የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረንስ:- “የአዲስ አበባና የኦሮምያ ጉዳይ በሁከት አይፈታም”

(በዘሪሁን ሙሉጌታ)

የአዲስ አበባ የተቀናጀ ማስተር ፕላን ተግባራዊ በሚሆንበት ጉዳይ ላይ ውይይት እየተካሄደ ባለበት በአሁኑ ወቅት አዲስ አበባ ወደ ኦሮምያ በመስፋት አጎራባች ከተሞች ወደ አዲስ አበባ ሊጠቃለሉ ነው፣ የኦሮምያ መሬት አለአግባብ ሊያዝ ነው በሚል በተለያዩ የኦሮምያ ክልል ዩኒቨርሲቲዎች የተነሳውን ተቃውሞ በተመለከተ ሁለት የኦሮሞ ብሔር ፓርቲዎች መግለጫ ሰጥተዋል።

የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረንስ (ኦፌኮ) ምክትል ሊቀመንበር አቶ ሙላቱ ገመቹ ለስንደቅ ጋዜጣ እንደገለፁት የአዲስ አበባና የኦሮምያ ጉዳይ በሁከት አይፈታም ብለዋል። ፓርቲያቸው አሁን በተማሪዎች እየተደረገ ካለው የተቃውሞ እንቅስቃሴ ጋር ምንም አይነት ግንኙነት እንደሌለውም አስረድተዋል። ፓርቲው ከሌሎች ሦስት የኦሮሞ ፓርቲዎች ጋር በመሆን ተወያይቶ አቋሙን ለህዝብ ተወካዮች ም/ቤትና ለፌዴሬሽን ም/ቤት እንዲሁም ለኦሮምያ ክልልና ለሌሎች የመንግስት አካላት ደብዳቤ በመፃፍ በሪኮመንዴ እንዲደርሳቸው መደረጉን አስታውሰው ጥያቄው በረብሻና በግርግር ሳይሆን በሰላማዊ መንገድ መቅረቡን አስታውሰዋል። ነገር ግን በአሁኑ ወቅት የዩኒቨርሲቲው የሚካሄደው ተቃውሞ ፓርቲያቸው እንደማያውቅና ይልቁኑ መንግስት ፓርቲዎቹ ላቀረቡት ጥያቄ ምላሽ እንዲሰጥ ሲሉ አሳስበዋል።

“እኛ የኦሮምያ ድንበር ተከብሮ ልማቱ ቢካሄድ ተቃውሞ የለንም። ከቻሉ ለገጣፎን ፓሪስ ያድርጉ፣ ቡራዩንም ለንደን ብትሆን ተቃውሞ የለንም። ልማቱ ሲካሄድ ግን የኦሮምያ ድንበር መከበር ይገባዋል” ያሉት አቶ ሙላቱ መንግሰት አሁን እየተነሳ ያለውን ተቃውሞ በጥንቃቄ ሊፈታው እንደሚገባም አሳስበዋል።

በሌላ በኩል የመላ ኦሮሞ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (መኦሕዴፓ) ለዝግጅት ክፍላችን በላከው መግለጫ ከሚያዝያ 17 እስከ 20 ቀን 2006 ዓ.ም ድረስ በክልሉ በሚገኙ ዩኒቨርስቲዎች የታየው የተማሪዎችና መምህራን ተቃውሞ በሰለጠነ መንገድ መፈታት እንዳለበት አሳስቧል።

ፓርቲው በላከው መግለጫ እስካሁን በአምስት ዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ የአዲስ አበባ የተቀናጀ ማስተር ፕላንን ላይ የዩኒቨርስቲ ተማሪዎች የተቃውሞ ሰልፍ ማካሄዳቸውንና በተማሪዎች ላይ ጉዳት መድረሱንም ገልጿል። በመሆኑም በተማሪዎቹ ላይ የሚወሰደው የኃይል እርምጃ ቆሞ ጉዳዩ በሰለጠነ መንገድ እንዲፈታ ሲል አሳስቧል።

የአዲስ አበባ አስተዳደርና የኦሮምያ አስተዳደር በጋራ እየመከሩበት ባለው ማስተር ፕላን ላይ በከተማዋና በዙሪያዋ ባሉ የኦሮምያ ከተሞች ያለው ልማት ለማቀናጀት የ10 እና የ25 ዓመት መሪ ፕላን ማዘጋጀቱ ይታወሳል። መሪ ፕላኑም ገና በውይይት ላይ ያለ መሆኑ ይታወቃል።
*******
ምንጭ፡- ሰንደቅ ጋዜጣ፣ ሚያዝያ 23/2006 – ርዕስ -“የአዲስ አበባና የኦሮምያ ጉዳይ በሁከት አይፈታም

Content gathered and compiled from online and offline media by Hornaffairs staff based on relevance and interest to the Horn of Africa.

more recommended stories