በረከት ስምዖን በመልካም ጤንነት ላይ ነው – በቅርቡ ይመለሳል

ሰሞኑን በማህበራዊ ድረ ገፆች አቶ በረከት ስምኦን የጤንነት ሁኔታው ጥሩ አይደለም፤ ከዛም አልፎ በህይወት የለም የሚሉ አሉባልታዎች ሲናፈሱ ነበር፡፡ አንዳንዶቹ መሞቱንስ አረጋግጠናል፤ ይልቁንስ የቀብር ቀኑን ንገሩን ሲሉም ተዘባብተዋል፡፡

እነዚህ በጥላቻ ፖለቲካ የናወዙ ተቃዋሚዎች በአንድ በኩል የኢሕአዴግን ከፍተኛ አመራሮች በማጥላላት ተጠምደው እየዋሉ በሌላ በኩል ደግሞ እነዚህን ግለሰቦች ከሰብዓዊ ፍጡር በላይ አድርገው በማሰብ ልክ እንደማይታመሙ ብሎም ሊሞቱ እንደማይችሉ ዘላለማዊ ፍጥረቶች አድርገው ይስሏቸዋል፡፡ ስለሆነም የጤንነት እክል ባጋጠማቸው ቁጥር ልዩ ስጦታ እንደተበረከተላቸው ይቆጥሩታል፡፡

ኢሕአዴግ በግለሰቦች ላይ ያልተጠንጠለጠለ ይልቁንም ሰፊ ሕዝባዊ መሰረት ያለው መሆኑን ካለመገንዘብና ለመገንዘብም ካለመፈለግ አባዜያቸው መውጣት ያቃታቸው ጭፍን ተቃዋሚዎች አሁንም ካለፈው ስህተታቸው መማር ተስኗቸው የአቶ በረከትን መሞት ልክ ከሰማይ እንደሚወርድ መና አንጋጠው ይጠብቃሉ፡፡Minister Bereket Simon

አቶ በረከት ስምኦን በማንኛውም ጊዜ እንደሚያደርገው ለጤና ምርመራና ለተሻለ የጤና ክትትል ወደ ውጪ አገር መውጣቱ እርግጥ ነው፡፡ አቶ በረከት ካለበት ቦታ ሆኖ ዛሬ ከቅርብ ሰዎቹ ጋር የስልክ መልዕክት የተለዋወጠ ሲሆን ያለበት የጤና ሁኔታም መልካም እንደሆነ ገልጧል፡፡ አቶ በረከት ከአምስት ቀናት በኋላ ወደ አገር ቤት እንደሚመለስም አረጋግጧል፡፡

ታጋይ በረከት ስምኦን ከትጥቅ ትግል ጀምሮ ለአዲሲቷ ኢትዮጵያ የሕዳሴ መሰረት ከጣሉ ግንባር ቀደም ሰዎች መካከል አንዱ ነው፡፡ ለኢትዮጵያ ብሔሮች፤ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች እንዲሁም ለሃይማኖቶች እኩልነት መረጋገጥና ለዜጎች ነፃነት ህይወቱን አሳልፎ የሰጠ የፅናት ተምሳሌት የቁርጥ ቀን ልጅ ነው፡፡

ህዝባዊ ፍቅራቸውና ውግንናቸው ከምላሳቸው ያላለፈው የዘመኑ የእድሜ እኩዮቹና ጓደኞቹ ትግሉን በመሸሽ ወደ አሜሪካና አውሮፓ ሲሰደዱ ታጋይ በረከት ስምዖን ግን ከራስ በፊት ለህዝብ ጥቅም መጠበቅ ከነበረው ፅኑ እምነት በመነሳት ከሌሎች የኢትዮጵያ ህዝብ የቁርጥ ቀን ልጆች ጋር ወደ በረሃ በመግባት ሰው በላውን የደርግ ስርዓት ፊት ለፊት ተጋፍጧል፡፡ የወጣትነት እድሜውን እንደ እድሜ እኩዮቹ ሳይዘልበትና የቅንጦት ህይወት መምራት ሳያምረው የሚያሳሳውን ህይወቱን ጭምር ለመስዋዕትነት አዘጋጅቶ ከሌሎች የህዝብ ልጆች ጋር በመሆን ሃገራችንን ከጨቋኙ የደርግ ስርዓት ታድጓታል፡፡

ከደርግ ውድቀት በኋላም አገራችንን ከመበታተን ጫፍ የመለሳት ሕገ መንግስት ሲረቅቅ ኢትዮጵያ በእኩልነት ላይ እንድትመሰረት በግሉ ሃሳቦችን በማመንጨት ጉልህ ሚና ነበረው፡፡ የዜጎችን ሄወት እየቀየረ የሚገኘውን የኢህአዴግ ፕሮግራምን በመቅረፅ ረገድም ሃገራዊ የመሪነት ሚናውን የተወጣ ታላቅ ባለውለታ ነው፡፡

መውጫ የሌለው መስሎ ከነበረው የድህነት አዙሪት ውስጥ ወጥተን በፈጣን እድገት ውስጥ ካሉ የአለም አገራት ተርታ ስማችን እንዲፃፋ፤ ሀገራችን ለዘመናት ስትታወቅበት ከነበረው ድህነት፤ ኋላቀርነትና የእርስ በርስ ጦርነት ምድብ ወጥታ ስሟ በበርካታ አለም አቀፍ መድረኮች በአብነት እንዲነሳ ባስቻለው የሕዳሴ ጉዟችን ውስጥ ታጋይ በረከት ስሞዖን የአንበሳውን ድርሻ ተወጥቷል፡፡ ታጋይ በረከት ለዚች አገር መለወጥ ያለ እረፍት የጣረ፤ ብዙ ሰርቶ ያሰራ፤ እውነተኛ የኢትዮጵያ የቁርጥ ልጅ መሆኑን ሁልጊዜም ሲያንፀባርቁ በሚኖሩ ደማቅ ቀለሞች ታሪኩን የፃፈ ታጋይ ነው፡፡

ለበረከት ስምዖን መልካም ጤንነትንና ረዥም እድሜን የምመኝለት የሰው ልጅ በኖረበት እድሜ ሊሰራው የሚገባውን ታላቅ ተግባር ስላልፈፀመ አይደለም፡፡ ለበረከት ስምዖን መልካም ጤንነትንና ረዥም እድሜን የምመኝለት ከድህነት ጋር ትንቅንቅ ውስጥ ያለችውን አገራችንን ሌላ እርምጃ ወደፊት ሊያስኬድ የሚችል ራዕይ ባለቤት ስለሆነ ነው፡፡ ለበረከት ስምዖን መልካም ጤንነትንና ረዥም እድሜን የምመኝለት የእድሜውን አብዛኛውን ክፍል የበላውን ትግልና የስራ ጫና አሳርፎ ጥቂትም ቢሆን የእፎይታ ጊዜ እንዲኖረው ስለምመኝለት ነው፡፡

መልካም ጤንነትንና ረዥም እድሜ፤ ለበረከት ስምዖን

መረጃ ላደረሳችሁኝ፤ በተለይም ለጋዜጠኛ ኤሊያስ ተክለወልድ እጅግ አድርጌ አመሰግናለሁ፡፡

Kebede Kassa

more recommended stories