የአናርኪው ረሰፒ (recipe for anarchy) – በኢትዮጵያ

አናርኪ(anarchy) በርካታ ትርጉሞች አሉት:: ብዙዎች የሚስማሙበት ትርጉሙ ግን አስፈጻሚ መንግስት የሌለው ማህበረሰብ ማለት ነው:: አናርኪስት(anarchist) ማለት ደግሞ መንግስት ወይም ህግና ሥርዓት ለአንድ ማህበረሰብ አስፈላጊ አይደሉም ብሎ የሚያምን እና ለዚህም ዓይነት አጋጣሚ እውን መሆን ጠንክሮ የሚሰራ ግለሰብ ነው::

የአናርኪስትነትን አስተሳሰብ እንደሀሳብ መከተል ወንጀል አይደለም:: ልክ በስርዓትና በህግ እንደሚያምን ሁሉ አስተሳሰቡን መያዝና በብዙ ሀገሮችም የማሰራጨት መብት አለው:: ጥቂት ወዳጆቻችንም ወደዚህ ፈሊጥ መንሽራተት ከጀመሩ ሰንብተዋል::

አናርኪስት ለመሆን የተመቻቹ ወይም የሚያበረታቱ ብዙ ጉዳዮች አሉ:: አንደኛው በማህበረሰባችን ያለው የሥራ አጥነት ችግር ነው:: ሌላኛው እየከፋ የሄደው ድህነትና ከዚያ ጎን ለጎን የሙስና መንሰራፋት ነው:: በተለይ ዜጎች በህጋዊ ተቋማትና በመንግስት አስተዳደር ላይ ዕምነት የሌላቸው መሆኑ የለውጥ ናፍቆትን ይጨምራል ወይም የማህበረሰብ ህግና ስርዓትን ተቀባይነት እንዲቀንስ ያደርጋል :: መንግስታት ይህንን ችግር ከመፍታት ይልቅ በእመቃና መረጃዎችን በማፈን ላይ ከተሰማሩ ደግሞ የበለጠ ጥፋትን ይጋብዛሉ:: ይህ ደግሞ ተስፋ ለቆረጡ ዜጎችና ማህበረሰብ ጥሩ ረሰፒ(recipe) ወይም ግብዐት ነው::

የማህበረሰብ አውታርና አናኪስትነት

አናርኪስትነት በእንደኛ ዓይነት ማህበረሰብ አደጋ አለው:: በተለይ ገጸ-መጽሐፍ /ፌስቡክ/ና ትዊተርን በመሳሰሉ የማህበረሰብ አውታሮች ስለምንጽፋቸውና ስለምናስተላልፋቸው ሀሳቦች ሐላፊነት ሊሰማን ይገባል:: በአኖኒመስ አካውንቶች ወይም ማንነታቸውን በፎቶና በአድራሻ የማያሳውቁ ሰዎች ከሌሎች ሰዎች የተለየ ሀላፊነትና ጥንቃቄ ያሻቸዋል::

ሌሎቻችንም ይህ ጉዳይ በማይታወቁ ሰዎች ላይ ጠበቅ እንዲልና በተለይም የመረጃዎቹን እውነትነት ለማረጋገጥ በመስራት ማጋለጥ ያስፈልጋል:: ያልተረጋገጠ እውነት ይዞ ከማጨብጨብ ከማጋጋል ከማራገብ መቆጠብ አለብን:: ይህን የሚፈጽሙትን አንተ ማን ነህ? እኛስ ለምን እንከተልሃለን? ዓላማና ሞቲቭህ ምንድን ነው? ብሎ በጥያቄ ማጣደፍ ያስፈልጋል:: ያህ ካልሆነ ይህን አይነት አሉባልታዎች የሰዎች ህይወትን የማጥፋትና ከፍተኛ ረብሻ የመፍጠር አቅም አላቸው::

የመረጃ ክፍተቶቹና እጦቶቹ በሚፈጠሩላቸው አጋጣሚዎች ተጠቅመው ፖለቲካዊና ስታትስቲካዊ ልብወለዶችንና አሻሚ ድምዳሜዎችን የሚያቀርቡ::የሚሽጡ:: የሚያከራዩ:: የሚያከፋፍሉ መኖራቸው ግልጽ ነው:: እነዚህ የመጨረሻው ዓላማህ ምንድነው? መረጃውንስ እንዴትና በምን አገኘኸው? የደረስክበትን ድምዳሜ እንዴትና በምን ቀመር ደረስክበት? ብሎ መጠየቅና ማጋለጥ ያስፈልጋል::

ብዙዎቹ የሚጠይቃቸው ሲገኝ በስንፍና ጎግል አድርገው ይሉታል ወይም ጥያቄውን በሌላ ጥያቄ ይሰብሩታል:: ወደ አንድ ድምዳሜ የሚወነጨፍ መሰሪ ጫፍ ሰጥተው አጣራው ይሉሃል::ቀጥተኛ መልስ የሌላቸው ሀላፊነት ስለማይሰማቸው ወይም ስለማይገዳቸው ነው:: እንደፈለጉ ነገር ይሰራሉ:: ይቆለምማሉ:: ነገር ያሳካሉ:: ያቀሳስራሉ:: የሞራልም የምክንያትም ስርዓት አይገዛቸውም:: ይህን ግሩፕ ሰደበልኝ ወይም ይህን ግሩብ ልክ አስገባልኝ እያልን ጮቤ የምንረግጥ ከሆነ መጨረሻው አያምርም::

የሥርዓት አልበኝነት ልጆች (Sons of Anarchy)

ይህ የቴሌቭዥን ተከታታይ ሾው ነው:: በአምስተኛው ሲዝን በአምስተኛው ክፍል ውስጥ ፊልሙ ሲጀምር እንዲህ የሚል ጉዳይ ይተረካል::የፊልሙ መሪ ተዋናይ ጄክስ ከእንቅልፉ እንደነቃ አልጋው ላይ ሆኖ የሚጀምረው ሀሳብ በራሱ ገዢ ድምጽ ይተረካል::እንዲህ ተርጉሜዋለሁ::

“ሰዎችን ነገሮችንና ተቋማትን አለመጥላት ያስቸግራል:: መንፈስህን ይሰብሩትና ስትደማ እያዩህ ደስ ይላቸዋል:: ስለዚህ ጥላቻ ስሜት የሚሰጥ ብቸኛው ነገር ነው:: ነገር ግን ጥላቻ የሰው ልጅን ምን እንደሚያደርግ አውቃለሁ::ተሁለት ይቀደዋል::ወደ አልሆነው ነገር ይቀይረዋል- ወደዚያ አልሆንም ብሎ ለራሱ አስቀድሞ ቃል ወደገባለት ጉዳይ:: ይህን ነው ልነግርህ የሚገባው::

አንዳንዴ ህይወቴን ሳስበው ገዳይ በሆኑ ድርጊቶች ሚዛን የተወጠረ ይመስለኛል:: ልወረውረው በሚገባውና ላከናውነው በሚገባው መሀል የተወጠረ:: ግብታዊ ምላሽ- ከአዕምሮዬ ቀድሜ ለመፍትሄ መሮጥ[ይቀናኛል]:: አዋዋሌን ሳየው አብዛኛው ጊዜ የሚጠፋው ከዚያ ቀን በፊት የደረሰውን ጉዳት ለማጽዳት በመሞከር ነው:: በዚያ ህይወት ውስጥ ወደፊት ወይም ተስፋ የለኝም:: ያለኝ ነገር ጥፋትና ጸጸት ነው::

ላሳውቅህ የምፈልገው በልቤ በሚሰማኝ ረባሽ ጉዳይ ክብደት ውስጥ ራሴን መደበቅ/መጠለል/ አልፈልግም::ከሶስት ቀን በፊት የምወደውን ጓደኛዬን ቀበርሁኝ:: ይህ የተሰለቸ ሀረግ የመምሰሉን ያህል ግን ግማሽ አካሌን እዚያ ሳጥን ውስጥ ተውሁት:: በሚገባ የማላውቀውንና ከእንግዲህ የማላየውን አካል::

እያንዳንዱ ቀን ልክ እንደ ሳጥን ነው- ወዳጆቼ:: ትከፈተዋለህ እውስጡ ምን እንዳለ ታያለህ:: በሳጥኑ ውስጥ ያለው ስጦታ ይሁን የሬሳ ሳጥን የምትወስነው አንተ ነህ::”

ይህ የፊልሙ ጥቂት ክፍል ሆኖ ሥርዓት አልበኝነትና ግድ የለሽነት እንዲፈጠር ምክንያት የሚሆኑትን ጉዳዮች በአጭሩ ለመመለስ ይሞክራል:: መነሻውም ጥላቻ ነው ወደ ሚል አጠቃላይ ድምዳሜ ይመራል:: በኛው ሀገር የብሔር ማንነቶች የፖለቲካ መደራጃ በመሆናቸው የተነሳ ጥቂት የማይባሉ ሰዎች የብሔር ጥላቻ እያጦዙ ነው:: ይህ ዘግናኝ ውጤት እንደሚኖረው ተገንዝቦ በሀላፊነት መንቀሳቀስ ያስፈልጋል::

ሒትለርና ጀርመን

ስለሂትለርና የያኔዋ ጀርመን ብዙ ተብሏል:: ከመሰልቸቱ የተነሳ ባላነሳው በወደድሁ:: የሆነ ሆኖ ብዙ የታሪክ ጸሐፊዎች ሂትለር ለምን አይሁዳውያኑን እንደሚጠላ ወይም የፀረ-ሴማውያን ጥላቻውን ምክንያት ለማወቅ ያልጎረጎሩት ጉድጓድ አልነበረም:: እስከ 2009 ድረስ የብዙዎቹ ድምዳሜ ያተኮረው በቪየና ስርቻዎች የልጅነት ጊዜውና አስተዳደጉና የልጅነት ትውስታዎቹ ላይ ነበር:: አንዳንዶቹ ቤተስቡን ሲከሱ ሌሎቹ ግማሽ አይሁዳዊ መሆኑን ዘግበዋል:: እናቱም በአንድ አይሁዳዊ ደካማ ዶክተር እጅ ህይወቷ እንዳለፈ የሚተርኩ መላምቶቻቸውንም ጨምረው አቅርበዋል::

ይሁንና በ2009 በRalf-George Reuth አማካኝነት ‘Hitler’s Jewish Hatred; Cliché and Reality’ በሚል ርዕስ የተጻፈው መጽሐፍ ለዚህ ክርክር እልባት ይሆናል ያላቸውን የሂትለርን የወቅቱ ግንዛቤዎች ዘርዝሯል:: ምናልባት በወቅቱ አብዛኛው የከተማ ንዑስ ከበርቴ የሚጋራው ጭፍን ጥላቻ ሂትለር አምርሮ ይዞት እንደነበረ ይተርካል:: በዚህም ምክንያት የአይሁዳውያኑ ንብረቶችና ድርጅቶች ፕሮፋይል ተደርገው ተቀምጠዋል::

ለምሳሌ በወቅቱ ከግማሽ በላይ የሚሆኑት ባንኮች የአክሲዮን ገበያዎችና የአክሲዮን አሻሻጭ ደላላዎች ጋዜጦችና መጽሔቶች እንዲሁም ከ80% በላይ የሚሆኑት የሱፕር ማርኬቶች ሰንሰለት የተያዘው በአይሁዳውያን መሆኑ ጥላቻውን የበለጠ ለማራገብ ጠቃሚ ግባቶች ሆነዋል::

ሂትለር ከዚህ ሌላ አይሁዳውያኑን ለጀርመን የአንደኛው ዓለም ጦርነት ሽንፈትና ለአይሁዳውያኑ መበልጸግ ለራሺያ አብዮት(ትሮትስኪና ሩብ አይሁዱ ሌኒን)ና ለኮሚኒስት አስተሳሰብ(ማርክስ) መፈልሰፍ ሁሉ ይኮንናቸው ነበር:: አልፎ ተርፎም በ1917 ሶቭየት ህብረት ስትመሰረት ለዓለም ሁሉ ችግሮችና ህመሞች ዋነኛ ተጠያቂዎቹ አይሁዶች ናቸው ብሎ ደመደመ::

ጸሐፊው ሩትዝ እንደሚለው ሁለት ጉዳዮች የሂትለርን አስተሳሰብ በእጅጉ ቀየሩት:: አንደኛው በድብቅና በሹክሹክታ የሚወራውን አይሁዳውያኑ የጀርመንን ኢኮኖሚንና ጀርመንን ከጀርባዋ የመውጋታቸውን አሉባልታ ተቀበለ:: በዚያ ላይ በ1919 ሙኒክ በተመሰረተው የሶቭየት ሪፐብሊክ ውስጥ አይሁዳውያኑ ከፍ ያለ ሚና መጫወታቸውን ተመለከተ:: ሂትለርና የጀርመን ብሔርተኞች ከያዙት አቋምና አስተሳሰብ በእጅጉ የሚቃረን በመሆኑም አይሁዳውያኑን እንዴት እንደሚያጠፋ ማሰብ ጀመረ ይለናል::

ምንም እንኳን እስከ ሁለተኛው የአለም ጦርነት አያውጣው እንጂ ለዚህ የዘር ወይም ጸረ-ሴሜቲክ አመለካከትና ጭፍን ጥላቻ የተጋለጠው ከልጅነቱ ጀምሮ ስላደገበትና ከሚግባባቸው ወዳጅ አይሁዳውያኑ ሳይቀር አንድ አይነት የጥላቻ ታሪክ እየሰማና እየተጸየፈ ስላደገም ነው ይለናል ሩትዝ:: ሂትለር በተለይ በሜየን ኬምፕ በጻፈው ማስታወሻው ላይ አይሁዳውያኑን ማየት እንደሚያመው ገልጿል::

ጭብጥ

የዚህ ጽሁፍ ጭብጥ በኢትዮጵያ በተለያየ ምክንያት የፍርድ መጓደልንና የፍትህ ማጣት ችግር የለም ወደ የሚል ድምዳሜ አይወስድም:: አድሎዓዊነት መጋነኑ ካልሆነ በቀር መኖሩን መካድ አይቻልም:: ለዚህ ደግሞ መንግስት ምላሽ የሚሰጥ ወይም ለማስተካከል የሚሞክር አለመሆኑም ግልጽ ነው:: አዲስ አበባ ያለው መንግስትና የስልጣን ዋልጌነት ወይም ሙስና የሁሉም የኢትዮጵያ ህዝቦችና ዜጎች ችግር ነው::

እንደማንኛውም መንግስት ከዚህ የሚጠቀሙም አሉ:: ይሁንና እኒህ የሁሉም ማህበረሰብ ክልሎች አባላት ናቸው:: ልክ እንደ ሂትለር ሁሉ የብዙሃኑን ከዚያም አልፎ አለም ዓቀፋዊውን ሁኔታና ችግር በነዚህ ምክንያት ነው የመጣብን ብሎ ወደ አንድ አቅጣጫና ማህበረሰብ ማመልከት መዘዙ የከፋ ነው:: ለሁሉም ችግር ማምለጫ ባዕዳንን ማጥፋት ነው ብሎ መደምደም ህሊና-ቢስነት ነው::

ይህ ወደ ኢትዮጵያ እንዳይመጣ ያስጨንቀኛል:: የሚንቀለቀል ጥላቻ አለ:: ሀላፊነት የሚሰማው ሰውም እየቀነሰ ነው:: የፖለቲካው ነጋዴዎችም ስለትርፋቸው እንጂ ከአፋቸው ስለሚወጣውና በየጽሁፎቻቸው ስለሚተላልፈው መልዕክት ወይም በሌሎች ላይ አደጋ ስለሚደቅነው ጉዳይ ማሰብ አይፈልጉም:: አንዳንዶቹም የጥላቻቸው እሳት የሚለበልበውን ምስኪን ማሰብ አይሹም:: ለትልልቆቹ ዝሆኖች የታሰበ ጉዳይ ዳፋው ለሳሩ እየደረሰው ነው:: መንግስትም የፖለቲካ ሰዎችም ሀላፊነት እንዲሰማችሁ ያስፈልጋል:: በቸር ያቆየን!
**********

Reagan Solomon

more recommended stories