ጥቂት ስለእንስትነት(Feminism) ጽንሰ ሀሳቦች

በዚህ ወር ለተከበረው ዓለም-አቀፍ የሴቶች ቀን ክብር ስል ስለእንስትነት(Feminism) ጽንሰ ሐሳቦችና ታሪካዊ አመጣጣቸው ማንበብ ተያይዣለሁ:: እኔ ራሴን የከተማ ሰውና ለሴቶች ክብር የምሰጥ አድርጌ አያለሁ:: በጣም የገረመኝ ታዲያ በዚህ ሰሞን ስለ እንስትነት ያነበብኩት እስከዛሬ ከማውቀው የተለየ በመሆኑ ነው:: መሠረታዊው ጽንሰ ሀሳብ የሚለው ዛሬ የጾታ (gender) ጽንሰ ሀሳብ ከሚገልፀው እምብዛም አይለይም::

የመጀመሪያዋ የእንስትነት (feminism) ጽንሰ ሀሳብ አቀንቃኝ በፓሪስ ከተማ ከቡርዣው ቤተሰብ የተወለደችውና ከ1908-1986 የኖረችው ሲሞን ዴ ቢዩቮይ ነች:: አድናቆትንና ጥልቅ ተጽዕኖ ማሳረፍ በቻለው ‘ ሁለተኛው ጾታ’ (1949) በሚለው መጽሐፏ ትታወቃለች:: ሲሞን ‘ሌላነት’ ወይም ‘ባዕድነት’ የሰው ልጅ መሰረታዊ የዕይታ ማዕቀፍ ነው ትላለች:: እንደ ሲሞን ሴትን የምንለያትና ትርጉም የምንሰጣት ከወንድ አንጻር እንጂ ከራሷ ከሴት ወይም ‘ሴትነት’ አንጻር አይደለም:: እሷ የአጋጣሚ ክስተት ነች:: ከተፈላጊው ከወንድ አንጻር ሴት አላስፈላጊ እንደሆነች አድርገን ነው የምናያት:: ወንዱ ነው ዋናው ጉዳይ:: እርሱ ፍጹም ነው:: እሷ ግን ‘ሌላ’ ወይም ‘ባዕድ’ ነች:: ሲሞን እውነቷን ነው::ወንዶቹ ቢበዛ ቢበዛ‹‹ዘ ሲግኒፊካንት አዘር›› /The Significant other/ የሚል ተቀጽላ ብንመርቅላቸው ነው::

እርግጠኛ ነኝ እንስትነት (feminism)ን አብዛኞቻችን የምናውቀው የአክራሪ እንስትነትን ጽንሰ ሀሳብ በምንረዳበት መንገድ ነው:: ይህ የወንዶች ብቻ ሳይሆን የሴቶችም አመለካከት ነው:: ለማንኛውም መሠርታዊው የእንስትነት ጽንሰ ሀሳብ የሚለው ወንድና ሴት በኢኮኖሚያዊ በማህበራዊና በፖለቲካው መስክ እኩል ይሆኑ ዘንድ መጣር ነው:: ይህ ዋነኛው(core) የእንስትነት ጽንሰ ሀሳብ ነው:: ነገር ግን በርካታ ቅጂዎች አሉት:: እያጠራን መሄዱ መልካም ሳይሆን አይቀርም::

1. ባህላዊ እንስትነት /Cultural Feminism/

ሴትና ወንድ መሰረታዊ ልዩነት አላቸው ብሎ ይቀበላል:: እንደዚሁም የሴቶች ልዩነት የተለየና ሊከበር(ሊወደስ) ይገባዋል ይላል:: የስነ አፈጣጠራቸው ልዩነት በባህሪይ ላላቸው ልዩነት አስተዋጽኦ አድርጓል ባይ ነው:: ለምሳሌ ሴቶች ከወንድ ይልቅ ደግና ቀና ናቸው ይላል:: ይህም ሴቶች የሚመሩት ዓለም ከጦርነት ነጻ ይሆናል የሚለውን አመለካካት ወልዷል:: የባህል እንስትነት ጾታዊነትን(sexism) ለማጥፋት የሴቶች የተለዩ ስጦታዎችንና ክህሎቶችን ያደንቃል:: የሴቶች መንገድና ልምድ የተሻለ ነው ብሎም ያስባል::

2. ኤኮፌምኒዝም /Eco-feminism/

የአባሆይ (Patriarchal) ፍልስፍናዎች ለሴቶች ለህጻናትና ለሌሎች በዙሪያችን ለሚገኙ ህይወት ላላቸው ነገሮች አይጠቅምም ይላል:: የአባሆይ መዋቅር ላለፉት 5000 ዓመታት የቆየ ሲሆን የሚያተኩረው በሴቶች ላይ በሚደረግ የጸና ጭቆናና ለመቆጣጠር በማይመቸው የሴቶች ‘ያልተገራ የዱር ባህሪይ’ ላይ እንደሆነ ያትታል:: በአጠቃላይ አለማችን የተሻለ ሰላም መረጋጋትና ዘለቄታዊ ልማት እንድታመጣ ሴቶች የማህበረሰብ መዋቅርና ሚና ማዕከል ወደ ሆኑበት የእማሆይ ዘመን መቀየር ግድ ይላል ብሎ ይቀበላል፡፡ የአባሆይ ዘመን ለአካባቢ ደንታ የሌለውና ከአካባቢው ኢኮሎጂ የሚገኘውን ማንኛውንም ሀብት በማውጣት/Extractive use/ መጠቀም ላይ ያተኮረ ስለሆነ በእማሆይ ዘመን ይህን ማስቀረት ይቻላል ብለው ያስባሉ::

3. ግላዊነት ወይም ሊብሪቴሪያን እንስትነት /Individualist or Libritarian/

ይህ ‘አነስተኛ’ የመንግስት ቁጥጥር ወይም ወደ አናርኮካፒታሊስትነት የቀረበ ፍልስፍና ነው:: ዋነኛው ትኩረት የግለሰቡ ነጻነት ራስን መቻል መብት አርነት ከተጽዕኖ መላቀቅና ብዙህነት ነው:: በሰፊውም ወንድን ያካትታል:: እንደዚሁም ትኩረት የሚያደርገው ሴቶችም ሆነ ወንዶች በጾታቸው ምክኒያት ስለሚደርስባቸው ተጽዕኖዎችና ተግዳሮቶች ነው::

4. ቁሳዊ እንስትነት /Material Feminism/

ይህ እንቅስቃሴ የተጀመረው በ19ኛው ክ/ዘመን መገባደጃ ላይ ነው:: የማጀት ሥራ ተጽዕኖ ለመቀነስ በሚልና በልማዳዊው የሴቶች የቤት ውስጥ ሥራዎች ለምሳሌ የምግብ ማብሰል ዓይነት ተጽዕኖዎች ላይ ያተኮረ ነው::

5. ለዘብተኛ እንስትነት /Moderate Feminism/

ይህ የእንስትነት ጽንሰ ሀሳብ በወጣት ሴቶች የተሞላና ታሪካዊ የሴቶች ጭቆናና መድልዎ አይመልከተንም ብለው የሚያስቡ ሴቶች ጥርቅም ነው:: እነዚህ ልማዳዊውና የቀድሞው የእንስትነት ሀሳቦች ከአሁኑ ጊዜ ጋር አይሄዱምና ለውጥ ያስፈልጋቸዋል:: እንስትነት/feminist/ የሚለውን እንደ ስም መቀበል ይከብዳቸዋል::

6. ብሔራዊ የሴቶች ተቋማት /National Women’s Organizations/

እኒህ ሴትና ወንድን እኩል ለማድረግ ለሴቶች የተለዩ መብቶችና ጥቅሞችን ማስጠበቅ አስፈላጊ ነው ብለው ያምናሉ:: ወንዶች ለሴቶች ጥቅሞች ተግዳሮቶች መሆን የለባቸውም ይላል:: ሴቶችን ከወንድ እኩል ለማድረግ ሴቶች ላይ ማተኮርና ለሴቶች የተለየ ጥቅም መቆም ያስፈልጋል ይላሉ::

7. ጽንፈኛ እንስትነት /Radical Feminism/

በርግጥ ይህ ጽንሰ ሀሳብ ለብዙዎቹ የእንስትነት ጽንሰ ሀሳቦች መራቢያ ሆኖ አገልግሏል::ተጽዕኖ ፈጣሪ የነበረባቸው አመታት ከ1967-75 ያሉት አመታት ናቸው:: በአሁን ዘመን ያን ያህል ዓለም አቀፍ ተቀባይነት የለውም:: ይሁንና ይህ ጽንሰ ሀሳብ የሴቶች ጭቆና በጣም መሰረታዊው ጭቆና ነው ብሎ ይረዳል:: እንደዚሁም የዘር የባህልና የምጣኔ ሀብት ድንበሮችን አልፎ ይተገበራል:: በማህበራዊ ለውጥ በተለይም በአብዮት ልኬት ያለ ለውጥን ይናፍቃል ይላል::

በተለይ በስነ ፍጥረት ላይ በተመሰረተ ባህርይና በባህል ተጽዕኖ ላይ በተመሰረተ ባህርይ መካከል ልዩነት ለመፍጠር ይሞክራል::

8. የአማዞን እንስትነት /Amazon Feminism/

የአማዞን እንስትነት የተክለ ሰውነት(የአካል) እኩልነትን ይቀበላል:: ስለዚህም የጾታ ሚና ነቀፌታዎችንና መድሎዎችን ይቃወማል:: እንደዚሁም ሴቶችንና ሴትነትን ገለልተኛ ደካማና አቅመ ቢስ አድርጎ የሚስላቸውን ትርክትና አመለካከት ይቃወማል::

9. ተነጣይ እንስትነት /Separatist Feminism/

ብዙ ጊዜ እኒህ በስህተት ሌዝቢያን እንደሆኑ ተደርጎ ይታሰባል:: ነገር ግን እኒህ ሴት ከወንድ አንዳንዴ ለእስከነአካቴው አንዳንዴም በጊዜያዊነት እንድትነጠል ያበረታታሉ:: ሴት ከወንድ ተነጥላ እራሷን ያለወንድ ማየት ለግል ዕድገትና አቅም ግንባታም ያስፈልጋል ይላሉ::

በእኛ ሀገር ሴቶች ብቻም ሳይሆን ወንዶችም ከዚህ የትኛው ላይ እንደምናተኩርና እንደምንደግፍ ግልጽ አይደለም:: ሌላው ቀርቶ የሴቶች ጉዳይ የኔ ጉዳይ ነው የሚል ስልጡን ወንድ ጥቂት ነው:: ሴቶችን ማልማት ግማሽ ህብረተሰባችንን ማልማት ነው:: በሰው ሀብት ልማት ዝቅተኛ የሆነችው ሀገራችን የተሻለ ደረጃ እንድትደርስ የሴቶቻችንን ሀብትነት በአብዛኛው ማህበረሰባችን ግማሽና ከግማሽ በላይ አስተዋጽኦ እንዳላቸው ተገንዝበን ልንከባከባቸው ይገባል::

*********

Reagan Solomon

more recommended stories