ዓለማየሁ አቶምሳ – ኪራይ ሰብሳቢነትን አምርሮ የታገለና ያታገለ

(አስቴር ኤልያስ)

ከአቶ አቶምሳ ሚጃ እና ከወይዘሮ አየለች ብሩ በምሥራቅ ወለጋ ዞን – ቢሎ ቦሼ ወረዳ – 1961 ዓ.ም የተወለዱት ታጋይአቶ ዓለማየሁ አቶምሳ በ1981 ዓ.ም ማለትም ልክ በ20 ዓመት ዕድሜያቸው ላይ ሳሉ ነበር የደርግን ሥርዓት ለመገርሰስ ሲካሄድ የነበረውን ትግል የተቀላቀሉት። የደርግ ሥርዓት ከተገረሰሰ በኋላም ትግላቸውን የቀጠሉት ታጋይ ዓለማየሁ፣ ዴሞክራሲያዊ አንድነት እንዳይገነባ ቆርጠው የተነሱትን ትምክህተኞች በመታገል ታላቅ መስዋዕትነት ከፍለዋል። በተለይም የኪራይ ሰብሳቢነት ከምንጩ እንዲደርቅ ታግሎ በማታገሉ ሒደት ከፍተኛ ሚና የተጫወቱ ከመሆናቸውም በተጨማሪ በክልሉ የልማት፣ የዴሞክራሲ፣ የሰላምና የመልካም አስተዳደር ዕቅዶች እንዲሳኩ እልህ አስጨራሽ ትግል በማድረግ የጎላ ሚና ነበራቸው።

ታጋይ ዓለማየሁ «ትክክለኛ ተግባር የትክክለኛ አስተሳሰብ ውጤት ነው» በሚለው የጸና ዕምነታቸው ይታወቃሉ። የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ርዕሰ መስተዳድርና የኦህዴድ ሊቀመንበር የነበሩት እኚህ ታጋይ የክልሉን ሕዝብ ከድህነትና ኋላ ቀርነት ለማላቀቅ የተነደፈውን ልማታዊና ዴሞክራሲያዊ አቅጣጫ ተግባራዊ በማድረጉ በኩል ተጨባጭ ውጤት ያስመዘገቡ በሳል መሪ ነበሩ።Alemayehu Atomsa

ላለፉት 24 ዓመታት ለኦሮሚያ ክልል ብሎም ለአገሪቱ ሕዝብ በቁርጠኝነት ሲታገሉ የቆዩት አቶ ዓለማየሁ፣ በተወለዱ በ45 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል። ዜና ዕረፍታቸው የተሰማበት የካቲት 27 ቀን 2006 ዓ.ም የክልሉን ብሎም የአገሪቱን ሕዝብ ልብ የሚሰብር ታላቅ ኀዘንና ድንጋጤ ፈጥሯል።

የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ባስተላለፈው የኀዘን መግለጫ እንዳመለከተው፤ ታጋይ ዓለማየሁ አንድም ቀን ተፃራሪ ከሆኑ አመለካከቶችና ተግባራት ጋር ንክኪ ሳይኖራቸውና «ታከተኝ» ሳይሉ ሙሉ ሕይወታቸውን ለድርጅታቸውና ለሕዝቡ አውለው አልፈዋል። ለትግሉ በከፈሉት መስዋዕትነት፣ ባሳዩት የዓላማ ፅናትና በሰጡት በሳል አመራር በመላው የኦህዴድ አባላትና የኦሮሞ ሕዝብ ዘንድ ታላቅ ይሁንታና ተሰሚነት ያላቸው መሪ ነበሩ። ከራሳቸውና ከቤተሰቦቻቸው ጉዳይ ይልቅ መላ ጊዜያቸውን ለድርጅትና ለመንግሥት ሥራ በመስጠታቸውም ይታወቃሉ።

አቶ ዓለማየሁ ከነሐሴ 2002 ዓ.ም ጀምሮ የኦህዴድ ሊቀመንበር፣ ከመስከረም 2003 ዓ.ም ጀምሮ ደግሞ የክክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ሆነው አገልግለዋል። ቀደም ሲልም በዞን አስተዳዳሪነት የሠሩ ሲሆን፣ ከ1988 እስከ 1994 ዓ.ም ደግሞ የክልሉ ፀጥታ ዘርፍ ኃላፊና የኦህዴድ የፖለቲካ ዘርፍ ኃላፊ በመሆን በቁርጠኝነት ማገልገላቸውን መግለጫው ያመለክታል። ከ1998 ዓ.ም እስከ 2002 ዓ.ም ባሉት ጊዜያት ደግሞ የኢትዮጵያ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ዋና ሥራ አስኪያጅ እንዲሁም የኦሮሚያ ክልል የመንግሥት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ኃላፊ በመሆን አገልግለዋል።

በድርጅት ውሳኔ የትምህርት ዕድል ተሰጥቷቸው በ1998 በሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ በሕግ ትምህርት የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን ማግኘታችውን መግለጫው ያመለክታል። በ2002 ዓ.ም ደግሞ ከቻይና ቤይጂንግ ዩኒቨርሲቲ በሕዝብ አስተዳደር ሁለተኛ ዲግሪያቸውን መቀበላቸውም ነው የተጠቀሰው።

መግለጫው እንዳመለከተው፤ በአቶ ዓለማየሁ አቶምሳ ህልፈተ ሕይወት ክልሉ ፅኑ ኀዘን ተሰምቶታል። ይሁንና የሕዝብ አገልጋይነታቸውን እንደጠበቁ ለሕዝብ መልካም ሠርተው በማለፋቸው የክልሉ መንግሥትና ሕዝብ ሊፅናና ይገባዋል።

በሌላም በኩልም የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ዶክተር ሙላቱ ተሾመ በአቶ አለማየሁ አቶምሳ ሞት የተሰማቸውን ኀዝን ገልጸው፣ የኢፌዴሪ መንግሥት ለክልሉ ሕዝብ መፅናናትና ለቤተሰቦቻቻው ብርታትን እንደሚመኝ ተናግረዋል። ፕሬዚዳንቱ ለኢትዮጵያ ሬዲዮና ቴሌቪዥን እንደገለጹት፣ አቶ ዓለማየሁ በሕይወት በነበሩበት ዘመን በተለያዩ የመንግሥት የሥራ ኃላፊነት ቦታዎች በመመደብ የተጣለባቸውን ኃላፊነት በትጋትና በቅንነት እንዲሁም በታማኝነት ተወጥተዋል። ለክልሉ ሕዝብና ለአገሪቱ የሰላምና የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ላበረከቱት አስተዋጽኦ በራሳቸውና በመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ስም ያላቸውን ልባዊ አድናቆት ገልጸዋል።

በተመሳሳይም የፌዴሬሽን ምክር ቤት የአቶ አለማየሁ አቶምሳ ከዚህ ዓለም በሞት መለየት ለአገራችን ሕዝቦች በተለይም ለክልሉ ሕዝብ ታላቅ ኀዘን መሆኑ ገልጿል።

ምክር ቤቱ ለዝግጅት ክፍላችን በላከው መግለጫ እንዳስታወቀው፣የፌዴሬሽን ምክር ቤት አባልና የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ፕሬዚዳት የነበሩት አቶ አለማየሁ አቶምሳ ከዚህ ዓለም በሞት በመለየታቸው ምክር ቤቱ ጥልቅ ኀዘን ተሰምቶታል። ምክር ቤቱ ለቤተሰቦቻቸውና ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ መፅናናትንም ተመኝቷል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ የኢፌዴሪ የመንግሥት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ርዕሰ መስተዳድር በአቶ አለማየሁ አቶምሳ ድንገተኛ ህልፈተ ሕይወት ከፍተኛ መደናገጥና ኀዘን ማስከተሉን ገልጿል። ጽህፈት ቤቱ ለዝግጅት ክፍላችን በላከው መግለጫ እንደገለጸው፤ በትግሉ ሂደት ዴሞክራሲያዊና ልማታዊ መስመር በጽናት ይዘው ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይሉ በሕመም ላይ እንኳን እያሉ የሕዝብን ጥቅም ለማረጋገጥ ቀን ከሌት የታገሉ ተወዳጅ ቆራጥና በሳል መሪ ነበሩ።

የኢትዮጵያ ሕዝብና መንግሥት በአቶ አለማየሁ አቶምሳ ህልፈተ ሕይወት የተሰማቸውን ጥልቅ ኀዘን ጽሕፈት ቤቱ አመልክቶ ለቤተሰቦቻቸው ለኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥትና ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝቦች እንዲሁም ለድርጅታቸውና ለትግል አጋሮቻቸው ሁሉ መጽናናትን ተመኝቷል። የቀብር ሥነ ሥርዓት አፈጻጸሙን የሚመለከቱ መረጃዎችንም ከክልሉ መንግሥት ጋር በመተባበር በተከታታይ ለሕዝብ ይፋ እንደሚያደርግም አስታውቋል።

ታጋይ ዓለማየሁ አቶምሳ ካለፉት ሁለት ዓመታት ወዲህ አልፎ አልፎ የጤና እክል ያጋጥማቸው ስለነበር ሕክምናቸውን ሲከታተሉ መቆየታቸው ይታወሳል። ይሁንና የተጣለባቸውን ኃላፊነት በተሟላ ሁኔታ ሲተገብሩ የቆዩ ሲሆን፣ በዚሁ ባለንበት የካቲት ወር ውስጥ ግን የድርጅት ሊቀመንበርነታቸውን በፈቃዳቸው ለኦህዴድ ሥራ አስፈፃሚና ማዕከላዊ ኮሚቴ አቅርበው ተቀባይነትም ማግኘቱ ይታወቃል።

ከታጋይ ዓለማየሁ ጋር በ2001 ዓ.ም በቻይና ቤይጂንግ ዩኒቨርሲቲ ሁለተኛ ዲግሪያቸውን አብረዋቸው የተማሩት የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት የፕሮዳክሽን መምሪያ ሥራ አስኪያጅ አቶ ወንድምኩን አላዩ፣ ገና የ45 ዓመት ሰው እንደመሆናቸው ብዙ መሥራት በሚችሉበት ጊዜያቸው ሕይወታቸው ማለፉ የሚያስቆጭ መሆኑን ነው ያመለክቱት።

«በቆይታችን ወቅት ትጋታቸው ያስገርመኝ ነበር። በቀን ቢያንስ ከስምንት ሰዓት በላይ ያነብቡ ነበር። በተለይም ለወደፊቱ ለአገር ጉዳይ ይጠቅማሉ ያሏቸውን መጻሕፍት ተከታትለው ይገዛሉ። በተለይ ሁሌ ያስገርመኝ የነበረው ሥነ ምግባራቸው ሲሆን፣ እኔም በቆይታዬ ከእርሳቸው ብዙ መልካም ተግባራትን መማር ችያለሁ። እንዲህ ዓይነት ታላቅና በመልካም ሥነ ምግባር የታነፀን ሰው ማጣት ሕመም ነው። አንድ የሚቆጨኝ ነገር ቢኖር በወጣትነት የዕድሜ ዘመናቸው እንዲሁም በቁርጠኝነታቸው ብዙ ማገልገል የሚችሉ ታላቅ ሰው በማጣታችን ነው» ይላሉ።

የአቶ አለማየሁ አስከሬን ትናንት ማታ ቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ሲደርስ አቀባበል ተደርጎለታል። የቀብር ሥነ ሥርዓቱም ቅዳሜ የካቲት 29 ቀን 2006ዓ.ም.በቅድስት ሥላሴ ቤተ ክርስቲያን እንደሚፈጸምና አስከሬኑም በወታደራዊ ሥነ ሥርዓት ታጅቦ በክብር እንደሚያርፍ የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አብዱላዚዝ መሐመድ በተለይ ከጋዜጣው ሪፖርተር ጋር ባደረጉት የስልክ ቃለምልልስ ገልጸዋል። የፀሎት ሥነ ሥርዓትና የአበባ ጉንጉን የማኖር ሥርዓት እንደሚካሄድ አስታውቀዋል።

እንደምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ ገለጻ፤ ከቀብር ሥነ ሥርዓቱ ቀደም ብሎ በመኖሪያ ቤታቸው የክልሉን የአመራር አካላት ጨምሮ የፌዴራል እና የሌሎች ክልሎች ርዕሰ መስተዳድሮች በተገኙበት ለአስከሬኑ የስንብት ሥነ ሥርዓት ይደረግለታል። በቀጣይም በአዲስ አበባ ስታዲየም እንዲሁ የክልሉ እና የፌዴራል ከፍተኛ የመንግሥት አመራር አካላት እንዲሁም የክልሉና የአዲስ አበባ ነዋሪዎች በተገኙበት የስንብት ሥነ ሥርዓት ይደረጋል። በአዲስ አበባ ስታዲየም በሚደረገው መርሐ ግብር የታጋይ አለማየሁ አቶምሳ የሕይወትና የትግል ታሪክ የሚመለከት መርሐ ግብር እንደሚካሄድ ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ ተናግረዋል። የተለያዩ የኀዘን መግለጫዎችም እንደሚተላለፉ ነው ያብራሩት።

**********

ምንጭ፡- አዲስ ዘመን የካቲት  28/2006፣ ርዕስ ‹‹ኪራይ ሰብሳቢነትን አምርሮ የታገለና ያታገለ››፣ በአስቴር ኤልያስ

 

Content gathered and compiled from online and offline media by Hornaffairs staff based on relevance and interest to the Horn of Africa.

more recommended stories