የጠላፊው ወንድም ከቪኦኤ እና ከሪፖርተር ጋዜጣ ጋር ያደረጉት ቃለምልልስ

የኢትዮጵያ አየር መንገድ አይሮፕላንን የጠለፈው ኃይለመድኅን አበራ ታላቅ ወንድም ዶ/ር እንዳላማው አበራ፤ ከቪኦኤው ሄኖክ ሰማእግዜር ጋር ያደረጉትን ቃለምልልስ የድምጽ ቅጂ እና ከሪፖርተር ጋዜጣ ጋዜጠኛ ጥበበ ሥላሴ ጥጋቡ ጋር ያደረጉትን ቃለምልልስ ጽሑፍ ከታች ያዳምጡ/ያንብቡ፡፡

********

ከቪኦኤ ጋር ያደረጉትን ቃለምልልስ 

********

ከሪፖርተር ጋዜጣ ጋር ያደረጉትን ቃለምልልስ

ሪፖርተር፡- ቤተሰቡ የሚገኝበትን ሁኔታ ገልጸውልን ወደ ውይይቱ ብንገባስ?
ዶ/ር እንዳላማው፡– እንግዲህ እንደተወራው በቅርቡ አጎታችን ሞቶ ሐዘን ላይ ነው የቆየነው፡፡ እናታችን ወንድሟን ቀብራ ተዝካር እያወጣች እያለ ነው፣ አሁን ደግሞ ልጇ አውሮፕላን ጠለፈ ተብሎ በፖሊስ ቁጥጥር ሥር መዋሉን የምትሰማው፡፡

ሪፖርተር፡- ከወንድምዎ ረዳት አብራሪ ኃይለመድኅን አበራ ጋር ለመጨረሻ ጊዜ የተገናኛችሁት መቼ ነው?
ዶ/ር እንዳላማው፡- የአጎታችን ቀብር ላይ ነበር የተገናኘነው፡፡ አጎታችን ዶ/ር እምሩ ሥዩም ይባላሉ፡፡ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መምህር ነበሩ፡፡ በድንገት በገጠማቸው ሕመም ሕይወታቸው አልፏል፡፡ ታህሣሥ 26 ቀን 2006 ዓ.ም. ይመስለኛል ለመጨረሻ ጊዜ የተገናኘነው፡፡ እኔ ሱዳን ነው የምሠራው፡፡ ዓርብና ቅዳሜ ዕረፍት በመሆኑ መጥቼ ነው የአጎቴን መሞት የተረዳሁት፡፡

ሪፖርተር፡- የአጎታችሁ አሟሟት ከብዙ ነገሮች ጋር እየተያያዘ ነው፡፡ መንስዔው ምን ነበር?
ዶ/ር እንዳላማው፡- ምክንያቱ ከልብ ሕመም ጋር የተገናኘ ነው፡፡ የሚኖረው ኅብር ሬስቶራንት ጀርባ ባለ የዩኒቨርሲቲ መምህራን መኖሪያ አፓርታማ ላይ ነበር፡፡ የእግር ጉዞ አድርጎ ታክሲ እንደተሳፈረ ነው ድንገት የሞተው፡፡ ባለታክሲው በጥርጣሬ ተይዞ ተመርምሮ ነው የተለቀቀው፡፡ እኛም ምንም የምንጠረጥረው ነገር ባለመኖሩ በሕመም ነው የሞተው ብለን አስከሬኑን ፈርመን ተቀብለናል፡፡ አሁን የምንሰማው ወሬ ሰው ገድሎት ነው፣ እንዲህ ነው እንዲያ ነው… የሚለው ትክክል አይደለም፡፡ እኔ ራሴ አስከሬኑን አይቼዋለሁ፡፡ ሕልፈቱ በሌላ ምክንያት ሳይሆን ከነበረበት የቆየ የደም ግፊትና የልብ ሕመም ጋር የተያያዘ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- የአጎታችሁ ሞት ለረዳት አብራሪው አውሮፕላን መጥለፍ ውሳኔ ምክንያት እንደሆነ በስፋት ይነገራል፡፡ ይህ እንደተባለው ተፅዕኖ ፈጥሮ ይሆን?
ዶ/ር እንዳላማው፡- እኛ እንደ ቤተሰብ ያልወደድነው ነገር ይህንን ምክንያት ማድረግ ነው፡፡ በእርግጥ ኃይለመድኅን ከአጎቱ ጋር በጣም ቅርበት ነበረው፡፡ እሱ ብቻ ሳይሆን ሁላችንም ቅርበት ነበረን፡፡ እንደ ወንድማችን ነበር የምናየው፡፡ እሱም እንደዚያው ነበር፡፡ ያደገው እኛ ቤት ነው፡፡ በሌላ ምክንያት ሳይሆን አባታችን እሱን ማስተማር ስለፈለገ ነበር፡፡ እናም ከአጎታችን ጋር የነበረን ቅርበት በጣም የጠነከረ ነው፡፡ ሁላችንም የምናማክረው እሱን ነበር፡፡ ያደግነው ደልጊ የምትባል መንደር ውስጥ ነበር፡፡ ደልጊ ከሰባቱ የጣና ደሴቶች አንዷ ናት፡፡ ኑሯችን በጣና ዙሪያ ነበር፡፡

ሪፖርተር፡- እስቲ ስለቤተሰቦቻችሁ ሁኔታ በዝርዝር አጫውቱን?
ዶ/ር እንዳላማው፡- የመጀመርያ ልጅ እንዳላማው፣ በመቀጠል ሃይማኖት፣ መድኃኒት፣ ተክለመድኅን፣ መንበረመድኅን፣ ተወልደመድኅን፣ ብርሃነመድኅን… እነዚህ ደልጊ የተወለዱ ናቸው፡፡ ነዋየመድኅን (አሁን በፊዚክስ ፒኤችዲ እየሠራች ነው)፣ ሕይወት… አጠቃላይ አሥራ አንድ ነን፡፡ ኃይለመድኅን ዘጠነኛ ልጅ ነው፡፡ እንዳላማውና ሃይማኖት ሐኪሞች ስንሆን ሌሎቹ ፊዚክስ፣ አርክቴክቸር፣ ወዘተ ያጠኑ ናቸው፡፡ ቤተሰቦቻችን በትምህርት ላይ ጠንካራ ዕምነት ስላላቸውና እኛም በትምህርት ውጤታማ በመሆናችን የተነሳ፣ አንዳንድ ሰዎች ይህ ቤተሰብ ራሱ አበራ ዩኒቨርሲቲ ነው መባል ያለበት ይላሉ፡፡ በአጠቃላይ ስድስት ሴቶችና አምስት ወንዶች ነን፡፡

ሪፖርተር፡- ኃይለመድኅን በልጅነቱ እንዴት ያለ ልጅ ነበር? ከእርስዎ ጋርስ ቀረቤታችሁ ምን ያህል ነው?
ዶ/ር እንዳላማው፡- እሱ ሲወለድ ጊዜ እኔ ተማሪ ነበርኩኝና ብዙም የጋራ ጊዜ አልነበረንም፡፡ የበለጠ የተግባባነው እኔ እዚህ ሥራ ቀይሬ ስመጣና እሱም አርክቴክቸር ትምህርት ቤት ሲገባ ነበር፡፡ ወቅቱም በ1993 ዓ.ም. ነበር፡፡ ኃይለመድኅን፣ ሕይወትና ትንሣዔ በጣም ይቀራረባሉ፡፡ በልጅነቱ በጣም ብሩህ አዕምሮ  (Intelligence) እንደነበረውና ንቁ ልጅ እንደነበር አስታውሳለሁ፡፡ በአራት ዓመቱ መጽሐፍ ያነብ ነበር፡፡ አስታውሳለሁ ልጅ እያለ ፀጉሩን ይላጭና አንድ ጓደኛዬ ‹‹ዛሬ ደግሞ ጅል መስለሀል›› ሲለው፣ ‹‹ኧረ! እንደዚህ ከሆነማ ሁሉም ወታደር ጅል ነዋ!›› ብሎ አስቆናል፡፡ እዚህም እያለ በጣም ጥሩ የሚባል ማኅበራዊ ግንኙነት ነበረው፡፡ በተለይ አርክቴክቸር ትምህርት ቤት እያለ ከተማሪዎች ጋር ይግባባ ነበር፡፡ ነገር ግን በጣም  ብዙ ሰው በተሰበሰበበት መሳተፍ ደስ አይለውም ነበር፡፡ በባህሪው ግን በጣም ለሰው ተቆርቋሪ ነው፡፡ ሰው ከተቸገረ ከአቅሙ በላይ ነው የሚያስበው፡፡ ለምሳሌ አንድ ሰው በገንዘብ መረዳት አለበት ከተባለ ከሚችለው በላይ አስተዋጽኦ ማድረግ ይፈልጋል፡፡

ሪፖርተር፡- እንግዲህ ኃይለመድኅን የአውሮፕላን አብራሪ የሆነው የአርክቴክቸር ትምህርቱን አቋርጦ ነው፡፡ ምናልባት ለበረራ የነበረው ፍቅር እንዴት ይገለጻል? ውሳኔውንስ እንዴት ተቀበላችሁት?
ዶ/ር እንዳላማው፡– አሥራ አንደኛ ክፍል እያለ ምን መሆን ትፈልጋለህ ስለው ፓይለት መሆን ነው የምፈልገው ይል ነበር፡፡ በአርክቴክቸር በሚመረቅበት ዓመት ዕድሜው ወደ 25 ነበር፡፡ አንድ ሴሚስተር ሲቀረው ነው ያቋረጠው፡፡ ትምህርቱን ያልጨረሰው የዕድሜ ጉዳይ ስለነበር ነው፡፡ ልጨርስ ቢል ዕድሜው ከሃያ አምስት ያልፋል ለዚህ ነበር ያቋረጠው፡፡ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ለአብራሪነት የዕድሜ ገደብ እንደሚያስቀምጥና ከሃያ አምስት ዓመት በላይ እንደማይቀበልም ያኔ ነበር የተገነዘብኩት፡፡

ሪፖርተር፡- የበረራ ትምህርቱን ከጀመረና የአየር መንገዱ ባልደረባ ከሆነ በኋላስ ስለነበረው ሁኔታ ምን የሚሉት አለ? አንዳች የማይመቸው ነገር ነበር እንዴ?
ዶ/ር እንዳላማው፡– እኔ በዚህ በኩል ብዙ የማውቀው ነገር የለም፡፡ ምናልባት ታናናሽ እህቶቻችን የበለጠ ያውቁ ይሆናል፡፡ በዚያ ላይ እኔ ላለፉት ስድስት ዓመታት ካርቱም ነው የምኖረው፡፡ አዲስ አበባ የምመጣው ቤተሰብ ለማየት ነው፡፡ ስለዚህ እሱ አየር መንገድ ሥራ ከጀመረ በኋላ ብዙም አልተገናኘንም፡፡ በአጋጣሚ ነው ልንገናኝ የምንችለው፡፡

ሪፖርተር፡- የአውሮፕላን ጠለፋውን እንዴት ነው የሰሙት?
ዶ/ር እንዳላማው፡– ባለፈው እሑድ የአጎታችን ተዝካር ነበር፡፡ ለተዝካሩ የተጠራው ሰው መጥቶ በጥሩ መስተንግዶ ተሸኘ፡፡ ከዚያም በአካባቢው ባህል መሠረት ቤተ ዘመድ ተሰብስቦ ሰኞ ጠዋት ተለቅሶ ነው የተለያየነው፡፡ ከዚያም ወደ ባህር ዳር ጉዞ ጀመርን፡፡ ጉዞ ጀምረን መንገድ ላይ ጎማ ተንፍሶ ቆመን ሳለ ነበር የአውሮፕላኑን መጠለፍ በሬዲዮ የሰማነው፡፡ ከዚያም ለአጐታችን ልጅ ለዓለሙ ስልክ ተደውሎ ጠላፊው ረዳት ፓይለቱ መሆኑን አሰማን፡፡ በቦታው እኔ፣ አባታችንና የአጎታችን ልጅ ዓለሙ አብረን ነበርን፡፡ እኛ በጊዜው የኃይለመድኅንን የበረራ ፕሮግራም በውል አናውቅም ነበርና እሱን አላሰብነውም፡፡

ሪፖርተር፡- ቤተሰብ እሱ መሆኑን ሲሰማ እንዴት ነበር ሁኔታው?
ዶ/ር እንዳላማው፡– በጣም ነበር የተደናገጥነው፡፡ በመጀመርያ ይህን ለማድረግ የሚያስችለው ምንም ፍንጭ ማግኘት አልተቻለም፡፡ በዚህ የተነሳ ነው፣ አይ በዚያ ምክንያት ነው ለማለት የሚያስችለን ነገር ያልነበረው፡፡ ለተወሰነ ጊዜም በድንጋጤ ተውጠን መነጋገር አልቻልንም ነበር፡፡ መጨረሻ ሁሉም የየራሱን መላምት ማምጣት ጀመረ፡፡ ቅጽበታዊ በሆነ አጋጣሚ ነው የሚል ነበር፡፡ ፓይለቱ ሲወጣ በሩን ቆልፎበት ነው የሚለው አነጋገር በጉርምስና ስሜት ከሰውዬው ጋር ተጋጭቶ ሊሆን ይችላል የሚለው ነገር አመዘነ ማለት ነው፡፡ ወሬው ግን ከቁጥጥር ውጪ ሆነ፡፡ እኛ ከእሱ መረጃ የምናገኝበት ምንም ዓይነት መንገድ የለም፡፡ ሁነኛ ምንጭ የሌላቸው ወሬዎችም መዛመት ጀመሩ፡፡ ያ ወሬ ደግሞ በቤተሰባችን ግንኙነት ላይ ችግር ፈጥሮ ነበር፡፡ አሁንም ያለው ሁኔታ ጥሩ አይደለም፡፡ ይኼን ያለው ማን ነው? ያን ያለው ማን ነው? መባባሉ ችግሩን አባባሰው፡፡ እናም ጥሩ የሚመስለኝ ከእሱ በቀጥታ ብንሰማ ነው፡፡ አሁን ባለን መረጃ የስዊዘርላንድ መንግሥት ጠበቃ ሳይመድብለት አይቀርም፡፡ እናም ጠበቃው ከእሱ የሰማውን እስኪነግረን ድረስ በትዕግሥት ብንጠብቅ ጥሩ ነው፡፡ በሌላ በኩል ይህንን ጠለፋ ለሌላ አጀንዳ መጠቀሚያ አድርጎ መሯሯጥ ቢገታ ጥሩ ነው፡፡ ምክንያቱም በቤተሰቡ ላይ ችግር ያመጣል፡፡ መለመን ካለብንም ሕዝቡን የምንለው ነገር እባካችሁ ከራሱ እስከምንሰማ ድረስ እንዲህ ነው፣ እንደዚያ ነው ማለቱን ብናቆም፡፡

ሪፖርተር፡- በመረጃ ደረጃ በስፋት የሚሰማው የታናሽ እህታችሁ ትንሣኤ አበራ መረጃ ነው፡፡ እሷስ ከምን ተነስታ ይሆን መረጃውን የሰጠችው?
ዶ/ር እንዳላማው፡- የጻፈችው በራሷ ነው፡፡ የጻፈቻቸው ነገሮችም እውነት ናቸው፡፡ ያው ከነበራቸው ቅርበት ነው፡፡ ሰው ይከታተለኛል፣ ምናምን ይኼ ከሥነ ልቦናው ጋር በተያያዘ የተባለው ነገር ነበር፡፡ ከእኔ ጋር የተገናኘነው ከወር በፊት ነበር፡፡ ከእህቶቹ ጋር ግን በቅርብ ተገናኝተዋል፡፡ የሚኖረው ገርጂ አካባቢ ነው፡፡ ሕይወትና ትንሣኤም እዚያው ናቸው፡፡ እናም ካልበረረ በአካል ወይም በስልክ ቀን በቀን ይገናኛሉ፡፡ እናም እሷ ያለችው እውነት ነው፡፡ ይኼ እውነት ነው ሲባል ግን በምክንያትነት መደምደሙ ግን ትክክል አይደለም፡፡ የአጎታችን ሞትም በምክንያትነት መቅረቡ ትክክል አይሆንም፡፡ በእርግጥ ሐዘኑ ከባድ ነው፡፡ ብዙ ነገር ነው ያጎደለብን ይኼ አይጠረጠርም፡፡ ይህም የሚያባብስ ምክንያት ሊሆን ይችላል፡፡ ይህንንም አንድ የሥነ ልቦና ባለሙያ ሊያብራራው ይገባል እንጂ፣ እንዲሁ በመላምት የአጎቱ ሞት ድብርቱን አባባሰው፣ ከዚያም ‹‹ፓራኖይድ›› ሆነ ምናምን ማለቱና መተንተኑ ከሙያ ክልል ውጪ ስለሆነ ለምንም ነገር አይበጅም፡፡ ቀጥታ ተያያዥነት ያለው ነገር የለም፡፡

ሪፖርተር፡- እሱ የሚከታተሉኝ ሰዎች አሉ የሚለውን እንዴት ትረዱታላችሁ?
ዶ/ር እንዳላማው፡- ማወቅ ይከብዳል ግን አንድ ነገር ነው፡፡ ለምሣሌ እኔ ወይ በጥቅም ወይ በሆነ ነገር ተነስቼ ብጋጭ ለቤተሰቦቼ እንዲህ እንዲህ ነው ብዬ ልናገር እችላለሁ፡፡ እንግዲህ ይህ የሁላችንም ማኅበራዊ ግንኙነት ውጤት ነው፡፡ ሰዎች ይከታተሉኛል የሚለው ነገር ግን ምናልባት ረቀቅ ያለ ወይም በተጨባጭ የሚታይ ላይሆን ይችላል፡፡ ለምሳሌ አንዳንድ ሰዎች ከፍርኃት በመነጨ ኤፍቢአይ፣ ሲአይኤ ይከታተለኛል ይላሉ፡፡ ኬጂቢ ወይም ያልታወቀ ኃይል… ወዘተ… በዚህ መንገድ በግምት እንሂድ ከተባለ በተጨባጭ የሚከታተሉት ሰዎች የነበሩ አይመስለኝም፡፡

ሪፖርተር፡- ምናልባት ግን ከዚህ ጋር በተያያዘ በውጪው ዓለም የምንሰማቸው ነገሮች አሉ፡፡ አንዳንድ ታዋቂ ሰዎች (ባለሙያዎች) መንግሥታዊ ወይም የፀጥታ ኃይል የመፍራት ነገር አለ፡፡ በእርግጥም የፀጥታ አካላት የሚከታተሏቸው ግለሰቦችም ይኖራሉ፡፡ ምናልባት የእሱ የፖለቲካ አቋም ይታወቅ ይሆን?
ዶ/ር እንዳላማው፡– እኔ እስከማውቀው ድረስ የየትኛውም የፖለቲካ ቡድን አባል አልነበረም፡፡ እንዲያውም ብዙ ጊዜ ቤት ውስጥ በምናደርገው ውይይት የመንግሥትን አቋም የመደገፍ አዝማሚያ ነው የሚያሳየው፡፡ በዚህ አጭር ጊዜ ውስጥ የተፈጠረ አዲስ ነገር ካለ በበኩሌ አላውቅም፡፡ ይኖራልም ብዬ አልገምትም፡፡ በዚህ ላይ እርግጠኛ ሆኜ መናገር አልችልም፡፡ በመሥሪያ ቤቱ ውስጥ ባለው ነገር (ኦፊስ ፖለቲክስ) ግን ምን እንዳለ የማውቀው የለም፡፡ በቢሮ ውስጥ መገለል፣ አድልኦና መሰል ችግሮች ገጥመውት ይሁን አይሁን አይታወቅም፡፡ ለእኔም ሆነ ለሌሎቹ የነገራቸው ነገር የለም፡፡ አድልኦና መገለሉ ተፈጽሞ እንኳን ቢሆን ያ ይከታተሉኛል ምናምን ከሚለው ነገር ጋር እንዴት ሊያያዝ እንደሚችልም የሚገባኝ ነገር የለም፡፡

ሪፖርተር፡- ከሥነ ልቦናው ጋር በተያያዘ ባለሙያ አይቶት ነበር እንዴ? ትንሣኤም የሥነ ልቦናው ሁኔታ በእሷም ላይ የሚታይ እንደነበር ፍንጭ ሰጥታለች፡፡
ዶ/ር እንዳላማው፡– መጨረሻ ያገኙት መድኃኒትና ሕይወት ናቸው፡፡ እናም ከመሄዱ በፊት መክረውታል፡፡ ባለሙያ እንዲያማክርም አሳስበውታል፡፡

ሪፖርተር፡- ከእርስዎ ጋር በተገናኛችሁ ጊዜ ግን የሆነ የተለየ ነገር አልታየበትም?
ዶ/ር እንዳላማው፡– ከእኔ ጋር የተገናኘነው ለአጎታችን ለቅሶ ነበር፡፡ እንዲያውም እኔና እሱ ቀብር አልደረስንም ነበር፡፡ በዚያን ቀን በተነሳነው ፎቶግራፍ እንደሚታየው እሱ የተለየ ነገር ውስጥ ስለመኖሩ ፊቱ ላይ የሚነበብ ነገር የለም፡፡ እንዲያውም ምን ዓይነት መልዕክት ደርሶት እንደነበር ባላውቅም፣ የሆነ የሚያስቅ ነገር እንደገጠመው ነው የምገምተው፡፡

ሪፖርተር፡- መጠጥና ሌሎች ተያያዥ ልማዶች ነበሩበት?
ዶ/ር እንዳላማው፡- መጠጥ አይጠጣም፡፡ አልፎ አልፎ ካለፉት ሦስት ዓመታት ወዲህ ቢራ መጠጣት የለመደ ይመስለኛል፡፡

ሪፖርተር፡- እስቲ ስለመጨረሻ ግንኙነታችሁ በደንብ ይንገሩን?
ዶ/ር እንዳላማው፡- ቅድም እንዳልኩት እኔና እሱ ዘግይተን ሐሙስ ቀን ነው በለቅሶው ላይ የተገኘነው፡፡ አስከሬኑ ማታውኑ በዩኒቨርሲቲ መኪና ተጭኖ መጣ፡፡ እኔ ትንሽ አሞኝ ነበር፡፡ እሱ ግን ደህና ነበር የሚመስለው፡፡ አሁን ትንሣኤ ያለችው ነገር ከዚያ በኋላ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- እንድ እህታችሁ መንበረ ሳትሆን አትቀርም ትዊተር ላይ ባሰፈረችው ጽሑፍ፣ ‹‹ውጭ አገር መኖር አይፈልግም፣ እኔን እንኳን በአገሬ እንድኖር ነበር የሚመክረኝ፤›› ብላ ነበር፡፡ ታዲያ ለምን ይሆን በስዊዘርላንድ ጥገኝነት መጠየቁ የተሰማው?
ዶ/ር እንዳላማው፡- ውጭ አገር መኖር አይፈልግም፡፡ እዚህ አገር ውስጥ ከሚገጣጠሙት ውስጥ አዲስ መኪና  ከገዛ ሦስት ወራት አይሞሉትም፡፡ እንዲህ ዓይነት ንብረት የገዛ ሰው ደግሞ ውጭ አገር ሄዶ ለመኖር የሚያስብ አይመስለኝም፡፡ ከቤቱ ውስጥ አንድ ዕቃ አላነሳም፡፡ ላፕቶፑን እንኳን አልያዘም፡፡ የተለመደችውን የበረራ ሻንጣ ብቻ ነው የያዘው፡፡ ተዘጋጅቶ እንዳላደረገው የሚያሳዩ ሰላሳ ምክንያቶች አሉ፡፡ የተዘጋጀበት ቢሆን ኖሮ በጣም ለሚቀርቡት እህቶቹ ንብረቱን ይሰጣቸው ነበር፡፡ 400,000 ሺሕ ብር የሚያወጣ መኪና በመግዛትም ገንዘቡን አያባክንም፡፡

ሪፖርተር፡- የሴት ጓደኛ ነበረችው?
ዶ/ር እንዳላማው፡- ለእኔ ያስተዋወቀኝ ሰው የለም፡፡ ግን እገምታለሁ፡፡ እህቶቹ በተለይ ሕይወት ይህን በደንብ ታውቃለች፡፡ ይህን ተከትሎም ብዙ ነገር ይሰማል፡፡ አንዲት ኢንተርኔት ካፌ ካላት ሴት ጋር ግንኙነት አለው ተብሏል፡፡ እንግዲህ ከሆነ ጥሩ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ሕይወቱና ማንነቱ እንዲህ መነጋገሪያ በመሆኑ እናንተ ምን ይሰማችኋል?
ዶ/ር እንዳላማው፡– የእሱ ሕይወት ብቻ አይደለም፡፡  የቤተሰቡንም ሕይወት ነው የሚነካው፡፡ አባታችን አራጣ አበዳሪ እንደነበሩም ተገልጿል፡፡ ይህ ቅጥፈት ነው፡፡ እውነት እንኳን ሆኖ ቢሆን ከዚህ ጉዳይ ጋር የሚያገናኘው ምን እንደሆነ አይገባኝም፡፡ ሊያስረዱኝ የሚችሉ ሰዎች ካሉም ይገርመኛል፡፡ በዚህ በጣም አዝነናል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ የደረጃ ዕድገት ጠይቆ ተከልክሏል የሚል ነገርም ሰምቻለሁ፡፡ የዚህ ወሬ መሠረት ግን ከየት እንደሆነ አልተገለጸም፡፡ ከዚህ ጋርም የሚያያዝበት አመክንዮ አልተቀመጠም፡፡ በተለይ ጉዳዩን ከፖለቲካ ጋር የሚያገናኙትም በርክተዋል፡፡ ቤተሰቡ ባለፀጋ መሆኑና እኛም በትምህርት የላቅን መሆናችን በግነት ነው የሚወራው፡፡ ከትንሿ ሕይወት በስተቀር ሁላችንም በመንግሥት ትምህርት ቤት ባህር ዳር ጣና ሐይቅ ነው የጨረስነው፡፡ ውጤታችንም በጣም ጥሩ የሚባል ነው፡፡

**************

Content gathered and compiled from online and offline media by Hornaffairs staff based on relevance and interest to the Horn of Africa.

more recommended stories