ስለደመወዝ ጭማሪው በሚዲያዎች የተሰራጨው ዘገባ መሰረተ ቢስ ነው – ሲቪል ሰርቪስ ሚኒስቴር

በቅርቡ መንግሥት ለሲቪል ሠራተኛው ያደረገው የደመወዝ ማስተካከያ ዝርዝር ይዘት በመጪዎቹ ሁለት ሳምንታት ውስጥ ይፋ እንደሚደረግ የሲቪል ሰርቪስ ሚኒስቴር አስታወቀ።

ሰሞኑን የደመወዝ ማስተካከያውን አስመልክቶ በተለያዩ የግል የመገናኛ ብዙኃን የተሰራጨው ዘገባ ምንጩ የማይታውቅና መሰረተ ቢስ መሆኑን ሚኒስቴሩ አስታውቋል።

ሚኒስትር ዴኤታዋ ዶክተር ምሥራቅ መኮንን፥ በአሁኑ ወቅት የደመወዝ ማስተካከያው ዝርዝር ሥራ በመከናወን ላይ መሆኑን ጠቁመው፥ ዝርዝሩ በመጪዎቹ ሁለት ሳምንታት ውስጥ ይፋ እንደሚሆን ገልጸዋል።

በአንፃሩ የተደረገውን የደመወዝ ማስተካከያ አስመልክቶ በተለያዩ የመገናኛ ብዙኃን የተሰራጨው ዘገባ መንግሥት የማያውቀው ከመሆኑ ባሻገር የተሳሳተና መሰረት ቢስ መሆኑንም አስታውቀዋል።

አስፈላጊ ሥራዎች ከተናቀቁ የተደረገው የደመወዝ ማስተካከያ ከሐምሌ ወር 2006 ዓ.ም ጀምሮ ለሠራተኛው የሚከፈል ይሆናል ያሉት ዶክተር ምስራቅ፥ የመንግሥት ሠራተኛውን የመኖሪያ ቤት እና የትራንስፖርት ችግር ለመቅረፍ እየተሰራ መሆኑንም ጠቁመዋል።

በተመሳሳይ መሰረታዊ የሚባሉ ሸቀጦችን በ “አለ በጅምላ” ድርጅት በኩል በማቅረብ ኅብረተሰቡ ሸቀጦችን ፍትሃዊ በሆነ ዋጋ እንዲያገኝ የሚያስችል አሰራር መዘርጋቱንም ጠቅሰዋል።

ኅብረተሰቡም በተደራጀ መንገድ ሕገ-ወጦችን በማጋለጥ ከመንግሥት ጎን ሊቆም እንደሚገባ ሚኒስትር ዴኤታዋ አሳስበዋል።

******
ምንጭ፦ ኢዜአ – ሀምሌ 9፣ 2006

Content gathered and compiled from online and offline media by Hornaffairs staff based on relevance and interest to the Horn of Africa.

more recommended stories