የዓባይ ልጆች ትንቅንቅ በታላቁ ሐይቅ – ቪክቶርያ

(በየማነ ናግሽ) 

ነሐሴ 4 ቀን 2006 ዓ.ም. ነው፡፡ በከፍተኛ ዶፍና ንፋስ የታጀበው የጠዋቱ ዝናብ ከቤት የሚያስወጣ አልነበረም፡፡ እንኳን ታክሲ ለሚጠብቅ ይቅርና የራሱን መኪና ለያዘም ሰው ብርዱ፣ ቅዝቃዜው የሚቋቋሙት አይደለም፡፡  የያዝኳት ትንሽ ጥላ ከኃይለኛው ንፋስና ዶፍ ጋር እየተታገለች ብዙም አላስጣለችኝም፡፡ ከተባለው ሰዓት ትንሽ ደቂቃዎች አሳልፌ ነበር በዓለም አቀፉ ቦሌ አየር ማረፊያ የደረስኩት፡፡

በማቆያ ስፍራም ወደተለያዩ አካባቢዎች የሚጓዙ ኢትዮጵያውያን፣ ጥቁር አፍሪካውያን፣ ሕንዳውያን፣ ቻይናውያንና አንዳንድ ዓረቦችም ይታያሉ፡፡ ወደማመራበት ጉዳይ አብረውኝ የሚጓዙ ሌሎች ሦስት ኢትዮጵያውያን መኖራቸውን ቀደም ብዬ ከመድረኩ አዘጋጆች ከተመላለስናቸው የኢሜይል መልዕክቶች የተገነዘብኩ ቢሆንም፤ ከወዲሁ ከማቆያ ስፍራ መለየት አልቻልኩም፡፡ Nile river basin

ከኢትዮጵያ ተነስተን ለአንድ ሰዓት ከአርባ አምስት ደቂቃ ያህል ከተጓዝን በኋላ በኢንቴቤ አየር መንገድ ለማረፍ ጥቂት ደቂቃዎች እንደሚቀሩን ተነግሮን አረፍን፡፡ የኢንቴቤ የአውሮፕላን ማረፊያ፤ የአገሪቱ ትልቁ የአውሮፕላን ማረፊያ ቢሆንም፤ ቦሌ የአውሮፕላን ማረፊያ አያህልም፡፡ የአየር ሁኔታው ግን የበረራ አገልግሎቱ ቀደም ብሎ እንደነገረን፤ ረጋ ያለና መልካም የሚባል ዓይነት ነበር፡፡

አሻራ ለመስጠት ወረፋ ይዘን ለብዙ ሰዓት ቆመናል፡፡ በአራት የወረፋ መስመሮች ከቆሙ ተሳፋሪዎች መካከል ከጥቁር አፍሪካውያን ይልቅ ከግማሽ በላይ ሕንዳውያን ሲሆኑ፣ ጥቂት ቻይናውያንም ነበሩ፡፡ ኋላ ላይ ጠይቄ ለማወቅ እንደቻልኩት፤ ዑጋንዳ፣ ኬንያና ታንዛንያ ውስጥ ያሉት የንግድ እንቅስቃሴዎች በሕንዳውያን መያዙን ነው፡፡ እንግሊዛውያን በእንግሊዝ ቅኝ ግዛት ሥር በነበሩት አገሮች ሕንዳውያንን እያመጡ ያሰፈሩዋቸው ለም መሬት ላይ ሲሆን ብዙዎቹም የተዋጣላቸው ነጋዴዎች ናቸው፡፡ በእነዚህ አገሮች ያሉት ሕንዳውያንም እንደ አንድ ማኅበረሰብ በአንዳንድ የንግድ እንቅስቃሴዎች እርስ በርስ የሚተባበሩ መሆናቸውን ተገንዝቤያለሁ፡፡ በተለይ የኤሌክትሮኒክስ ንግድ በእነሱ ቁጥጥር መሆኑ ተነግሮኛል፡፡

የአካባቢው ነዋሪ ለሕንዳውያኑ አሉታዊ ምልከታ የለውም፡፡ እንዲያውም አንዳንድ የእርሻና የንግድ ዕውቀት ይዘው ስለገቡ ብዙ ሰው እንደሚወዳቸው ሰምቻለሁ፡፡ ይህንን ስሰማ በተለያዩ የአገራችን አካባቢዎች ደገኞች እየተባሉ ለዓመታት ኑሮ መሥርተውና ንብረት አፍርተው ወደ ትውልድ ቦታችሁ ካልሄዳችሁ ተብለው የሚፈናቀሉት ወደ ጭንቅላቴ መጡብኝ፡፡

ኢንቴቤ

ለአንድ ሰዓት ያህል ወረፋ ይዘን አሻራ ከሰጠን በኋላ ከኤርፖርቱ መውጪያ ‹‹VOA›› የሚሉ በትላልቅ ፊደላት የተጻፉባቸው ባጅ ያንጠለጠሉ ሰዎች አየን፡፡ ተቀባዮቻችን መሆናቸው ነው፡፡

በኢትዮጵያ አየር መንገድ ትራንዚት አድርገው ከመጡት የምሥራቅ አፍሪካ ጋዜጠኞች ጋርም ተገናኝተናል፡፡ እንዲሁም የግብፅ ጋዜጠኞችን እዚሁ ነበር የተዋወቅናቸው፡፡ አንድ ወንድና ሦስት ሴቶች የነበሩ ሲሆን አንደኛዋ ‹‹መይ እባላለሁ፤ ግብፃዊ ነው የምትመስለው›› በማለት ነበር የተዋወቀችን፡፡

ሁሉም እስኪመጡ በአንድ ማቆያ ስፍራ የጠበቅን ሲሆን፣ እጅግ ዘግይተው የወጡት ኢትዮጵያውያኖቹ ጋዜጠኞች ነበሩ፡፡ ከባልደረቦቼ እንደሰማሁት ከሆነ፤ የደህንነት ሠራተኞች ኢትዮጵያውያንን እየለዩ በአንድ ስፍራ በማቆየት የተለየ ምርመራ እያደረጉባቸው ነበር፡፡ ብዙ ኤርትራውያንና ሶማሊያውያን በኢትዮጵያ ፓስፖርት መግባታቸውም ለዚሁ ምክንያት እንደሆነ ለማወቅ ብችልም የአልሸባብ ጥቃት ሰለባ የሆነችው ዑጋንዳ በኢትዮጵያውያን ላይ ብቻ ልዩ ምርመራና እንግልት የምታደርግበት ምክንያት ግን ግልጽ አይደለም፡፡

ግብፃውያኑ ‹‹ወንድሞቻችን፣ እህቶቻችን›› በሚሉ የእንግሊዝኛ ቃላቶች ደጋግመው ሲያወሩ ነበር፡፡ የተመደበልን መኪና የተያዘልን ሆቴል እስኪደርስ ድረስ የግብፃውያኑ ድምፅ ጮክ ብሎ ነበር የሚሰማው፡፡ አራቱም የግብፅ ጋዜጠኞች በደንብ የሚተዋወቁ መሆናቸው ከአነጋገራቸው ይታወቃል፡፡

መይ አሁንም፤ ግብፃውያንን እንደምንመስል ነገረችን፤ ሌላው አብሮን የነበረ ጥቁር አፍሪካዊም ሱማሌ እንደምንመስል ነገረን፣ ሌላኛውም፤ ኤርትራውያን እንደምንመስል ነበር ያወራው፡፡ እኛ እርስ በእርሳችን ተያይተን ነገሩ ፈገግ አሰኘን፡፡ ‹‹እነሱ እኛን ይመስላሉ ወይስ እኛ እነሱን እንመስላለን?›› የሚል ጥያቄ በሁላችንም ውስጥ የተፈጠረ ይመስላል፡፡ በእርግጥም፤ በዚሁ የአንድ ሳምንት የዑጋንዳ ቆይታችን ውስጥ ብዙዎች ‹‹Where are you from?›› የሚለው ጥያቄያቸውን ሳይጨርሱ ‹‹ኤርትራዊ ነህ/ነሽ፣ ሶማሊያዊ ነህ/ነሽ›› የሚሉ ግምቶች ፈጥነው ሲናገሩ አስተውለናል፡፡

ከኢትዮጵያ የሔድነው ጋዜጠኞች ፆታ ስብጥር የግብፃውያኑን ተቃራኒ ሲሆን፣ አንድ ሴትና ሦስት ወንዶች ነበርን፡፡ እኔ ከሪፖርተር፤ መስከረም ጌታቸው ከኢሬቴድ፣ አረጉ ባሌህ ከሔራልድ እንዲሁም ግሩም አባተ ከካፒታል ጋዜጣ ይገኙባቸዋል፡፡

በዑጋንዳ ቆይታችን ኢንቴቤ ውስጥ ‹‹ሌክ ቪክቶርያ›› በተባለው ሆቴል ነበር ማረፊያ የተያዘልን፡፡ ስብሰባውም ውይየቱም በአብዛኛው እዚሁ ሆቴል ውስጥ ነበር የተዘጋጀው፡፡ ሌክ ቪክቶርያ ሆቴል፣ ታላቁ ሐይቅ በሚል የሚታወቀው የቪክቶርያ ወንዝ ስያሜ የተሰጠው ሲሆን፤ በአገሪቱ ከሚገኙት ትላልቅ ሆቴሎች መካከል ነው፡፡ የአገሪቱ ዋና ዋና የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች በዋና ከተማዋ በካምፓላ የሚገኙ ቢሆንም፤ የአገሪቱ ትልቁ ኤርፖርት፣ የፕሬዚዳንቱ መኖሪያና አንዳንድ ትላልቅ ተቋሞች እዚህ ከተማ ይገኛሉ፡፡

ሌክ ቪክቶርያ ሆቴል ከኤርፖርቱ በቅርብ ርቀት ሲገኝ አጠገቡም የአገሪቱ የዕፀዋትና የዱር እንስሳት ማዕከላት ይገኛሉ፡፡ 144 መኝታ ያለው ይኼው ባለ አራት ኮከብ ሆቴል፤ የመዋኛ ገንዳ ጨምሮ፣ የመዝናኛ ፓርክ ያለው ሲሆን፣ አንድ ዓለም አቀፍ ሆቴል ሊኖረው የሚችል ሙሉ አገልግሎቶች ይገኝበታል፡፡ ከአንድ ጫፍ ወደ ሌላው ጫፍ ለመድረስ ረዥም የእግር ጉዞ የሚጠይቅ ሲሆን፣ ያረፈውም በ4180 ስኩየር ካሬ ሜትር ላይ ነው፡፡ ትላልቅ የመሰብሰቢያና የቢዝነስ አዳራሾችም አሉት፡፡

የናይል ልጆች- በትንሿ ክፍል

እኛ ኢትዮጵያውያን ዓባይ እያልን የምንጠራው የተቀረው ዓለም ‹‹ብሉ ናይል›› እያለ የሚጠራውን ነው፡፡ አኮቦንና ተከዜን ጨምሮ በሦስት አቅጣጫ የሚመጡ ወንዞች ዓባይን ይገብሩታል፡፡ ኢትዮጵያ ብቻ የዓለማችን ረዥሙ ለሆነው ናይል ወንዝ ከ86 በመቶ በላይ ውኃ ታመነጫለች፡፡ በጠቅላላ አሥር አገሮች እንደአቅማቸው ለናይል ወንዝ አስተዋጽኦ ያደርጋሉ፡፡ ወንዙን ጥቅም ላይ ያዋለች ብቸኛዋ አገር ግን ሙሉ ለሙሉ የውኃው ተቀባይ የሆነችው ግብፅ ናት፡፡ ግብፅ ለወንዙ የምታደርገው አስተዋጽኦ የለም ማለት ይቻላል፡፡ በተቃራኒው ለወንዙ ትልቅ አስተዋጽኦ የምታደርገው ኢትዮጵያ ከተቀሩት አገሮች በሙሉ ኋላ ቀርና ሕዝቦቿ በድህነት የሚማቅቁባት ብቸኛ አገር ነች፡፡

በቅርቡ ኢትዮጵያ የውኃ ሀብቷን ለመጠቀም በምታደርገው ጥረት ከግብፅ ጋር የገባችበት እንካስላንትያ የሚታወቅ ነው፡፡ ላለፉት አሥር ዓመታት በተደረገው የጋራ ጥረት አንድ የጋራ የሕግ ማዕቀፍ (CFA) ለማፅደቅ የተደረገ ጥረት መና አልቀረም፡፡ ግብፅና ሱዳን በእምቢተኝነታቸው ጸንተው አልፈረሙም፡፡ ስድስት ፈራሚ አገሮች በፓርላማቸው ለማስጸደቅ በሒደት ላይ ይገኛሉ፡፡ ታንዛንያ፣ ኬንያና ዑጋንዳ ወደ ፓርላማቸው በማቅረብ ላይ ይገኛሉ፡፡ ኢትዮጵያና ሩዋንዳ በፓርላማቸው አጽድቋል፡፡

እነዚህንና ሌሎች የፕሮፌሽናሊዝም ጉዳዮች ላይ ለመወያየት ይመስላል አንድ ፕሮግራም የተዘጋጀው፡፡ በአሜሪካ መንግሥት ወጪና በአሜሪካ ድምፅ ሬዲዮ እንዲሁም እዚያው ኢንቴቤ በከተመው ናይል ቤዚን ኢንሽየቲቭ አስተባባሪነት የተዘጋጀው ይኼው የውይይት መድረክ ከኤርትራ ውጪ፣ ከግብፅ ከኢትዮጵያና ከዑጋንዳ እያንዳንዳቸው አራት አራት፣ ከኬንያ ሦስት፣ ከታንዛኒያ ሁለት እንዲሁም ከሱዳን፣ ከደቡብ ሱዳን፣ ከብሩንዲና ከኮንጐ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ እያንዳንዳቸው አንድ አንድ ጋዜጠኞች በጠቅላላ 24 የተጠሩበት ሲሆን፣ ጋዜጠኞቹ ከናይል ፖለቲካ ጋር በተያያዘ በስፋት በመዘገባቸው በእያንዳንዱ አገሮች በሚገኙ የአሜሪካ ኤምባሲዎች የተመረጡ ናቸው፡፡ ምርጫው ከሕትመትም ከኤሌክትሮኒክስም ያካተተ ሲሆን፣ ዘጠኝ ሴቶች የተቀሩት ወንዶች ናቸው፡፡

የቪኦኤ የበላይ ጠባቂ ብሮድካስቲንግ ቦርድ ኦፍ ዳይሬክተር የተቋሙ የዓለም አቀፍ የሥልጠና ኃላፊ ሚስስ ጆአን ሞወር እንዲሁም የናይል ተፋሰስ ኢንሽየቲቭ (NBI) ኤክስኪዩቲቭ ዳይሬክተር አቶ ተፈራ በየነ በንግግር የከፈቱት መድረክ ለአንድ ሳምንት የቆየ ሲሆን ወደ አንዳንድ ወሳኝ ቦታዎችም የጉዞ ፕሮግራሞችን አካቷል፡፡

ራሳችንን ባስተዋወቅንበት የመጀመርያ ቀን የመጣንበትን ድርጅትና አገር እንዲሁም ከመድረኩ የምንጠብቀውን ነገር ገለጽን፡፡ ሁለት ግብፃውያን ሴትና ወንድ አጠገቤ ተቀምጠዋል፡፡ የመጀመርያው ጽሑፍ አቅራቢ ዶ/ር አብዱል ካሪም ሰይድ በNBI ውስጥ የውኃ ሐብት አስተዳደር ኃላፊ ናቸው፡፡

‹‹Hydrology, Interconnectedness, Legal Regimes on the Nile›› በሚለው ርእስ ነበር ጥናታቸውን ያቀረቡት፡፡ ዶ/ር አብዱል አቀራረባቸው በጣም የተወደደና ለውይይት የሚጋብዝ ነበር፡፡ በአሁኑ ወቅት በናይል ዙርያ ያለው ብቸኛው የጋራ ተቋም NBI እንደሆነ ሆኖም ግብፅ ጥላ መውጣቷ ጉዳት እንጂ ጥቅም እንደሌለው ነበር ያወሩት፡፡

ጽሑፍ አቅራቢው ፊት ለፊት የተቀመጠችው ግብፃዊቷ መይ ኤል ሻፊ ተቅበጠበጠች፡፡ ገና በመጀመርያው ቀን መጀመርያው ጽሑፍ ላይ ብንሆንም፤ ጥናቱ ቀርቦ እስኪያልቅ ምንም ትዕግስት አላገኘችም፡፡ ጥናት አቅራቢውን አቋርጣ ‹‹NBI የተፋሰስ አባል አገሮችን አይወክልም›› ‹‹ግብፅ ለምን እንደወጣች ታውቃለህ?›› ወዘተ የሚሉ በጣም ከፍ ባለ ድምፅ የታጀቡ ጥያቄዎች አዘነበች፡፡ ዶ/ር አብዱል ጥያቄውን ተቀብላው ተገቢ ምላሽ ሰጡ፡፡ ግብፃውያኑ ምንም አልተዋጠላቸውም፡፡ ሌሎችም እያቋረጡ ለምን እንዲህ ሆነ ለምን እንዲህ ተደረገ በሚል አጥኚውን የማይመለከቱ አንዳንድ አስተያየትና ጥያቄም አዘነቡ፡፡ ቤቱ ግራ ተጋባ፡፡ ጥናቱን ጠቅልሎ ሳይቀርብ ጊዜ ሊያልቅ ሆነ፡፡ ጥናት አቅራቢው ከወሰዱት ጊዜ በላይ መይ ብዙ ጊዜ እየወሰደች ታወራለች፡፡ አዘጋጆቹም ግራ ተጋቡ፡፡ ‹‹መጀመርያ አቅርቤ ልጨርስና ጥያቄ ታነሳላችሁ ብለው፤›› በናይል ዙርያ የተደረጉ ድርድሮችና ያሉትን ስምምነቶች ጠቃቀሱ፡፡ ጥናቱ ከቀረበም በኋላ፤ ሌሎች ጋዜጠኞች ዕድል አላገኙም፡፡ ግብፆች እየተቀባበሉ አሰለቹን፡፡ በተሳታፊዎች ግራ መጋባት ይታያል፡፡ ጥናት አቅራቢው የግብፆችን አካሄድ የተገነዘቡ ይመስል፤ በተረጋጋ እና ሌሎች ተሳታፊዎችን ማዕከል ባደረገ መልኩ፤ የሌሎች አገሮችንም የመልማት ፍላጎት እያጣቀሱ መልስ መስጠት ቀጠሉ፡፡ አንድ ቀን ‹‹በኢንቴቤ ካምፕ›› የሐበሻ ሬስቶራንት የእራት ግብዣ ያደረጉልን አቶ ተፈራ በየነ፤ ጋዜጠኛዋን እንደሚያውቋት ነገሩን፡፡ በተገኘችበት መድረክ ሁሉ ተመሳሳይ ድርጊት እንደምትፈጽም፤ ሆን ተብሎ የሚሠራ እንደሆነም አወጉን፡፡

መጀመርያ በግብፆች የተደራጀ ተሳትፎ ደስተኛ ይመስሉ የነበሩ የመድረኩ አስተባባሪ፣ ጆአን ሞውር ፊታቸው እየተቀያየረ መጣ፡፡ መድረኩ በዚሁ ከቀጠለ የታሰበው ውይይትና ክርክር አይሳካም፡፡ ጠያቂዎች በቀረቡ ጥናቶች ላይ ብቻ እንዲያተኩሩ፣ ጥያቄያቸውንም ግልጽና አጭር እንዲሆን በተደጋጋሚ ተማጸኑ፡፡

ዶ/ር አብዱል በጉዳዩ ላይ ጥልቅ ዕውቀት ባይኖራቸው ኑሮ፤ ሆን ተብሎ የተቀነባበረው መድረክን የመቆጣጠር አልያም በናይል ጉዳይ በዘጋቢዎች ላይ ተፅዕኖ የማሳደር ስልት ይሳካ ነበር፡፡ NBI ‹‹እንዲህ ነው›› ‹‹ግብፅ የሌለችበት ተቋም እንደ አካባቢያዊ ተቋም መወሰድ አይችልም›› ወዘተ የሚሉና ተሳታፊዎችን የሚረብሽ ድምፀት ሲሰማ ነበር፡፡ ከአንድ ሰው ውጪ ሌላ ሰው ጥያቄ ለማቅረብ ሳይችል ክፍለ ጊዜው ተጠናቀቀ፡፡

ከሻይ ዕረፍት በኋላ፣ ሌላ ጥናት አቅራቢ እንስት ‹‹በናይል ለምን መተባበር አስፈለገ›› በሚል የናይል የውኃ አቅርቦት በተነፃፃሪ ትንሽ መሆኑ፣ አባል አገሮቹ የውኃ ፍላጎታቸው እየጨመረ መምጣቱ፤ ቀደም ሲል የነበሩት 1929 እና 1959 ስምምነቶችንና በተመለከተ፣ በላይኛውና በታችኛው ተፋሰስ አገሮች ያሉ ውዝግቦችን በተመለከተ ያቀርባሉ፡፡

ማይ አሁንም፣ ጥናት አቅራቢዋን አቋርጣ ሕጎቹ ምን ያህል ትክክል እንደሆኑ፣ እነዚህ ሕጎች በሌላ መተካት እንደሌለባቸው ተናገረች፡፡ ጥናት አቅራቢዋ ደሮዚ ካጋዋ፤ ግራ ተጋቡ፡፡ ሐሳባቸውን መጨረስ አልቻሉም፡፡ መጫን ከብዷቸዋል፡፡ አጠገቤ የተቀመጠውን ግብፃዊው መሐመድ ዋዲን ተመለከተች፡፡ መናገር እንዳለበት ተናበቡ፡፡ እሱም ቀጠለ፡፡ አጠገቡ የተቀመጠችውም ማይኩን ተቀበለች፡፡ አንዳንዴ የሚናገሩት ተደጋጋሚ ሐሳብ ነው፡፡ አጥኚዋ ስምምነቶቹ ከግብፅና ከሱዳን ውጪ የሌሎች አካል እንዳልሆኑ፣ የጋራ ስምምነትና ተቋም መመሥረት ለጋራ ትብብር ግድ መሆኑን አቀረቡ፡፡ ጥናታቸውንም ሳይጨርሱ እንዲያቆሙ ታስቦ ነበር፡፡ የሄራልዱ አረጉ ጥናቱ እንዲቀጥል ሐሳብ አቀረበ፡፡ ቀጥሎም በግብፆች እንቅስቃሴ ግራ የተጋባች የመድረኩ መሪ ሚስስ ጆአን አዲስ እጅ መፈለግ ጀመረች፡፡ እስካሁን በነበረው አካሄድ ከቀጠሉ ከመድረክ የምንጠብቀውን ያህል አናገኝም፡፡ ዕድል ተሰጠኝ፡፡ እዚህ የተገኘነው መንግሥትን ወክለን ሳይሆን፣ ፕሮፌሽናሎች በመሆናችን፣ የረጋ ክርክርና ውይይት እናደርግ ዘንድ ጥቂት ሰዎች ከመስመር እየወጡ ጊዜ መግደልን እንዲያቆሙ ስጠቁም ግብፆቹ ተጠቂነት ተሰማቸው፡፡ ከዚህ በፊት ካይሮ በሔድኩበት ወቅት ከታክሲ ሾፌር እስከ ዩኒቨርሲቲ ፕሮፌሰር ለናይል ያላቸው አስተሳሰብ አንድና ሙሉ ለሙሉ የተዛባ እንደሆነ፤ እነዚህ ጋዜጠኞችም የሚያቀርቡዋቸው አመለካከቶች የዚሁ አስተሳሰብ (mind set) እንደሆነ ገለጽኩ፡፡

እነዚህ የቆዩ ስምምነቶች (1929 እና 1959) በሁለቱም አገሮች የእንግሊዝ መንግሥት ራሱ የፈረማቸው፤ ሙሉ ለሙሉ ለግብፅ የተቀረውም ለሱዳን የሚሰጥ በመሆኑ ለሌሎች አገሮች ቅንጣት ታህል ውኃ እንደማይፈቅዱ፣ አገሮች እንደ ስምምነት እንዴት እንደሚቆጥሩዋቸው ግርምት እንደሚፈጥርብኝ ገለጽኩ፡፡ ‹‹መይ፣›› ማይኩን ይዛ ያዙኝ ልቀቁኝ አለች፡፡

የውኃ ደህንነት፤ ተፈጥሮዓዊ ውኃውን የመጠቀም መብት፤ ግብፅና የናይል ስጦታ፤ ወዘተ የመሳሰሉ ቃላቶች እየተደረደሩ እዚህ ግባ የማይባል ረዥም ጊዜ ወሰዱ፡፡

ጆአን ማይኩን ለመውሰድ እየፈለገች አሁንም ሁለቱ እጅ አወጡ፡፡ ሞና ስዊላም ለናይል ቲቪ ኢንተርናሽናል የምትሠራ ስትሆን የተሻለ እንግሊዝኛ ታወራለች፡፡ ቢያንስ ሐሳቧን በሚገባ መልኩ ትገልጻለች፡፡ ዕድሉ ተሰጣት፡፡ አሁን ድምፀታቸው እየቀነሰ መጥቷል፡፡ ግብፅ ካለው አጠቃላይ አስተሳሰብ ወጣ ብለው እንደ ፕሮፌሽናልና እንደ አዲስ ትውልድ እንዲያስቡ ያቀረብኩት አስተያየት አልጣማቸውም፡፡

በቀን ስድስት ጊዜ የመብራት መቆራረጥ እንደሚገጥማት ሞና አወራች፡፡ ‹‹የናይልን ውኃ መንካት በግብፃውያን ሕይወት መጫወት ነው፤ ናየል ሕይወታችን ነው…›› ቀጠለች፡፡ ሌሎች ጋዜጠኞች እየተገረሙ ነው፡፡ እየሆነ ባለው ግራ ተጋብተዋል፡፡ አሁንም መሐመድ ተነሳ ተመሳሳይ ነገር አወራ፡፡

ማርዋ ተውፊክ የዕውቁ የአልአህራም ጋዜጣ፣ ጋዜጠኛ ነች፡፡ እንኳን ለመድረክ የሚሆን ይቅርና ከሰው ጋር ለመግባባት የሚያስችል እንግሊዝኛ አትችልም፡፡ ግን ታወራለች፡፡ ምን እንዳለች የሚገባው ጥቂት ሰው ብቻ ነው፡፡ አንዳንዶቹ በመካከላችን እየሆነ ባለው ነገር ግራ የተጋቡ ይመስላል፡፡ አንዳንዶቹ ግን አስተያየት መስጠት ጀምረዋል፡፡ የመድረኩ መሪም በግብፃውያኑ መቅበዝበዝ የተሰላቹ ይመስል፡፡ እጅ ሲያወጡ እንዳላየ መሆን ጀመሩ፡፡ ደህና መከራከርያ የሚያቀርብ መሐመድ ብቻ ነው፡፡ እሱም ቢሆን ያለው መረጃ በሙሉ የተሳሳተ ነው፡፡

ከሁለት ዓመት በፊት ካይሮ ላይ በነበረኝ የአንድ ወር ቆይታ የታዘብኩት ምንም አልተለወጠም፡፡ አንዳንድ ግብፃውያን፣ የናይል ውኃ ከግብፅ ተነስቶ በኢትዮጵያ ዞሮ እንደሚመጣ ጭምር ያምናሉ፡፡ ፕሮፌሰሮችም እንዲህ ዓይነት እምነት ባይኖራቸውም፤ ከ‹‹አንዲት የደም ጠብታ የውኃ ጠብታ›› እንደሚበልጥባቸው የሚሰብኩ አሉ፡፡ ናይልን እንደመልአክ የናይል ውኃን የነካም እንደ ሰይጣን የሚቆጥሩም አሉ፡፡ ኢትዮጵያውያንን ከሰይጣን ጐራ ያስቀምጡናል፡፡ ጥናት አቅራቢዋ ገለልተኛ እንዳልሆነች ተናገሩ፡፡ ቅሬታቸውም በዚህ አላበቃም፡፡ ከግብፅ ጥናት አቅራቢዎች ለምን አልመጡም ብለው ያዙን ልቀቁን አሉ፡፡

መድረክ መሪዋ ቅሬታውን ተቀብለው የግብፅ አምባሳደር መጥተው ንግግር እንዲያደርጉ ዕድል እንሰጣለን አሉ፡፡ ባልታወቀ ምክንያት አልሆነም፡፡ በእራት ሰዓት ከፕሮግራሙ አዘጋጆች አንዷ አጠገባችን ተቀመጠች፡፡ ጉዳዩን ራሷ አነሳችልን፡፡ ‹‹ለመሆኑ ጋዜጠኞች ናቸው?›› ብስጭት አለችባቸው አለችን፡፡ መድረኩን ወዳልተፈለገ አቅጣጫ እየመሩ ሰው እንዳይነጋገር እያደረጉ እንደሆነ ማወቋን ነገረችን፡፡ የእኛም አቀራረብ እንደተመቻት ገለጸችልን፡፡ ከፕሮግራሙ በኋላ እኛ ባቀረብነው ማከራከርያና በጥናት አቅራቢዎች ገለልተኝነት ቅሬታ ቢጤ እንደተሰማቸው መግለጻቸውን አውቀናል፡፡ ፕሮግራሙ እንደተጠናቀቀ፤ የእራት ፕሮግራም ላይ አልተገኙም፡፡ በዑጋንዳ የግብፅ አምባሳደራቸው እንደወሰዳቸው ሰማን፡፡

ዝናብ ብርቃቸው

ቀን ሁለት፤ ውሏችን በናይል ቤዚን ኢንሼቲቭ ሴክሬታርያት ነበር፡፡ በፊት አንድ ጥናት አቅራቢ የሃይድሮ ኤሌክትሪክ ግድቦች ከፀሐይ፣ ከንፋስና ሌሎች የኃይል ምንጮች ሲነፃፀር በቀላል ወጪ የሚሠራ ነው፡፡ በውኃ ላይ የሚያደርሰው ጉዳትም የጐላ አይደለም በሚል አቅርበው ነበር፡፡ ግብፃውያን በተለይ ስለ ግድብ መልካም የሚያወራ እንደ ጠላት ነው የሚያዩት፡፡ መይም አሁንም ጮኸች፡፡ የተሰጣት ምላሽም የባሰ አናደዳት፡፡

ከዋተር ገቨርናንስ ኢንስቲትዩት የመጡት ሄነሪ ባዚራ ‹‹DAMS: The Environment Impact›› በሚል ጥናት አቀረቡ፡፡ ሄነሪ አቀራረባቸው ጥሩ ሆኖ ሳለ ገና ከጅምሩ ‹‹ይህንን ጥናት ስጀምር ኢትዮጵያ ውስጥ እየተሠራ ስላለው ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ማኅበራዊ ተፅዕኖ ጥናት ፈልጌ አጣሁ፡፡ በአግባቡ አልተጠናም›› ብለው በታችኛው አገሮች ሊያደርሰው የሚችል ጉዳት እንደሚኖር አቀረቡ፡፡ የኢትዮጵያን ሄራልድ አዘጋጅ አረጉ፤ ዕድሉ ተሰጥቶት አጥኚው የያዙት መረጃ የተሳሳተ መሆኑን የዓለም አቀፍ የውኃ ባለሞያዎች ቡድን ሪፖርት ዋቢ አድርጎ አስተያየትና ጥያቄ አቀረበ፡፡ ሰውየው ለግብፃውያን አዘኔታ ቢጤ እያሳዩም ቢሆን፤ የተለሳለሰ ምላሽ ሰጡ፡፡ በዚህ መሀል ዝናብ ጣለና ግብፃውያኑ ዝናብ ብርቅ ሆኖባቸው በመስኮት ለማየት ለጥናት አቅራቢው እንዲጠብቃቸው ዓይነት ጥያቄ አቀረቡ፡፡ ተሳታፊዎች በሳቅ ፈረሱ፡፡ እውነትም መይ በመጀመርያው ቀን ‹‹እኛ’ኮ ምንም አማራጭ የለንም፡፡ ዝናብ የሚባል አናውቅም፡፡ Egypt is desert›› የሚል ጩኸቷ ማረጋገጫ ይመስላል፡፡

አዲስ መረጃ ላለመስማት ጭንቅላታቸውን የዘጉት ግብፃውያኑ ለመጀመርያ ጊዜ የሚያስደስት ጥናት አቅራቢ አገኙ፡፡ ጥናት አቅራቢው በሃይድሮ ኤሌክትሪክ ግድቦች ምትክ በውቅያኖስ ውስጥ ሆነው ለመርከብ እና ለተመሳሳይ አገልግሎት የሚውሉ አዲስ ቴክኖሎጂ መጠቀምን ነበር እንደ መፍትሔ የጠቆሙት፡፡ ግብፃውያን ምሳም አልበሉም፡፡ አራቱም ለአንድ ሰዓት ያህል ቃለመጠየቅ ሲያደርጉላቸው ነበር፡፡ ማታውኑ በታላቁ የቪክቶርያ ወንዝ በነበረን የጀልባ ሽርሽርም ከሞና በስተቀር ሦስቱ አልተገኙም፡፡ አምባሳደራቸው እንደጠራቸው ለማወቅ ቻልን፡፡

ይህንን ደስታቸውን ግን ከአንድ ቀን በላይ አላጣጣሙትም፡፡ በግብፅም በኢትዮጵያም ለብዙ ዓመታት በግድቡ ልማት ላይ ጥናት ያደረጉ ኦላን ኒኮል የተባሉት ጥናት አቅራቢ በተለይ ኢትዮጵያ ድህነትን ለማጥፋት ግድቦች ከመሥራት ውጭ ምንም አማራጭ የላትም ሲሉ ደመደሙ፡፡ በእያንዳንዱ አገር ሌላ ተመራጭ ቴክኖሎጂ መኖሩንም ጠቁመው ነበር፡፡ ለመስኖ ጭምር ጥቅም ላይ እንዲውል መጠቆማቸው፣ ግብፃውያንን አበሳጨ፡፡ ‹‹አሁን ግድቡ በውኃው ላይ ጉዳት የለውም ነው የምትለው?›› ማይ ጠየቀች፡፡ ‹‹No›› ነበር ምላሻቸው፡፡ ‹‹ወደግድቡ የሚገባ ውኃ በአንድ ጊዜ ይሞላ ካልተባለ በየትኛውም አገር ሃይድሮ ግድብ በውኃው ፍሰት ላይ ጉዳት አድርሶ አያውቅም›› ያሉት በሙሉ ራስ መተማመን ነበር፡፡

ከኬንያ የመጣው አንድ ጋዜጠኛ፤ ኢትዮጵያ የተለያዩ የውኃ አማራጮች እንዳለት ጠቅሶ፤ በዓባይ ላይ መሥራት ብታቆምስ የሚል ሐሳብ አቅርቦ ነበር፡፡ ቀደም ብሎም ታላቁ የዓባይ ግድብ ሲጠናቀቅ አጠቃላይ 80 ኪሎ ሜትር ኩቢክ የናይል ውኃ ቆሞ፤ አምስት ቢሊዮን ኩቢክ ሜትር ውኃ ብቻ ይፈሳል፡፡ ይሔ ደግሞ የግብፃውያንን ሕይወት አደጋ ላይ ይጥላል የሚል ሐሳብ አቅርቦም ነበር፡፡ የተሳሳተ መረጃውን በማስተካከል፣ ያቀረበው ሐሳብ ተቀባይነት የሌለው መሆኑን ማቅረቤ በብዙዎች ተቀባይነት አግኝቷል፡፡ ጋዜጠኛውም ስህተት መሥራቱን አምኖ ይቅርታ እስከመጠየቅ ደርሷል፡፡

በአራተኛው ቀን የጎበኘነውን የዑጋንዳን ቡጃጋሊን ግድብም በምሳሌነት አቀረቡ፡፡ በነጭ ናይል ምንጭ አካባቢ (ጂንጃ) የተሠራው ግድብ በአንድ ቢሊዮን ዶላር አካባቢ ያለቀ ሲሆን የታላቁን የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ እየሠራ ባለው የጣልያኑ ሳሊኒ የታነፀ ነው፡፡ 200 ሜጋ ዋት ኢነርጂ የማመንጨት አቅም አለው፡፡ ዑጋንዳ ከራሷ በተረፈ ለኬንያም ኢነርጂ እንደምትሸጥ ተነገረን፡፡ ግብፆች ማየት የፈለጉት ግድብ አልነበረም፡፡

ከኢንቴቤ እስከ ካምፓላ ከዚያም ጂንጃ (የነጭ ዓባይ ምንጭ) የአራት ሰዓት የመኪና ጉዞ አደረግን፡፡ አካባቢው ለምለም ነው፡፡ ሆኖም ዓይነ ግቡ የነበረው የነጭ ዓባይ ምንጭ የአውንስ ፏፏቴ በአሁኑ ወቅት ፏፏቴነቱ ቀርቷል፡፡ እዚያው የተሠራው ግድብ ውኃ እስከ ላይ በመሙላቱና የፏፏቴውን መስህብነት በማስቀረቱ ብዙ ዑጋንዳውያን እንዳዘኑ ሰምተናል፡፡

በመድረኩም እንደተናገሩት በግላችንም እንዳወራናቸው አብዛኞቹ ጋዜጠኞች የተሳሳተ መረጃ እንደነበራቸው ገልጸውልናል፡፡ ከኢትዮጵያ የጋዜጠኞች ቡድን ጋር መመካከር፣ ውይይቱ በዘላቂነት የሚቀጥልበት አካባቢያዊ የጋዜጠኞች የውይይት መድረክ እንዲቋቋም ያቀረብኩት ጥያቄ በግብፃውያን ተቃውሞ የገጠመው ቢሆንም፤ አብዛኞቹ ጋዜጠኞች በናይል ላይ የነበራቸው የተሳሳተ መረጃ ማስተካከል እንደቻሉ ገልጸው ሐሳቡን አድንቀው ኢኒሼቲቩ እንዲቀጥልና የአሜሪካ መንግሥት እንደጀመረው መርዳቱን እንዲቀጥል ሐሳብ አቅርበው ተለያይተናል፡፡

ግብፃውያኑ በማጠቃለያ ሐሳባቸው ላይ በቀረቡት ጥናቶችም ሆነ በተደረጉት ውይይቶች እጅግ ማዘናቸውን ገልጸው፤ የተሰማቸውን ከፍተኛ ቅሬታ አቅርበው እኛንም ወቅሰዋል፡፡

*********
ምንጭ፡- ሪፖርተር ነሐሴ 18/2006

more recommended stories