና እስካከበረች ብቻ ነው ሊሆን የሚችለው። ቃልዋን ባፈረሰች ዕለት ግን እነዛን ጥቅሞችና ሃላፊነቶች ወዲያው ታጣለች። በተጨባጭ የሆነውም ይኸው ነው። ኤርትራ 14ኛ ክፍለሃገር ሆና የኢትዮጵያ አካል ስትደረግም ያንኑ የቅኝ ግዛት ድንበሯን እንደያዘች ነበረ።

የኤርትራ የግዛት ወሰን በመሰረቱ በቅኝ ግዛትና ቅኝ ግዛት የወለዳቸው ውሎች ውጤት ይሁን እንጂ  የጊዜው የኢትዮጵያ መሪዎች ጉዳዩን የያዙበት አኳሃን ለከፈልነው የአንድ ትውልድ የህይወትና የደም ዋጋ ማብቃቱን የሚክድ ግለሰብ ሆነ ቡድን እሱ ደጋግሞ ማሰብ ያለበት ይመስለኛል። ሲጀመር ምክንያታዊ ሆነም አልሆነም በንጉሳችን ፊርማ ነው ኤርትራ የተፈጠረችው። ቀጥሎም አክሊሉ ሀብተወልድን በመሳሰሉ ታላላቅ የዲፕሎማሲ ሰዎቻችን ጥረትና የሃያላን ሀገራት ወዳጆቻችን መልካም ፈቃድ መልሰን ብናገኛትም አሁንም በስንት ውጣ ውረድ የተገባውን የፌደሬሽን ቃልኪዳን ባፈረሱት ሌላው ንጉሳችን ፊርማ ደግመን ልናጣት ችለናል። ይህንን እውነታ መቀበልና ሃላፊነት መውሰድ ያስፈልጋል። እውነታውን መቀበልና ሃላፊነት መውሰድ ቀጥሎ ለተፈጠረው አውዳሚ ብረታዊ ተጋድሎ ለምናስቀምጠው የአፈታት አቅጣጫ በእጅጉ ይወስናል። ኢትዮጵያ ያጣችው “አሁን መለስ ብዬ ሳየው” እያለ ታሪክን የሚተች ፖለቲከኛ ሳይሆን ሃላፊነት የሚወስድ ትውልድና አመራር ነው። መለስ ብለን ማየት ካለብን ላሁኑና ለወደፊት ዕድላችን መልካም ዕድል የሚፈጥር ጉዳይ ላይ እንጂ ከነበርንበት የጦርነት አዙሪት የሚያደርሰንን መንገድ ለማበጀት ከቶ መሆን የለበትም። ሃላፊነት መውሰድ ተገቢ ከመሆኑ ባሻገር ሌላ ተመሳሳይ ችግር እንዳይፈጠር ለራስም ሆነ ለቀጣይ ትውልድ አመራር በቂ ትምህርት ያስተላልፋል። ሀገሪቱም በተረት ተረትና የተተበተብ ታሪክና ሀገራዊነት(irrational patriotism) ሳይሆን በእውነተኛ ታሪክ የተማገሩ እሴቶችን ወደ መፍጠርና ማበልፀግ ይመራታል።

ለኤርትራ ትግል ይፋ ያልሆኑ ገፊ ምክንያቶችና የኢትዮጵያውያን ስጋቶች ተመጋጋቢ ሆነው ይታዩኛል። የኤርትራን ህጋዊ መልከአ ምድር ከቅኝ ግዛት የሚመነጭ ይሁን እንጂ የኤርትራውያን ሀገራዊነት ግን በአመዛኙ ኢትዮጵያን “በማንበርከክ” ላይ የተመሰረተ ነው። የትጥቅ ትግሉን የጀመሩ ሰዎች የአከባቢውን ጂኦፖለቲካዊ እንድምታ ተንትነዋል። ከውጭ ትብብር አንፃር ግብፅ በአባይ ላይ እንዲሁም የአረቡ ዓለም ሃገራት “የክርስትያን ደሴት” የሆነችውን ሃገር ለመፈተሽ የነበራቸውን ቀጣይ ፍላጎት   ለትግሉ የሚኖራቸውን የግብአትነት ፋይዳ በሚገባ አጢኗል። ዋንኛውና ለትግሉ እስትንፋስ ሆኖ ያገለገለው ፕሮፓጋንዳ ግን ኢትዮጵያ የባህር በርዋን አጥታ ከፊታቸው እንደምትሟሟ የነበራቸው ህልም ነው። ኢትዮጵያውያን ለ30 ዓመታት ሙሉ እንዲዋጉ ያደረጉዋቸውን  ምክንያቶች ለኤርትራውያን አማፂዎችም ምክንያቶች ሆነው አገልግለዋል። “ኋላቀሩ” የኢትዮጵያ አገዛዝ ሲያበቃ ኤርትራን በአጭር ጊዜ ውስጥ ወርቅና ጨርቅ እንደምትሆን ባንፃሩ ደግሞ ባህር በርዋን ተቀምታ “ኮምፓስ አልባ” የምትሆነው ኢትዮጵያ በኤርትራውያን መልካም ፈቃድ የሸቀጦቻቸውን ማራገፊያ ሆና እንደምትኖር ነበር ታላቁ ህልማቸው። የኤርትራውያን ተጋድሎ የኢትዮጵያን የባህር ባለቤትነት ከማሳጣት ውጪ ህልውና አልነበረውም። በመሆኑም ለኢትዮጵያ የባህር በር ሊያስገኝላት ወደሚያስችል ድርድር የሚገቡበት ዕድል ዝግ ነበር። የለንደኑ ተደራዳሪ ቡድን መሪ የነበሩት መለስ ዜናዊም ሆን የሚመሩት ድርጅታቸው ይህንን እውነታ በውል የተረዱ ነበሩ። “ብለን ነበር” ከሚለው ፖለቲካዊ ፍጆታ ይልቅ ከኤርትራውያን ጋር  የሚኖረንን  መልካም ትብብር የበለጠ ሚዛን መስጠታቸውም እውነት ነው። የሻዕቢያ መንግስት መሰሪነት የፈጠረውን ክስተት የጉዳዩን ተገቢነት አይለውጠውም። ከዚህ ውጪ በጊዜው የነበረው ብቸኛ መንገድ ጦርነቱ መቀጠል ብቻ ነው። ህወሓት ደግሞ ይህንን የመሰለ ትውልድን ያኮላሸ ዕብደት ለማስቆም የተላከ ፍቱን መድሃኒት ሆኖ አገለገለ። የባህር በር ከመንፈሳዊ ኩራትና ጌጥነት ባለፈ ኢትዮጵያም ሆነ ኤርትራ አለመጥቀሙን ስለሆነም ያለባህር መኖርና መበልፀግ እንደሚቻል ለመላው ዓለም አሳየ።

ሌላው ትልቁ የአተናተን ችግር ደግሞ ኤርትራ በህወሓት መልካም ፈቃድ ነፃ የወጣች ሀገር ተደርጎ መታሰቡ ነው። በጊዜው በነበረ ተጨባጭ ሁኔታ የህወሓት አቋሞች የፈለጋቸው ዓይነት ቢሆኑ የኤርትራን ዕጣ ፈንታ አወሳሰን ላይ ትናንሽ የአፈፃፀም ችግሮች ትተን ከተከናወነው ሂደት ውጪ ሌላ ዓይነት አማራጭ የነበረ አይመስለኝም። በኔ እምነት የኤርትራን ትግል ለማኮላሸት የህወሓት/ኢህአዴግ ትጥቅ ትግል አለመኖርን ግድ ይል ነበረ። ስለዚህ ህወሓት መወቀስ ካለበት በኤርትራ ዕድል አወሳሰን ላይ ለውጥ በማያመጣ አቋሙ በመመስረት ሳይሆን ኢትዮጵያን ነፃ በማውጣት ሂደት ላይ የተከሰተውን የኤርትራ ነፃነት በጎን ወጤትነት እንዲከሰት ማስቻሉ መሆን ነበረበት። ከመግለጫዎቻቸው እንደተረዳሁት ግን ህወሓት ያካሄደው ትግል እንደሚኮሩበት ነው። በመሆኑም ገብሩ አስራት ዳቦኣቸውን በተመሳሳይ መብላትም ማቆየትም ኣይቻላቸውም። ትጥቅ ትግሉ ትክክልና የሚኮሩበት ከነበረ ሂደቱ ያስከተለው ውጤትም መቀበል ግድ ይላል። በኔ እምነት የህወሓት  የኤርትራ ነፃነት መቀበል ከታሪክና ህግ በላይ በወጪ-ፋይዳ (cost-benefit) ትንተና ላይ የተመሰረተ ፕራግማቲክና ተራማጅ አቋም ነበረ።አሁን ገብሩ አስራት እንደሚነግሩን ከሆነ ግን የህወሓት ትግል አስፈላጊ አልነበረም ወደሚለው መደምደሚያ የሚያደርስ ነው። ህወሓት በዋነኝነት መወደስ ያለበት ደርግ በመጣሉ አይደለም። ኢትዮጵያን በመበታተን ቋፍ ላይ እንድትገኝ ምክንያት ለሆኑት ችግሮች ከሱ በፊት ባልተለመድ መልኩ መሰረታዊ ሊባሉ የሚችሉ መፍትሔዎች ማበጀቱ እንጂ። ለዚህ ለዚህማ የጃንሆይም የድርጉም አገዛዞች እስኪበቃቸው ድረስ ተመላልሰውበታል። በዚሁ መሃል የመበታተን አደጋ ተጋርጦባት የነበረችው ሃገር ኢትዮጵያ ነበረች። በአራቱም አቅጣጫዎች በጦርነት እሳት እየተለበለበች  “የሶማሊያን እጣ ልትጎነጭ አንድ ሐሙስ የቀራት” ተብሎም የተነገረላት ተስፋቢስ ሃገር ነበረች። ይህንን ታሪክ ለመቀልበስ የራሱን ሚና የተጫወተው ህወሓትና አመራሩ በሃገራዊ ጥቅሞች አሳልፎ መስጠት ውንጅላ ሲከሰስ ማየት አስገራሚ ነው። በኔ እምነት እስካሁን የህወሓት አመራር(ገብሩን ጨምሮ የኋላ ኋላ ቢፀፅታቸውም) ካስተላለፋቸው ውሳኔዎችና ካራመዳቸው ጠቃሚ አቋሞች የኤርትራው ጉዳይ በመጀመሪያው ረድፍ ይሰለፋል። ይህ የተለየ አቋሙ ነው ቢያንስ አሁን ላለነው ሁኔታ ያበቃን። ይህ አቋም  በመሰረቱ በኢትዮጵያ የፖለቲካ ሃይሎች አሰላለፍ ውስጥ አዲስ ሊባል የሚችል ባህል ያስተዋወቀ ነው። ኤርትራ ላይ የፈለጋቸው ዓይነት ሀገራዊ ጥቅሞች አለን ብለን ብናስብም ከኤርትራ ህዝብ መልካም ፈቃድ ውጪ የማሰብን ኢተገቢነት  በትክክል ያሳየ ነበር። በተቃራኒው ደግሞ ኤርትራ እስትንፋስም ሆነ አንገት እንዳልሆነች በተግባር አይተን ስናረጋግጥ እርስ በርሳችን በመገዳደል ያሳለፍናቸውን ዓመታት በእጅጉ እንድንቆጭባቸው አድርጎንና በቂ ትምህርት ሰጥቶን አልፏል፤ ለዛውም ከታሪክ የምንማር ሰዎች ከሆንን ማለት ነው።

ገብሩ አስራት  የህወሓት አመራር በወቅቱ የወሰደው ውሳኔ ከመኮነን ያለፈ መፍትሔ ሲያበጁ አላየሁም። እርግጥ ነው ማንም አካዳሚሺያን ሊለው የሚችለውን ያህል “ታሪካዊና ህጋዊ ሰነዶችን በሚገባ በማገላበጥ አቋም ሊወሰድና የደረሱትን ጥፋቶች መመለስ ይገባል” ብለዋል። ይህ አባባላቸው ፖለቲካዊ ትክክለኝነትን እንጂ ተግባራዊ መፍትሔን አያሳይም። ይህንን እያሉ ያሉት ከህወሓት አመራርነታቸው እስከተለዩበት ድርስ ያለውን ጊዜ  ብናሰላ እንኳ አቋም ከተወሰደ ከ27 ዓመታት በኋላ መሆኑ ነው። የህወሓት አመራር የወቅቱ አቋም ምንም ሆነ ምን ኤርትራ ነፃ ሀገር ከሆነች 24 ዓመቷ ልትደፍን ተቃርባለች። እንደ ፖለቲካ ሰውና ፓርቲ መሪ ያሁኑ ፀፀታቸው ምን ሊጠቅመን ይችላል? ህወሓት ያኔ የወሰደው ፖለቲካዊ አቋም እንደ ዘበት ስሕተት ሆኖ ቢገኝ እንኳን ባለንበት ጊዜ በምን መልኩ ተስተካክሎ ወደ ተግባር የሚተረጎም ህጋዊና ሰላማዊ የኢትዮጵያ ጥቅም ሊለወጥ ይችላል? “ችግሩን እንጂ መፍትሔውን አላውቅም” ዓይነት ኣካሄድ የመረጡ ይመስለኛል። ከዚህ ሁሉ ግርግርና እንካ ሰላንትያ በኋላም በዚሁ ጥያቄ ላይ ያበረከቱት አዲስ እውቀት ያለ አይመስለኝም። የነገሩን ተፈጥሮ ጥግ ብናደርሰው ደግሞ እስኪበቃን ስንጋተው የኖርነውን የትምክህቱ ጎራ ቅጥያ ሃሳብ ነው። ህወሓት/ኢህአዴግ ለመቃወም ሌላ ወንበር(state) ያለ የማይመስለው ተቋሚ አካል ናቸውና አልፈርድባቸውም። ስለሆነም ጠቅልለው የብሔር ብሔረሰቦችን መብት ለምን ተከበረ ብሎ ከሚበግነው ሃይል ጋር መሰለፍ ነበረባቸው። ምክንያቱም ሰልፍ ካላሳመሩ መፅሐፍ መሸጥም በራስ አቋም ላይ የሚገነባ ፖለቲካኛነትም ባለቤት መሆን በዋዛ የሚታደሉት ጉዳይ አልሆነምና ነው።

ሲጠቃለል የኤርትራ ጥያቄ  የቅኝ ግዛት ወይስ የራስን ዕድል በራስ የመወሰን ጥያቄ የሚለውን ጉዳይ በመሰረቱ ለችግሩ መፍትሔ ብዙም ፋይዳ ያልነበረውና አሁንም የሌለው ጥያቄ ነው። የችግሩ መንስኤ ምንም ይሁን ምንም መፍትሔው ግን የኤርትራን ህዝብ በድምፀ-ውሳኔ ዕድሉን እንዲወስን ከማድረግ ውጪ ሌላ አማራጭ አለመኖሩን በመሆኑም ህወሓት በዚሁ ረገድ የወሰደውን ታሪካዊ አቋም ለኤርትራ ተብሎ የተወሰደ አቋም ሳይሆን ኢትዮጵያ በጊዜው  አጋጥመዋት ከነበሩት አንገብጋቢ ጥያቄዎች የኤርትራን ጉዳይ ከመፍታት ውጪ  የሚፈቱ እንዳልነበሩ አበክሮ በመገንዘቡ ነው በዬ አምናለሁ። ጉዳዩ በምልሰት ሲመዘንም የአፈታቱ ብስለት በእጅጉ የሚደነቅ ጊዜ የማይሽረው ህያው ታሪክ ነው። የኢትዮጵያችን የጤንነት ጉዞም ከዚሁ እርምጃ ይጀምራል።

… ይቀጥላል

**********

Teweldebrhan Kifle

more recommended stories