ኢ-ተቋማዊ፣ ኢ-ደንባዊ ተፅዕኖ ተደርጎብኛል – ኢ/ር ግዛቸው ሺፈራው (የአንድነት የቀድሞ ሊቀመንበር)

የአንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ ሊቀመንበር የነበሩትና በታህሳስ ወር 2006 ዓ.ም በተካሄደው ምርጫ ከፍተኛ ድምጽ በማግኘት ኃላፊነት የተረከቡት ኢንጂነር ግዛቸው ሺፈራው ሰሞኑን በራሳቸው ፈቃድ በድንገት ከኃላፊነታቸው ለቀዋል። የአንድነት ፓርቲ ብሔራዊ ምክር ቤት ሰሞኑን ስብሰባ አካሂዶ የኢንጂነር ግዛቸውን መልቀቂያ በመቀበል በምትካቸው ከወራት በፊት ከፓርቲው ሥራ አስፈፃሚነት ራሳቸውን ካገለሉት አንዱ የነበሩትን አቶ በላይ ፍቃዱን ቀጣይ ፕሬዚዳንት አድርጎ መርጧቸዋል። ኢንጂነር ግዛቸው ኃላፊነታቸውን ለምን በድንገት ሊለቁ እንደቻሉ ባልደረባችን ፍሬው አበበ አነጋግሮአቸዋል።

ፍሬው አበበ፡- ከኃላፊነትዎ በድንገት ሊለቁ የቻሉበት ምክንያት ምንድነው?

ኢ/ር ግዛቸው፡- ይህንን ሁኔታ ጥቅምት 1 ቀን 2007 ዓ.ም ለሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ፣ ጥቅምት 2 ቀን 2007 ዓ.ም ለብሔራዊ ምክር ቤቱ ባስገባሁት የሥራ መልቀቂያ ደብዳቤ ገልጫለሁ። ሪፖርትም አቅርቤያለሁ። በዚሁ መሠረት ነው ጉዳዩን የማብራራው። ዋናው የለቀኩበት ምክንያቴ በአጠቃላይ መልኩ ከውስጥ እና ከውጪ ሀገር በአንድነት ፓርቲ ላይ በተደረገ ኢ-ተቋማዊ፣ ኢ-ደንባዊ እና ቡድናዊ ተፅዕኖ ምክንያት ነው። የአንድነትን ሥራ ከተቋም፣ ከደንብ የማስወጣት ሥራ ስላለ ነው። ይህንን ነገር በሁለት ከፍዬዋለሁ። በውጪ ሀገር እና በሀገር ውስጥ በተደረገ ቡድናዊ ተፅዕኖ በሚል። በውጪ ሀገር ኢትዮጵያዊያን እና ትውልደ ኢትዮያዊያን የምንላቸው ከ10 እስከ 20ሺ ኪሎ ሜትር ርቀው ያሉ ዲያስፖራዎች ከፍተኛ ክብር የምንሰጣቸው ናቸው። ሦስትም ሆነ ሃያ ዓመታት በውጪ ሀገር ተቀምጠው ሀገራቸውን አልረሱም። በፖለቲካው አካባቢም የተሻለ ለውጥ እንዲኖር አጠቃላይ ዲያስፖራው ያለውን አስተዋፅኦን በበጎ መልኩ ነው የማየው። ለዚህም በግሌ ከፍተኛ አክብሮትና አድናቆት አለኝ። ነገር ግን አጠቃላይ መልኩ ጥሩ ሆኖ በአጋጣሚ በአንዳንድ መሪነት የሚቀመጡ ሰዎች ያለውን በጎ ነገር ለመጥፎ ሥራ ይጠቀሙበታል። የአንድነት የድጋፍ ሰጪ ማኅበራት በውጪ ሀገር አሉ፤ እነሱ በእኔ ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ አድርገዋል። ኢ-ተቋማዊ፣ ኢ-ደንባዊ በሆነ መንገድ።

ፍሬው አበበ፡- ተፅዕኖው ምንድነው? Gizachew Shiferaw - UDJ Andinet former Chairman

ኢ/ር ግዛቸው፡- አንድነትን እንደ ኤጀንት የመጠቀም ፍላጎት አላቸው። በገንዘብ ይረዱናል፣ በዚያ ምክንያት የማዘዝ፣ የአንጋሽነት ሚና ለመጫወት ይሞክራሉ፤ ይህንን ደግሞ እኔ አልቀበልም። እነሱ የፓርቲው ደጋፊ ናቸው እንጂ የወሳኝነት ቦታውን ይዘው፣ ግዛቸው ይውጣ፣ እገሌ ይምጣ ሊሉ የሚችሉበት ሁኔታ ሊኖር አይችልም። እናም በየሚዲያውና ማኅበራዊ ድረገጾች ከፍተኛ ዘመቻ ነው ያካሄዱት። ይህም የሆነበት ምክንያት በእነሱ ትዕዛዝ ባለመመራቴ ነው። እኔ ደግሞ እስካለሁ ድረስ አንድነት የራሱ ተቀም፣ ብሔራዊ ም/ቤት አለ፣ ጠቅላላ ጉባዔ አለ፣ ፓርቲውን የሚያንቀሳቅሰው በኢትዮጵያ ያለው ተጨባጭ ሁኔታ ነው። እነሱ ደጋፊዎች ናቸው፣ እንደ ኢትዮጵያዊ ድምፃቸው ማሰማት፣ ኅሳባቸውን መግለጽ ይችላሉ። ግን አሠራሩ መዋቅራዊ መሆን አለበት። ግዛቸውን ካልፈለጉት እኔን የሚያወርደኝ ጠቅላላ ጉባዔ እና ብሔራዊ ምክር ቤቱ ነው። ስለዚህ ለእሱ ደብዳቤ መፃፍ ይችላሉ። በራሳችን ድረገጽ ላይ ግዛቸው ይውረድ፣ ፒቲሽን እንፈራረማለን የሚለው እጅግ አሳፋሪና ኢ-ተቋማዊ፣ ኢ-ደንባዊ፣ ኢ-ዴሞክራሲያዊ አካሄድ ነው። ይህ ሁኔታ ከፍተኛ ልዩነት ፈጥሯል። በዚህ ምክንያት የገንዘብ ማዕቀብ አድርገዋል። የሚያሳዝነው የኢትዮጵያ ተቃዋሚ ፓርቲ የውጪ ሀገር ጥገኛ ነው። የሪሶርስ፣ የገንዘብ ጥገኛ ነው። ይሄ የሚያሳፍር ነው። በእኛም በኩል ይሄ ነገር እንደ ድክመት መውሰድ አለብን። ይህንን የገንዘብ ግንኙነታችንን መሠረት በማድረግ እኛን ማዘዝ ይፈልጋሉ። እኔ ደግሞ ዓላማ አለ፣ መርህ አለ፣ ደንብ አለ፣ ተቋም አለ፤ የአንድነት ኃይል ያለው አዲስ አበባ ነው። ከውጪ የሚመጣ ኃይል አይነቀንቀውም የሚል ጽኑ አቋም አለኝ። ገንዘቡን መርዳታቸው ደግሞ የዜግነት ግዴታቸው ነው፤ ዕርዳታ አታድርጉት ብዬ ብዙ ጊዜ ነግሬያቸዋለሁ። እኛ እዚህ እሥራት፣ ክትትልና ወከባ ችለን ነው ያለነው። ይህ መስዋዕትነት ከገንዘብ በላይ ነው። ገንዘብ መርዳት የዜግነት ግዴታ እንጂ አንድነትን ወይም ግዛቸውን በግል መርዳት ሊሆን እንደማይችል ነግሬያቸዋለሁ።

ሀገር ውስጥ ያለው ከውጪው ጋር የተያያዘ ነው። ትልቁ ችግራቸው ግንኙነታቸው ተቋማዊ ሳይሆን ግለሰባዊ ነው። እንደዚሁም ቡድናዊ ነው። የዚያ ነፀብራቅ ሀገር ውስጥ አለ። ከእነሱ ጋር የሚገናኙ፣ ፓርቲውን ተቋማዊ ባልሆነ መንገድ ለመምራት የመሞከር ነገር አለ። ሰሞኑን የተወሰኑ ቡድኖች መቀሌ ሄደው ከአረና ፓርቲ ሰዎች ወደ አንድነት ፓርቲ አስገብተዋል። ይህ ፓርቲው ሳያውቀው የተደረገ ነው። ይሄ ተቋማዊ አይደለም። ሌሎችም ብዙ ችግሮች አሉ። እኔን የመረጠኝ ጠቅላላ ጉባዔ ነው። በቂ ድጋፍም አለኝ። መቀጠል እችላለሁ። ግን በእንዲህ ዓይነት ተቃርኖ እና አለመግባባት የእኔ በኃላፊነት ላይ መቀጠል የሚጎዳው አንድነትን ነው። ስለዚህ መልቀቁ ጥሩ አማራጭ ሆኖ አግኝቼዋለሁ።

ፍሬው አበበ፡- በሀገር ውስጥም በውጪም የነበረብዎት ተፅዕኖ ኃላፊነትዎን እንዲለቁ የሚጠይቅ ጭምር ነበር?

ኢ/ር ግዛቸው፡- አዎ! በቀጥታ ኃላፊነቴን እንድለቅ የሚጠይቅ ነው። ፒቲሽን ለማሰባሰብም ሞክረዋል። ደብዳቤም ጽፈውልኛል። እኔ ግን ከሁሉም በላይ የሚያሳስበኝ የአንድነት ፓርቲ ሠላም ጉዳይ ነው። ግዛቸው ወርዶ ሌላ መምጣት ይችላል።

ይሄ ነገር ሰፋ ባለ መንገድ የታቀደበት ነው ብዬ አምናለሁ። በምርጫ 2002 ዋዜማ አንድነት ከፍተኛ ውዝግብ ውስጥ ገብቶ ነበር፤ በተወሰኑ ቡድኖች። አሁን ሰዎቹ ሰማያዊ ፓርቲ ውስጥ ነው ያሉት። በምርጫ ዋዜማ አሁንም እንዲህ ዓይነቱ ፕሮጀክት የተደገመ ይመስለኛል። ይህ የእኔ የግል አስተያየት ነው። ወደኃላፊነት ስመጣም ፈልጌ ሳይሆን አባላቱ ጠይቀውኝ ነው። በምርጫው ወቅት የተገኘው ድምፅ እኔ 327 ሳገኝ ተወዳዳሪዬ የነበረው አቶ ግርማ 29 ድምፅ ነው ያገኘው። አሁንም በአዲስ አበባም በክልልም ከፍተኛ ድጋፍ አለኝ። በኃላፊነቴ ላይ ለመቀጠል ምንም ችግር አልነበረብኝም። ነገር ግን እስቲ ሌላ መንገድ የለም ወይ ከሚለው አንፃር ለፓርቲው ሠላምና ቀጣይነት በማሰብ ጭምር ያደረኩት ነው።

በኢትዮጵያ የተቃውሞ ፖለቲካ ውስጥ ያሉ ችግሮችና ውዝግቦች በምርመራ ጋዜጠኝነት ሊሠራ የሚገባው ይመስለኛል። መኢአድ፣ ሰማያዊ፣ እኛም ጋር ችግር አለ። ይሄ ምንድነው በሽታው ብለን መመርመርና ማወቅ አለብን። ምናልባት ከኅብረተሰባችንም አስተሳሰብ ሊሆን ይችላል። የዴሞክራሲ ባህላችን ገና ያልዳበረ ስለሆነ ልዩነትን አናስተናግድም። ልዩነትን የምንወስደው ወደ ጠብ ነው። የመቧደን ባህርይ አለን።

ፍሬው አበበ፡- ከአንድ ወር በፊት ራሳቸውን ከአንድነት ሥራ አስፈፃሚ ያሰናበቱ አባላት የዚህ የተፅዕኖው አካላት ነበሩ ማለት ይቻላል?

ኢ/ር ግዛቸው፡- አዎ! በውጪ ሀገር ካሉት ጋር ግንኙነት አላቸው። በውጪ ያሉትም የሚፈልጉት ይህ ቡድን ወደ ሥልጣን እንዲመጣ ነው።

ፍሬው አበበ፡- በአጠቃላይ በፓርቲ ውስጥ የሚታየው ቡድናዊ ስሜት የሚጠቅም ነው ብለው ያስባሉ?

ኢ/ር ግዛቸው፡- አይጠቅምም፤ ለአንድነት ፓርቲ ብቻ አይደለም፤ ለኢትዮጵያ ፖለቲካም አይጠቅምም።
******
ምንጭ፡- ሰንደቅ
ጋዜጣ፣ ጥቅምት 2007

Content gathered and compiled from online and offline media by Hornaffairs staff based on relevance and interest to the Horn of Africa.

more recommended stories