የአንድነቶች የእርስ-በርስ የፌስቡክ ጦርነት

ሰሞኑን ዘና ከምልባቸው ነገሮች አንዱ በአንድነት አመራሮችና አባላት መካከል ያለው የቃላት ጦርነት ነው፡፡ በተለይ በኢንጅነር ዘለቀ ረዲና በአቶ ግርማ ካሳ መካከል፡፡ እንደሚታወቀው አንድነት አሁን ‘የኢንጂነር ግዛቸዉ አንድነት’ እና ‘የበላይ ፍቃዱዉ አንድነት’ በሚል ለሁለት ተከፍሏል፡፡ ተክሌ በቀለ ለጊዜው ‘ሶስተኛውን አንድነት’ ለመመስረት የሚያስችል በቂ ድጋፍ ስለሌላቸው ‘ከሁለተኛው አንድነት’ ጋር ተዳምረው ያሉበት ሁኔታ ነው ያለው /ሁ.ነ.ያ/፡፡

እኔ እንደታየኝ ከሆነ ለፓርቲው መሰበርም ሆነ ለቃላት ጦርነቱ ዋና መነሻ /ultimate cause/ ይሄው የአመራሩ መከፋፈል ነው፡፡ በርግጥ ሰሞኑን የተከሰተ ‹‹ኢንጂነር ግዛቸው የውህደት አመቻች ኮሚቴውን አፈረሰብን›› የሚል ምክንያት እንዳለ አውቃለሁ፡፡ ይች ግን ሰበብ ቢጤ /immediate cause/ ነች፡፡Andinet UDJ party logo

ወደ መነሻ ነጥቤ ልምጣና በሁለቱ የፓርቲው አባሎች መካከል የተደረጉ ልውውጦችን ላስነብባችሁ፡፡ በዚህ አጋጣሚ ሁለቱን ግለሰቦች ለማስተዋወቅ ያክል አቶ ዘለቀ ረዲ ማለት አሁን በአንድነት ፓርቲ ውስጥ አመራር ናቸው፡፡ ውግንናቸው ደግሞ ከኢንጂነር ግዛቸው ጋር እንደሆነ ከፅሁፎቻቸው ለመረዳት አይከብድም፡፡ የፓርቲው የአደረጃጀት ጉዳዮች ሃላፊ እስከመሆንም የደረሱ ናቸው፡፡ ባለፈው አመት እንዲሁ በፓርቲው አመራሮች መካከል በተነሳ ውዝግብ ከዚህ ወንበራቸው ተነስተው አነስ ወዳለች ወንበር ተሸጋግረዋል፡፡ በግሌ ስገመግማቸው ጥሩ ፀሃፊ ናቸው፡፡ አቶ ግርማ ካሳ ደግሞ በአሜሪካ የሚኖሩ ተራ የፓርቲው አባል ናቸው፡፡ ውግንናቸው ከበላይ ፍቃዱ ጋር ነው፡፡ እኝህን በግሌ ስገመግማቸው ደፋር ፀሃፊ ናቸው፡፡ በፈለጉት ጉዳይ ደስ እንዳላቸው ይፅፋሉ፡፡ እኒህ ሰሞኑን የተከሰሱ ጋዜጦችና መፅሄቶችም ‘ደስ ይበላቸው’ እያሉ ያትሙላቸው ነበር፡፡

ርዕሴ ላይ ‘ኢንጂነሮቹና አቶዎቹ’ ያልኩት ይህን ጊዜያዊ አሰላለፍ አይቼ ነው፡፡ ሁለቱ የፓርቲው አባላት ሰሞኑን የነበራቸውን መጎሻሸም ወደ ከፍተኛ የቃላት ጦርነት /full scale fighting/ አሸጋግረውታል፡፡ እናም በመጨረሻው ፅሁፎቻቸው እንዲህ ተባብለዋል፡፡

ኢንጂነር ዘለቀ ረዲ

“በእርግጥ አቶ ግርማን በጽሁፍ እንጂ በአካል አላውቃችውም፡፡ አንዳንድ በአካል የሚያውቋቸው ሰዎች ግን በእድሜ ገፋ ያደረጉ ሰው እንደሆኑ ነግረውኛል። ሆኖም ሰሞኑን እያደረጉ ያሉትን ነገር ስመለከት ግን ሌላው ቀርቶ በእድሜ ደረጃ በሰል ያሉ የሀገራችን ሰዎች ሲያደርጉ የነበረውን ሳይሆን በተቃራኒ እንደ አላዋቂ ሰው የሚያደርገውን ሲያደርጉ ማየቴ በእጅጉ አሳዝኖኛል።”

አቶ ግርማ ካሳ

“የኔ እድሜ እዚህ ላይ ለምን እንደተነሳ ባይገባኝም፣ የስድሳዎቹ ትዉልድ እንዳልሆንኩ ግን ይወቁልኝ። ደርግ ሲመጣ ሕጻን ልጅ ነበርኩ።”

ኢንጂነር ዘለቀ ረዲ

“ይቅርታ ይደረግልኝና በአንድነት መካከል የነበረው የፕሬዝዳንት ውድድሩም ከሮ እስኪበጠስ ያደረሱት እኚሁ ሰው ናቸው። እገሌን ኢንዶርስ እናደርጋለን፤ እገሌ ይበቃዋል እያሉ ውሳኔ ሰጭ ሆኑ፡፡ ነገሮችን ከእርስ በርስ ክርክር አልፎ የማህበራዊ ድህረ ገጾች ማዳመቂያ አደረጉት።”

አቶ ግርማ ካሳ

“እንደ አንድነት ደጋፊ አስተያየቴን ጽፊያለሁ። ይሄ ደግሞ ዴሞክራሲያዊ መብቴ ነው። «አትናገሩ፣ አትጻፉ፣ አስተያየት አትስጡ» የሚል ፖለቲካ ኢሕአዴጎች አካባቢ ያለ ነው። እነ አቶ ከበደ ካሳ ተናገሩ፣ ጻፉ የተባሉትን ብቻ እንደሚጽፉና እንደሚናገሩ፣ እኛም የአንድነት አመራሮች ማንበብ የሚፈልጉትን ብቻ ጻፉ የሚሉን ከሆነ ችግር ነው።”

ኢንጂነር ዘለቀ ረዲ

“ሰውየው በአንድ ጎን ከሚሰሙት ውጭ ግራ ቀኝ አያዩም። ከአንድ ወገን በሰሙት ብቻ ሲፈርዱ አይቻቸዋለሁ። ትክክል አይደሉም ሲባሉ እንኩዋን የተሳሳቱበት ቦታ ካለ ቆም ብሎ ከማሰብና ሥህተታቸውን ከማረም ይልቅ አለመሳሳታቸውን ለማሳመን መከረኛ ብዕራቸውን ያሾላሉ።”

አቶ ግርማ ካሳ

“ጠመንጃና ጡንቻ አይነሳ እንጂ ብእርስ ከሾለ ይጠቅማል እንጂ አይጎዳም። ብእርን የሚፈሩ ደካሞች፣ በራሳቸው የማይተማመኑና የኃይል፣ የስድብና የማስፈራራት ፖለቲካን የሚያራምዱ አምባገነኖች ናቸው።”

ኢንጂነር ዘለቀ ረዲ

“እኔ እዚህ አብሬ እየሰራሁ ያልገባኝን አሜሪካን ሀገር ሆነው አቶ ግርማ ካሳ የገባቸው ነገር በእጅጉ ግራ ያጋባል።”

አቶ ግርማ ካሳ

“አሜሪካ አገር ነው የምኖረው። ያ ደግሞ አገር ቤት ከሚኖሩ ግማሽ ወይንም ሶስት አምስተኛ ኢትዮጵያዊ አያደርገኝም።”

በዚህ የፌስቡክ ክርክር ላይ ኢንጂነር ዘለቀ ብዙም ደጋፊ ያገኙ አይመስሉም፡፡

የፓርቲው ም/ሊ/መንበር/ተክሌ በቀለም  ለአቶ ግርማ ካሳ ወግነው ባወጡት ፅሁፍ እንዲህ ሲሉ ዝተውባቸዋል::

“የአመለካከት ትግሉ ከስርአቱ ጋር ብቻ ሳይሆን ከጎናችን ካሉቱም ጋር ሆኖ ቀጥሏል፡፡ ይህንንም ከተገነዘብን ቆይተናል፤ ለዉጥ የሻትነዉም ለዚህ ነዉ፡፡ የፕሬዝዳንቱ {የኢንጂነር ግዛቸው} ቃል አቀባይ ሃላፊነት ቦታን የመዉስድ ፍላጎትዎንም በግሌ አደንቃለሁ፡፡ እኛ በዚህ አመራርና ዉሳኔ አሰጣጥ ለዉጥ ስለማይመጣ የካቢኔዉ አባላት ሆነን አብረን አንሰራም አልን እንጂ ሌላ ግምገማና ጉርጎራ ዉስጥ አልገባንም፤ ለሱ እንደርስበታለን፡፡”

ኢንጂነር ዘለቀ ረዲ አሁን የፅሁፍ ስቱዲዮ ልገባ ስል ባወጡት ጽሁፍ ደግሞ በአቶ ተክሌ በቀለ ‘የኢንጂነሩ ቃል አቀባይ መሆን ትፈልጋለህ’ መባላቸው ስላንገበገባቸው ይመስላል “ጆሮ ለባለቤቱ ባእድ ነው” ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ እንግዲህ ለአቶ ተክሌ ‘ይሉህን በሰማህ ገበያ ባልወጣህ’ እያሏቸው ነው ማለት ነው፡፡ ምንም እንኳን አቶ ተክሌ አሁን “ግምገማና ጉርጎራ ውስጥ አልገባንም፤ ለሱ እንደርስበታለን” ቢሉም ኢንጂነር ዘለቀ ቀድመው መግባት የፈለጉ ይመስላሉ፡፡

ካፈነገጡት አመራሮች ውስጥ አንዱ የሆኑት አቶ ዳንኤል ተፈራም “ለአቶ ዘለቀ ረዲም ሆኑ ሌሎች የአንድነት ሰዎች ፌስ ቡክ ላይ መሽጎ ነገር መጎንጎን አይጠቅምም፡፡” ሲሉ ዘልፈዋቸዋል፡፡ ፌስቡክ ላይ ከሚጎነጉኑት አንዱ አቶ ግርማ ካሳ መሆናቸውን ልብ ላለ ግን ‘ምነዋ የአቶ ዳንኤል ማሳሰቢያ ለተቃወሟቸው ኢንጂነር ዘለቀ ብቻ ሆነ? መጎንጎን መጎንጎን ነው፡፡’ የሚል ጥያቄ ማስነሳቱ አይቀርም፡፡ ያም ሆነ ይህ በጥቅሉ ሲታይ ኢንጂነር ዘለቀ ረዲን አንዳንዶች ቢደግፏቸውም ብዙዎች ተቃውመዋቸዋል፡፡ ፅናቱን ይስጥዎት ብያለሁ፡፡

አቶ ግርማ ካሳ በዚህ ፅሁፋቸው ላይ “አቶ ከበደን ለጊዜው ልተዋቸውና…” በማለት የሆነ ጊዜ እንደሚመጡብኝ በተዘዋዋሪ ዝተውብኛል፡፡ እንዳመጣብኝ እጠብቅዎታለሁ እንጂ የት እሄዳለሁ? ግን በንጉሱ ዘመን የተወለደ ሰው በደርጉ ዘመን ከተወለደ ጋር መነታረክ አይበጀውምና ቢቀርብዎት ይሻልዎታል፡፡ ይህን ምክሬን ሳይሰሙ ቀርተው ብዕርዎትን ቢያሾሉ ግን እኔም ጋር ያለው ላጲስ አይደለምና ‘ማርያምን አልምርዎትም’፡፡ Lol.

በነገራችን ላይ ይህ አንድነት ቤት የተፈጠረ እሰጣ እገባ ለሰማያዊ ፓርቲ አባሎች ሰርግና ምላሽ ሆኗል ሲባል ሰምቻለሁ፡፡ አንዳንዶቹም ለዚህ ያበቃን ‹‹የበሳሉ መሪያችን ኢንጂነር ይልቃል ጌትነት ብልህ አመራር ነው›› ብለዋል በፌስቡክ ግድግዳቸው፡፡ አቤል ኤፍሬም የተባለ ኢንጂነር ይልቃል ጌትነትን የማደንቅባቸው 5 ምክንያቶች በሚል ከዘረዘራቸው ውስጥ “ያልተጠና ውህደት እንደማያዋጣ ቀድመው መረዳታቸውና አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ ከሰማያዊ ውጭ ፓርቲ አለ ብለው ያለማመን ድፍረታቸው” መሆኑን ገልጧል፡፡

በመጨረሻ አገር ውስጥ ላላችሁ ለአንድነት ፓርቲ ተራ አባላት ባትሰሙኝም አንድ ምክር ልለግሳችሁና ላብቃ፡፡ እናንተ በዚህ ጉዳይ ጣልቃ ባትገቡ መልካም ነው፡፡ ጦርነቱ ሲበርድ ትመጣላችሁ፡፡ እስከዛው የኢፌዴሪ ፓርላማ አባላት ከመረጣቸው ህዝብ ጋር ለመመካከር እረፍት እንደወጡት እናንተም ዞር ዞር እያላችሁ የህዝቡን የልብ ትርታ ብታዳምጡ መልካም ነው እላችኋለሁ፡፡

**********

Kebede Kassa

more recommended stories