አቶ አንዳርጋቸው ተያዙና ብዙ ተዛዘብን

(እውነቱ ነጋ)

አገር ማለት ምን ማለት ነበር የሚባለው? አዎን አገር ማለት ሰው ነው፤ ሰው ማለትም አገር። አገር እኮ እኛ ነን። እኔና እርስዎ። እርግጥም እኮ ነው፤ አገር ያለ ሰው፤ ሰውም ያለ አገር እንዴት ይታሰባል? እንዴትም!

አገሬን እወዳለሁ ስንል እራሴን እወዳለሁ ማለታችን እንደሆነ ግልጽ ነው። ምክንያቱም አገር ያለ ሰው ተራራው ወንዙ አሊያም ሸለቆው ብቻውን አገር ሊሆን አይችልምና ነው። በዚያው ልክ አገር ብሎ ነገር ወዲያ ካሉም እኔም ወዲያልኝ ማለትዎ አይደል?

ነገሬ ወዲህ ነው። ሰሞኑን… ሰሞኑን እንኳ አይመስለኝም ትንሽ ሳይቆይ አልቀረም። በሀገራችን ዙሪያ በተለይ በፖለቲካው መስክ ትኩሳት ሆኖ የቆየው የግንቦት ሰባቱ አቶ አንዳርጋቸው ፅጌ ለኢትዮዽያ መንግስት ተላልፈው የመሰጠታቸው ነገር ነበር። Andargachew Tsige - Ginbot 7

የግለሰቡ መያዝ ሀገር ወዳድ ለሆነ ሁሉ መልካም ዜና እንጂ ያን ያህል ቡራ ከራዩ የሚያስብል ጉዳይ አልነበረም። እንደ አለመታደል ሆኖ ግን አገር ማለት እኛ ነን የሚለውን ብያኔ ያልተረዱ ሁሉ አገር ሊያጠፋ የሚንቀሳቀስ አሸባሪ ድርጅት ከፍተኛ አመራር ተያዙ ተብሎ ያዙኝ ልቀቁኝ ማለት አስተዛዝቦናል።

እስኪ ልብ ይበሉ። አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ በሽብርተኛነት በተፈረጀ ድርጅት ውስጥ ትልቅ ስፍራ ያላቸው ግለሰብ ናቸው። እኒህን ግለሰብ መያዝ አሸባሪ ድርጅታቸውን ከማፈራረስ አይተናነስም። አይ አይ እንዴት ተደርጎ የሚል ካለም እንኮ የእርሳቸው መያዝ የድርጅቱን ከይሲ ተግባር በብዙ መጠን ወደኋላ የመጎተት ያህል እንደሆነ የሚያስማማ ይመስለኛል። ምክንያቱም ግለሰቡ በቁጥጥር ሲል ሲውሉ የድርጅቱን የ2014 እቅድ ጨምሮ በርካታ የጥፋት ሰነዶችን ይዘው እንደነበር እራሳቸው በአንደባታቸው ተናግረዋልና ነው። ከዚህ በላይ ምን የምስራች አለ?

ስለዚህ አገርዎንና ወገንዎን የሚወዱ ከሆነ በአቶ አንዳርጋቸው መያዝ ልንደሰት ይገባል ባይ ነኝ። ከዚህ ውጭ ግን በእኔ እምነት ከውጭም ከውስጥም እያየነው እንዳለው ጎንበስ ቀናውን ማብዛቱ ትርፉ ትዝብት ድካሙም የውርንጭላ ነው።

አንድ ሀቅ አለ። በግንቦት ሰባትም ይሁን በጀሌዎቹ በሀገራችን ላይ ሊፈጸም የሚታቀደው የሽብር ጥቃት ሁሉ ተግባራዊ ቢሆን ልንሞት የምንችለው እኔና እርስዎ እንጂ እዚያ ባህር ማዶ ሆነው የቁራ ጩኸት የሚያሰሙት ፎርጅድ ኢትዮዽያዊያን አይደሉም። እነሱ ካልጮሁ ስለማይኖሩ በየሰበብ አስባቡ መጮሀቸው ግብራቸው ነውና ተዎቸው ይጩሁ።

እኔና እርስዎ ግን ውዷ አገራችን ተስፋ በቆረጡ ጨለምተኞች ፈንጅ እንድትታመስ ልንፈቅድ አይገባም። አቶ አንንዳርጋቸውና መሰሎቻቸው ለምን ታሰሩ? ብሎ መጮህ ለምን የሽብር ጥቃት አልተፈፀመብንም የማለት ያህል ነው። ሽብርንና ሽብርተኝነትን ለማውገዝ በእርሰዎ ላይ ወይንም ከቤተሰብዎ አባል በአንዱ ላይ የግድ የሽብር ጥቃት መፈፀም የለበትም። ምክንያቱም ብልህ ሰው ከሰው የሚማር ነውና የእኛ ቢቀር እንኮ ከጎረቤቶቻችን የሽብር ጥቃት ብዙ የምንማረው ሀቅ አለን።

እኛ ስራ ላይ ነን። መንግስትም ስራ ላይ ነው። ግንቦት ሰባትና መሰሎቹ ደግሞ ሴራ ላይ። ይሄንን ሴራ እየተከታተሉ ማፈራረስ ደግሞ የመንግስት ሁለተኛም ብቻ ሳይሆን የቅድሚያ ቅድሚያ የሚሰጠው ስራው ሊሆን ይገባል። በዚህ ስራው ላይ ታዲያ ሰላም ወዳድ የሆነ ሁሉ ሊያግዘው እንጂ ሊያወግዘው አይገባም። ምክንያቱም አገርም ሆነ መንግስት እኮ እኔና እርስዎ ነን። ስለዚህ የእኛ ሰዎች የእኛን ስራ ሲሰሩ ሊጮሁ የሚገባቸው የእኛ ያልሆኑቱ ብቻ ናቸው።

ለምሳሌ እነማን?

የመጀመሪያዎቹ የእኛ የወገን ያልሆኑቱ እዚሁ በጉያችን ውስጥ መሽገው ያሉቱ ጥቂት የተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎችና አመራሮቻቸው ናቸው። «መልከ ጥፉን በስም ይደግፉ» እንዲሉ ስማቸውን ብቻ እያሳመሩ ግብራቸውን አጠልሽተው የሚንቀሳቀሱ ፓርቲዎችና አመራሮቻው «መንግስት አልቻለም» ለማስባል የማይቆፍሩት ድንጋይ የለም። በአንድ በኩል «መንግስት የአገሪቷን አንድነት ስጋት ላይ ጥሏል» እያሉ ህዝቡን ያደነቁራሉ። በሌላ በኩል ደግሞ የአገርን አንድነት አደጋ ላይ ከሚጥሉ ስጋቶች መካከል አንዱ የሆነውን ሽብርን የመከላከል ስራ ሲሰራ ሌላኛውን የጩኸት ቅኝታቸውን ያሰሙናል። ለመሆኑ የቱ ነው አቋማቸው? የቱስ ነው ዓላማቸው? እስኪ ጠይቁልን።

በእኛ ስር ሆናችሁ እኛን የሚያጠፋ ሴራ እያደራችሁ «የእናንተ ነን» ስትሉን አይተንና ሰምተን ከመገረም ውጭ ምን ልንል እንችላለን? ዛሬ ህዝብ አውቋል። ህዝብ አያውቅም አትበሉ። ህዝብ አዋቂ ነው። የማታውቁት እናንተ ህዝብ አያውቅም ብላችሁ የምታስቡት አላዋቂዎች ናችሁ። ብታውቁማ ኑሮ አንድ በሚያደርገን አገራዊ ጉደይ አንድ ሆነን በሚያለያየን ደግሞ ተለያይተን በሰለጠነ መንገድ ልዩነታችንን ማጥበብ እንችል ነበር። እናንተ ግን ከእኔ ወዲያ አዋቂ … በሚል ትምክህት ታጥራችሁ «የጠላቴ ጠላት ለእኔ ወዳጄ ነው» በሚለው ብሂል ተመርታችሁ ነጋ ጠባ ሊያጠፉን ለሚሰሩ የጥፋት ኃይሎች ጥብቅና ትቆማላችሁ።

ኧረ ለመሆኑ ኢትዮዽያዊነታችሁን ወደ የት ሸጣችሁት? ኢትዮዽያዊነታችሁ መታወቂያችሁ ላይ ብቻ ሆኖ ቀረ? ኢትዮዽያዊ ብትሆኑ ኖሮማ አቶ አንዳርጋቸውና እርሳቸው ከሚመሩት ድርጅት ጋር ግንኙነት ያላቸው ግለሰቦች በህግ ጥላ ስር ሲወድቁ «የሞኝ ዘፈን ሁልጊዜ አበባየሆሽ» የሚያስብላችሁን ዘፈናችሁን ባላሰማችሁን፤ እኛም ባልታዘብናችሁ ነበር። ለማንኛውም ዛሬም ጊዜው አልረፈደምና የእኛ መሆናችሁን በተግባር አሳዩን፤ የእኛን ሰላም ከማይፈልጉ አጥፊዎች ጋር ያሰራችሁትን የሰማኒያ ወረቀት ቀድዳችሁ ጣሉ።

ሌሎችም አሉ?

ሌሎቹ የእኛ ወገን ያለሆኑት የእኛ ሰዎች በአውሮፓና አሜሪካ ተሰግስገው ያሉቱ ፎርጅድ ኢትዮጵያዊያን ናቸው። የእነዚህ ወገኖች ጩኸት ሁልጊዜ ይገርመኛል። መንግስትን መቃወም አንድ ነገር ነው። የጸረ ሽብር እንቅስቃሴን መቃወም ግን የለየለት እብደት እንጂ ሌላ ምን ሊባል ይችላል? ለመሆኑ እነሱ ባሉባቸው አገሮችና ከተሞች ያለው የጸረ ሽብር ህግ ምን ይል ይሆን? ፈንጅ ለሚወረውርብህ ዳቦ መልስለት? ወይንስ ግራህን ለሚመታህ ቀኝህን ስጠው? ይሄ እንዳልሆነ እንኳን እነሱ እኛም እዚህ ሆነን አሳምረን እናውቀዋለን።

ለመሆኑ አሜሪካ ለደህንነቴ ስትል ያልፈተሸችው ሀገር፣ ያላሰረችው ግለሰብ፣ ያላፈራረሰችውስ ድርጅት ይኖር ይሆን? እንኳንስ በሀገሯ ምድር ይቅርና በሰው አገር ሳይቀር በመሬትና በሰማይ (በሰው አልባ አውሮፕላንም ሳይቀር) ያላመሰቃቀለችው አገር ወደየት ይገኛል? የአፍጋኒስታንን፣ የኢራቅን፣ የፓኪስታንና የሌሎች አገራትን ምድር ካለይም ከታችም በሚታይም በማይታይም መልኩ የምታምሰው ለአገራቱና ለዜጎቻቸው ደህንነት አስባ ይሆን? አዎን ካሉኝ የዋህ መሆን አለብዎት! እነ ፈረንሳይስ ቢሆኑ የማሊን፣ የማዕከላዊ አፍሪካ ሪፖብሊክንና የሌሎችንም ምድር እያተረማመሱት ያሉት ለአፍሪካዊያኑ አዝነው ነው? አይምሰልዎት፤ አይደለማ! ሊሆንም አይችልም። የእነሱ ስጋት የዛሬ ሳይሆን የነገ ነው። በአገራቱ እየተፈለፈለ ያለው ሽብርተኛ አድጎና ጎልምሶ ነገ እኛንም ይበላናል ብለው ሰለሚሰጉ ብቻ ነው።

እኛ ግን የራሳችንን የዛሬ ስጋት ዛሬ ላይ ስንከላከል የሚጮኸው ብዙ ነው። ሌላው ቢጮህ አይገርመኝም ነበር። የሚያሳዝነው ግን የእኛ ወገን የሆኑቱ ኢትዮጵያዊያን ዋነኛ ጯሂ መሆናቸው ያንገበግባል። ለዚህም እኮ ነው ፎርጅድ ኢትዮጵያዊያን ማለቴ።

ከእነዚህ የውሸት ኢትዮጵያዊያን ጩኸት ባሻገር የሚገርመኝ የአስተሳሰብ ጨቅላነታቸው ነው። አቶ አንዳርጋቸው የተያዙ ሰሞን ሰልፍ ያልወጡባቸው ከተሞች ያልጮሁባቸው አደባባዮችና ኤንባሲዎች የሉም ማለት ይቻላል። ታዲያ በጩኸታቸው መካከል እንዲህ የሚል መፈከርም ተሰምቶ ነበር፤ «ሞተናል፤ ተዋርደናል፤ የታሰርነው እኛ ነን፤ እኛም አንዳርጋቸው ነን…»

አዎን እኔም የምንላችሁ ይሄንኑ ነው። ከሞታችሁ ቆይታችኋል፤ ከተዋረዳችሁ ሰነባብታችኋል። አገሩን የከዳ ለወገኑ ግድ የሌሌው ሰው አንዴት ብሎ ባለ ክብር፤ እንዴትስ ብሎ አለሁ ይላል? እናም እናንት የትናንት ኢትዮጵያዊያን ከሞታችሁ ቆያችሁ፤ እኛም አንቅረን ከተፋናችሁ ከራረምን። እናንተ እኮ ግድብም ሲገነባ የምትጮሁ፤ አሸባሪም ሲያዝ የምታለቅሱ፤ ቤት ሲገነባ የሚከፋችሁ መንገድም ሲሰራ የምታለቅሱ ትንሳኤያችሁ የራቃችሁ ሙታን ናችሁ። ህያው ብትሆኑማ ኖሮ ክፉውን ከደጉ ለይታችሁ በጮሃችሁ፤ እኛም ባገዝናችሁ። እናም እባካችሁ አደብ ግዙ ቀልብ ይኑራችሁ።

ለመሆኑስ አላማችሁ ምንድን ነው? መንግስትን ማስወገድ? ጥሩ! ይሄ ከሆነ መንገዱ እናንተ እንደምታስቡት አቀበት የበዛበት ሳይሆን ቀናና ቀላል ስለሆነ ኑና እንያችሁ። ስትመጡ ታዲያ የተሻለ አማራጭም ይዛችሁ ይሁን፤ ከዚያ እንፈትሽ፤ ካዋጣን ድምጻችንን እንስጣችሁ፤ መንግስትም ሁኑ። አለበለዚያ ግን በሰው አገር ላይ ሆኖ የቁራ ጩኸት መጮህ ትርፉ እደግመዋለሁ ትዝብት ነው።

በታሪካችን ወደ ወገኖቹ ሽብርተኛ የሚልክ ኢትየጵያዊ ታይቶም ተሰምቶም አይታወቅ። የእኛ ታሪክ የሚናገረው የመጣብንን ወራሪ ሁሉ በአንድ ላይ ሆነን መክተን እንደምንመልስ እንጂ እራሳችን የእራሳችን ወራሪ እንዳልሆንን ነው። ይሁንና ይህ ጉልህና ሌሎች የሚቀኑበት ታሪካችን እድሜ ለእናንተ እያበላሻችሁት ነው። በግልጽ ሽብር የሚያራምድ ድርጅትን በገንዘብና በሞራል እየደገፋችሁ እየላካችሁ ልታስፈጁን ነው። እንደናንተማ ቢሆን አዲስ አበባም ብቻ ሳትሆን ሌሎች ከተሞች ሁሉ በንጹሀን ደም በጨቀዩ ነበር። እንደመታደል ሆኖ ግን ይህ አልሆነም፤ እንዲሆንም አንፈቅድም። ይልቁንም በቆፈራችሁት ጉድጓድ ልክ የምትቀበሩት እናንተ የሽብር የእንጀራ ልጆች ናችሁና ከቻላችሁ ጉድጓድ አትቆፍሩ ካልቻላችሁ ግን አርቃችሁ አትቆፍሩት የሚገባበት አይታወቅምና።

ለመሆኑ ኢትዮጵያ ሽብርን ስትዋጋ ስህተት እናንተ ያላችሁባቸው አገራት ሽብርን ሲዋጉ ግን ትክክል የሚሆኑት በምን መስፈርት በምንስ ልኬት ነው? የኢትዮጵያ የጸረ ሽብር ህግ ከየት የመጣ ይሆን? እናንተ አክራሪ ዳያስፖራዎች ከምትኖሩባቸው አገራት ቃል በቃል የተቀዳ አይደለምን? ታዲያ በዚህ ህግ መሰረት ማን አሸባሪ እንደሆነ፣ የቱስ ድርጅት አሸባሪ ነው የሚለው በግልጽ የተቀመጠ አይደለምን? ነው በአንድ ወቅት እንደተባለው የጥቁር ሰው ደም ደም አይደለምና ዝም ብሎ ይፍሰስ? ይሄ መልስ የሚሻ ጥያቄ ነው።

በመጨረሻም መልዕክቴ አንድ ነው። በሰለጠነው አገር ላይ ሆናችሁ ለምን እንደሰለጠነ ሰው ማሰብ ተሳናችሁ? ወይንስ የያዛችሁት አቋም የስልጡን መስሏችሁ ይሆን? ወይንስ የሰልጣኔ ትርጉሙ ተቀይሮ ስልጣኔ ማለት የገዛ ወገንን በፈንጅ መጨረስና ማስጨረስ ሆኗል? ይሀ ከሆነ እንደ እኔ እንደ እኔ ምንጊዜም ያልሰለጠንኩ ተብዬ ከጋርዮሽ አሰተሳሰቤ ጋር መሞትን እመርጣለሁ። እወነታው ግን ይሄ አይመስለኝም። አውቆ የተኛን ሆኖባችሁ እንጂ እውነታው ጠፍቷችሁ አይደለም።

እስከዚያው ድረስ ማለት የሚቻለው አንድ ነገር ብቻ ነው። እናንተም ሆናችሁ ሁልጊዜም ሰባት እንጂ አስር የማይሞላው ድርጅታችሁ የምትሸርቡት ሴራ እኛ ዘንድ ለመድረስ ቅንታት ታህል አቅም የሌለው መሆኑን አውቃችሁ አርፋችሁ ተቀመጡ። እኛ ስራ ላይ ነን አትረብሹን። እናንተ የሰው አገር አቅኑ። እኛ ደግሞ የእናንተንም ጨምረን እየሰራን እንጠበቃችኋላን ስለ ስራ የምታስቡ ከሆነ ማለቴ ነው። ስለሽብር የምታስቡ ከሆነ ግን ይህችን ጣል አድርጌላችሁ ላብቃ፤ «አልሆነልሽም አንቺ ጋለሞታ ቂጣሽን በልተሽ ወደ መኝታ» አበቃሁ ቸር ይግጠመን።

*******
ይሀ ጽሁፍ በአዲስ ዘመን ጋዜጣ የሀምሌ 25ቀን 2006 ዓ.ም ላይ የወጣና የጸሁፉ ርዕስ ብቻ ተቀይሮ የተወሰደ ነው።

Content gathered and compiled from online and offline media by Hornaffairs staff based on relevance and interest to the Horn of Africa.