አባይ ወልዱ:- የግንቦት 20 የድል ፍሬ መነሻ ምዕራባዊ ዞን የተከፈለው መስዋዕት ነው

የኢትዮጵያ ሕዝብ በግንቦት 20 ለተቀዳጃቸው ደማቅ የድል ፍሬዎች መነሻ በትግራይ ክልል ምእራብ ዞን የተከፈለው መስዋእትነት መሆኑን የክልሉ ርእሰ መስተዳድር አቶ አባይ ወልዱ ገለፁ፡፡

23ኛው የግንቦት 20 የድል በአል በክልል ደረጃ የህወሐት የትጥቅ ትግል ዋና ማእከል በነበረው በትግራይ ምእራባዊ ዞን ደጀና በሚባል ልዩ ስፍራ በድምቀት ተከብሯል፡፡ Abay Weldu - TPLF chairman and Tigrai president

በሰላማዊ ሰልፍና በተለያዩ ዝግጅቶች በድምቀት በተከበረው በዚሁ በአል ላይ የዞኑ አጎራባች የሆኑ የሱዳን ልኡካን ቡድን አባላትን ጨምሮ የትግራይ ክልል የሥራ ሃላፊዎች፣ የህወሐት አንጋፋ ታጋዮች፣ የድርጅቱ መሪዎች፣ ከምእራብ ዞን የተለያዩ ወረዳዎች የተውጣጡ ነዋሪዎች ተገኝተዋል፡፡

የክልሉ ርእሰ መስተዳድር አቶ አባይ ወልዱ በበዓሉ ላይ እንደተናገሩት በትግራይ ምእራባዊ ዞን ህዝቡና መሪ ድርጅቱ ህወሐት ከበርካታ ፀረ ሰላም የፖለቲካ ድርጅቶች ጋር መራራ ጦርነት አካሂደዋል፡፡

የገዢ መደቦች የትግራይን ሕዝብ በሃይል ለማንበርከክና አንድነቱ እንዲላላ መሬቱን በመቆራረስ በታትነውታል፣ በቋንቋው እንዳይማር አድርገውታል ያሉት አቶ አባይ የትግሉ መነሻ ጽናትና የተገኘው ደማቅ ድል ደግሞ የጭቆናና የግፍ ውጤት ነው ብለዋል፡፡

በመራራው የትጥቅ ትግል ወቅት ደጀና፣ቃሌማ፣ ካዛዝባንና ፀገዴ የጦርነቱ ዋና ማእከላት ሆነው ማገልገላቸውን ገልፀዋል፡፡

በጀግኖች ሰማእታት የተገነባውና ውጤታማ የሆነው እስትራቴጂ የተቀረፀውና ለኢትዮጵያ ሕዝብ ሰላም፣ዴሞክራሲና ልማት ምንጩ የዞኑ ሕዝብ እንደሆነም አቶ አባይ አስረድተዋል፡፡

የዞኑ ህዝብ ባካሄዳው ትግል ዛሬ የበርካታ የመሰረተ ልማት ተጠቃሚ መሆኑንም የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ፍስሐ በርኼ ገልጠዋል፡፡

በበአሉ ላይ የተገኙት የሱዳን ልኡካን ተወካይ በበኩላቸው ሕዝብ ባካሄደው ትግል በተገኘው ድል እየተጠቀሙ መሆናቸውን ገልፀዋል፡፡
*********
ምንጭ፡- ኢዜአ፣ ግንቦት 20፣ 2006 –  “
የግንቦት 20 የድል ፍሬ መነሻ ምእራባዊ ዞን የተከፈለው መስዋእት ነው”.

Content gathered and compiled from online and offline media by Hornaffairs staff based on relevance and interest to the Horn of Africa.