የሶማሌ ክልል ሚሊሻ በድሬደዋ ዩኒቨርስቲ ባንዲራ ተከለ

የድሬደዋ ዩኒቨርስቲ የሶማሌ ክልል መስተዳድር የባለቤትነት ጥያቄ ተነስቶበት ካለፈው ቅዳሜ ጀምሮ በሚሊሻ ተቆጣጥሮት የነበረ ሲሆን፤ የፌደራል ጉዳዮች ሚኒስትር ዶ/ር ሽፈራው ተ/ማርያም፣ የቀድሞ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ አዲሱ ለገሠ፣ የግብርና ሚኒስትሩ አቶ ተፈራ ደርበውን ጨምሮ ሌሎች የፌደራል ባለስልጣናት በጉዳዩ ጣልቃ ገብተው ማረጋጋታቸውን ምንጮች ጠቁመዋል፡፡

Dire Dawa University gate
Dire Dawa University gate

የዩኒቨርስቲው ባለቤት እኔ ነኝ የሚል ጥያቄ ያነሣው ሶማሌ ክልል ቦታውን በክልሉ ሚሊሻዎች አስከብቦ የክልሉን ባንዲራ ሰቅሎ የነበረ ሲሆን፣ የፌደራል ባለስልጣናቱ በጉዳዩ ጣልቃ መግባታቸውን ተከትሎ ክልሉ ሐሙስ እለት ሚሊሻዎቹን ከአካባቢው ቢያስወጣም የክልሉ ባንዲራ አሁንም በዩኒቨርስቲው አካባቢ እየተውለበለበ መሆኑ ተጠቁሟል፡፡

የድሬደዋ ዩኒቨርስቲ የሚገኘው በድሬደዋ አስተዳደር በኩል “ቀበሌ 02” ተብሎ የሚጠራ ሲሆን፤ የሶማሌ ክልል መስተዳድር በበኩሉ፤ ዩኒቨርስቲው አጠገብ “በሶማሌ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ቦረን ገጠር አስተዳደር” የሚል ታፔላ እንደተከለ ምንጮች ገልፀዋል፡፡

በአካባቢው የሚገኙ መኖሪያ ቤቶችም ባለሁለት ካርታ መሆናቸውን የገለፁት ነዋሪዎች፣ በሶማሌ ክልል እና በድሬደዋ ከተማ አስተዳደር ካርታ የወጣላቸው እንደሆኑ ጠቁመዋል፡፡ እንዲሁም ዩኒቨርስቲው ጀርባ የሚገኙ ገበሬዎች ባነሱት የመሬት ጥያቄ ምክንያት ያለ አጥር ክፍቱን የተቀመጠ መሆኑንም ምንጮች ገልፀዋል፡፡
********
ምንጭ፡- አዲስ አድማስ፣ ሚያዝያ 26/2006 – ርዕስ ‹‹የድሬደዋ ዩኒቨርሲቲ ባለቤትነት የሶማሌ ክልልንና የከተማዋ አስተዳደርን አወዛገበ››.

Content gathered and compiled from online and offline media by Hornaffairs staff based on relevance and interest to the Horn of Africa.

more recommended stories