ጠ/ሚ ኃይለማርያም ደሳለኝ በፓርላማ ተገኝተው ማብራሪያ የሰጡባቸው ዋና ዋና ጉዳዮች

የኢፌዴሪ 4ኛው የሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት ዛሬ ባካሂደው ስብሰባ በፌዴራል መንግስት የ2007 ረቂቅ በጀት ላይ ዝርዝር ውይይት በማካሄድ የበጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ረቂቅ በጀቱን አስመልከቶ ያቀረበውን ሪፖርትና የውሳኔ ሀሳብ መርምሮ የበጀት አዋጁን አፅድቋል፡፡

የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ በጀቱን በተመለከተና ከም/ቤቱ አባላት ለሚነሱ የተለያዩ ጥያቄዎች ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ማብራሪያ ከሰጡባቸው ጉዳዮች ውስጥ፤ የ2007 ሀገራዊ ምርጫ ዝግጅት፣ ለመንግስት ሰራተኞች የተደረገው የደመወዝ ማስተካከያ፣ በጡረታ የሚተዳደሩ ዜጎች የኑሮ ሁኔታ፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከአዲሱ የግብፅ ፕሬዝዳንት አል ሲሲ ጋር ያደረጉት ውይይትና የብሔራዊ ስታዲየም ግንባታ ጉዳይ ይገኙበታል፡፡PM Hailemariam Desalegn in Parliament

የ2007 ዓ.ም ሐገራዊ ምርጫ

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያ ደሳለኝ የ2007 ዓ.ም ሐገራዊ ምርጫ ሰለማዊ ማድረግ የሚችለው ህዝቡ ነው ብለዋል። ለዚህም ህዝቡ ከቅድመ ምርጫ እስከ ድህረ ምርጫ ድረስ በነቂስ ወጥቶ ተሳታፊ እንዲሆን መንገስት የበኩሉን ሥራ እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

መንግስት ምርጫውን ፍትሐዊ፣ ዴሞክራሲያዊ እና ነጻ ለማድረግ በቁርጠኝነት እየሰራ ነው። ተወዳዳሪ ፓርቲዎችም በምርጫ ሥነ- ምግባር ህጉ መሰረት በመንቀሳቀስ የበኩላቸውን ድርሻ መወጣት አለባቸው ብለዋል አቶ ኃይለማርያም።

በፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ላይ በጋራ ሥራዎች እየተሰሩ ሲሆን የምክር ቤቱ አባል ያልሆኑ ፓርቲዎች ህጉን ተከትለው በመስራት ምርጫውን እንከን የለሽ ማድረግ ይገባቸል ብለዋል። ከዚህ ውጭ ምርጫውን ለመበጥበጥ የሚነሱ ኃይሎች የሚኖሩ ከሆነ ግን መንግስት ህግ የማስከበር ኃላፊነቱን ይሰራል ነው ያሉት።

የ2007 ዓ.ም ሐገራዊ ምርጫን እንከን የለሽ ለማድረግ ህዝቡ፣ የምርጫ ቦርድ፣ ፓርቲዎች እና የሚመለከታቸው አካላት ሁሉ የድርሻቸውን እንዲሰሩ ጥሪ አቅርበዋል። 

የግድቡ ግንባታ ለአፍታም ቢሆን አይዘገይም

በአባይ ላይ የኛ አቋም ግልጽና የማይዋዥቅ ነው፡፡ የናይልን ውሃ በፍትሃዊነት የመጠቀምና ከዚህም በተጨማሪ በታችኞቹ የተፋሰሱ ሀገራት ላይ የከፋ ጉዳት እንዳይኖረው የማድረግ አቋም ነው፡፡ አዲሱ የግብጽ መንግስት አቋሜ አዲስ ምዕራፍ በመክፈት በአዲስ ገጽ ለመጻፍ ተዘጋጅቻለሁ የሚል ነው፡፡ የኛ አቋም ይህንኑ ተቀብሎ በጋራ ለመስራት ነው፡፡

በየትኛውም ሁኔታ የኢትዮጵያ ህዝብና መንግስት አቋም የግድቡ ግንባታ ለአፍታም ቢሆን እንደማይዘገይ መሆኑን ነግረናቸዋል፡፡

ከአዲሱ የግብጽ መንግስት ጋር የሶስትዮሽ የጋራ የቴክኒክ ኮሚቴ ስራውን እንዲጀምር፣ የጋራ ኮሚሽን በአመት አንዴ የነበረው በየሶስት ወሩ እየተገናኘ እንዲወያይ ተስማምተናል፡፡ በአጠቃላይ ድርድሩ በዚህ መልኩ ተጠናክሮ እንዲቀጥል እምነት አለ፡፡ ነገር ግን አሁንም ድርድሩ ቀላል እንደማይሆን እንገምታለን፡፡

በእነሱ በኩል ያለውን ይህን በጎ አቋም ይዘን በኛ በኩል የተያዘውን አቋም አጠናክረን በማስቀጠል እነሱን ወደዚሁ አቋም ለማምጣት ጠንክረን እንሰራለን፡፡ ይህን አጠናክረን በማስቀጠል ከግብጽ ጋር በአባይ ጉዳይ ላይ ብቻ ሳይሆን በሌሎች አፍሪካዊ ጉዳዮችም በጋራ ለመስራት በኛ በኩል የማይናወጥ አቋም አለን፡፡

የዋጋ ግሽበት የሚከሰትበት ምንም አይነት ኢኮኖሚያዊ ምክንያት የለም

የደመወዝ ማስተካከያ መደረግ የነበረበት ዘንድሮ አልነበረም፡፡ ባለፈው አመት ነበር ሊደረግ የሚገባው፡፡ የዘገየበት ምክንያት በዋናነት የደመወዝ ማስተካከያ ሲደረግ የዋጋ ግሽበት እንዳያስከትል የዋጋ ግሽበቱ አንድ አሃዝ መሆን ስለነበረበት ነው፡፡ ይህም ዘላቂ መሆኑን ማረጋገጥ ይገባ ነበር፡፡

የዋጋ ግሽበቱን አንድ አሃዝ እንዲሆን ማድረግ ችለናል፡፡ ይህም ለአንድ አመት ያህል የቆየ ዘለቄታ እንዳለው ተጠንቷል፡፡ ለአንድ አመት ተኩል ያህል ግሽበቱ በአንድ አሃዝ ውስጥ መቆየቱን ካጠናን በኋላ የደመወዝ ማስተካከያ ቢደረግ የዋጋ ግሽበት እንደማያመጣ አረጋግጠናል፡፡

ይህ ብቻ ሳይሆን የ2007 የመንግስት በጀት ሲዘጋጅ የመንግስት የበጀት ጉድለት የዋጋ ንረትን እንደማያስከትል ማረጋገጥ ነበረብን፡፡ ይህ ተሰርቷል፡፡ ም/ቤቱም በዝርዝር ከተወያየበት በኋላ አምኖበታል፡፡ ስለሆነም የዋጋ ግሽበት የሚከሰትበት ምንም አይነት ኢኮኖሚያዊ ምክንያት የለም፡፡

ከዚህ በተጨማሪ ከአሁን በፊት መንግስት የዋጋ ግሽበትን ለመከላከል የወሰዳቸው እርምጃዎች ሁሉ አሁንም ተጠናክረው ይወሰዳሉ፡፡

በመሰራታዊ ሸቀጦች ላይ በፊት ስናደርገው እንደነበረው አሁንም ድጎማ ማድረጋችን ይቀጥላል፡፡ እንደ ስኳርና ዘይት ያሉ ሸቀጦች ይቀርባሉ፡፡

ስለዚህ የዋጋ ንረት ከመጣም ሊሆን የሚችለው ስግብግብ ነጋዴዎች በራሳቸው ጊዜ ተነስተው ሊጨምሩት የሚችሉት ዋጋ ነው፡፡ ይህ ከሆነ መዋጊያው ስልት መንግስት ሰራተኛ የሆኑትም ሆኑ ያልሆኑ ሸማቾች በራሳቸው ጊዜ ተደራጅተው ህጉ በሚፈቅድላቸው መሰረት እነዚህን ነጋዴዎች መታገል ነው፡፡ በተበታተነ ሳይሆን በተደራጀ መልኩ መታገል መጀመር አለባቸው፡፡ መንግስት ያቋቋመው የንግድ ውድድርና የሸማቾች ጥበቃ ባለስልጣን ደግሞ እነዚህን ተከታትሎ የሚወስደው እርምጃ ይኖራል፡፡

ከዚሁ ጋር ተያይዞ የተነሳው የጡረተኞች ጉዳይ ነው፡፡ በ2003 ዓ.ም እንዳደረግነው ሁሉ አሁንም በነሱ ክፍያም ላይ ማስተካከያ ተደርጓል፡፡

የውጭ ምንዛሪ እጥረት በበጀት አመቱ አሳሳቢ አይሆንም

በሀገራችን የውጭ ንግድ ዋና መሰረት ግብርና ሲሆን ቡና ቀዳሚውን ድርሻ ይይዛል፡፡ በአንድ ሄክታር ሲመረት ከነበረው 4 ኩንታል ወደ 8 ኩንታል ምርቱን ማሳደግ ብንችልም ሌሎች ሀገራት በአንድ ሄክታር ከሚያመርቱት 24 ኩንታል ለመድረስ ግን ገና ይቀረናል፡፡ ባለው ተስማሚ የአየር ሁኔታ ተጠቅመን ምርቱን አሁን ካለንበት የ50 በመቶ አፈጻጸም ገና መጨመር እንችላለን፡፡

ከቡና ቀጥሎ በውጭ ንግድ ሰሊጥ ከፍተኛውን ድርሻ የሚይዝና በቅርቡ ከቡና የመሪነቱን ቦታ ይረከባል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ሰሊጥ ሊመረትባቸው የሚችልባቸው አካባቢዎች አሮሚያ፤ ደቡብ፤ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ፤ አፋር እና ሶማሌን ጨምሮ ተስማሚ የአየር ሁኔታ ስላለ ለማስፋፋት እየተሞከረ ይገኛል፡፡ በሰሊጥ አምራችነታቸው የሚታወቁት አማራ እና ትግራይም ቢሆኑ አፈጻጸማቸው ከ50 በመቶ በታች ነው፡፡

ከግብርና ምርቶች መካከል ጥራጥሬ ሶስተኛ ደረጃ ይይዛል፡፡ በሀገራችን 2 ሚሊየን ሄክታር መሬት የኮትቻ አፈር በመሆኑ በማንጣፈፍ በዓመት ሁለት ጊዜ ጥራጥሬን ለማምረት ተችሏል፡፡ ግን በሚፈለገው ደረጃ ተተግብሯል ለማለት አይቻልም፡፡ በአትክልት እና ፍራፍሬም በኩልም እንዲሁ፡፡

በአበባ ልማት መቀዛቀዝ ታይቶ የነበረ ቢሆንም ባለፉት ስድስት ወራት በመስኩ የሀገር ውስጥ እና የውጭ ባለሃብቶች ተሳትፎ ጨምሯል፡፡ በባህላዊ ማዕድን ሃብት ረገድም የወርቅ ዋጋ መውደቅ ተጽእኖ ፈጥሮብናል፡፡ በዋና ዋና የውጭ ንግድ ምርቶች በታቀደው መሰረት ባይፈጸምም በውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት በኩል የተሻለ ነገር ስላለ የውጭ ምንዛሪ እጥረት ብዙም አያሳስብም፡፡ 

የስፓርት ክህሎትን ለማሳደግ ልዩ ትኩረት ተሰጥቷል፡፡

ክልሎች የእግር ኳስ ስታዲየም ለመገንባት በስፋት እየተንቀሳቀሱ ናቸው፡፡ ከዚህ በተጨማሪ አንዳንድ ከፍተኛ ትምህርት ተቋሞችም ጭምር በዚህ ስራ ላይ ገብተውበታል፡፡ ያጠናቀቁም አሉ፡፡ ይህ የስፓርት ክህሎትን ለማሳደግ ልዩ ትኩረት መሰጠቱን ያሳያል፡፡

አሁን ጥያቄው የተነሳው እዚህ አዲስ አበባ የሚገነባው ብሄራዊ ስታዲየም ጉዳይ ነው፡፡ እንደሚታወቀው በጨረታ ሂደት ላይ ሂደቱን የሚያጓትቱ ችግሮች ያጋጥማሉ፡፡ በዚህኛውም ከዲዛይን ጋር በተያያዘ በደል ደርሶብኛል የሚል አካል በማጋጠሙ ጉዳዮ ወደ ፍርድ ቤት ሄዷል፡፡ ጉዳዩ ወደ ፍርድ ቤት የሄደ ስለሆነ መንግስት በዚህ ጉዳይ ገብቶ የሚፈጥረው ጫና ሊኖር አይችልም፡፡ ስለዚህ እሱን መጠበቅ ይገባል፡፡

አሁን ባለኝ መረጃ መሰረት ክርክሩ በሳምንት ጊዜ ውስጥ እልባት ያገኛል፡፡ ያም ሆኖ ከፍርድ ቤት ውጭ ባሉት ጉዳዮች ላይ ስራዎች ሲሰሩ ነበር፡፡ እንደ የስታዲየሙን አጥር መስራት፤ ለልማቱ ሲባል መነሳት የነበረባቸውን ነዋሪዎች ጉዳይ መጨረስ የመሳሰሉት ሲሰሩ ነበር፡፡

ስለሆነም የፍርድ ቤቱ ስራ እንደተጠናቀቀ ወደ ተግባር የምንገባበት ነው፡፡ ይህን ያክል ከባድ የሚባል ስራም አይደለም፡፡

******

Kebede Kassa

more recommended stories