ማንነቴ ማነው? የብሔር ማንነት አምባገነንነት

በደርግም፣ በህወሃትም፣ በኢህአፓም፣ በኢዲህም፣ ….ተሰልፈው ‘ለህዝቤና ለሃገሬ የወደፊት መፃኢ እድል ይጠቅማል’ ተብለው በተሰለፉበትና ባመኑበት አላስፈላጊ መተላለቅ ሰላባ ለሆኑ ምስኪን የሃገሪትዋ ልጆች የሰላም እረፍት ይሁንላቸው። አሁን እኛ ያለንበትን ትግልም ሆነ የዘበናይ ህይወት ሳያዩ ቤተሰባቸውን በትነው በየገደሉና በየጎዳናው ቀርተዋልና።

ይህ አሁን በየመድረኩ የምንሰበከው ‘የብሔር ብሄረሰብ ብቻ ማንነት’ ፍልስምና ግን እነዚህ ሰማእታት ከታገሉለትና ከወደቁለት በተለየ አይን ያወጣ የመብት ረገጣነት እየተቀየረ ያለ ይመስለኛል። በተለይ በግል ከዚህ በፊት የማውቃቸው ቅን አሳቢዎች በዚህ ማህበራዊ መድረክ የሚያንፀባርቁት በብሄር ብሄረሰብ ሥም የማንነትን መብት ጭፍለቃ ሳነብ ስጋቴ እየናረ ነው። በዚህች ሃገር ብሔር ብሔረሰቦች መብታቸው የተሟላ አልነበረም። ማንነታቸውም (ባህላቸው፣ ቋንቋቸው …) ሙሉ በሙሉ በእኩልነት የተከበረና እኩል የመበልፀግ እድል አላገኘም፤ ይህ ማንነታቸው አልፎ አልፎም በሚያስተዳድራቸው አካል ሳይቀር መናናቁና መረሳቱ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ባህልቸው እንዲደበዝዝ ማድረጉ አይቀሬ ነው። አሁን የብሔር ብሔረሰቦች መብት በህግ ጭምር ተረጋገጠ። ከዚህ በላይ አልፎ ግን ኢትዮጵያ በነበራት ከሦስት ትውልዶች በላይ ጊዜ በፈጀ የጦርነት፣ የአገዛዝ፣ የረሃብ፣ የመስፋፋት፣ የስደት፣ የወረራ … ታሪኩዋ የተነሳ “የብሔር ማንነቴ ተደበላልቋልና የዚህ ታሪክ ማንነቴ ነው እኔን የሚገልፀኝ” የሚለውን ህዝብ ላይ ይህንን ያህል ማንነቱን የሚያንጓጥጥና ህልውናውን እስከመኖሩም የሚክድ ‘ኢትዮጵያዊ ማንነት የለም’ የሽብር ጦርነት መክፈት የነዛን ሰማእታት ደም እንደመምጠጥ ነው የሚቆጠረው፤ የተዋደቁት የራሳቸውን የብሔር ማንነት ለማስከበር እንጂ የውህድ ማንነትን ለመጨፍለቅ ነው ብዬ ስለማላምን ነው። የብሔራችሁን ማንነት የምታስከብሩት ወይንም የተከበረላችሁ የሚመስልላችሁ የግድ የኢትዮጵያ ታሪክ የፈጠረውን የውህድ ብሔር ማንነትን በማንጓጠጥ፣ በመፈረጅ፣ ሽብር በመንዛት … ብቻ ነው እንዴ?

እንነጋገር ከተባለ ከፍረጃ ሳጥን ወጥተን ፊት ለፊት እንነጋገር። እኔ አሁን የተዋቀሩት የማንነት የፖለቲካ ቡድኖች መብት ባከብርም አባል አይደለሁም። በአማርኛ አፌን ስለፈታሁና ኦርቶዶክስ ክርስትናን ከ40 ቀን እድሜዬ ጀምሮ ስለተከተልኩ ‘አማራ ነህ’ ብሎ ማንነቴን የሚወስን የዘመኑ ዘመነኛ መሰል አምባገነንነትንም አልቀበልም። ስንትና ስንት ብሄረሰብንና አፍ መፍቻ ቋንቋን በአንድ ክልል ከልሎ ‘ያንተ ብሄርና አፍ መፍቻ ቋንቋህ እኔ አውቄልሃለሁና በዚህ ብሄር ተጠራ: በዚህ ቋንቋ ተዳኝ: በዚህ ቋምቋም ተማር፤ ምክንያቱም የታገልንልህ እና የሞትንልህ መብትህ ነውና’ የሚል የአሻንጉሊት ጨዋታ ለሚነግረኝም መሳቅ አይሆንልኝም።

ይህንን ውህድ ማንነት ቀደም ሲል ከመዐህድ፣ ከነፍጠኛ፣ ከትምክህተኛ፣ … አሁን ደግሞ ከሰማያዊ፣ ከአንድነት … ጋር በግድ በመፈረጅ የሚከበር የብሔር ማንነት ሊገባኝ አይችልም። በቃ ከነጠላ ብሔር ብሔረሰብ እኩል ውህድ የብሔር ማንነትም የዚህች ሃገር አንዱ የውርስ ማንነት ነው፤ እኩል የጠራ ማንነት ነው፤ ለነጠላ ብሄር ብሄረሰብ ማንነቶች ጌጣቸው እንጂ ስጋታቸው አይደለም፤ የነጠላ ብሄር ብሄረሰብ ማንነት የጣት ቀለበታቸው እንጂ ፈንጂያቸው አይደለም። ይህ ማንነት እራሱን ኢትዮጵያዊ ብሎ መሰየሙ ከላይ ያነሳሁዋቸው እና ወደታችም አሁን በማነሳቸው ወደንም ይሁን ተገደን ያለፍንባቸው ብሔራዊ ብቻ ሳይሆን አለማቀፋዊ የኢትዮጵያዊነት ጫናዎች መገልጫ በመሆኑ እንጂ ምንም ሌላ የሚያስፈርጅ አመክንዮ አታገኙም። እኔ በአማርኛ አፌን እንድፈታ፣ ከሃገሪቱዋ ሁለትና ሶስት ብሔር ትዳር እንድወለድ፣ እዚህ ጫፍ ወደዛ ጫፍ እንድንቀሳቀስና ይህንን ውህድ ማንነት እንድላበስ የምትሉዋቸውና የፈረጃችሗቸው ቡድኖች ያደረጉት አስተዋይፆ ኢምንት ነው። እናንተም የመጀመሪያ ማንነታችሁ ነጠላው በሔራችሁ እንደሆነላችሁ ሁሉ ማንነቴ መሰረቱ ወደዳችሁም ጠላችሁም የብዙ ዘመን የኢትዮጵያ ያለፈ ታሪክ ነው። ወደውም ይሁን ተገደው ቅድመ አያቶቼ የዛ ታሪክ ዋና ተሳታፊ በመሆናቸው ማንነቴን ፈጥረዋልና ለውህድ ማንነቴ ስያሜ ‘ኢትዮጵያዊ’ ማለቴ ልክ ነው፤ ከብሄር ማንነት እኩል እውቅና፣ እኩል ቦታ እና እኩል ክብር እኩል የማንነት መታወቂያ ካርድ ሊሰጠው ግድ ይላል፤ ይህ ውህድ ማንነት ያለቋንቋው ሊዳኝም ሆነ ሊማር አይገባውምም፤ ከሶስት ትውልድ በፊት ለተፈፀመ ጥፋትም ቂም መመለሻ አድርጎ ማንነቴን ማቅረብ የዘር ማጠፋት ሙከራ ነው።

የኢትዮጵያ ታሪክ ደግሞ አንድ ገዢ ወይንም አንድ ብሔር ወይንም ኢትዮጵያኖች ብቻ የፈጠሩት አይደለም። ከሁሉም ብሔሮች አሻራ በላይ አለማቀፋዊ የዘመናት የተፅዕኖ በትርም አለበት። ኦሮሞዎች ግዛታቸውን ለማስፋፋት ወደሰሜን እየተመሙ ባይማርኩና ጃላ (ወዳጅ ወይንም ኦሮሞ) ባያደርጉ፣ የግራኝ አገዛዝ እስልምናን ወደሰሜን በኃይል ባያስፋፋ፣ ድርቅ ህዝብን ከአንድ ጎጥ ወደሌላ ባያንቀሳቅስ፣ የአውሮፓ መንግስታት የሶስትዮሽ ስምምነት አድርገው የአፍሪካን ቀንድ ባይቀራመቱ ኖሮ … የእኔ ውህድና ኢትዮጵያዊ ማንነት ላይፈጠር ይችል ነበር። ቅድሚያ ማንነቴም እንደናንተው ብሄሬ ይሆንና ኢትዮጵያዊነት የዜግነት ማንነቴም [ብቻ] በሆነ ነበር።

ከላይ በገለፅኳቸው በቂ ምክንያቶች የእኔ ማንነቴም ዜግነቴም በቃ ኢትዮጵያዊ ነው። ኢትዮጵያ የምትባል ሃገር ካንገፈገፋችሁ ያንን ችግር መነጋገር አግባብም ልክም ነው። የብዙዎችንም የኢትዮጵያዊ ዜግነት መስፈርት ጥያቄ እረዳለሁ፤ በመነጋገር የሚፈታም ይመስለኛል። ኢትዮጵያዊ የሚባል ማንነትና ታሪክ ግን ለመሰረዝ መሞከር እራስን ከማጥፋት ጋር ይመሳሰልብኛል።

ይህን ውህድ ኢትዮጵያዊ ማንነትን ስትክድና ስታንጓጥጥ የራስህንም የብሔር ማንነት እየካድክና እያንጓጠጥክ  መሆኑን ቆም ብሎ ማሰቡ ብልህነት መሰለኝ። ውህድ ማንነቴ እኮ ያንተ ማንነት አንድ አካል ነው። ኢትዮጵያዊ ማንነት ያሰኘኝም እኮ ውህዱ የኢትዮጵያ ታሪክ ስለወለደኝ ነው። ኦሮሞና አማራን፣ አማራና ትግሬን …  ያጋባውና ልጆች አብረው እንዲያፈሩ ያደረጋቸው “የአማራው አምባገነንነት” ብቻ አይደለም፤ ድርቁም፣ ወረራውም፣ የኦሮሞው አምባገነንነትም፣ የኢስላም መሪ አምባገነንነትም፣ የክርስትና መሪ አምባገነንነትም (በዘመኑ የነበሩ አንዳንድ የኃይማኖቶቹ መሪዎች እንጂ ኃይማኖቶቹ ሰላምና እኩልነትን ያዘሉ ነበሩና) … ሁሉም የድርሻቸውን አበርክተው ነው። በዚህ የኢትዮጵያ ታሪክ አንዱን ብሔር ከሌላው ማግነን፣ አንዱን ማንኳሰስ የብሔረሰቦቹን ታሪክና ባህል ማናናቅ እንጂ ማክበር አይመስለኝም፤ ማን ከማን ያንስና። ታሪክ ሰሪ እንጂ የሌላውን ታሪክ ነጋሪ ብቻ ሆኖ ለዘመናት ያሳለፈ ብሄር ባለቤት ነን እንዴ? የድርቅ ስደት ብሄር ለይቶ ነበር እንዴ? አውሮፓውያኖችና ግብፆች የወረሩን ብሄር ለይተው ነው እንዴ? ይህንን ስል ግን ብሄሮች ባለፈው ታሪካቸው ሙሉ መብት ነበራቸው ብዬ እየተከራከርኩ አይደለም። እንኳን ባለፈው አሁንም ለሙሉ መብት ብዙ መስራት ይጠበቅብናልና፤ ከያንዳንዱ ብሄር በተፅእኖም ሆነ ባለማወቅ ተደብቀው ያሉና ለአለም የሚጠቅሙ የብሄር ብሄረሰቦች እሤት እንዳለን አውቃለሁና።

ምናልባትም የአውሮፓዎቹ የሶስትዮሽ የቅርምት ስምምነት ወይንም የግፆቹ ወረራ ተሳክቶ ቢሆን ኖሮ እንኳን የእኔ ውህድ ማንነት ሊፈጠር ቀርቶ የኦሮሞና የአማራው ብሄር እራሱ በተለያዩ ሁለትና ሶስት የተበጣጠሱ ሃገራት በተገኙ ነበር። አሁን በህብረትና ባንድ ሃገር የሚኖረው ብዙኃን ኦሮሞ የተገኘው በአማራ መስዋእትነትና በሚኒሊክ ጀግንነት ብቻ ነው እንዴ? ያኔ ኦሮሞው ለአንድነቱ አልተዋደቀም እንዴ? ያን ጊዜ የኦሮሞ ፈረሶች ባማረ መስካቸው ላይ ተኝተው የኦሮሞው የሾለ ጦር ከራስጌ ተገትሮ ነበር እንዴ? ሁሉም የደከመለት የኢትዮጵያ ታሪክ እኮ ነው። የድሎት ኑሮ በሌለው የተጋድሎ ታሪክ እንኳን: ብሄሮችን አስተሳስሮ እኔን እኔ ያደረገኝ ይህ የኢትዮጵያ ታሪክ እኮ ነው። እና ቅድሚያ ማንነቴ ስያሜው ‘ኢትዮጵያዊ’ ቢሆን ምን ያናድዳል፤ ምንስ ያስፍራል? የእኔ ውህድ ማንነቴ ‘ኢትዮጵያዊ’ ቢባል የብሄር ‘ማንነት ብቻ’ ላላቸው ደስታ እንጂ ስጋት ይሆናል እንዴ? ሁለት ሰዎች ተጋብተው ከጋራ ሥጋቸው ተቆርሶ ልጅ ሲወልዱ በህግም ሆነ በስብእና መስፈርት ያስደስታል እንጂ ያናድዳል እንዴ? የሁለቱም ልጅ እንጂ አንዱን ክደህ የሌላው ብቻ ሁን ያስብላል እንዴ? የጋብቻውን መከባበርና መናናቅ የልጁን የሁለትዮሽነት ያስቀይራል እንዴ? ምናልባት አባት እናቱ ላይ በደል ሊፈፅም ቢችል ልጁ የበደሉ ቂም መመለሻነት ‘የአባትህ አይደለህም’ ወይንም ‘የእናትህ አይደለህም’ ወደሚል ድምዳሜ ያስኬዳል እንዴ? ወደውም ይሁን ተገደው የፈፀሙት ግንኙነት አንዴ ልጁን አስገኝቶዋልና እንደገና ወደ ሆድ አይመልሱት፤ ልጁ እራሱን ሆኖ ከመኖር ሌላ በአባትና በናቱ የሆነውን እንዳልሆነ ማድረግ ይችላል እንዴ?

አብዛኞቻችን ከኢትዮጵያዊ ዜግነት በተጨማሪ የዚህ ኢትዮጵያዊ ማንነትም ባለቤት ነን ። ‘እኔ የዚህ ኢትዮጵያዊ ማንነት ባለቤት አይደለሁም ፤ ማን ነቴ ብሄሬ ብቻ ነው፤ ዜግነቴን ግን ገና ከሌሎች ብሄር ብሄረሰቦች ጋር ተደራድሬ የምወስነው ነው’ የሚልም መብቱ ነው፤ እሱንቱን እስከገለፀለት ድረስ እኔ ለእርሱ አዋቂ አይደለሁምና ደስ ይለኛል ። ግን የእርሱን የብሄር ማንነት በተወሰነ መልኩ የምጋራ የኢትዮጵያዊ ማንነቴ የሚበልጥብኝ እኔንም በእኔነቴ ማወቅ ግድ ይለዋል። ዜግነትን ሲደራደር እኔንም ሊያስታውስ ይገባዋል። ለነገሩ እኔ የእርሱን ማንነት በተወሰነ መልኩ እየተጋራሁት ማንነቴን ካናናቀ እንዴት ነው ከማንነቱ ጋር ትንሽም የጋርዮሽ ከሌላቸው ሌሎች ብሔር ብሄረሰቦች ጋር ‘ኢትዮጵያዊነትን በመከባበር እደራደራለሁ’ የሚል ሞራል እሚኖረው? ይህ ወሳኝ እራስን መጠየቂያና ማንቂያ ደወል ይመስለኛል። ‘ለብሔር መብት ሰምአት ሆኑልን ፤ እኛም የእነርሱን ራእይ እናስፈፅማለን ’ የሚሉቱ ደጋግመው ሊያስቡበት ይገባል ። ምክንያቱም ይህ ‘የብሄር ማንነት ብቻ’ አምባገነናዊ አስተሳሰብ ዲሞክራሲያዊ ያልሆነ መሆኑን በዚህ መረዳት ይቻላልና፤ ውህዱን የኢትዮጵያ ታሪክ (በመቶም ይሁን በሺ ዓመታት ይሰላ) የፈጠረውን የብሔር ብሔረሰቦች የአብራክ ክፋይ ውህድ ማንነት በዚህና በዚያ ፈርጆ፣ ገነጣጥሎ፣ ‘ማንነትህን እኔ አውቄልሃለሁ’ ብሎ፣ … የተሟላ የህዝቦችንም ሆነ የብሔር ብሔረሰቦችን መብት አስከበርኩ ማለት ወይንም ማስከበር በኢትዮጵያ ዘበት ነውና።

የብሔር ብሔረሰቦች መብት ተከብሯል ፤ የበለጠ እየተከበረም ነው፤ መከበርም አለበት (አስፈላጊ ከሆነም እስከመገንጠልም ይከበር። ለትውልዱ ጥሩ እንዳል ሆነ ባውቅም ድሮ እንጂ አሁን መገንጠልን አልፈራም። ጉዳቱም ሆነ ጥቅሙ እኔ ላይ ብቻ አይዘንም፤ ህዝብ እስካመነበት ድረስ ምን አገባኝ። በዚህ ሁለት አስርት ዓመታት የተረዳሁት ነገር ቢኖር መገንጠልን የምንቃወምበት ስጋት የባሰ መገንጠልን እየገፋፋ መሆኑን ነው)። የብሔር ብሔረሰቦች ክብሩን የበለጠ ምሉእ የሚያደርገው ግን እነዚህ ብሄር ብሔረሰቦች ከደም ከአጥንታቸው አዋጥተው በኢትዮጵታዊ ታሪክ አምጠው የወለዱትን ውህድ የብሄር ማንነት ክብር እና ቦታ ሲሰጡት ነው። ሰማእታቶች የተጋደሉትም ለዚህ ምሉእ የሃገሪቱዋ ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች ማንነት እንጂ አሁን እዚህ ማህበራዊ መድረክ ላይ በዚህና በዚያ በሚቀነቀኑ ፅንፍና ‘እኔ አውቅልሃለሁ’ የተምታታ ‘የብሔር ማንነት ብቻ’ አጥርነት ለማነቅና አምባገነን ለመሆን አይመስለኝም ። ከሆነም የብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች መከራችን ገና አልተቋጨም ማለት ነው።

የተነሳሁበት ነገረ-አርእስት ገድቦኝ እንጂ የብሔር ማንነታቸውን ከኢትዮጵያዊነት ያስቀደሙትን ወገኖቻችንን ማንነት የሚያብጠለጥሉት ተመሳሳይ አምባገነናዊ እሳቤ ለሃገራችን ሃገራዊ ህልውና ጠንቅ የሚሆን ይመስለኛል። ኢትዮጵያ ለዘለአለም የምትኖረው ለሁላችንም ማንነት የተሟላ የማንነት ልብስ ተከባብረን ስንላበስላት ነው፤ ለህዝቦቿ አምባገነናዊ ማንነት ጭኖ ዲሞክራሲና ኢትዮጵያ ብሎ ማንባት የአዞውን እንዳይሆንብን ያሰጋልና።

*********

Sisay Demeku

more recommended stories