‹አንድነት› ፓርቲ ከ‹መድረክ› ታገደ | የኢቴቪ እና የሰንደቅ ጋዜጣ ዘገባ

‹መድረክ› በሚል አጭር ስያሜው የሚታወቀው የተቃዋሚ ፓርቲዎች ግንባር፤ ‹አንድነት ለፍትህ እና ዲሞክራሲ ፓርቲ›ን በዚህ ሳምንት ከአባልነት ማገዱን አስመልክቶ የኢቴቪን እና የሰንደቅ ጋዜጣን ዘገባ ከዚህ በታች አቅርበናል፡፡

**********
የኢቴቪ ዘገባ 

የኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዲሞክራሲያዊ አንድነት መድረክ ትላንት 9ኛ መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤውን አካሂዷል፡፡ አንድነት ለዲሞክራሲና ፍትህ ፓርቲ ከመድረክ አባል ፓርቲነት በግዚያዊነት እንዲታገድ ጉባኤው መወሰኑንም የመድረክ አመራሮች አስታውቀዋል፡፡ የአንድነት ለዲሞክራሲና ፍትህ ፓርቲ ፕሬዝዳንት ኢንጅነር ግዛቸው ሽፈራው በበኩላቸው የመድረክ ውሳኔ ትክክል አይደለም ብለዋል፡፡
ለተጨማሪ የሙሉቀን ካሳሁን ዘገባ ቪዲዮውን ይመልከቱ:-

***********
የሰንደቅ ጋዜጣ ዘገባ

መጠሪያውን የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ አንድነት መድረክ (መድረክ) አድርጎ ለአለፉት አምስት ዓመታት ሲንቀሳቀስ የቆየው የፖለቲካ ግንባር ህብረብሔራዊ የሆነውን የአንድነት ለዲሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ አንድነትን ማገዱን ተከትሎ ሙሉ በሙሉ የብሔር ፓርቲዎች ግንባር ሆነ።

መድረክ ባለፈው ቅዳሜ የካቲት 15 ቀን 2006 ዓ.ም አዲስ አበባ ውስጥ በሚገኘው ጽ/ቤቱ ባካሄደው ጠቅላላ ጉባኤ መጠናቀቅ በኋላ በህብረ ብሔር የተደራጀውንና በሀገሪቱ አንድነት ላይ ጠንካራ አቋም የሚያራምደውን አንድነት ፓርቲን በማገድ በአንፃሩ በደቡብ ክልል ተመዝግቦ እየተንቀሳቀሰ የሚገኘውን የሲዳማ አርነት ንቅናቄ (ሲአን) በአባልነት በመያዝ ሙሉ በሙሉ የብሔር ፓርቲ ስብስብ ሆኖ ለመቀጠል ወስኗል።

ቀደም ሲል የህብረብሔር አደረጃጀት ሲከተሉና ብሔር ተኮር አደረጃጀት የሚከተሉ ፓርቲዎች በጋራ ሊያሰራቸው የሚችል የፖለቲካ መስመር አይኖርም በሚል ከፍተኛ ትችት በግንባሩ ላይ ሲሰነዘር መቆየቱ ይታወሳል። ይህንንም ተከትሎ የብሔር ጥያቄ አፈታት፣ የመሬት ባለቤትነት ጥያቄና የፌዴራል አደረጃጀት ልዩነቶች በመድረክና አንድነት መካከል ሲፋጬ መቆየታቸው አይዘነጋም። ሆኖም በእነዚህ ጥያቄዎች ላይ የጋራ መግባባት ባለመደረሱ ግንባሩ ተሰርቶ ባላለቀ ፕሮግራም የተዋቀረ በመሆኑ ውጤታማነቱ ላይ ጥያቄ ሲነሳ ቆይቷል።

ከዘጠነኛው የመድረክ ጠቅላላ ጉባኤ በኋላ “ደንብና ፕሮግራም አላከበረም” በሚል ምክንያት አንድነትን በማገድ በብሔር የተደራጀውን ሲአን ተቀባይነት በማግኘቱ ሳቢያ በአሁኑ ወቅት የመድረክን ግንባር የፈጠሩት ሁሉም በብሔር የተደራጁ ፓርቲዎች ሆነዋል። በዚህም መሠረት ከትግራይ የአረና ትግራይ ለዴሞክራሲና ለሉአላዊነት (አረና) ከደቡብ የደቡብ ህብረትና የኢትዮጵያ ሶሻል ዲሞክራሲ (ኢሶዴፓ) በጋራ ተዋህደው የፈጠሩት የኢትዮጵያ ማህበረ ዲሞክራሲ -ደቡብ ህብረት አንድነት ፓርቲ (አማደዲአፓ) እንዲሁም የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረንስ (አፌኮ) እና አሁን ግንባሩ የተቀበለው የሲዳማ አርነት ንቅናቄ (ሲአን) መድረክን ሙሉ በሙሉ በብሔር ወይም በቡድን ከዚያም ሲያልፍ የሶሻል ዲሞክራሲ ባህሪን በሚያቀነቅኑ ፖለቲከኞች የበላይነት መያዙን የሚጠቁም ውሳኔ አስተላልፏል።

ከመድረክ ጠንሳሾች መካከል ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ በአንድነት በመድረክ መካከል ያለው ልዩነት ማጥበብ ባለመቻላቸው ሙሉ በሙሉ ከፓርቲ ፖለቲካ እራሳቸውን ማግለላቸው፣ እንዲሁም በብሔር የተደራጁትንና በህብረብሔር የተደራጁ ኃይሎች የሚገናኙበት “አማካይ ስፍራ” ይኖራል በሚል ብዙ የደከሙት አቶ ስዬ አብርሃ በከፊልም ቢሆን ከፓርቲ ፖለቲካ መራቃቸው አይዘነጋም።

ከየካቲት 15ቱ የመድረክ ጠቅላላ ጉባኤ ውሳኔ በኋላ የመድረክ ፕሮግራም የሰፋ ልዩነት በሌላቸው የብሔር ፓርቲዎች ሙሉ በሙሉ መያዙ በሀገሪቱ የተቃውሞ ካምፕ ውስጥ ያለውን የአደረጃጀት ልዩነት ላይ ወሳኝ የፖለቲካ ክስተት ተደርጎ እየታየ ነው። በአሁኑ ወቅት በብሔር የተደራጁ ፓርቲዎች የሰብዓዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶች በአግባቡ አለመከበራቸው እና ከመገንጠል መብት በስተቀር ሀገሪቱን እየመራ ካለው የኢትዮጵያ ሕዝቦች ዲሞክራሲያዊ ግንባር (ኢህአዴግ) በአብዛኛው የፖለቲካ ተመሳሳይነት ያላቸው በመሆኑ መድረክ ከገዢው ፓርቲ ጋር ያለው ልዩነት መሰረታዊ ሳይሆን የአፈፃፀም እንደሆነም የሚጠቅሱ ወገኖች አሉ። በተለይ በመሬት ባለቤትነት ጥያቄ፣ በቡድን መብት ቅድሚያ መስጠትና ነፃ ገበያን እንዲሁም በፌዴራሊዝም ጥያቄ ላይ ከኢህአዴግ ብዙም እንደማይርቅ እየተነገረ ነው።

በአንፃሩ አንድነትን የመሰሉ ፓርቲዎች ከኢህአዴግም ሆነ አሁን መድረክ ውስጥ ካሉ ፓርቲዎች ጋር መሠረታዊ ልዩነት ያላቸው ናቸው። በመሬት ባለቤትነት፣ በፌዴራሊዝም፣ በቡድን መብት አከባበርና በገበያ ስርዓት በመሰረታዊ ደረጃ ልዩነት ያላቸው የሊብራል ዲሞክራሲ አቅጣጫን የሚከተሉ መሆኑ ይታወቃል። በዚህ አቅጣጫ ውስጥ ያሉት አንድነት፣ ኢዴፓ፣ ሰማያዊና መኢአድ ፓርቲዎች በዋናነት የሚጠቀሱ ናቸው።

በቅዳሜው እለት የመድረክ ጠቅላላ ጉባኤም አንድነት ፓርቲ የመድረክ ደንብና ፕሮግራም አላከበረም የሚለው የእግድ ውሳኔ በሽፋንነት ቢቀርብም ውሳኔው ግን የፖለቲካ የአቅጣጫ ልዩነት መሆኑ የሚጠቁሙ መረጃዎች አሉ። መድረክ አንድነትን ያገደው ከመኢአድ ጋር በባህርዳር ከተማ ትዕይነት ሕዝብ እያካሄደ ባለበት መሆኑም የመድረክና የአንድነት ልዩነት የደንብ ማክበርና አለማክበር አለመሆኑን የሚጠቁም ነው። በተለይ አንድነት በቅርቡ ጠቅላላ ጉባኤውን በማካሄድ አዲስ አመራር ከመረጠ በኋላ ከመድረክ ጋር “ውህደት” ካልሆነ በሌላ አደረጃጀት መቀጠል ተገቢ አለመሆኑ መወሰኑም ለአሁኑ እገዳ በር ከፍቷል እየተባለ ነው።

በሌላ በኩል የአንድነት የአረና የውህደት ሂደት ግልፅ አለመሆን በአንፃሩ የአንድነትና የመኢአድ ግንኙነት መጠናከርም በብሔርና ህብረብሔር ያለውን የአደረጃጀትና የአላማ ልዩነት ጎልቶ እንዲወጣ ያደረገው ይመስላል። አሁን ባለው የምርጫ ዋዜማ ላይ በአደረጃጀት ልዩነት ሲወሳሰብ የነበረው ልዩነት ነጥሮ ወጥቶ ፓርቲዎቹ ያዋጣል በሚሉት መስመር መጓዝ መጀመራቸው ለመራጩም ሕዝብ ጠቀሜታ እንዳለው እየተገለፀ ነው።

እስከቅርብ ጊዜ ድረስ የውህደት ማዕከል ሆኖ በርካታ ስራዎች ሲሰራ የነበረው አንድነት ከመድረክ በመታገዱ በአንድነትና በመኢአድ መካከል ያለውን የመዋሐድ ፍላጎት ሊያጠናክረው ይችላል። በተጨማሪም ውህደትን በአፈፃፀም ችግሮች እየሸሸ ያለው ሰማያዊ ፓርቲም በፕሮግራም ከሚመሳሰሉት አንድነትና መኢአድ ጋር ሊስራ የሚችልባቸው ዕድሎች ሊፈጠሩ ይችላሉ። የመድረክ የወቅቱ ሊቀመንበር ዶ/ር መረራ ጉዲና አንድነት ከመድረኩ የታገደው የመድረክን ደንብና ፕሮግራም አክብሮ ባለመንቀሳቀሱ ነው ሲሉ ለሰንደቅ ጋዜጣ ገልጸዋል። ከሌሎቹ አባል ፓርቲዎች ጋር ሲነፃፀር በአንድነት መቸገራቸውን የጠቀሱት ዶ/ሩ በተለይም አንድነቶች ስለመድረክ አሉታዊ ነገሮችን መናገራቸው፣ መድረክን በተመለከተ በውስጣቸው ያላቸው አረዳድ ግልፅ አለመሆን፣ በጋራ የወሰናቸውን ውሳኔዎች የማክበርና ያለማስከበር ጥያቄ ግራ የሚያጋባ እንደሆነባቸው፣ የፓርቲው መሪዎችና መድረክ ጋር የሚልኳቸው ተወካዮች ኀሳብ አለመጣጣም እንዳስቸገራቸው ነው የጠቀሱት።

“አንድነቶች እንዋሐድ ማለታቸው” ክፋት የለውም የሚሉት ዶ/ር መረራ የመድረክና የአንድነት ልዩነት “ውህደት” ከሚባለውም ይሰፋል፤ ውህደት ጠቃሚ ነው ቢሉ ምንም ችግር የለውም፤ እኛም በውስጣችን እየተዋሃድን ነው። እስክንዋሀድ የግን የግንባሩ ደንብና ስርዓትም ሆነ ፕሮግራም አክብሮ መንቀሳቀስ ግድ ነው። አሁንም ቢሆን መሪዎቹ የሰጡትን አስተያየት የግለሰብ አስተያየት አድርጎ የመመልከቱ ነገር ስላለ ይሄ መስተካከል አለበት፣ እስካሁንም በመድረክ ላይ የሰጡትን አስተያየት በይፋ እስካስተባበሉ ድረስ በመድረክ መቀጠል ይችላሉ። ያካልሆነ ግን እስከ ስድስት ወር እንደታገዱ ይቆያሉ ብለዋል።

“የሁለቱ ፓርቲዎች ልዩነት ደንብና ፕሮግራም ያለማክበር ብቻ ነው ወይ?” ተብለው የጠየቁት ዶ/ር መረራ፤ የፕሮግራም ልዩነት ቢኖር እንኳ በግንባር መስራቱ ክፋት የለውም። በዓለም ላይ ቀኝና ግራም አብረው ተቀናጅተው ይሰራሉ። በጀርመንና በእስራኤል የቀኝና የግራ ኃይሎች አብረው ሀገር ይመራሉ፤ ዋናው አብሮ የመስራት ፍላጎት መኖር ነው ብለዋል።

“በተስማማንባቸው ጉዳዮች ላይ አብረን እየሰራን እያንዳንዱ የፖለቲካ ድርጅት ደግሞ የራሱን አቋም ይዞ ይቆያል። አንድ ሁለት ጉዳዮች ለጊዜው ይቆዩ ብለን ወስነናል” የሚሉት ዶ/ር መረራ በመድረክና በአንድነት መካከል ያለው ልዩነት የቀኝና የግራን ያህል የሚሰፋ አይደለም ብለዋል።

በአንድነት በኩል መድረክ አይሰራም፣ ፖለቲካውንም ከቢሮ አላስወጣም የሚለው ቅሬታ በተመለከተ ዶ/ር መረራ ሲመልሱ ጥያቄው አከራካሪ መሆኑን ጠቅሰው መድረክን ማነው እንዳይሰራ ያደረገው ሲሉ ጥያቄውን በጥያቄ መልሰዋል። ሀቁ ግን እስካሁን መድረክ በአግባቡ መንቀሳቀስ አለመቻሉ እዚህ ደረጃ ላይ መድረሱ አንዱ ማሳያ እንደሆነ ጠቅሰው ያሉት አማራጮች ተጠናክሮ መቀጠል ወይም ካልተቻለ በግል መስራት መሞከር ነው ብለዋል።

የአንድነት ፓርቲ ፕሬዝዳንት ኢንጂነር ግዛቸው ሽፈራው በበኩላቸው በዶ/ር መረራ ሀሳብ አይስማሙም። “ማሰብ ያለብን መድረክም ሆነ አንድነት ተባብረን ፖለቲካውን ማሳደግ ይገባል” ያሉት ኢንጂነር ግዛቸው የፖለቲካ ትግሉን ከቢሮ አውጥተን ወደ ሕዝቡ ማነቃነቅ ቢሆንም የመድረክ ውሳኔ ግን ፖለቲካውን ከቢሮ አውጥቶ ወደ ሕዝብ እያወረደ ያለውን አንድነትን ማገድ መሆኑ ተገቢ አይደለም ብለዋል።

“አንድነት መድረክን ገምግሞ ደካማ የፖለቲካ አቅም እንዳለውና ማሻሻል እንደሚገባውም በፅሑፍ ሰጥተናል። የፅሑፉም አላማ አቅመደካማነታችንን አስወግደን ወደውህደት ሄደን ትግሉን እናጠናክር ነው ያልነው። ይሄ አቋማችን የሚያሳግደን ከሆነ አንቀበልም” ያሉት ኢንጂነር ግዛቸው “አሁንም ቢሆን መድረክ የቢሮም በለው ከአንድ ጊቢ ትንሽ እንቅስቃሴ ወጥቶ እንዲታገል አሁንም እንዋሃድ እንላለን” ብለዋል። አሁን ብንታገድም ጥሪያችንን በአዎንታዊ ጎኑ ማስተላለፍ እንቀጥላለን ሲሉም አስረድተዋል።

ኢንጂነር ግዛቸው ሽፈራው አንድነት የጣሰው ደንብና መመሪያ የለም ብለዋል። ይልቁኑ የአንድነት አመራሮች መድረክን በተመለከተ ስብስቡ እየሰራ አይደለም፤ መንቀሳቀስ አለበት የሚል አስተያየት ሰጥተዋል። ይህ አስተያየት ደግሞ ትክክል አይደለም እያሉ ነው። በእኛ በኩል ፓርቲያችን የሊብራል ፓርቲ እንደመሆኑ የፓርቲያችን አመራሮች እንደ ግለሰብነታቸው መድረክን ተችተዋል። ነገር ግን እንደ ፓርቲ አንድነት መድረክን ያወገዙበት አጋጣሚ የለም ብለዋል። በመሆኑም አንድነት ፓርቲ የግለሰብን አስተያየት አያስተባብልም። አንድነት የሊብራል ዲሞክራት ፓርቲ በመሆኑ አባሎቹ ያሉትን ሁሉ አያስተባብልም፤ የሚያስተባብለው ነገር የለም ሲሉ አረጋግጠዋል።

“እኛ አሁንም የምንፈልገው መድረክ ወደ ስራ ገበቶ፣ ከቢሮ ወጥቶ፣ ውህደት እናድርግ የሚል መልዕክት አለን” ያሉት ኢንጂነር ግዛቸው እገዳውም ዲሞክራሲያዊ አይደለም። እገዳውም በአንድነት ፓርቲ ላይ የሚፈጥረው ምንም አይነት ተፅዕኖ የለም፤ እስከመጨረሻውም ወደ ውህደት እንሂድ የሚለውን ጥያቄ በመያዝ፤ አንድ ጠንካራ ብሔራዊ አመራር እንፍጠር የሚለውን ጥሪ እስከ መጨረሻው እንገፋበታለን ብለዋል። በቅርቡም የፓርቲው ብሄራዊ ም/ቤት እንደተቋም ተነጋግሮበት በይፋ አቋማችንን እናሳውቃለን ብለዋል።

********

Content gathered and compiled from online and offline media by Hornaffairs staff based on relevance and interest to the Horn of Africa.

more recommended stories