የአማራ ክልላዊ መንግስት ለ2,094 የህግ ታራሚዎች ይቅርታ አደረገ

የአማራ ክልላዊ መንግስት የዘመን መለወጫን በዓል ምክንያት በማድረግ ለሁለት ሺህ የህግ ታራሚዎች ይቅርታ ማድረጉን የክልሉ ፍትህ ቢሮ አስታወቀ።

የቢሮው ኃላፊ አቶ ፍርዴ ቸሩ ዛሬ እንደገለጹት የክልሉ መንግስት የህግ ታራሚዎቹን በይቅርታ የለቀቀው በማረሚያ ቤት ቆይታቸው በፈፀሙት ወንጀል ተጸጽተው የባህሪ ለውጥ በማምጣታቸው ነው።

ታራሚዎቹ የባህሪ ለውጥ ስለማምጣታቸው በክልሉ በተቋቋመው የይቅርታ ቦርድ ተጣርቶ ለክልሉ ምክር ቤት ስራ አስፈጻሚ ለውሳኔ በቀረበው መሰረት ይቅርታው የተሰጣቸው መሆኑን ገልጸዋል።

ለታራሚዎች ይቅርታ የሚሰጠው በክልሉ መንግስት ተሻሽሎ በፀደቀው የይቅርታ አዋጅ ቁጥር 136/98 መሰረት በሀገር፣በህዝብ ጥቅምና ደህንነት ላይ ስጋት ለማይሆኑ የህግ ታራሚዎች እንደሆነም አስታውቀዋል፡፡

ይቅርታው በዘር ማጥፋት፣በሙስና፣ በጠለፋ፣ በአስገድዶ መድፈር፣ በውንብድና፣ በሰዎች ዝውውር፣በታክስ ማጭበርበርና ሌሎች ከባድ ወንጀሎች ጥፋተኛ ተብለው በህግ የተፈረደባቸውን ታራሚዎች እንደማያካትት ገልጸዋል።

የክልሉ መንግስት በማረሚያ ቤት ቆይታቸው የተሻለ ባህሪ ላመጡ ታራሚዎች ይቅርታ ያደረገላቸው በክልሉ ህዝብ ስም መሆኑን ገልጸው የይቅርታው ተጠቃሚዎች መስከረም አንድ ቀን ከማረሚያ ቤቱ እንደሚለቀቁ አስታውቀዋል፡፡

ታራሚዎቹ ወደ ህብረተሰቡ ሲቀላቀሉ ህብረተሰቡ በፈፀሙት ወንጀል መታረማቸውን በመረዳት ተቀብሎ እንዲንከባከባቸውና እንዲደግፋቸው ግንዛቤ የማስጨበጥ ስራ መሰራቱን ተናግረዋል።

የክልሉ መንግስት በይቅርታ መልቀቅ ከጀመረ ከ1999ዓ.ም ጀምሮ እስካለፈው ዓመት በይቅርታ በተለቀቁት ታራሚዎች ላይ ባካሄደው ጥናት 99 ነጥብ 3 በመቶ የሚሆኑት ዳግም ወንጀል ሳይፈጽሙ ከህብረተሰቡ ጋር በሰላም እየኖሩ መሆናቸውን ማረጋገጥ መቻሉን አቶ ፍርዴ ገልጸዋል፡፡
********
ምንጭ፡- ኢዜአ፣ ጳጉሜን 3/2006.

Content gathered and compiled from online and offline media by Hornaffairs staff based on relevance and interest to the Horn of Africa.

more recommended stories