የአዲስ አበባ አዳማ የፈጣን መንገድ ግንባታ ተጠናቀቀ

ከአስር ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ የተደረገበት የአዲስ አበባ አዳማ የፈጣን መንገድ ግንባታ ተጠናቀቀ።

የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን እንዳስታወቀው፥ ከ10 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር በላይ የወጣበት መንገዱ በዘመናዊነቱ በአገሪቱ የመጀመሪያው ነው ።

ከቻይና ኤግዚም ባንክ በተገኘ ብድርና በኢትዮጵያ መንግሥት በተያዘለት በጀት ነው ግንባታው የተካሄደው።

80 ኪሎ ሜትር የሚረዝመው የአዲስ አዳማ የፈጣን መንገድ 31 ሜትር ስፋት ሲኖረው፥ በአንድ ጊዜም በግራና በቀኝ ስድስት ተሽከርካሪዎችን ያስተናግዳል።

መንገዱ በአሁኑ ወቅት ከአዲስ አበባ  አዳማ  ለመጓዝ  የሚወስደውን ከአንድ ሰዓት  የበለጠ ጊዜን  ወደ 40  ደቂቃ  የሚያሳጥር ነው ።

በቀን እስከ 20 ሺህ ተሽከርካሪ በሚያስተናግደው ነባሩ የአዲስ አበባ  አዳማ መንገድ  ላይ የሚስተዋለው የትራፊክ መጨናነቅና  አደጋን ይህ ፈጣን  መንገድ  የሚያስቀር ይሆናል።

በመስከረም 2003 ዓ.ም. ግንባታው የተጀመረው መንገዱ  ስምንት ትልልቅ ድልድዮችን፣ ከ77 በላይ አነስተኛ ድልድዮችን፣ 43 የሚደርሱ የእግረኛና የተሽከርካሪ መተላለፊያዎች የተገነቡለት፥ 80 ኪሎ ሜትር ርዝማኔ አለው፡፡

የመንገዱን  ግንባታ  ያከናወነው የቻይና ኮሙኒኬሽን ኮንስትራክሽን ኩባንያ ነው።
*******
ምንጭ፡- ፋና – መጋቢት 27፣ 2006

Content gathered and compiled from online and offline media by Hornaffairs staff based on relevance and interest to the Horn of Africa.

more recommended stories