ቃለ-መጠይቅ| ከኢትዮጲያዊ ጌይ እና የተመሳሳይ ፆታ ግንኙነት ተከራካሪ ሮቤል ሀይሉ ጋር

በአንድ ወይም በሌላ ምክንያት – ሰሞኑን የተመሳሳይ ፆታ ግንኙነት ወይንም ጌይ(gay) ግለሰቦች ጉዳይ አጀንዳ ሆኗል፡፡ በጉዳዩ ላይ ከሁለቱም ወገን ያለውን አመለካከት እኩል ለማቅረብ የነበረን ዕቅድ አልተሳካም፡፡ መንግሰት በጌዮች ላይ ጠንካራ እርምጃ መውሰድ እንዳለበት ከሚወተውቱት ከዶ/ር ስዩም አንቶኒዮስ ጋር ያቀድነው ቃለ-መጠይቅ እሳቸው ለአንድ ሳምንት ከሀገር ውጭ በመሆናቸው ሊዘገይ ችሏል፡፡ ስለሆነም እንደተመለሱ በቪዲዮ የተደገፈ ቃለ-መጠይቅ የምናቀርብ ይሆናል፡፡ ለዛሬ ግን ኢትዯጲያን በመወከል ካቻዓምና በ‹‹MR Gay World›› ላይ ኢትዯጲያን ወክሎ ከቀረበው ሮቤል ሀይሉ ጋር ያደረግነውን ቃለ-ምልልስ አቅርበናል፡፡

ሮቤል ሀይሉ ራሱን እንደሚከተለው ይገልጻል፡፡
‹‹የተወለድኩት 1979 አዲስ አበባ ውስጥ ልዩ ስሙ ኮልፌ ተብሎ በሚጠራ አካባቢ ነው። የመጀመሪያ እና ሁለተኛ ደረጃ ትምርቴን የትከታተልኩትም እዛው ኮልፌ ውስጥ ነው። 2001 ከአዲስ አበባ ዩንቨርስቲ የመጀመሪያ ዲግሬዬን በኢንፎርሜሽን ሲስተም ይዣለሁ። ከ2003 ጀምሮ የሁለተኛ ዲግሪዬን በመማር እና በመስራት ላይ ደቡብ አፍሪካ ውስጥ እገኛለው። ከ1996 ጀምሮ በሀገር ውስጥ ከ2003 ጀምሮ ደግሞ ከሃገር ውጪ የተመሳሳይ ፆታ ግንኙነት መብት ተክራካሪ ሆኜ እስራለው። በ2004 ለመጀመሪያ ጊዜ ኢትዯጲያን እና አፍሪካን ወክዬ MR Gay World ላይ ተወዳድሪያለው። በአሁኑ ሰዓት Ethiopian LGBTI የሚል ማህበር እኔና መሰል ጋደኞቼ አቃቁመን በኢትዯጲያ የተመሳሳይ ፆታ መብት ላይ እየሰራው እገኛለው።››

ዳንኤል ብርሃነ፡
የተመሳሳይ ጾታ ግንኙነት የህይወታቸው ዘይቤ የሆኑ ሰዎች ራሳቸውን ‹‹ዜጋ›› ብለው ይጠራሉ ሲባል ሰምቻለሁ፡፡ ይሄ ትንሽ ግራ የሚያጋባ ነው፡፡ በአንፃሩ ‹‹ግብረ-ሰዶማዊ›› የሚለው ቃል ኩነናን/ ውግዘትን ያዘለ ስያሜ ነው፡፡ አንተን እና መሰል ሰዎችን ለመግለጽ ልጠቀምበት የምችለው ገለልተኛ ቃል/ስያሜ ምንድነው?

ሮቤል ሀይሉ፡
‹‹የህይወት ዘይቤ›› በሚለው አልስማም፣ ምክንያቱም ‹‹ዘይቤ›› የሚለው ቃል ‹‹በምርጫ ወይም በተለምዶ የሚተገበር ፈሊጥ ወይም ኣኳሃን ወይም መንገድ›› የሚለዉን ያመለክታል። የተመሳሳይ ፆታ የፍቅር ግንኙነትን ደግሞ በሳይንስ አንደሚጠራው የሰዉ “Sexual Orientation” እንጂ ላይፍ ስታይል(life style) ወይም ዘይቤ አይደለም።

ወደ ጥያቄዉ ስመለስ፡- እርግጥ ነው ለምን “ዜጋ” ተብለን ራሳችን አንደምንጠራ ትንሽ ግራ ሊያጋባ ይችላል። ቃሉን መጠቀም መቼ እንደተጀመረ በእነማን አንደተጀመረ በትክክል ባላውቀዉም፣ ለምን አንዳስፈለገ ግን መናገር የምችል የመስለኛል። በአማርኛ ቋንቋ እኛን የሚገልጽ ቃል ባለመኖሩ ነዉ ብዬ እገምታለሁ። ማለትም የተመሳሳይ ፆታ የፍቅር ግንኙነት ያላቸዉን ወንዶች ወይም ሴቶችን የሚገልጽ ቃል እስካሁን ከ ግብረሰዶም ወይም ከፀያፉ “ቡሽቲ” ከሚለው ቃል ዉጪ ሌላ ቃል አላውቅም። እነዚህ ቃላቶች ደግሞ አኛን አይወክሉንም። የመጀመሪያዉ መሰረቱን ሃይማኖታዊ ሀጥያትን መሰረት ያደረገ ሲሆን ጥላቻና እና ውግዘትን ከማሳየት ያለፈ እኛን በማንኛዉም መልኩ አይገልፀንም።

አዚህ ላይ የቋንቋ ተመራማሪዎች ቢረዱን ደስ ይለናል ። የሚገርመው ነገር የተቃራኒ ፆታ የፍቅር ግንኙነት ያላቸዉ ሰዎች በእንግሊዘኛዉ “Heterosexual” ለሚለው ቃል የአማርኛ ቃል አቻ ያለዉም አይመስለኝም አስካሁን በማውቀው። ለተመሳሳይ ፆታ የፍቅር ግንኙነት ፍላጎት ላለዉ ሰዉ በእንግሊዘኛ አጠራሩ “Homosexual” ለሚለው አቻ ቢኖረው ‹‹ዜጋ›› የሚለዉን ቃል መተካት ይቻላል። ለጊዜው ግን ‹‹ዜጋ›› የሚለው ቃል ብዙ ነገሮችን በአንድ ላይ የሚገልፅ ቃል ነው። ከነዚም ማህል ዋንኞቹ 1ኛ/ ኢትዮጲያዊ መሆናችን ስለሚያሳይ። 2ኛ/ ልዩ መግባቢያ ሆኖ እራሳችን ከማንኛውም አይነት ጥቃት ስለሚከላከል እና ወዘተ።

በቅርቡ አንድ ‹‹ዜጋ›› ብሎግር [addisgayscafe.wordpress.com] በጥንቱ የኢትዮጲያ ቋንቋ በግእዝ የሚተካ ቃል መኖሩን ደርሶበታል። ከወንድ ጋራ ወሲብ የሚፈፅም ወንድን የሚገልጽ “ሃዋር ብአሲ ” የሚል የግእዝ ቃል አጊንቷል። ለጊዜው ለተመሳሳይ ፆታ የፍቅር ግንኙነት ያላቸዉ ሴቶችን ባያካትትም የቋንቋዋ ተመራማሪዎች ይህንን መነሻ አድርገው ገለልተኛ አና በሳይንስ ላይ የተመሰረተ ቃል ቢያበጁ ምኞቴ ነዉ።

ዳንኤል ብርሃነ፡
ሕፃናት ወንዶችን ዒላማ ታደርጋላችሁ ይባላል፡፡ እንዲያውም አንዳንዶች በናንተ እና Pedophile በሚባሉት (ከሕፃናት ጋር ወሲብ የማድረግ ፀባይ ባላቸው ሰዎች) መሀል ልዩነት አይታያቸውም፡፡

ሮቤል ሀይሉ፡-
በጣም አመሰግናለው፡፡ ስለጥያቄው አንተ እንዳልከው ማህበረሰቡ “ፔዶፊልያ”ን(Pedophilia) እና የተመሳሳይ ፆታ ግንኙነት አንድ አድርጎ ነው የሚመለከተው። ነገር ግን “ፔዶፊልያ” ማለት ከህፃናት ጋር የግብረ ስጋ ግንኙነት የመፈፀም ባህሪ ያላቸው ሰዎች ናቸው። ከተመሳሳይ ፆታ ወይም ከተቃራኒ ፆታ ካላቸዉ ህፃናት ጋር ሊሆን ይችላል። ይሄ ደግሞ ከተመሳሳይ ፆታ ግንኙነት ጋር ምንም አይነት አንድነትም ሆነ ትስስር የለውም። ብዙ ጊዜ በዜና ወይም በተለያየ ሚዲያዎች እንደምንሰማው እድሜያቸዉ ካልደረሰ ህፆናቶች ጋር ገብረሥጋ ግንኙነት የፈፀሙ ወንዶች ታሪክ ይነገራል፣ ይህ ድርጊት ነዉ ፔዶፊልያ የሚባለው። እኛም አንደ ማንኛዉም የህብረተሰብ ክፍል በጣም የምንቃወመው እና የምናወግዘው ፀያፍ ድርጊት ነው።Robel Hailu - Ethiopian LGBT

አኔም ሆንኩ መሰል ጓደኞቼ በልጅነታችን ፆታዊ ጥቃት አልደረሰብንም። አንደማንኛዉም ሰዉ ለአቅመ አዳም ወይም ለአቅመ ሄዋን ስንደርስ ፆታዊ ፊላጎታችን ከተቃራኒ ፆታ ይልቅ ለመሰሎችችን መሆኑን እናግኝዋለን። አንደማንኛዉም ሰዉ ተመሳሳይ ፍላጎት ካለው ሰዉ ጋራ የፍቅር ግንኙነት መስርተን ኑራችንን እንኖራለን።

እዚህ ላይ ማህበረሰባችን እንዲያውቀውና እንዲገነዘብልኝ የምፈልገው ነገር የተመሳሳይ ፆታ ግንኙነት(homosexuality) ማለት የተመሳሳይ ፆታ የፍቅር ግንኙነት እንጂ የግብረ ሥጋ ግንኙንት ብቻ አለመሆኑን። ይሄ ማለት heterosexual ሰው ከተቃራኒ አቻው ጋር ፍቅር እንደሚይዘው ሁሉ ይሄኛው ደሞ የተመሳሳይ ፆታ የፍቅር ግንኙነት ነው።

ዳንኤል ብርሃነ፡
አንድ ጌይ ያልሆነ ሰው ጌይ ከሆነ ሰው ጋርወሲብ ግንኙነት ከፈፀመ እሱም/እሷም ጌይ ይሆናል/ትሆናለች፡፡ ስለሆነም ጌዮች ቁጥራቸውንየሚያበዙት(በማባበል፤ በገንዘብ ወይም በግዴታ) ወሲብ በመፈፀም ነው የሚል አስተሳሰብ አለ፡፡

ሮቤል ሀይሉ፡-
እውነት ለመናገር አንዳንዴ ከማህበረሰባችን ውስጥ የሚነሱ ጥያቄዎች በጣም የሚያሳዝኑ ህሊናን የሚጐዱ ናቸው። ሆኖም ይህ አይነት አመለካከት የተፈጠረው ሚዛናዊነት በጎደላቸው ሚዲያዎች እና በእምነት ተቋማት የተሳሳተ አስተምህሮ ነው። ማንም ሰው ከተመሳሳይ ፆታ ጋር ግንኙነት ስለፈፀመ እሱም እንዲያ ይሆናል የሚለው አስተሳሰብ መሰረት የሌለውና ተራ አሉባልታ ነው። የተመሳሳይ ፆታ ግንኙነት የፍቅር ግንኙነት ነው እንጂ የግብረ ሥጋ ግንኙነት ብቻ አይደለም። ማህበረሰባችን ሊያውቀውና ሊረዳ የሚገባው ነገር ቢኖር የተመሳሳይ ፆታ ጋር ግንኙነትን ከግብረ ሥጋ ግንኙነት ነጣጥሎ ማየት የገባዋል።

ቁጥራችን ተበራክቷል በሚለው አምለካከት ላይ ብዙም አልስማም ። አኔ አንደሚመስለኝ አሁን አሁን ትኩረት ተሰጥቶን ሲነገርና ብዙ ሲወራ ሰዎች ስለኛ ማወቅ ጀመሩ ፣ አዲስ ነገር የተፈጠረ ወይም ከሰማይ የወረደ አስመስለዉ አንጂ ቁጥራችን በዝቶ ኣይደለም። ሌላው ምንአልባት ራሳቸወን ደበቀው፣ ሰዉ አይረዳንም ብለው ሲኖሩ የነበሩ ሰዎች ብቅ ብቅ እያሉ ስለሆነም ሊሆን ይችላል። የበዛም ሆነ የቀነሰ ነገር የለም ፣ የግንዛቤ መጨመር እንጂ።

ዳንኤል ብርሃነ፡
የጌይ ሰዎችን የወሲብ ዝንባሌ በስነ-ልቦና ምክር/ህክምና (psychiatric therapy) መቀየር ይቻላል የሚሉ አሉ፡፡ ያ ትክክል ቢሆን አንተ ለመታከም ፈቃደኛ ነህ?

ሮቤል ሀይሉ፡-
ጌይ መሆን ምንም አይነት “Therapy” ወይም መድኃኒት የሚያስፈልገው በሽታ አይደለም። እራሴን ከመቀበሌ በፊት ብዙ ብዙ ጥረቶችን እና ሙከራዎችን አድርጊያለው እራሴን ለመቀየር ምክንያቱም ያደኩበት ማህበረሰብ እኔነቴን አምኜ ከመቀበል ይልቅ ሰውን መስዬ እንዴት መኖር እንዳለብኝ እያስተማረ ነው ያሳደገኝ።

“Therapy” አለ የሚሉ ሰዎች ጌይ ወይም ሌዝብያን መሆን በሽታ ነዉ ከሚል አስተሳሰብ የመነጨ ነዉ። ይሄ አመለካከት ግን በብዙ ጥናቶች እና ምርምሮች ወድቅ ሆኗል። ጌይ ወይም ሌዝብያን ምንም አይነት የአይምሮ በሽታ ወይም “mental disorder” አንዳልሆነ አንጋፋ አለም አቀፍ የስነ አይምሮ ምሁራን ማህበራት አምነዉበት ከበሽታዎች መዝገብ ተሰርዛል። ስለዚህ የተመሳሳይ ፆታ ፍቅር ግንኙነት ያላቸዉ ሰዎች ወንዶችም ሆኑ ሴቶች Therapy አያስፈልጋቸውም ። አንዲህ መሆናችን የተፈጥሮ ጉዳይ ሲሆን “Therapy” ደግሞ ተፈጥሮን የመቀየር ሃይል የለውም ሊኖረውም አይገባም።

ዳንኤል ብርሃነ፡
አንተ ራስህን በይፋ እንደጌይ አሳውቀሀል፡፡ ወደ ኢትዮጲያ መምጣት ትፈራለህ?

ሮቤል ሀይሉ፡-
በርግጥ ሀገሬ ብመለስ በጣም ደስ ይለኛል ነገር ግን ኢትዮጲያ ውስጥ ያለው ሁኔታ በጣም አስጊ ነዉ። ብዙ የጥላቻ አመለካከቶች ፣ የግድያ ዛቻዎች ደርሰዉብኛል። በማንኛዉም ድረ ገፅ ላይ ገብተህ ብትመለከት፣ ብዙ የሃገሬ ሰዎች ይገደል ብለዉ ባንድነት ይፅፋሉ ካሃገር ውጪ ያለዉ የኢትዮጲያ ማህበረሰብ ብዙ ስቃይ አድርሶብኛል። በነዚህ ምክንያት ሀገሬ መመለስ በጣም አስፈሪ ነዉ። ወደፊት ነገሮች ተቀይረው ማህብረሰቡ በተመሳሳይ ፆታ ግንኙነት ላይ ያለውን የአስተሳሰብ ልዩነት ሲያመጣ በትክክል አገሬ ገብቼ ለኰሚኒቲዬም ሆነ ለሀገሬ ብዙ ነገር የመስራት አላም አለኝ። በቅርብ በአገራችን ላይ እንደማንኛው ሰው ያለፍርሃት እና ውግዘት መኖር እንድንችል የኢትዮጲያ መንግስት ብዙ ሥራ መሥራት ይጠበቅበታል።

**********

Daniel Berhane

more recommended stories