የአዲስ አበባ እና የኦሮምያ ልዩ ዞን የጋራ ማስተር ፕላን እያወዛገበ ነው

(አበባየሁ ገበያው እና አለማየሁ አንበሴ)

አዲስ አበባንና የኦሮሚያ ልዩ ዞን ከተሞችን በልማት ለማስተሳሰር ላለፉት ሁለት ዓመታት ጥናት ሲካሄድ የቆየ ሲሆን፤ የተቀናጀ የጋራ ልማቱን ለመተግበር የተዘጋጀው የጋራ ማስተር ፕላን ባለፈው ሳምንት በአዳማ በተካሄደ የአሰልጣኞች ስልጠና ላይ ለውይይት ቀርቦ ነበር፡፡

የአዲስ አበባንና የኦሮሚያ ልዩ ዞን ከተሞችን የ10 ዓመትና 25 ዓመት የልማት ዕቅዶች የያዘው የጋራ ማስተር ፕላን የተለያዩ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና አስተዳደራዊ ጥያቄዎችና ስጋቶችን የቀሰቀሰ ሲሆን ህገ መንግስታዊ ጥያቄም አስነስቷል፡፡

የኦሮሚያ ልዩ ዞን እስካሁን የአዲስ አበባ  ቆሻሻ መጣያ ሆኖ እንደቆየ የጠቀሱት አንድ የውይይቱ ተሳታፊ፤ አንድ ከተማ ዕቅድና ፕላን ይዞ ሲነሳ የራሱ ፖሊሲ አይኖረውም ወይ?” ሲሉ ጠይቀው “አንዱ ተቀባይ አንዱ ሰጪ ሆኖ እስከመቼ ይዘለቃል? ብለዋል፡፡ ልዩ ዞኑ በኦሮሚያ ክልል ውስጥ እንደመኖሩ ጨፌ ኦሮሚያ በዞኑ ላይ የመወሰን ስልጣን አለው የገለፁት እኚሁ ተናጋሪ፤ ጨፌ ኦሮምያ በጉዳዩ ላይ ሳይወያይና ሳይወስን ወደ ተግባር ከተገባ ስልጣን መጋፋት አይሆንም ወይ?” በማለት አስረግጠው ጠይቀዋል፡፡ ሌላው አስተያየት ሠጪ በበኩላቸው፤ “አገሪቱ የምትተዳደረው በፌደራሊዝም ስርዓት ነው፤ በመጀመሪያ ህዝቡ መወያየት ነበረበት፡፡ ጥናቱ ከተጀመረ ሁለት ዓመት ቢሆነውም ጉዳዩ ሳይነገር ቆይቶ አሁን ነው የተነሳው፡፡ ህገመንግስቱ በፖሊሲም ሆነ በፕሮጀክት ቀረፃው ላይ ህዝቡ መሳተፍ አለበት ይላል፤ ነገር ግን ተግባራዊ አልሆነም፡፡” ሲሉ ተችተዋል፡፡Addis Ababa - Oromia - old and new master plan

በመድረኩ ላይ የተሰየሙት አመራሮች በበኩላቸው፤ የጋራ ማስተር ፕላኑ ከሌሎች ያደጉ ሀገሮች የተኮረጀ መሆኑን ጠቁመው፤ እነ አሜሪካ፣ ጀርመንና ፈረንሳይ በዚህ ሁኔታ ነው ያደጉት ብለዋል፡፡ አስተያየት ሰጪዎች በበኩላቸው፤ “ሌሎች አገሮች ተሞክሮዎች መኮረጅ መልካም ቢሆንም ስንኮርጅ ከአገሪቱ ተጨባጭ ሁኔታ ጋር እየተገናዘበ መሆን እንዳለበት ገልፀዋል፡፡ “ይሄ በፊንፊኔ ዙሪያ ብቻ ያለ ኦሮሞ ጉዳይ ሳይሆን የእያንዳንዱ ኦሮሞ ጉዳይ ነው፤ ሁሉም ሊወያይበት ይገባል፡፡” ሲሉም አክለዋል፡፡  የጋራ ፕላኑ አርሶ አደሩን ለስደትና ለሥራ አጥነት ይገፋል ለሚለው የተሳታፊዎቹ አስተያየት የመድረኩ መሪዎች ሲመልሱ፤ በጉዳዩ ላይ የተሰሩ ዘላቂ ጥናቶች እንዳሉ ጠቁመው “አርሶ አደሩ ተገቢው ካሣ እየተከፈለው ተደራጅቶ እንዲሰራ እገዛ ይደረግለታል” ብለዋል፡፡ የጋራ ልማት ከጋራ ችግር ነው የሚነሣው ያሉት አወያዮቹ፤ የኦሮምያ ልዩ ዞን ልዩ ተጠቃሚ ይሆናል የሚለውን የህገመንግስቱን ድንጋጌ የተቀናጀው የጋራ ፕላን ተግባራዊ እንደሚያደርገው ተናግረዋል፡፡

የጋራ ማስተር ፕላኑን አስመልክቶ ለአዲስ አድማስ ማብራሪያ የሰጡት የፕሮጀክት ጽ/ቤቱ ም/ስራ አስኪያጅ አቶ ለአለም አዲስ የተዘጋጀው ማስተር ፕላን የኦሮምያ ልዩ ዞን ከተሞችን ወደ አዲስ አበባ እንዲጠቃለሉ የሚያደርግ ሣይሆን በመሠረተ ልማት ተሳስረው በጋራ የሚያደርጉበትን ሁኔታ የሚፈጥር ነው ብለዋል፡፡

አዲስ አበባ ውሃ፣ የማገዶ እንጨት፣ የከብት መኖ፣ የወተት አቅርቦት፣ አትክልት የመሣሰሉትን በዙሪያዋ ካሉ ከተሞች እንደምታገኝ የገለፁት አቶ ለአለም፤ በዙሪያዋ ያሉ ከተሞች በበኩላቸው የስራና የትምህርት ዕድል፣ የትራንስፖርትና ሌሎች አገልግሎቶች ከአዲስ አበባ ያገኛሉ ብለዋል፡፡

ከ25 አመት በኋላ የዘመነች ከተማን ለመፍጠር ያስችላል የተባለው ማስተር ፕላን በአዲስ አበባና ኦሮሚያ ልዩ ዞን ከተሞች መካከል የጋራ ተጠቃሚነትን ያሰፍናል ተብሏል፡፡ የኦሮሚያ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳደር አቶ አብዱላዚዝ አህመድ፤ የጋራ ማስተር ፕላኑ ሁለቱን ክልሎች በጋራ ተጠቃሚ የሚያደርግ በመሆኑ አስተዳደራቸው በበጐ እንደሚቀበለው ገልፀዋል፡፡

በሌላ በኩል የኦሮሞ ተቃዋሚ ፓርቲዎች የተቀናጀ ማስተር ፕላኑን የተቃወሙ ሲሆን የመድረክ ግንባር አባል የሆነው የኦሮሞ ፌደራላዊ ኮንግረስ ሰሞኑን ለጋዜጠኞች በሰጠው መግለጫ፤ ፕላኑ ተግባራዊ እንዳይሆን ጠይቋል፡፡ “የኦሮሚያ ልዩ ዞን ከተሞችንና ወረዳዎችን ከትልቋ ከተማ ፊንፊኔ ጋር በልማት ለማስተሳሰር በሚል ሰበብ ብቻ እየተወሰደ ያለው እርምጃ በሊዝ የሚሸጠውን የመሬት አቅርቦት ለማሟላት ነው” ብሏል – ፓርቲው፡፡

የፓርቲው ዋና ፀሃፊ አቶ በቀለ ነጋ በሰጡት ማብራሪያ፤ አዲስ አበባን ከኦሮምያ ልዩ ዞን ጋር ለማስተሳሰር የሚደረገው ሩጫ የህገ መንግስት ጥያቄ የሚያስነሳ ነው ይላሉ፡፡ “ክልሎች የራሳቸው የሆነ ዳር ድንበር አላቸው፤ የራሳቸው አስተዳደርም አላቸው፤ አዲስ አበባ ደግሞ በኦሮሚያ ስር ስላልሆነች ማስተር ፕላን መሰራት ካለበት በኦሮሚያ ክልል ባለቤትነት ነው” ሲሉ ይሞግታሉ፡፡ እቅዱ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርን የመሬት ችግር ለመፍታት እንጂ ለልማት አይደለም የሚሉት አቶ በቀለ፤ አዲስ አበባ የመሰረተ ልማት አቅርቦቶችን በስፋት የምታገኘው ከኦሮሚያ መሆኑን ጠቅሰው የኦሮሚያ ልዩ ዞን በልማት መተሳሰሩ አሁንም የተጠቃሚነት ሚዛኑን ለአዲስ አበባ እንዲያደላ የሚያደርግና በአካባቢው ያሉ ኦሮሞዎችን ጥቅም የሚነካ ነው ብለዋል፡፡

የጋራ ማስተር ፕላኑ ከኦሮሚያ መሬት ብቻ አይደለም የሚነጥቀው የሚሉት የፓርቲው ዋና ፀሐፊ፤ በአካባቢው ያሉ ኦሮሞዎች የቋንቋና የማንነት ጉዳይም ለአደጋ የሚያጋልጥ ነው ሲሉ ይከራከራሉ፡፡ “የመሬት ነጠቃ ብቻ ሳይሆን በግልፅ ህገ መንግስቱን በጣሰ መልኩ የማንነት ነጠቃም ነው” ይላሉ አቶ በቀለ፡፡ “አዲስ አበባ የኦሮምያ እምብርት ናት” የሚለው የአመታት ጥያቄ ባልተመለሰበት ሁኔታ፣ የማስፋፊያ እቅዱ ተግባራዊ ሊደረግ መሆኑ አሳሳቢ ነው ያሉት ዋና ፀሐፊው፤ አዲስ አበባ በአሁን ወቅት የመብራት፣ የውሃና የመሳሰሉ አገልግሎቶችን ከኦሮሚያ ልዩ ዞን  እንደምታገኝ ጠቅሰው፤ በአንፃሩ ከጥቂት ዓመታት በፊት አሣ ይጠመድባቸው የነበሩ አቃቂ ወንዝን የመሳሰሉ መዲናዋን የሚያቋርጡ ወንዞች፣ በከተማዋ ፍሳሾች ተመርዘው የኦሮሚያ ልዩ ዞን

ነዋሪዎች ላይ አደጋ እያስከተሉ ነው ብለዋል – የተመረዘውን ውሃ ለመጠጥ እና ለከብቶቻቸው እንዲሁም ለመስኖ እርሻቸው እንዲጠቀሙ  መገደዳቸውን በመጠቆም፡፡ “ህዝባችን በመርዝ የተበከለ ውሃ እየጠጣ ነው” ሲሉ የሚያማርሩት አቶ በቀለ፤ “የአካባቢው የኦሮሚያ ነዋሪዎች ጥቅማቸው ተነክቷል፤ የመኖር ህልውናቸውም አደጋ ላይ ወድቋል የምንለው በዚህ መነሻ ነው” ብለዋል፡፡  ከጥቂት ዓመታት በፊት በአዲስ አበባ ዙሪያ የነበሩ የገበሬ ማህበራት መሬታቸው እየተነጠቀ ያለ ቅድመ ሁኔታና ግንዛቤ መተዳደሪያቸውን ከግብርና ወደ ሌላ መስክ እንዲቀይሩ መገደዳቸውን ያስታወሱት አስተያየት ሰጪው፤ በዚህ የተነሣ ከመሬቱ የተፈናቀለው ገበሬ በችግር ላይ ነው ብለዋል፡፡ “እኛ ጥያቄያችን የአዲስ አበባ ድንበር የት ላይ ነው የሚቆመው የሚለው ነው” ያሉት አቶ በቀለ፤ መንግስትን በተለያዩ አግባቦች እንጠይቃለን ብለዋል፡፡ የመድረክ ስራ አፈፃፀም አባል አቶ ገብሩ ገ/ማርያም በበኩላቸው፤ የፌደራል ስርአቱ ሲዋቀር ሁሉም ክልሎች የማይጣስ የማይገሰስ ድንበር እንደሚኖራቸው መደንገጉን አስታውሰው፤ አሁን በመንግስት የተያዘው አቅጣጫ በቀጥታ ይህን ድንጋጌ መጣስ ነው፣ ጥሰቱ እንዲቆም መግለጫ ከማውጣት ባሻገር የምንችለውን ሁሉ እናደርጋለን ብለዋል፡፡

በሽግግር መንግስቱ ወቅት በህገመንግስት ማርቀቅ ተግባር ላይ ጉልህ ሚና የነበራቸው የቀድሞው የኢፌዲሪ ፕሬዚዳንትና የታሪክ ምሁር ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ፤ አወዛጋቢውን የአዲስ አበባ ከተማ ታሪካዊ ዳራ ያስታውሳሉ፡፡ በደርግ ጊዜ የሃገሪቱን መዲና ሰፊና ትልቅ ለማድረግ ታስቦ፣ በአራቱም ማዕዘናት የማስፋፊያ እቅዶች ነበሩ የሚሉት ዶ/ር ነጋሶ፤ ድንበሩ ናዝሬት፣ ወልቂጤ፣ አምቦ ድረስ እንዲሆን ታስቦ ነበር ይላሉ፡፡ “ደርግ ከወደቀ በኋላና በሽግግሩ ጊዜ አዲስ ማስተር ፕላን ተዘጋጅቶ አሁን ያለው ድንበር እንዲሆን ተወሰነ፣ አዲስ አበባና ኦሮሚያም በግልፅ ድንበራቸው ይካለል ተባለ” ያሉት ዶ/ር ነጋሶ፤ የተባለው የማካለል ስራ በግልፅ ስለመፈፀሙ መረጃ እንደሌላቸውና አሁን የተፈጠረው ቅሬታም የዚሁ መነሻም ሊሆን እንደሚችል ተናግረዋል፡፡ 

አዲስ አበባ በኦሮሞ ብሄርተኞች የባለቤትነት ጥያቄ የሚነሳባት ከተማ ነች የሚሉት ዶ/ር ነጋሶ፤ በሽግግሩ ወቅትም ሆነ በምርጫ 97 ጊዜ ‹በአፄ ምኒልክ በሃይል የተወረረች የኦሮሞዎች ግዛት ነች” የሚል ጉዳይ ተነስቶ ህዝበ ውሳኔ እንዲካሄድ ጥያቄ መቅረቡንና ብዙ ንትርክ ማስነሳቱን ጠቁመው፤ ሆኖም እስካሁን ጥያቄው መልስ ስለማግኘቱ እርግጠኛ አይደለሁም ብለዋል፡፡ “አሁን ላይ የሚነሳው ጥያቄ በልማት የመተሳሰር ጉዳይ ብቻ ከሆነ ቀድሞውንም ተሳስረዋል፣ የመሬት ሽሚያ ተስፋፍቶ ለገጣፎን በመሳሰሉ አካባቢዎች የኦሮሚያ አርሶ አደሮች መሬት ተወስዷል፣ አሁን እየተደረገ ያለው ያንን አጠናክሮ የሚያስቀጥል ደባ ነው” የሚሉ አስተያየቶች እየተሰነዘሩ እንደሆነ የተናገሩት ዶ/ሩ፤ በህገ መንግስቱ አንቀፅ 49 ንዑስ አንቀፅ 5 ድንጋጌ መሰረት የኦሮምያ ልዩ ጥቅም ባይጠበቅም በመሰረተ ልማት መተሳሰር የሚለው አጀንዳ ግን በሌላው አለምም የሚሰራበት በመሆኑ የሚያስኬድ ነው ብለዋል፡፡

በህገ መንግስቱ አንቀፅ 49(5) “የኦሮሚያ ክልል፣ የአገልግሎት አቅርቦት ወይም የተፈጥሮ ሃብት አጠቃቀምንና የመሳሰሉ ጉዳዮችን በተመለከተ እንዲሁም አዲስ አበባ በኦሮሚያ ክልል መሃል የሚገኝ በመሆኑ የሚነሱ ሁለቱን የሚያስተሳስሩ አስተዳደራዊ ጉዳዮችን በተመለከተ ያለው ልዩ ጥቅም ይጠበቅለታል” የሚል ድንጋጌ መስፈሩን የጠቀሱት ዶ/ር ነጋሶ፤ እስካሁን ግን ኦሮሚያ እንኳንስ ጥቅም ሊያገኝ መሬቱን እየተነጠቀ ነው ብለዋል፡፡ “የኦሮሚያ ልዩ ዞን ለግንባታ የሚውሉ ድንጋይና ጠጠር የመሳሰሉ የተፈጥሮ ሃብቶችን ጨምሮ የተለያዩ የመሰረተ ልማት አቅርቦቶችን ለአዲስ አበባ ገባሪ ሆኗል” ሲሉም ተችተዋል፡፡ በአንድ ወቅት የኦሮምያ ምክር ቤት በጉዳዩ ላይ ያለውን ቅሬታ ለፌዴሬሽን ምክር ቤት በደብዳቤ ማስታወቁን የሚያስታውሱት ዶ/ር ነጋሶ፤ ምላሽ ስለማግኘቱ ግን መረጃው እንደሌላቸው ተናግረዋል፡፡ እነዚህ ያልተመለሱ ጥያቄዎች ባሉበት ሁኔታ የተቀናጀ የጋራ ልማት ፕላን ተግባራዊ ሊደረግ መታሰቡ አግባብ አለመሆኑን ጠቅሰው፤ አሰራሩ ግን አዲስ እንዳልሆነና የሰለጠኑ ሃገራትም አስተዳደራዊ ጉዳይ ውስጥ ጣልቃ ሣይገቡ የጋራ መሰረተ ልማቶችን በጋራ አቅደው እንዲሚሰሩ ተናግረዋል፡፡

የተቀናጀ የጋራ ልማት ፕላኑ የ10 ዓመት እና የ25 ዓመት ግቦችን ያስቀመጠ ሲሆን በሁለቱ ተጎራባቾች መካከል በሚፈጠረው የመሰረተ ልማት ትስስሮች ከ10 እና ከ25 ዓመት በኋላ አዲስ አበባ የምትደርስበትን ደረጃ ይገልፃል፡፡ ከ10 ዓመት በኋላ አዲስ አበባን የአለማቀፍ ጉባኤዎችና ድርጅቶች መቀመጫ፣ ከአፍሪካ 2 ተመራጭ ከተሞች አንዷ፣ ዘላቂ አለማቀፍ የዲፕሎማቲክ መዲና እንዲሁም ከ10 ምርጥ የቱሪስት መዳረሻ አንዷ የማድረግ ዕቅድ ያስቀመጠው የጋራ ፕላኑ፤ ከ25 አመት በኋላ ደግሞ ከ5ቱ ምርጥ የቱሪስት መዳረሻ አንዷ የማድረግ ግብ አስቀምጧል፡፡

በአሁኑ ወቅት የአዲስ አበባ ክፍለ ከተሞችና ወረዳዎች አደረጃጀት ለአገልግሎት አሰጣጥ ምቹ አለመሆናቸውን የሚጠቁመው የጋራ ፕላኑ፤ ከተማዋን በ15 ክፍለ ከተሞችና በ137 ወረዳዎች ለመሸንሸን መታቀዱን ያመለክታል፡፡ የኦሮሚያ ልዩ ዞን ከተሞች የሆኑት ሰበታ፣ ሱሉልታ፣ ለገጣፎ-ለገዳዲ፣ ቡራዩ፣ ገላን-ዱከም ደግሞ ከ8-10 የሚደርሱ ወረዳዎች እንደሚኖራቸው ይገልፃል፡፡

ከ10 እና 25 ዓመታት በኋላ በሁለቱ ትስስሮሽ የትራንስፖርት አገልግሎት፣ የኢንዱስትሪ ልማት፣ የመንገድ ትስስሮሽ፣ የማዘጋጃ ቤታዊ አገልግሎት፣ የነዋሪው ኢኮኖሚ፣ የቤቶች ልማት፣ የህዝብ ቁጥሩ፣ የአካባቢ ጥበቃ እንዲሁም የህንጻ ግንባታዎች ምጣኔ ምን ላይ ሊደርስ እንደሚችል የሚጠቁም ግምታዊ ስሌት በጋራ ፕላኑ እንደተካተተ ለማወቅ ተችሏል፡፡
*********
ምንጭ፡- አዲስ አድማስ – ሚያዝያ 7፣ 2006 – ርዕስ ‹‹የአዲስ አበባና የኦሮምያ ልዩ ዞን የጋራ ማስተር ፕላን እያወዛገበ ነው››.

Content gathered and compiled from online and offline media by Hornaffairs staff based on relevance and interest to the Horn of Africa.

more recommended stories