አንድነት ፓርቲ፡- ሰማያዊ ፓርቲ የልጆች ክበብ ነው-በሰልፋቸው 114 ሰው አልተገኘም

  • ሰማያዊ ፓርቲ 114 አባላት አሉት ወይ የሚለው ላይ ጥርጣሬ አለኝ፡፡
  • ፓርቲ አይደለም እኮ! ትናንሽ ልጆች የተሰበሰቡት ክበብ ነው፡፡
  • ፖለቲካ ማለት ፌስቡክ ላይ ሄደህ መለጠፍ አይደለም፡፡ የሆኑ ሰዎች ስማቸውን ሳይናገሩ ምስላችውን የአንበሳ ወይም የነብር አድርገው ይለጥፉና ዘራፍ ሊሉ ይችላሉ፡፡

ባለፈው ወር አንድነት ፓርቲ ባዘጋጀው ሰልፍ ላይ ለመሳተፍ የሄዱ የሰማያዊ ፓርቲ አባላት፣ በአንድነት ፓርቲ አመራሮች ተከልክለው ተመለሱ የሚል ዜና ተሰምቶ ነበር፡፡

የሰማያዊ ፓርቲ የህዝብ ግንኙነት ሀላፊ የሆነው ወጣት ብርሀኑ ተክለያሬድ የዕለቱ ዕለት ስለሁኔታው በፌስቡክ ባሰፈረው አስተያየት፡- ‹‹በጣም ከፍቶኛል በጣም አዝኛለሁ በፖለቲካ ህይወቴ ብዙ ነገር ደርሶብኛል እንደዛሬው ግን ከፍቶኝ አያውቅም፡፡ነፍስ ካወቅኩ ጀምሮ ያለቀስኩበት ቀን ከ2 ጊዜ አይዘልም ዛሬ ግን ጓደኞቼ እስከሚገረሙብኝ ድረስ ስቅስቅ ብዬ አልቅሻለሁ፡፡ እንደ ሌባ ከዚህ ሰልፍ ውጡ ተብለን ስንወጣ የተሰማኝ ስሜት……ግን ይሄ መንገድ የት ያደርሳል›› የሚል አስተያየት ማስፈሩ ይታወሳል፡፡

ጉዳዩን አስመልክቶ አዲስ አበባ የሚታተመው ሎሚ መጽሔት፤ ከዘለቀ ረዲ (ኢንጂነር) ጋር ቃለ-ምልልስ አድርጓል፡፡ ዘለቀ ረዲ እስካለፈው ዓመት ድረስ የአንድነት ፓርቲ የድርጅት ጉዳይ ሀላፊ የነበሩ ሲሆን፤ በአሁኑ ወቅት የፓርቲው የውጭ ጉዳይ ሀላፊ ናቸው፡፡

ቃለ-ምልልሱ የሆርን አፌይርስ አንባቢዎችን ትኩረት ይስባል ብለን ስላመንን፤ በኮምፒውተር በማስተየብ እዚህ አቅርበነዋል፡፡ [አንዳንድ የአርትኦት ስህተት የሚመስሉ የሚስተዋሉ ቢሆንም፤ በጣም እርግጠኛ ከሆንንባቸው በጣት የሚቆጠሩ ቦታዎች በቀር ዕርማት ለማድረግ አልደፈርንም]

[የሰማያዊ ፓርቲ አመራር የሰጡትን ምላሽ ለማንበብ እዚህ ጋር ይጫኑ]
*****

ሎሚ መጽሔት፡- ባለፈው ሚያዝያ 26 ያከናወናችሁት ሠልፍ ከህዝቡ ምን ዓይነት ምላሽ አገኘ?

ዘለቀ ረዲ፡- የአንድነት ሰልፍ የሚገርም ነው፤ የሚገርመው ሰዉ ፍርሀት የሚባል ነገር ትቶ ለመብት መታገል መጀመሩ ነው፡፡ አይገርመኝም የምልህ ደግሞ አንድነት ከሰራው ስራ አኳያ ያን ያህል ሠው መውጣቱ አዲስ ነገርና ድንገታዊ ነገር አይደለም፡፡ አንድነት በጣም ነው የሰራው፡፡ የአንድነት የአዲስ አበባ ዞን አባላትና የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባላት በጣም ነው የሠሩት፡፡ ከዛ በላይም ይወጣ ነበር፡፡ የኢህአዴግ ካድሬዎች በየቦታው መንገድ እየዘጉ አያስፈራሩ እንዲመለስ አድርገዋል፡፡ አንድነት በእውቀት ላይ የተመረኮዘ ፖለቲካ ነው እያካሄደ ያለው፡፡ በዛ ደረጃ ባታደንቀው ይሄ ሆኗል ባትለውም፤ በትክክል ደግሞ አንድነት የሠራውን ያህል ያላገኘበት አጋጣሚ ነው ያለው፡፡

ሎሚ መጽሔት፡- በወቅቱ የሰማያው ፓርቲ አባላት ለእናንተ ድጋፍ ለመስጠት መጥተው ነበር፡፡ በመጡበት ወቀት ‹‹ጫና ተደርጎብን እንዳንካፈል ተደርገናል›› ብለዋል፡፡ ጫና ፈጣሪ ከተባሉት የአንድነት አመራሮች መካከል ደግሞ አንዱ አንተ መሆንህ ተጠቅሶል፡፡ ለመሆኑ ጫናውን ለማድረስ ለምን አስፈለገ?

ዘለቀ ረዲ፡- እኔ በመጀመሪያ ደረጃ ሠማያዊ ፓርቲዎች መታገዝ ያለባቸው ናቸው ብዬ አምናሁ፡፡ በፓርቲ ደረጃም መብቃት ያለባቸው ናቸው፡፡ በእኔ ግምት ሰማያዊ ፓርቲ ወደ ፓርቲነት አላደገም፤ አንዳንዴ የሚሰሩት ስራ በሙሉ የልጅ ስራ ነው፡፡Zeleke Redi - Ethiopia Andinet UDJ party leadership

ከመጀመሪያ ልጀምርልህ፤ የእኛ ሀገር ትግል የሚጠይቀው ለስልጣን ሩጫና ፉክክር ሳይሆን በመጀመሪያ የነፃነት ትግሉ ነው መቅደም ያለበት፡፡ የእኛ ሀገር ህዝብ ጠንካራ የሆነ ተቃዋሚ ፓርቲ ተፈጥሮነት ይሄን አምባገነናዊ መንግስት የሚለውጥ ፓርቲ ነው የሚፈልገው፡፡ የሰማያዊ ፓርቲን ጉዳይ ስትመለከተው አንድ ሆኖ መስራት ላይ ፍላጎት የለም፡፡ ‹‹እኛ ሚኒስተር መሆን የሚችሉ 20 ሰዎች አሉን›› የሚል ነገር ነው የሚያሰሙት፡፡ 15 ሰው ሆነህ ኢህአዴግን አትለውጠውም፡፡

ወደ እውነቱ ስንመጣ፤ እነዚህ ልጆች በዚህ ዕድሜያቸው መዋሸት ከጀመሩ ፖለከቲካውን አያውቁትም ማለት ነው፡፡ ፖለቲካ ማለት ፌስቡክ ላይ ሄደህ መለጠፍ አይደለም፡፡ የሆኑ ሰዎች ስማቸውን ሳይናገሩ ምስላችውን የአንበሳ ወይም የነብር አድርገው ይለጥፉና ዘራፍ ሊሉ ይችላሉ፡፡ ማንነታቸው አይታወቅም፡፡

[ወደ ሰልፉ] ሠማያዊ ፓርቲዎች መጥተዋል፡፡ አነርሱ አንዳሉት 114 አይደሉም፤ አራት ሰዎች ናቸው የመጡት፡፡ በመጀመሪያ ደረጃ ሰማያዊ ፓርቲ 114 አባላት አሉት ወይ የሚለው ላይ ጥርጣሬ አለኝ፡፡ ባዘጋጁት ሰልፍ ላይም 114 ሰው አልተገኘም፡፡ በጎንደርም ያዘጋጁተን ሰልፍ ኣይተዋል፡፡ አዲስ አበባ ያዘጋጁትን ሰልፍ አይተነዋል፡፡ በነዛ ሰልፍ ላይ ያልታየና ያልተገኘ 114 ሰው የአንድነት ሰልፍ ላይ ተገኘ ብለው ቢሉ ውሸት ነው፡፡ ሰማያዊ ፓርቲን አሁን ከመውቀስ ይልቅ ፓርቲ እንዲሆኑ መርዳት ያስፈልጋል፡፡ ብቻችንን ሳንዋሀድ ሄደን ለውጥ እናመጣለን፤ አንዋሀድም፤ ትግሉን አጋር አናደርገውም የሚሉት የእውቀት ማነስ ነው እንጂ መዋሃድ የህዝቡ ጥያቄ መሆኑ አልገባቸውም፡፡

‹‹ሰማያዊ ፓርቲ›› የሚል ቲሸርት ለብሰው ነው የመጡት፡፡ ይሄ የልጅነት ነገር ነው፡፡ ያቺን ለብሰው ፊት ለፊት ቆመው ‹‹ሰማያዊ ፓርቲ ያዘጋጀው ሰልፍ›› ለማለት ፈልገው እንደሆነ አላውቅም፡፡ ትብብር የሚባለው ደግሞ ሁሉን ነገር አንድ ላይ ሆነህ ስትሰራ እንጂ ሰልፍ ላይ መጥተህ ቲሸርት ለብሰህ መቆምም አይደለም፡፡ ለዛውም ደግሞ እነርሱ በዋሹት መስመር አይደለም የነበረው፡፡ ሰማያዊ ፓርቲ ነን ብለው አራት ሆነው መጡ፤ ይሄ ቁጥር በስንት ቢባዛ 114 እንደሚሆን አላውቅም፡፡ አራቱ ሰዎች አራት ጥሩንባ ይዘው መጥተዋል፤ አራቱም ቲሸርት የለበሱ ናቸው፡፡እንደውም እኔ ‹‹ከነቲሸርታቸሁ ገብታችሁ ተሰለፉ›› ነው ያልኳቸው፡፡ ትብብርና በጋራ መስራት ማለት ይሄ አይደለም፣ ሆኖም እናንተ ከዚህ ትማሩበት ዘንድ ገብታችሁ ተሰለፉ ነው ያልናቸው፡፡

ከዛ ትንሽ ቆይተው የሆኑ ልጆች መጡ፤ ‹‹አንድነቶች አባረሩን›› ብለው ስለነገሯቸው ነው የመጡት፡፡ ሲመጡ እኔን አግኝተውኛል፡፡ ‹‹እናንተ ከመጣችሁ እኛ እንታሰራል ብለውናል›› አሉ፡፡ ይሄ ማለት የአንድነት አባላትን ምን ለማለት ታስቦ እንደሆነ መገንዘብ ይቻላል፡፡ የሰማያዊ ፓርቲ አባላት ከእኛ ጋር ተቀላቅለው ሲሰለፉ እኛ እልታሠራለን ማለት ነው፡፡ በመጀመረጃ ደረጃ ሰማያዊ ፓርቲ ይህንን ለማሳካት ፓርቲ መሆን አለበት፡፡ ፓርቲ ሊሆን ሲችል በጋራ መስራት ያስባል፡፡ ፓርቲ ሲሆን አንድነትን ያስባል፤ ፓርቲ ሲሆን ሀገራዊ አስተሳሰብ ይኖራቸዋል፡፡ አሁን ሀገራዊ አስታሳሰብ የላቸውም፡፡ በጋራ መስራት አይፈልጉም፤ ብቻቸውን የሚሄዱ ሰዎችን ፓርቲ ናቸው ብሎ መጥራት ከባድ ነው፡፡ ምርጫ ቦርድ ስለመዘገባቸው ፓርቲ ብሎ የመጥራት ግዴታ አለብኝ እንጂ አጠቃላይ ስመለከታቸው ግን ፓርቲ ናቸው ብዬ ለማመን ያስቸግረኛል፡፡

ይሄንንም ስልህ ግን እነርሱ ፓርቲ ለመሆን እንዲችሉ በእኛ በኩል አነሱን ማብቃት ይጠበቅብናል፡፡ እኔም ሌሎቹ ጓደኞቼም የኢትዬጲያ ህዝብም ሰማያዊ ለፓርቲነት እንዲበቃ ብንሰራ ጥሩ ይመስለኛል፡፡ ፌስቡክ ላይ ‹‹ተባረርን›› ምናምን የሚለው ነገር ለጥፈዋል፡፡ አንደኛ የሰማየዊ ፓርቲ አባላት የተለየ ነገር ግንባራቸው ላይ አልተፃፈም፡፡ አንድነት የጠራው መላው የኢትየጲያን ህዝብ ነው፡፡ ሰዎች ወደ ሰልፉ እንዲገቡለት የሚጠይቅ አንድ ትልቅ ፓርቲ የገቡትን ሰዎች ማባረር አይፈልግም፡፡ በሰልፉ ላይ የገቡትን የሰማያዊ ፓርቲ አባላት ውጡ እያልን ብናባርር፤ ‹‹ህዝቡ ለምንድነው ይሄንን ያደረጋችሁት?›› ብሎ ይጠይቀናል፡፡ ይቺ ቲሸርት ለብሶ መምጣቱ የፖለቲካ ንግድ ነው፡፡ ምንም ስለማያተርፉበት ‹‹ለብሳችሁ ግቡ›› ነበር ያልኳቸው፡፡ እንዴት ስሜቴ እንደጦፈ ግን አላውቅም፡፡ በአጠቃላይ ግን ልጆቹ ወጣቶች ስለሆኑ እነርሱን ከመጥቀም አንፃር ፓርቲ ደረጃ ብናደርሳቸው የተሻለ ነው ብዬ ነው የማስበው፡፡

ሎሚ መጽሔት፡- በአንድነትና በሰማያዊ ፓርቲ መካከል ያለመግባባት(ግፊት) አለ?

ዘለቀ ረዲ፡- ነገርኩህ እኮ! በአንድነትና በሰማያዊ ፓርቲ መካከል ፍቅርና ፀብ አለ ብለህ ለመናገር መጀመሪያ ደረጃ ሰማያዊ ወደ ፓርቲነት ማደግ አለበት፡፡ ፓርቲ አይደለም እኮ! ትናንሽ ልጆች የተሰበሰቡት ክበብ ነው፡፡ ፀብ የሚባል ነገር በምን ሊመጣ ይችላል?

አንድነት አነርሱን ለማብቃት ይፈልጋል፡፡ ፓርቲዎች እንዲሰበሰቡ ይፈልጋል፡፡ ከዚህ አንፃር፤ አንድነት በመጀመሪያ ደረጃ ከፓርቲዎች ጋር የሚጣላ ፓርቲም አይደለም፡፡ ፓርቲዎችን አሰባስቦ ትግሉን ወደፊት ለመምራት እየሠራ ያለፓርቲ ነው፡፡ ከሰማያዊ ፓርቲም ሆነ ከሌሎች ፓርቲዎች ጋር ፀብ ብሎ የሚያስበው ነገር የለም፡፡ አንድነት ፓርቲ በፓርቲዎች ብቻ ሳይሆን በግለሰቦች ደረጃም ፀብ እንዲኖር አይፈልግም፡፡

አንድነት ፓርቲን ተመልከት፤ ሀገራዊ መሰረት ያለው ነው፡፡ የትኛውም ክልል ብትሄድ አንድነት ጽ/ቤት አለው፡፡ በቀደም (እሁድ) አዲስ አበባ ከነበረው ሰልፍ ይልቅ በደቡብ ክልል ያዘጋጀነው ሰልፍ ይበልጥ ነበር፡፡ እዛ ያሉ ሰዎች፤ ሰው አንሶ ለሆነ ለአዲስ አበባ አናበድራችሁ እያሉ ይደውሉልን ነበር፡፡ እኛ ሰልፍ ባደረግንበት ደቡብ ክልል ውስጥ፤ በጣም የሚያስፈራው ተቃዋሚ መሆን ሳይሆን ኢህአዴግ መሆን ነው፡፡

ከአዲስ አበባ እስከ አፋር፣ ጋምቤላ፣ ሞያሌ፣ ሁመራ፣ አክሱም ጽ/ቤት ያለው ፓርቲ፤ አዲስ አበባ ውስጥ እንኳን ጽ/ቤት ከሌለው ፓርቲ ጋር ብንጣላ ጥቅም የለውም፡፡ አንድነት ከፓርቲዎች ጋር የሚጣላም ፓርቲ አይደለም፡፡ በዚህ ደረጃም ራሱ ማሰብም ተገቢም አይደለም፡፡ እየሰራንበት ያለነው እንደ ትግል ስልትም አድርገን እየሄድንበት ያለው መንገድ ፓርቲዎችን አንድ አድርጎ ትግሉን ወደ አንድ ማምጣት የሚችል ነው፡፡

ሎሚ መጽሔት፡- እንዲህ ያሉ ገጠመኛች ከመጪው ምርጫ አንፃር ውዝግብ አይኖራቸውም ብለህ ታስባለህ?

ዘለቀ ረዲ፡- ውዝግብ ስትል?

ሎሚ መጽሔት፡- አለመግባባቶች ሲፈጠሩ ተቃዋሚዎች አንድ ሆነው ከመስራት ይልቅ የራሳቸውን ደጋፊ ለማግኘት ሲሉ ሕብረት እየጠፋ ነው የሚሉ አስተያየቶች፤ ምርጫው ለተቃዋሚዎች ፈተና እንዲሆን አያደርጉም?

ዘለቀ ረዲ፡- በእውነቱ ውዝግብ አለ ብዬ አላምንም፡፡ በውዝግቦች መካከል ንግድ እንነግዳለን ብለው የሚያስቡ አሉ፡፡ ፌስቡክ ላይ አንደለጠፉት ማለት ነው፡፡ ይሄ ግን ህዝቡን የሚመለከት አይመስለኝም፡፡ ህዝቡ ከአንድነት ጋር በጋራ የመስራት ሁኔታ ነው የተያያዘው፤ ማደራጀት፣ ማንቃት፣ ማስተማር፣ በሰላማዊ ሰልፍ ደሞ ህዝቡ መብቱን እንዲለማመድ ማድረግ ላይ ነው ያለነው፡፡

እስካሁን አንድነት ያዘጋጃቸውን ሰልፎች አይተሀል፡፡ ለምሳሌ ባህር ዳር የተደረገው ሰልፍ ውሰድ፡፡ ያሁሉ ሰው በባዶ እግሩ ሲሄድ ነበር፡፡ ያ ሁሉ ሰው ባህርዳር ላይ እንደሚኖር የታየው በዛ ሰልፍ ነው፡፡ ሁለተኛ ደሴ ላይ አንድነት ያዘጋጀውን ሰልፍ አይተሃል፤ በሙሉ ነቅሎ ወጣ፡፡ ግማሽ በግማሽ ስራ የለም ፤ መኪና ማለፍ አይችልም ነበር ማለት ይቻል ነበር፡፡ ታቦት በሚወጣት ቀን የዛን ያህል ስው አይወጣም፡፡ ምክንያቱም በታቦት ቀን የሙስሊም፣ የፕሮቴስታንት ኃይማኖት ተከታዬች ስለማይገኙ ነው፡፡ ሰልፉ ላይ ግን ሁሉም አንድ ሆኖ ወጣ፡፡ የአዲስ አበባውን ሰልፍ ስትመለተከው ከእኛ ቢሮ ጀምሮ እስከ አድዋ አደባባይ ድረስ አልተነቃነቀም ነበር፡፡ በመቶ ሺህዎች የሚቆጠር ህዝብ ወጥቷል ማለት አንድነት ምን እየሰራ እንደሆነ የሚያሳይ ነው፡፡ ህዝቡ እየፈለገ ያለው የሚሰራ ፓርቲ ነው፡፡

ምናልባት ኢህአዴግ አንዳንድ ነገሮችን ሊፈጥር ይችላል፡፡ ለምሳሌ የአንድነትን ሰላማዊ ሰልፍ ለማደናቀፍ ያሰበው ከወር በፊት ነው፡፡ ሰማያዊ ‹‹ፓርቲዎች›› ተሸጉጠው ሰልፍ ጠርተው ነበር፡፡ ተመልከት! የሰማየዊ ፓርቲ ዕለት የወጣውን እና የኛ ግዜ የወጣውን ሕዝብ ልዩነት ተመልከተው፡፡ ሕዝቡ በደንብ አንድነትን እየተረዳ ነው የመጣው፡፡ ለጨዋታና ለፖለቲካ ትርፍ የሚሄዱትን እና በቀጥታ ለለውጥ የሚሄዱትን ፓርቲዎችን ለይቷቸዋል፤ ምንም ብዥታ የሚፈጥር ነገር የለም፡፡ ብዙ ፓርቲዎች ከአንድነት ጋር ለመቀላቀል እየሞከሩ ነው፡፡ ብዙ ትላልቅ እንደነአስራት አብርሃም ያሉ አንድነትን ተቀላቅለዋል፡፡ አንድነት ህዝባዊ መሠረትና ጠንካራ የፖለቲካ አቋም ያለው ፓርቲ መሆኑን የምንገነዘብ ይመስለኛል፡፡ ሁሉም ወደአንድነት ይመጣሉ፡፡ በ2007 ዓ.ም ምርጫ ውዝግብ አይኖርም፡፡ ህዝቡ ለምርጫ ብቻ መጥተው የፓርላማ ወንበር ለመያዝ የሚሄዱትን አይመርጣቸውም፡፡ ለኢህአዲግ ፈተና የሚሆነው የሚሰራ ፓርቲ ነው፡፡
***************

Daniel Berhane

more recommended stories