የፌደሬሽኑ ስርዓተ-መንግስት ፍዳ

[ተወልደብርሃን ክፍለ ([email protected])]

የኢትዮጵያ ስርዓተ-መንግስት “ነብያት” በፌደራል ስርዓታችን ውስጥ የሚታዩትን ክስተቶች ከስርዓቱ ባህሪያውነት እንደሚመነጩ ለማሳየት ለምእተ ዓመታት አብሮን የዘለቀውን “የአንዲት ኢትዮጵያ” ቲስሳቸውን “ትክክለኛነት” በአስረጂነት ለመጠቀም ብዙ ሲደክሙ ይስተዋላሉ። ከዚህ ጎራ በተቃራኒ አሃዳዊውም ሆነ ፌደራላዊውን ስርዓተ-መንግስታት መለየት የተሳነው፣ የኢትዮጵያዊነት አቋራኝ ዘለበቶችን ለመበጣጠስ የቆረጠ፣ ንፁሃን ዜጎችን በማጥላላት፣ በማሰቃየትና በመጨፍጨፍ የደለበ የጭፍኖች ስብስብ እናገኛለን። በነዚህ ጎራዎች መሃል ደግሞ ገዢው ፓርቲ በሚፈጥራቸው የመልካም አስተዳድር ችግሮች የተነሳ ፅንፈኞ እንዲፋፉ ፤ ትንቢታቸውን የሰመረ ያህል እንዲወራጩ የበኩሉን አስተዋፅኦ እያበረከተ ይገኛል። በውጤቱም ቁጥራቸው የማይናቅ ዜጎች በፌደረሽኑ ዘላቂነት ላይ ከቅንነት የሚመነጭ ተገቢ ስጋት እንዲያድርባቸው ምክንያት እየሆነ ነው።

1. ፖለቲካዊ ስርዓቱንና ፖለቲካዊ ስልጣንን ማምታታት እንደ ስልት

የቀኝ ዘመም አክራሪው ሃይል ዋንኛ የትግል አጀንዳ የፖለቲካ ስርዓቱ በመሰረቱ መቀየርን ማዕከል ያደረገ ነው። ይህ አጀንዳ ኢህገ-መንግስታዊ በመሆኑ ለዲሞክራሲ መጎልበት የሚጫወተው ሚና አነሰ ቢባል አሉታዊ ሲሆን የክፋቱ ጥግ ደግሞ ስርዓት አልበኝነትን በማንገስ እስካሁን የተመዘገቡትን ድሎች በዜሮ የማባዛት ያህል ነው። ይህ ሃይል የፌደራል ስርዓተ-መንግስት ባህሪያዊ ህፀፅ የፈጠረው አይደለም። ይልቁንስ የፌደራል ስርዓት ለመፈጠሩ ዋነኛ ምክንያት ይኸው ሀይል የሚወክለውን አስተሳሰብ አንግቦ ለዘመናት ተጭኖን የኖረ ስርዓት ነው። በህገ-መንግስቱና በሀገመንግስታዊ ስርዓቱ እንዲሁም ከህገ መንግስቱ የሚመነጩትን ተቋሞች አምርሮ ይጠላል። በመሆኑም አጀንዳዎቹ ሁሉ በስርዓተ መንግስት ለውጥ ላይ ያተኮሩ ናቸው። ስልጣን ላይ ያለው መንግስት መለወጥ የቅርብና ትንሹ ዓላማው ነው። የመጨረሻና ዋናው ግቡ ግን ያሸነፍነውን ስርዓት መልሶ ነፍስ እንዲዘራ ማድረግ ነው። የዴሞክራሲ የበላይነትን የመቀበልም ሆነ ከአዲሱ ስርዓት ጎን ለጎን መራመድ የሚችል ሃይል አይደለም። ምክንያቱም የዴሞክራሲ የበላይነት ለህገ-መንግስቱና ለተቋሞቹ ከመገዛት ውጪ ሊታሰብ አይችልምና ነው። የፖለቲካ ክርክሮቻችን በማህበረ-ኢኮኖሚያዊ ችግሮቻችን ዙሪያ መሆናቸው ቀርቶ በስርዓታችንና ስርዓታዊ ተቋሞቻችን እንዲታጠሩ በማድረግ እርምጃዎቻችን ከዕለት ዕለት እንዲቀንሱ በሂደትም ወደኋላ እንዲቀለበሱ እናም አማራጮቻችን በማጥበብ በራስ መከላከል ክልል ውስጥ እንድንታጠር የሚችለውን ሁሉ እያደረገ ነው። ይህ ሀይል ያለጥርጥር መሸነፍ አለበት። እስካሁን ባገሪቱ ሁለንተናዊ እውነታ ላይ ያደረሰው በደል ከበቂ በላይ እንደሆነ ሊነገረው ይገባል። ህገ-መንግስቱና ህገ-መንግስታዊ ስርዓቱ ሳይቀበል ከዚሁ በተገኙ ተሩፋቶች ላይ በአውንታዊነት ተጠቃሚ ሊሆን ኣይቻለውም። ነገረ ስራው ሁሉ ገዢው ፓርቲና ጠባቡ ሃይል በሚፈጥሩዋቸው ችግሮችና ክፍተቶች ተጠቅሞ ስርዓቱን ማፍረስ ነው። ሀገራዊ መግባባት ሊኖር የሚችለው መነሻችን ህገ-መንግስትና ህገ-መንግስታዊ ስርዓቱ ያለ አንዳች ማመንታት መቀበል ሲቻል ብቻ ነው። ስለሆነም ስርዓቱን ለማፍረስ እየተፈፀመ ያለውን ደባ ለፖለቲካ ስልጣን ከሚደረግ ትግል ጋር መምታታት የለበትም። ለሃገራችን ደህንነትና ዴሞክራሲያዊ አንድነት መቀጠልና መበልፀግ ሲባል የዚህ ሃይል የቁራ ጩኸት በዜጎች ንቁ ተሳትፎ ማብቃት አለበት። መንግስት መቼም ቢሆን፤ ምንም ቢያደርግ የኒዮሊበራል ቀሳውስቱ ባርኮት አያገኝም። ምንም ቢታገስ እናም በመታገሱ ምክንያት የቱንም ያህል ውድመትና ጥፋት ቢደርስ መልሶ የሚጠቃው እራሱና ጉዳት የደረሰበት የህብረተሰብ ክፍልና ከባቢ ነው። ስለሆነም ሌሎችን ለማሳመን ሲባል ሚስኪኑና ሰላም ወዳዱ ህዝብ ለጉዳት መዳረግ የለበትም።

2. የታሪክ እስረኞች

እላይ ከተጠቀሰው ሃይል በተቃራኒ ዋልታ እራሱን ከታሪክ እስረኝነት ማላቀቅ የተሳነውና በጠባብ አጀንዳ የታጠረ ጎራ እናገኛለን። የዚህ አመለካከት በዋነኝነት በኦነግና ኦእነግ የሚቀነቀን ሲሆን በአዲሱ ስርዓተ-መንግስት የጠገጉትን ቁስሎች ላይ እንጨት መስደድ ከምንም ነገር በላይ ያስደስተዋል። የኦሮሞ ህዝብ በቀደሙቱ ስርዓታት መበደሉ እውነት ነው። ለዚህም ነው ታግሎ በማሸነፍ እራሱን እያስተዳደረ ያለው። ይህ በትግል የተገኘውን ራስ የማስተዳደር እድል ኦነጎች የሚዋጥላቸው ክኒን አልሆነም። ስለሆነም ያምታታሉ። አሜሪካና አውሮፓ ውስጥ ተቀምጠው በሚነፉት ፊሽካ ዩኒቨርሲቲዎቻችንን ያናውጣሉ። ክፉና ደጉን እንዲሁም እውነትንና ቅጥፈትን በምክንያታዊ አእምሮ አብጠርጥሮ እንዲለይ ተስፋ የተጣለበት የዩኒቨርሲቲ ተማሪ ንብረትን ለሚያወድምና ህይወትን ለሚቀጥፍ ሁከት “ሆ” ብሎ ሲነሳ ከማየት በላይ የሚያሳዝን ነገር የለም። ይህ ድንቁርናን ከማምለክ የሚተናነስ ችግር አይደለም። እንኳን አመፅ ክርክርም ቢሆን እውነት ሳይጨብጡ ዘው ብለው የሚገቡበት ነገር አይደለም።

የኦነጎች የትግል ማጠንጠኛ ሰለባነት(victimhood) ነው። ሰለባነት የትግል ዋነኛ ገፊ በሚሆንበት ሁኔታ ዴሞክራሲ አበቃለት ማለት ነው። የኤርትራ የነፃነት ትግል ዋነኛ ገፊ ከነፃነት በኋላ ሊመጣ የታሰበውን ዴሞክራሲያዊ ስርዓት አልነበረም። ወሳኝ የትግል እርሾ ሆነው ያገለገሉት በተቀሩት ኢትዮጵያውያን ላይ ያሳደሩት ጥላቻ እንዲሁም የሰለባነት ስሜት ነበር። ነፃነቱን ተከትሎ የመጣውን መአት በዓይናችን በብረቱ እያየንና እየታዘብን ነው። የኦነግ ትግል እርሾዎችም ጥላቻና ሰለባነት ናቸው። በእንደዚህ ዓይነቱ ሁኔታ የሚመራ ትግል ወዳጅና ጠላት አይለይም። የዴሞክራሲያዊ አንደነት ጥቅሞችን አይቀበልም። ምክንያቱም እንደዚያ ከሆነ ህልውናው ስለሚያበቃ ነው። የጠባቡ ሃይል አጀንዳ እውነትን ለህዝብ ማድረስ ሳይሆን ዜናን መፍጠር ነው። በየጊዜው የሚነድፋቸው ስልቶች “ሰበር” ዜናን ታሳቢ ያደረጉ ናቸው። የሰዎች ስሜት ገንፍሎ መፍሰስ አለበት። በውጤቱም ሰው ይሞታል፤ ንብረት ይወድማል። ይህ አልተሳካ እንደሆነ የቆዩ ወይም ጭራሽኑ ኢትዮጵያዊ ያልሆኑ ምስሎችን ከአርካይቭ በማካተት ኡኡታው ለመላው ዓለም እንዲደርስ አበክሮ ይሰራል። ይህ በድንቁርና ጨለማ ውስጥ የተመሰረተ ስንኩል የትግል ስልት ነው። ጨለማው ሲገፈፍ ግን ትግሉ የሚቆምበት እግር የለውም።

ትርጉም ያለው ለውጥ ሊመጣ ከሆነ ይህ የጥላቻና “የሰለባነት” መንፈስ መሰበር አለበት:: የጥላቻና የሰለባነት ስሜት ሌሎች ሰለባዎችን ከመፍጠር የዘለለ ለኦሮሞ ህዝብ የሚያመጣለት አንዳች ፋይዳ የለም። በአሁኑ ጊዜ የአፄ ሚኒሊክ ህጋዊ ወራሽ የሆነ አካል በዚህ ሀገር የለም። በሳቸው ጊዜ የተፈጸሙትን መልካምም ሆኑ መጥፎ ነገሮች ትምህርት ከመውሰድ ታልፎ የፖለቲካ ግብ ለማስቆጠር የሚውሉ ከሆነ ሞራላዊ የበላይነቱ ምኑ ላይ ነው ያለው? አዲሱ ትውልድ ከሳቸው በምን እንደሚሻል የማሳየት ትልቅ ሸክም አለበት። ከኛ ዘመን በአንድ ምዕተ-ዓመት የሚቀድሙ ፣ ያልተማሩና ፈውዳል መሰረተ-ኢኮኖሚ የነበራትን ሃገር የመሩ ሰው ከኖሩበት ዘመን ውጭ ለመመዘን መዳዳት ግብዝነትና በታሪክ እስረኝነት መኖርን መምረጥ ነው። የትምክህተኛውን ሃይል መሰሪ አስተሳሰብ መዋጋት የሚቻለው “ዓይን ላጠፋ ዓይን” የሚለውን ተረት በመከተል አይደለም፤ ባስተዋይነትና በታጋሽነት እንጂ።

የኦሮሞ ተራማጅ ሃይሎች ይህን የሰለባነት መንፈስ ታግለው ማሸነፍ ይጠበቅባቸዋል። በሰለባነትና ሌሎችን በመጥላት ላይ የተመሰረተ አስተሳሰብ በዋነኛነት የሚጎዳው አስተሳሰቡን የሚያስተናግደው ህዝብና ከባቢ ነው። ከባቢያዊነት በራሱ ግብ አይደለም። በከባቢያዊ ጌታነትና በህዝቦች ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት መካከል ያለውን ልዩነት የሰማይና የምድር ያህል የተራራቀ ነው። የኤርትራና የደቡብ ሱዳን አሳዛኝ ሁኔታ እዚህ ላይ ማንሳቱ በጣም ጠቃሚ ነው። እነዚህ ሃገራት ለነፃነት የከፈሉት መስዋእትነት አሁን እየደረሰ ካለው ጥፋት በእጅጉ ያነሰ ነው። ህዝቦቹም የበፊት ገዥዎቻቸው ካደረሱባቸው በደሎች በብዙ እጥፍ የከፋ በደል በገዛ ልጆቻቸው አየተጋቱ ነው። ኦነግም አይሳካለትም እንጂ ከዚያ የተለየ ለኦሮሞ ህዝብ የሚያቀርብለት ህብስተ-መና የለም። ይህ ታዲያ ትምክህተኛው ሃይል ሁሌ እንደሚመፃደቅበት ለዘበት የሚቀርብ ጉዳይ ሳይሆን በዴሞክታሲያዊ ብሔረተኝነትና ከባቢያዊነት መካከል ያለውን ልዩነት የብርሃንና የጨለማ ያህል ቁልጭ ያለ ልዩነት መሆኑን ሁለንተናዊ ትግል በማድረግ ማሳየት ነው። ሰለባነት ታላቁን የኦሮሞ ህዝብ የሚመጥን አይደለም። ሰለባነት አመልካችነቱ የኋሊት ነው። ሰፊው ህዝብ ደግም የኋሊት በመጓዝ የሚያተርፈው አንዳች ጥቅም የለም።

መደምደሚያ

የፌደራሉ ቅርጸ-መንግስት ብዝሃነታችንን ለማስተናገድ ታስቦ የተፈጠረ አገልጋይ የአደረጃጀት መሳሪያ እንጂ መባ የሚያቀርቡለት አንዳች መለኮታዊ ሃይል አይደለም። ኢትዮጵያችን ለዘመናት በድህነት፣ ኃላቀርነትና የርስ የርስ በርስ ጦርነት ስትታመስ የኖረችው አሃዳዊ ስርዓተ መንግስት ትከተል ስለነበር ብቻ አይደለም፤ ዲሞክራሲያዊ ስላልነበረች እንጂ። የአዲሲቷ ኢትዮጵያ ዋስትናም እኩልነት የተረጋገጠበት ዴሞክራሲያዊ አስተዳደር ብቻ ነው። አደረጃጀቱ በህብረቱ ላይ ጥርጣሬ የነበራቸው ወገኖችን ለማስተናገድ እድል ፈጥሯል። የሁሉም ችግሮች ብቸኛ መፍትሔ እንዲሆን የተፈጠረ ግን አልነበረም፤ ሊሆንም አይችልም። ከውጭም ከውስጥም ሲገዘግዙት የማይናውጥ ዐለትም አይደለም። ስለሆነም የቅራኔዎች ቋሚና ቀጣይ መፍቻ ቁልፍ ሆኖ እንዲያገለግል ከተፈለገ የዜጎች ባጠቃላይና የፖለቲካ ሀይሎች በተለይ ገንቢ ሚናቸውን መጫወት ግድ ይላቸዋል። ይህ ይሆን ዘንድ ግን በሁለቱ ተቃራኒ ዋልታዎች የሚገኙትን የትምክህትና የጠባብ ሀይሎች በመረጡት መንገድ ማሸነፍ ግድ ይላል። ኢትዮጵያችን የአብዮቶች ቤተሙከራ መሆንዋን ማብቂያ ጊዜው አሁን ነው።

********

Teweldebrhan Kifle

more recommended stories