በሚኒስትር ሬድዋን ሁሴን ጋዜጣዊ መግለጫ የተነሱ 5 ዋና ዋና ነጥቦች

የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጽ/ቤት ኃላፊ ሚኒስትር ሬድዋን ሁሴን፤ ባፈው ሰኞ ነሐሴ 12/2006 ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡

በመግለጫው ከተነሱት ዋና ዋና ነጥቦችን በአምስት ንዑስ-አርዕስት ከዚህ በታች አቅርበናል፡፡

[ባለፈው ወር በአሜሪካ ተቃዋሚዎች በመንግስት ላይ በጥቅሉ እና በሳቸው ላይ በተናጥል ያደረጉትን ተቃውሞ አስመልክቶ የሰጡትን አስተያየት ግን ለብቻው በሌላ ገጽ አቅርበነዋል፡፡ ለማንበብ ይህን (link) ይጫኑ፡፡

አምስት መጽሔቶችና አንድ ጋዜጣን በአንድ ጊዜ ክስ መመስረት ለምን አስፈለገ? Redwan Hussien - Ethiopia Government

መንግስት የሚጠበቅበት ከመንገድ ወጥቶ የዜጐችን ሰላምና ደህንነት ማረጋገጥ ነው። በዚህ ረገድ አምስት መጽሔቶች ከሆኑ ሀገር የሚያተራምሱት አምስቱ ይጠየቃሉ። አንድ ብቻ ከሆነ አንድ ይጠየቃል። ለነገሩ ሁላችሁም እነዚህ መጽሔቶች ምንድን ነው የሚጽፉት? አጀንዳ ከየት ያገኛሉ? አጀንዳውን እንዴት ይቀባበላሉ? የሚለውን ጉዳይ የምንጋራ ይመስለኛል። ሙያዊ ስራዎችን ነበር የሚሰሩት? የንግድ ጋዜጦች ለመሆን ነው ማዕከል አድርገው የሚሰሩት? የሚለውን አይተን ምንድን ነው የሚሰሩት? ምንድን ነው የሚጽፉት የሚለውም ይታወቃል። ከየት አጀንዳ ያመጣሉ፣ ከየት ድጋፍ ያገኛሉ የሚለው ይታወቃል። ቢያንስ ይጠረጠራል።

ይህን ታሳቢ ካደረግን አለፍ ገደም እያሉ ስራ ሲሰሩ ያጠፉትንም ሁሉ ይቀጡ ከተባለ በርካታ ያልተጠየቁት የመጠየቅ እድል አለ። ወደዚያ አልሄድንም ሰዎች መማር አለባቸው። ሕግ መከበር አለበት። የመንግስት ሆደ ሰፊነትም ገደቡን ካለፈ ሆደ ሰፊነት ይቀርና ተጠያቂነትን ያስከትላል። ኃላፊነትን አለመወጣት ያስከትላል። ከዚህ ጋር ተያይዞ የተወሰደ እርምጃ አለ። ክስ ነው የቀረበው። ይህ ክስ ምን ያህል አጥጋቢ ነው? ምን ያህል ሚዛን ይደፋል የሚለውን ዐቃቤ ሕግ የራሱን ማስረጃ ያቀርባል። እነሱም የራሳቸውን ይከራከራሉ። ዳኞች መዝገቡ ካረካቸው ካጠገባቸው ውሳኔያቸውን ያስቀምጣሉ። ውሳኔው ቅጣት ከሆነ የሚሰጡትን ቅጣት እናያለን። ነፃ ነው በቂ ጥፋት አይደለም ካሉም ውሳኔያቸውን አክብረን እንንቀሳቀሳለን ማለት ነው። ግን በቂ ምክንያት አለ። ከበቂ በላይ አለ ብቻ ሳይሆን እንደዚህ አይነት ተመሳሳይ ጥፋት ይፈለግባቸው ተብሎ ቢወሰድ ወይም በጥፋታቸው መጠን እያንዳንዳቸው በሰልፍ ይጠየቁ ከተባለ በርካታ ያልተጠየቁትንም መጠየቅ ይቻላል።

የዓለም ባንክ የብር ምንዛ አስር በመቶ እንዲቀነስ ያቀረበውን ምክር በተመለከተ

[የዓለም ባንክ በቅርቡ ባወጣው መግለጫ፡- መንግስት የብር ምንዛሪ በአስር በመቶ እንዲቀንስ ቢያደርግ፤ በኤክስፖርት ገቢ ላይ የአምስት በመቶ ጭማሪና በዓመታዊ የኢኮኖሚ ዕድገት ላይ የሁለት መቶ ጭማሪ ማግኘት ይቻላል ሲል መክሯል፡፡]

‹‹የቀረቡ አማራጮች በሙሉ አይተገበሩም፣ መንግሥት አጠቃላይ አማራጮችን ግንዛቤ ውስጥ አስገብቶና ትርፍና ወጪውን አገናዝቦ በአጠቃላይ ለኢኮኖሚው ይጠቅማል የሚለውን ዕርምጃ ነው የሚወስደው፤›› ብለዋል፡፡

መንግሥት በ2002 ዓ.ም. የብር የመግዛት አቅምን በአሥር በመቶ፣ በ2003 ዓ.ም. ደግሞ 20 በመቶ በመቀነስ ወደ ዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ትግበራ መግባቱን አስታውሰዋል፡፡

‹‹ይህ የተደረገው በተረጋጋ የማክሮ ኢኮኖሚ ሁኔታ ውስጥ በመሆን የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድን ለመተግበር በማቀድ ነው፤›› ብለዋል፡፡

መንግሥት የብር የመግዛት አቅምን ዝቅ እንዲል ከማድረጉ በፊት ስፋት ያለው የማክሮ ኢኮኖሚ ትንተና እንደሚያደርግ የገለጹት ሚኒስትሩ፣ ‹‹አሁን ባለው ሁኔታ በጣም የጎላ የምንዛሪ ቅነሳ የምናደርግበት ምክንያት የለም፡፡ ተለቅ ያለ ቅነሳ አሁን ትክክለኛ ነው ተብሎ አይታሰብም፤›› ብለዋል፡፡

ሩስያ እና ኤርትራ የጋራ የጦር ልምምድ አቅደዋል ስለመባሉ

የሩስያና ኤርትራን ወታደራዊ የጦር ልምምድ ስምምነት በተመለከተ ሀገሮች የራሳቸው ፍላጐት ያላቸው በመሆኑ በዚሁ መልኩ የሚታይ ነው። ሁኔታዎቹ በተግባር ምን ይመስላሉ የሚለውን በሚደረጉ ለውጦች መሠረት የሚታይ ነው የሚሆነው። ከእኛ ጥቅም ጋር ምን ያህል ይጋጫል? ይያያዛል? በዚህስ ረገድ ምን ማድረግ ይቻላል የሚለውን በሂደት የሚታይ ነው። ለውጡን ተከትሎ አቋም የምንይዝ ይሆናል። አሁን ባለበት ሁኔታ ላይ ግን የተለየ አስተያየት የምንሰጥበት ነገር የለም።

የአፍሪካና አሜሪካ የመሪዎች ጉባዔ እና የኢትዮ-አሜሪካ የንግድና የኢንቨስትመንት ፎረም

ፕሬዝዳንት ዶክተር ሙላቱ ተሾመ እና ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ የተሳተፉባቸው የአፍሪካና አሜሪካ የመሪዎች ጉባዔ እና የኢትዮ-አሜሪካ የንግድና የኢንቨስትመንት ፎረም የኢትዮጵያን ስኬት ማስተዋወቅ የተቻለበት እንደነበር አቶ ሬድዋን አንስተዋል።

ኢትዮጵያ ባለፉት ቀናቶች ሁለት ወሳኝ አለም አቀፍ መድረኮችን በመካፈል በሃገሪቱ ያለውን ሁለንታናዊ እንቅስቃሴ ለአለም በማስተዋወቅ፤ አህጉርና አለም አቀፍ እውቅናዎችን ማትረፏንም ነው ሚንስትሩ ያስታወሱት። ኢትዮጽያ በአሜሪካ በተካፈለችባቸው የኢንቨስትመንትና የመሪዎች ጉባኤ ውጤታማ ተግባሯን ለአለም እንድታስተዋውቅ ምቹ አጋጣሚን የፈጠረ እንደነበር፤

የመጀመሪያው መድረክ በፕሬዘዳንት ሙላቱ ተሾመ የተመራው የኢትዮ አሜሪካ የኢንቨስትመንት ፎረም ሲሆን፥ ይህ ፎረም በርካታ አለም አቀፍ ኩባንያዎች ያካተተ እንደመሆኑ መጠን ፤ ሃገር በቀል ኩባንያዎች ከሌላው አለም ኩባንያዎች ጋር ልምድ እንዲቀስሙ ሁኔታዎች የተመቻቹበት ነበር ብለዋል። ይህ መድረክ ከተለያየ አለም ተውጣጥተው በኢትዮጵያ ኢንቨስት የሚያደርጉ ኩባንያዎች ውጤታማ መሆናቸውን ያረጋገጡበት እንደነበርም ነው የጠቀሱት። በአሜሪካን የሚገኙ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትየጵያውያን በሃገራቸው ገብተው በመረጡት የስራ ዘርፍ ኢንቨስት ሊያደርጉ ቢችሉ ፤ ውጤታማ እንደሚሆኑ በተግባር ተመስክሯል መድረኩ ሃገሪቱን በአለም አቀፍ ታዋቂ ኩባንያዎች ዘንድ በነዳጅ ፍለጋና በሌሎችም ዘርፎች እንዲሰማሩ ተመራጭ እንድትሆን እድል የሚሰጥ እንደሆነም ነው ያወሱት።

የተገኘው ቱርፋት ይህ ብቻ አይደለም ያሉት ሚኒስትሩ፥ ሃገር በቀል ኩባንያዎች ከአሜሪካ አቻዎቻው ጋር በሽርክና ለመስራት ምቹ አጋጣሚን የፈጠረላቸው እንደነበርም አስታውሰዋል።

በተጨማሪም መንግስትም በማንኛውም ሙያ ውስጥ ለሚሰማሩ ባለሃብቶች አስፈላጊውን እግዛ ለማድረግ ዝግጁነቱን በማሳየቱ፥ በሃገር ውስጥ ውጤታማ የሆኑ ኩባንያዎች በኢትዮጵያ ያለውን ምቹ የኢንቨስትመንት ፖሊስና ስትራቴጂ ለቀሪው አለም እንዲያስተዋውቁ ያስቻለ እንደነበርም አንስተዋል።

ሁለተኛውና በዋሽንግተን አዘጋጅነት የተካሄደው የአፍሪካ አሜሪካ የመሪዎች ጉባኤም ቢሆን ኢትየጵያ የዜጎቿን ህይወት ለመቀየርና የግብርናውን ክፍለ ኢኮኖሚ ለማሻሻል ፤ እየሄደችበት ያለው ርቀት ከሌሎች የአፍሪካ ሃገራት በሞዴልነት የተቀመጠ ስኬት ነበር ብለዋል።

የማህበረሰቡን የጤና ሁኔታ በማሻሻል ፣ የምስራቅ አፍሪካን ሰላም ለማስጠበቅ ፣ በደቡብ ሱዳን የተከሰተውን አለመረጋጋት ዴሞክራሲያዊ በሆነ ሁኔታ ለመፍታት ውጤታማ ስራዎችን እንዳከናወነች መነሳቱም ሌላኛው ስኬት ነበር ብለዋል። ይህም የውጭ ግንኙነት ፖሊሲውን ውጤታማነት ያሳያል።

የታላቁ ህዳሴ ግድብን አሰመልክቶ የሦስትዮሽ ውይይቱ ሊጀመር ነው ስለመባሉ

የታላቁ ህዳሴ ኤሌክትሪክ ሃይል ማመንጫ ግድብን አሰመልክቶ በግብጽ አሻፈረኝ ባይነት ተቋርጦ የነበረው የሶሰትዮሽ ድርድርም፤ ግብፅ ዳግም ለመደራደር ፍላጎቷን በማሳየቷ ፤ በሶስት ዋና ዋና ጉዳዮች ላይ ውይይቱ እንዲቀጥል ኢትዮጵያ ፍላጎቷን መግለጿንም እስታውሰዋል።

የግብፅ ፕሬዝደንት ከጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ጋር በዚህ ጉዳይ ላይ ውይይት አድርገዋል። ከተወያዩባቸው መካከል በተለይ ከሕዳሴው ግድብ ጋር ከተያያዙት መካከል የሃይድሮ ሞዴሊንግ አንዱ ነው። ይህ ማለት ግድቡ በምን ያህል ጊዜና ስፋት ሊሞላ ይችላል የሚለው ነበር የሚያሳስባቸው። ይህን በሳይንሳዊ ሞዴል ጥናት ተረጋግጦ ብናውቀው የሚል ኀሳብ አላቸው። በእኛ በኩል ጥናቱ አለ። እናውቀዋለን። እነሱን ተሳታፊ ያደረገ ሌላም ጥናት ቢደረግ በእኛ በኩል ችግር የለውም።

ሌላው የአካባቢ ተፅዕኖ ዳሰሳ ነው። ይህንን በተመለከተ በእኛ በኩል ጥናቱ አለ ችግር የለውም። ሆኖም ሦስተኛ ወገን ባለበት ይጠና የሚል ጥያቄ አንስተዋል። በእኛ በኩል ቢጠና ችግር የለውም። በመንግስታችንም ይህን ለማድረግ አቋም ተወስዷል። በሦስቱ ሀገሮች ከተቻለ ወይም ራሳቸው መክፈል ከቻሉ ጥናቱ በሦስተኛ ወገን ቢደረግ ችግር የለውም።

ግብጾች አዲስ ራዕይ በሕዳሴ ግድብ ላይ ይዘናል ብለዋል ለተባለው፤ በእኛ በኩል የሚታወቅ የለም። የእኛ ራዕይ ግን ግልፅ ነው። የምንገነባው ግድብም የኢትዮጵያ እና የግብፅን ጥቅም ያረጋግጣል። ይህ የእኛ ቋሚ መርህ ነው። በዚህ መልኩ ራዕያቸው ከመጣ እንወያያለን። ከዚህ ውጪ ከሆነ ግን እንደማንም ሃሳብ እናዳምጠዋለን። በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ኤሌትሪክ ኃይል ማመንጫ ግድብ ዙሪያ ተቋርጦ የነበረው የሶስትዮሽ ድርድር የኢትዮጵያን መሰረታው ፍላጎቶች በማይነካ መልኩ እንደሚቀጥልም አቶ ሬድዋን አስታውቀዋል።

**********

**********

Fetsum Berhane is an Ethiopian resident, economist researcher and a blogger on HornAffairs.

more recommended stories