ኢዴፓ በመንግስት ጫና ሳቢያ ስብሰባውን ሠረዝኩ አለ

ከኢትዮጵያውያን ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢዴፓ) የተሰጠ መግለጫ

የኢትዮጵያውያን ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢዴፓ) ሐምሌ 12 ቀን 2006 ዓ.ም ከቀኑ 7 ሰዓት ጀምሮ በተለያዩ ወቅታዊና አገራዊ ጉዳዮች ዙሪያ ከህዝብ ጋር ተገናኝቶ ለመወያየት የሚያስችል ህዝባዊ ስብሰባ አዲስ አበባ ከተማ ሜክሲኮ አደባባይ አጠገብ በሚገኘው መብራት ኃይል አዳራሽ እንደሚያካሂድ ፕሮግራም ይዞ ነበር፡፡Ethiopian Democratic Party

የአዲስ አበባ አስተዳደር በከንቲባ ጽ/ቤት የሰላማዊ ሰልፍና ስብሰባ ማሳወቂያ ክፍልም ለስብሰባው እውቅና ሰጥቷል፡፡

ነገር ግን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ፖሊስ በቅስቀሳ ላይ የተሰማሩትን የፓርቲያችንን አባላት ሐምሌ 10 እና 11 2006 ዓ.ም አግቷቸዋል፡፡ ህዝባዊ ቅስቀሳውም እንዲቋረጥ ተደርጓል፡፡

በዚህም ምክንያት የኢትዮጵያውያን ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢዴፓ) ሥራ አሥፈጻሚ ኮሚቴ በጠራው አስቸኳይ ስብሰባ በጉዳዩ ላይ ተወያይቶ የሚከተለውን አቋም ወስዷል፡፡

1. መንግስት የመድብለ ፓርቲ ሥርዓት ግምባታን አደጋ ላይ ሊጥል የሚችል ኢ-ዴሞክራሲያዊ አካሄድን በአሥቸኳይ እንዲያቆም፣

2. ለህዝባዊ ስብሰባው የምናደርገውን ህዝባዊ ጥሪ እንዳናካሂድ መከልከላችን ዴሞክራሲያዊ፣ ፍትሃዊ ሂደትንና ሰላማዊ ትግሉን በእጅጉ የሚጎዳ እርምጃ በመሆኑ መንግስት ከእንዲህ አይነት ፀረ- ዴሞክራሲ ድርጊት እንዲታቀብ፣

3. ኢዴፓ የጠራውን ህዝባዊ ስብሰባ ተከትሎ ቅስቀሳውን በተገቢው ሁኔታ እንዳያከናውን በመከልከሉ ለከፍተኛ የገንዘብና የጉልበት ኪሳራ ተዳርጓል፡፡ በመሆኑም የሚመለከተውን መንግስታዊ አካል በህጋዊ አግባብ የምንጠይቅ መሆኑን ፣

4. በሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ ሂደት ውስጥ በመሳተፍ ለዴሞክራሲው ግንባታ የበኩላችንን ድርሻ እየተወጣን ባለንበት በአሁኑ ወቅት ለስብሰባው ህዝባዊ ጥሪ እንዳናደርግ መከልከላችን መንግስት ለዴሞክራሲ ግንባታ ያለውን ቁርጠኝነት ጥያቄ ላይ የሚጥል መሆኑን ፣

5. ኢዴፓ በሀገራዊ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ም/ቤት አባል ሆኖ ለሠላማዊ ትግሉ መጠናከር የበኩሉን ገንቢ አስተዋጽዖ ሲያበረክት የቆየ ቢሆንም በም/ቤቱ ያለውን የወደፊት ተሳትፎ የሚፈትሽ መሆኑን፣

6. በብዙሀን መገናኛ ጥሪ ተደርጎላችሁ፣ በደብዳቤ ተገልጾላችሁ፣ ሰው በሰው መረጃው ደርሷችሁ ስብሰባውን ለመካፈል ያሰባችሁ ሁሉ በተደረገብን ክልከላ ምክንያት ህዝባዊ ስብሰባውን ላለማድረግ የተገደድን በመሆኑ ስብሰባው የተሰረዘ መሆኑን ከይቅርታ ጋር ፓርቲው ይገልጻል፡፡

የኢትዮጵያውያን ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢዴፓ) ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ

——

Content gathered and compiled from online and offline media by Hornaffairs staff based on relevance and interest to the Horn of Africa.

more recommended stories